መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
መጽሐፍ ቅዱስ ባሪያ አሳዳሪነትን ይፈቅዳል?
ባልንጀራን መውደድ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ትምህርቶች አንዱ ነው። ይሁን እንጂ ፍቅር፣ ጭቆና ከተሞላበት ባሪያ አሳዳሪነት ጋር ይቃረናል። በመሆኑም አንዳንድ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባሪያ አሳዳሪነት መጠቀሱ ግራ ያጋባቸዋል።
በጥንት ዘመን አምላክ ሕዝቡ ባሪያዎች እንዲኖሯቸው ፈቅዶ ነበር። (ዘፍጥረት 14:14, 15 የ1954 ትርጉም) በሐዋርያት ዘመን ጭምር ባሪያ አሳዳሪዎችና ባሪያዎች የሆኑ ክርስቲያኖች ነበሩ። (ፊልሞና 15, 16) ታዲያ ይህ ማለት መጽሐፍ ቅዱስ ጭቆና የተሞላበት ባሪያ አሳዳሪነትን ይፈቅዳል ማለት ነው?
ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር የሚጋጩ ማኅበራዊ መዋቅሮች
መጽሐፍ ቅዱስ መጻፍ ከመጀመሩ በፊት ሰዎች ከአምላካዊ መመሪያዎች ጋር የሚጋጩ ማኅበራዊ መዋቅሮችንና ኢኮኖሚያዊ ሥርዓቶችን አቋቁመው ነበር። አምላክ በጽሑፍ በሰፈረው ሕጉ ላይ ከእነዚህ ልማዶች መካከል አንዳንዶቹን ያወገዘ ሲሆን ሌሎቹን ልማዶች ግን እንዲቀጥሉ ፈቅዷል፤ ከእነዚህም መሃል ባርያ አሳዳሪነት ይገኝበታል።
የጥንቱን የእስራኤል ብሔር ማኅበራዊ አወቃቀር አስመልክቶ ዚ ኢንተርናሽናል ስታንዳርድ ባይብል ኢንሳይክሎፒዲያ “ሥርዓቱ የተዋቀረው እንደ ወንድማማቾች ተሳስበው እንዲኖሩ በሚያስችል ሁኔታ ከመሆኑም ሌላ ድህነት የሌለበት እንዲሁም መበለቶች፣ መጠጊያ ያጡ ሰዎች ወይም ወላጅ አልባ ልጆች ለብዝበዛ የማይዳረጉበት እንዲሆን ታስቦ ነበር” በማለት ይናገራል። በመሆኑም ቀደም ሲል የተቋቋመው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መዋቅር እንዲሁ እንዲቀጥል ከመፍቀድ ይልቅ፣ ሕዝቡ የባሪያ አሳዳሪነትን ሥርዓት ተግባራዊ የሚያደርግ ከሆነ የአምላክ ሕግ፣ ባሪያዎች በርኅራኄና በፍቅር እንዲያዙ የሚያስችል መመሪያ ይዟል።
ባሪያ አሳዳሪነት በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን
በሙሴ አማካኝነት በተሰጠው ሕግ ውስጥ የተካተቱትን የሚከተሉትን ደንቦች ተመልከት፦
● ሰውን አፍኖ በመውሰድ መሸጥ በሞት ያስቀጣ ነበር። (ዘፀአት 21:16) ይሁን እንጂ፣ ድህነትን ለማስወገድ የሚያስችል ይህ ሁሉ ዝግጅት ቢደረግም አንድ እስራኤላዊ፣ ምናልባት ሀብቱን አባክኖ ዕዳ ውስጥ ቢዘፈቅ ራሱን ለባርነት መሸጥ ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ግሰለቡ ትርፍ ገቢ ሊያገኝና በዚያም ራሱን ከባርነት ነፃ ሊያወጣ ይችል ነበር።—ዘሌዋውያን 25:47-52
● ይህ ዓይነቱ የባሪያ አሳዳሪ ሥርዓት በብዙ አገሮች ለዘመናት ሲሠራበት እንደኖረው ዓይነት ጭቆና የተሞላበት ሥርዓት አልነበረም። ዘሌዋውያን 25:39, 40 እንዲህ ይላል፦ “ከወገንህ አንዱ ከመካከልህ ቢደኸይ፣ ራሱንም ለአንተ ቢሸጥ፣ እንደ ባሪያ አድርገህ አታሠራው። በመካከልህ እንዳለ ቅጥር ሠራተኛ ወይም እንደ እንግዳ አድርገህ ቍጠረው።” ስለዚህ ይህ በእስራኤል የሚገኙ ድሆችን ለመደገፍ የተደረገ ፍቅራዊ ዝግጅት ነበር።
● ሲሰርቅ የተገኘ አንድ ሰው ሕጉ በሚያዘው መሠረት ለሰረቀው ነገር ካሳ መክፈል ሳይችል ቢቀር ባሪያ ሆኖ ሊሸጥና በዚህ መንገድ ዕዳውን ሊከፍል ይችላል። (ዘፀአት 22:3) አሳዳሪውን በማገልገል ዕዳውን ከፍሎ ሲጨርስ ነፃ ይወጣል።
● አምላክ ለእስራኤል የሰጠው ሕግ ጭካኔና ግፍ የተሞላበት ባሪያ አሳዳሪነትን ይከለክል ነበር። ባሪያ አሳዳሪዎች ባሪያዎቻቸውን እንዲቀጡ ቢፈቀድላቸውም እንኳ ከመጠን ያለፈ ቅጣት ግን የተከለከለ ነበር። አንድ ባሪያ አሳዳሪ፣ ባሪያውን ቢገድል የበቀል ቅጣት ይበየንበታል። (ዘፀአት 21:20) ባሪያው ጥርሱ ወልቆ ወይም ዓይኑ ጠፍቶ አካሉ ቢጎድል በነፃ ይለቀቃል።—ዘፀአት 21:26, 27
● ባሪያ የሆነ አንድ እስራኤላዊ በባርነት የሚያገለግልበት ዘመን እጅግ ቢበዛ ስድስት ዓመት ነበር። (ዘፀአት 21:2) እስራኤላዊ የሆኑ ባሪያዎች አገልግሎት መስጠት በጀመሩበት በሰባተኛው ዓመት ነፃ ይለቀቃሉ። ግለሰቡ በባርነት ያገለገለበት ጊዜ ምንም ይሁን ምን፣ በመላው አገሪቱ ያሉ እስራኤላውያን ባሪያዎች ሁሉ በየ50 ዓመቱ ነፃ እንዲወጡ ሕጉ ያዝዝ ነበር።—ዘሌዋውያን 25:40, 41
● አንድ ባሪያ ሲለቀቅ ጌታው ልግስና እንዲያሳየው ይጠበቅበታል። ዘዳግም 15:13, 14 እንዲህ ይላል፦ “በምታሰናብተውም ጊዜ ባዶ እጁን አትስደደው። ከመንጋህ፣ ከዐውድማህና ከወይን መጭመቂያህ በልግስና ስጠው።”
በኢየሱስና በሐዋርያቱ ዘመን ባርነት በሮማ ግዛት ውስጥ በሰፊው የተንሰራፋ ልማድ ነበር። ክርስትና እየተስፋፋ ሲሄድ ባሪያዎችም ሆኑ ባሪያ አሳዳሪ የነበሩ ግለሰቦች ምሥራቹን ተቀብለው ክርስቲያን መሆናቸው የሚጠበቅ ነገር ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስም ሆነ ሐዋርያቱ ምሥራቹን የተቀበሉ ሰዎች ማኅበረሰቡ የሚተዳደርበትን ሥርዓት ለመለወጥ ጥረት እንዲያደርጉ አላስተማሩም። ከዚህ ይልቅ ባሪያዎችም ሆኑ ባሪያ አሳዳሪዎች መንፈሳዊ ወንድማማቾች እንደመሆናቸው መጠን እርስ በርስ እንዲዋደዱ ተመክረዋል።—ቆላስይስ 4:1፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:2
ባርነት የሚያከትምበት ጊዜ
ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የተያያዘ ማንኛውም ጥያቄ በሚነሳበት ጊዜ እንደሚደረገው ሁሉ የባሪያ አሳዳሪነት ጉዳይ ሲነሳም ከሁኔታው ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ነገሮች በሙሉ ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። ቅዱሳን መጻሕፍትን በጥንቃቄ ስንመረምር አምላክ በሰዎች ላይ በሚፈጸመው ግፍ እንደሚያዝን እንረዳለን።
በተጨማሪም እንዲህ ያለው ምርምር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሶ የሚገኘው፣ በአምላክ ሕዝቦች መካከል የነበረው ባርነት በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች እንደሚያስቡት ጭቆናና ግፍ የተሞላበት እንዳልነበር እንድንገነዘብ ያስችለናል። ደግሞም መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ከሁሉም ዓይነት ባርነት እንደሚገላግለን ይገልጻል። በዚያን ጊዜ የሰው ዘር በአጠቃላይ የተሟላ ነፃነት ያገኛል።—ኢሳይያስ 65:21, 22
ይህን አስተውለኸዋል?
● መጽሐፍ ቅዱስ በባሪያዎች ላይ የሚፈጸመውን ግፍ ይፈቅዳል?—ዘሌዋውያን 25:39, 40
● ክርስቲያኖች ባሪያዎችን እንዴት ሊይዟቸው ይገባ ነበር?—ቆላስይስ 4:1
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
አምላክ በሰዎች ላይ በሚፈጸመው ግፍ ያዝናል
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል ምንጭ]
© G.M.B. Akash/Panos Pictures