የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g98 10/8 ገጽ 20-22
  • ማሽኮርመም ስህተት ነውን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ማሽኮርመም ስህተት ነውን?
  • ንቁ!—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ያገባ ሰው ከሆነ
  • በፆታ ስሜት መሳሳብ
  • ያላገባ ሰው ከሆነስ?
  • ማሽኮርመም ምንም ጉዳት የለውም?
    የወጣቶች ጥያቄ
  • ከችግሮች ለመራቅ የሚረዳ ምክር
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2018
  • ልባችሁን በመጠበቅ በሥነ ምግባር ንጹሕ ሆናችሁ ኑሩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2004
  • አንተንም የሚመለከት አከራካሪ ጉዳይ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2006
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1998
g98 10/8 ገጽ 20-22

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

ማሽኮርመም ስህተት ነውን?

“ማሽኮርመም ብልጣ ብልጥነት ወይም ማታለል ወይም ስህተት እንደሆነ አድርገን የምናስበው ለምንድን ነው? እንዲህ ብለን ማሰብ የለብንም! ማሽኮርመም ራሱን የቻለ ጨዋታ ነው! ሌላኛው ወገን እንዲደሰት ስለምታደርግ ረቺና ተረቺ የሌለበት ጨዋታ ነው።”—ሱዛን ራቢን፣ በኒው ዮርክ ሲቲ የሚገኘው የስኩል ኦቭ ፍለርቲንግ ዲሬክተር

ብዙ ሰዎች ማሽኮርመም የተለመደ፣ ምንም ጉዳት የማያስከትል እንዲያውም ከሰዎች ጋር ቅርርብ ለመፍጠርና ቅርርቡን ዘላቂ ለማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ አድርገው ይቆጥሩታል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በምዕራባውያን አገሮች “የማሽኮርመም ጥበብ” ክፍል የሆኑትን አካላዊ መግለጫዎች፣ አስተያየት፣ ሰረቅ አድርጎ መመልከትና ትኩር ብሎ ማየትን የሚያስተምሩ መጻሕፍት፣ መጽሔቶችና ልዩ ኮርሶች እንደ አሸን ፈልተዋል።

ማሽኮርመም ምንድን ነው? ለዚህ ቃል በርካታ ትርጉሞችና ፍቺዎች ተሰጥተዋል። አንድ መዝገበ ቃላት “ከልብ ያልሆነ ፍቅር ወይም የጾታ ስሜት የሚቀሰቅስ” ባሕርይ በማለት ይፈታዋል። ሌላ መዝገበ ቃላት ደግሞ ማሽኮርመም የሚለውን ቃል “በቁም ነገር ሳይታሰብበት የሚገለጽ ፍቅራዊ ስሜት” የሚል ፍቺ ይሰጠዋል። በመሆኑም የሚያሽኮረምም ሰው የማግባት ዕቅድ ሳይኖረው የጾታ ፍላጎት መግለጫዎችን የሚያሳይ ነው የሚለው ፍቺ ባጠቃላይ ተቀባይነት ያገኘ ሐሳብ ይመስላል። ማሽኮርመም ምንም ጉዳት የማያስከትል ተደርጎ መታየት አለበት? መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ማሽኮርመም ያለው አመለካከት ምንድን ነው?a

ምንም እንኳ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ስለ ማሽኮርመም በቀጥታ የተጠቀሰ ሐሳብ ባናገኝም የአምላክን አመለካከት ማወቅ እንችላለን። እንዴት? ከጉዳዩ ጋር ዝምድና ያላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በመመርመር ነው። እንዲህ በማድረግ ‘የማስተዋል ችሎታችን መልካሙንና ክፉውን መለየት እንዲችል’ እናሰለጥነዋለን። (ዕብራውያን 5:14) በመጀመሪያ ደረጃ ማሽኮርመም ባለ ትዳር የሆኑ ሰዎች ሊያሳዩት የሚገባ ባሕርይ መሆን አለመሆኑን እንመልከት።

ያገባ ሰው ከሆነ

ባልና ሚስቶች ለብቻቸው ሆነው አንዳቸው ለሌላው ፍቅራቸውን መግለጻቸው የተለመደ ነገር ነው። (ከዘፍጥረት 26:8 ጋር አወዳድር።) ይሁን እንጂ ከጋብቻ ውጭ ላሉ ግለሰቦች እንዲህ ዓይነቱን ስሜት ማሳየት ከአምላክ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ይቃረናል። ይሖዋ የትዳር ጓደኛሞች የጠበቀና የመተማመን መንፈስ የሰፈነበት ዝምድና እንዲኖራቸው ይፈልጋል። (ዘፍጥረት 2:24፤ ኤፌሶን 5:21-33) ጋብቻን ቅዱስና ዘላቂ ጥምረት አድርጎ ይመለከተዋል። ሚልክያስ 2:16 ስለ አምላክ ሲናገር ‘መፋታትን ይጠላል’ ይላል።b

ባለ ትዳር የሆነ ሰው ማሽኮርመሙ አምላክ ለጋብቻ ካለው አመለካከት ጋር ይስማማል? ትዳር እያለው የሚያሽኮረምም ሰው ቅዱስ ለሆነው የአምላክ ዝግጅት ማለትም ለጋብቻ አክብሮት እንደሌለው ስለሚያሳይ ጉዳዩ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ከዚህም በላይ ኤፌሶን 5:33 አንድ ክርስቲያን ባል ‘የገዛ ሚስቱን እንደ ራሱ አድርጎ እንዲወዳት’ እና ሚስትም ‘ለባልዋ ጥልቅ አክብሮት እንዲኖራት’ ያዛል። ማሽኮርመም የቅናት ስሜት የሚቀሰቅስ ነው፤ ታዲያ ለትዳር ጓደኛው ፍቅር ወይም አክብሮት ያለው ሰው ይህን ቢያደርግ ተገቢ ይሆናልን?

በተጨማሪም ማሽኮርመም ወደ ምንዝር ሊያመራ የሚችል መሆኑ የጉዳዩን አሳሳቢነት ከፍ ያደርገዋል፤ ምንዝር ደግሞ ይሖዋ በቀጥታ የሚያወግዘው ኃጢአት ብቻ ሳይሆን አታላይነት እንደሆነ አድርጎም ይገልጸዋል። (ዘጸአት 20:14፤ ዘሌዋውያን 20:10፤ ሚልክያስ 2:14, 15፤ ማርቆስ 10:17-19) እንዲያውም ይሖዋ ምንዝርን ከባድ ኃጢአት አድርጎ ስለሚመለከተው የትዳር ጓደኛቸው ታማኝነት በማጉደል በደል የፈጸመባቸው ሰዎች እንዲፈቱ ይፈቅድላቸዋል። (ማቴዎስ 5:32) ታዲያ ይሖዋ ማሽኮርመምን የመሰለ አጉል ቀልድ ይፈቅዳል ብለን ማሰብ እንችላለን? አንድ አፍቃሪ ወላጅ ልጁ በተሳለ ቢላዋ እንዲጫወት እንደማይፈቅድለት ሁሉ አምላክም እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት አይፈቅድም።

መጽሐፍ ቅዱስ ምንዝርን በተመለከተ የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ይሰጣል:- “በጉያው እሳትን የሚታቀፍ፣ ልብሶቹስ የማይቃጠሉ ማን ነው? በፍም ላይ የሚሄድ፣ እግሮቹስ የማይቃጠሉ ማን ነው? ወደ ሰው ሚስት የሚገባም እንዲሁ ነው፤ የሚነካትም ሁሉ ሳይቀጣ አይቀርም።” (ምሳሌ 6:27-29) ይሁን እንጂ ምንዝር ባይፈጸምም እንኳን ትዳር እያለው የሚያሽኮረምም ሰው በፆታ ስሜት መሳሳብን ወደሚያስከትል አደገኛ ሁኔታ ሊያመራ ይችላል።

በፆታ ስሜት መሳሳብ

አንዳንድ ሰዎች የፆታ ግንኙነት ባይፈጽሙም እንኳ ከትዳራቸው ውጪ የፆታ ምኞት የሚያድግባቸውን ዝምድናዎች አዳብረዋል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ “ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል” ሲል አስጠንቅቋል። (ማቴዎስ 5:28) ኢየሱስ ከልብ አልፎ የማይሄደውን የፆታ ምኞት የተቃወመው ለምንድን ነው?

አንዱ ምክንያት ‘ከልብ . . . ዝሙት ስለሚወጣ’ ነው። (ማቴዎስ 15:19) ሆኖም ይህ ዓይነቱ ዝምድና ምንዝር ወደ መፈጸም ደረጃ የተቃረበ ባይሆንም ጎጂ ነው። እንዴት? አንድ መጽሐፍ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚከተለውን ማብራሪያ ሰጥቷል:- “ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ሆናችሁ ከምታሳልፉት ሕይወት በጣም ከፍተኛ የሆነ ጊዜና ጉልበት የሚሻማ ማንኛውም ሥራ ወይም ዝምድና ታማኝነትን እንደ ማጉደል ተደርጎ የሚቆጠር ነው።” አዎን፣ ከሌላ ሰው ጋር በፆታ ስሜት መሳሳብ ለትዳር ጓደኛ መዋል ያለበትን ጊዜ፣ ትኩረትና ፍቅር ሊሰርቅ ይችላል። ኢየሱስ ሌሎች እንዲያደርጉልን የምንፈልገውን እኛም ለእነሱ እንድናደርግላቸው ከሰጠን ትእዛዝ አንጻር ጉዳዩን ስናየው፣ ባለ ትዳር ሆኖ የሚያሽኮረምም ሰው ‘የትዳር ጓደኛዬ እንዲህ ብታደርግ ምን ይሰማኛል?’ ብሎ ራሱን መጠየቁ ተገቢ ይሆናል።—ምሳሌ 5:15-23፤ ማቴዎስ 7:12

አንድ ሰው እንዲህ ዓይነቱን ተገቢ ያልሆነ ስሜታዊ ቅርርብ መስርቶ ከነበረ ምን ማድረግ አለበት? አግባብ ያልሆነ ስሜታዊ ግንኙነት የመሠረተ አንድ ባለ ትዳር መኪና እየነዳ ከሚያንቀላፋ ሰው ጋር ይመሳሰላል። ትዳሩና ከአምላክ ጋር ያለው ዝምድና ከመበላሸቱ በፊት ምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ሙሉ በሙሉ መገንዘብና ወዲያውኑ ቆራጥ እርምጃ መውሰድ አለበት። ኢየሱስ አንድ ሰው በአምላክ ፊት ያለውን ጥሩ አቋም የሚያበላሽበት ከሆነ ዓይንን የመሰለ ውድ ነገር አውጥቶ መጣል ወይም እጅን ቆርጦ መጣል እንዳለበት በተናገረ ጊዜ ሥር ነቀል እርምጃ የመውሰድን አስፈላጊነት በምሳሌ ገልጿል።—ማቴዎስ 5:29, 30

ስለዚህ ከግለሰቡ ጋር የምትገናኙበትን ቦታና ጊዜ በተመለከተ ገደብ ማበጀታችሁ ጥበብ ይሆናል። ከግለሰቡ ጋር ብቻችሁን እንድትሆኑ የሚያደርጉ ሁኔታዎች እንዳይፈጠሩ መጠንቀቅ አለባችሁ። በምትሠሩበት አካባቢ ከሆነ ደግሞ በጭውውታችሁ መሠረታዊ ይዘት ላይ ገደብ ማበጀት አለባችሁ። እንዲያውም ከዚህ ሰው ጋር ያላችሁን ማንኛውንም ግንኙነት ማቋረጥ ያስፈልጋችሁ ይሆናል። ከዚህ በኋላ አንድ ሰው የሚያያቸውንና የሚያስባቸውን ነገሮች፣ ስሜቶቹን እንዲሁም ባሕርይውን በተመለከተ በሚገባ ራሱን መግዛት ይኖርበታል። (ዘፍጥረት 39:7-12፤ መዝሙር 19:14፤ ምሳሌ 4:23፤ 1 ተሰሎንቄ 4:4-6) ባለ ትዳር የነበረው ኢዮብ “ከዓይኔ ጋር ቃል ኪዳን ገባሁ፤ እንግዲያስ ቆንጆይቱን እንዴት እመለከታለሁ?” ብሎ በተናገረ ጊዜ ግሩም ምሳሌ ትቷል።—ኢዮብ 31:1

በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ባለ ትዳር የሆነ ሰው በማሽኮርመም ተግባር መጠመዱ አደገኛ ከመሆኑም በላይ ቅዱስ ጽሑፋዊም አይደለም። ሆኖም ነጠላ ሰዎችን በተመለከተስ መጽሐፍ ቅዱስ ያለው አመለካከት ምንድን ነው? ከተቃራኒ ጾታ ጋር ዝምድና ለመመስረት የሚያስችል የተለመደ፣ ጉዳት የማያስከትል ወይም አስፈላጊ ነገር ተደርጎ መታየት አለበት? ጉዳት ሊያስከትልስ ይችላል?

ያላገባ ሰው ከሆነስ?

ሁለት ነጠላ የሆኑ ሰዎች የመጋባት ዕቅድ ይዘውና ንጹሕ ካልሆነ ድርጊት ተቆጥበው አንዳቸው ለሌላው ፍቅራዊ ስሜት ቢያሳዩ ምንም ስህተት የለበትም። (ገላትያ 5:19-21) ይህ ዓይነቱ ስሜት ገና ጥናታዊ ቅርርብ በጀመሩበትና የመጋባታቸው አጋጣሚ አናሳ ሆኖ በሚታይበት ወቅትም ሊከሰት ይችላል። በጥሩ ዓላማ ተነሳስተው እስከሆነ ድረስ እንዲህ ዓይነቱን ስሜት ማሳየት ተገቢ አይደለም ማለት አይቻልም። ይህ ባሕርይ ማሽኮርመም ነው ሊባል አይችልም።

ሆኖም ነጠላ የሆኑ ሰዎች ለጨዋታ ያክል በማሽኮርመም ዓይነት አንዳንድ የፍቅር መግለጫዎችን ቢያሳዩ ምን ለማለት ይቻላል? ያላገቡ ስለሆኑ ምንም ጉዳት የሌለው ሊመስል ይችላል። ይሁን እንጂ ሊከሰት የሚችለውን የስሜት ቁስል አስብ። የሚያሽኮረምመው ሰው የሚያሳየው ሁኔታ ከታሰበው በላይ ከበድ ያለ ትርጉም ሊሰጠውና ከፍተኛ ሥቃይና ሐዘን ሊያስከትል ይችላል። “የምትዘገይ ተስፋ ልብን ታሳዝናለች፤ የተገኘች ፈቃድ ግን የሕይወት ዛፍ ናት” የሚሉት የምሳሌ 13:12 ቃላት ምንኛ እውነት ናቸው! ምንም እንኳ ሁለቱም ሰዎች ከልብ እንደማይፈላለጉ የሚተዋወቁ መሆኑን ቢናገሩም አንዳቸው ሌላው ስለሚያስበውና ስለሚሰማው ነገር እንዴት እርግጠኞች ሊሆኑ ይችላሉ? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ የሚል መልስ ይሰጣል:- “የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኮለኛ እጅግም ክፉ ነው፤ ማንስ ያውቀዋል?”—ኤርምያስ 17:9፤ ከፊልጵስዩስ 2:4 ጋር አወዳድር።

በተጨማሪም በሽታ ወይም ያልተፈለገ እርግዝና ሊያስከትል የሚችለውን ዝሙት የመፈጸም አደጋ አስብ። መጽሐፍ ቅዱስ ዝሙትን ይከለክላል፤ እንዲሁም ሆን ብለው ዝሙት የሚፈጽሙ ሰዎች የአምላክን ሞገስ ያጣሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖች ፈተናውን መቋቋም እንዲችሉ ‘ዝሙትን በተመለከተ ብልቶቻቸውን መግደል’ እንዳለባቸውና ወደ ዝሙት የሚመራውን ‘የፍትወት ምኞት’ ማስወገድ እንደሚኖርባቸው አስጠንቅቋቸዋል። (ቆላስይስ 3:5፤ 1 ተሰሎንቄ 4:3-5) በኤፌሶን 5:3 ላይ ዝሙት መጥፎ ምኞት ሊያነሳሳ በሚችል መንገድ በመካከላችን ‘ከቶ መሰማት’ እንደሌለበት መክሮናል። ማሽኮርመም ከዚህ ምክር ጋር ይቃረናል። ሌላው ቀርቶ አምላክ ጾታን በተመለከተ ጤናማ ያልሆነ ጭውውት ከማድረግ እንድንቆጠብ አጥብቆ ያዘናል።

የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ማሽኮርመም አንድን ሰው እጅግ ሊጎዳ የሚችል እንደሆነና የጋብቻ መስራች የሆነውን ይሖዋን የማያስከብር መሆኑን ይገልጻሉ። መጽሐፍ ቅዱስ አግባብነት የሌለውን የማሽኮርመም ድርጊት በተመለከተ ያለው አመለካከት ሰዎችን ከስሜት ጉዳት የሚጠብቅ ስለሆነ በእርግጥም ፍቅራዊና ምክንያታዊ ነው። ይህም በመሆኑ አምላክን የሚወዱ ሰዎች ተገቢ ካልሆነ የማሽኮርመም ድርጊት ይርቃሉ፤ እንዲሁም ተቃራኒ ጾታ ላላቸው ሰዎች ንጹሕ አመለካከት የሚኖራቸው ከመሆኑም በላይ አክብሮት ያሳያሉ።—1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10፤ 5:1, 2

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ማሽኮርመም፣ ከጾታ ስሜት ነፃ በሆነ መንፈስ ወዳጃዊ ወይም ተግባቢ ከመሆን ፈጽሞ የተለየ መሆኑ መዘንጋት የለበትም።

b በየካቲት 8, 1994 የንቁ! (የእንግሊዝኛ) እትም ላይ የወጣውን “አምላክ የሚጠላው ምን ዓይነት ፍቺን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

© The Curtis Publishing Company

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ