ግዞት በሳይቤሪያ!
ቫሲሊ ካሊን እንደተናገረው
በከፍተኛ የመድፍ ድብደባ እየተናጠ ባለ አካባቢ፣ አንድ ሰው ያለምንም መደናገጥ በረጋ መንፈስ መጽሐፍ ቅዱስ ሲያነብ ብትመለከቱ ይህን የእርጋታ መንፈስ እንዴት ሊያገኝ እንደቻለ ለማወቅ አትጓጉም? ከ56 ዓመት በፊት አባቴ የተመለከተው እንዲህ ያለ ሁኔታ ነበር።
ጊዜው ሐምሌ 1942 ሲሆን ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በእጅጉ ተፋፍሞ የነበረበት ወቅት ነው። የጀርመን ጦር በዩክሬን፣ ቪልሻኒትሳ የተባለችውን አባቴ ይኖርባት የነበረችውን መንደር አቋርጦ ሲያልፍ አባቴ ጥቂት አረጋውያን ወደሚኖሩበት ቤት ጎራ አለ። የመድፍ ጥይቶች በአካባቢው እየወደቁ ሲፈነዱ ሰውዬው በቆሎ እየቀቀለ መጽሐፍ ቅዱስ ያነብ ነበር።
ከአምስት ዓመት በኋላ በዚያን ወቅት የሶቪዬት ኅብረት አካል በነበረችውና በስተ ምዕራብ በምትገኘው ኢቫኖ-ፍራንኮፍስክ በምትባለው ውብ የዩክሬይን ከተማ አቅራቢያ ተወለድኩ። ከጊዜ በኋላ አባቴ ከዚያ የይሖዋ ምሥክር ሰው ጋር ስለተገናኘበት የማይረሳ ጊዜም ሆነ አስፈሪ ስለነበሩት የጦርነቱ ዓመታት ነግሮኛል። ሕዝቡ በሁኔታው በጣም ተጎሳቁሎና ግራ ተጋብቶ የነበረ ሲሆን ብዙዎቹም ‘ይህን ያህል የፍትሕ መጓደል የበዛው ለምንድን ነው? በሺህ የሚቆጠሩ ንጹሐን ሰዎች የሚሞቱት ለምንድን ነው? አምላክ ይህ ሁሉ ሲሆን ዝም ብሎ የሚመለከተው ለምንድን ነው? ለምን? ለምን? ለምን?’ በማለት ይጠይቁ ነበር።
አባቴ በዕድሜ ከገፋው ሰውዬ ጋር እነዚህን በመሰሉ ጥያቄዎች ላይ ረዘም ላለ ሰዓት ግልጽ የሆነ ውይይት አደረገ። ሰውዬው የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን እያወጣ አባቴን ለረዥም ጊዜ ግራ ሲያጋቡት ለነበሩት ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ሰጠው። አምላክ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ሁሉንም ዓይነት ጦርነቶች እንደሚያስወግድና ምድር አስደሳች ወደሆነ ገነትነት እንደምትለወጥ አብራራለት።—መዝሙር 46:9፤ ኢሳይያስ 2:4፤ ራእይ 21:3, 4
አባቴ ወዲያውኑ ወደ ቤት መጣና “የሚገርም ነው፣ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር አንድ ጊዜ ባደረግኩት ውይይት ዓይኔ በራ! እውነትን አገኘሁ!” በማለት በደስታ ተናገረ። አዘውትሮ ወደ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ይሄድ የነበረ ቢሆንም ቀሳውስቱ ለጥያቄዎቹ አንዳችም አጥጋቢ መልስ ሊሰጡት እንዳልቻሉ ተናገረ። በመሆኑም አባቴ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረ፤ እናቴም አብራው ማጥናት ጀመረች። ከዚህም በተጨማሪ ሦስት ልጆቻቸውን ማለትም ገና የ2 ዓመት ልጅ የነበረችውን እህቴንና የ7 እና የ11 ዓመት ዕድሜ የነበራቸውን ወንድሞቼን ማስተማር ጀመሩ። ከዚያም ብዙም ሳይቆይ ቤታቸው በቦምብ ክፉኛ በመመታቱ ከአንዲት ክፍል በስተቀር የቀረው ሁሉ ወደመባቸው።
እናቴ በአንድ ትልቅ ቤተሰብ ውስጥ ያደገች ሲሆን አምስት እህቶችና አንድ ወንድም ነበሯት። አባቷ በአካባቢያቸው ከነበሩት ሃብታም ሰዎች መካከል አንዱ ሲሆኑ ለቦታቸውና ለክብራቸው የሚጨነቁ ሰው ነበሩ። በዚህም የተነሳ መጀመሪያ ላይ ዘመድ አዝማዶቻችን ቤተሰቦቼ የያዙትን አዲስ እምነት ተቃወሙ። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ ከእነዚህ ተቃዋሚዎች መካከል ብዙዎቹ ምስልን ለአምልኮ መጠቀምን የመሰሉ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ሃይማኖታዊ ልማዶችን እርግፍ አድርገው በመተው ከወላጆቼ ጋር በእውነተኛው አምልኮ ተባብረዋል።
ቀሳውስት ሰዎችን በማስተባበር በምሥክሮቹ ላይ እንዲነሱ አደረጉ። በዚህም የተነሳ የአካባቢው ነዋሪዎች ወላጆቼ የሚኖሩበትን ቤት መስኮቶች በመሰባበር ወላጆቼን ማስፈራራት ጀመሩ። ወላጆቼ ይህ ሁሉ ችግር ቢደርስባቸውም መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናታቸውን ግን አላቆሙም። በዚህም የተነሳ በ1947 ይሖዋን በመንፈስና በእውነት በሚያመልክ ቤተሰብ ውስጥ ተወለድኩ።—ዮሐንስ 4:24
ወደ ግዞት መወሰድ
ገና የአራት ዓመት ልጅ የነበርኩ ቢሆንም እንኳ ሚያዝያ 8, 1951 ማለዳ ላይ የተከሰተውን ነገር ፈጽሞ አልረሳውም። ውሻ የያዙ ወታደሮች ወደ ቤታችን መጡ። አገር ለቅቀን እንድንወጣ ማዘዣ የወጣበትን ወረቀት ሰጡንና ቤታችንን መፈተሽ ጀመሩ። በተሰጠን የሁለት ሰዓት ጊዜ ውስጥ ቤታችንን ለቅቀን ለመውጣት ስንጣደፍ መትረየስ የታጠቁና ውሻ የያዙት ወታደሮች ደጃፋችን ላይ ቆመው፣ የውትድርና የደንብ ልብስ የለበሱ ሰዎች ደግሞ በጠረጴዛችን ዙሪያ ተቀምጠው ይጠብቁ ጀመር። ሁኔታው ስላልገባኝ ተደናገጥኩና ማልቀስ ጀመርኩ።
ወላጆቼ ከአሁን በኋላ የይሖዋ ምሥክር እንደማይሆኑና ዳግመኛም ከእነርሱ ጋር እንደማይተባበሩ በሚያረጋግጥ ሰነድ ላይ እንዲፈርሙ ታዘዙ። ከፈረሙ በቤታቸውና በትውልድ አገራቸው በነፃነት እንዲኖሩ ይፈቀድላቸው ነበር። ሆኖም አባቴ “የትም ቦታ ብትወስዱን አምላካችን ይሖዋ ከእኛ ጋር እንደሚሆን የጸና እምነት አለኝ” በማለት በድፍረት መለሰ።
“እስቲ ስለ ቤተሰብህና ስለ ልጆችህ አስብ” በማለት መኮንኑ ተማጸነው። “የምትሄዱት እኮ ወደ መዝናኛ ቦታ ሳይሆን በሰሜን ጫፍ ወደሚገኘው ከዓመት እስከ ዓመት በረዶ ወደማይለየውና በየመንገዱ ድቦች ወደማይጠፉበት ሥፍራ ነው።”
በዚያን ወቅት “ሳይቤሪያ” የሚለው ቃል በጣም አስፈሪና ለሁሉም እንግዳ የሆነ ቦታ ነበር። ሆኖም ለይሖዋ የነበረን ከፍተኛ ፍቅርና እምነት ይህ የማይታወቅ ቦታ የሚያሳድረውን የፍርሃት ስሜት እንድንቋቋመው ረድቶናል። ንብረታችን በአንድ ተጎታች ሰረገላ ላይ ተጭኖ ወደ ከተማ ተወሰድን። ከዚያም ከሌሎች ከ20 እስከ 30 ከሚሆኑ ቤተሰቦች ጋር በዕቃ መጫኛ ፉርጎ ላይ ተጭነን እልም ወዳለው የሳይቤርያ ዱር ወይም ምድረ በዳ መጓዝ ጀመርን።
በመንገዱ ላይ ባሉት ባቡር ጣቢያዎች ግዞተኞችን የጫኑና በፉርጎዎቹ ላይ “የይሖዋ ምሥክሮች” የሚል ጽሑፍ ያለባቸው ባቡሮች ተመለከትን። በዚህ መንገድ በሺህ የሚቆጠሩ ምሥክሮችና ቤተሰቦቻቸው በሰሜንና በሩቅ ምሥራቅ ወደሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች እየተወሰዱ እንዳሉ ብዙዎች በማወቃቸው ይህ ራሱ ጥሩ ምሥክርነት ነበር።
ይህ በሚያዝያ 1951 የተካሄደው የይሖዋ ምሥክሮችን ከየቦታው እያፈሱ ወደ ግዞት የመላክ እንቅስቃሴ በታሪክም በደንብ ተመዝግቦ ይገኛል። ታሪክ ጸሐፊው ዎልተር ኮላርስ ሃይማኖት በሶቪየት ሕብረት በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ይህን ጉዳይ አስፍረዋል:- “ይህ በሩስያ ለሚገኙት ‘የይሖዋ ምሥክሮች’ ማብቂያ ሳይሆን በስብከት እንቅስቃሴያቸው የአዲስ ምዕራፍ መክፈቻ ነበር። እንዲያውም ወደ ግዞት እየሄዱ ሳለ በየባቡር ጣቢያው ሲቆሙ እምነታቸውን ለማሰራጨት ይጥሩ ነበር። የሶቪየት መንግሥት እነርሱን ሲያስወጣ እምነታቸው እንዲሰራጭ ከማድረግ ሌላ የፈየደው ነገር አልነበረም። ‘ምሥክሮቹ’ ምንም እንኳ ከባድ የጉልበት ሥራ ወደሚሠራበት ማጎሪያ ካምፕ የተወሰዱ ቢሆንም ቀድሞ ይኖሩበት ከነበረው ገለልተኛ መንደር ወጥተው ይበልጥ ሰፊ ወደሆነ ዓለም ተሸጋግረዋል።”
እንደ ዱቄት፣ በቆሎና ባቄላ ያሉ ጥቂት እህሎች እንድንወስድ ፈቃድ በማግኘታችን ቤተሰባችን ዕድለኛ ነበር ማለት ይቻላል። እንዲያውም አያቴ አሳማ እንዲያርድ ተፈቅዶለት ስለነበር ለእኛና ለሌሎች ምሥክሮች የሚበቃ ምግብ ማግኘት ችለን ነበር። በጉዞ ላይ እያለን ከልብ በመነጨ ስሜት እንዘምራቸው የነበሩ መዝሙሮች ከባቡር ፉርጎዎቹ ውጭ ይሰሙ ነበር። ይሖዋ ለመጽናት የሚያስችለንን ጥንካሬ ሰጥቶናል።—ምሳሌ 18:10
ሩስያን ለማቋረጥ ሦስት ሳምንት የፈጀ ጉዞ ካደረግን በኋላ በመጨረሻ ከፍተኛ ቅዝቃዜ ወዳለበት፣ ገለልተኛ ወደሆነውና ብዙ ኪሎ ሜትሮች ርቆ ወደሚገኘው ሳይቤሪያ ደረስን። በኢርኩትስክ አውራጃ ቸንስክ ውስጥ ወደሚገኘው ቶሬያ ወደሚባለው ባቡር ጣቢያ ተወሰድን። ከዚያም ሰነዳችን “የዘላለም መኖሪያችን” እንደሆነ አድርጎ ወደሚገልጸው በጣም ርቆ ወደሚገኝ አንድ ትንሽ መንደር ተወሰድን። የ15 ቤተሰቦች ንብረት በበረዶ ላይ በሚንሸራተት ጋሪ ተጫነና አንድ ትራክተር የጸደይ ወቅት በፈጠረው ጭቃ ላይ እየጎተተ ወሰደው። ወደ 20 የሚጠጉ ቤተሰቦች በሰፋፊ መጠለያዎች ውስጥ እንዲሰፍሩ ተደረገ። ባለ ሥልጣናቱ የይሖዋ ምሥክሮች የተጠሉ ሰዎች ናቸው ብለው ቀደም ብለው ለአካባቢው ነዋሪዎች ነግረዋቸው ነበር። በዚህም የተነሳ መጀመሪያ ላይ ሰዎች ይፈሩን የነበረ ከመሆኑም በላይ እኛን ለመቅረብ አይፈልጉም ነበር።
በግዞት እያለን የተሰጠን ሥራ
የይሖዋ ምሥክሮች ዛፍ የመቁረጥ ሥራ ተሰጥቷቸው ነበር። ሆኖም ሁኔታው ምቹ አልነበረም። ግንዶችን በመጋዝ መቁረጡ፣ መፍለጡ ከዚያም በፈረስ በሚጎተቱ ጋሪዎች ላይ ጭኖ መውሰዱና በኋላም በባቡር ፉርጎዎች ላይ የመጫኑ ሥራ ሁሉ የሚከናወነው በእጅ ነበር። በተለይ ደግሞ ትንኞች እንደ ጉም አካባቢውን በሚሸፍኑበት ጊዜ ምንም ማምለጫ ስለሌለ ሁኔታውን ይበልጥ ከባድ ያደርገዋል። በተለይ አባቴ በጣም ተሠቃየ። ሰውነቱ በሙሉ አብጦ የነበረ ሲሆን መጽናት ይችል ዘንድ ይሖዋን አጥብቆ ለመነ። ይህ ሁሉ መከራ ቢደርስባቸውም አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች ከእምነታቸው ፈጽሞ ንቅንቅ አላሉም።
ከዚያም ወደ ኢርኩትስክ ተወሰድንና ቤተሰቦቼ ቀደም ሲል የእስረኞች ካምፕ በነበረ ቤት ውስጥ እየኖሩ በጡብ ፋብሪካ እንዲሠሩ ተደረገ። ጡቦቹን ከፍተኛ ሙቀት ካለው ትልቅ ምድጃ ውስጥ የሚያወጡት በእጃቸው ሲሆን በየጊዜው እያደገ የሚሄደውን የሥራ ኮታ ለማሟላት ልጆችም ወላጆቻቸውን መርዳት ነበረባቸው። ይህ ሁኔታ በጥንቷ ግብፅ የነበሩትን እስራኤላውያን ባርነት ያስታውሰን ነበር።—ዘጸአት 5:9-16
ምሥክሮቹ ቀደም ሲል እንደተወራባቸው “የሕዝብ ጠላቶች ሳይሆኑ” ጠንካራ ሠራተኞችና ሃቀኞች መሆናቸው የኋላ ኋላ ግልጽ እየሆነ መጣ። ባለ ሥልጣናትን የሚሳደብ ወይም አሠሪዎች የሚያስተላልፉትን ውሳኔ የሚቃወም አንድም ምሥክር አለመኖሩ በሁሉም ዘንድ የታወቀ ሆነ። እንዲያውም እምነታቸው በብዙዎች ዘንድ የተወደደ ሆነ።
መንፈሳዊነታችን
ምሥክሮቹ ወደ ግዞት ከመላካቸው በፊት፣ በጉዞ ላይ እያሉ በመጨረሻም በግዞተኝነት በሰፈሩበት ቦታ ሁሉ በተደጋጋሚ ይፈተሹ የነበረ ቢሆንም ብዙዎች የመጠበቂያ ግንብ መጽሔቶችንና ሌላው ቀርቶ መጽሐፍ ቅዱስ ደብቀው ለመያዝ ችለው ነበር። ከጊዜ በኋላ እነዚህ ጽሑፎች በእጅና በሌሎች ዘዴዎች ተባዙ። በመጠለያዎቹ ውስጥ ዘወትር ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ይደረጉ ነበር። የመጠለያዎቹ ተቆጣጣሪ እየዘመርን ካገኘን እንድናቆም ያዝዘን ስለነበር መዘመራችንን እናቆማለን። ሆኖም ወደሚቀጥለው መጠለያ ሲሄድ እንደገና መዘመር እንጀምራለን። ፈጽሞ ሊያስተወን አልቻለም።
የስብከት ሥራችንንም ቢሆን ሊያስቆሙት አልቻሉም። ምሥክሮቹ በየትኛውም ቦታ ያገኙትን ሰው ሁሉ ያነጋግሩ ነበር። ብዙውን ጊዜ ታላላቅ ወንድሞቼና ወላጆቼ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዴት አድርገው ለሌሎች ሰዎች እንደሚያካፍሉ ይነግሩኝ ነበር። ይህ ጥረታቸው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ቅን በሆኑ ሰዎች ልብ ውስጥ ሥር እንዲሰድ አድርጓል። በዚህም የተነሳ በ1950ዎቹ መግቢያ ላይ የይሖዋ መንግሥት በኢርኩትስክ እና በአካባቢው በስፋት ሊታወቅ ችሏል።
መጀመሪያ ላይ ምሥክሮቹ እንደ ፖለቲካ ጠላቶች ተደርገው ይታዩ ነበር፤ ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ ድርጅታችን ሙሉ በሙሉ ሃይማኖታዊ መሆኑ ታወቀ። እንዲህም ሆኖ ባለ ሥልጣናት ሥራችንን ለማስቆም ከመሞከር ወደኋላ አላሉም። ስለዚህም በቀላሉ ዓይን ውስጥ እንዳንገባ ስንል ሁለት ወይም ሦስት ቤተሰቦች ብቻ እየሆንን ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መሰብሰብ ጀመርን። በየካቲት ወር 1952 አንድ ማለዳ ላይ ከባድ ፍተሻ ተደረገ። ከዚያም አሥር ምሥክሮች ተያዙና ታሰሩ፣ የቀረነውም ወደ ተለያዩ ቦታዎች ተወሰድን። የእኛ ቤተሰብ አንድ መቶ የሚያክሉ ሰዎች ወደሚኖሩባትና ከኢርኩትስክ ከተማ 30 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ ወደምትገኘው ኢስክራ ወደምትባል መንደር ተወሰደ።
ሁኔታዎች ቢለዋወጡም መጽናት
የመንደሩ አስተዳዳሪ በሚያስገርም መንገድ ጥሩ አቀባበል አደረገልን። ሕዝቡ ትሑትና ወዳጃዊ መንፈስ የነበረው ሲሆን እንዲያውም ብዙዎቹ እኛን ለማገዝ ከየቤታቸው ወጡ። በግምት 17 ካሬ ሜትር ስፋት ባለው ጠባብ ክፍል ውስጥ እኛን ጨምሮ ሦስት ቤተሰቦች በአንድነት እንድንኖር ተደርጎ ነበር። ብርሃን ለማግኘት እንጠቀም የነበረው በኩራዞች ነበር።
በቀጣዩ ቀን ጠዋት ላይ ምርጫ ይካሄድ ነበር። ቤተሰቦቼ ቀደም ሲል የአምላክን መንግሥት የመረጡ መሆኑን ተናገሩ፤ እርግጥ ሰዎቹ ምንም አልገባቸውም። በዚህም ምክንያት ትላልቆቹ የቤተሰባችን አባላት ወደ እስር ቤት ተወስደው ሙሉ ቀን እዚያው እንዲቆዩ ተደረገ። ከዚያም በርካታ ሰዎች ስለ እምነታቸው ጠየቋቸው። ይህም የሰው ዘር ብቸኛ ተስፋ የአምላክ መንግሥት እንደሆነ ለመናገር ጥሩ አጋጣሚ ከፈተላቸው።
በኢስክራ መንደር በኖርንባቸው አራት ዓመታት ጊዜ ውስጥ አብሮን ሊሰበሰብ የሚችል በአቅራቢያችን የሚኖር አንድም የይሖዋ ምሥክር አልነበረም። ወደ ሌላ መንደር ለመሄድ ከአዛዡ የይለፍ ፈቃድ ማግኘት ነበረብን፤ ወደ እዚህ የተላክንበት ዋነኛ ምክንያት ከሌሎች ሰዎች ጋር እንዳንገናኝ ለማድረግ ስለነበር ብዙውን ጊዜ ፈቃድ አይሰጠንም ነበር። ሆኖም ምሥክሮቹ በቅርቡ ያገኙት መንፈሳዊ ምግብ ካለ ለሌሎች ለማካፈል እርስ በርሳቸው ለመገናኘት ይጥሩ ነበር።
ስታሊን በ1953 ከሞተ በኋላ እንደ ወንጀለኛ ተቆጥረው የተፈረደባቸው ምሥክሮች በሙሉ የእስር ጊዜያቸው ከ25 ዓመት ወደ 10 ዓመት ዝቅ ተደረገላቸው። ከዚያን ጊዜ በኋላ በሳይቤሪያ የሚኖሩ ሁሉ ከቦታ ወደ ቦታ ለመንቀሳቀስ የሚያስችል የይለፍ ፈቃድ ማግኘት አላስፈለጋቸውም። ሆኖም ባለ ሥልጣናት ወዲያውኑ ፍተሻ ማድረግ ጀመሩና መጽሐፍ ቅዱስ ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎች የተገኘበትን ምሥክር ማሰር ጀመሩ። ከዚያም ለምሥክሮቹ ብቻ የተከለሉ ልዩ ካምፖች ተዘጋጁና 400 የሚሆኑ ወንድሞችና 200 የሚሆኑ እህቶች በእነዚሁ በኢርኩትስክ አካባቢ በተዘጋጁት ካምፖች ውስጥ እንዲሰፍሩ ተደረገ።
በሶቪየት ኅብረት በምንገኝ የይሖዋ ምስክሮች ላይ ይደርስ የነበረውን ስደት የሚገልጹ ዜናዎች በዓለም ዙሪያ ወደሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ተሰራጩ። በዚህም የተነሳ ከ1956 አጋማሽ እስከ የካቲት 1957 ድረስ በዓለም ዙሪያ ተደርገው በነበሩት 199 የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ እኛን የሚመለከት አቤቱታ ቀረበ። በድምሩ 462,936 ተሰብሳቢዎች ያጸደቁት ይህ አቤቱታ በዚያን ወቅት የሶቪየት ጠቅላይ ሚንስትር ለነበሩት ለኒኮላይ ኤ ቡልጋኒን ተላከ። ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል አንዳንዶቹ ነፃ እንድንለቀቅና “በሩስያ፣ በዩክሬንና እንደ አስፈላጊነቱ ደግሞ በሌሎች ቋንቋዎችም የተዘጋጁ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔቶችንም ሆነ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠቀሙባቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ሌሎች ጽሑፎች የማግኘትና የማተም ፈቃድ እንዲሰጠን” የሚጠይቁ ነበሩ።
በዚህ ወቅት የእኛ ቤተሰብ ከኢርኩትስክ 20 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኘው ኩድያኮቮ ወደሚባል መንደር ተልኮ ነበር። በዚያ መንደር ለሰባት ዓመታት ኖርን። በ1960 ፍዮዶር የተባለው ወንድሜ ኢርኩትስክን ለቅቆ ሲሄድ በቀጣዩ ዓመት ደግሞ ታላቅ ወንድሜ አገባ፣ እህቴም ወደ ሌላ አካባቢ ሄደች። ከዚያም በ1962 ፍዮዶር ሲሰብክ ተያዘና ታሰረ።
ያደረግኩት መንፈሳዊ እድገት
መጽሐፍ ቅዱስን ከሌሎች ጋር ሆነን ለማጥናት ከምንኖርበት ከኩድያኮቮ መንደር 20 ኪሎ ሜትር የሚያክል ርቀት በእግር ወይም በብስክሌት መጓዝ ነበረብን። ስለዚህም ከሌሎች ምሥክሮች ጋር በቀላሉ መገናኘት እንችል ዘንድ ወደ ኢርኩትስክ ለመዛወር ጥረት አደረግን። ሆኖም የምንኖርበት መንደር ባለ ሥልጣን መኖሪያ ለመቀየር ያደረግነውን ጥረት ከመቃወሙም በላይ ጥረታችን እንዲሰናከል ለማድረግ ያልቆፈረው ጉድጓድ አልነበረም። የተወሰኑ ጊዜያት ካለፉ በኋላ ግን ይህ ሰው ለእኛ ያለው አመለካከት እየተሻሻለ በመሄዱ ከኢርኩትስክ 10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ፒቮቫሪካ ወደምትባል መንደር ለመዘዋወር ቻልን። በዚያ አንድ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ የነበረ ሲሆን የእኔም ሕይወት መለወጥ ጀምሮ ነበር። በፒቮቫሪካ የተደራጁ የጉባኤ መጽሐፍ ጥናት ቡድኖችና መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን በበላይነት የሚቆጣጠሩ ወንድሞችም ነበሩ። የተሰማኝን ደስታ ልገልጽላችሁ አልችልም!
በዚህ ወቅት ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ከፍተኛ ፍቅር አዳብሬ ስለነበር ለመጠመቅ ፈለግኩ። ነሐሴ 1965 በትንሿ ኦልካ ወንዝ ስጠመቅ ምኞቴ ሁሉ እውን ሆነ። በዚህ ወቅት ሌሎች በርካታ አዳዲስ ምሥክሮችም ተጠምቀዋል። እንዲሁ ለሚመለከተን ሰው ለሽርሽር የመጣንና ወንዝ ውስጥ የምንዋኝ ነበር የምንመስለው። ብዙም ሳይቆይ የቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የበላይ ተመልካች ሆኜ ተሾምኩ። ከዚያም ኅዳር 1965 ፍዮዶር ከእስር በመለቀቁ ደስታችን እጥፍ ድርብ ሆነ።
ሥራው እየበለጸገ የሄደበት መንገድ
በ1965 ሁሉም ግዞተኛ እንዲሰበሰብ ተደረገና ወደ ፈለግንበት ቦታ መሄድ እንደምንችል ተነገረን። “ዘላለማዊው መኖሪያችን” በዚህ መንገድ አበቃለት። የተሰማንን ደስታ መገመት ትችላላችሁ! ከመካከላችን ብዙዎች ወደ ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ሲሄዱ ሌሎች ደግሞ ይሖዋ መንፈሳዊ እድገታችንንና እንቅስቃሴያችንን በባረከበት በዚያው ቦታ ለመቅረት መረጡ። ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ ልጆቻቸውን፣ የልጅ ልጆቻቸውንና የልጅ ልጅ ልጆቻቸውን በሳይቤሪያ ያሳደጉ ሲሆን ይህም ቦታው ቀደም ሲል ይታሰብ የነበረውን ያህል የሚያስፈራ አለመሆኑን የሚያሳይ ነበር።
በ1967 ከማሪያ ጋር ተዋወቅን፤ የእርሷም ቤተሰቦች ከዩክሬን ወደ ሳይቤሪያ ተግዘው የነበሩ ሲሆን ሕፃናት በነበርንበት ወቅት ቪልሻኒትሳ በምትባል በአንዲት የዩክሬን መንደር አብረን ኖረናል። በ1968 ተጋባንና ከጊዜ በኋላ ያሮስላፍ የተባለ አንድ ወንድ ልጅና ከዚያም ኦክሳና የተባለች አንዲት ሴት ልጅ በመውለድ ተባርከናል።
የቀብርና የጋብቻ ሥነ ሥርዓቶችን ብዙ ሆነን አንድ ላይ ለመሰብሰብ እንጠቀምባቸው ነበር። በተጨማሪም እነዚህን አጋጣሚዎች በሥነ ሥርዓቱ ላይ ለተገኙ ምሥክር ላልሆኑ ዘመዶችና ወዳጆች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ለማብራራት እንጠቀምባቸው ነበር። ስለ ትንሣኤ ተስፋ ወይም የይሖዋ ዝግጅት ስለሆነው የጋብቻ ሥርዓትና በአዲሱ ዓለም ስለምናገኛቸው በረከቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ በሰበክንባቸው በእነዚህ ጊዜያት የደህንነት አባላት በተደጋጋሚ ተገኝተው አዳምጠዋል።
በአንድ ወቅት የቀብር ንግግር አቅርቤ እንደጨረስኩ አንድ መኪና ድንገት መጣና በሮቹ በኃይል ተከፈቱ። ከዚያም ውስጥ ከነበሩት ሰዎች አንዱ ወጣና መኪናው ውስጥ እንድገባ አዘዘኝ። ፈጽሞ አልፈራሁም ነበር። ደግሞም እኛ በአምላክ የምናምን ሰዎች እንጂ ወንጀለኞች አይደለንም። ሆኖም የጉባኤያችንን የአገልግሎት ሪፖርቶች በኪሴ ውስጥ ይዤ ነበር። በዚህ ምክንያት ልታሰር እንደምችል አውቅ ስለነበር አብሬያቸው ከመሄዴ በፊት ለባለቤቴ ገንዘብ መስጠት እችል እንደሆነ ጠየቅኩ። ከዚያም እዚያው በእነርሱ ፊት በተረጋጋ መንፈስ የገንዘብ ቦርሳዬን ከጉባኤው ሪፖርቶች ጋር አንድ ላይ አድርጌ ሰጠኋት።
ከ1974 ጀምሮ እኔ እና ማሪያ በምንኖርበት ቤት ውስጥ በድብቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎችን ማዘጋጀት ጀመርን። አንድ ትንሽ ልጅ ስለነበረን እንዳያውቅብን ስንል ሥራችንን የምናከናውነው ሌሊት ነበር። ይሁን እንጂ የምንሠራውን ለማወቅ ከፍተኛ ጉጉት ስላደረበት እንቅልፍ የወሰደው በማስመሰል የምንሠራውን ነገር አሾልቆ ይመለከት ነበር። ከጊዜ በኋላ “ስለ አምላክ የሚናገሩትን መጽሔቶች ማን እንደሚያዘጋጃቸው አውቃለሁ” አለን። ሁኔታው ትንሽ ቢያስፈራንም ይሖዋ ለዚህ አስፈላጊ ለሆነ ሥራ ሲል ቤተሰባችንን እንዲጠብቅ ሁልጊዜ እንጸልይ ነበር።
ውሎ አድሮ ባለ ሥልጣናት ለይሖዋ ምሥክሮች ጥሩ አመለካከት በማሳደራቸው በዩሶልዬ-ሲቢርስኮዬ ከተማ በሚገኘው በሚር የኪነ ጥበብና መዝናኛ ማዕከል ትልቅ ስብሰባ ለማድረግ ዝግጅት አደረግን። ስብሰባችን የሚካሄደው ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና ለክርስቲያናዊ ሕብረት ብቻ መሆኑን ለከተማው ባለ ሥልጣናት አረጋገጥንላቸው። ጥር 1990 ከ700 የሚበልጡ ሰዎች በስብሰባው ላይ በመገኘታቸው አዳራሹ ጢም ብሎ ከመሙላቱም በላይ የበርካታ ነዋሪዎችን ትኩረት ስቦ ነበር።
ስብሰባው ካለቀ በኋላ አንድ ዘጋቢ “ለመሆኑ ልጆቻችሁን መቼ አሠልጥናችኋቸው ነው?” በማለት ጠየቀ። እርሱም ሆነ በስብሰባው ላይ የተገኙ ሌሎች ሰዎች ይህን አራት ሰዓት የፈጀ የሕዝብ ስብሰባ ልጆች በትኩረት ሲከታተሉ በመመልከታቸው በጣም ተገርመዋል። ወዲያውም በአካባቢው የሚታተም አንድ ጋዜጣ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ጥሩ ዘገባ ይዞ ወጣ። “[ከይሖዋ ምሥክሮች] ትምህርት መቅሰም ይቻላል” ሲል ገልጿል።
በተገኘው ከፍተኛ ዕድገት መደሰት
በ1991 በሶቪየት ኅብረት ሰባት የአውራጃ ስብሰባዎች ያደረግን ሲሆን በስብሰባዎቹም ላይ 74,252 ሰዎች ተገኝተዋል። የቀድሞዋ የሶቪየት ኅብረት ሪፑብሊኮች ራሳቸውን ከቻሉ በኋላ በሞስኮ እንዳገለግል በይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል ተመደብኩ። እዚያም በመንግሥቱ ሥራ የማበረክተውን ድርሻ ማስፋት እችል እንደሆነ ጥያቄ ቀረበልኝ። በዚያን ወቅት ያሮስላፍ ትዳር ከመመሥረቱም በላይ ልጅ ወልዶ የነበረ ሲሆን ኦክሳናም በአሥራዎቹ እድሜ ላይ ትገኝ ነበር። ስለዚህ በ1993 እኔ እና ማሪያ በሞስኮ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመርን። በዚያው ዓመት በሩስያ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ድርጅት አስተዳደር መምሪያ አስተባባሪ ሆኜ እንድሠራ ተሾምኩ።
አሁን እኔ እና ማሪያ ከሴንት ፒተርስበርግ ወጣ ብሎ በሚገኘው በአዲሱ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ በመሥራት ላይ እንገኛለን። በሩስያ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመሩ ያሉት የመንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማሟላት ከሌሎች ታማኝ ወንድሞች ጋር አብሮ መሥራት ለእኔ ትልቅ መብት ነው። ዛሬ በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ሪፑብሊኮች ከ260,000 የሚበልጡ ምሥክሮች ያሉ ሲሆን በሩስያ ብቻ ከ100,000 የሚበልጡ ምሥክሮች አሉ!
እኔ እና ማሪያ የተወደደ መኖሪያችን በነበረው በሳይቤሪያ የሚገኙትን በመንግሥቱ አገልግሎት በታማኝነት እየተካፈሉ ያሉትን ውድ ዘመዶቻችንንና ወዳጆቻችንን እናስታውሳለን። ዛሬ ትልልቅ ስብሰባዎች በዚያ የሚደረጉ ሲሆን በኢርኩትስክና በአካባቢው 2,000 የሚሆኑ ንቁ ምሥክሮች አሉ። በእርግጥም “ታናሹ ለሺህ የሁሉም ታናሹ ለብርቱ ሕዝብ ይሆናል” የሚለው በኢሳይያስ 60:22 ላይ የሚገኘው ትንቢት በዚያ የዓለም ክፍልም ፍጻሜውን እያገኘ ነው።
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1959 በኢርኩትስክ ከአባቴ፣ ከቤተሰቦቼና ከሌሎች ግዞተኞች ጋር
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በኢስክራ በግዞት የነበሩ ልጆች
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በተጋባንበት ዓመት
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአሁኑ ወቅት ከማሪያ ጋር