ከሃያ ዘጠነኛው ፎቅ የተሰጠ አስተያየት
በኒው ዮርክ ከተማ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሕንፃ ሃያ ዘጠነኛ ፎቅ ላይ ደርሰህ ከአሳንሱሩ ስትወጣ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቢሮ የት እንደሚገኝ የሚጠቁም ትንሽ ሰማያዊ ምልክት ታገኛለህ። ይህ ቢሮ ዋነኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰብዓዊ መብቶች እንቅስቃሴ የሚከናወንበትን የጄኔቭ፣ ስዊዘርላንድ ዋና መሥሪያ ቤት ይወክላል። በጄኔቫ የሚገኘውን ቢሮ በበላይነት የሚመሩት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር የሆኑት ሜሪ ሮቢንሰን ሲሆኑ የኒው ዮርኩን ቢሮ የሚመሩት የግሪክ ተወላጅ የሆኑት ኤልሳ ስታማቶፑሉ ናቸው። ሚስስ ስታማቶፑሉ መልካም ፈቃዳቸው ሆኖ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ አንድ የንቁ! ዝግጅት ክፍል አባል ተቀብለው ስላለፉት አምስት አሥርተ ዓመታት የሰብዓዊ መብቶች እንቅስቃሴ ያላቸውን አስተያየት ሰጥተዋል። ከቃለ ምልልሱ የተገኙ አንዳንድ አስተያየቶች እንደሚከተለው ቀርበዋል።
ጥ. ሰብዓዊ መብቶችን በማስፋፋት ረገድ ምን እድገት የተገኘ ይመስልዎታል?
መ. ሦስት የእድገት ዘርፎችን በምሳሌነት ልጠቅስልህ እችላለሁ:- በመጀመሪያ፣ ከ50 ዓመት በፊት የሰብዓዊ መብቶች ጽንሰ ሐሳብ በዓለም አቀፉ አጀንዳ ውስጥ ፈጽሞ አይገኝም ነበር። በአሁኑ ጊዜ ግን የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ በሁሉም ቦታዎች ይነሳል፣ ሁሉም ለተግባራዊነቱ ታጥቋል። ከጥቂት አሥርተ ዓመታት በፊት ስለ ሰብዓዊ መብቶች ሰምተው የማያውቁ መንግሥታት አሁን ስለዚሁ ጉዳይ መነጋገር ጀምረዋል። ሁለተኛ፣ በአሁኑ ጊዜ መንግሥታት ለዜጎቻቸው ሊያሟሉ የሚገቧቸውን ግዴታዎች የሚገልጹ በርካታ ስምምነቶች የተካተቱበት ዓለም አቀፋዊ ሕግ ወይም የሕግ መጽሐፍ አለን። [ገጽ 7 ላይ የሚገኘውን “የሰብዓዊ መብቶች ዓለም አቀፋዊ ሕግ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።] ይህን ሕግ ለማሰባሰብ የብዙ ዓመታት ልፋት ጠይቋል። ይህ በጣም የምንኮራበት የሥራ ውጤት ነው። ሦስተኛው ምሳሌ ዛሬ ከማንኛውም ጊዜ በበለጠ ሁኔታ ብዙ ሰዎች በሰብዓዊ መብቶች እንቅስቃሴዎች ውስጥ ይካፈላሉ። በተጨማሪም ሰብዓዊ መብቶችን ስለሚመለከቱ ጉዳዮች በአንደበተ ርቱዕነት ሊናገሩ ይችላሉ።
ጥ. ምን እንቅፋቶች አጋጥመዋችኋል?
መ. በተመድ የሰብዓዊ መብቶች ፕሮግራሞች ውስጥ ባሳለፍኩት የ17 ዓመት የሥራ ዘመን ተስፋ አስቆራጭ የሆኑ ችግሮች እንዳሉብን ተገንዝቤያለሁ። በጣም ትልቁ ችግር መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ጥያቄዎችን እንደ ሰብዓዊነት ጥያቄ ሳይሆን እንደ ፖለቲካዊ ጥያቄ መመልከታቸው ነው። ፖለቲካዊ ሥጋት ስለሚኖርባቸው የገቧቸውን የሰብዓዊ መብት ውሎች ተግባራዊ ለማድረግ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ይቀራሉ። እንደነዚህ ባሉት ጊዜያት የሰብዓዊ መብት ውሎች በድን ፊደላት ብቻ ሆነው ይቀራሉ። ሌላው ድክመት ተመድ እንደ ቀድሞዋ ዩጎዝላቭያና ሩዋንዳ፣ አሁን በቅርቡ ደግሞ እንደ አልጀሪያ በመሰሉት አገሮች የተፈጸሙትን የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች ለማስቆም አለመቻሉ ነው። ተመድ በእነዚህ አገሮች የተፈጸመውን ጭፍጨፋ ለማስቀረት አለመቻሉ በጣም ትልቅ ድክመት ነው። ሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር የሚያስፈልገው መዋቅር ተዘርግቷል። ተግባር ላይ የሚያውላቸው አካል ግን ያስፈልጋል። ታዲያ ይህን የሚፈጽመው ማን ነው? አብዛኛውን ጊዜ ጥበቃ ሊያደርጉ የሚችሉት አገሮች ብሔራዊ ጥቅም አደጋ ላይ እስካልወደቀ ድረስ የሚፈጸመውን የሰብዓዊ መብቶች ረገጣ ጣልቃ ገብቶ የማስቆም የፖለቲካ ፈቃደኛነት አይታይም።
ጥ. ስለ ወደፊቱ ጊዜስ ምን ይታይዎታል?
መ. ወደ መላው የሰው ዘር ሰብዓዊ መብቶች መከበር በሚያመራው ጎዳና ላይ ተፈታታኝ ሁኔታዎች መኖራቸው፣ በሌላ በኩል ደግሞ ጥሩ ተስፋ ይታየኛል። ኢኮኖሚው ዓለም አቀፋዊ እየሆነ በመምጣቱና ትላልቅ የንግድ ድርጅቶች የሰው ጉልበት ርካሽ ወደሆነባቸው አገሮች እንዲስፋፉ በመገፋፋታቸው ምክንያት የሚፈጠረው አደገኛ ሁኔታ በጣም ያሳስበኛል። ዛሬ፣ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ሰብዓዊ መብቶችን የሚጋፉ መንግሥታትን ልንወቅስና ጫናም ልናደርግባቸው እንችላለን። በድንበር ዘለል የንግድ ስምምነቶችና ውሎች ምክንያት ሥልጣንና ኃይል ከመንግሥታት እጅ ወጥቶ ዓለም አቀፍ በሆኑት የኢኮኖሚ ኃይሎች እጅ ውስጥ ሲገባ ማንን ልንወቅስ እንችላለን? እነዚህን የኢኮኖሚ ኃይሎች የመቆጣጠር ሥልጣንና ችሎታ ስለማይኖረን እንደ ተመድ ያሉት በይነ መንግሥታዊ ድርጅቶች አቅም በጣም ይዳከማል። ይህ አዝማሚያ ከሰብዓዊ መብቶች አንጻር ሲታይ በጣም ጎጂ ነው። አሁኑኑ የግሉን ዘርፍ በሰብዓዊ መብት አጠባበቅ እንቅስቃሴ መርከብ ላይ ማሳፈር በጣም ወሳኝ ነው።
ጥ. ተስፋውስ?
መ. የሰብዓዊ መብቶች ባሕል በዓለም አቀፍ ደረጃ መስፋፋት ነው። በትምህርት አማካኝነት ሰዎች ስለ ሰብዓዊ መብቶች ያላቸው ግንዛቤ ከፍ እንዲል ማድረግ አለብን ማለቴ ነው። ይህ ቀላል ሥራ እንዳልሆነ የታወቀ ነው። ምክንያቱም የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት የሚጠይቅ ተግባር ነው። ተመድ ከአሥር ዓመታት በፊት ሕዝቦችን ስለ መብቶቻቸው፣ አገሮችን ደግሞ ስለ ኃላፊነቶቻቸው የሚያስተምርበት ዓለም አቀፍ የሆነ የማስተማር ዘመቻ የጀመረው በዚህ ምክንያት ነው። በተጨማሪም ተመድ ከ1995 እስከ 2004 ያሉትን ዓመታት “ስለ ሰብዓዊ መብቶች ትምህርት የሚሰጥባቸው ዓመታት” ሲል ሰይሟል። ትምህርት የሰዎችን አእምሮና ልብ ይለውጣል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ይህ የወንጌሉን ቃል የሚመስል ቢሆንም ስለ ሰብዓዊ መብቶች በሚሰጥ ትምህርት ረገድ እውነተኛ አማኝ ነኝ። በሚቀጥለው መቶ ዓመት መላው ዓለም የሰብዓዊ መብቶችን ባሕል እንደ ራሱ ርዕዮተ ዓለም አድርጎ እንደሚመለከት ተስፋ አደርጋለሁ።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የሰብዓዊ መብቶች ዓለም አቀፋዊ ሕግ
ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ በተጨማሪ የሰብዓዊ መብቶች ዓለም አቀፋዊ ሕግ አለ። በሁለቱ መካከል ምን ዝምድና አለ?
የሰብዓዊ መብቶችን ዓለም አቀፋዊ ሕግ በአንድ መጽሐፍ ብንመስል ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ በዚህ መጽሐፍ እንደ ምዕራፍ 1 ሊቆጠር ይችላል። ምዕራፍ 2 እና 3 ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳንና ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የባሕላዊ መብቶች ቃል ኪዳን ይሆናሉ። በምዕራፍ 4 እና 5 ውስጥ ሌሎች ተጨማሪ ፕሮቶኮሎች ተካትተዋል።
ዓለም አቀፉ ድንጋጌ ብሔራት ምን ማድረግ እንደሚኖርባቸው የሚናገርና ሞራላዊ ጠቀሜታ ያለው ሰነድ እንደሆነ ሲታሰብ ተጨማሪዎቹ አራት ሰነዶች ግን ሕጋዊ አስገዳጅነት ያላቸውና ብሔራትን እንዲህ አድርጉ ብለው የሚያዝዙ ሰነዶች ናቸው። እነዚህን ሰነዶች ማርቀቅ የተጀመረው በ1949 ቢሆንም ሁሉም ተግባራዊ ሊሆኑ የቻሉት ከበርካታ አሥርተ ዓመታት በኋላ ነው። ዛሬ እነዚህ አራት ሰነዶች ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ ጋር ተጣምረው የሰብዓዊ መብቶች ዓለም አቀፋዊ ሕግ ይባላሉ።
ተመድ ከዚህ ዓለም አቀፋዊ ሕግ በተጨማሪ ሌሎች ከ80 የሚበልጡ ሰብዓዊ መብቶችን የሚመለከቱ ውሎች አጽድቋል። አንዲት የሰብዓዊ መብቶች ሊቅ “ስለዚህ በዓለም አቀፋዊው ሕግ ውስጥ የተጠቃለሉት የሰብዓዊ መብት ውሎች ከሁሉ የላቀ ቦታ የሚሰጣቸው ናቸው ብሎ ማሰብ ስህተት ነው” ብለዋል። “ለምሳሌ ያህል በ1990 የጸደቀው የሕፃናት መብቶች ኮንቬንሽን ከማንኛውም ዓለም አቀፋዊ የተመድ ሰነዶች የበለጠ ሰፊ ተቀባይነት ያገኘ ሰነድ ቢሆንም የሰብዓዊ መብቶች ዓለም አቀፋዊ ሕግ ክፍል ግን አይደለም። ‘የሰብዓዊ መብቶች ዓለም አቀፋዊ ሕግ’ የሚለው ስያሜ የተመረጠው አንድን መደበኛ የሆነ ጽንሰ ሐሳብ ለመግለጽ ሳይሆን የሕዝቦችን ትኩረት ለመሳብ ነው። በእርግጥም ትኩረት የሚስብ ሐረግ እንደሆነ ትስማማላችሁ።”a
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ይህ ጽሑፍ በተጻፈበት ጊዜ 191 ብሔራት (183 የተመድ አባል አገሮችና 8 አባል ያልሆኑ አገሮች) የሕፃናት መብቶችን ኮንቬንሽን ተቀብለዋል። ያልተቀበሉት ሁለት አገሮች ብቻ ሲሆኑ እነርሱም ሶማልያና ዩናይትድ ስቴትስ ናቸው።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኤልሳ ስታማቶፑሉ
[ምንጭ]
UN/DPI photo by J. Isaac