የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g99 2/8 ገጽ 25-27
  • ገንዘብ ማግኘት የምችለው እንዴት ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ገንዘብ ማግኘት የምችለው እንዴት ነው?
  • ንቁ!—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ሥራ ማፈላለግ
  • ሥራ ለመቀጠር ማመልከቻ ማስገባት
  • የግል ሥራ መሥራት
  • ሚዛንህን ጠብቅ!
  • ገንዘብ ማግኘት የምችለው እንዴት ነው?
    ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2
  • ሥራ ላገኝ (እንዲሁም ቋሚ ልሆን) የምችለው እንዴት ነው?
    ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች
  • ሥራ ለማግኘት የሚረዱ አምስት ቁልፍ ሐሳቦች
    ንቁ!—2005
  • በሥራህ መደሰት ትችላለህ
    ከአምላክ ፍቅር ሳትወጡ ኑሩ
ንቁ!—1999
g99 2/8 ገጽ 25-27

ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች ...

ገንዘብ ማግኘት የምችለው እንዴት ነው?

“ጠቀም ያለ ገንዘብ የሚያስገኝ ሥራ እፈልጋለሁ።”—ታኒያ

ብዙ ወጣቶች እንደ ታኒያ ይሰማቸዋል። አንድ ሰርዞ የተባለ ወጣት “መኪና ለመግዛትና ወደ ገበያ ወጥቼ የፈለግኩትን ልብስ ለመግዛት እንድችል ገንዘብ እፈልጋለሁ” በማለት ተናግሯል። “ለትንሹም ለትልቁም ወላጆቼኝ ማስቸገር አልፈልግም።” ወጣቷ ሎሪአንም ሥራን በተመለከተ ያላት አስተያየት ከዚህ የተለየ አይደለም። “ሴት እንደመሆኔ መጠን ገበያ ወጥቼ ዕቃ መሸመት ደስ ይለኛል” በማለት ተናግራለች።

ዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ዎርልድ ሪፖርት የተባለው መጽሔት እንደገለጸው “[በዩናይትድ ስቴትስ] የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ለመጨረስ አንድና ሁለት ዓመት ከቀራቸው ተማሪዎች መካከል ከአራቱ ሦስቱ ከትምህርት ቤት ሰዓት በኋላና ቅዳሜና እሁድ የሚሠሩ መሆናቸው” አያስገርምም። ይህ ሁኔታ በዛሬው ፍቅረ ነዋይ በተጠናወተው ዓለም ውስጥ በሰፊው ተስፋፍቶ የሚገኘውን ሚዛኑን የሳተ ‘የገንዘብ ፍቅር’ በተሰወነ መጠን የሚያንጸባርቅ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 6:10) ይህ ማለት ግን ገቢ እንዲኖራቸው የሚፈልጉ ወጣቶቸ ሁሉ በፍቅረ ነዋይ ወጥመድ ተይዘዋል ማለት አይደለም።

መጽሐፍ ቅዱስ ‘ገንዘብ እንደ ጥላ ነው’ በማለት ይናገራል። (መክብብ 7:12) ክርስቲያን ወጣት እንደመሆንህ መጠን ገንዘብ ማግኘት የምትፈልግባቸው ጥሩ ምክንያቶች ይኖርህ ይሆናል።a ለምሳሌ ያህል ወጣቱ አቪን በሳምንት ሁለት ቀን የሚሠራበትን ምክንያት ሲናገር “የዘወትር አቅኚ [የሙሉ ጊዜ አገልጋይ] እንደመሆኔ መጠን ራሴን ለመደገፍ ያስችለኛል” ብሏል።

አንተም የትርፍ ሰዓት ሥራ ማግኘት የምትፈልግበት ተመሳሳይ ምክንያቶች ይኖሩህ ይሆናል። ምናልባት በትላልቅ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ግብ አውጥተህ ይሆናል። ወይም ለጉባኤ ስብሰባዎች የሚሆን ተጨማሪ ልብስ መግዛት አስፈልጎህ ይሆናል። ያም ሆነ ይህ እነዚህን ነገሮች ለማግኘት ገንዘብ ያስፈልጋል። አምላክ ‘መንግሥቱን ለሚያስቀድሙ’ ሁሉ የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች እንደሚሰጣቸው ኢየሱስ ቃል ገብቷል። (ማቴዎስ 6:33) ይሁን እንጂ ይህ እጅህን አጣጥፈህ ትቀመጣለህ ማለት አይደለም። (ከሥራ 18:1-3 ጋር አወዳድር።) ታዲያ ገንዘብ ማግኘት የሚያስፈልግህ ከሆነ ልትወስዳቸው የምትችላቸው አንዳንድ ተግባራዊ እርምጃዎች ምንድን ናቸው?

ሥራ ማፈላለግ

ሥራ ለመጀመር ያለህን እቅድ ወላጆችህም ይስማሙበታል እንበል። መጀመሪያ መውሰድ የሚኖርብህ እርምጃ ሥራ እየፈለግህ እንዳለህ ለጎረቤቶችህ፣ ለአስተማሪዎችህና ለዘመዶችህ መንገር ነው። እነርሱን በቀጥታ መጠየቁ የሚያሳፍርህ ከሆነ ወጣት በነበሩበት ጊዜ ሥራ ያገኙት እንዴት እንደሆነ እንዲነግሩህ ልትጠይቃቸው ትችላለህ። አንዳንድ ሊጠቅም የሚችል ሐሳብ ሊሰጡህ ይችላሉ። ሥራ በመፈለግ ላይ እንዳለህ የሚያውቁት ሰዎች ቁጥር እየተበራከተ ሲሄድ የምታገኛቸው መረጃዎችና ጥቆማዎችም የዚያኑ ያህል እየበዙ ይሄዳሉ።

ከዚያም በጋዜጦች ላይ የሚወጡ፣ በንግድ አካባቢዎች፣ በትምህርት ቤትና በተለያዩ ቦታዎች የሚለጠፉ ክፍት የሥራ ቦታ ማስታወቂያዎችን ተከታተል። “ሥራ ያገኘሁት በዚህ መንገድ ነው” ሲል ዴቭ የተባለ አንድ ወጣት ይናገራል። “ጋዜጣ ላይ አንብቤ በፋክስ መልእክት ላክሁና በኋላ ስልክ ደወልኩ።” ይሁን እንጂ በርካታ ክፍት ሥራዎች በማስታወቂያ የማይወጡ መሆናቸውን ታውቃላችሁ? ሰቨንቲን የተባለ አንድ መጽሔት እንዳለው ከሆነ አንዳንዶች “ባለ ጉዳዩ ቀርቦ እስካልጠየቀ ድረስ ከአሥር ሥራዎች መካከል ሦስት አይገኙም።” ምናልባትም ቀጣሪው ለአንተ የሚሆን ክፍት የሥራ ቦታ እንዲፈልግልህ ልታደርገው ትችል ይሆናል!

ይሁን እንጂ እንዴት? ‘እኔ የሥራ ልምድ የለኝም’ ብለህ ታስብ ይሆናል። እስኪ ለአንድ አፍታ አስብ። ወላጆችህ ራቅ ወዳለ አካባቢ በሄዱባቸው ጊዜያት ታናሽ ወንድምህን ወይም እህትህን ወይም የጎረቤት ልጅ ጠብቀህ ታውቃለህ? ይህ ለኃላፊነት የምትበቃ መሆንህን የሚያሳይ ነው። አባትህ መኪና ሲጠግን ረድተኸው ታውቃለህ? ይህም መካኒክ የመሆን ዝንባሌ እንዳለህ የሚያሳይ ሊሆን ይችላል። ታይፕ መምታት ወይም በኮምፒዩተር መጠቀም ትችላለህ? ወይም ትምህርት ቤት በአንዳንድ የፈጠራ ሥራዎች ጥሩ ውጤት አግኝተህ ታውቃለህ? እነዚህ ሥራ ለመቀጠር የሚያስችሉ አሳማኝ ነጥቦች ናቸው።

በትርፍ ጊዜህ መሥራት የምትወዳቸውን ነገሮችንና ዝንባሌዎችህንም አቅልለህ አትመልከታቸው። ለምሳሌ ያህል አንድ ዓይነት የሙዚቃ መሣሪያ መጫወት የምትችል ከሆነ በሙዚቃ መሣሪያ መሸጫዎች ውስጥ ለአንተ የሚሆን ክፍት የሥራ ቦታ አታጣ ይሆናል። በሱቁ ውስጥ ካሉት መሣሪያዎች ጋር የተዛመደ ዝንባሌ ስላለህ እዚያ ብትቀጠር ገዢዎችን ለማስተናገድ እንደምትችል ጥርጥር የለውም።

ሥራ ለመቀጠር ማመልከቻ ማስገባት

የሥራ ቃለ መጠይቅ ሊደረግልህ ቀጠሮ ይዘሃል እንበል። ውጫዊ ሁኔታህ ራሱ ስለሚናገር ለአለባበስህና ለሰውነት አያያዝህ ትኩረት መስጠት ይኖርብሃል። “ለኃላፊነት የምትበቃ፣ ንጹሕ፣ የተደራጀህ” መሆንህን ሊያሳይ አለዚያም ከዚህ ተቃራኒ መልእክት ሊያስተላልፍ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያን ሴቶች “በሚገባ ልብስ ከእፍረትና ራሳቸውን ከመግዛት ጋር ሰውነታቸውን ይሸልሙ” ብሎ ማበረታታቱ የሚገባ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 2:9) ይህ ጥቅስ ለወንዶችም ይሠራል። ሥራው ምንም ይሁን ምን ቅጥ ያጣ ወይም የተዝረከረከ ልብስ ለብሰህ ለቃለ መጠይቅ አትሂድ።

ዝንባሌህና ጠባይህም ስለ አንተ የሚናገረው ብዙ ነገር አለው። ወርቃማውን ሕግ ሥራበት:- ሌሎች እንዲይዙህ በምትፈልገው መንገድ አንተም እንዲሁ ሌሎችን ያዛቸው። (ማቴዎስ 7:12) የቀጠሮ ሰዓት አክብር። ሞቅ ያለ ስሜት ያለህና ንቁ ሁን። ጥሩ ጠባይ አሳይ። ያለምንም ማጋነንና ጉራ ለሥራው ብቁ ነኝ የምትልበትን ምክንያት አስረዳ። የምትሰጠው መልስ ነጥቡን የሚያስጨብጥ ይሁን።

ንጹህና በሚገባ የተቀናበረ ማመልከቻ ይዞ መቅረብ (ወይም ቀደም ብሎ መላክ) ጥሩ እንደሆነ አንዳንድ ባለሙያዎች ሐሳብ ይሰጣሉ። ማመልከቻው ላይ ስምህን፣ አድራሻህን፣ የስልክ ቁጥርህን፣ የምትፈልገውን የሥራ ዓይነት፣ የትምህርት ደረጃህን (የወሰድከው ሌላ ስልጠናም ካለ ጥቀስ)፣ ያለህን የሥራ ልምድ (በክፍያም ሆነ በፈቃደኛ ሠራተኛነት የሠራህበትን ይጨምራል)፣ ያለህን ልዩ ሙያ፣ በትርፍ ጊዜህ መሥራት የምትወዳቸውን ነገሮች (ይህ ስለ ችሎታህ ፍንጭ የሚሰጥ ሊሆን ይችላል) ካካተትህ በኋላ ማስረጃዎቹንም ማቅረብ የምትችል መሆንህን የሚገልጽ ማስታወሻ አስፍር። በተጨማሪም ለሥራው የድጋፍ ሐሳብ የሚያቀርቡልህን ሰዎች ስም፣ አድራሻና ስልክ ቁጥር በሌላ ወረቀት ላይ በዝርዝር ማስፈርም ትችል ይሆናል። እርግጥ ሰዎቹ ፈቃደኛ መሆናቸውን አስቀድመህ ማረጋገጥ ይኖርብሃል። እነዚህ ሰዎች ቀደም ሲል በሠራህባቸው መሥሪያ ቤቶች የነበሩ አሠሪዎችህ፣ አስተማሪህ፣ የትምህርት ቤት አማካሪ፣ በቅርብ የምታውቀው ትልቅ ሰው በሌላ አባባል ስላለህ ሙያ፣ ችሎታ ወይም ስለ ጠባይህ ሊመሰክር የሚችል ማንኛውም ሰው ሊሆን ይችላል።

የግል ሥራ መሥራት

ይሁንና ከፍተኛ ጥረት አድርገህም ሥራ ለማግኘት ያደረግከው ጥረት ሁሉ መና ሆኖ ቢቀርስ? ይህ በብዙ አገሮች የሚያጋጥም የተለመደ ችግር ነው። ሆኖም ተስፋ አትቁረጥ። የግል ሥራ ማቋቋም መፍትሔ ሆኖ ታገኘው ይሆናል። ይህ ምን ጥቅም አለው? የሥራ ሰዓትህን ራስህ መወሰን እንድትችልና ከፈለግህ ረዘም ያለ ሰዓት አለዚያም አጠር ያለ ሰዓት እንድትሠራ ነፃነት ይሰጥሃል። እርግጥ ነው የግል ሥራ በራስ አስቦ መነሳሳትን፣ ራስን መገሠጽንና ቀዳሚ ሆኖ ለመገኘት ፈቃደኛ መሆንን ይጠይቃል።

ይሁን እንጂ በምን ዓይነት የሥራ መስክ መሠማራት ትችላለህ? እስቲ ለአንድ አፍታ ስለ ጎረቤቶችህ አስብ። ሌላ ማንም ሰው የማያቀርባቸውን ሸቀጣ ሸቀጦች ማቅረብ ወይም አንድ ዓይነት አገልግሎት መስጠት ያስፈልግ ይሆን? ለምሳሌ ያህል እንስሳ ትወዳለህ እንበል። ገንዘብ በማስከፈል የጎረቤቶችህን የቤት እንስሳት ማጠብ ወይም የፀጉራቸውን ንጽሕና መንከባከብ ትችላለህ። ወይም የሙዚቃ መሣሪያ መጫወት ትችል ይሆናል። ምናልባት ሌሎችን ማስተማር ትችል ይሆን? ወይም ደግሞ መስኮት ማጠብ ወይም ጽዳት የመሰሉትን ብዙውን ጊዜ በሌሎች ዘንድ የተናቁ ሥራዎችን የመሥራት ጉዳይ ሊሆን ይችላል። አንድ ክርስቲያን በገዛ እጆቹ ለመሥራት የሚያፍርበት ምንም ምክንያት የለም። (ኤፌሶን 4:28) ሌላው ቀርቶ አንድ አዲስ ሙያ ለመማር ልትሞክር ትችል ይሆናል። ቤተ መጻሕፍት ሄደህ ራስ አገዝ መጻሕፍትን ልታነብ ወይም ከጓደኞችህ አንዱ እንዲያስተምርህ ልትጠይቅ ትችላለህ። ለምሳሌ ያህል ወጣቱ ጃሹዋ ትምህርት ቤት ገብቶ የቁም ጽሕፈት ተማረ። ከዚያም የሠርግና የግብዣ ጥሪ ወረቀት በማዘጋጀት አነስተኛ ንግድ ጀመረ።—“መፍጠር የምትችላቸው ሥራዎች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

ልታስብበት የሚገባ ጉዳይ አለ። ጥቅሙንና ጉዳቱን እንዲሁም ከሥራው ጋር ተዛማጅነት ያላቸውን ሌሎች ጉዳዮች ሳታጤን በችኮላ አንድ ዓይነት ሥራ አትጀምር። (ሉቃስ 14:28-30) በመጀመሪያ ከወላጆችህ ጋር ተማከር። በተጨማሪም ተመሳሳይ ሥራ የሚያካሂዱ ሌሎች ሰዎችን አነጋግር። ግብር እንድትከፍል ይጠበቅብህ ይሆን? ፈቃድ ማውጣትስ ይኖርብህ ይሆን? ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት በአካባቢህ ያሉ ባለ ሥልጣናትን አነጋግር።—ሮሜ 13:1-7

ሚዛንህን ጠብቅ!

በሌላ በኩልም ልታከናውን ከምትችለው በላይ በርካታ ነገር የመሸከም አደጋ አለ። ሎሪአን ሥራ ስለያዙ አንዳንድ ወጣቶች ስትናገር:- “ከትምህርት ቤት የሚሰጣቸውን አብዛኛውን የቤት ሥራ አይሠሩም። በጣም ስለሚደክማቸው ክፍል ውስጥም በትኩረት መከታተል ያስቸግራቸዋል” ብላለች። በአንዳንድ የዓለም ክፍል የሚኖሩ ወጣቶች ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት ሲሉ ረዥም ሰዓት ከመሥራት የተሻለ ሌላ አማራጭ እንደሌላቸው እሙን ነው። ይሁን እንጂ የአንተ ሁኔታ ከዚያ የተለየ ከሆነ ለምን ራስህን ችግር ውስጥ ትከታለህ? ትምህርት እየተማሩ በሳምንት ውስጥ ከ20 የሚበልጥ ሰዓት መሥራት መጠኑን ያለፈ እንደሚሆንና ፍሬ ቢስ እንደሚያደርግ በርካታ ባለሙያዎች ይናገራሉ። አንዳንድ ባለ ሙያዎች በአንድ ሳምንት ውስጥ ከስምንት ወይም ከአሥር ያልበለጠ ሰዓት መሥራት በቂ እንደሆነ ሐሳብ ይሰጣሉ።

ጊዜህን፣ ጉልበትህንና ኃይልህን ከትምህርት ሰዓት በኋላ በሚሠሩ ሥራዎች ላይ ከመጠን በላይ የምታጠፋ ከሆነ ጤንነትህ፣ የትምህርት ውጤትህ በተለይ ደግሞ መንፈሳዊነትህ ይዳከማል። አዎን፣ ‘በባለጠግነት ማታለልና በሌላውም ነገር ምኞት’ የሚታነቁት አዋቂ ሰዎች ብቻ አይደሉም። (ማርቆስ 4:19) ስለዚህ ሚዛንህን ጠብቅ። ሰሎሞን “በድካምና ነፋስን በመከተል ከሁለት እጅ ሙሉ ይልቅ አንድ እጅ ሙሉ በዕረፍት ይሻላል” በማለት ከመጠን በላይ በሥራ ስለ መጠመድ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል።—መክብብ 4:6

አዎን፣ ገንዘብ ማግኘት አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው እንደ ወጣት አቪን ገንዘብ ለማግኘት ያነሳሳህ ውስጣዊ ግፊት ጤናማና አምላካዊ ከሆነ ይሖዋ ጥረትህን እንደሚባርክልህ እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ። ሆኖም በምትሠራው ሥራ ከመጠን በላይ ደክመህ “የሚሻለውን ነገር” ማለትም መንፈሳዊ ጥቅሞችን ችላ እንዳትል ጥንቃቄ አድርግ። (ፊልጵስዩስ 1:10) ምንም እንኳ ገንዘብ እንደ “ጥላ” ሆኖ ሊያገለግል ቢችልም እውነተኛ ስኬት ሊያስገኝልህ የሚችለው ከይሖዋ ጋር የመሠረትከው ዝምድና ነው።—መክብብ 7:12፤ መዝሙር 91:14

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በኅዳር 22, 1990፤ በታኅሣሥ 8, 1990 እና በመስከረም 22, 1997 የእንግሊዝኛ ንቁ! መጽሔት እትም ላይ “ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .” በሚለው አምድ ሥር ከትምህርት ሰዓት ውጭ ሥራ መሥራት ያለውን ጥቅምና ጉዳት ለማመዛዘን የሚያስችሉ ነጥቦች ወጥተዋል።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

መፍጠር የምትችላቸው ሥራዎች

• መስኮት ማጽዳት ጋዜጦች መሸጥ ወይም ማድረስ

• አትክልተኝነት ወይም አጨዳ

• ልጅ መጠበቅ

• የቤት እንስሶችን መመገብ፣ ማናፈስ ወይም ማጠብ

• ጫማ መጥረግ

• የተቀደደ ልብስ መስፋት ወይም መተኮስ

• ፍራፍሬና የጓሮ አትክልት መትከልና መሸጥ

• ዶሮ ማርባት ወይም እንቁላል መሸጥ

• ታይፕ መምታት ወይም ራፖር መጻፍ

• መላላክ

• በየቤቱ የሚከፋፈሉ ነገሮችን ማድረስ

• ሙዚቃ ወይም ሌሎች የትምህርት ዓይነቶችን ማስተማር

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከመጠን በላይ በሥራ መጠመድ የክፍል ውጤትህ እንዲያሽቆለቁል ሊያደርግ ይችላል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ