ኬሚካላዊ ፀረ ተባይ መድኃኒቶች ተባዮችን በመግደል ብቻ አይወሰኑም
በብራዚል የሚገኝ የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው
አርሶ አደር ዶሚንጎስ ዶስ ሳንቶስ በደቡባዊ ብራዚል በሚገኘው እርሻው የበቀለውን የካሳቫ ማሳ ተመልክቶ “በጣም ግሩም ሆኗል!” አለ። ደስ የሚሰኝበት በቂ ምክንያት ነበረው። የተክሎቹ ቅጠሎች አንድ ተባይ እንኳን አርፎባቸው የሚያውቅ አይመስሉም። እንዲህ ሊሳካለት የቻለው ኬሚካላዊ ፀረ ተባይ መድኃኒት ረጭቶ ነው? አይደለም። “አምናና ዘንድሮ አንዲት ጠብታ ፀረ ተባይ እንኳን መግዛት አላስፈለገኝም” ይላል ዶሚንጎስ።
ዶሚንጎስ ሰብላቸውን ከተባዮች ለመከላከል ኬሚካላዊ ፀረ ተባይ መድኃኒቶችን ለመጠቀም ከሚያመነቱ በርካታ ገበሬዎች አንዱ ነው።a እነዚህ ገበሬዎች የኬሚካል ፀረ ተባዮችን ግልጋሎት ፈጽሞ በሚያስቀሩ ወይም ቢያንስ በሚቀንሱ ዘዴዎች ይጠቀማሉ። “ምን ዘዴዎች አሉ?” በማለት ሳኦ ፓውሎ አጠገብ በሚገኝ የብርቱካን እርሻ ምርምር የሚያካሂዱትን ሳንድሮ ሙለር የተባሉ የእርሻ ተመራማሪ ጠየቅኩ። “ገበሬዎች ፀረ ተባይ መድኃኒት መርጫዎችን መጠቀም የጠሉት ምን ምክንያት ቢኖራቸው ነው?”
የፀረ ተባይ መድኃኒቶች ኡደት
ሳንድሮ፣ ኬሚካላዊ ፀረ ተባዮች ከሚያስከትሏቸው ጉዳቶች አንዱን እንድገነዘብ ለመርዳት እንዲህ በማለት ቀጠሉ:- “አንድ የፖሊሶች ጓድ የባንክ ዘራፊዎችን ለመያዝ እያባረረ ነው እንበል። ዘራፊዎቹ ለማምለጥ ሲሉ አንድ የመሥሪያ ቤት ሕንጻ ውስጥ ገቡ። ከመሥሪያ ቤቱ ሰዎች ጋር ተቀላቅለው ስለተሰወሩባቸው ፖሊሶቹ ሄሊኮፕተር እንዲላክላቸው ጠይቀው በሕንጻው ላይ የጋዝ ቦምብ እንዲጣል አደረጉ። ጋዙ ዘራፊዎቹን ብቻ ሳይሆን ምንም ወንጀል የሌለባቸውን የመሥሪያ ቤቱን ሠራተኞችና የሕንጻውን የጥበቃ ሠራተኞች ይገድላል። አንድ ገበሬ በሰብሉ ላይ ፀረ ተባይ መድኃኒቶችን ደጋግሞ በሚረጭበት ጊዜ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ሁኔታ ይፈጸማል። ጎጂዎቹን ተባዮች፣ ማለትም ዘራፊዎቹን በሚገድልበት ጊዜ ጠቃሚዎቹን፣ ማለትም የጥበቃ ሠራተኞቹን ጭምር ይገድላል።”
“ቢሆንም ቢያንስ ሰብሉ ከጥፋት ድኗል” ስል መለስኩላቸው። ሳንድሮ በጅምላ የሚረጩ ፀረ ተባይ መድኃኒቶች ጎጂ የሆነ ኡደት እንደሚያስከትሉ ገለጹልኝ። እንዴት? አንዳንድ ተባዮች አንዳንድ ፀረ ተባይ መድኃኒቶችን የመቋቋም አቅም ስለሚኖራቸው በመድኃኒቱ ርጭት ሳይሞቱ ይቀራሉ። ከዚያ በኋላ የገበሬው ርጭት ምሥጋና ይግባውና ከዚህ ተመለሱ የሚሏቸው ‘የጥበቃ ሠራተኞች’ ወይም ጠቃሚ ሶስት አፅቄዎች በሌሉበት ሙሉውን ማሳ በቁጥጥራቸው ሥር ያደርጋሉ።
እነዚህ ፀረ ተባይ መድኃኒቱን የመቋቋም አቅም ያላቸው ተባዮች ምግብ እንደልብ በሚያገኙበትና የተፈጥሮ ጠላት በሌለበት ሁኔታ በፍጥነት ስለሚራቡ ገበሬው በድጋሚ፣ ምናልባትም ከበፊቱ የበለጠ ኃይል ያለው ፀረ ተባይ መድኃኒት ለመርጨት ይገደዳል። በደቡብ አሜሪካ በሚገኙ አንዳንድ ባቄላ አብቃይ አካባቢዎች ገበሬዎች በየሳምንቱ መድኃኒት ለመርጨት ተገድደዋል። የዚህ ኡደት የመጨረሻ ውጤት ምን ይሆናል? አንድ ገበሬ “ፀረ ተባይ መድኃኒት ከዘራህ መርዝ ማጨድህ አይቀርም” ብሏል።
በፀረ ተባይ መድኃኒት መጠቀም—የተሻለ አማራጭ ነውን?
ተባዮችን በመርዝ የሚገድል ሰው ራሱንም መመረዙ እንደማይቀር ጥናቶች አረጋግጠዋል። ጌ ሩራል የተባለው መጽሔት እንደዘገበው በብራዚል ብቻ በየዓመቱ 700,000 የሚያክሉ ሰዎች በፀረ ተባይ መድኃኒቶች ይመረዛሉ። በአማካይ በየ45 ሰኮንዶች አንድ ሰው ይመረዛል ማለት ነው! በመላው ዓለም በየዓመቱ 220,000 ሰዎች ለመርዘኛ ፀረ ተባይ መድኃኒቶች በመጋለጣቸው ምክንያት እንደሚሞቱ የዓለም ጤና ድርጅት ዘግቧል። ከዚህ በተጨማሪ ፀረ ተባይ መድኃኒቶች በአካባቢያችን ላይ በጣም ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላሉ።
አንዳንድ ሰዎች ፀረ ተባይ መድኃኒቶችን መጠቀም በርካታ ችግሮችን ከመጋበዝ በስተቀር ምንም ፋይዳ እንደሌለው ቢያስቡም ተባዮቹ ከሚያስከትሉት ጉዳት አንጻር ሲታይ የተሻለ አማራጭ ነው ብለው የሚያስቡም አሉ። ይህን አባባላቸውን ለመደገፍ እንደሚከተለው ያለ የመከራከሪያ ሐሳብ ያቀርባሉ:- በፀረ ተባዮች ተጠቅሞ በቂ ምግብ ከማግኘትና በፀረ ተባዮች መጠቀም አቁሞ ከመራብ አንዱን መምረጥ የግድ ነው። በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ የመጣ ሲሆን ለእርሻ የሚውለው ለም መሬት ግን እያነሰ ሄዷል። ምድር አቀፍ ረሐብ እንዳይከሰት ከተፈለገ ሰብሎችን የሚያጠፉ ጎጂ ነፍሳትን መከላከል ያስፈልጋል።
ተባዮች የሚያስከትሉት ጉዳት ቀላል እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ደግነቱ ግን ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ በርካታ ገበሬዎች ሰብሎችን በመርዘኛ ፀረ ተባዮች ከመርጨት የተሻለ አማራጭ መኖሩን እየተገነዘቡ ነው። ይህ ዘዴ ኢንተግሬትድ ፔስት ማኔጅመንት (የተቀናጀ ተባይ መከላከያ) ወይም አይ ፒ ኤም ይባላል።
አይ ፒ ኤም—ጥሩ አማራጭ
በፒራሲካባ ከተማ የሳኦ ፓውሎ ዩኒቨርሲቲ የኤንትሞሎጂ መምሪያ ኃላፊና የተፈጥሮ ተባይ መከላከያ ዘዴ እውቅ ተመራማሪ ለሆኑት ለፕሮፌሰር ኤቮንዮ በርቲ ፊልሆ “አይ ፒ ኤም ምንድን ነው?” የሚል ጥያቄ አቀረብኩላቸው። ፕሮፌሰር በርቲ የአይ ፒ ኤም ዋነኛ ግብ የፀረ ተባይ መድኃኒቶችን አጠቃቀም በተቻለ መጠን መቀነስና የተወሰኑ ጎጂ ተባዮችን ብቻ ነጥለው በሚገድሉ ፀረ ተባይ መድኃኒቶች መጠቀም ነው ሲሉ ገልጸዋል። በዚህ ዓይነት የሚካሄደው ቁጥብ ርጭት ተፈጥሮአዊ በሆኑ የተባይ መቆጣጠሪያ ዘዴዎች ይታገዛል።
እንደነዚህ ካሉት ዘዴዎች አንዱ ሰብሎችን ማፈራረቅ ነው። ለምሳሌ ያህል አንድ ገበሬ በየዓመቱ በቆሎና ባቄላ እያፈራረቀ ይዘራል እንበል። በቆሎ የሚወዱና ባቄላ ግን የማይጥማቸው ተባዮች ተርበው ያልቃሉ ወይም በቆሎ ወደሚያገኙበት ሌላ እርሻ ለመሄድ ይገደዳሉ። በሚቀጥለው የአዝመራ ዓመት በቆሎ ሲዘራ ተባዮቹ ቢያንስ ለጊዜው በዚያ ማሳ ላይ አይኖሩም። በቆሎ ወዳዶቹ ተባዮች በሚመለሱበት ጊዜ ሌላ ዓይነት ሰብል በቅሎ ስለሚቆያቸው ወዲያው ጓዛቸውን ጠቅልለው ለመመለስ ይገደዳሉ።
ሌላው የአይ ፒ ኤም ዘርፍ ደግሞ ባዮሎጂያዊ ቁጥጥር ነው። በዚህ ዘዴ ገበሬዎች የተባዮች የተፈጥሮ ጠላቶች በሆኑ ነፍሳት፣ ባክቴሪያዎች፣ ቫይረሶችና ፈንገሶች ይገለገላሉ። ለምሳሌ ያህል ብራዚላውያን ተመራማሪዎች በርካታ አባ ጨጓሬዎች ባኩሎቫይረስ በተባሉት ቫይረሶች ሲያዙ እንደሚሞቱ አስተዋሉ። ይህ ቫይረስ በሰው ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት ስለማያስከትል ቫይረሱ የተጨመረበት ፈሳሽ ቢረጭ የአኩሪ አተርና የካሳቫ ሰብሎችን የሚበሉ አባ ጨጓሬዎችን መቆጣጠር እንደሚቻል አሰቡ። ዘዴው ሠርቷል። አባ ጨጓሬዎች መድኃኒቱ የተረጨባቸውን ሰብሎች በተመገቡ በጥቂት ቀናት ውስጥ ሞቱ። የሞቱት አባ ጨጓሬዎች ለቀጣዩ ጦርነት ጥሩ መሣሪያ ሆነው ስለሚያገለግሉ ከተባዮቹ መሞት በተጨማሪ ሌላ ጥቅም ሊገኝ ችሏል። እንዴት?
ፕሮፌሰር በርቲ እንዳብራሩት “ገበሬው በቫይረሱ የተለከፉትን አባ ጨጓሬዎች ሬሳ በምግብ መደባለቂያ መሣሪያ ውስጥ ጨምሮ ካላመና ካጣራ በኋላ የተጣራውን ፈሳሽ በማቀዝቀዣ ውስጥ ያስቀምጣል።” ከዚያ በኋላ ፈሳሹን በውኃ በጥብጦ በሰብሉ ላይ ይረጫል።
ይህ ባዮሎጂያዊ ፀረ ተባይ መድኃኒት እንደ ኬሚካሉ መድኃኒት ፈጣን ላይሆን ቢችልም አንድ ተመራማሪ እንዳሉት ውጤቱ እስከ 90 በመቶ ይደርሳል።
ተባዮችን በተፈጥሮአዊ ዘዴዎች ድል መምታት
ጠቃሚ በሆኑ ሶስት አፅቄዎች ተጠቅሞ ጎጂ ተባዮችን መቆጣጠር ሌላው አስፈላጊ የሆነ የባዮሎጂያዊ ተባይ ቁጥጥር ዘርፍ ነው። ይሁን እንጂ ገበሬዎች በዚህ ዘዴ እንዲጠቀሙ ለማሳመን ጥረት ቢደረግም በብራዚልም ሆነ በሌሎች አገሮች የሚኖሩ ብዙ ገበሬዎች ፈቃደኛ አልሆኑም። ለምን? ሆን ብሎ ሶስት አፅቄዎችን ማሳ ላይ መልቀቅ በአንድ የመኖሪያ ሕንጻ ላይ በረሮዎችን ከመልቀቅ የተለየ ሆኖ አይታያቸውም። “ለአብዛኞቹ ገበሬዎች ሁሉም ሶስት አፅቄዎች ተክል በላተኞች ናቸው። ማንም ገበሬ ቢሆን ማሳው ላይ ምንም ዓይነት ሶስት አፅቄ እንዲኖር አይፈልግም” ይላሉ ፕሮፌሰር በርቲ።
ስለዚህ ባዮሎጂያዊ ተባይ መከላከያ ሰፊ ተቀባይነት የሚያገኘው ገበሬዎች አንዳንድ ሶስት አፅቄዎች ረዳቶቻቸው መሆናቸውን ሲገነዘቡ ብቻ እንደሆነ ግልጽ ነው። ለምሳሌ ያህል የካሊፎርንያ፣ ዩ ኤስ ኤ ፍራፍሬ አብቃዮች በ1800ዎቹ ዓመታት መገባደጃ ላይ ሌዲበግ በተባሉት ሶስት አፅቄዎች ተገልግለዋል። በዚያ ጊዜ ከአውስትራሊያ ሳይታወቅ የገቡ ጎጂ ሶስት አፅቄዎች በሎሚና በብርቱካን ተክሎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰው ነበር። ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሌዲበግ የተባሉት ሶስት አፅቄዎች እነዚህን ወራሪዎች በቁጥጥር ሥር አውለው የካሊፎርንያን የፍራፍሬ እርሻ ከጥፋት አድነዋል!
ፋይዳ ያለው ቁጥጥር
ዛሬም አንዳንድ የብራዚል ገበሬዎች የዡዋኒና (ትንሿ ጆአና ማለት ሲሆን በዚህ አገር ለሌዲበግ የተሰጠ ስያሜ ነው) ‘የጥበቃ ሠራተኝነት’ በጣም አስተማማኝ መሆኑን መገንዘብ ጀምረዋል። በሳንድሮ ጥበቃ ሥር በሚገኘው የብርቱካን እርሻ እየተዘዋወርን እያለ “በዚህ የብርቱካን ተክል የተክል ቅማሎችን የምንከላከለው በዡዋኒና ነው” አሉኝ። በአንድ የብርቱካን ተክል አጠገብ ቆም አሉና አንዱን ቅርንጫፍ ሳብ አድርገው አስጎነበሱት። አፊድ የሚባሉት ከወረቀት መርፌ ጭንቅላት የማይበልጥ መጠን ያላቸው የእፀዋት ቅማሎች አፋቸውን በቅጠሎቹ ላይ ተክለው የተክሉን ፈሳሽ ይመጣሉ።
እነዚህ ቅማሎች ‘ለጥበቃ ሠራተኞቹ’ በምግብነት ያገለግላሉ። እንዲያውም አንዳንዶቹ የሌዲበግ ዝርያዎች እያንዳንዳቸው በሕይወት ዘመናቸው እስከ 800 ቅማሎች ይበላሉ። ታዲያ ይህ ምን ያህል ውጤት ይኖረዋል? ሳንድሮ እንደሚሉት “በብርቱካን ተክሎቹ ዙሪያ ለሌዲበግና ለሌሎች የተፈጥሮ ጠላቶች መራቢያ የሚሆን በቂ ሣርና አረም ከኖረ አጥጋቢ ውጤት ያስገኛል።” በዚህ እርሻ ባዮሎጂያዊ የቁጥጥር ዘዴ መጠቀም ከመጀመራችን በፊት በየሁለት ሳምንቱ ኬሚካላዊ ፀረ ተባይ እንረጭ ነበር ይላሉ ሳንድሮ። ዛሬ ግን እንደ ሌዲበግ ያሉት ሶስት አፅቄዎች ምስጋና ይግባቸውና የፀረ ተባይ መድኃኒት የሚረጨው በሁለት ወይም በሦስት ወር አንድ ጊዜ ብቻ ነው።
ሌዲበግ ገበሬዎች ሊጠቀሙባቸው ከሚችሉት በርካታ የተፈጥሮ አጋሮች አንዷ ብቻ ነች። ንቦች፣ ተርቦች፣ ወፎች፣ ሸረሪቶች፣ እንቁራሪቶች፣ ጉርጦችና ሌሎች ተቆጥረው የማያልቁ በርካታ ፍጥረታት ቀንና ሌሊት በጥበቃ ሥራ ላይ ከተሰማሩ ተባይ ተከላካይ ጭፍሮች የሚመደቡ ናቸው። ዓሦች ሳይቀር የፀረ ተባይ መድኃኒት ምትክ ሆነው አገልግለዋል። እንዴት?
በቻይና በኪያንግሱ ክፍለ ሀገር የናንኪንግ የእርሻና የደን መምሪያ ባልደረባ የሆኑት ሲያኦ ፋን የተባሉ ተመራማሪ በጎርፍ በተጥለቀለቁ የሩዝ ማሳዎች ላይ ዓሦች እንዲራቡ በመደረጋቸው የፀረ ተባይ መድኃኒቶች አስፈላጊነት ሊቀንስ እንደቻለ ሪፖርት አድርገዋል። ተባዮች ወደ ውኃው እንዲወድቁ ገበሬዎቹ በተክሎቹ ላይ ገመድ ያወዛውዛሉ። “ፕላንትሆፐር የተባሉት ተባዮች ከሩዙ ተክል ላይ ሲወድቁ የሞቱ መስለው ስለሚተኙ ዓሦቹ በቀላሉ ይበሏቸዋል” ሲሉ ፋን ገልጸዋል።
በተጨማሪም አነስተኛ ፀረ ተባይ መጠቀም ጠቃሚ የሆኑ ሶስት አፅቄዎች በሕይወት እንዲኖሩ ያስችላል። እነዚህ ሶስት አፅቄዎች ተባዮቹን ከሚመገቡት ዓሦች ጋር በመተጋገዝ የሩዙን ተባዮች ይዋጋሉ። ለባዮሎጂያዊ ተባይ ቁጥጥር ምስጋና ይድረስና መርዛማ ፀረ ተባዮችን በብዛት መጠቀም የቀረ ነገር ሆኗል በማለት ፋን ይገልጻሉ። በዚህ ምክንያት የሚገኘው የጤንነትና የሥነ ምህዳር ጥቅም ግልጽ ነው ሲሉ አክለው አመልክተዋል።
ገበሬዎች በአይ ፒ ኤም ለመጠቀም የሚነሳሱት ለኢኮኖሚያዊ ጥቅም ሲሉ እንጂ ለሥነ ምህዳር መሻሻል አስበው እንዳልሆነ አይካድም። በውድ ዋጋ የሚገዙ ፀረ ተባይ መድኃኒቶችን አጠቃቀም መቀነስ ብዙ ወጪ ያስቀራል። ይህ ደግሞ ከእርሻው ጠቀም ያለ ትርፍ እንዲገኝ ያስችላል። ትርፍ ደግሞ በማንኛውም ጊዜ ማንንም ሰው የሚያማልል ነገር ነው። ይሁን እንጂ በዚህ መንገድ የሚገኘው ትርፍ የእርሻ ሰብሎችን መመረዝና በአካባቢ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ካስቻለ አይ ፒ ኤም ገበሬዎችንም ሆነ ሸማቾችን፣ እንዲሁም ሥነ ምህዳራችንን ጠቀመ ማለት ነው። አንድ ታዛቢ እንዳሉት አይ ፒ ኤም ሥራ ላይ ሲውል “ተጠቃሚ የማይሆን ወገን የለም።”
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በሰፊው ሥራ ላይ የዋሉት የተባይ ማጥፊያ መድኃኒት ዓይነቶች (1) ፀረ ሶስት አፅቄ፣ (2) ፀረ አረም፣ (3) ፀረ ፈንገስ እና (4) ፀረ አይጥ ተብለው የሚታወቁ ሲሆን እያንዳንዱ የተባይ ማጥፊያ መድኃኒት ዓይነት ስያሜውን ያገኘው ከሚቆጣጠራቸው የተባይ ዓይነቶች ነው።
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የፀረ ተባይ መድኃኒቶች ቅርስ
በመላው ዓለም የሚኖሩ ገበሬዎች በሙሉ ዛሬውኑ በተቀናጀ የተባይ ቁጥጥር ዘዴ መጠቀም ቢጀምሩ እንኳን በፀረ ተባይ መድኃኒቶች ምክንያት የተፈጠረው ችግር መፍትሔ አያገኝም። የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) ባወጣው ግምታዊ አኃዝ መሠረት ባልበለጸጉ አገሮች ተከማችተው የሚገኙ ከአንድ ሚልዮን ኩንታል የሚበልጡ ፀረ ተባይ መድኃኒቶች አሉ። የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ፕሮግራም የሚያሳትመው አወር ፕላኔት የተባለ መጽሔት እንዳለው ከሆነ “ከዚህ ክምችት ውስጥ አብዛኛው ክፍል በእርዳታ ስምምነቶች አማካኝነት ተገኝቶ ሥራ ላይ ያልዋለ ነው።” በዚህ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ በአደገኛነታቸው የሚታወቁት ዲ ዲ ቲ እና ሌሎች ፀረ ተባይ መድኃኒቶች በብዛት ይገኛሉ። አወር ፕላኔት ይህ የፀረ ተባይ መድኃኒቶች ቅርስ ካልተወገደ “ከፍተኛ አደጋ እንደሚመጣ ሊጠበቅ ይችላል” ብሏል።
ይህን ክምችት ለማስወገድ ግን ብዙ ወጪ ይጠይቃል። በአፍሪካ ብቻ የተከማቸውን ፀረ ተባይ መድኃኒት ለማስወገድ እስከ 750 ሚልዮን ብር የሚደርስ ወጪ ይጠይቃል። ታዲያ ይህን የሚያክል ወጪ ማን ይሸፍን? ፋኦ ፀረ ተባዮቹን የለገሱት አገሮች ወጪውን እንዲሸፍኑ ጥሪ አቅርቧል። ይሁን እንጂ ፋኦ እንዳመለከተው “አግሮኬሚካል ኩባንያዎች አብዛኛውን ጊዜ ከመጠን በላይ የሆነ ወይም አስፈላጊ ያልሆነ ፀረ ተባይ መድኃኒት በማቅረብ ረገድ ሚና ስለነበራቸው እርዳታ መስጠት አለባቸው።” ይሁን እንጂ እስከ አሁን ድረስ እነዚህ ኩባንያዎች “የቆየውን ክምችት ለማስወገድ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለመርዳት ፈቃደኛ አልሆኑም።”
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የተሻሻሉ ተክሎች አከራካሪ የሆኑት ለምንድን ነው?
በተባዮች ላይ ከታለሙት መሣሪያዎች አንዱ ባዮቴክኖሎጂ ነው። የሰው ልጅ ስለ ዲ ኤን ኤ ሞሊኪውል ውስጣዊ አሠራር ያለው እውቀት እየጨመረ በመሄዱ ተመራማሪዎች የተለያዩ የዲ ኤን ኤ ቁራጮችን ከተለያዩ የእጽዋት ዝርያዎች ወስደው አንድ ላይ በማጣመር ተባዮችን የመከላከል አቅም ያላቸው ተክሎች ለማስገኘት ችለዋል።
ለዚህ ምሳሌ የሚሆነን በቆሎ ነው። ጀነቲካዊ መሐንዲሶች ከሌላ ምንጭ የተገኘ አንድ ጂን በበቆሎ ዲ ኤን ኤ ውስጥ አስገቡ። በዚህ መንገድ የገባው አዲስ ጂን ተባዮችን የሚቀስፍ ፕሮቲን አስገኘ። በዚህ መንገድ ጠላቶቹ የሆኑትን ሶስት አፅቄዎች በሙሉ ለመቋቋም የሚችል የተሻሻለ በቆሎ ሊገኝ ቻለ።
ይሁን እንጂ በዚህ መንገድ የተሻሻሉ እጽዋት ብዙ ውዝግብ አስነስተዋል። ተቃዋሚዎች እነዚህ የተሻሻሉ ተክሎች ሰዎችን ሊያሳምሙ ወይም በምንም የማይበገሩ አረሞች ሊሆኑ ይችላሉ በማለት ይከራከራሉ። አንዳንድ ሳይንቲስቶች ሶስት አፅቄዎችን የሚገድል ጂን የገባላቸው ተክሎች የተባዮችን የመከላከል አቅም ሊቀሰቅሱ ይችላሉ በማለት ያስጠነቅቃሉ። ኤንትሞሎጂስቱ በርቲ “ለጀነቲካዊ ምሕንድስና ያለንን የጋለ ስሜት በረድ ማድረግ ይኖርብናል” በማለት ያስጠነቅቃሉ። “ፀረ ተባይ መድኃኒቶች ተአምረኛ ናቸው ተብለው ይወደሱ በነበሩበት በ1950ዎቹ ዓመታት ሰዎች ምን ያህል ፈንጥዘው እንደነበረ ታስታውሳላችሁ? ዛሬ ግን ያ ሁሉ ፈንጠዝያ ትክክል አለመሆኑን አውቀናል። ተአምረኛ ፀረ ተባዮች ተአምረኛ ሶስት አፅቄዎች አስገኝተዋል። የዛሬዎቹ የተሻሻሉ ተአምረኛ እጽዋት ምን ዓይነት ችግር ሊያመጡ እንደሚችሉ ማን ሊያውቅ ይችላል?”
ባዮሎጂያዊ ችግሮችን በሙሉ መፍታት ቢቻል እንኳን ጀነቲካዊ ጥንቅሮች በሳይንቲስቶች መነካካታቸው አንዳንድ ሰዎችን የሚያሳስብ የሥነ ምግባር ጥያቄ አስነስቷል። አንዳንዶች ባዮቴክኖሎጂ የቆየውን የፀረ ተባይ ችግር ሊፈታ ቢችል እንኳን አዲስ የሥነ ምግባር ችግር ያስከትልብናል ይላሉ።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንዲት ሌዲበግ በመቶ የሚቆጠሩ ተባዮችን ልትበላ ትችላለች