ከሳንባ ነቀርሳ ጋር ለሚደረገው ፍልሚያ የተቀየሰ አዲስ ስልት
ሳንባ ነቀርሳ (TB) ለብዙ ዘመናት የሰውን ሕይወት ለሕልፈት ሲዳርግ የቆየ ተላላፊ በሽታ ከመሆኑም ሌላ ይህ ስጋት አሁንም ቢሆን ስላልተወገደ የዓለም የጤና ድርጅት ጊዜውን ጠብቆ ከሚፈነዳ ፈንጂ ጋር አመሳስሎታል። የዓለም የጤና ድርጅት ስለ ሳንባ ነቀርሳ ያወጣው ሪፖርት “ከጊዜ ጋር እሽቅድድም ይዘናል” በማለት ያስጠነቅቃል። የሰው ልጅ ይህንን ፈንጂ ማምከን ከተሳነው “በትንፋሽ ከሚዛመትና እንደ ኤድስ መፍትሔ ከሌለው” መድኃኒቶችን ከተለማመደ በሽታ ጋር የሚፋጠጥበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። የዓለም የጤና ድርጅት ሳንባ ነቀርሳ ሊያስከትል የሚችለውን አስከፊ ውጤት ለማስተዋል ዓይናችንን የምንገልጥበት ጊዜ አሁን ነው ሲል አጥብቆ አሳስቧል። “በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኝ እስትንፋስ ያለው ሰው ሁሉ . . . ይህ አደጋ ሊያሳስበው ይገባል።”
ይህ አባባል ተጋንኗልን? በፍጹም። እስቲ አስበው አንድ በሽታ ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ እንደ ካናዳ ያለን የአንድ አገር ሕዝብ በአሥር ዓመታት ውስጥ ሙልጭ አድርጎ ሊያጠፋ ይችላል ቢባል ጉዳዩ ምን ያህል የዓለምን ትኩረት ይስብ ነበር! ይህ የማይመስል ነገር ሆኖ ሊታይ ቢችልም አደጋው በተጨባጭ አንዣብቦ ይገኛል። በዓለም ዙሪያ ሳንባ ነቀርሳ ሕይወታቸውን የሚቀጥፈው ሰዎች ቁጥር ኤድስ፣ ወባ እና የቆላ በሽታዎች በአንድ ላይ ተዳምረው ከሚፈጁዋቸው ሰዎች ቁጥር የሚበልጥ ሲሆን በዚህ በሽታ በየዕለቱ 8,000 ሰዎች ይሞታሉ። በአሁኑ ጊዜ በሳንባ ነቀርሳ በሽታ እየተሰቃዩ ያሉ 20 ሚልዮን ሰዎች ሲኖሩ በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ውስጥ ደግሞ እስከ 30 ሚልዮን የሚደርሱ ሰዎች ሊሞቱ ይችላሉ። ይህ ደግሞ ከካናዳ ነዋሪዎች የሚበልጥ ቁጥር ነው።—ገጽ 24 ላይ የሚገኘውን “የሳንባ ነቀርሳ ዓለም አቀፍ ስርጭት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
የምሥራች
ይሁን እንጂ ዛሬ ተስፋ ሰጭ ነገር ተገኝቷል። ከአሥር ዓመታት ሙከራ በኋላ ተመራማሪዎች ሃይ የሚለው አጥቶ ሕይወት ሲቀጥፍ የኖረውን ሳንባ ነቀርሳ በቁጥጥር ሥር ለማዋል የሚያስችል ስትራቴጂ ቀይሰዋል። የቀድሞው የዓለም የጤና ድርጅት ዲሬክተር ዶክተር ሂሮሺ ናካጂማ ይህን አዲስ ስትራቴጂ “በዚህ አሥር ዓመት ውስጥ በጤናው መስክ ከታዩት እመርታዎች መካከል ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነው” ብለውታል። በዓለም ጤና ድርጅት የዓለም አቀፉ የሳንባ ነቀርሳ ፕሮግራም ዲሬክተር የሆኑት ዶክተር አራታ ኮቺ ደግሞ “የሳንባ ነቀርሳን ወረርሽኝ ለማንበርከክ” ፈር የቀደደ እርምጃ ነው ብለውታል። ለዚህ ሁሉ ደስታ ምክንያቱ ምንድን ነው? ዶትስ (DOTS) የተባለው የሕክምና ዘዴ ነው።
ዶትስ የአጭር ጊዜ የቅርብ ክትትል ሕክምናን (directly observed treatment, short- course) የሚያመለክት ምህጻረ ቃል ነው። ይህ የሳንባ ነቀርሳ በሽተኞች አንድም ቀን ሆስፒታል መተኛት ሳያስፈልጋቸው ከስድስት እስከ ስምንት ወር በሚደርስ ጊዜ ውስጥ እንዲፈወሱ ለማድረግ የሚያስችል የሕክምና ዘዴ ነው። ዶትስ ስኬታማ እንዲሆን አምስት ነገሮች መሟላት አለባቸው። የዓለም የጤና ድርጅት እንዳለው ከእነዚህ ነገሮች መካከል የትኛውም ከጎደለ የሳንባ ነቀርሳ ሰለባዎችን ለማዳን የመቻላችን ሁኔታ “ከእጃችን ሾልኮ ይጠፋል።” እነዚህ አምስት ነገሮች ምንድን ናቸው?
● 1. የቅርብ:- በጣም አደገኛ የሆነው የሳንባ ነቀርሳ ዓይነት በሕክምና ምርመራ የማይገኘው ነው። በመሆኑም የጤና ሠራተኞች በማኅበረሰባቸው ውስጥ ያሉትን የተላላፊ ሳንባ ነቀርሳ ሕሙማን ለይተው በማግኘት ላይ እንዲያተኩሩ የዓለም የጤና ድርጅት አጥብቆ አሳስቧል።
● 2. ክትትል:- ሁለተኛው የዶትስ መርኅ የበሽተኛው ፈውስ በራሱ በታማሚው ላይ ሳይሆን በጤና ተቋማት ጫንቃ ላይ እንዲያርፍ ማድረግ ነው። የጤና ጣቢያ ሠራተኞች ወይም ሥልጠና ያገኙ እንደ ሱቅ ሠራተኛ፣ መምህር ወይም የቀድሞ የሳንባ ነቀርሳ ሕሙማን ያሉ ፈቃደኞች ታማሚው በየቀኑ የተመደበለትን እያንዳንዱን መድኃኒት መውሰዱን ይከታተላሉ። ‘ታማሚውን የሚከታተሉት’ ሰዎች ለሕክምናው ስኬታማነት የሚኖራቸው ድርሻ በቀላሉ የሚገመት አይደለም። ምክንያቱም ሳንባ ነቀርሳ እስከ ዛሬ ድረስ የዘለቀበት አንዱ ምክንያት ሕሙማኑ መድኃኒቱን ቶሎ ስለሚያቋርጡ ነው። (በገጽ 24 ላይ የሚገኘውን “በማገርሸት ላይ የሚገኘው ለምንድን ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ለጥቂት ሳምንታት ብቻ መድኃኒቱን ከወሰዱ በኋላ እንደተሻላቸው ስለሚሰማቸው እንክብሎቹን መውሰድ ያቆማሉ። ይሁንና የሳንባ ነቀርሳውን ባሲለሶች ከሰውነት ውስጥ ጨርሶ ለማስወገድ መድኃኒቱ ከስድስት እስከ ስምንት ወር ድረስ መወሰድ ይኖርበታል።
● 3. ሕክምና:- በእነዚህ ስድስትና ስምንት ወራት ውስጥ የጤና ሠራተኞች የሕክምናውን ውጤት በመከታተል ታማሚው ያሳየውን መሻሻል ይመዘግባሉ። በዚህ መልኩ ሕሙማኑ ሙሉ በሙሉ መዳናቸውንና በሽታውን ለሌሎች የማያስተላልፉ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይችላሉ።
● 4. የአጭር ጊዜ:- የአጭር ጊዜ ኬሚፈውስ (chemotherapy) በመባል የሚታወቁትን የፀረ ሳንባ ነቀርሳ መድኃኒቶች በትክክለኛው ዓይነትና መጠን ለተባለው ያህል ጊዜ መውሰድ የዶትስ ስትራቴጂ አራተኛው መርኅ ነው። እነዚህ በተጣማጅነት የሚወሰዱ መድኃኒቶች የሳንባ ነቀርሳውን ባሲለሶች ለመግደል የሚያስችል አቅም አላቸው።a ሕክምናው በፍጹም መቋረጥ ስለሌለበት በቂ መጠን ያለው መድኃኒት ሊኖር ይገባል።
● 5. !:- የዓለም የጤና ድርጅት የዶትስን ስትራቴጂ አምስተኛ መርኅ በቃል አጋኖ ምልክት ወክሎታል! ይህም የገንዘብ አጠቃቀምንና ቀና ፖሊሲዎችን የሚያመለክት ነው። የዓለም የጤና ድርጅት የጤና ተቋማት ከመንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የሚመደበውን ገንዘብ በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲያውሉና የሳንባ ነቀርሳ ሕክምናን የየአገራቸው የጤና መርኃ ግብር አካል እንዲያደርጉት አጥብቆ ያሳስባል።
በገንዘብ አጠቃቀም ረገድ የዶትስ ፖሊሲ የገንዘብ ካዝናውን ለያዙት ፖሊሲ አውጪዎች የሚወደድ ሆኖላቸዋል። የዓለም ባንክ፣ ዶትስ “በሽታን . . . በመከላከል ረገድ እጅግ ገንዘብ ቆጣቢ ከሆኑት ዘዴዎች አንዱ ነው” ብሎታል። የዓለም የጤና ድርጅት እንዳወጣው ስሌት ከሆነ በድሃ አገሮች ውስጥ ይህን ስትራቴጂ ለመጠቀም የሚያስፈልገው የነፍስ ወከፍ ጠቅላላ ወጪ 100 የአሜሪካ ዶላር ነው። “አልፎ አልፎ ይህ ስሌት በታዳጊ አገሮች ውስጥ በነፍስ ወከፍ ከአሥር ሣንቲም በላይ (ዩኤስ) የሚደርስ ሲሆን እጅግ የከፋ የኢኮኖሚ ሁኔታ ባለባቸው ቦታዎች እንኳ ይህንን ወጭ መሸፈን ከባድ አይሆንም።” ይሁን እንጂ ክፍያው ዝቅተኛ ሆነ ማለት ውጤታማነቱ አነስተኛ ነው ማለት አይደለም።
ምን ያህል ውጤታማ ነው?
በመጋቢት 1997 አንድ የዓለም የጤና ድርጅት ተወካይ የዶትስ ስትራቴጂ በተወሰነ መጠን ጥቅም ላይ መዋሉ “በአሥር ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለም አቀፉ የሳንባ ነቀርሳ ወረርሽኝ ረገብ እንዲል አድርጓል” ሲሉ አስታውቀዋል። “ዶትስ ጥቅም ላይ በዋለባቸው አካባቢዎች ሁሉ ፈውሱ ወደ እጥፍ በሚጠጋ መጠን አድጓል።” ሳንባ ነቀርሳ በስፋት በተዛመተባቸው አካባቢዎች የተካሄዱት የዶትስ የሙከራ ፕሮጄክቶች እንኳ ስትራቴጂው ግቡን እንደመታ ያሳያሉ። የዓለም የጤና ድርጅት የጠቀሳቸውን የስትራቴጂውን ስኬት የሚጠቁሙ ጥቂት ምሳሌዎች ተመልከት።
ሕንድ ውስጥ “ዶትስ 12 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች ያሉበትን ክልል በሚሸፍኑ የሙከራ ጣቢያዎች ውስጥ ተሠርቶበታል። . . . በአሁኑ ጊዜ ከአምስት በሽተኞች አራቱ ከሳንባ ነቀርሳ ነፃ ሆነዋል።” በባንግላዴሽ አንድ ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎችን ባቀፈ የሙከራ ፕሮግራም “[ከሳንባ ነቀርሳ ሕሙማኑ] 87 በመቶ የሚያክሉት ተፈውሰዋል።” በአንድ የኢንዶኔዥያ ደሴት ደግሞ የዶትስ ፕሮጄክት “በበሽታው ከተለከፉት አሥር ሰዎች መካከል ዘጠኙን እያዳነ ነው።” በቻይና የተካሄዱ የሙከራ ፕሮጄክቶች 94 በመቶ የሚያክሉትን በመፈወስ “አስገራሚ ውጤት” አስመዝግበዋል። በአንድ የደቡብ አፍሪካ ከተማ “[ከሳንባ ነቀርሳ ሕሙማኑ መካከል] ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት ስኬታማ በሆነ መንገድ ሕክምና አግኝተዋል።” ዶትስ በቅርቡም በኒው ዮርክ ከተማ ተጀምሮ አስገራሚ ውጤት እያስገኘ ነው።
ዶክተር ኮቺ ይህ ስትራቴጂ “በየትኛውም ቦታ ሊሠራበትና 85 በመቶና ከዚያም በላይ ፈውስ ሊያስገኝ እንደሚችል” በበርካታ አገሮች የተካሄደው የመስክ ሙከራ አረጋግጧል ሲሉ ደምድመዋል።
እጅግ የሚጋነን ባይሆንም ትልቅ መሻሻል ታይቷል
የሰውን ልጅ እንደ ቅጠል ከሚያረግፉት ተላላፊ በሽታዎች አንዱ የሆነውን ይህን በሽታ ድል ሊያደርግ የሚችለውና ብዙም ወጪ የማይጠይቀው ይህ የዶትስ ስትራቴጂ በፍጥነት እየተስፋፋ መሆን አለበት ብለህ መጠበቅህ አይቀርም። “ይሁንና” ይላሉ አንድ የዓለም የጤና ድርጅት ባለ ሥልጣን “ፍቱንነቱ የተረጋገጠለትንና ገንዘብ ቆጣቢ የሆነውን ይህን የዓለም የጤና ድርጅት የሳንባ ነቀርሳ መቆጣጠሪያ ስትራቴጂ ተግባራዊ ያደረጉት አገሮች ጥቂት መሆናቸው ያስገርማል።” እንዲያውም በ1996 መጀመሪያ ላይ በአገር አቀፍ ደረጃ ይህን ስትራቴጂ ተግባራዊ ያደረጉት አገሮች 34 ብቻ ነበሩ።
የሆነ ሆኖ መሻሻል ይታያል። በ1993 የዓለም የጤና ድርጅት ዓለም አቀፍ የሳንባ ነቀርሳ መከላከያ አስቸኳይ አዋጅ ከማውጣቱ አስቀድሞ ከ50 የሳንባ ነቀርሳ በሽተኞች መካከል የዶትስ ሕክምና ያገኘው አንዱ ብቻ ነበር። ዛሬ ይህ ቁጥር ከ10 አንድ ሆኗል። በ1998 ወደ 96 የሚደርሱ አገሮች የዶትስን ስትራቴጂ እንደተጠቀሙ ሪፖርት ተደርጓል። ተጨማሪ አገሮች የዶትስን ስትራቴጂ ተቀብለው ተግባራዊ ካደረጉ የሳንባ ነቀርሳ በሽተኞች ዓመታዊ ቁጥር ‘በአሥር ዓመት ውስጥ ብቻ በግማሽ ይቀንሳል።’ ዶክተር ኮቺ “ፍቱን መሆኑ የተመሠከረለት የጤና አጠባበቅ ዘዴ አግኝተናል። የቀረው ነገር በስፋት ጥቅም ላይ ማዋል ብቻ ነው” ብለዋል።
የሰው ልጅ ሳንባ ነቀርሳን በተሳካ መንገድ ለመዋጋት የሚያስፈልገው እውቀቱም ሆነ መሣሪያው አለው። የታጣው ‘እነዚህ መድኃኒቶች በዓለም ዙሪያ ጥቅም ላይ መዋላቸውን የሚከታተል ብቻ ነው።’ የዓለም የጤና ድርጅት ለሐኪሞችና ለሌሎች የጤና ሠራተኞች በሙሉ ባሠራጨው ጽሑፍ ላይ “ምንድን ነው የምንጠብቀው?” ብሎ መጠየቁ ምንም አያስገርምም።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a መድኃኒቶቹ አይሰናይዘድ፣ ራይፋምፒን፣ ፒራዛይናሚድ፣ ስትሬፕተማይሲን እና ኤታምቢውቶልን ይጨምራሉ።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
በእያንዳንዷ ሴኮንድ በምድራችን ላይ የሚኖር አንድ ሰው በሳንባ ነቀርሳ ይለከፋል
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
‘ሕይወት አድን መድኃኒቶች መደርደሪያ ላይ ተቀምጠው በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ይቀጠፋል’—ዶክተር አራታ ኮቺ
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“የዶትስ ስትራቴጂ በዚህ አሥርተ ዓመት ውስጥ የታየ ከሁሉ የላቀ የሕክምና እመርታ ሆኗል።”—የዓለም የጤና ድርጅት ጋዜጣዊ መግለጫ
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በማገርሸት ላይ ያለው ለምንድን ነው?
ሳንባ ነቀርሳ (TB) ፈውስ ከተገኘለት አራት አሥርተ ዓመታት አልፈዋል። ሆኖም ከዚያ ወዲህ ከ120 ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎች በሳንባ ነቀርሳ ሲሞቱ 3 ሚልዮን የሚያክሉ ደግሞ በዚህ ዓመት ይሞታሉ። በሽታው ፈውስ ያለው ሆኖ ሳለ ይህን ያህል ሰዎች በሳንባ ነቀርሳ የሚሞቱት ለምንድን ነው? በሦስት ዋና ዋና ምክንያቶች ሲሆን እነዚህም ቸልተኝነት፣ ኤች አይ ቪ/ኤድስ እንዲሁም መድኃኒቶችን የተላመደ ሳንባ ነቀርሳ ናቸው።
ቸልተኝነት። ዓለም ያተኮረው እንደ ኤድስና ኢቦላ ባሉት ተላላፊ በሽታዎች ላይ ነው። ይሁን እንጂ በ1995 በኢቦላ እና በሳንባ ነቀርሳ የሞቱትን ሰዎች ቁጥር ስናነጻጽር በኢቦላ አንድ ሰው ሲሞት በሳንባ ነቀርሳ 12,000 ሰዎች ያልቁ ነበር። እርግጥ ሳንባ ነቀርሳ በታዳጊ አገሮች የተለመደ በሽታ ከመሆኑ የተነሣ ሰዎች ያለ ነገር አድርገው ተቀብለውታል። በበለጸጉት አገሮች ደግሞ በሽታውን ለማዳን የሚችሉ ፍቱን መድኃኒቶች መደርደሪያዎች ላይ ተቀምጠው በሽታው እንዲስፋፋ ተፈቅዶለታል። እንዲህ ያለው ዓለም አቀፍ ቸልተኝነት የብዙዎችን ሕይወት ለሕልፈት የሚዳርግ ትልቅ ስህተት መሆኑ ታይቷል። ዓለም ለሳንባ ነቀርሳ የሰጠው ትኩረት ቀንሶ ሳለ የሳንባ ነቀርሳው ባሲለሶች ይበልጥ እየተጠናከሩ ሄደዋል። ዛሬ በሰው ዘር ታሪክ ታይቶ በማያውቅ መጠን በብዙ አገሮች ብዙ ሰዎችን እያጠቁ ነው።
ኤች አይ ቪ/ኤድስ። ሳንባ ነቀርሳ የኤች አይ ቪና የኤድስ የጉዞ ጓደኛ ሆኗል። ሰዎች የሰውነታቸውን በሽታ የመከላከል አቅም በሚያዳክመው ኤች አይ ቪ ቫይረስ ሲለከፉ በሳንባ ነቀርሳ የመያዝ አጋጣሚያቸው በ30 እጥፍ ይጨምራል። በአሁኑ ጊዜ ያለው የኤች አይ ቪ ወረርሽኝ የሳንባ ነቀርሳ በሽተኞች ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉ ምንም አያስገርምም! በ1997 የኤች አይ ቪ ቫይረስ ከነበረባቸው መካከል በሳንባ ነቀርሳ የሞቱት 266,000 ሰዎች እንደሆኑ ይገመታል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኤች አይ ቪ/ኤድስ ፕሮግራም ዲሬክተር የሆኑት ፒተር ፒዮት “እነዚህ ከያዛቸው ሳንባ ነቀርሳ ለመገላገል የሚያስችላቸውን አነስተኛ ዋጋ ያለው የፀረ ሳንባ ነቀርሳ መድኃኒት ለማግኘት ያልታደሉት ሰዎች ናቸው” ብለዋል።
መድኃኒቶችን የተላመደ ሳንባ ነቀርሳ። የሰውን የአንቲባዮቲክ ጥቃት የሚቋቋሙ “መድኃኒቶችን የተላመዱ ሚክሮቦች (Superbugs)” በሳይንስ ነክ ልብ ወለዶች ውስጥ ብቻ የሚነገሩ ነገሮች ነበሩ። በሳንባ ነቀርሳ ረገድ ግን እነዚህ ነገሮች በፍጥነት እውነት እየሆኑ መጥተዋል። እስካሁን ድረስ ከ50 ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎች መድኃኒቶችን በተላመደው (MDR) የሳንባ ነቀርሳ ዓይነት ሳይለከፉ አልቀሩም። እንደተሻላቸው ስለተሰማቸው፣ መድኃኒት በማለቁ ወይም ሕመሙ በኅብረተሰቡ ውስጥ የሚያሳፍር በመሆኑ መድኃኒቱን ጥቂት ሳምንታት ብቻ ወስደው የሚያቆሙ ሕሙማን በሰውነታቸው ውስጥ ያሉትን የሳንባ ነቀርሳ ባሲለሶች ሁሉ ሳይገድሏቸው ይቀራሉ። ለምሳሌ ያህል በአንዲት የእስያ አገር ከሦስት የሳንባ ነቀርሳ ሕሙማን መካከል ሁለቱ ሕክምናቸውን ያለጊዜው ያቆማሉ። ሳይጠፉ የቀሩት ባክቴሪያዎች በሰውነታቸው ውስጥ የቀረውን የፀረ ሳንባ ነቀርሳ መድኃኒት ሁሉ ተዋግተው ስለሚያሸንፉት እነዚህ ሰዎች እንደገና በሚታመሙበት ጊዜ በሽታውን ለማዳን ይበልጥ አስቸጋሪ ይሆናል። ከዚህ የተነሣ ታማሚው ራሱ ያለበት ሳንባ ነቀርሳም ሆነ እርሱ የሚያስተላልፍባቸው ሰዎች የሚይዛቸው ሳንባ ነቀርሳ መድኃኒት የማይበግረው ሆኖ ቁጭ ይላል። ይህ ኤምዲአር የሚባለው ጋኔን አንዴ ከተለቀቀ ደግሞ የሰው ልጅ በቁጥጥሩ ሥር ሊያውለው ይችል ይሆን? የሚለው አስፈሪ ጥያቄ ይጋረጥብናል።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የሳንባ ነቀርሳ ዓለም አቀፍ ስርጭት
የሳንባ ነቀርሳ (TB) ወረርሽኝ ስርጭት፣ የሚጠይቀው ወጪና የሚቀጥፈው ሕይወት ከዓመት ዓመት እየጨመረ ሄዷል። የዓለም የጤና ድርጅት ያሰባሰባቸው ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት ድምጹን አጥፍቶ ሰው የሚፈጀው ይህ በሽታ በመስፋፋት ላይ ነው። አንዳንድ ምሳሌዎች እነሆ:- “ፓኪስታን ከሳንባ ነቀርሳ ጋር በሚደረገው ውጊያ እጁዋን ሰጥታለች።” “ሳንባ ነቀርሳ በታይላንድ የመልሶ ማጥቃት እርምጃ እየወሰደ ነው።” “ዛሬ ብራዚል ውስጥ ሳንባ ነቀርሳ ለጤና እክልና ሞት ምክንያት ከሆኑት ግንባር ቀደም ችግሮች አንዱ ሆኗል።” “የሳንባ ነቀርሳ ችግር የሜክሲኮን ሕዝብ ቀስፎ ይዞታል።” በሩሲያ “የሳንባ ነቀርሳ ሕሙማን ቁጥር በፍጥነት እያሻቀበ ነው።” በኢትዮጵያ “ሳንባ ነቀርሳ በመላ አገሪቱ በከፍተኛ መጠን ተስፋፍቷል።” “ደቡብ አፍሪካ በዓለም ላይ ሳንባ ነቀርሳ በከፍተኛ መጠን ከሚታይባቸው አገሮች አንዷ ሆናለች።”
በዓለም ላይ ከሚኖሩት 100 የሳንባ ነቀርሳ በሽተኞች መካከል 95ቱ የሚኖሩት ድሃ በሚባሉት አገሮች ውስጥ ቢሆንም በሽታው በበለጸጉት አገሮችም እየተስፋፋ ነው። በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ በዩናይትድ ስቴትስም የሳንባ ነቀርሳ ሕሙማን እንደሆኑ ሪፖርት የተደረገው ሰዎች ቁጥር ፈጣን ጭማሪ አሳይቷል። የዩናይትድ ስቴትሷ ጋዜጠኛ ቫለሪ ጋርትሴፍ “ሳንባ ነቀርሳ ዳግም አሜሪካውያንን ማሸበር ይዟል” ብላለች። በተመሳሳይም የኔዘርላንድ የሳንባ ነቀርሳ ማኅበር ዲሬክተር የሆኑት ዶክተር ያፕ ብሩክማንስ የሳንባ ነቀርሳ ወረርሽኝ “በምሥራቅ አውሮፓና በምዕራብ አውሮፓ አንዳንድ ክፍሎች እየከፋ” መሄዱን ተናግረዋል። ሳይንስ የተባለው መጽሔት የነሐሴ 22, 1997 እትም “ሳንባ ነቀርሳ ግንባር ቀደም የጤና ችግር ሆኖ ይቀጥላል” ማለቱ ምንም አያስገርምም።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የሳንባ ነቀርሳ ንድፍ ተገኘ
ተመራማሪዎች በቅርቡ የሳንባ ነቀርሳ ባክቴሪየምን ጀነቲካዊ ንድፍ ዝርዝር ማግኘት ችለዋል። ለንደን በሚገኘው ኢምፔሪያል ኮሌጅ ስኩል ኦቭ ሜድሲን የሚሠሩት ዶክተር ዳግላስ ያንግ ይህ “ከሰው ልጅ ቀንደኛ ጠላት ጋር ለሚደረገው ውጊያ አዲስ ምዕራፍ ከፋች ነው” ብለዋል። የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለው ከሆነ ይህ ግኝት “ወደፊት የፀረ ሳንባ ነቀርሳ መድኃኒትና ክትባት ለማግኘት ለሚደረገው ጥረት ይህ ነው የማይባል ድርሻ ያበረክታል።”—ዘ ቲቢ ትሪትመንት ኦብዘርቨር፣ መስከረም 15, 1998
[በገጽ 25 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
እነዚህ መድኃኒቶች ተቀናጅተው የሳንባ ነቀርሳን ባሲለሶች መግደል ይችላሉ
[ምንጮች]
Photo supplied by WHO, Geneva
Photo: WHO/Thierry Falise
[በገጽ 26 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
አንድን በሽተኛ ለማዳን 100 የአሜሪካ ዶላር ያስፈልጋል
[ምንጮች]
Photo: WHO/Thierry Falise
Photo supplied by WHO, Geneva
[በገጽ 23 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]
Photo: WHO/Thierry Falise
Photo supplied by WHO, Geneva
Photo: WHO/Thierry Falise