የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g99 8/8 ገጽ 18-19
  • ፀሐይ አፍቃሪዎች ለቆዳችሁ ጥንቃቄ አድርጉ!

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ፀሐይ አፍቃሪዎች ለቆዳችሁ ጥንቃቄ አድርጉ!
  • ንቁ!—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ምን ማድረግ ትችላለህ?
  • ለረጅም ጊዜ ለፀሐይ መጋለጥህ ሊያሳስብህ ይገባል?
    ንቁ!—2009
  • በቆዳ ቀለምህ ደስተኛ ሁን
    ንቁ!—2010
  • የእባብ ቆዳ
    ንቁ!—2014
  • በአቍማዳ ውስጥ ያለ እንባ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2008
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1999
g99 8/8 ገጽ 18-19

ፀሐይ አፍቃሪዎች ለቆዳችሁ ጥንቃቄ አድርጉ!

ብራዚል የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው

የዕረፍት ጊዜህን በባሕር ዳርቻ እየተዝናናህ ማሳለፍ ትወዳለህ? ተራራ መውጣትስ ትወዳለህ? የምትወድ ከሆነ ከቤት ውጭ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መካፈል ከሚያስደስታቸው በሚልዮን ከሚቆጠሩ ሰዎች መካከል አንተም ትገኝበታለህ ማለት ነው። ይሁን እንጂ ጥንቃቄ ልታደርግበት የሚገባ አንድ ጉዳይ አለ:- በእነዚህ እንቅስቃሴዎች ብዙ ጊዜ ማሳለፍ ማለት ለፀሐይ ይበልጥ መጋለጥ ማለት ነው። ይህ የሚያስከትለው ጉዳት ይኖራል? ጉዳት ካለውስ ራስህን መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው?

“ቆዳህ ትልቁና ከሌሎቹ የሰውነትህ አባላካላት ይበልጥ ለእይታ የተጋለጠ የሰውነትህ ክፍል ነው” በማለት ዶክተር ደብሊው ሚቸል ሳምስ ጁንየር ጽፈዋል። ቆዳህ የሰውነትህ ፈሳሽ እንዳያልቅ ከመከላከሉም በላይ ሙቀት ይሰጥሃል። ቅዝቃዜን፣ ሙቀትን፣ ሕመምንና ንዝረትን እንዲሁም ሻካራና ለስላሳ ነገሮችን ለመለየት ይረዳሃል። እንዲሁም ቆዳህ ለአጥንት ግንባታ ወሳኝ የሆነውን ቫይታሚን ዲ በማዘጋጀት ረገድ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። ቫይታሚን ዲ የሚዘጋጀው ደግሞ በፀሐይ ብርሃን እርዳታ ነው።

ይሁን እንጂ ቆዳን ለፀሐይ ብርሃን ከሚገባው በላይ ማጋለጥ የሚያስከትለው አደጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። ወደ ምድር ገጽ የሚደርሰው የፀሐይ ጨረር ታህተቀይ እና የሚታይ ብርሃንን በውስጡ የያዘ ሲሆን በኤ እና በቢ ፈርጆች (ዩ ቪ ኤ እና ዩ ቪ ቢ) የተከፈለው ልእለ ሃምራዊ ብርሃንም ይገኝበታል። ደስ የሚለው ግን ከባቢ አየር ፀሐይ የምታመነጫቸውን ኮስማዊ ጨረሮች፣ የጋማ ጨረሮችና ኤክስሬይዎች ውጦ ያስቀራቸዋል። የከባቢ አየር ኦዞን ንብር ልእለ ሃምራዊ ሲ ጨረርን (ዩ ቪ ሲ) ሙሉ በሙሉ እዚያው የሚያስቀር ከመሆኑም በላይ አብዛኞቹን የዩ ቪ ኤ እና የዩ ቪ ቢ ጨረሮች አጣርቶ ያስቀራቸዋል። የሚያሳዝነው ግን ይህ የኦዞን ንብር ጉዳት እየደረሰበት ያለ መሆኑ ነው። ብዙ ሳይንቲስቶች የተወሰኑ አቀዝቃዥ ንጥረ ነገሮችና (refrigerants) የጋዝ ብናኞች ለችግሩ መንስኤ እንደሆኑ ይናገራሉ። መንስኤው ምንም ይሁን ምን ለፀሐይ መጋለጥ ለጤንነት ይበልጥ አደገኛ እየሆነ መጥቷል።

ልእለ ሃምራዊ ጨረር ቆዳህን ከመጥበሱም በላይ በቆዳህ ላይ ቡናማ ቀለም ያላቸው ነጠብጣቦች እንዲፈጠሩ ያደርጋል። በተጨማሪም ቆዳህ እያደር እየወፈረና እየደረቀ እንዲሄድ ያደርገዋል። ከዚህም ሌላ ልእለ ሃምራዊ ጨረር የቆዳህን የመለጠጥ አቅም በማዳከም ያለ ዕድሜ ማርጀትና የቆዳ መሸብሸብ ያስከትላል። ከሁሉም የከፋው ግን ከመጠን በላይ ለልእለ ሃምራዊ ጨረር መጋለጥ ሰውነትህ በሽታ የመከላከል አቅሙን እንዲያጣና ቆዳህ ቆስሎ በካንሰር እንዲያዝ ሊያደርግ የሚችል መሆኑ ነው። በዚህ ላይ ደግሞ የተጎዳ ወይም በበሽታ የተጠቃ ቆዳ መልክህን ሊያበላሽና ከዚያም አልፎ የመረበሽ ስሜትና የመንፈስ ጭንቀት ሊያስከትልብህ ይችላል።

ምን ማድረግ ትችላለህ?

የፀሐይ ትኩሳት በሚያይልበት ሰዓት እንደምታደርገው ለቆዳህ በየዕለቱ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባሃል። ምን ማድረግ ትችላለህ? ፀሐይ የሚከላከሉ ልብሶች ከማድረግና ለፀሐይ የምትጋለጥበትን የጊዜ ርዝመት ውስን ከማድረግም በተጨማሪ የፀሐይን ጨረር የሚከላከል የቆዳ ቅባት መጠቀም እንደሚረዳ የሚናገሩ ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክር ልትከተል ትችላለህ። ውጤታማ የሆነ የቆዳ ቅባት ልትመርጥ የምትችለው እንዴት ነው? ፋብሪካው ኤስ ፒ ኤፍ በሚል ያሰፈረውን ቅባቱ ያለውን ጨረር የመከላከል ኃይል የሚያመለክት መግለጫ ተመልከት። መግለጫው ላይ የተጠቀሰው ቁጥር እየጨመረ በሄደ መጠን ቅባቱ የመከላከል አቅሙ የዚያኑ ያህል ከፍተኛ ይሆናል። ነጣ ያለ ቆዳ ያላቸው ሰዎች ጠቆር ያለ የቆዳ ቀለም ካላቸው ሰዎች የበለጠ ከፍተኛ የመከላከል አቅም ያለው ቅባት መጠቀም ይኖርባቸዋል። እዚህ ላይ ልብ ልትለው የሚገባ አንድ ጉዳይ አለ:- ኤስ ፒ ኤፍ በሚል የተሰጠው መግለጫ ቅባቱ የዩ ቪ ቢ ጨረሮችን በመከላከል ረገድ ያለውን አቅም ብቻ የሚያመለክት ነው። ስለዚህ ዩ ቪ ኤ ጨረርን ጨምሮ ሌሎች በርካታ የጨረር ዓይነቶችን የመከላከል አቅም ያላቸው ቅባቶች ብትጠቀም የተሻለ ይሆናል።

ልጆች በተለይ ደግሞ ነጣ ያለ ቆዳ ያላቸው ከሆኑ በቀላሉ ፀሐይ ይጎዳቸዋል። ከዚህም በላይ ብዙውን ጊዜ ልጆች ከአዋቂዎች ይበልጥ ለፀሐይ ብርሃን የተጋለጡ ናቸው በማለት ፎቱፕሮቴሳው የተባለ ጽሑፍ ተናግሯል። በመጀመሪያዎቹ 18 ዓመታት የልጅህን ቆዳ ከፀሐይ ለመጠበቅ አንዳንድ እርምጃዎች መውሰድህ ልጅህ በቆዳ ካንሰር የመያዙን ዕድል በእጅጉ ሊቀንሰው ይችላል በማለት ፎቱፕሮቴሳው ገልጿል።

ሕይወት በምድር ላይ እንዲኖር የፀሐይ ብርሃን የግድ አስፈላጊ ነው። ፍንትው ብላ በወጣች ፀሐይ የማይደሰት ማን አለ? ሆኖም ቡናማ የቆዳ ቀለም የቁንጅናና የወጣትነት ተምሳሌት እንደሆነ አድርገው በሚያሳዩ ውብ ምስሎች አትታለል! ከልክ በላይ ለፀሐይ ከመጋለጥ በመታቀብ ቆዳህን ብሎም ጤንነትህን ጠብቅ።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ቆዳህን ከጉዳት ጠብቅ!

1. በተለይ የፀሐይ ጨረር በሚያይልበት ከ4:00 ሰዓት እስከ 10:00 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ ራስህን ከፀሐይ ጠብቅ።

2. ሌላው ቀርቶ ደመናማ በሆኑ ቀናት ከዩ ቪ ኤ እና ከዩ ቪ ቢ ጨረሮች የሚከላከልና የኤስ ፒ ኤፍ መጠኑ 15 ወይም ከዚያ በላይ የሆነ የቆዳ ቅባት ተጠቀም።

3. ከቤት ውጭ በምትሆንበት በተለይ ደግሞ በምትዋኝበት ወይም በሚያልብህ ጊዜ በየሁለት ሰዓቱ ጨረር መከላከያ ቅባት ተቀባ።

4. የፀሐይን ጨረር የሚከላከሉና ብርሃን የማያሳልፉ ልብሶች ልበስ። ጠቆር ያለ ቀለም ያላቸው ልብሶች ይበልጥ የመከላከል ጠባይ አላቸው።

5. ቢያንስ ቢያንስ አሥር ሳንቲ ሜትር የሚደርስ ክፈፍ ያለው ባርኔጣና ልእለ ሃምራዊ ጨረር የሚከላከል ሌንስ ያለው የዓይን መነጽር አድርግ።

6. በተቻለ መጠን ጥላ ሥር ሁን።

7. አብዛኞቹን ጎጂ የፀሐይ ጨረሮች ከሚያንጸባርቁ እንደ ውኃ፣ አሸዋና በረዶ ካሉ ብርሃን አንጸባራቂ አካላት ራቅ።

[ምንጭ]

(በአሜሪካ የቆዳ ጥናት አካዳሚ ከተዘጋጀው ስኪን ሳቪ ከተባለው ጽሑፍ የተወሰደ)

[በገጽ 19 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ቆዳህን ከፀሐይ በመጋረድ ጤንነትህንና መልክህን ጠብቅ

የፀሐይን ብርሃን የሚያንጸባርቁ አካላት ባሉበት አካባቢ ተጨማሪ ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ ነው

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ