የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g01 12/8 ገጽ 8-12
  • ድብደባ ለሚፈጸምባቸው ሴቶች የሚሆን እርዳታ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ድብደባ ለሚፈጸምባቸው ሴቶች የሚሆን እርዳታ
  • ንቁ!—2001
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ሚስቶቻቸውን የሚደበድቡ ባሎች ሊለወጡ ይችላሉን?
  • ወንዶች ሴቶችን የሚደበድቡት ለምንድን ነው?
    ንቁ!—2001
  • “ምናልባት አሁን ይለወጥ ይሆናል”
    ንቁ!—2001
  • በቤተሰብ ውስጥ ጠብ የማይኖርበት ጊዜ
    ንቁ!—1998
  • በቤተሰብ ውስጥ ለጠብ መንስኤ የሚሆነው ነገር ምንድን ነው?
    ንቁ!—1998
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—2001
g01 12/8 ገጽ 8-12

ድብደባ ለሚፈጸምባቸው ሴቶች የሚሆን እርዳታ

ጥቃት የሚፈጸምባቸውን ሴቶች ለመርዳት ምን ሊደረግ ይችላል? በመጀመሪያ ደረጃ አንድ ሰው የሚደርስባቸውን ነገር በሚገባ መረዳት መቻል አለበት። ብዙውን ጊዜ የሚደርስባቸው ጉዳት አካላዊ ብቻ አይደለም። በአብዛኛው ዛቻና ማስፈራሪያም ስለሚደርስባቸው ምንም ዋጋ እንደሌላቸውና ምንም ማድረግ እንደማይችሉ ሆኖ ይሰማቸዋል።

በመግቢያው ርዕስ ላይ ታሪኳ የተጠቀሰውን የሮክሳናን ሁኔታ ተመልከት። አንዳንድ ጊዜ ባለቤቷ ቃላትን መሣሪያ አድርጎ ይጠቀማል። “ያንቋሽሸኛል” ስትል ሮክሳና ተናግራለች። “ ‘ትምህርት እንኳን አልጨረሽም። ያለ እኔ እንዴት ልጆቹን ማሳደግ ትችያለሽ? ለምንም ነገር የማትበቂ ሰነፍ እናት ነሽ። ለመሆኑ ጥለሽኝ ብትሄጂ መንግሥት ልጆቹን እንድትወስጂ የሚፈቅድልሽ ይመስልሻል?’ ይለኛል።”

የሮክሳና ባል በገንዘብ ወጪም ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ይጨቁናታል። መኪናቸውን እንድትነዳ የማይፈቅድላት ከመሆኑም በላይ በቀን ውስጥ በተደጋጋሚ ስልክ እየደወለ ምን እንደምታደርግ ይከታተላል። በአንድ ጉዳይ ላይ የራሷን ምርጫ የሚጠቁም አስተያየት ከሰጠች በቁጣ ይገነፍላል። ስለዚህ ሮክሳና ምንም ዓይነት አስተያየት መስጠት እንደሌለባት ታውቃለች።

ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው በትዳር ጓደኛ ላይ የሚፈጸም በደል በጣም ውስብስብ የሆነ ርዕሰ ጉዳይ ነው። እርዳታ መስጠት ትችል ዘንድ በርኅራኄ ለማዳመጥ ሞክር። ብዙውን ጊዜ የእንዲህ ዓይነት ድርጊት ሰለባ የሆነች ሴት የሚደርስባትን ነገር ለመናገር እንደምትቸገር አትዘንጋ። ግብህ አቅሟ በሚፈቅድላት መጠን ሁኔታውን ለመቋቋም በምትወስዳቸው እርምጃዎች ጥንካሬ እንድታገኝ መርዳት መሆን ይኖርበታል።

ድብደባ የሚፈጸምባቸው አንዳንድ ሴቶች ከባለሥልጣናት እርዳታ መሻት ያስፈልጋቸው ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ ችግሩ እንደ ፖሊስ ጣልቃ ገብነት ያለ ሁኔታ እስኪጠይቅ ድረስ ከባድ ደረጃ ላይ በሚደርስበት ጊዜ በደሉን የሚፈጽመው ሰው ድርጊቱ ምን ያህል አሳሳቢ እንደሆነ እንዲገነዘብ ሊያደርገው ይችል ይሆናል። ይሁንና በአብዛኛው የተፈጠረው ችግር ካለፈ በኋላ ግለሰቡ ለውጥ ለማድረግ የነበረውን ሐሳብ መልሶ እንደሚተወው አይካድም።

ድብደባ የተፈጸመባት ሚስት ከባልዋ መለየት ይኖርባታልን? መጽሐፍ ቅዱስ ከትዳር ጓደኛ መለያየትን አቅልሎ አይመለከተውም። ሆኖም ድብደባ የሚፈጸምባት ሚስት ጤናዋን ምናልባትም ሕይወቷን ሳይቀር ለአደጋ ከሚያጋልጥ ሰው ጋር አብራ እንድትኖር አያስገድድም። ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጳውሎስ “ብትለያይ ግን ሳታገባ ትኑር ወይም ከባልዋ ትታረቅ” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 7:​10-16፤ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) መጽሐፍ ቅዱስ በጣም አስከፊ ሁኔታዎች በሚፈጠሩበት ጊዜ መለያየትን የማይከለክል በመሆኑ አንዲት ሴት በዚህ ረገድ የምትወስደው ውሳኔ ለራስዋ የተተወ ነው። (ገላትያ 6:​5) ማንም ሰው ቢሆን አንዲት ሚስት ከባልዋ እንድትለይ ለማሳመን መሞከር የለበትም፤ ወይም ደግሞ አንዲት ድብደባ የሚፈጸምባት ሴት ጤናዋ፣ ሕይወቷና መንፈሳዊነቷ አደጋ ላይ በሚወድቅበት ጊዜ በደል ከሚፈጽምባት ባልዋ ጋር መኖሯን እንድትቀጥል ማንም ሰው ሊገፋፋት አይገባም።

ሚስቶቻቸውን የሚደበድቡ ባሎች ሊለወጡ ይችላሉን?

በትዳር ጓደኛ ላይ በደል መፈጸም የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በቀጥታ የሚጻረር ድርጊት ነው። ኤፌሶን 4:​29, 31 ላይ የሚከተለውን ቃል እናገኛለን:- “ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ። መራርነትና ንዴት ቊጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ።”

የክርስቶስ ተከታይ ነኝ የሚል ማንኛውም ባል በሚስቱ ላይ በደል የሚፈጽም ከሆነ እወዳታለሁ ሊል አይችልም። ሚስቱን የሚበድል ከሆነ የሚሠራቸው ሌሎች መልካም ነገሮች ሁሉ ምን ዋጋ ይኖራቸዋል? ‘የሚማታ’ ሰው በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ልዩ መብቶችን ለማግኘት ብቃት አይኖረውም። (1 ጢሞቴዎስ 3:​3 NW፤ 1 ቆሮንቶስ 13:​1-3) እንዲያውም ምንም ዓይነት የንስሐ ፍሬ ሳያሳይ በተደጋጋሚ በቁጣ የሚገነፍል ክርስቲያን ነኝ የሚል ሰው ከክርስቲያን ጉባኤ ሊወገድ ይችላል።​—⁠ገላትያ 5:​19-21፤ 2 ዮሐንስ 9, 10

ጠበኛ የሆኑ ወንዶች ለውጥ ሊያደርጉ ይችላሉን? አንዳንዶቹ ተለውጠዋል። ብዙውን ጊዜ ግን የትዳር ጓደኛውን የሚደበድብ ሰው (1) ተግባሩ ስህተት መሆኑን አምኖ ካልተቀበለ፣ (2) ምግባሩን ለመለወጥ ፍላጎት ከሌለውና (3) እርዳታ ካልጠየቀ ለውጥ ያደርጋል ብሎ መጠበቅ ዘበት ነው። የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ ለውጥ ለማድረግ ሊገፋፋ የሚችል ከፍተኛ ኃይል እንዳለው ተገንዝበዋል። የማወቅ ጉጉት አድሮባቸው ከእነርሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ያጠኑ በርካታ ሰዎች አምላክን ለማስደሰት የሚገፋፋ ጠንካራ ፍላጎት አዳብረዋል። እነዚህ አዳዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ይሖዋ አምላክን በተመለከተ ‘ዐመፃን የሚወዱትን ነፍሱ እንደምትጠላቸው’ ተምረዋል። (መዝሙር 11:​5 አ.መ.ት ) የትዳር ጓደኛውን የሚደበድብ ሰው የባሕርይ ለውጥ ማድረግ እንዲችል ከመማታት መቆጠብ ብቻ ሳይሆን ለሚስቱ ያለውን አመለካከትም ሙሉ በሙሉ መለወጥ ይኖርበታል።

አንድ ሰው የአምላክን እውቀት ሲያገኝ ሚስቱን እንደ አገልጋይ ሳይሆን እንደ “ረዳት፣” እንደ በታች ሳይሆን ‘አክብሮት’ እንደሚገባት አድርጎ መመልከት እንዳለበት ይማራል። (ዘፍጥረት 2:​18፤ 1 ጴጥሮስ 3:​7) በተጨማሪም ርኅራኄ ማሳየትና የሚስቱን አመለካከት መስማት እንዳለበት ይማራል። (ዘፍጥረት 21:​12፤ መክብብ 4:​1) የይሖዋ ምሥክሮች የዘረጉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮግራም ብዙ ባለትዳሮችን ጠቅሟል። ሥልጣኑን አላግባብ የሚጠቀም፣ አምባገነን ወይም ጉልበተኛ የሆነ ሰው በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ ቦታ የለውም።​—⁠ኤፌሶን 5:​25, 28-30

“የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ ነው።” (ዕብራውያን 4:​12 አ.መ.ት ) ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ጥበብ ባለ ትዳሮች የሚገጥሟቸውን ችግሮች በሚገባ እንዲያጤኑና እነዚህን ችግሮች ለመወጣት የሚያስችል ቆራጥነት እንዲኖራቸው ይረዳቸዋል። ከዚህ ይበልጥ ግን መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋ ሰማያዊ ንጉሥ ታዛዥ በሆኑ የሰው ዘሮች ሁሉ ላይ በሚገዛበት ጊዜ የሚመጣውን ከጥቃት ነፃ የሆነ ዓለም የመውረስ አስተማማኝ የሆነና የሚያጽናና ተስፋ ይዟል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ችግረኛውን ከቀማኛው እጅ፣ ረዳት የሌለውንም ምስኪን ያድነዋልና። ከግፍና ከጭንቀት ነፍሳቸውን ያድናል።”​—⁠መዝሙር 72:​12, 14

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ሥልጣኑን አላግባብ የሚጠቀም፣ አምባገነን ወይም ጉልበተኛ የሆነ ሰው በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ ቦታ የለውም

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን ማረም

• ድብደባ የሚፈጸምባቸው ሴቶች ለባሎቻቸው ድርጊት ተጠያቂ ናቸው።

ሚስቶቻቸውን የሚደበድቡ ብዙ ባሎች ድርጊቱን እንዲፈጽሙ የሚያነሳሷቸው ሚስቶቻቸው እንደሆኑ በመግለጽ ራሳቸውን ከተጠያቂነት ነፃ ለማድረግ ይሞክራሉ። የቤተሰቡ ወዳጅ የሆኑ አንዳንድ ሰዎች ሳይቀሩ ሚስትየው አስቸጋሪ እንደሆነችና ባልየው አልፎ አልፎ ራሱን መቆጣጠር ቢሳነው ምንም እንደማያስደንቅ አድርገው ሊያስቡ ይችላሉ። ይህ ግን የጥቃቱ ሰለባ በሆነችው ሴት ከማመካኘትና ድርጊቱን የሚፈጽመውን ሰው ከተጠያቂነት ነፃ ከማድረግ ተለይቶ አይታይም። እውነት ለመናገር ከሆነ ድብደባ የሚፈጸምባቸው ሚስቶች ብዙውን ጊዜ የባሎቻቸውን መንፈስ ለማረጋጋት የማያደርጉት ጥረት የለም። ከዚህም በላይ በማንኛውም ሁኔታ ቢሆን የትዳር ጓደኛን መደብደብ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም። ዘ ባተረር​—⁠ኤ ሳይኮሎጂካል ፕሮፋይል የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “በሚስቶቻቸው ላይ ጥቃት በመፈጸማቸው የተነሳ በፍርድ ቤት ትእዛዝ የሥነ ልቦና ሕክምና የሚደረግላቸው ወንዶች የመደብደብ ሱስ የተጠናወታቸው ናቸው። ቁጣቸውን ለማብረድ፣ ካደረባቸው የመንፈስ ጭንቀት ለመገላገል፣ የሚፈጠሩትን ግጭቶች ኃይል ተጠቅመው ለመፍታትና ውጥረትን ለማርገብ መሣሪያ አድርገው ይጠቀሙበታል። . . . ብዙውን ጊዜ ተጠያቂነታቸውን አምነው አይቀበሉም ወይም ችግሩን አክብደው አይመለከቱትም።”

• አንድ ሰው አልኮል መጠጣቱ ሚስቱን እንዲደበድብ ያነሳሳዋል።

አንዳንድ ወንዶች በሚጠጡበት ጊዜ ይበልጥ ጠበኛ እንደሚሆኑ አይካድም። ይሁን እንጂ አልኮሉን ማመካኛ ማድረግ ምክንያታዊ ነውን? ኬ ጄ ዊልሰን ዌን ቫዮለንስ ቢጊንስ አት ሆም በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “ሰውየው መስከሩ ራሱን ከመውቀስ ይልቅ ድርጊቱን የሚያመካኝበት ነገር እንዲያገኝ ያደርገዋል” ሲሉ ጽፈዋል። አክለውም እንዲህ ብለዋል:- “ኅብረተሰባችን የሰከረ ሰው በቤት ውስጥ የሚፈጽመውን የኃይል ድርጊት ለመቀበል ብዙም የሚቸገር አይመስልም። ድብደባ የተፈጸመባት ሴት ባልዋን እንደሚበድላት አድርጋ ከመመልከት ይልቅ ከባድ ጠጪ ወይም የአልኮል ሱሰኛ እንደሆነ አድርጋ መመልከት ይቀናታል።” ዊልሰን እንዳመለከቱት እንዲህ ያለው አስተሳሰብ አንዲት ሴት “ሰውየው መጠጣቱን ካቆመ ድብደባውንም ያቆማል” የሚል የማይሆን ተስፋ እንዲያድርባት ሊያደርግ ይችላል።

በአሁኑ ጊዜ ብዙ ተመራማሪዎች አልኮል መጠጣትና የትዳር ጓደኛን መደብደብ ሁለት የተለያዩ ችግሮች እንደሆኑ አድርገው መመልከት ጀምረዋል። ደግሞም ሱስ የሚያስይዙ ነገሮችን የሚወስዱ አብዛኞቹ ወንዶች የትዳር ጓደኞቻቸውን አይደበድቡም። ዌን ሜን ባተር ዊሜን የተባለው መጽሐፍ ደራሲዎች እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “ሰውየው ሚስቱን መደብደቡን እንዲቀጥል የሚያደርገው መሠረታዊው ምክንያት ሚስቱን መቆጣጠር፣ ማስፈራራትና ተገዢ ማድረግ መቻሉ ነው። . . . ይህ ሰው አልኮል ከልክ በላይ የመጠጣትና አደገኛ ዕፆችን የመውሰድ ልማድ የተጠናወተው ነው። ሆኖም የኃይል ድርጊት እንዲፈጽም የሚያነሳሳው ይህ ልማድ ነው ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው።”

• የትዳር ጓደኛቸውን የሚደበድቡ ወንዶች ከሁሉም ሰው ጋር ይጋጫሉ።

ብዙውን ጊዜ የትዳር ጓደኛውን የሚደበድብ ሰው ለሌሎች ጥሩ ጓደኛ መሆን ይችላል። የውጪ አልጋ የቤት ቀጋ ይሆናል። የቤተሰቡ ወዳጅ የሆኑ ሰዎች ሚስቱን እንደሚደበድብ ሲሰሙ ለማመን የሚቸገሩት ለዚህ ሊሆን ይችላል። እውነታው ግን ሰውየው ሚስቱን ተገዢ ለማድረግ ጨካኝ መሆንን መምረጡ ነው።

• ሴቶች መመታታቸውን አይቃወሙም።

ይህ አስተሳሰብ መሄጃ የሌላት አንዲት ሴት ልታደርገው የምትችለው ነገር አለመኖሩን ካለመረዳት የመነጨ ሊሆን ይችላል። ድብደባ የሚፈጸምባት ሚስት ለአንድ ለሁለት ሳምንት ሊያስጠጓት የሚችሉ ጓደኞች ይኖሯት ይሆናል፤ ከዚያ በኋላስ እንዴት ትሆናለች? ሥራ መያዝና የቤት ኪራይ እየከፈሉ ልጆችን ማሳደግ የማይቻል ነገር ይሆንባታል። በተጨማሪም ሕጉ ልጆቹን ይዛ እንዳትሄድ ይከለክላት ይሆናል። አንዳንዶች እንዲህ ለማድረግ የሞከሩ ቢሆንም ካሉበት ታድነው በግድ አለዚያም ደግሞ በአንዳንድ ማባበያዎች ተመልሰው እንዲገቡ ተደርጓል። ይህን መረዳት ያልቻሉ ወዳጆች እንዲህ ያሉት ሴቶች የሚፈጸምባቸውን በደል እንደማይቃወሙ አድርገው በተሳሳተ መንገድ ሊያስቡ ይችላሉ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ