የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g99 5/8 ገጽ 17-19
  • ሐሜት ይሄን ያህል ጎጂ ነውን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሐሜት ይሄን ያህል ጎጂ ነውን?
  • ንቁ!—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ለሐሜት የሚጋብዘን ምንድን ነው?
  • ጎጂ ሐሜት የሚያስከትለው መዘዝ
  • ከጎጂ ሐሜት መቆጠብ
  • ማዳመጥ—የሐሜት ሌላኛው ገጽታ
  • ሐሜቱን እንዴት ማስቆም እችላለሁ?
    ንቁ!—2007
  • ሐሜት መጥፎ የሆነው ለምንድን ነው?
    ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2
  • ሰዎች ስለ እኔ የሚያወሩት ለምንድን ነው?
    የወጣቶች ጥያቄ
ንቁ!—1999
g99 5/8 ገጽ 17-19

ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች ...

ሐሜት ይሄን ያህል ጎጂ ነውን?

“በምማርበት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንደ ወረርሽኝ የተዛመተው አደገኛ ዕፅ፣ የጦር መሣሪያ ወይም ድብድብ ሳይሆን ሐሜት ነው። የእኛ ትልቁ ችግር ይህ ነው።”—የ16 ዓመቷ ሚሼልa

አንዳንዶች ደስ የሚል ነገር ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ የለም አደገኛ መርዝ ነው ይላሉ። አብዛኛውን ጊዜ በመጽሔትና በጋዜጣ አምዶች እንዲሁም በቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ውስጥ አይጠፋም። በተጨማሪም የወሬ ቅመም ሆኖ ያገለግላል። ለመሆኑ ይህ ምንድን ነው? ስለ ሌሎች ሰዎችና ስለ ግል ጉዳዮቻቸው የሚደረግ ተራ ጭውውት ሲሆን በሌላ አባባል ሐሜት ተብሎ ይታወቃል።

“ሰማህ እንዴ?” የሚሉትን ቃላት ያክል የሰዎችን ትኩረት በቅጽበት የሚስብ አነጋገር ያለ አይመስልም። እነዚህን ቃላት ተከትሎ የሚወራው ወሬ እውነት ወይም ልብ ወለድ አለዚያም ሁለቱም የተጨማመረበት ሊሆን ይችላል። ሁኔታው ምንም ይሁን ምን በሐሜት የመካፈሉ ፈተና ኃይለኛ ሊሆን ይችላል። የ17 ዓመቷ ሎሪ “ወደድንም ጠላን የሌሎች ሰዎችን የግል ጉዳይ ለማወቅ መጓጓታችን አይቀርም” ስትል ተናግራለች። “የሆነ ትኩስ ወሬ ስትሰሙ ሮጣችሁ ለጓደኞቻችሁ እንደምትነግሩ የታወቀ ነው።”

ለሐሜት የሚጋብዘን ምንድን ነው?

ሐሜት ይሄን ያህል ትኩረታችንን የሚስብ የሆነው ለምንድን ነው? አንደኛው ምክንያት ሰዎች በማኅበራዊ ኑሮ የተሳሰሩ በመሆኑ ነው። በሌላ አነጋገር ሰዎች ስለ ሌሎች የማወቅ ፍላጎት አላቸው። በዚህም የተነሳ ብዙውን ጊዜ ከሌሎች ጋር ስናወራ ርዕሳችን መስመሩን ይቀይርና ጓደኞቻችንና የምናውቃቸው ሰዎች በቅርቡ ስላከናወኗቸው ወይም ስለገጠሟቸው ነገሮች መነጋገር እንጀምራለን።

ታዲያ ይህ ስህተት ነውን? ሁልጊዜ ስህተት ነው ማለት አይቻልም። ብዙውን ጊዜ ተራ የሆኑ ጭውውቶች ማን እንደሚያገባ፣ ማን ልጅ እንደወለደ፣ ማን እንደታመመና እነዚህን የመሰሉ ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን ለማወቅ ይረዳሉ። ሌላው ቀርቶ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች የእምነት ባልደረቦቻቸው ስለገጠሟቸው አዳዲስ ጉዳዮች ይነጋገሩ ነበር። (ኤፌሶን 6:21, 22፤ ቆላስይስ 4:8, 9) በእርግጥም ስለ ጓደኞቻችንና ስለ ምናውቃቸው ሰዎች የምናደርገው ተራ ጭውውት እርስ በርሳችን ሐሳብ የምንለዋወጥበትና ያለንን ጤናማ ዝምድና ጠብቀን የምናቆይበት ዋነኛ መንገድ ነው።

ጎጂ ሐሜት የሚያስከትለው መዘዝ

ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ስለ ሌሎች ሰዎች የግል ሕይወት የሚያወሩት ከአሳቢነት በመነጨ ስሜት ላይሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል የ18 ዓመቷ ዲየድራ “ሰዎች ተወዳጅነት ለማግኘት ሲሉ ያማሉ። አንድ ነገር ሲነገራቸው ከዚያ የተሻለ አንድ ታሪክ በማወቃቸው [ተወዳጅነት] እንደሚያተርፉ ሆኖ ይሰማቸዋል” ብላለች። ሌላው ቀርቶ ሐሜተኛው የሌሎችን ቀልብ ለመሳብ ያለው ፍላጎት ሐቁን እንዲያጣምም ሊገፋፋው ይችላል። “ታሪኩን የምታውቅ ከሆነ በፈለግከው መንገድ ቀያይረህ ልታቀርበው ትችላለህ” በማለት የ17 ዓመቷ ራሄል ተናግራለች። “የራስህን መቼት ፈጥረህ ታሪኩን እንደፈለግህ ልትቀባባው ትችላለህ ማለት ነው።”

አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ብድር ለመመለስ ሲሉ ከእውነት የራቀ ሐሜት ይነዛሉ። “በአንድ ወቅት በጓደኛዬ ላይ የሐሰት ወሬ ነዛሁ” በማለት የ12 ዓመቷ ኤሚ ተናግራለች። “ይህን ያደረግኩት ስለ እኔ የሆነ ነገር ተናግራ ስለነበረ ነው።” ውጤቱስ ምን ሆነ? “መጀመሪያ ላይ ሠራሁላት ብዬ አስቤ ነበር።” ይሁን እንጂ ኤሚ ንግግሯን በመቀጠል “ወሬው ወዲያው ከቁጥጥር ውጪ በመውጣቱ ምነው መጀመሪያ ላይ አፌን ዘግቼ ቢሆን ኖሮ ብዬ እስክቆጭ ድረስ በጣም ረበሸኝ” ስትል ገልጻለች።

አንዲት የአእምሮ ጤና ባለሙያ እንደተናገሩት ሐሜት “እንደ ሰደድ እሳት በፍጥነት ሊዛመት” ይችላል። (ከያዕቆብ 3:5, 6 ጋር አወዳድር።) ይህ በሚከሰትበት ጊዜ ውጤቱ ጎጂ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል በምሥጢር ሊያዝ የሚገባው አንድ ጉዳይ ወደ ሁሉም ጆሮ ቢደርስስ? ወይም ሐሜቱ ውሸት ቢሆንና ወሬውን በማሰራጨትህ ምክንያት የአንድን ሰው ጥሩ ስም ብታጎድፍስ? የ12 ዓመቱ ቢል “ከጓደኞቼ አንዱ አደገኛ ዕፅ ይወስዳል ብሎ የሐሰት ወሬ ነዛብኝ። ይህ ስሜቴን በጣም ጎዳው” ሲል ተናግሯል።

ከጎጂ ሐሜት መቆጠብ

መጽሐፍ ቅዱስ “ሞትና ሕይወት በምላስ እጅ ናቸው” ሲል የሚገልጸው ያለ ምክንያት አይደለም። (ምሳሌ 18:21) አዎን፣ የምንናገረው ቃል ለልማት አለዚያም ለጥፋት እንደሚውል መሣሪያ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል። የሚያሳዝነው ግን በዛሬው ጊዜ ብዙዎች ምላሳቸውን የሚጠቀሙበት ለጥፋት መሆኑ ነው። መዝሙራዊው ዳዊት “እነርሱ ምላሳቸውን እንደ ሰይፍ ይስላሉ፤ እጅግ የከፋ ቃላትን እንደ ፍላጻ አነጣጥረው ይወረውራሉ። የሐሰት ወሬ በንጹሕ ሰው ላይ ያሰራጫሉ” ብሎ እንደገለጻቸው ዓይነት ሰዎች ናቸው።—መዝሙር 64:2-4 የ1980 ትርጉም

መጽሐፍ ቅዱስ “ውሸተኛ ከንፈር በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው” በማለት ስለሚናገር አምላክን ለማስደሰት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው የሐሰት ወሬዎችን መንዛት አይገባውም። (ምሳሌ 12:22) ሆን ብሎ እውነት ያልሆነ ነገር ፈጥሮ ማውራት ወይም ከአንዱ ወደ ሌላ ማስተላለፍ መዋሸት ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ ክርስቲያኖች ‘ውሸትን ማስወገድና ከባልንጀሮቻቸው ጋር እውነት መነጋገር’ እንዳለባቸው ይገልጻል።—ኤፌሶን 4:25

ስለዚህ ስለ አንድ ሰው ከመናገርህ በፊት ‘ሐቁን በትክክል አውቃለሁ? የምናገረው ነገር ሌሎች ለሰውየው ያላቸው ግምት ዝቅ እንዲል የሚያደርግ ይሆን? ከሆነ ይህን ነገር እንድናገር ያነሳሳኝ ምንድን ነው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ነገሩ እውነት መሆኑ ብቻ ወሬውን ለመንዛት ምክንያት እንደማይሆን አትዘንጋ። በተለይ ደግሞ የአንድን ሰው ስም የሚያጎድፍ ከሆነ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።

ሌላው መነሳት ያለበት ጥያቄ ‘ሌሎችን የማማ ከሆነ ምን ዓይነት ስም ነው የማተርፈው?’ የሚለው ነው። አዎን፣ ሌሎችን ማማትህ ስለ አንተም ማንነት የሚያስተላልፈው መልእክት ይኖራል። ለምሳሌ ያህል ክሪስተን ስትናገር “ስለ ሌሎች ሰዎች በማውራት ብዙ ጊዜ የምታጠፋ ከሆነ የራስህ ሕይወት አያስደስትህም ማለት ነው” ብላለች። ሊሳ፣ ሐሜተኛ የሚል ስም ማትረፏ የቅርብ ጓደኛዋን አመኔታ እንድታጣ አድርጓት እንደነበር ታስታውሳለች። “ዳግመኛ እኔን ለማመን እስከ መቸገር ደርሳ ነበር” ስትል ተናግራለች። “እንደገና እምነት ልትጥልብኝ የምትችል ሰው ሆኜ መገኘት ነበረብኝ። ይህ በጣም የሚያሳዝን ነበር።”

በሐሜተኝነት የምትታወቅ ከሆነ ሰዎች ልትጎዳቸው የምትችል ዓይነት ሰው እንደሆንክ አድርገው በማሰብ ሊርቁህ ይችላሉ። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ዘዋሪ ሐሜተኛ ምሥጢርን ይገልጣል፤ ከንፈሩን የሚያሞጠሙጥ ሰውን አትገናኘው” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 20:19) ይሁን እንጂ አንድም ቃል ሳትተነፍስ ጎጂ ሐሜት እንዲዛመት አስተዋጽዖ ልታበረክት እንደምትችል ታውቃለህ?

ማዳመጥ—የሐሜት ሌላኛው ገጽታ

ለሐሜት ቢያንስ ሁለት ሰዎች ያስፈልጋሉ። የሚናገርና የሚያዳምጥ። የአዳማጩ ተጠያቂነት ከተናጋሪው ያነሰ ቢመስልም መጽሐፍ ቅዱስ በጉዳዩ ላይ ያለው አመለካከት ግን ከዚህ የተለየ ነው። ምሳሌ 17:4 ላይ እንዲህ እናነባለን:- “ክፉ ሰው የበደለኛን ከንፈር ይሰማል፤ ሐሰተኛም ወደ ተንኮለኛ ምላስ ያደምጣል።” ስለዚህ ሐሜት የሚያዳምጥ ሰውም ከባድ ኃላፊነት አለበት። ስቴፈን ኤም ዋይለን የተባሉ ደራሲ “ሐሜት ማዳመጥ ከማውራት ይበልጥ ጎጂ የሚሆንባቸው መንገዶች አሉ” ሲሉ ገልጸዋል። ይህ የሆነበት ምክንያት ምንድን ነው? ዋይለን “በጉጉት ማዳመጣችሁ ተናጋሪው መናገሩን እንዲቀጥል ያበረታታዋል” በማለት አክለው ተናግረዋል።

ታዲያ ጎጂ ሐሜት ወደ ጆሮህ በሚደርስበት ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? ራስህን ሳታመጻድቅ በቀላሉ እንዲህ ልትል ትችላለህ:- ‘ወሬያችንን ብንቀይርስ’ ወይም ‘ስለዚህ ጉዳይ ማውራት ደስ አይለኝም። ደግሞም በሌለችበት ስለ እሷ ማውራቱ አስፈላጊ አይደለም።’

ይሁን እንጂ በውይይታቸው ለመካፈል ፈቃደኛ ባለመሆንህ ምክንያት ሰዎች ቢርቁህስ? በአንድ በኩል ይህ ሁኔታ እንደ ጥበቃ ሆኖ ሊያገለግልህ ይችላል። እንዴት? ከአንተ ጋር በሚሆንበት ጊዜ ሌሎችን የሚያማ ሰው አንተንም ከሌሎች ጋር ሆኖ ሊያማ እንደሚችል አስታውስ። ስለዚህ ሌሎችን በነገር ከማይቦጭቁ ወጣቶች ወይም ትላልቅ ሰዎች ጋር በመቀራረብ ራስህን ከብዙ ሃዘን ልትጠብቅ ትችላለህ። ዋይለን እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “ሌሎችን ባለማማታችሁ ምክንያት በሕይወታችሁ ላይ ሊደርስ የሚችልን ችግር ከማስቀረታችሁ ውጭ ምንም ነገር እንደማይቀርባችሁ ወዲያው ትገነዘባላችሁ። እምነት የሚጣልበት ሰው በመሆን በሰዎች ዘንድ ጥሩ ስም ስለምታተርፉ መጨረሻችሁ ያማረ ይሆናል።”

ከሁሉም ይበልጥ ግን በአምላክ ዘንድ ጥሩ ስም ታተርፋለህ። ስለ ሌሎች የምንናገረው ነገር በአምላክ ዘንድ ለውጥ ያመጣል። ኢየሱስ ክርስቶስ “ሰዎች ስለሚናገሩት ስለ ከንቱ ነገር ሁሉ በፍርድ ቀን መልስ ይሰጡበታል፤ ከቃልህ የተነሣ ትጸድቃለህና ከቃልህም የተነሣ ትኮነናለህ” በማለት አስጠንቅቋል።—ማቴዎስ 12:36, 37

እንግዲያው ሐዋርያው ጳውሎስ “በጸጥታ ለመኖር [ተጣጣሩ]፣ የራሳችሁን ጉዳይ [አስቡ]” በማለት የሰጠውን ምክር መከተሉ ጥበብ ነው። (1 ተሰሎንቄ 4:11 የ1980 ትርጉም) እንዲህ ማድረግህ ከሌሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖርህና በአምላክ ፊትም ጥሩ አቋም እንድትይዝ ይረዳሃል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a አንዳንዶቹ ስሞች ተለውጠዋል።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

“የዓለማችን ትልቁ የሐሜት ሞተር”

ይህን ታውቅ ኖሯል? ኢ-ሜል ወደ መድረክ ብቅ ካለበት ጊዜ ጀምሮ ሐሜት በዘመናዊው ቴክኖሎጂ ዓለም ውስጥም ሰርጿል። እንዲያውም ሴት ጎደን የተባሉ ደራሲ ኢ-ሜልን “የዓለማችን ትልቁ የሐሜት ሞተር” ሲሉ ጠርተውታል። ኢ-ሜል የሚሰጠውን ጥቅም ባይክዱም የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል:- “አንድ ሰው አንድ ሐቅ የሆነ ነገር ወይም የተዛባ መረጃ ሊያቀርብና ወዲያውኑ በሺህ ለሚቆጠሩ ሰዎች ሊዳረስ ይችላል።”

ኢ-ሜል በቅጽበት ከፍተኛ ቁጥር ላላቸው ሰዎች ሊተላለፍ ይችላል። ጎደን እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “ኢ-ሜል ክብደት ያለውንና በሚገባ የታሰበበትን መልእክት በስልክ መስመር አማካኝነት ከፍጥነት ጋር አቀናጅቶ ሊያስተላልፍ የሚችል የመጀመሪያው አዲስ የመገናኛ ዘዴ ነው።” እንግዲያው ኢ-ሜል በምትልክበት ጊዜ የመልእክትህን ዓላማ ግልጽ ማድረግ ይኖርብሃል። በተጨማሪም በተቻለ መጠን ያልተረጋገጠ መረጃ ለጓደኞችህ አታስተላልፍ።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ከአንተ ጋር በሚሆንበት ጊዜ ሌሎችን የሚያማ ሰው ... አንተንም ከሌሎች ጋር ሆኖ ማማቱ አይቀርም

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ