የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g 12/10 ገጽ 5-8
  • ገናን በተመለከተ ሐቁ ምንድን ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ገናን በተመለከተ ሐቁ ምንድን ነው?
  • ንቁ!—2010
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ሐሰተኛ በዓል!
  • የገና በዓል ልማዶችን መከተል ስህተት አለው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2015
  • የገና በዓል በምሥራቃውያን ዘንድ ሳይቀር የሚከበረው ለምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ገና በእርግጥ ክርስቲያናዊ በዓል ነውን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • የዘመናዊው የገና በዓል አመጣጥ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—2010
g 12/10 ገጽ 5-8

ገናን በተመለከተ ሐቁ ምንድን ነው?

ስለ ሃይማኖታዊ በዓላትና ትምህርቶች እውነታውን ማወቅ አስፈላጊ እንደሆነ ይሰማሃል? እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ሳታነሳ አትቀርም፦ (1) ኢየሱስ የተወለደው በእርግጥ ታኅሣሥ 29 (ታኅሣሥ 25 እ.ኤ.አ) ነው? (2) “ጠቢባኑ” እነማን ነበሩ? ቁጥራቸውስ ሦስት ነበር? (3) ወደ ኢየሱስ የመራቸው ምን ዓይነት “ኮከብ” ነበር? (4) የገና አባት ከኢየሱስና ከልደቱ ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው? (5) አምላክ በገና በዓል ሰሞን የሚታየውን ስጦታ የመለዋወጥ ልማድ እንዴት ይመለከተዋል?

እስቲ እነዚህን ጥያቄዎች ከመጽሐፍ ቅዱስና ከታሪክ አንጻር እንመልከታቸው።

(1) ኢየሱስ የተወለደው ታኅሣሥ 29 ነው?

እምነት፦ ኢየሱስ የተወለደው ታኅሣሥ 29 (ታኅሣሥ 25 እ.ኤ.አ) እንደሆነ የሚታመን ሲሆን ልደቱ በዚህ ዕለት ይከበራል። የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል ያዘጋጀው የአማርኛ መዝገበ ቃላት፣ ገና “በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ታህሳስ 29 . . . የሚከበር ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት ቀን” እንደሆነ ይገልጻል።

ምንጩ፦ ዘ ክሪስማስ ኢንሳይክሎፒዲያ እንደገለጸው “[ገና] ታኅሣሥ 25 ላይ መከበር የጀመረው መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት በማድረግ ሳይሆን . . . በዓመት መጨረሻ ላይ ይከበሩ የነበሩ የሮማውያን አረማዊ በዓላትን በመከተል ነው”፤ በሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ ይህ ጊዜ የሚውለው ቀኖቹ አጭር በሚሆኑበት ወቅት አካባቢ ነው። እነዚህ በዓላት የእርሻ አምላክ የሆነው ሳተርን የሚከበርበትን የሳተርናሊያ በዓል “እንዲሁም ሁለት የፀሐይ አማልክት ይኸውም የሮማውያኑ ሶል እና የፋርሳውያኑ ሚትራ የሚከበሩባቸውን ጥምር በዓላት ያካትታሉ” ይላል ይኸው ኢንሳይክሎፒዲያ። የእነዚህ አማልክት የልደት በዓላት የሚከበሩት በጁልያን የዘመን አቆጣጠር መሠረት ቀኑ በጣም አጭር በሆነበት ዕለት ይኸውም በታኅሣሥ 25 ነበር።

እነዚህ የአረማውያን በዓላት “ክርስቲያናዊ” በዓላት የሆኑት በ350 ዓ.ም. ሲሆን በዚህ ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጁልየስ ቀዳማዊ፣ ታኅሣሥ 25 የክርስቶስ የልደት ቀን መሆኑን አውጀው ነበር። ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሪልጅን እንዲህ ብሏል፦ “ቀኖቹ አጭር በሚሆኑበት ጊዜ አካባቢ የሚከበሩት በዓላት በሙሉ ቀስ በቀስ በልደት [በገና] በዓል ተተኩ። ከሞት የተነሳውን ክርስቶስን (ሶል ኢንቪክቱስ ተብሎም ይጠራል) ለማመልከት በፀሐይ ምስል መጠቀም እየተለመደ የመጣ ሲሆን ቀደም ሲል . . . በነገሥታት አናት ላይ ይደረግ የነበረው የፀሐይ ምልክት በክርስትና ቅዱሳን አናት ላይ በሚደረገው አክሊለ ብርሃን ተተካ።”

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ የተወለደበትን ቀን አይናገርም። ያም ቢሆን ኢየሱስ ታኅሣሥ 29 (ታኅሣሥ 25 እ.ኤ.አ) እንዳልተወለደ በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ኢየሱስ በተወለደበት ወቅት እረኞች በቤተልሔም አቅራቢያ “ሌሊት ሜዳ ላይ መንጎቻቸውን ሲጠብቁ” እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ሉቃስ 2:8) ቀዝቃዛ የሆነው የዝናብ ወቅት አብዛኛውን ጊዜ የሚጀምረው በጥቅምት ወር ነው፤ በዚህ ጊዜ በተለይ እንደ ቤተልሔም ባሉት ደጋማ አካባቢዎች የሚኖሩ እረኞች በጎቻቸውን የሚያሳድሩት መጠለያ ባለው ቦታ ነበር። በጣም ቀዝቃዛ የሆነው ወር ታኅሣሥ ሲሆን በዚህ ወቅት አንዳንድ ጊዜ በረዶ ይጥላል።a

የጥንቶቹ ክርስቲያኖች (ብዙዎቹ ኢየሱስ አገልግሎቱን ሲያከናውን አብረውት ነበሩ) በየትኛውም ቀን ቢሆን የኢየሱስን ልደት አክብረው የማያውቁ መሆኑ ልብ ሊባል የሚገባው ነው። እነዚህ ክርስቲያኖች ኢየሱስ ባዘዛቸው መሠረት ያከበሩት ሞቱን ብቻ ነበር። (ሉቃስ 22:17-20፤ 1 ቆሮንቶስ 11:23-26) እንዲያም ሆኖ አንዳንዶች ‘ገና ከአረማውያን በዓል የተወረሰ መሆኑ ለውጥ ያመጣል?’ ይሉ ይሆናል። አዎን፣ ለአምላክ ለውጥ ያመጣል። ኢየሱስ ክርስቶስ “እውነተኛ አምላኪዎች አብን በመንፈስና በእውነት [እንደሚያመልኩት]” ተናግሯል።—ዮሐንስ 4:23

(2) “ሰብአ ሰገል” ስንት ነበሩ? ምን ዓይነት ሰዎችስ ነበሩ?

እምነት፦ “ሰብአ ሰገል” ወይም “ጠቢባን” የሆኑ ሦስት ሰዎች በአንድ “ኮከብ” እየተመሩ ከምሥራቅ እንደመጡና በግርግም ውስጥ ተኝቶ ለነበረው ለኢየሱስ ስጦታ እንዳቀረቡለት የሚያሳዩ ሥዕሎችን ማየት የተለመደ ነው። በሥዕሎቹ ላይ አንዳንድ ጊዜ እረኞችም ይታያሉ።

ምንጩ፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሰው አጭር ትረካ ውጭ “ስለ ሦስቱ ጠቢባን የተጻፈው ነገር ሁሉ በአብዛኛው ከአፈ ታሪክ የመጣ ነው” ይላል ዘ ክሪስማስ ኢንሳይክሎፒዲያ።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኢየሱስን የጎበኙት “ጠቢባን” ስንት እንደነበሩ አይናገርም። ሁለት፣ ሦስት አሊያም አራት ወይም ከዚያ በላይ ሊሆኑ ይችላሉ። እንደ አማርኛው አዲሱ መደበኛ ትርጉም ያሉ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች እነዚህን ሰዎች “ጠቢባን” ብለው ይጠሯቸዋል፤ ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ ቃሉ ሜጆይ ሲሆን ኮከብ ቆጣሪ ወይም ጠንቋይ የሚል ፍቺ አለው፤ በ1954 ትርጉም ላይ እነዚህ ሰዎች “ሰብአ ሰገል” የተባሉ ሲሆን ትርጉሙም ኮከብ ቆጣሪዎች፣ የጥንቆላ ሰዎች ማለት ነው። እንደነዚህ ያሉ ሰዎች “በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ” መሆናቸውን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ዘዳግም 18:10-12) ኮከብ ቆጣሪዎቹ ከምሥራቅ በመነሳት ረጅም ርቀት ተጉዘው (ምናልባትም ለወራት ሊሆን ይችላል) ስለመጡ ኢየሱስን ያገኙት ግርግም ውስጥ ተኝቶ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ “ቤት” ውስጥ ነበር። እዚያም “ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር [እንዳዩት]” መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—ማቴዎስ 2:11

(3) ኮከብ ቆጣሪዎቹን የመራቸው ምን ዓይነት ኮከብ ነበር?

ኮከቡ ሰዎቹን ወዴት እንደመራቸው መመልከታችን ፍንጭ ይሰጠናል። በመጀመሪያ ደረጃ ኮከቡ ሰዎቹን በቀጥታ ወደ ቤተልሔም አልመራቸውም፤ ከዚህ ይልቅ ወደ ኢየሩሳሌም የመራቸው ሲሆን በዚያም ስለ ኢየሱስ ያቀረቡት ጥያቄ ንጉሥ ሄሮድስ ጆሮ ደረሰ። ሄሮድስ ይህን ሲሰማ “ኮከብ ቆጣሪዎቹን በድብቅ ጠርቶ” ጥያቄ አቀረበላቸው፤ እነሱም በቅርቡ ስለተወለደው “የአይሁድ ንጉሥ” ነገሩት። ከዚያም ሄሮድስ “ሄዳችሁ ሕፃኑን በደንብ ፈልጉ፤ ባገኛችሁትም ጊዜ . . . መጥታችሁ ንገሩኝ” አላቸው። ይሁንና ሄሮድስ ስለ ኢየሱስ ማወቅ የፈለገው መልካም ነገር አስቦ አልነበረም። ይህ ትዕቢተኛና ጨካኝ ንጉሥ ኢየሱስን ለመግደል ቆርጦ ነበር!—ማቴዎስ 2:1-8, 16

የሚገርመው ነገር ኮከብ ቆጣሪዎቹ ከንጉሡ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ “ኮከቡ” በስተደቡብ ወደምትገኘው ወደ ቤተልሔም መራቸው። እዚያም ሲደርሱ ኢየሱስ በነበረበት ቤት ላይ ‘ቆመ።’—ማቴዎስ 2:9, 10

ይህ ተራ ኮከብ እንዳልነበረ ምንም ጥያቄ የለውም! የኢየሱስን መወለድ ለእረኞች ለማብሰር በመላእክት የተጠቀመው አምላክ፣ አረማዊ የሆኑ ኮከብ ቆጣሪዎችን መጀመሪያ የኢየሱስ ጠላት ወደሆነ ሰው ከዚያ በኋላ ደግሞ ወደ ኢየሱስ ለመምራት በኮከብ የሚጠቀምበት ምን ምክንያት ይኖራል? ከዚህ ማየት እንደምንችለው ኮከቡ፣ ሰይጣን የክፋት ዓላማውን ለማሳካት የተጠቀመበት መሣሪያ ነበር ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ይሆናል፤ ሰይጣን እንደነዚህ ባሉ ምልክቶች የመጠቀም ችሎታ አለው። (2 ተሰሎንቄ 2:9, 10) ከላይ ከተመለከትናቸው ነጥቦች አንጻር በገና ዛፍ አናት ላይ የቤተልሔም ኮከብ የሚባል ጌጥ የሚደረግ መሆኑ በጣም ይገርማል።

(4) የገና አባት ከኢየሱስና ከልደቱ ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው?

እምነት፦ በብዙ አገሮች፣ የገና አባት ለልጆች ስጦታ እንደሚያመጣ ይታመናል። ብዙ ጊዜ ልጆች የገና አባት ስጦታ እንዲሰጣቸው ደብዳቤ ይጽፉለታል፤ የገና አባት እነዚህን ስጦታዎች በሰሜናዊ ዋልታ በሚገኘው ዋና መኖሪያው በሚሠራበት ጊዜ ትናንሽ መናፍስት እንደሚረዱት ይታመናል።

ምንጩ፦ ስለ ገና አባት (ሳንታ ክላውስ) የሚነገረው አፈ ታሪክ የመነጨው፣ በትንሿ እስያ (በአሁኗ ቱርክ) የምትገኘው የማይረ ሊቀ ጳጳስ ከነበረው ቅዱስ ኒኮላስ እንደሆነ በብዙዎች ዘንድ ይታመናል። ዘ ክሪስማስ ኢንሳይክሎፒዲያ “ስለ ቅዱስ ኒኮላስ የተጻፈው ነገር በሙሉ ማለት ይቻላል በአፈ ታሪክ ላይ የተመሠረተ ነው” ይላል። “ሳንታ ክላውስ” የሚለው ስያሜ “ሴንት ኒኮላስ” በደች ቋንቋ ከሚጠራበት ሲንተርክላስ ከሚለው አጠራር የመጣ ሊሆን ይችላል። ከታሪክም ሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር የገና አባትን (ሳንታ ክላውስን) ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የሚያያይዘው አንዳች ነገር የለም።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “አሁን ውሸትን ስላስወገዳችሁ እያንዳንዳችሁ ከባልንጀራችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ።” ከማንም ይበልጥ የሚቀርቡን ‘ባልንጀሮቻችን’ የቤተሰባችን አባላት ናቸው። (ኤፌሶን 4:25) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ‘እውነትን እንድንወድ’ እንዲሁም ‘ከልባችን እውነትን እንድንናገር’ ይመክረናል። (ዘካርያስ 8:19፤ መዝሙር 15:2) እርግጥ ነው፣ በገና ዕለት ስጦታዎችን የሚያመጣው የገና አባት እንደሆነ ለልጆች መናገር ምንም ጉዳት የሌለው ይመስል ይሆናል፤ ይሁን እንጂ በክፋት ተነሳስተን ባይሆንም እንኳ ልጆችን ማታለል ተገቢ ነው? ደግሞስ የጥበብ አካሄድ ነው? ኢየሱስን ለማክበር ተብሎ በሚደረግ በዓል ላይ ልጆችን ማታለል እርስ በርሱ የሚጋጭ ነገር እንደሆነ አይሰማህም?

(5) አምላክ በገና በዓል ሰሞን የሚታየውን ስጦታ የመስጠት ልማድና ፈንጠዝያ እንዴት ይመለከተዋል?

እምነት፦ በገና ሰሞን የሚታየውን ስጦታ የመስጠት ልማድ ለየት የሚያደርገው ነገር አለ፤ ይኸውም በአብዛኛው ሰዎች ስጦታ ሲሰጡ እነሱም ስጦታ እንደሚመጣላቸው ይጠብቃሉ። በሌላ አባባል ስጦታ የመለዋወጥ ልማድ ይንጸባረቃል። ከዚህም በተጨማሪ በዚህ ሰሞን ፈንጠዝያ እንዲሁም አለልክ መብላትና መጠጣት የተለመደ ነው።

ምንጩ፦ የጥንቱ የሮማውያን የሳተርናሊያ በዓል መከበር የሚጀምረው ታኅሣሥ 17 ሲሆን በዓሉ ስጦታዎችን በሚለዋወጡበት በታኅሣሥ 24 ያበቃ ነበር። ሰዎች በቤታቸውና በጎዳናዎች ላይ ግብዣ የሚያደርጉ ሲሆን በዚህ በዓል ላይ ከልክ በላይ መጠጣት፣ ፈንጠዝያና ውካታ የተለመደ ነበር። ከሳተርናሊያ በዓል ቀጥሎ የጥር ወር መባቻ ይከበራል። በዚህ ጊዜም በአብዛኛው ለሦስት ቀን ያህል የሚቆይ በዓል ይኖራል። የሳተርናሊያ በዓልና የጥር ወር መባቻ ለተከታታይ ቀናት የሚከበር አንድ በዓል ይመስሉ ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? ደስታና ልግስና የእውነተኛው አምልኮ ክፍል ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቃን ሆይ፤ . . . ደስ ይበላችሁ፤ ሐሤትም አድርጉ፤ ቅን ልብ ያላችሁም ሁሉ፣ እልል በሉ” ይላል። (መዝሙር 32:11) እንዲህ ያለው ደስታ አብዛኛውን ጊዜ ከልግስና ጋር የተያያዘ ነው። (ምሳሌ 11:25) ኢየሱስ ክርስቶስ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል” ብሏል። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) በተጨማሪም “ሰጪዎች ሁኑ” ብሏል፤ በሌላ አባባል መስጠት የሕይወታችሁ ክፍል ይሁን ማለቱ ነበር።—ሉቃስ 6:38

እንዲህ ያለው ልግስና በዘልማድ ወይም በባሕል አስገዳጅነት ስጦታ ከመስጠት በጣም የተለየ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛው የልግስና መንፈስ እንዴት ያለ እንደሆነ ሲገልጽ “አምላክ በደስታ የሚሰጠውን ሰው ስለሚወድ እያንዳንዱ ሰው ቅር እያለው ወይም ተገዶ ሳይሆን በልቡ ያሰበውን ይስጥ” ይላል። (2 ቆሮንቶስ 9:7) ግሩም የሆነውን ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ የሚከተሉ ሁሉ ስጦታ የሚሰጡት ከልብ ተነሳስተው ከመሆኑም ሌላ ስጦታ ለመስጠት የግድ የተወሰነ ጊዜ አይጠብቁም። እንዲህ ያለው ልግስና የአምላክን በረከት የሚያስገኝ ሲሆን ፈጽሞ ከባድ ሸክም አይሆንም።

ሐሰተኛ በዓል!

የገናን በዓል ገጽታዎች በሙሉ ማለት ይቻላል ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር ስንመረምራቸው ከአረማውያን የመጡ አሊያም የመጽሐፍ ቅዱስን ዘገባ አዛብተው የያዙ እንደሆኑ እንገነዘባለን። በመሆኑም የገና በዓል ልማዶች ክርስቲያናዊ የሆኑት በስም ብቻ ነው ማለት እንችላለን። ታዲያ ገና የክርስትና በዓል ሊባል የቻለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ እንደተናገረው ክርስቶስ ከሞተ ከተወሰኑ መቶ ዓመታት በኋላ ብዙ ሐሰተኛ አስተማሪዎች ብቅ አሉ። (2 ጢሞቴዎስ 4:3, 4) እነዚህ ሐቀኝነት የጎደላቸው ሰዎች ይበልጥ ትኩረት ያደረጉት እውነትን በማስተማር ላይ ሳይሆን ክርስትናን ለአረማውያኑ በሚማርክ መንገድ በማቅረብ ላይ ነበር። ስለሆነም ተወዳጅ የሆኑ የአረማውያን ሃይማኖታዊ በዓላትን ቀስ በቀስ በመቀበል “የክርስትና” በዓላት ብለው ሰየሟቸው።

መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ያስጠነቅቃል፦ “እነዚህ ሐሰተኛ አስተማሪዎች አስመሳይ ቃላት በመናገር እናንተን መጠቀሚያ ለማድረግ ይጎመጃሉ። ሆኖም ከብዙ ዘመን በፊት የተበየነባቸው ፍርድ አይዘገይም፤ ጥፋት እንደሚደርስባቸውም ጥርጥር የለውም።” (2 ጴጥሮስ 2:1-3) የይሖዋ ምሥክሮች ይህንን ማስጠንቀቂያም ሆነ መላውን መጽሐፍ ቅዱስ በቁም ነገር የሚመለከቱት ሲሆን እንደ አምላክ ቃል አድርገው ይቀበሉታል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) በመሆኑም ሐሰተኛ የሆኑ ሃይማኖታዊ ልማዶችን ወይም በዓሎችን አይቀበሉም። ታዲያ እንዲህ ዓይነት አቋም መውሰዳቸው ደስታ ያሳጣቸው ይሆን? በፍጹም! ቀጥለን እንደምንመለከተው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ሰዎችን ነፃ እንደሚያወጣ ከራሳቸው ተሞክሮ መመልከት ችለዋል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ኢየሱስ የተወለደው በጥንቶቹ አይሁዳውያን አቆጣጠር ኤታኒም በሚባለው ወር (መስከረም-ጥቅምት) ይመስላል።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

አረም የዘራ አረም ያጭዳል

በአንድ ወቅት የቤተ ክርስቲያን ባለሥልጣናት “አረማዊ ምንጭ ያላቸው እምነቶችን አጥብቀው ይዋጉ ነበር” በማለት ክሪስማስ ከስተምስ ኤንድ ትራዲሽንስ—ዜር ሂስትሪ ኤንድ ሲግኒፊካንስ የተባለው መጽሐፍ ይናገራል። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ግን የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን ይበልጥ የሚያሳስባቸው እውነትን ማስተማራቸው ሳይሆን የአባላቶቻቸው ቁጥር መብዛቱ ሆነ። ስለሆነም አረማዊ ልማዶችን አይተው እንዳላዩ ማለፍ ጀመሩ። ቆየት ብለው ደግሞ እነዚህን ልማዶች ተቀበሏቸው።

መጽሐፍ ቅዱስ ‘ምንም ዘራችሁ ምን ያንኑ መልሳችሁ ታጭዳላችሁ’ ይላል። (ገላትያ 6:7) አብያተ ክርስቲያናት በማሳቸው ላይ የአረማዊ እምነት ዘሮችን ዘርተው ሲያበቁ “አረም” ፈልቶ በማየታቸው ሊገረሙ አይገባም። ይህን ማድረጋቸው ካመጣቸው ውጤቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦ የኢየሱስን ልደት ለማክበር ተብሎ የሚደረገው በዓል የስካርና የፈንጠዝያ ወቅት ሆኗል፤ ሰዎች ቤተ ክርስቲያን መሄዳቸው ቀርቶ ወደ ገበያ አዳራሾች ይጎርፋሉ። በተጨማሪም ብዙዎች ስጦታ ለመግዛት ሲሉ በዕዳ ይዘፈቃሉ፤ እንዲሁም ልጆች እውነቱን ከተረቱ፣ የገና አባትን ከኢየሱስ ክርስቶስ መለየት አቅቷቸው ግራ ይጋባሉ። በእርግጥም አምላክ “ርኩስ የሆነውንም ነገር መንካት አቁሙ” ብሎ የተናገረው ያለ ምክንያት አይደለም።—2 ቆሮንቶስ 6:17

[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በጥንቱ የሳተርናሊያ በዓል ላይ ይደረግ እንደነበረው ሁሉ በገና በዓል ሰሞን ፈንጠዝያ፣ አለልክ መብላትና መጠጣት የተለመደ ነው

[ምንጭ]

© Mary Evans Picture Library

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ