ዓለም አቀፋዊ የጠፈር ጣቢያ፣ ምድርን የሚዞር ቤተ ሙከራ
ከሁለት ዓመት ገደማ በኋላ ጥርት ባለ የምሽት ሰማይ ወደ ላይ አንጋጠህ ስትመለከት ከዋክብትንና ጨረቃን ብቻ ሳይሆን የፕላኔቶችን ያህል የሚያበራ ሰው ሠራሽ “ኮከብም” ትመለከት ይሆናል። በአሁኑ ጊዜ በመገንባት ላይ ያለውና ሁለት ኳስ ሜዳዎች የሚያክል መጠን ያለው ይህ ሰው ሠራሽ ግዙፍ አካል ‘ፒራሚዶች ከተሠሩ ወዲህ በግዙፍነቱ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት የምህንድስና ፕሮጄክት’ ተብሎ ተገልጿል። ይህ ግዙፍ አካል ምንድን ነው?
ግንባታው ሲጠናቀቅ ከ100,000 የሚበልጡ ሠራተኞች የተካፈሉበት ቋሚ የጠፈር ምርምር ቤተ ሙከራ የሚደረግበት ዓለም አቀፋዊ የጠፈር ጣቢያ (አይ ኤስ ኤስ) ይሆናል። ከእነዚህ ሠራተኞች መካከል አብዛኞቹ በሩስያ፣ በካናዳና በዩናይትድ ስቴትስ በመሥራት ላይ የሚገኙ ሲሆን ሌሎች ብዙዎች ደግሞ በስዊድን፣ በስዊዘርላንድ፣ በስፔይን፣ በቤልጅየም፣ በብሪታንያ፣ በብራዚል፣ በኔዘርላንድ፣ በኖርዌይ፣ በኢጣሊያ፣ በዴንማርክ፣ በጀርመን፣ በጃፓንና በፈረንሳይ በመሥራት ላይ ናቸው። አይ ኤስ ኤስ ተሠርቶ ሲጠናቀቅ 88 ሜትር ርዝመትና 109 ሜትር ስፋት ይኖረዋል። የሁለት ቦይንግ 747 አውሮፕላኖች ክፍሎችን የሚያክል የሥራ ቦታና የመኖሪያ ክፍሎች ይኖሩታል ማለት ነው። የጠፈር ጣቢያው ሥራ ሲገባደድ 520 ቶን ክብደት የሚኖረው ሲሆን የግንባታ ሥራው ቢያንስ ቢያንስ 50 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ ይሆናል!
ለምርምር በሚል ሽፋን ይህን ያህል ከፍተኛ ወጪ መውጣቱ ያሳሰባቸው አንዳንድ ተቺዎች አይ ኤስ ኤስን “ከጥቅሙ ኪሳራው የሚያመዝን በይነ ኮከባዊ” ሲሉ ጠርተውታል። በሌላ በኩል ደግሞ የጠፈር ጣቢያው አቀንቃኞች ጣቢያው ለአዲስና ለረቀቁ የኢንዱስትሪ ቁሶች፣ የመገናኛ ዘዴዎች ቴክኖሎጂና ለሕክምና ምርምር መፈተሻ ማዕከል ይሆናል የሚል እምነት አላቸው። ይሁን እንጂ የጠፈር ተመራማሪዎች በአይ ኤስ ኤስ ግድግዳዎች ላይ የቤተ ሙከራ ዕቃዎችን ከመግጠማቸው በፊት የጣቢያው አካላት አንድ በአንድ መገጣጠም ያለባቸው ሲሆን ይህ ሁሉ መከናወን ያለበት ደግሞ ጠፈር ላይ ነው!
ጣቢያውን በጠፈር ላይ መገንባት
አይ ኤስ ኤስ እጅግ ግዙፍ በመሆኑ በምድር ላይ ሊገጣጠም አይችልም። ምክንያቱም የራሱ ክብደት መልሶ ያፈራርሰዋል። ሳይንቲስቶች ይህን እክል ለመወጣት የጠፈር ጣቢያውን ለመሥራት የሚያገለግሉና በጠፈር ላይ የሚገጣጠሙ የተለያዩ ክፍሎችን ምድር ላይ እየሠሩ ነው። እነዚህን የተለያዩ ክፍሎች ወደ ጠፈር ለመውሰድ በሩስያ አምጣቂዎችና በዩናይትድ ስቴትስ የጠፈር መንኮራኩሮች 45 በረራዎች ማድረግ ይጠይቃል።
ጣቢያውን በጠፈር ላይ የመገጣጠሙ ሥራ ጠፈርን የማያቋርጥ ለውጥ የሚታይበት የግንባታ ማዕከል የሚያደርግ መጠነ ሰፊ ሥራ ነው። ሠራተኞቹና ቁሶቹ ምህዋር ላይ ሆነው ከ100 በላይ የሚሆኑ የጣቢያው ክፍሎች ይገጣጠማሉ። ከዓለም ዙሪያ የተውጣጡ የጠፈር ተመራማሪዎች በብዙ መቶ ለሚቆጠሩ ሰዓታት ከመንኮራኩራቸው ውጪ በጠፈር ላይ በመጓዝ አብዛኛውን ሥራ በእጃቸው ማከናወን ይኖርባቸዋል።
የሩስያ ሥሪት የሆነውና ዛርያ (“የጸሐይ መውጣት” ማለት ነው) የሚል ስያሜ የተሰጠው 20 ቶን የሚመዝነው የአይ ኤስ ኤስ የመጀመሪያ አካል ካዛክስታን ውስጥ ከሚገኘው የባይክኑር የመንኮራኩር ማምጠቂያ ማዕከል ኅዳር 20, 1998 ላይ እንዲመጥቅ ተደረገ። ይህ አካልም ሆነ ከዚሁ አካል ጋር የሚገጠሙት ሌሎች የጣቢያው ክፍሎች ምድርን መዞራቸውን ይቀጥሉ ዘንድ በቂ ነዳጅ ያስፈልገው ነበር። ዛርያ ከመጠቀ ከሀያ ቀናት በኋላ ኢንዴቨር የተባለችው መንኮራኩር ዩኒቲ የሚል ስያሜ የተሰጠውን አሜሪካ ሠራሽ አካል ይዛ መጠቀች።
ኢንዴቨር በተሰኘችው መንኮራኩር የመጠቁት ሠራተኞች ታኅሣሥ 1998 በጠፈር ላይ በተካሄደው የመጀመሪያ የግንባታ ሥራ ፈታኙን ተግባር ማከናወን ጀመሩ። የጠፈር ተመራማሪዋ ናንሲ ኩሪ ከምድር 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውንና 20 ቶን የሚመዝነውን ዛርያ የተሰኘውን አካል ይዞ ዩኒቲ ከተባለው የጣቢያው አካል ጋር ለማገናኘት 15 ሜትር ርዝመት ያለው የሮቦት ክንድ ተጠቅማለች። ከዚያም ጄሪ ሮስ እና ጄምስ ኒውማን የተባሉት የጠፈር ተመራማሪዎች የኤሌክትሪክና የኮምፒዩተር ሽቦዎችን እንዲሁም ፈሳሽ ነገሮችን የሚያስተላልፉ የፕላስቲክ ቱቦዎችን ከሁለቱ የጣቢያው ክፍሎች ውጪ አገናኙ። እነዚህ መስመሮች መያያዛቸው በሁለቱ የጣቢያው ክፍሎች መካከል የኤሌክትሪክ ኃይል ለማስተላለፍና አየሩን የሚያቀዘቅዝና ለመጠጥነት የሚያገለግል ውኃ እንዲዘዋወር ለማድረግ ይረዳል። የጠፈር ተመራማሪዎቹ እነዚህን ተግባራት ለማከናወን ሦስት ጊዜ ከመንኮራኩራቸው ውጪ በጠፈር ላይ የተጓዙ ሲሆን ይህም በድምሩ ከ21 ሰዓት በላይ ፈጅቷል።
ሮኬቶችና መንኮራኩሮች በየጥቂት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ የጣቢያውን አዳዲስ ክፍሎች እየያዙ ሲመጥቁ አይ ኤስ ኤስ የሩስያ ስሪት ከሆነው ከዛርያ ነጠላ ክፍል ተነስቶ 520 ቶን የሚመዝን የጠፈር ጣቢያ ይሆናል። ይህ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የሚሄደው ጣቢያ የምድርን የስበት ኃይል መቋቋም ያለበት በመሆኑ ባለበት ምህዋር ውስጥ መዞሩን እንዲቀጥል ማድረጉ በጣም ፈታኝ ነው። በመሆኑም በማንኛውም ጊዜ ወደ ምድር ተመልሶ የመውደቅ አስጊ ሁኔታ ተጋርጦበታል። ጣቢያው ከቦታው ዝንፍ እንዳይል ለማድረግ በየጊዜው መንኮራኩሮች ወደ ጣቢያው በመምጠቅ ከፍታውን ጠብቆ መቀጠል የሚያስችለውን ኃይል ይሰጡታል።
በቦታው ያለው የስበት ኃይል ወደ ዜሮ የሚጠጋ በመሆኑ በአይ ኤስ ኤስ ላይ ለሚካሄደው ምርምር ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል። በዚያ ቦታ ያለው የስበት ኃይል በምድር ላይ ካለው የስበት ኃይል ጋር ሲወዳደር አንድ ሚልዮንኛ ብቻ ነው። ከሁለት ሜትር ከፍታ ላይ የተጣለ አንድ እርሳስ ምድር ላይ ለመውደቅ የሚፈጀው ጊዜ 0.5 ሴኮንድ ሲሆን በጠፈር ጣቢያው ላይ ግን የሚፈጅበት ጊዜ አሥር ደቂቃ ነው! አይ ኤስ ኤስ ቤተ ሙከራ ሆኖ የሚያገለግለው እንዴት ነው? ይህስ የአንተን የዕለት ተዕለት ሕይወት ሊነካ የሚችለው እንዴት ነው?
ምድርን የሚዞር ቤተ ሙከራ
የአይ ኤስ ኤስ ግንባታ ሥራ በ2004 ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። ከዚያ በኋላ በአንድ ጊዜ ከሰባት የማይበልጡ የጠፈር ተመራማሪዎች ወደዚህ ግዙፍና ውስብስብ ጣቢያ ይሄዳሉ። አንዳንዶቹ በርከት ላሉ ወራት እዚያው ይቆያሉ። የጽንፈ ዓለም መስኮት የሚል ስያሜ የተሰጠው የአይ ኤስ ኤስ ተመራማሪዎች ቡድን በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሳይንቲስቶች የነደፏቸውን የተለያዩ ዓይነት በርካታ ሙከራዎች ያካሂዳል።
ለምሳሌ ያህል የስበት ኃይል በጣም ደካማ በሚሆንበት ጊዜ የዕፅዋት ሥሮች ወደ ውስጥ ጠልቀው አይገቡም፣ ቅጠሎቻቸውም ብዙ ማደግ አይችሉም። ስለዚህ ሳይንቲስቶች ዕፅዋት የስበት ኃይል በሌለበት ቦታ ምን ሁኔታ እንደሚኖራቸው ለማወቅ ሙከራዎች ለማድረግ አቅደዋል። ከዚህም በተጨማሪ የፕሮቲን ክሪስታሎች በጠፈር ላይ በሚሆኑበት ጊዜ ዕድገታቸው የሚጨምር ከመሆኑም በላይ ቅርጻቸው ተመጣጣኝ ይሆናል። ስለዚህ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ውስጥ ይበልጥ የጠሩ ክሪስታሎች ማፍራት ይቻል ይሆናል። በዚህ ረገድ የሚገኘው እውቀት ተመራማሪዎች በሽታ በሚያስከትሉ በተለዩ ፕሮቲኖች ላይ ያነጣጠሩ መድኃኒቶች እንዲሠሩ ይረዳቸው ይሆናል። በምድር ላይ ፈጽሞ ሊሠሩ የማይችሉ ቁሶችን የስበት ኃይል በጣም ደካማ በሆነበት ቦታ መሥራት ይቻል ይሆናል።
ወደ ዜሮ የሚጠጋ የስበት ኃይል ባለበት ቦታ የሰው ልጅ አጥንቶችና ጡንቻዎች እየመነመኑ ይሄዳሉ። ቀደም ሲል የጠፈር ተመራማሪ የነበሩት ማይክል ክሊፎርድ “ከሳይንሳዊ ምርምሩ አንዱ በጠፈር ላይ ለረጅም ጊዜ መቆየት በሰውነት ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ በመረዳት ላይ ያተኮረ ይሆናል” ብለዋል። የአጥንትን መመንመን እንዴት ማስቀረት እንደሚቻል ለማወቅ ቢያንስ ቢያንስ አንድ ሙከራ መካሄዱ አይቀርም።
በጠፈር ላይ መቆየት የሚያሳድረውን ዘላቂ ተጽዕኖ ማወቁ ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስደውን ወደ ማርስ የሚደረገውን በረራ አንድ ቀን እውን ለማድረግ አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል። “ይህ ረጅም ጊዜ የሚወስድ ጉዞ ነው” ሲሉ ክሊፎርድ ሐቁን ሳይሸሽጉ ተናግረዋል። “[የጠፈር ተመራማሪዎቹ] ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲመለሱ የማድረግ ብቃት እንዲኖረን እንፈልጋለን።”
ከዚህም በተጨማሪ የአይ ኤስ ኤስ አቀንቃኞች በጠፈር ጣቢያው ላይ የሚደረገው ምርምር ሕይወት የተገነባባቸውን መሠረታዊ ነገሮች ይበልጥ ለማወቅ ያስችላል ሲሉ ይተነብያሉ። ይህ እውቀት ካንሰርን፣ ስኳር በሽታን፣ ኤምፊዚማንና ከሰውነታችን በሽታ መከላከያ ሥርዓት ጋር ግንኙነት ያላቸውን በሽታዎች ማከም የሚቻልባቸው አዳዲስ ዘዴዎች ለማግኘት አስተዋጽኦ ያደርግ ይሆናል። በአይ ኤስ ኤስ ላይ የሚኖሩት ቤተ ሙከራዎች ከተፈጥሮ ኅብረሕዋስ ጋር የሚመሳሰሉ ሕዋሳት የሚያድጉበት ባዮሪአክተር ይኖራቸዋል። ሳይንቲስቶች የሰው ልጆችን ስለሚያጠቁ በሽታዎችና እነዚህን በሽታዎች በተሳካ ሁኔታ ማከም ስለሚቻልባቸው መንገዶች ለማወቅ ጥረት ያደርጋሉ። በተጨማሪም የከባቢ አየር ጋዞችን፣ የዛጎል ተሬ (coral-reef) ቀለም መልቀቅን፣ አውሎ ነፋሳትንና ሌሎች በምድር ላይ የሚታዩ ተፈጥሯዊ ክስተቶችን ለማጥናት የሚያስችል 50 ሴንቲ ሜትር የሚሆን መስኮት በጣቢያው ላይ ይኖራል።
“ሰላም የሚያወርድ ቤተ ሙከራ?”
ሆኖም ለአንዳንዶቹ የአይ ኤስ ኤስ ዋነኛ አቀንቃኞች ጣቢያው ከተንሳፋፊ ቤተ ሙከራነት በተጨማሪ ሌላም ትርጉም አለው። ጣቢያው በአፖሎ ፕሮግራም ወቅት የአፖሎ የጠፈር ተመራማሪዎች ጽላት ላይ ቀርጸው ጨረቃ ላይ የተከሉትን “ወደዚህ የመጣነው ለመላው የሰው ልጅ ሰላም ነው” የሚለውን ቃል ዳር የሚያደርስ እንደሆነም አድርገው ይመለከቱታል። በሰባዎቹ ዓመታት ዕድሜ ላይ የሚገኙት የጠፈር ተመራማሪው ጆን ግሌን አይ ኤስ ኤስን “ሰላም የሚያወርድ ቤተ ሙከራ” ሲሉ ከገለጹት በኋላ የሚከተለውን ሐሳብ አክለው ተናግረዋል:- “አሥራ ስድስት አገሮች በምድር ላይ አንዳቸው ሌላውን የሚጎዳ ነገር የሚሠሩበትን መንገድ ሲቧጥጡ ከመክረም ይልቅ በጠፈር ላይ ሁሉም በአንድነት እንዲሠሩ በር ይከፍትላቸዋል።” እሳቸውም ሆኑ ሌሎች አይ ኤስ ኤስ ብሔራት በተናጠል ሊወጧቸው የማይችሏቸውን ሆኖም ሁሉም ጥቅም ሊያገኙባቸው የሚችሉባቸውን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ፕሮጄክቶች ተባብሮ መሥራትን ሊማሩ የሚችሉበት ቦታ እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል።
ይሁን እንጂ ብዙዎች በምድር ላይ ተስማምተው መሥራት ያልቻሉት ብሔራት በጠፈር ላይ በሰላም ተባብረው የመሥራታቸው ጉዳይ ያጠራጥራቸዋል። በዚያም ሆነ በዚህ አይ ኤስ ኤስ የሰው ልጅ ወደማይታወቀው ዓለም ተሻግሮ እዚያ ባሉት ሁኔታዎች ሥር ሊከናወኑ የሚችሉትን ነገሮች ለማወቅ ያለውን ውስጣዊ ግፊት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። በእርግጥም ይህ ግዙፍ ፕሮጄክት የሰው ልጅ ያለውን ጀብዱ የመፈጸም ስሜትና አዲስ ነገር የማወቅ ከፍተኛ ፍላጎት የሚያንጸባርቅ ነው።
[በገጽ 27-29 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]
ከጠፈር ጣቢያዎች ጋር ዝምድና ያላቸው ዘመናት
1869:- አሜሪካዊው ኤድዋርድ ኤቨርት ሄል ዘ ብሪክ ሙን በሚል ርዕስ ሰው ይዛ ስለመጠቀች ከሸክላ የተሠራች የጠፈር ሳተላይት አጠር ያለ ታሪክ አሳትመው ነበር።
1923:- የሩማንያ ተወላጅ የሆኑት ሄርማን ኦቤርት “የጠፈር ጣቢያ” የሚለውን ስያሜ አወጡ። ይህን ስያሜ ሲያወጡ በአእምሯቸው ይዘውት የነበረው ወደ ጨረቃና ወደ ማርስ ለሚደረገው በረራ መነሻ ሆኖ የሚያገለግልን ቦታ ነበር።
1929:- ሄርማን ፖቶክኒክ ዘ ፕሮብሌም ኦቭ ስፔስ ትራቭል በተባለው መጽሐፋቸው ላይ የጠፈር ጣቢያን ዕቅድ ጠቅለል አድርገው ገልጸዋል።
በ1950ዎቹ:- የሮኬት መሐንዲስ የሆኑት ቨርነር ቮን ብሮን ከምድር በላይ 1,730 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ስለሚዞር ክብ ቅርፅ ስላለው አንድ ጣቢያ ገልጸዋል።
1971:- ሶቭየት ኅብረት በታሪክ ውስጥ የመጀመሪያ የሆነችውን ሳልዩት 1 የተሰኘች የጠፈር ጣቢያ አመጠቀች። ሦስት የጠፈር ተመራማሪዎች በዚህች ጣቢያ ውስጥ ለ23 ቀናት ቆይተዋል።
1973:- ስካይላብ የተባለ የመጀመሪያው የዩናይትድ ስቴትስ የጠፈር ጣቢያ ምድርን መዞር ጀምሮ የነበረ ሲሆን ሦስት የጠፈር ተመራማሪዎች ቡድንን የሚያስተናግድ ነበር። ይህ ጣቢያ በአሁኑ ጊዜ በጠፈር ላይ አይገኝም።
1986:- ሶቭየቶች የሰው ልጅ ለዘለቄታው በጠፈር ላይ መመላለስ የሚችልበትን ሁኔታ ለመፍጠር ብለው የሠሯትን ሚር የተሰኘችውን የመጀመሪያዋን የጠፈር ጣቢያ አመጠቁ።
1993:- ዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የጠፈር ጣቢያ (አይ ኤስ ኤስ) በመገንባቱ ሥራ እንዲተባበሯት ለሩስያ፣ ለጃፓንና ለሌሎች አገሮች ጥሪ አቀረበች።
1998/99:- የመጀመሪያዎቹ የአይ ኤስ ኤስ ክፍሎች ከወጣው የጊዜ ሰሌዳ አንድ ዓመት ዘግይተው ወደ ምሕዋር እንዲመጥቁ ተደረገ።
[ሥዕሎች]
ከላይ:- የጣቢያው ግንባታ በ2004 ሲጠናቀቅ የሚኖረውን ገጽታ የሚያሳይ የሰዓሊያን ንድፍ
ዛርያና ዩኒቲ የተሰኙት የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ የጣቢያው አካላት ተጣምረዋል
ሮስና ኑውማን ለሦስተኛ ጊዜ በጠፈር ላይ ሲራመዱ
ዕቅድ ከተያዘላቸው በርካታ የጠፈር በረራዎች አንዱ
ስካይላብ
ሚር
[ምንጭ]
ከገጽ 27-29:- NASA photos