የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g99 12/8 ገጽ 22-25
  • ከወንጀለኛነት ተስፋ ወዳለው ሕይወት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከወንጀለኛነት ተስፋ ወዳለው ሕይወት
  • ንቁ!—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ወደ ወንጀል ጎዳና አመራሁ
  • ወደ አደገኛ ዕፆች ዓለም ገባሁ
  • መጀመሪያ ሀብት ማካበት፣ ከዚያ በኋላ ሕይወትን ማስተካከል
  • ፍጹም የሆነ ለውጥ
  • ቀና መንገድ በመከተሌ ያገኘኋቸው ወሮታዎች
  • መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
  • ከኤድስ የከፋ ነገር
    ንቁ!—1993
  • ከዕፅ ሱስ መላቀቅ የምችለው እንዴት ነው?
    ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 1
  • መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2012
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1999
g99 12/8 ገጽ 22-25

ከወንጀለኛነት ተስፋ ወዳለው ሕይወት

ኮስታ ኩላፒስ እንደተናገረው

ዓይኖቼን ባለሁበት ወኅኒ ቤት የቆሸሹ ግድግዳዎች ላይ ተክዬ እተክዛለሁ። ከወንጀለኛነት ሕይወት ተላቅቄ አዲስ ሕይወት መጀመር እችል ዘንድ ከፍተኛ ገንዘብ ማግኘት የምችልበትን መንገድ መዘየድ አለብኝ የሚል ቁርጥ ውሳኔ ላይ ደረስኩ።

በብስጭትና በሐዘን ተውጬ እዚያው በተቀመጥኩበት ሳወጣና ሳወርድ ባለፈው ዓመት የሞቱት 11 ጓደኞቼ ትዝ አሉኝ። አንዱ በነፍስ ግድያ ወንጀል ስቅላት ተፈርዶበት ሞተ። ሌላው ደግሞ በነፍስ ግድያ ወንጀል ችሎት ፊት የሚቀርብበትን ጊዜ እየተጠባበቀ ሳለ የራሱን ሕይወት አጠፋ። ሦስቱ አደገኛ ዕፆችን ከመጠን በላይ በመውሰዳቸው ሕይወታቸውን አጡ። ሁለቱ በጎዳና ላይ በተፈጠረ አምባጓሮ ተደብድበው ሕይወታቸው አለፈ። አራቱ ደግሞ በመኪና አደጋ ሞቱ። ከዚህም በተጨማሪ ሌሎች ጥቂት ያይደሉ ጓደኞቼ ከባድ ወንጀሎች ፈጽመው በተለያዩ ወኅኒ ቤቶች ውስጥ ታስረው ይገኛሉ።

ጨለማ ባጠላበት የወኅኒ ቤት ክፍሌ ውስጥ ሆኜ ማንነቱን ባላውቅም እንኳ ከዚህ የወንጀለኛነት ሕይወት መላቀቅ የምችልበትን መንገድ እንዲያሳየኝ አምላክን በጸሎት አጥብቄ ተማጸንኩት። ለዚህ ጸሎቴ መልስ ያገኘሁት ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ነበር። በመካከሉ ግን ከባድ የሆነ አካላዊ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ በሰው ላይ ጥቃት ፈጽመሃል ከሚለው የከረረ ክስ ነፃ መሆን ቻልኩ። ከዐቃቤ ሕጉ ጋር ያደረግነው ድርድር ለፍሬ በመብቃቱ ቀለል ባለ ክስ ተወንጅዬ የቅጣት ፍርዱ ተቀነሰልኝ። በመጀመሪያ ግን እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ልዘፈቅ የቻልኩት እንዴት እንደሆነ ልንገራችሁ።

የተወለድኩት በ1944 በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ውስጥ ሲሆን ያደግኩትም በዚሁ ከተማ ውስጥ ነው። የልጅነት ሕይወቴ አስደሳች አልነበረም። አባቴ ሁልጊዜ ከልክ በላይ እየጠጣ የቤተሰባችንን ሰላም ይበጠብጥ ነበር። በተጨማሪም የቁማር ሱሰኛ ነበር። ስሜቱ በጣም ይለዋወጥ ስለነበር ሁላችንንም በተለይ ደግሞ እናቴን ይሰድባትና ክፉኛ ይደበድባት ነበር። ከዘወትሩ ጠብ ለማምለጥ ስል ጎዳና መዋል ጀመርኩ።

ወደ ወንጀል ጎዳና አመራሁ

በዚህም የተነሳ ገና በልጅነቴ ብዙ ነገር ተማርኩ። ለምሳሌ ያህል ገና የስምንት ዓመት ልጅ ሳለሁ ሁለት ትምህርቶች ቀስሜ ነበር። የመጀመሪያው ከጎረቤታችን አሻንጉሊቶች ሰርቄ በተያዝኩበት ወቅት ነበር። አባቴ ክፉኛ ደበደበኝ። “ሁለተኛ አንድ ነገር ሰርቀህ ባገኝህ አንተን አያርገኝ!” ሲል የሰጠኝ ማስፈራሪያ አሁንም ድረስ ጆሮዬ ላይ ያስተጋባል። ሁለተኛ ላለመስረቅ ሳይሆን ሰርቄ ላለመያዝ ቁርጥ ውሳኔ አደረግኩ። ‘በሚቀጥለው ጊዜ አንድ ነገር ስሰርቅ ማንም እንዳይነቃብኝ እደብቀዋለሁ’ ብዬ አሰብኩ።

ገና ልጅ ሳለሁ የቀሰምኩት ሁለተኛው ትምህርት ደግሞ ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው። ትምህርት ቤት የግብረ ገብ ትምህርት ስንማር አስተማሪያችን አምላክ የግል ስም እንዳለው ነገረችን። “የአምላክ ስም ይሖዋ” መሆኑን ስትነግረን በጣም ተገረምን። “በተጨማሪም በልጁ በኢየሱስ ስም እስከጸለያችሁ ድረስ የምታቀርቡትን ጸሎት ሁሉ ይሰማል” አለችን። ምንም እንኳ ይህ ትምህርት ወደ ወንጀለኛነት ሕይወት ከማምራት ባያግደኝም በልጅነት አእምሮዬ ላይ የተወው አሻራ ነበር። ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብቼ በነበረበት ወቅት ከሱቅ ዕቃ በመስረቅና ቤት ሰብሮ በመግባት ወንጀል የተዋጣልኝ ሆኜ ነበር። ከትምህርት ቤት ጓደኞቼ መካከል ብዙዎቹ የተለያዩ ወንጀሎችን ፈጽመው ጸባይ ማረሚያ ገብተው የወጡ በመሆናቸው ከእኔ ምንም የሚሻሉ አልነበሩም።

ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ልማደኛ ወንጀለኛ ሆንኩ። ገና በአሥራዎቹ ዓመታት ዕድሜ ላይ እያለሁ ሰውን አስፈራርቶ በመንጠቅ፣ ቤት በመዝረፍ፣ መኪና በመስረቅና በሌሎች የኃይል ድርጊቶች ስፍር ቁጥር የሌለው ወንጀል እፈጽም ነበር። በየካራምቡላ ቤቱና በየመጠጥ ቤቱ እዞር ስለነበርና ሴተኛ አዳሪዎችን ከወንዶች ጋር ለሚያገናኙ ሰዎች፣ ለሴተኛ አዳሪዎችና ለወንጀለኞች እላላክ ስለነበር በከፍተኛ የሙያ ትምህርት ቤት እከታተለው የነበረውን ትምህርት የመጀመሪያ ዓመት እንኳ ሳልጨርስ አቋረጥኩ።

አብዛኛውን ጊዜዬን አጠፋ የነበረው የሚያጋልጣቸውን ማንኛውንም ሰው አካለ ጎዶሎ ከማድረግ ከማይመለሱ ምንም ርኅራኄ የሌላቸው ወንጀለኞች ጋር ነበር። ስላከናወንኳቸው ነገሮች ጉራ ከመንዛት ይልቅ አፌን ይዤ መቀመጥ ወይም ደግሞ ገንዘቤን ከማሳየት መታቀብ እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። እንዲህ ማድረጉ ወንጀል መፈጸሙን በስፋት ከማሳወቅ ሌላ የሚፈይደው ነገር የለም። ይህ ደግሞ ፖሊስ ጆሮ ሊደርስና ከባድ ምርመራ ሊያስከትል ይችላል። ይበልጥ የከፋው ደግሞ የጥቅሙ ተካፋዮች መሆን የሚፈልጉ ሌሎች ወንጀለኞችን ያልተጠበቀ ጥያቄ ሊያስከትል የሚችል መሆኑ ነው።

ሆኖም እነዚህን ጥንቃቄዎች እያደረግኩም እንኳ አንዳንድ ጊዜ ፖሊስ ሕገወጥ በሆኑ ድርጊቶች ይካፈላል የሚል ጥርጣሬ አድሮበት ክትትል ያደርግብኝ ነበር። ይሁን እንጂ ከወንጀል ድርጊት ጋር ሊያነካካኝ ወይም ሊያስወነጅለኝ የሚችል ማንኛውም ነገር በእጄ እንዳይገኝ ከፍተኛ ጥንቃቄ አደርግ ነበር። አንድ ቀን ፖሊስ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ቤታችንን በድንገት ወረረ። በአካባቢያችን የሚገኝ ሸቀጦችን በጅምላ የሚያከፋፍል የአንድ ነጋዴ መደብር ተዘርፎ ስለነበር የኤሌክትሪክ ዕቃዎችን ለማግኘት ቤታችንን ሁለት ጊዜ በረበሩት። ምንም ነገር አላገኙም። አሻራዬን ለመውሰድ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱኝ። ሆኖም ክስ አልመሠረቱብኝም።

ወደ አደገኛ ዕፆች ዓለም ገባሁ

ከ12 ዓመቴ ጀምሮ አእምሮን የሚቆጣጠሩ አደገኛ ዕፆችን አዘውትሬ መውሰድ ጀመርኩ። እነዚህን ዕፆች ያለ ገደብ በመውሰዴ ጤንነቴ መቃወስ ጀመረ። እንዲያውም የምወስደው ዕፅ ከመጠን እያለፈ ለአደጋ የተጋለጥኩባቸው ጊዜያት ነበሩ። ብዙም ሳይቆይ ከወንጀለኞች ጋር የጠበቀ ትስስር ካለው አንድ ዶክተር ጋር ተዋወቅኩ። በዚህም ሳቢያ የአደገኛ ዕፆች አዘዋዋሪ ሆንኩ። አደገኛ ዕፆችን ለጥቂት አዘዋዋሪዎች ብቻ የማቀርብ ከሆነ ለአደጋ ይበልጥ የሚጋለጡት እነርሱ በመሆናቸው እኔ ብዙም ለአደጋ ልጋለጥ እንደማልችል ተገነዘብኩ።

የሚያሳዝነው ግን በአደገኛ ዕፆች ዝውውር ከእኔ ጋር ግንኙነት ከነበራቸው ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ እነዚህን ዕፆች ከመጠን በላይ ወስደው ሞተዋል ወይም ደግሞ ዕፆቹ በሚያሳድሩባቸው ግፊት ከባድ ወንጀሎች ፈጽመዋል። አንድ “ጓደኛችን” አንድን የታወቀ ዶክተር ሕይወት አጠፋ። ይህ በመላ አገሪቱ ዋና ርዕሰ ዜና ሆነ። እኔን ሊወነጅለኝ ሞክሮ ነበር። ሆኖም እኔ ፖሊስ ቤቴ ድረስ እስከመጣበት ጊዜ ድረስ ስለተፈጸመው ነገር ምንም የሰማሁት ነገር አልነበረም። እርግጥ ፖሊስ ብዙ ጊዜ እየመጣ ስለተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ይጠይቀኝ ነበር።

ይሁን እንጂ አንድ ቀን አንድ የቂል ሥራ ሠራሁ። ለአንድ ሳምንት ያህል አደገኛ ዕፆችንና አልኮል ከልክ በላይ ስወስድ ከቆየሁ በኋላ በመካከላችን አለመግባባት በመፈጠሩ ሁለት ሰዎችን ደበደብኳቸውና ከባድ ጉዳት አደረስኩባቸው። በነጋታው ጠዋት ጠቁመው አስያዙኝ። ሆን ብለህ ከባድ አካላዊ ጉዳት ለማድረስ ስትል ደብድበሃል በሚል ክስ ተወንጅዬ ታሰርኩ። ወኅኒ ቤት የወረድኩት በዚህ ሳቢያ ነበር።

መጀመሪያ ሀብት ማካበት፣ ከዚያ በኋላ ሕይወትን ማስተካከል

ከወኅኒ ቤት ከወጣሁ በኋላ በአንድ የመድኃኒት ኩባንያ ውስጥ የንብረት ክፍል ኃላፊ ሆኖ የሚሠራ ሰው እንደሚፈለግ ሰማሁ። ማመልከቻ አስገባሁና ለሥራው ብቁ እንደሆንኩ በመግለጽ አሠሪውን አሳመንኩት። በዚያው ኩባንያ ውስጥ የሚሠራ አንድ ጓደኛዬ የድጋፍ ሐሳብ አቀረበልኝና ሥራውን አገኘሁ። ብዙ ገንዘብ ማግኘት የምችልበትና ወደ ሌላ ቦታ ሄጄ ንጹሕ ሥነ ምግባር ያለው ሕይወት መምራት የምችልበት ጥሩ አጋጣሚ እንዳገኘሁ አድርጌ አሰብኩ። ስለዚህ የሥራውን የተለያዩ ዘርፎች በተቻለ መጠን በፍጥነት ለማወቅ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ከመጀመሬም በላይ በየቀኑ ማታ ማታ እያመሸሁ የሁሉንም መድኃኒቶች ስም ማጥናት ጀመርኩ። ይህ ወደ አዲስ ሕይወት የሚመራ መንገድ እንደሆነ እርግጠኛ ሆኜ ነበር።

ዕቅዴ አመቺ ጊዜ እስኪፈጠር ድረስ መጠበቅና አሠሪዎቼ እምነት የሚጥሉብኝ ዓይነት ሰው ሆኜ መገኘት ነበር። ከዚያ በኋላ አመቺ ጊዜ ሲፈጠር ሰብሬ በመግባት በጥቁር ገበያ ላይ ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጡትን የመድኃኒት ዓይነቶች በብዛት ሰርቄ በመሸጥ በአንድ ጀምበር መክበር ነው። ካለሁበት ሁኔታ ለመላቀቅና አዲስ ሕይወት ለመጀመር ያለኝ ዕቅድ እንዳይስተጓጎል ስል ወንጀሉ ሲፈጸም በቦታው እንዳልነበርኩ አድርጌ ማሳመን የምችልበት ምንም እንከን የማይገኝለት ብልሃት ቀየስኩ።

ዕቅዴን ተግባራዊ የማደርግበት ጊዜ ደረሰ። አንድ ቀን ሌሊት ድምፄን አጥፍቼ መጋዘን ውስጥ ከገባሁ በኋላ በመቶ ሺህ የሚቆጠር ዶላር በሚያወጡ መድኃኒቶች የተሞሉ መደርደሪያዎች አየሁ። ከወንጀልና ከዓመፅ ነፃ የሆነ ሕይወት መምራት የምችልበት ዕድል ታየኝ። ሆኖም በሕይወቴ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ሕሊናዬ ይረብሸኝ ጀመር። ሕሊና ያለኝ መሆኑን እንኳ ከናካቴው ዘንግቼው በነበረበት ወቅት ላይ ይህ ድንገተኛ የሆነ የሕሊና ወቀሳ ሊከሰት የቻለው ለምንድን ነው? ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት እንደሆነ ልንገራችሁ።

ይህ ከመሆኑ ከተወሰኑ ሳምንታት በፊት ከሥራ አስኪያጁ ጋር ስለ ሕይወት ትርጉም ውይይት አድርገን ነበር። በውይይታችን መካከል አንድ ነጥብ አንስቶ ስለነበር አንድ ሰው አማራጭ በሚያጣበት ጊዜ መጸለይ ይችላል ብዬ መልሼለት ነበር። “ወደ ማን ነው የሚጸልየው?” ሲል ጠየቀኝ። “ወደ አምላክ” ብዬ መለስኩለት። “አዎን፣ ግን ሰዎች የሚጸልዩላቸው ብዙ አማልክት አሉ፣ አንተ የምትጸልየው ወደማን ነው?” አለኝ። “ሁሉን ቻይ ወደሆነው አምላክ” አልኩት። ቀጠለና “ስሙ ማን ነው?” ሲል ጠየቀኝ። “ምን ማለትህ ነው?” አልኩት። “ልክ አንተና እኔ እንዲሁም ሌላ ማንኛውም ሰው ስም እንዳለው ሁሉ ሁሉን ቻይ የሆነውም አምላክ የግል ስም አለው” ሲል መለሰለኝ። አባባሉ ምክንያታዊ ቢሆንም እንኳ ትንሽ አበሳጨኝ። ስለዚህ “እሺ ታዲያ የአምላክ ስም ማን ነው?” አልኩት ትንሽ በስጨት ብዬ። “ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ስም ይሖዋ ነው!” ሲል መለሰልኝ።

በዚህ ጊዜ በድንገት አንድ ነገር ትዝ አለኝ። ገና የስምንት ዓመት ልጅ እያለሁ ትምህርት ቤት የተማርኩት ትምህርት አእምሮዬ ላይ አቃጨለ። ከሥራ አስኪያጁ ጋር ያደረግነው ውይይት ያሳደረብኝ ተጽዕኖ በጣም የሚያስገርም ነበር። ለሰዓታት ቁጭ ብለን ጥልቀት የተሞላበት ውይይት አደረግን። በሚቀጥለው ቀን ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው እውነት የተባለውን መጽሐፍ አመጣልኝ።a ያን ቀን ማታ መጽሐፉን ከዳር እስከ ዳር አነበብኩትና እውነትንና የሕይወትን ትክክለኛ ትርጉም እንዳገኘሁ ሆኖ ተሰማኝ። በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት አብዛኛውን ጊዜያችንን ያሳለፍነው በዚያች አስገራሚ ሰማያዊ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጹትን የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች በመወያየት ነበር።

ስለዚህ ረጭ ባለውና በጨለማ በተዋጠው መጋዘን ውስጥ ተቀምጬ ሳለሁ መድኃኒቶቹን ለመስረቅና ለመሸጥ ያወጣሁት ዕቅድ ሁሉ ስህተት እንደሆነ ሕሊናዬ ነገረኝ። ሁለተኛ አንዳችም ነገር ላለመስረቅ ቁርጥ ውሳኔ በማድረግ ድምፄን አጥፍቼ ወጣሁና ወደ ቤት ሄድኩ።

ፍጹም የሆነ ለውጥ

በቀጣዮቹ ቀናት አዲስ የሕይወት ጎዳና ለመከተል እንደወሰንኩ ለቤተሰቦቼ ነገርኳቸው። በተጨማሪም የተማርኳቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ለእነሱ ማካፈል ጀመርኩ። አባቴ ከቤት ሊያባርረኝ ፈልጎ ነበር። ሆኖም ወንድሜ ጆን ከእኔ ጎን በመቆም “ኮስታ በሕይወቱ ውስጥ ከወንጀል ነፃ የሆነ ነገር ሲያደርግ ይህ መጀመሪያው መሆኑን እያወቅክ እንዴት ታባርረዋለህ? እኔ ስለዚህ ጉዳይ ይበልጥ ማወቅ እፈልጋለሁ” ሲል አባቴን ተናገረው። ጆን መጽሐፍ ቅዱስ እንዳስጠናው ሲጠይቀኝ ደስታዬ ወሰን አልነበረውም። ከዚያን ጊዜ አንስቶ አደገኛ ዕፆች ከእኔ ለመውሰድ የሚመጣ ሰው ሁሉ በዕፆቹ ፋንታ የእውነትን መጽሐፍ እየያዘ ይሄድ ነበር! ብዙም ሳይቆይ በዚህ መጽሐፍ አማካኝነት 11 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች መምራት ጀመርኩ።

ከጊዜ በኋላ የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ የይሖዋ ምሥክር እንዳልሆነ አወቅኩ። ሚስቱ የይሖዋ ምሥክር ከሆነች 18 ዓመት ገደማ የሆናት ቢሆንም እርሱ ግን “ከእውነት ጋር የተያያዘ ነገር ለማድረግ ምንም ጊዜ” አልነበረውም። ስለዚህ አንድ ተሞክሮ ያለው ምሥክር በቋሚነት መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያስጠናኝ ሁኔታዎችን አመቻቸልኝ። ማጥናት ከጀመርኩ በኋላ ብዙም ሳልቆይ በሕይወቴ ውስጥ ልጋፈጣቸው የሚገቡ ሌሎች ጉዳዮችም እንዳሉ ተገነዘብኩ። በመሆኑም የአምላክ ቃል እውነት እከተላቸው ከነበሩት ዓለማዊ መንገዶች መላቀቅ እንድጀምር ተጽዕኖ ያሳደረብኝ ወዲያውኑ ነበር።—ዮሐንስ 8:32

ይሁን እንጂ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ነገሮች የተለዋወጡበት ፍጥነት ግራ አጋባኝ። ከፍተኛ ለውጥ የሚጠይቁ ሁኔታዎች ከፊቴ ተደቅነዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴ የሚጠቁመኝን አቅጣጫ መከተሌን ከቀጠልኩ በሥጋና በመንፈስ መካከል የሚካሄድ የተጧጧፈ ውጊያ እንደሚጠብቀኝ መገንዘብ ጀመርኩ። በሌላ በኩል ደግሞ ስከተለው በቆየሁት የአኗኗር መንገድ መመላለሴን ከቀጠልኩ ልሞት እንደምችል ወይም ቢያንስ ቢያንስ አብዛኛውን የሕይወት ዘመኔን በወኅኒ የማሳለፍ ዕጣ እንደሚገጥመኝ ተገንዝቤያለሁ። ስለዚህ ብዙ ካሰብኩና ከልቤ ከጸለይኩ በኋላ የእውነትን መንገድ ለመከተል ቁርጥ ውሳኔ አደረግኩ። ከስድስት ወራት በኋላ ሚያዝያ 4, 1971 ላይ በመጠመቅ ራሴን ለይሖዋ አምላክ መወሰኔን በገሃድ አሳየሁ።

ቀና መንገድ በመከተሌ ያገኘኋቸው ወሮታዎች

ወደ ኋላ መለስ ብዬ የወንጀለኛነትን ጎዳና ለመተው ቁርጥ ውሳኔ ካደረግኩበት ጊዜ ጀምሮ ያገኘኋቸውን በረከቶች ሳስብ አንዳንድ ጊዜ በደስታ ስሜት እዋጣለሁ። በእነዚያ ከፍተኛ ለውጥ በተካሄደባቸው ጥቂት የመጀመሪያ ሳምንታት ውስጥ ከእኔ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀምረው ከነበሩት 11 ሰዎች መካከል አምስቱ አሁንም በእውነት ጎዳና ላይ እየተጓዙ ነው። እናቴም መጽሐፍ ቅዱስ አጥንታ የተጠመቀች ምሥክር በመሆን በ1991 እስከሞተችበት ጊዜ ድረስ አምላክን በታማኝነት አገልግላለች። ሁለቱ ወንድሞቼ ሕይወታቸውን ለይሖዋ በመወሰን በአሁኑ ጊዜ ሽማግሌዎች ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው። አክስቴም እውነትን እንድትማር ልረዳት ችያለሁ። ላለፉት 15 ዓመታት የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ሆና ሠርታለች።

እሠራበት የነበረው የመድኃኒት ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ በሕይወቴ ውስጥ ባደረግኳቸው ለውጦች በጣም ተበረታትቶ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ይበልጥ አክብዶ መመልከት ጀመረ። እኔ ከተጠመቅኩ ከአንድ ዓመት በኋላ እሱም ሕይወቱን ለአምላክ መወሰኑን በውኃ ጥምቀት አሳየ። ከጊዜ በኋላ በፕሪቶሪያ በሚገኝ በአንድ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ ለብዙ ዓመታት ሽማግሌ ሆኖ አገልግሏል።

በአሁኑ ጊዜ ራሷን ለይሖዋ ከወሰነች ክርስቲያን እህት ጋር ትዳር መስርቼ በመኖር ላይ ነኝ። ሊኦኒ እና እኔ በ1978 ወደ አውስትራሊያ ሄድን። በዚያም ኢላይጃ እና ፖል የተባሉት ሁለት ወንዶች ልጆቻችን ተወለዱ። ቤተሰቤ የሚሰጠኝ ማበረታቻ ጥሩ የብርታት ምንጭ ሆኖልኛል። በአውስትራሊያ ዋና ከተማ ካንቤራ ውስጥ ሽማግሌ ሆኜ የማገልገል መብት አግኝቻለሁ። ወደ መከራና ወደ ሞት እየመራኝ ከነበረው ትርጉም የለሽ የወንጀለኛነት ሕይወት ስላላቀቀኝ ይሖዋን በየዕለቱ አመሰግነዋለሁ። ከዚህም በላይ ደግሞ ለእኔም ሆነ ለምወዳቸው ሰዎች እውነተኛ ተስፋ በመስጠት ሕይወቴ ትርጉም ያለው እንዲሆን አድርጎልኛል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የ12 ዓመት ልጅ ሳለሁ

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዛሬው ጊዜ ከሚስቴና ከሁለት ወንዶች ልጆቼ ጋር

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ