ከገንዘብ ይበልጥ ዋጋማ የሆነ ነገር
ካናዳ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው
በብሪጅታውን ኖቫ ስኮሻ ውስጥ የሚታተመው ዘ ሞኒተር የተባለው ጋዜጣ በርዕሰ አንቀጹ ላይ “ለሴት ልጅዋ የሰጠቻት ስጦታ ከየትኛውም የገንዘብ መጠን የላቀ ዋጋ ያለው ነገር ነው” ሲል ገልጿል። ስጦታው ምንድን ነው? “ሐቀኛ በመሆን የተወችው ግሩም ምሳሌ” ነው።
አና እና ልጅዋ ታንያ ወደ አንድ ያገለገሉ ዕቃዎች መሸጫ ጎራ አሉና ለታንያ መጽሐፍ ቅዱስ መያዣ የሚሆን ነጭ ቦርሳ ገዙ። እቤት ከደረሱ በኋላ ታንያ በቦርሳው ውስጥ ያለውን ዚፕ ስትከፍት 1,000 የካናዳ ዶላር በማግኘቷ በጣም ተገረመች። ወዲያውኑ እናትና ልጅ ተያይዘው ቦርሳውን ወደገዙበት ቦታ ተመልሰው ሄዱና ቦርሳውን ለሸጠችላቸው ሴት ገንዘቡን መልሰው ሰጧት። ቀደም ሲል ብዙም ጥቅም ላይ ያልዋለው ይህ ቦርሳ በአልዛይመርስ በሽታ ሲሰቃዩ ቆይተው ከጥቂት ጊዜ በፊት የሞቱት የሴትየዋ እናት ንብረት የነበረ ይመስላል። በተጨማሪም ሰዎቹ ቦርሳውን ከመሸጣቸው በፊት በደንብ አድርገው አልፈተሹትም። ሴትዬዋ ከልብ በመነጨ የምስጋና ስሜት “ያደረጋችሁት ነገር በሰዎች ላይ የነበረኝን እምነት መልሶ ገንብቶልኛል። አሁንም ሐቀኛ የሆኑ ሰዎች መኖራቸውን ማወቁ የሚያበረታታ ነው” ብላለች።
አንድ በአካባቢው የሚታተም ጋዜጣ አና የተናገረችውን የሚከተለውን ሐሳብ በመጥቀስ የተፈጸመውን ሁኔታ በመጀመሪያው ገጹ ላይ ዘግቧል:- “የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን ይህን ከማድረግ ሌላ ወደ አእምሯችን የሚመጣ ሐሳብ አይኖርም። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ [ሕሊና] አለን። በተጨማሪም ለታንያ ትክክል የሆነውን ነገር ማስተማር እንፈልጋለን።” ለታንያ ይህ አዲሱ ነጭ ቦርሳ ሐቀኝነትን አስመልክቶ ያገኘችውን ትምህርት ሲያስታውሳት የሚኖር ልዩ ማስታወሻ ይሆንላታል።