ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች ...
የሚፈጸምብኝን ግፍ መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?
“በሌሎች ዘንድ የሚከበሩት ገንዘብ ያላቸው ሰዎች ብቻ ናቸው። የሚቀምሰው ምግብና ራሱን የሚያስጠጋበት ቤት የሌለው እንደ እኛ ዓይነቱ ምስኪን ግን እንደ እንስሳ ነው የሚታየው። አንድ ቀን ማንም ልብ ሳይለኝ አንዱ ጥግ ሞቼ እገኛለሁ ብዬ እሰጋለሁ።”—አርኑልፎ፣ የጎዳና ተዳዳሪ የሆነ የ15 ዓመት ልጅ
ይህ ዓለም በግፍ የተሞላ ነው። ከተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (UNICEF) የወጣ አንድ ዘገባ እንዲህ ይላል:- “ባለፉት አሥር ዓመታት ከ2 ሚልዮን የሚልቁ ልጆች በጦርነት ተገድለዋል፤ ሌሎች ከ4 ሚልዮን የሚበልጡ ደግሞ ሕይወታቸው ቢተርፍም እንኳ የተወሰነ የአካል ክፍላቸውን አጥተዋል፤ ከአንድ ሚልዮን የሚበልጡ ሌሎች ደግሞ ጦርነት ባስከተለው ጠንቅ ወላጆቻቸው ሞተውባቸዋል ወይም ከቤተሰቦቻቸው ተለያይተዋል።” ከዚህም በተጨማሪ ጥቂቱ የዓለም ክፍል በሃብትና በብልጥግና ሲምነሸነሽ አብዛኛው የዓለም ክፍል ግን በረሃብና በድህነት ይማቅቃል። በታዳጊ አገር የሚኖሩ እንደ አርኑልፎ ያሉ በርካታ ልጆች የመማር ዕድል ተነፍገዋል።
በተለይ ደግሞ ግፍ የሚፈጽሙብህ ሊወዱህና ሊንከባከቡህ የሚገባቸው ሰዎች ከሆኑ በጣም ልትጎዳ ትችላለህ። ሱሳና የተባለችውን የ17 ዓመት ሴት ልጅ ሁኔታ ተመልከት። እናቷ እርሷንና ሁለት ታናናሽ ወንድሞቿን ጥላቸው ሄደች። “ይህ ከሆነ አሁን ዓመታት ተቆጥረዋል” ትላለች ሱሳና በምሬት። “እናቴ የምትኖረው እኔ በምኖርበት ከተማ ውስጥ ቢሆንም እንኳ አንድም ቀን አብሬያት እንድኖር ጠይቃኝ አታውቅም። ሌላው ቀርቶ ‘እወድሻለሁ’ የሚል ቃል እንኳ ከአፏ ወጥቶ አያውቅም። ይህ ደግሞ እስከ አሁን ድረስ ያናድደኛል።” አንተም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል በደል ደርሶብህ ከሆነ ያደረብህን የቁጣ ስሜት መቆጣጠር ያስቸግርህ ይሆናል። በልጅነቷ በጾታ የተነወረች አንዲት ሴት “በአምላክ ላይ እንኳ ሳይቀር መጥፎ ስሜት እንዲያድርብኝ አድርጎኝ ነበር” ብላለች።
በደል ሲፈጸምብህ ማዘንህና መበሳጨትህ ያለ ነገር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ግፍ ጠቢቡን ያሳብደዋል” በማለት ይናገራል። (መክብብ 7:7) ዕለት ተዕለት ግፍ የሚፈጸምብህ ከሆነ የመንፈስ ጭንቀት ሊይዝህ ይችላል። (ከመዝሙር 43:2 ጋር አወዳድር።) በዚህም የተነሳ ግፍ የሚያከትምበትን ጊዜ ለማየት ትናፍቅ ይሆናል። በመካከለኛው አሜሪካ የምትኖር አንዲት ልጅ እንዲህ በማለት ታስታውሳለች:- “በ13 ዓመቴ የተማሪዎች ንቅናቄ አባል ሆንኩ። አንድም የሚራብ ልጅ እንዳይኖር ለማድረግ አንድ ዓይነት አስተዋጽዖ የማበርከት ከፍተኛ ምኞት ነበረኝ። . . . ከዚያም ከታጣቂ ታጋዮች ጋር አበርኩ።” ሆኖም ፍትሕን ከማስፈን ይልቅ አብረዋት ያሉት ወታደሮች ይህ ነው የማይባል በደል ፈጸሙባት።
እንዲህ ዓይነቶቹ ሁኔታዎች አብዛኞቹ ሰዎች ካሉበት አዘቅት ውስጥ ራሳቸውን ለማውጣት የሚያስችል አቅም እንደሌላቸው ያሳስቡናል። እንግዲያው ግፍ የሚፈጸምባቸው ሰዎች የሚገጥሟቸውን ችግሮች መቋቋም የሚችሉት እንዴት ነው?a የሚሰማህን ምሬትና ብስጭት መቆጣጠር የምትችለውስ እንዴት ነው?
መራርነትንና ንዴትን ማስወገድ
በዚህ የነገሮች ሥርዓት ‘የመጨረሻ ቀን’ ውስጥ እንደምንኖር በየጊዜው ራስህን ማሳሰብ ይኖርብህ ይሆናል። በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ ሰዎች “ተሳዳቢዎች፣ . . . ፍቅር የሌላቸው፣ ዕርቅን የማይሰሙ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች” እንደሚሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ ተንብዮአል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-4) የብዙዎች የሥነ ምግባር ስሜት ‘ደንዝዟል።’ (ኤፌሶን 4:19) በዚህም የተነሳ ግፍ ልናስቀረው የማንችል የሕይወት ክፍል ሆኗል። ስለዚህ “በአገሩ ድሆች ሲገፉ፣ ፍርድና ጽድቅም ሲነጠቅ ባየህ ጊዜ በዚህ ነገር አታድንቅ።”—መክብብ 5:8
መራርነት ሙሉ በሙሉ በቁጥጥሩ ሥር እንዳያደርግህ መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ የተገባ ነው። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ “መራርነትና ንዴት ቊጣም . . . ከእናንተ ዘንድ ይወገድ” ይላል። (ኤፌሶን 4:31) ለምን? ምክንያቱም ቁጣን አምቆ መያዝ የኋላ ኋላ ራስን ጉዳት ላይ ሊጥልና ጥፋት ሊያስከትል ይችላል። (ከምሳሌ 14:30፤ ኤፌሶን 4:26, 27 ጋር አወዳድር።) በተለይ ደግሞ የተቆጣኸው “በእግዚአብሔር ላይ” ከሆነ ይህ ሁኔታ መድረሱ አይቀሬ ነው። (ምሳሌ 19:3) በአምላክ ላይ መቆጣትህ ከማንም በላይ ሊረዳህ ከሚችለው አምላክ ጋር ያለህን ዝምድና በእጅጉ ሊያበላሽብህ ይችላል። ይሖዋ “ልቡ በእርሱ ዘንድ ፍጹም የሆነውን ያጸና ዘንድ ዓይኖቹ በምድር ሁሉ ይመለከታሉ” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—2 ዜና መዋዕል 16:9
ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ ሲናገር “መንገዱም ሁሉ የቀና [“ፍትሐዊ፣” NW] ነው፤ የታመነ አምላክ፣ ክፋትም የሌለበት፣ [“ፍትሕ የማያጓድል፣” NW] እርሱ እውነተኛና ቅን ነው” በማለት ይናገራል። (ዘዳግም 32:4) ግፍ ሊኖር የቻለው አዳምና ሔዋን በማመፃቸው ምክንያት ነው። (መክብብ 7:29) ‘ሰውን ለጉዳቱ የገዛው’ አምላክ ሳይሆን ሰው ራሱ ነው። (መክብብ 8:9) ከዚህም በተጨማሪ ‘ዓለም በሞላው በክፉው’ ማለትም በሰይጣን ዲያብሎስ “እንደ ተያዘ” አስታውስ። (1 ዮሐንስ 5:19) በዓለም ላይ እየደረሰ ካለው ግፍ ሁሉ በስተጀርባ ያለው ይሖዋ ሳይሆን ሰይጣን ነው።
ግፍ የሚያከትምበት ጊዜ
ደግነቱ ግፍ ለሁልጊዜው የሚቀጥል ነገር አይደለም። ይህን ማስታወስህ ችግሩን እንድትቋቋም ሊረዳህ ይችላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ይኖር የነበረ አሳፍ የተባለ አንድ ሰው ያሳለፈውን ተሞክሮ ተመልከት። አሳፍ ይኖር የነበረው አምላክን እናገለግላለን በሚሉ ሰዎች መካከል ቢሆንም በዙሪያው ብዙ የግፍ ድርጊቶች ይፈጸሙ ነበር። ጨካኝ ሰዎች ሌሎችን በመበደላቸው ምክንያት ቅጣት ሊደርስባቸው ሲገባ ከችግር ነፃ የሆነና የተንደላቀቀ ኑሮ የሚመሩ ይመስሉ ነበር! አሳፍ “የኃጢአተኞችን ሰላም አይቼ . . . ቀንቼ ነበር” በማለት ሳይሸሽግ ተናግሯል። አሳፍ እነዚህ ነገሮች ሐሳቡን ሙሉ በሙሉ እንዲቆጣጠሩት በመፍቀዱ ለጊዜውም ቢሆን ሚዛኑን እንዲስት አድርገውት ነበር።—መዝሙር 73:1-12
ከጊዜ በኋላ አሳፍ ከፍተኛ የአስተሳሰብ ለውጥ አደረገ። ክፉዎችን በማስመልከት “በድጥ ስፍራ አስቀመጥኻቸው፣ ወደ ጥፋትም ጣልኻቸው” በማለት ተናግሯል። (መዝሙር 73:16-19) አዎን፣ አሳፍ ይዋል ይደር እንጂ ክፋት የሚፈጽሙ ሰዎች ከቅጣት እንደማያመልጡ ተገንዝቦ ነበር። ብዙውን ጊዜ ኃጢአታቸው ስለሚያገኛቸው ለእስር ይዳረጋሉ፣ የገንዘብ ክስረት ይገጥማቸዋል፣ ከሥራ ይባረራሉ ወይም ከነበሩበት ከፍተኛ የሥልጣን ቦታ ይወርዳሉ። ዘገየ ቢባል ክፉዎች አምላክ በዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ላይ የጥፋት ፍርድ በሚያስፈጽምበት ጊዜ ‘መጥፋታቸው’ አይቀሬ ነው።—መዝሙር 10:15, 17, 18፤ 37:9-11
አምላክ በቅርቡ ነገሮችን እንደሚያስተካክል ማወቅህ ንዴትህንና ብስጭትህን እንድትቆጣጠር ሊረዳህ ይችላል። “ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይመክራል። “በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን አስቡ። ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ። ተወዳጆች ሆይ፣ ራሳችሁ አትበቀሉ፣ ለቊጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤ በቀል የእኔ ነው፣ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና።”—ሮሜ 12:17-19፤ ከ1 ጴጥሮስ 2:23 ጋር አወዳድር።
እርዳታና ድጋፍ ማግኘት
ሆኖም የደረሰብህ በደል እንደ መጥፎ ትዝታ ያለ የስሜት ጠባሳ ጥሎብህ አልፎ ይሆናል። ዩኒሴፍ ባወጣው አንድ ዘገባ መሠረት “ተደጋጋሚ የኃይል ድርጊት የተፈጸመባቸው ልጆች በሌሎች ላይ እምነት ማጣትን ጨምሮ በእምነታቸውና በዝንባሌያቸው ላይ ከፍተኛ ለውጥ ያስከትልባቸዋል። በተለይ ደግሞ የአካል ወይም የጾታ ጥቃት የሰነዘረባቸው ሰው ቀደም ሲል እንደ ጎረቤታቸው ወይም እንደ ወዳጃቸው አድርገው ይመለከቱት የነበረ ሰው ከሆነ ይህ ሁኔታ ይከሰታል።”
እነዚህ ችግሮች ቶሎ የሚሽሩ አይደሉም። ይሁን እንጂ አፍራሽ ስሜት ወይም መጥፎ ትዝታ አስተሳሰብህን የሚቆጣጠረው ከሆነ እርዳታ ማግኘት ያስፈልግሃል ማለት ነው። (ከመዝሙር 119:133 ጋር አወዳድር።) በመጀመሪያ የደረሰብህን ሁኔታ በተመለከተ ቀጥተኛ ማብራሪያ የሚሰጥ ጽሑፍ ልታነብ ትችላለህ። ለምሳሌ ያህል የንቁ! መጽሔት በጾታ ለተነወሩ፣ ለተዘረፉና በልጅነታቸው በደል ለተፈጸመባቸው ሰዎች ተግባራዊ ምክር የሚሰጡ በርካታ ርዕሶች ይዞ ወጥቷል። የሚያሳስቡህን ነገሮችና ስሜትህን ከልብ ለሚያዳምጥህ ለአንድ የጎለመሰ ሰው ብታካፍል ከፍተኛ ጥቅም ሊያስገኝልህ ይችላል። (ምሳሌ 12:25) ምናልባትም ለወላጆችህ ልትነግራቸው ትችል ይሆናል።
ሆኖም የወላጅ ድጋፍ ማግኘት በማያስችል ሁኔታ ላይ የምትገኝ ከሆነስ? ከክርስቲያን ጉባኤ ድጋፍ ለማግኘት ጥረት አድርግ። በይሖዋ ምሥክሮች መካከል የሚገኙ የጉባኤ ሽማግሌዎች መጥፎ ሁኔታ ለሚደርስባቸው ሰዎች እንደ መጠጊያ ሆነው ያገለግላሉ። (ኢሳይያስ 32:1, 2) ችግርህን በማዳመጥ ብቻ ሳይወሰኑ ተግባራዊ መሆን የሚችል ምክርም ሊለግሱህ ይችላሉ። ሌሎች የጎለመሱ ክርስቲያኖችም እንደ ‘ወንድሞች፣ እህቶችና እናቶች’ ሊሆኑልህ እንደሚችሉ አትርሳ። (ማርቆስ 10:29, 30) እናቷ ጥላት የሄደችውን ሱሳናን ታስታውሳለህ? እርሷና ወንድሞቿ ከክርስቲያን ጉባኤ ድጋፍ አገኙ። አንድ ክርስቲያን አገልጋይ ለሱሳና ቤተሰብ ትኩረት በመስጠት ልዩ እንክብካቤ በማድረጉ ሱሳና እንደ አሳዳጊ አባቷ አድርጋ ልታየው ችላለች። እንዲህ ያለው ድጋፍ “እንድንጎለምስና በእውነት ውስጥ ጸንተን እንድንቆም ረድቶናል” በማለት ሱሳና ትናገራለች።
በየዕለቱ ትርጉም ያለው እንቅስቃሴ ማድረግ ጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል ጠበብት ይናገራሉ። ትምህርት ቤት መሄዱና የቤት ውስጥ ሥራዎችን ማከናወኑ ብቻ እንኳ አእምሮህ አፍራሽ ከሆኑ አስተሳሰቦች እንዲርቅ በማድረግ ረገድ የማይናቅ አስተዋጽዖ ያበረክታሉ። በተለይ ደግሞ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን ልማድ በማድረግ አዘውትረህ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘትህና ምሥራቹን መስበክህ ጥቅም ያስገኝልሃል።—ከፊልጵስዩስ 3:16 ጋር አወዳድር።
ግፍ ከምድረ ገጽ የሚወገደው የአምላክ መንግሥት መጥቶ በመላው ምድር ላይ የአምላክን ፈቃድ ሲያስፈጽም ብቻ ነው። (ዳንኤል 2:44፤ ማቴዎስ 6:9, 10) እስከዚያው ድረስ ግን ይህን ችግር መቋቋም ትችል ዘንድ የተቻለህን ሁሉ አድርግ። የአምላክ መንግሥት ገዥ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ “ችግረኛውን ከቀማኛው እጅ፣ ረዳት የሌለውንም ምስኪን ያድነዋልና። ለችግረኛና ለምስኪን ይራራል፣ የችግረኞችንም ነፍስ ያድናል” የሚለውን ተስፋ እያሰብክ ተጽናና።—መዝሙር 72:12, 13
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ምንም እንኳ ይህ ርዕስ ባልበለጸጉ አገሮች የሚኖሩ ወጣቶች ሊደርስባቸው በሚችለው ግፍ ላይ ያተኮረ ቢሆንም በውስጡ የቀረቡት መሠረታዊ ሥርዓቶች ማንኛውም ዓይነት ግፍ ለሚደርስበት ግለሰብ የሚሠሩ ናቸው።
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“በአምላክ ላይ እንኳ ሳይቀር መጥፎ ስሜት እንዲያድርብኝ አድርጎኝ ነበር”
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መሰል ክርስቲያኖች የሚሰጡህ ድጋፍ ግፍን እንድትቋቋም ሊረዳህ ይችላል