ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .
ሳፈቅረው ምላሽ ባይሰጠኝ ምን ማድረግ ይሻለኛል?
“በጭንቀትና በሐሳብ ተውጫለሁ። ከልጁ ጋር ፍቅር ይዞኛል። ይሁን እንጂ ለእኔ ምን ዓይነት ስሜት እንዳለው አላውቅም። ምን ባደርግ ይሻለኛል? የሚሰማኝን ልንገረው? ኧረ፣ ይህንንስ በፍጹም አላደርገውም! ሌሎች ምን ይሉኛል?”—ሁደa
ሁደ የተባለች አንዲት ሊባኖሳዊት ወጣት አንድ ሰው አፍቅራ የነበረ ቢሆንም እርሱ ግን ምንም ዓይነት ምላሽ አልሰጣትም። እንዲህ ዓይነቱ ችግር አይከሰትም ማለት አይቻልም። ዜነ የተባለች ሌላ ወጣትም ተመሳሳይ ሁኔታ ገጥሟታል። እንዲህ በማለት ታስታውሳለች:- “ጎረቤታችን ስለነበረ በየቀኑ አየው ነበር። በጣም ቆንጆ ልጅ ነው። በዚህም የተነሳ አፈቀርኩት።”
እርግጥ ነው፣ አንዲት ክርስቲያን ልታገባው የምትችለው ዓይነት ሰው እንደሆነ አድርጋ በማሰብ አንድን ግለሰብ ማፍቀሯ ምንም ስህተት የለበትም። (ምሳሌ 5:15፤ 1 ቆሮንቶስ 7:39) እንዲሁም አንዲት ሴት አግብታ ቤተሰብ ለመመሥረት መፈለጓ ምንም ስህተት የለውም። ይሁን እንጂ ተስማሚ የትዳር ጓደኛ ይሆነኛል ብለሽ ያሰብሽውን አንድ ሰው ብታፈቅሪና እርሱ ግን እንዳፈቀርሽው የማያውቅ ወይም ለፍቅርሽ ምንም ዓይነት ምላሽ የማይሰጥ ቢሆንስ?
በፍቅር መያዝ የሚያስከትለው ሥቃይ
እንደ ሁደ ሁሉ አንቺም በከፍተኛ የስሜት ነውጥ ውስጥ እንዳለሽ ሆኖ ይሰማሽ ይሆናል። ከፍተኛ የደስታ ስሜት ይሰማሽና ወዲያው ደግሞ እልም ብሎ ይጠፋ ይሆናል። “አንዳንድ ጊዜ በጣም ደስተኛ እሆናለሁ። ሌላ ጊዜ ደግሞ ጥልቅ ሐዘን ይሰማኛል” በማለት ዜነ ተናግራለች። ምላሽ ያላገኘ ፍቅር ስጋት፣ እንቅልፍ ማጣትና ሌላው ቀርቶ የመንፈስ ጭንቀት ሊያስከትል ይችላል።
መጽሐፍ ቅዱስ በምሳሌ 13:12 ላይ “የምትዘገይ ተስፋ ልብን ታሳዝናለች” ይላል። የጠበቁት ነገር የሕልም እንጀራ ሆኖ ሲቀር ደግሞ ከባድ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል! ነጋ ጠባ ስለ እርሱ ታስቢ ይሆናል፤ በተጨማሪም ምንም ይሁን ምን ብቻ እሱን የሚመለከት ወሬ መስማት ያስደስትሽ ይሆናል። ትኩረቱን ለመሳብ የተለያዩ ዘዴዎችን ትጠቀሚ ይሆናል፤ ወይም ከእሱ ጋር ለመሆን ስትይ የተለያዩ ሰበብ አስባቦች ትፈጥሪ ይሆናል። አብረሽው ስትሆኚ ደግሞ የመረበሽ ስሜት ይታይብሻል።
ያፈቀርሽው ሰው አልፎ አልፎ ለየት ያለ ትኩረት ሲሰጥሽና ሌላ ጊዜ ደግሞ ለአንቺ ምንም ዓይነት የተለየ ስሜት እንደሌለው የሚያሳይ ነገር ሲያደርግ ስትመለከቺ ሁኔታው በጣም ግራ ሊያጋባሽ ይችላል። እንዲሁም ለሌላ ሰው ለየት ያለ ትኩረት ሲሰጥ ወይም ለሌሎች ደግነትና አክብሮት ሲያሳይ ስትመለከቺ በውስጥሽ የቅናት ስሜት ሊቀሰቀስ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “ቁጣ ምሕረት የሌለው ነው፣ መዓትም እንደ ጎርፍ ነው፤ በቅንዓት ፊት ግን ማን ይቆማል” በማለት ይናገራል።—ምሳሌ 27:4
ሁደ “አስተሳሰቤን ባላስተካክል ኖሮ በውስጤ የነበረው በቃላት ልገልጸው የማልችለው የቅናት ስሜት ሊያሳብደኝ ይችል ነበር” ስትል ሳትሸሽግ ተናግራለች። ራስንም ወደ መጥላት ሊያደርስ ይችላል። ሁደ “ያላፈቀረኝን ሰው በማፍቀሬና በዚህም ሳቢያ ለደረሰብኝ ሥቃይ ሁሉ ራሴን እወቅስ ነበር” ስትል ተናግራለች።
በምዕራቡ ዓለም የምትኖር አንዲት ወጣት ያደረባትን የፍቅር ስሜት ለግለሰቡ ለመንገር ላይከብዳት ቢችልም ሁሉም ሴቶች እንዲህ ያደርጋሉ ማለት ግን አይደለም። እንዲያውም በአንዳንድ ባሕሎች አንዲት ሴት በራሷ ተነሳሽነት እንዲህ ያለውን እርምጃ ብትወስድ ተገቢ ያልሆነና በጣም አሳፋሪ የሆነ ድርጊት እንደፈጸመች ሊያስቆጥራት ይችላል። ታዲያ አንድን ሰው ብታፈቅሪና እርሱ ግን ላደረብሽ ፍቅር ምንም ዓይነት ምላሽ ባይሰጥ ልታደርጊው የምትችይው ነገር ምንድን ነው?
ስሜትሽን ረጋ ብለሽ መርምሪ
በመጀመሪያ ደረጃ ረጋ ባለ መንፈስና በሃቀኝነት ስሜትሽን መርምሪ። መጽሐፍ ቅዱስ “በገዛ ልቡ የሚታመን ሰው ሰነፍ ነው” በማለት ያስጠነቅቃል። (ምሳሌ 28:26) ለምን? ምክንያቱም ልባችን ብዙውን ጊዜ የሚሰጠው ፍርድ የተሳሳተ በመሆኑ ነው። (ኤርምያስ 17:9) እንዲያውም ብዙውን ጊዜ የማፍቀር ምልክት ነው ብለን ያሰብነው ነገር ሌላ ነገር ሆኖ ሊገኝ ይችላል። “ሰዎች ትኩረት እንዲሰጡኝና ፍቅር እንዲያሳዩኝ እፈልጋለሁ” በማለት ሁደ ተናግራለች። “የሚያፈቅረኝና የሚያስብልኝ ሰው ያስፈልገኛል። በልጅነቴ ፍቅራዊ እንክብካቤ አግኝቼ አላደኩም። ይህም በእኔ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሮብኛል።” ያደግሽው ፍቅር በሌለውና ቁጡ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ ከሆነ በሌሎች ዘንድ የመፈቀርና ተቀባይነት የማግኘት ፍላጎትሽ ከፍተኛ ሊሆን ይችላል። ታዲያ ለዚህ መፍትሔው ከተቃራኒ ፆታ ጋር መፋቀር ብቻ ነውን?
የባዶነትና የብቸኝነት ስሜት የሚያጠቃቸው ሰዎች ብዙውን ጊዜ ጥሩ የትዳር ጓደኛ አይወጣቸውም። በጣም ያስፈልገኛል ብለው የሚያስቡትን ነገር ለማግኘት ሲሉ ብቻ ዘለው ጋብቻ ውስጥ ይገባሉ። ይሁን እንጂ እውነተኛ ደስታ የሚገኘው በመቀበል ሳይሆን በመስጠት ነው። (ሥራ 20:35) ስለዚህ አንዲት በራሷ የምትተማመንና ‘ከራሷ ጥቅም ይልቅ የሌሎችን ጥቅም የምታስቀድም’ ሴት በጋብቻ ውስጥ የሚገጥሟትን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመቋቋም የተሻለ ብቃት ይኖራታል።—ፊልጵስዩስ 2:4
እንድታገቢ የሚገፋፋ ተጽዕኖ ካለብሽ ከተቃራኒ ፆታ የምታገኚውን ማንኛውንም ትኩረት በተሳሳተ መንገድ ልትተረጉሚው ትችያለሽ። አንዳንድ ጊዜ አንዲት ወጣት ጓደኞቿና ቤተሰቦቿ የሚያደርጉባት ተጽዕኖ የማፍቀርና የመፈቀር ፍላጎት እንዲያድርባት ሊያደርግ ይችላል። በአንዳንድ ኅብረተሰቦች ውስጥ ያለው ባሕል አንዲት ሴት ለትዳር እንደደረሰች ወዲያው እንድታገባ ጫና ያደርጋል። ውሜን ኢን ዘ ሚድል ኢስት የተባለ መጽሐፍ “አንዲት ሴት ወደ ሠላሳ ዓመት ዕድሜዋ እየተጠጋች ካለችና ገና ያላገባች ከሆነች ቤተሰቧ ሁሉ ስለ እርሷ መጨነቅ ይጀምራሉ” በማለት ይናገራል። አንድ አባት የቤተሰቡ ክብር እንዳይነካ በማሰብ ሴቶች ልጆቹ የወጣትነት ዕድሜያቸው ከማለፉ በፊት ቶሎ መዳር ይፈልጋል።
ሆኖም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሠፈሩት መሠረታዊ ሥርዓቶች ከባህል የላቀ ቦታ ሊሰጣቸው ይገባል። ቅዱሳን ጽሑፎች ደግሞ ወጣቶች ‘የአፍላ ጉርምስና ዕድሜያቸው’ ከማለፉ በፊት እንዳያገቡ አጥብቀው ይመክራሉ። (1 ቆሮንቶስ 7:36) ታዲያ የምትቀርቢያቸው ወዳጆችሽ ወይም ወላጆችሽ እንድታገቢ ከፍተኛ ተጽዕኖ ቢያሳድሩብሽስ? አምላካዊ አክብሮት የነበራት ሱነማዊቷ ልጃገረድ ‘ፍቅሯ ራሱ ፈቅዶ እስኪነሣ ድረስ ቀስቅሰው እንዳያስነሱት’ ጓደኞቿን በመሃላ ይዛቸው እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። (መኃልየ መኃልይ 2:7 የ1980 ትርጉም) አንቺም በተለይ ወላጆችሽ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ከሆኑ ያለሽን የጸና አቋም ብትገልጪላቸው ጥሩ ውጤት ሊያስገኝልሽ ይችላል።
እውነታውን መቀበል
አሁንም ቢሆን ያፈቀርሽውን ሰው በተመለከተ ልትጋፈጪያቸው የሚገቡ እውነታዎች አሉ። እንዲህ ማድረጉ ቀላል ላይሆንና በስሜትሽ ላይም ጉዳት ሊያስከትልብሽ ይችላል። ሆኖም ቅዱሳን ጽሑፎች “እውነትን ግዛ አትሽጣትም” በማለት አጥብቀው ይመክራሉ። (ምሳሌ 23:23) ራስሽን እንዲህ እያልሽ ጠይቂ:- ‘እርሱን ለማፍቀር የሚያበቃ በቂ ምክንያት አለኝን? ይህን ሰው ምን ያህል አውቀዋለሁ? ስለ አስተሳሰቡ፣ ስለ ስሜቶቹ፣ ስለ አመለካከቱ፣ ስለ ልማዱ፣ ስለ ሥነ ምግባሩ፣ ስለ ችሎታው፣ ስለ ተሰጥኦውና ስለ አኗኗር ዘይቤው ምን ያህል አውቃለሁ?’
ሌላው ሊታሰብበት የሚገባው ነገር ደግሞ ግለሰቡ በእርግጥ ለአንቺ ለየት ያለ ስሜት አለው ወይ የሚለው ጉዳይ ነው። ብዙውን ጊዜ የተለመዱ የደግነት ወይም ወዳጃዊ መግለጫዎች የተሳሳተ ትርጉም ይሰጣቸዋል። “በደግነት አንዳንድ ነገሮች ያደርግልኝ ነበር” ትላለች ሁደ። “እኔ ግን የሚናገራቸውንና የሚያደርጋቸውን ነገሮች ወዶኝ ነው በሚል በራሴ መንገድ እተረጉማቸው ነበር፤ ምክንያቱም እፈልግ የነበረው ያንን ነው። ሆኖም ለእኔ የተለየ ስሜት እንደሌለው ሳውቅ በጣም አፈርኩ። ለእርሱ የምገባ ሰው እንዳልሆንኩና አንድ የጎደለኝ ነገር እንዳለ ሆኖ ተሰማኝ።”
ምናልባት አንቺም የዚህ ዓይነት ተሞክሮ አሳልፈሽ ከነበረ እንዲህ ያለው ስሜት ተሰምቶሽ ይሆናል። ሆኖም እርሱ አላፈቀረሽም ማለት በሌሎችም ዘንድ ልትፈቀሪ አትችይም ማለት አይደለም። ደግሞም በዓለም ላይ ያለው ወንድ እርሱ ብቻ አይደለም!
የተጎዳውን ስሜት መጠገን
እርግጥ ነው፣ የተጎዳው ስሜትሽ እስኪጠገን ድረስ ጥቂት ጊዜ ሊወስድ ይችላል። ለዚህ ምን ሊረዳሽ ይችላል? እርዳታ ልታገኚ የምትችዪበት አንደኛው መንገድ ልታዳምጥሽ ለምትችል ለአንዲት ጎልማሳ ክርስቲያን “ወዳጅ” ጉዳዩን ግልጥልጥ አድርገሽ መንገር ነው። (ምሳሌ 17:17) ምናልባት ልታነጋግሪያት የምትችይ በዕድሜ የገፋች ሴት በጉባኤሽ ውስጥ ትኖር ይሆናል። እርዳታና ድጋፍ በመስጠት በኩል ክርስቲያን ወላጆችም ትልቅ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ። ዜነ እንዲህ በማለት ታስታውሳለች:- “በጉባኤያችን ያለች አንዲት ክርስቲያን ሴት የሆነ የሚረብሸኝ ነገር እንዳለ ተረዳች። እኔንም ለመርዳት የሚያስችል ብስለት ነበራት። ነፃነት ስለተሰማኝ ምንም ሳላስቀር የልቤን አጫወትኳት። ጉዳዩን ለወላጆቼ እንድነግራቸው አበረታታችኝ። ከዚያም ወላጆቼን አነጋገርኳቸው፤ እነርሱም ችግሬን ተረድተው አስፈላጊውን እርዳታ አደረጉልኝ።”
በተጨማሪም ጸሎት ያለውን ኃይል አስታውሱ። (መዝሙር 55:22) ሁደ እንዲህ ትላለች:- “ወደ ይሖዋ ያቀረብኩት ጸሎት ከሥቃዬ እንድገላገል ረድቶኛል። በተጨማሪም ጠቃሚ የሆኑ ርዕሶችን ከመጠበቂያ ግንብ እና ከንቁ! መጽሔቶች ማንበቤ ረድቶኛል።” በተጨማሪም ራስሽን ከሌሎች አለማግለልሽ አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች አንዱ ነው። (ምሳሌ 18:1) ከሌሎች ሰዎች ጋር ጥሩ ዝምድና መሥርቺ። “ሌላው የረዳኝ ነገር” ትላለች ዜነ “ራሴን በሥራ ማስጠመዴና አቅኚ [የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ] መሆኔ ነው። በተጨማሪም በጉባኤ ውስጥ ካሉ ከሌሎች ሴቶች ጋር የነበረኝን ወዳጅነት አሳደኩ። ይህም በመንፈሳዊ እድገት እንዳደርግ ረድቶኛል።”
መጽሐፍ ቅዱስ “ለመውደድ ጊዜ አለው” በማለት ይናገራል። ውሎ አድሮ ለፍቅርሽ ምላሽ የሚሰጥሽን ሰው ታገኚ ይሆናል። (መክብብ 3:8) ይሖዋ አምላክ ሰውን ሲፈጥር በጋብቻ ውስጥ በሚገኝ ፍቅር የመደሰት ፍላጎት በውስጡ ተክሏል። አንቺም አንድ ቀን ታላቁ ፈጣሪያችን ያዘጋጀው የዚህ ጥሩ ዝግጅት ተቋዳሽ ልትሆኚ ትችያለሽ። እስከዚያው ጊዜ ድረስ ግን ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ከአሳብ ነፃ የሆነ’ ብሎ ከጠራው በነጠላነት ከምታሳልፊው ጊዜ ከፍተኛ ጥቅም ለማግኘት ለምን ጥረት አታደርጊም? (1 ቆሮንቶስ 7:32–34) “አንተ [ይሖዋ] እጅህን ትከፍታለህ፣ ሕይወት ላለውም ሁሉ መልካምን ታጠግባለህ” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል በማንኛውም ሁኔታ ሥር ፍጻሜውን እንደሚያገኝ ቅንጣት ያህል አትጠራጠሪ።—መዝሙር 145:16
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱትን ሰዎች የግል ጉዳይ በምሥጢር ለመያዝ ስንል ስማቸውን በሌላ ተክተነዋል።
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንዳንድ ጊዜ ደግነት በተሳሳተ መንገድ ይተረጎማል