በ2000 ኮምፒዩተሮች ከአገልግሎት ውጭ መሆናቸው አንተንም ይነካ ይሆን?
ኮምፒዩተር ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም መድረክ ላይ ብቅ ባለበት ጊዜ የሰው ልጅ ኤሌክትሪክን ከፈለሰፈ ወዲህ እንዲህ ያለ አስደናቂ ነገር ተፈልስፎ አያውቅም ተብሎ ነበር። ዛሬ፣ በርካታ አሥርተ ዓመታት ያለፉ ሲሆን ብዙ ሰዎች ኮምፒዩተር ባይኖር ኖሮ ምን እንሆን ነበር እስከማለት ደርሰዋል። ይህ የምታነበው መጽሔት የተዘጋጀው በኮምፒዩተር እርዳታ ነው። ኮምፒዩተር በርካታ መረጃዎችን ሊያስቀምጥና በተፈለገበት ጊዜ በቅጽበት መልሶ ሊሰጥ ይችላል። አዎን፣ ኮምፒዩተር በጣም አስደናቂ መሣሪያ ነው! ኮምፒዩተር ባይፈለሰፍ ኖሮ ዓለማችን ምን ትሆን ነበር?
በሰለጠኑት የዓለም አካባቢዎች በአንድ መንገድ ወይም በሌላ በኮምፒዩተሮች የማይነካ የሕይወት ዘርፍ የለም። የምትተዳደረው በጡረታ አበል ወይም ከመንግሥት በምታገኘው የአካል ጉዳተኛ አበል ከሆነ፣ ወይም የታክስ ተመላሽ ገንዘብ፣ ወይም የኢንሹራንስ ክፍያ ወይም ማንኛውንም እነዚህን የመሰለ ክፍያ የምታገኝ ከሆነ ይህን ገንዘብ የማግኘት ዕድልህ በኮምፒዩተሮች ላይ የተመካ ነው። በደመወዝ የምትተዳደር ሠራተኛ ከሆንክ ደመወዝህ የሚዘጋጀው በኮምፒዩተር መሆኑ አይቀርም። በባንክ ነክ ተቋሞች ውስጥ የሚቀመጠውን ገንዘብና የሚከፈለውን ወለድ የሚከታተሉትና የሚያሰሉት ኮምፒዩተሮች ናቸው። በዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ የሚገኙትን እንደ ኤሌክትሪክ ማመንጫና ውኃ ማጣሪያ ያሉትን መሣሪያዎች የሚቆጣጠሩት ኮምፒዩተሮች ናቸው። ለዶክተሮች፣ ለክሊኒኮችና ለሆስፒታሎች ምርመራ በማድረግና ሕይወት በማዳን ረገድ ከፍተኛ አገልግሎት ይሰጣሉ። ኮምፒዩተሮች የአየር ሁኔታ በመቆጣጠርና አውሮፕላኖችን ከግጭት በመጠበቅ ረገድ ጠቃሚ አገልግሎት ያበረክታሉ።
የኮምፒዩተሮች ብልህነት እስከ ምን ድረስ ነው?
ኮምፒዩተሮች የኮምፒዩተሮቹን ፕሮግራም ከሚጽፉት ሰዎች የበለጠ ብልህ ሊሆኑ አይችሉም። ኮምፒዩተር ለቀረቡለት ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጠው የተሰጠውን መመሪያ በመጠቀም ብቻ ነው። የራሱ እውቀት ወይም የማሰብ ችሎታ የለውም። ኮምፒዩተሩ ከተሳሳተ ለስህተቱ ኃላፊ የሚሆኑት የኮምፒዩተሩን አሠራር ያስተካከሉት ወይም ፕሮግራሙን የጻፉት ሰዎች ናቸው። በትክክል ከሠራ ደግሞ ሊመሰገን የሚገባው ሰው ነው። ኮምፒዩተር አንዳንድ ሥራዎችን ከሰው በበለጠ ቅልጥፍናና ፍጥነት ሊሠራ ቢችልም መልስ ሊሰጥ የሚችልበት ዘዴ ካልተቀየሰለት ለጥያቄዎች መልስ መስጠት አይችልም።
ለምሳሌ ያህል የሰው ልጅ በ1950ዎቹና በ1960ዎቹ ዓመታት ለአንዳንድ ኮምፒዩተሮች ባዘጋጃቸው ፕሮግራሞች ረገድ አርቆ ተመልካችነት ጎድሎታል። በዚያ ጊዜ የኮምፒዩተሮችን መረጃ የመያዝ አቅም ከፍ ማድረግ ከፍተኛ ወጪ ይጠይቅ ስለነበረ መረጃ የመያዝ አቅማቸውን በቁጠባ ሊጠቀም የሚችልባቸውን መንገዶች ፈለገ። በኮምፒዩተር ውስጥ እያንዳንዱ ፊደል ወይም እያንዳንዱ ቁጥር የተወሰነ ቦታ ይይዛል። ስለዚህ ቀደም ያሉት ፕሮግራም ጸሐፊዎች ቀኖችን በሚያስገቡበት ጊዜ የሚይዙትን ቦታ መጠን ለመቀነስ ሲሉ ሁለቱን የመጀመሪያ የዓመተ ምህረት ቁጥሮች ማስቀረት ጀመሩ። ለምሳሌ ያህል 1965ን “65፣” 1985ን “85፣” 1999ን “99” ብቻ ተብሎ ሲጻፍ ቆይቷል። 1985ን አትሞ ማውጣት ሲያስፈልግ ከ“85” በፊት “19” መጨመር የሚያስቸግር ነገር አልነበረም። ባለፉት ጥቂት አሥርተ ዓመታት የተዘጋጁት በሚልዮን የሚቆጠሩ ፕሮግራሞች ይህን አጭር መንገድ በመጠቀም የተጻፉ ናቸው። ብዙ ፕሮግራመሮች ፕሮግራሞቻቸው በ21ኛው መቶ ዓመት መባቻ ላይም ሲሠራበት ይቆያል ብለው ስላላሰቡ ይህ ቀለል ያለ ዘዴ ከባድ ችግር ያስከትላል ብለው አላሰቡም ነበር። ይሁን እንጂ ይህን ዘዴ የሚጠቀሙ ፕሮግራሞች አሁንም በሥራ ላይ ያሉ ሲሆን 2000 ዓመትን “00” ብለው ይመዘግባሉ።
አንዳንድ ኮምፒዩተሮች “00” የሚለውን ቁጥር 1900 ብለው ይተረጉማሉ! ኮምፒዩተሩ በ1999 የሚጀምር የአምስት ዓመት ብድር ተከፍሎ የሚያልቀው በ1904 እንደሆነ አድርጎ ሲያሰላ በኮምፒዩተሩ ፕሮግራም ላይ ምን ዓይነት ቀውስ ሊፈጠር እንደሚችል ልትገምት ትችላለህ! በአንዳንድ ሁኔታዎች በዚህ ምክንያት በሚፈጠረው ስህተት የተነሣ ሙሉው የኮምፒዩተር ፕሮግራም ሥራውን ሊያቆም ሲችል የባሰ በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ ፕሮግራሙ ሙሉ በሙሉ ከአገልግሎት ውጭ ይሆናል።
ቶሮንቶ ስታር የተባለው ጋዜጣ “የማይክሮቺፕ መፈልሰፍ ከኤሌክትሪክ መፈልሰፍ ጋር ሊወዳደር የሚችል የኢንዱስትሪ አብዮት ያመጣልን ቢሆንም ፈልሳፊዎቹ ፈጽሞ ባላሰቡት መንገድ ለበለጠ አደጋ የተጋለጥን እንድንሆን አድርጎናል” ሲል ጽፏል። በተጨማሪም ስታር “1900ን ከ2000 ዓመት የመለየት ችሎታ የሌላቸው የኮምፒዩተር አውታሮችና ማይክሮቺፖች በመላው ዓለም ይገኛሉ። እነዚህ አውታሮች ተለይተው ካልታወቁና ካልተለወጡ በመላው ዓለም ላይ ከፍተኛ ቀውስ ሊፈጠር ይችላል” ብሏል።
አንዳንድ ጠበብት ምን ይተነብያሉ?
የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት አባል የሆኑት የዩታው ሮበርት በነት “እኔን ጨምሮ ሁሉም ሰው ምን ያህል ከባድ ችግር ሊፈጠር እንደሚችል የየራሱን ግምታዊ አስተያየት እየሰጠ ነው። የሚደርሰውን ችግር በትክክል ማወቅ የሚቻለው ከ2000 ዓመት መባቻ ወይም ከመባቻው ከአንድ ወይም ከሁለት ሳምንት በኋላ ነው” ብለዋል። አንድ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት አማካሪ ደግሞ “እንዲያውም በኢኮኖሚውም ሆነ በሰዎች ሕይወት ላይ ከፍተኛ ችግር ሊያስከትሉ የሚችሉ ሁኔታዎች ይመጣሉ . . . ብሎ ለመናገር የሚያስደፍሩ ምክንያቶች አሉ” ብለዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ማዕከላዊ መረጃ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ “በኤሌክትሪክ ማሠራጫ መሣሪያዎች ላይ፣ በቴሌኮሙኒኬሽን አውታሮች ላይና በባንክ አገልግሎቶች ላይ ከፍተኛ ምስቅልቅል ይፈጠራል ብለን እንሰጋለን” ብለዋል። ከዓለም ዙሪያ የተገኙ ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት በአሁኑ ጊዜ እንኳን አንዳንድ ኮምፒዩተሮች እስከ 2000 ዓመትና ከዚያ በኋላ ያሉ ዓመታትን ሲመዘግቡ ችግር አጋጥሟቸዋል።
ዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ወርልድ ሪፖርት እንደዘገበው “በሆስፒታሎችና በጤና ተንከባካቢ ድርጅቶች የሚገኙ የበሽተኞች ሂሣብ ማስከፈያና የኢንሹራንስ መዝገቦች የችግሩ ገፈት ቀማሾች ስለሚሆኑ በጤናው ክፍለ ኢኮኖሚ ብዙ ችግር እንደሚያጋጥም ጠበብት ተንብየዋል። የበሽተኞች መከታተያ መሣሪያዎችን ጨምሮ አንዳንድ የሕክምና መሣሪያዎች ከአገልግሎት ውጭ የመሆን አደጋ ተጋርጦባቸዋል። ብዙ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሰጭ ድርጅቶች ችግሩን ለመፍታት የተንቀሳቀሱት ብዙ ዘግይተው ስለሆነ በአንዳንድ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ መኖሩ አይቀርም።” አንድ የካናዳ ጋዜጣም ይህንኑ ስጋት በማስተጋባት “ሆስፒታሎቻችንና የሕክምና ቴክኖሎጂዎቻችን በማይክሮቺፕ ላይ የተመኩ ናቸው። ስለዚህም የኮምፒዩተር አውታሮች እክል ሲደርስባቸው ሰዎች ሊሞቱ ይችላሉ” ብሏል። አንድ የሆስፒታል አስተዳዳሪ “በሥራችን ባሕርይ ምክንያት ከማንም ይበልጥ የምንጎዳው እኛ ነን። ሌሎቹ ኢንዱስትሪዎች የሞትና የሽረት ችግር ላይደርስባቸው ይችላል” በማለት ሐዘናቸውን ገልጸዋል።
ይበልጥ ጽልመተኛ የሆኑ የኮምፒዩተር ባለሞያዎች የአክሲዮን ገበያዎች እንደሚወድቁ፣ አነስተኛ የንግድ ድርጅቶች እንደሚዘጉና በሁኔታው የተደናገጡ ገንዘብ አስቀማጮች ባንኮችን እንደሚያስጨንቁ ይተነብያሉ። በዩናይትድ ስቴትስ ምክትል የመከላከያ ሚኒስቴሩ በኮምፒዩተሮች ላይ የሚደርሰውን ዓለም አቀፍ ቀውስ ኤል ኒኞ ከተባለው የአየር ሁኔታ መዛባት ጋር በማመሳሰል “ፈጽሞ ያልጠበቅነው ከባድ ችግር መድረሱ አይቀርም ብዬ አምናለሁ” ብለዋል።
የአሜሪካ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት “ኮምፒዩተሮች ከጥር 1, 2000 በፊት ካልተስተካከሉ በራሽያ በሚገኙ የንግድ ድርጅቶች ላይ ትልቅ መዓት ይወርዳል” ብለዋል። የሮይተር ዜና ድርጅት “የጀርመን ኩባንያዎች በሁለተኛው ሺህ ዓመት በሚደርሰው የኮምፒዩተር ቦምብ ፍንዳታ ረገድ ገና ከእንቅልፋቸው አልነቁም። የፍንዳታው ፍንጣሪ መላውን አውሮፓ ያዳርሳል” ብሏል። የአንድ ምርምር ተቋም ዳይሬክተር “ስለ ኦስትሪያ፣ ስለ ስዊዘርላንድ፣ ስለ ስፔይን፣ ስለ ፈረንሳይና ስለ ኢጣሊያም ተመሳሳይ አስተያየት መስጠት ይቻላል” ብለዋል።
ባንኮክ ፖስትም ታይላንድ የሚያጋጥማትን የኮምፒዩተር ችግር ጠቁሟል። “በአካባቢው የሚገኙ ብሔራዊ የስታትስቲክስ ቢሮዎች ከባለ ሁለት ፈርጅ ችግር ጋር ተፋጥጠዋል። 2000 ዓመት በኮምፒዩተሮቻቸው ላይ የሚያመጣውን ችግር የማስወገድና የተባበሩት መንግሥታት መረጃ አገልግሎት ባለው መሠረት አዲስ የሕዝብ ቆጠራ ሥርዓት የመዘርጋት ችግር ተጋርጦባቸዋል።” አውስትራሊያ፣ ቻይና፣ እንግሊዝ፣ ሆንግ ኮንግ፣ አየርላንድ፣ ጃፓንና ኒው ዚላንድም ተመሳሳይ ችግር ተደቅኖባቸዋል። በእርግጥም ገና መፍትሔ ያላገኘ ዓለም አቀፍ ችግር ነው።
የሚጠይቀው ከፍተኛ ወጪ
አንዳንድ ጠበብት የኮምፒዩተሮቹን ቀውስ ለማስተካከል በጣም ብዙ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ ገምተዋል። ለምሳሌ፣ የዩ ኤስ የአስተዳደርና የበጀት ቢሮ የፌደራል መንግሥቱን ኮምፒዩተሮች ብቻ ለማስተካከል 4.7 ቢልዮን ዶላር እንደሚጠይቅ ገምቷል። አንድ የጠበብት ቡድን የፌደራል መንግሥቱን ኮምፒዩተሮች ለማስተካከል ይበልጥ ተጨባጭነት የሚኖረው ግምት 30 ቢልዮን ዶላር ነው ብሏል። በመላው ዓለምስ ምን ያህል ወጪ ይጠይቅ ይሆን? ኒው ዮርክ ፖስት የተባለው ጋዜጣ እንደዘገበው “ሶፍት ዌሮችን ለማስተካከል 600 ቢልዮን ዶላር እንደሚጠይቅና አንዳንድ ማስተካከያዎች ባለመሳካታቸው ምክንያት ለሚደርሰው የካሣ ጥያቄ 1 ትሪልዮን ዶላር ወጪ እንደሚደረግ ይገመታል።” ሌላ የጠበብት ቡድን “ለጥገና፣ ለካሣ ጥያቄና ሥራ በመፍታት ለሚባክነው ጊዜ የሚከፈለው ወጪ 4 ትሪልዮን ዶላር ሊደርስ እንደሚችል” ገምቷል። ኒው ዮርክ ፖስት “በ2000 ዓመት የሚደርስብን ችግር በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ አጋጥሞ የማያውቅ ከፍተኛ ኪሣራ የሚያስከትል ይሆናል” ሲል ጽፏል። ሌላው ሪፖርት ደግሞ “የሰው ልጅ እስከዛሬ ካጋጠሙት በሙሉ በግዙፍነቱ፣ በአደገኛነቱና በአክሳሪነቱ ተወዳዳሪ የሌለው ፕሮጀክት ሳይሆን አይቀርም” ብሏል።
የሚሰጡት አስተያየቶች ይለያያሉ
ችግሩ አንተን በግልህ እንዴት ይነካህ ይሆን? ይህ የሚመካው በምትኖርበት አገር ሁኔታና ከአንተ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ድርጅቶች በሚወስዱት የማስተካከያ ጥረት ላይ ይሆናል። ስለሆነም ምንም ዓይነት ችግር ላያጋጥምህ ወይም ከቀላል ብስጭት እስከ ከባድ ችግር የሚለያይ ሁኔታ ሊገጥምህ ይችላል። በተለይ ከጥር 1, 2000 በኋላ ባሉት የመጀመሪያ ሳምንታት እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሊከሰት ይችላል። በጣም የሚያሳስብህ ሁኔታ ካለ፣ ወይም እንደ ጤንነት መከታተያ የመሰለ ልዩ መሣሪያ ተጠቃሚ ከሆንክ፣ አገልግሎት የሚሰጥህን የንግድ ድርጅት ወይም ተቋም ማነጋገርና በ2000 ምዕተ ዓመት መባቻ በምትጠቀምበት መሣሪያ ወይም በምታገኘው አገልግሎት ላይ ምን ሁኔታ ሊከሰት እንደሚችል ማጣራት ያስፈልግሃል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በ2000 ስለሚከሰተው ችግር ብዙ ተለፍፏል። አንዳንዶች ችግሩ በጣም ከባድ ነው ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ ችግሩ ከሚገባው በላይ ተጋንኗል ይላሉ። አንዳንዶች ባንኮች ጨርሰው ይንኮታኮታሉ ሲሉ የባንክ ጠበብት ደግሞ 2000 ከመድረሱ በፊት ችግሩ በአብዛኛው መቀረፉ አይቀርም ይላሉ። የዩናይትድ ስቴትስ ፌደራል ኮምኒኬሽን ኮሚሽን ኃላፊ “መላው የቴሌፎን አውታር ምስቅልቅሉ ይወጣል ብሎ የሚያምን ሰው የለም” ብለዋል። ይሁን እንጂ በምዕተ ዓመቱ መባቻ ላይ የቴሌፎን ችግሮች መከሰታቸው የማይቀር መሆኑን ቢያምኑም ችግሮቹ ከማናደድ የማያልፉ ቀላል ችግሮች እንደሚሆኑ ተናግረዋል። ብዙ ድርጅቶች የሚከተለውን ለውጥ ለማወቅ በቤተ ሙከራዎቻቸው በርካታ ምርምር እያደረጉ ነው። ይህም ብዙ ችግሮችን ከወዲሁ ለመቅጨት ያስችል ይሆናል። ቢሆንም መላው ዓለም የ2000 ዓመቱ ችግር ምን ያህል ከባድ እንደሆነ የሚያውቀው ቀኑ ሲደርስ ብቻ ይሆናል።