የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g 6/06 ገጽ 7-9
  • በመጨረሻ በምድር ላይ ሰላም ይሰፍናል!

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በመጨረሻ በምድር ላይ ሰላም ይሰፍናል!
  • ንቁ!—2006
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ዓመጽ ችግራችንን አይፈታም
  • በአምላክ መታመን ያለብን ለምንድን ነው?
  • ሰላም በምድር ላይ ለዘላለም ይሰፍናል!
  • ሽብርተኝነት የሚወገድበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?
    ተጨማሪ ርዕሰ ጉዳዮች
  • “አትፍሩ፣ አትደንግጡም”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2003
  • በደም የተጻፈ ታሪክ
    ንቁ!—2006
  • ዓመፅ ለዘለቄታው የሚወገደው እንዴት ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—2006
g 6/06 ገጽ 7-9

በመጨረሻ በምድር ላይ ሰላም ይሰፍናል!

አንዳንዶች ፖለቲካዊ ነጻነት ለማግኘትና ንጹሕ ሃይማኖት ለመመሥረት ብቸኛው አማራጭ ዓመጽ ይመስላቸዋል፤ እንዲሁም የማይፈለጉ ገዥዎችን ለማስወገድ ብቸኛው መንገድ የኃይል እርምጃ እንደሆነ ይሰማቸዋል። አንዳንድ መንግሥታትም ሥርዓት ለማስከበርና ተገዢዎቻቸውን በቁጥጥራቸው ሥር ለማድረግ ሲሉ የሽብር ተግባር ይፈጽማሉ። ሽብርተኝነት ለአገዛዝና ማኅበራዊ ለውጥ ለማምጣት ውጤታማ መሣሪያ ነው ከተባለ ሰላምን፣ ብልጽግናንና መረጋጋትን ማስፈን ይገባዋል። በተጨማሪም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ዓመጽና ፍርሃት መቀነስ አለባቸው። ታዲያ እንዲህ ያለ ውጤት ተመልክተናል?

እውነታው እንደሚያሳየው ሽብርተኝነት ሰዎች ለሕይወት ሊኖራቸው የሚገባውን አክብሮት ይቀንሳል፤ እንዲሁም ወደ ደም መፋሰስና ወደ ጭካኔ ይመራል። የሽብር ተጠቂዎች በጣም ስለሚያዝኑ ብዙውን ጊዜ አጸፋ ለመመለስ ይነሳሳሉ፤ ይህም ወደባሰ ጭቆና ስለሚመራ ተጨማሪ በቀል ለመፈጸም ያነሳሳል።

ዓመጽ ችግራችንን አይፈታም

የሰው ልጆች በሺህ ለሚቆጠሩ ዘመናት ፖለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ችግሮቻቸውን በራሳቸው መንገድ ለመፍታት ሲሞክሩ ቆይተዋል። ነገር ግን ያደረጓቸው ሙከራዎች ሁሉ ከሽፈዋል። መጽሐፍ ቅዱስም “እግዚአብሔር ሆይ፤ የሰው ሕይወት በራሱ እጅ እንዳልሆነች፣ አካሄዱንም በራሱ አቃንቶ ሊመራ እንደማይችል ዐውቃለሁ” በማለት ይህ የሆነበትን ምክንያት ይናገራል። (ኤርምያስ 10:23) ኢየሱስ “የጥበብ ትክክለኛነት በሥራዋ ይገለጣል” ብሏል። (ማቴዎስ 11:19 የ1980 ትርጉም) እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ያላቸው አንድምታ ሽብርተኝነት የተሳሳተ ተስፋ እንደሆነ ይጠቁማል። ሽብርተኝነት የሚያፈራው ፍሬ ነፃነትና ደስታ ሳይሆን ሞት፣ መከራና ጥፋት ነው። ይህ መጥፎ ፍሬ 20ኛውን መቶ ዘመን ሞልቶት የነበረ ከመሆኑም በላይ የ21ኛውንም መቶ ዘመን መባቻ አጥለቅልቆታል። ብዙ ሰዎች ሽብርተኝነት መፍትሄ ሳይሆን ራሱ አንዱ ችግር እንደሆነ ይናገራሉ።

“በየዕለቱ ከቤተሰቤ ወይም ከጓደኞቼ መካከል ማንም ባልሞተ ብዬ እመኛለሁ . . . ለዚህ ግን ተዓምር ሳያስፈልገን አይቀርም።” እንዲህ ብላ የጻፈችው በሽብርተኞች ጥቃት ታምሶ በነበረ አገር ውስጥ የምትኖር ወጣት ነች። ይህች ወጣት የተናገረቻቸው ቃላት ብዙ ሰዎች የደረሱበትን መደምደሚያ የሚያንጸባርቅ ነው:- የሰው ልጅ ችግሮች መፍትሄ ከሰው አቅም በላይ ነው። ሽብርተኝነትን ጨምሮ በአሁኑ ጊዜ በምድር ላይ ያሉትን ችግሮች መፍታት የሚችለው የሰው ልጆች ፈጣሪ ብቻ ነው። ነገር ግን በአምላክ መታመን ያለብን ለምንድን ነው?

በአምላክ መታመን ያለብን ለምንድን ነው?

አንደኛው ምክንያት፣ ይሖዋ ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን ሕይወት የሰጠን ከመሆኑም በላይ ሰላምና እርካታ አግኝተን በሕይወታችን እንድንደሰት ስለሚፈልግ ነው። የአምላክ ነቢይ የነበረው ኢሳይያስ እንዲህ ብሎ ለመጻፍ ተነሳስቷል:- “እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ አባታችን ነህ፤ እኛ ሸክላዎች፣ አንተም ሸክላ ሠሪ ነህ፤ ሁላችንም የእጅህ ሥራ ነን።” (ኢሳይያስ 64:8) ይሖዋ የሰው ዘር አባት ነው፤ እንዲሁም የሁሉም ብሔር ሰዎች ለእርሱ ውድ ናቸው። ሽብርተኝነትን የሚቀሰቅሱት የፍትሕ መጓደልና ጥላቻ በእርሱ ስህተት የተፈጠሩ ነገሮች አይደሉም። በአንድ ወቅት ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “እግዚአብሔር ሰውን ቅን አድርጎ [ሠራው]፣ ሰዎች ግን ውስብስብ ዘዴ ቀየሱ” ብሏል። (መክብብ 7:29) የሽብርተኝነት ዋነኛው መንስኤ የአምላክ ብቃት ማነስ ሳይሆን የሰዎች ክፋትና የአጋንንት ተጽዕኖ ነው።—ኤፌሶን 6:11, 12

በይሖዋ እንድንተማመን የሚያስችለን ሌላው ምክንያት ደግሞ፣ የሰው ልጆችን ስለፈጠረ የችግራቸው መንስኤ ምን እንደሆነና እንዴት መፍታት እንደሚቻል ከማንም በበለጠ የሚያውቅ በመሆኑ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በምሳሌ 3:19 ላይ “እግዚአብሔር በጥበብ ምድርን መሠረተ፤ በማስተዋል ሰማያትን በየስፍራቸው አጸና” በማለት ይህንን ሐቅ ያረጋግጣል። በአምላክ ላይ ሙሉ እምነት የነበረው በጥንት ዘመን የኖረ አንድ ሰው እንዲህ ብሎ ጽፏል:- “ረድኤቴ ከወዴት ይመጣል? ረድኤቴ ሰማይንና ምድርን ከፈጠረ፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ ይመጣል።”—መዝሙር 121:1, 2

በአምላክ እንድንታመን የሚያስችለን ሦስተኛው ምክንያት ደግሞ ይሖዋ ከፍተኛ ደም መፋሰስ የሚያስከትሉ ድርጊቶችን ለማስቆም ኃይል ያለው መሆኑ ነው። በኖኅ ዘመን ‘ምድር በዐመፅ ተሞልታ’ ነበር። (ዘፍጥረት 6:11) አምላክ አፋጣኝ የሆነ የፍርድ እርምጃ የወሰደ ሲሆን ፍርዱ ምድር አቀፍ ይዘት ነበረው። መጽሐፍ ቅዱስ “[አምላክ] ለቀድሞው ዓለም ሳይራራ በኀጢአተኞች ላይ የጥፋት ውሃ” እንዳመጣ ይናገራል።—2 ጴጥሮስ 2:5

መጽሐፍ ቅዱስ በኖኅ ዘመን ከደረሰው የጥፋት ውኃ ትምህርት ማግኘት እንዳለብን ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “ጌታ፣ በእውነት እያመለኩት የሚኖሩትን ከፈተና እንዴት እንደሚያድናቸውና ዐመፀኞችን እየቀጣ ለፍርድ ቀን እንዴት ጠብቆ እንደሚያቈያቸው ያውቃል።” (2 ጴጥሮስ 2:9) አምላክ የተሻለ ሕይወት ለማግኘት ከልብ የሚፈልጉትንና የሌሎችን ሕይወት መራራ የሚያደርጉትን ሰዎች ለይቶ ያውቃቸዋል። የሌሎችን ሕይወት መራራ የሚያደርጉትን ሰዎች “ኀጢአተኞች እስከሚጠፉበት” ጊዜ ድረስ ለይቶ ያቆያቸዋል። ነገር ግን ሰላም ለሚፈልጉ ሰዎች ጽድቅ የሚኖርበትን አዲስ ምድር አዘጋጅቷል።—2 ጴጥሮስ 3:7, 13

ሰላም በምድር ላይ ለዘላለም ይሰፍናል!

የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች “ምድር” የሚለውን ቃል የሰው ልጆችን ለማመልከት ብዙ ጊዜ ተጠቅመውበታል። ለምሳሌ ያህል፣ ዘፍጥረት 11:1 በ1954 ትርጉም “ምድርም ሁሉ” ማለትም በዚያን ጊዜ የነበሩት ሰዎች አንድ ቋንቋ እንደነበራቸው ይናገራል። ሐዋርያው ጴጥሮስ ስለ “አዲስ ምድር” ሲናገር በአእምሮው ይዞ የነበረው ይህን ፍቺ ነው። ይሖዋ አምላክ ዓመጽንና ጥላቻን በጽድቅና በፍትሕ በመተካት ሰብዓዊውን ኅብረተሰብ ያድሳል። መጽሐፍ ቅዱስ በሚክያስ 4:3 ላይ እንዲህ የሚል ትንቢት ይናገራል:- “እርሱ በብዙ ሕዝብ መካከል ይፈርዳል፤ በሩቅና በቅርብ ባሉ ኀያላን መንግሥታት መካከል ያለውን ግጭት ያቆማል፤ ሰይፋቸውን ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ያደርጉታል። አንዱ መንግሥት በሌላው መንግሥት ላይ ሰይፍ አያነሣም፤ ከእንግዲህም የጦርነት ትምህርት አይማሩም።”

ይህ ትንቢት ፍጻሜውን ሲያገኝ ሰዎች ምን ዓይነት ሕይወት ይኖራሉ? ሚክያስ 4:4 “እያንዳንዱ ሰው በገዛ ወይኑ ሥር፣ ከገዛ በለሱም ሥር ይቀመጣል፤ የሚያስፈራቸው አይኖርም” ይላል። ገነት በሆነው ምድር ላይ ማንም ሰው የሽብርተኞች ጥቃት ይፈጸም ይሆናል ብሎ አይፈራም። ይህ ተስፋ እንደሚፈጸም ታምናለህ? ይህንን ቃል ‘የተናገረው የእግዚአብሔር ጸባኦት አፍ’ በመሆኑ ሊታመን የሚችል ነው።—ሚክያስ 4:4

ስለዚህ ሽብርተኞች የሚፈጥሩት ስጋት እያየለ ቢመጣም፣ እንዲሁም ብሔራት በሚፈጸመው ዓመጽ ምክንያት ቢርዱም ሰላም ወዳድ ለሆኑ ሰዎች ያለው መፍትሄ በይሖዋ ላይ መታመን ነው። እርሱ ሊፈታው የማይችለው ችግር የለም። ይሖዋ የሚደርሰውን ጉዳትና ስቃይ አልፎ ተርፎም ሞትን ያስወግዳል። መጽሐፍ ቅዱስ “ሞትንም ለዘላለም ይውጣል። ጌታ እግዚአብሔር ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል” ይላል። (ኢሳይያስ 25:8) በአሁኑ ጊዜ ሽብርተኝነት ባስከተለው ስቃይና ፍርሃት የተሞሉ ውብ አካባቢዎች በቅርቡ የሰላም ፍሬ ይትረፈረፍባቸዋል። የሰው ልጆች በጣም የሚመኙት፣ “የማይዋሸው አምላክ” እንደሚያመጣው ቃል የገባውን እንዲህ ያለውን ሰላም ለማግኘት ነው።—ቲቶ 1:2፤ ዕብራውያን 6:17, 18

ከጥይትና ከፈንጂ የተሻለ አማራጭ

ከዚህ ቀጥሎ ያሉትን አስተያየቶች የሰጡት ፓለቲካዊ ለውጥ ማምጣት የሚቻለው በዓመጽ እንደሆነ ያምኑ የነበሩ ግለሰቦች ናቸው።

  • “የታሪክ መጻሕፍትን ሳነብ ነገሥታትና ከፍተኛ ባለ ሥልጣናት ምንጊዜም ድሆችን እንደሚጨቁኑ ተረዳሁ። ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው ሰዎች ሥቃይ ይሰማኝ ነበር። ይህ ችግር እንዴት መፈታት እንደሚችል ካሰብኩ በኋላ ጠመንጃ ማንሳት አለብን የሚል መደምደሚያ ላይ ደረስኩ።”—ራሞንa

  • “በትጥቅ ትግል ውስጥ ገብቼ ነበር። ዓላማዬ የቀድሞውን መንግሥት መቃወምና በዓለም ሕዝቦች መካከል ያለውን የኑሮ ልዩነት የሚያስወግድ ማኅበረሰብ መፍጠር ነበር።”—ሉቻን

  • “ከልጅነቴ ጀምሮ የፍትሕ መጓደል ያበሳጨኝ ነበር። ይህም ድህነትንና ወንጀልን እንዲሁም ጥሩ ትምህርትና ሕክምና አለማግኘትን ይጨምራል። ሁሉም ሰው እንዲማር፣ የጤና እንክብካቤ እንዲደረግለት፣ ቤት እንዲኖረውና ሥራ እንዲያገኝ ማድረግ የሚቻለው በመሣሪያ ኃይል እንደሆነ አምን ነበር። በተጨማሪም ሥርዓታማ መሆንና የአካባቢውን ነዋሪዎች ማክበር የማይፈልግ ሰው መቀጣት እንዳለበት ይሰማኝ ነበር።”—ፒተር

  • “እኔና ባለቤቴ የተቃውሞ ዓመጽን የሚያበረታታ ምስጢራዊ ድርጅት አባላት ነበርን። ለኅብረተሰቡ ደህንነትንና ሥርዓታማነትን የሚያሰፍን እንዲሁም ለሁሉም እኩልነት የሚያመጣ መንግሥት የማቋቋም ዓላማ ነበረን። በአገራችን ፍትሕን ማስፈን የሚቻለው በዓመጽ ብቻ እንደሆነ ይሰማን ነበር።”—ሉርዴስ

እነዚህ ግለሰቦች ለሥቃይ የተዳረገውን የሰው ልጅ ለመርዳት ኃይል ለመጠቀም ሞክረዋል። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ካጠኑ በኋላ ግን የአምላክ ቃል የተሻለ አማራጭ መኖሩን እንደሚገልጽ ተገነዘቡ። መጽሐፍ ቅዱስ በያዕቆብ 1:20 ላይ “የሰው ቊጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አያመጣም” ይላል።

ሰብዓዊውን ኅብረተሰብ መቀየር የሚችለው የአምላክ አገዛዝ ብቻ ነው። እንደ ማቴዎስ ምዕራፍ 24 እና 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5 ያሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች የአምላክ መንግሥት ይህንን የሚፈጽምበት ጊዜ እንደቀረበ ያሳያሉ። አንተም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት እነዚህን እውነታዎች እንድትማር እናበረታታሃለን።

a ስሞቹ ተቀይረዋል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ