ቴክኖሎጂ የሚያሳድረው ተጽዕኖ—በልጆችህ ላይ
ልጆች የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም ረገድ የተካኑ ከመሆናቸው የተነሳ በቴክኖሎጂው ዓለም በተለምዶ “የአገሬው ተወላጆች” ተብለው ይጠራሉ፤ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን መጠቀም የሚከብዳቸው አዋቂዎች ደግሞ “መጤዎች” እንደሆኑ ይነገራል።
በሌላ በኩል ግን፣ ኢንተርኔት በመጠቀም ረጅም ጊዜ የሚያሳልፉ ልጆች የሚከተሉት አዝማሚያዎች እንደሚታዩባቸው ተስተውሏል፦
የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ጥገኛ ይሆናሉ።
በኢንተርኔት አማካኝነት ጥቃት ሊፈጽሙ ወይም ጥቃት ሊፈጸምባቸው ይችላል።
ፈልገውም ሆነ ሳይፈልጉ ለብልግና ምስሎችና ጽሑፎች (ፖርኖግራፊ) ሊጋለጡ ይችላሉ።
ማወቅ የሚኖርብህ ነገር
ጥገኝነት
በኢንተርኔት አማካኝነት የሚደረጉ አንዳንድ ነገሮች፣ ለምሳሌ ጨዋታዎች ሱስ የማስያዝ ከፍተኛ ኃይል አላቸው። ይህ መሆኑ ሊያስገርመን አይገባም። ሪክሌሚንግ ኮንቨርሴሽን የተባለው መጽሐፍ “የሞባይል አፕሊኬሽኖች የሚሠሩት ስልካችን ላይ ተተክለን እንድንውል ለማድረግ ታስበው ነው” በማለት ይናገራል። ማስታወቂያዎች ያሏቸውን አፕሊኬሽኖች በመጠቀም ሰፊ ጊዜ ባሳለፍን ቁጥር አስተዋዋቂዎቹ ይበልጥ ትርፋማ ይሆናሉ።
ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ልጆችህ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ጥገኛ እንደሆኑ ይሰማሃል? ጊዜያቸውን በተሻለ መንገድ እንዲጠቀሙበት ልትረዳቸው የምትችለው እንዴት ነው?—ኤፌሶን 5:15, 16
በኢንተርኔት አማካኝነት የሚፈጸም ጥቃት
አንዳንድ ሰዎች ኢንተርኔት ሲጠቀሙ ከሌላው ጊዜ ይበልጥ ቁጡ ሊሆኑ፣ ያልታረመ አነጋገር ሊጠቀሙ እንዲሁም ለሌሎች ሰዎች ስሜት ደንታ ቢሶች ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህ ደግሞ በሌሎች ላይ ጥቃት ወደመፈጸም ሊመሩ የሚችሉ ባሕርያት ናቸው።
አንዳንድ ሰዎች ማኅበራዊ ሚዲያዎችን አላግባብ የሚጠቀሙት በሌሎች የመወደድ ወይም ተከታዮችን የማግኘት ከልክ ያለፈ ፍላጎት ስላላቸው ነው። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ሰው ሌሎች በሆነ መንገድ እንዳገለሉት ከተሰማው፣ ለምሳሌ አንድ ግብዣ ላይ እንዳልተጠራ ካወቀ ስሜቱ ሊጎዳና በደል እንደተፈጸመበት ሊሰማው ይችላል።
ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ልጆችህ ኢንተርኔት ሲጠቀሙ ጥሩ ምግባር ያሳያሉ? (ኤፌሶን 4:31) ሌሎች በፕሮግራማቸው ላይ ባያካትቷቸው ምን ይሰማቸዋል?
የብልግና ምስሎችና ጽሑፎች
ኢንተርኔት ላይ የብልግና ይዘት ያላቸውን ምስሎችና ጽሑፎች ማግኘት በጣም ቀላል ነው። ወላጆች፣ የማጣሪያ ሶፍትዌሮች ልጆቻቸው የሚያዩትን ነገር ለመቆጣጠር ሊረዷቸው ቢችሉም ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ እንዳልሆኑ መገንዘብ ይኖርባቸዋል።
የብልግና ይዘት ያላቸውን ምስሎች በኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች አማካኝነት መላላክ (ሴክስቲንግ) በሕግ ሊያስጠይቅ ይችላል። በአንዳንድ ሁኔታዎች ሥር የአገሪቱን ሕጎችና የግለሰቦቹን ዕድሜ ግምት ውስጥ በማስገባት የብልግና ምስሎችን የሚላላኩ ሰዎች የልጆች ፖርኖግራፊን በማሰራጨት ወንጀል ሊከሰሱ ይችላሉ።
ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ልጆችህ የብልግና ምስሎችን ለማየት ወይም ለመላክ እንዳይፈተኑ ልትረዳቸው የምትችለው እንዴት ነው?—ኤፌሶን 5:3, 4
ምን ማድረግ ትችላለህ?
ልጆችህን አሠልጥን
በቴክኖሎጂው ዓለም ውስጥ “የአገሬው ተወላጆች” እንደሆኑ የሚነገርላቸው ልጆች የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም ረገድ በጣም ጎበዞች ቢሆኑም አመራር ያስፈልጋቸዋል። ኢንዲስትራክቴብል የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው “እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው ሳታሠለጥኑ ለልጆቻችሁ የሞባይል ስልክ ወይም ሌሎች መሣሪያዎችን መስጠት ዋና ሳይችሉ የመዋኛ ገንዳ ውስጥ ዘለው እንዲገቡ ከመፍቀድ ያልተናነሰ ኃላፊነት የጎደለው ድርጊት ነው።”
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ልጅን ሊሄድበት በሚገባው መንገድ አሠልጥነው፤ በሚያረጅበት ጊዜም እንኳ ከዚያ ፈቀቅ አይልም።”—ምሳሌ 22:6
ልትሠራባቸው የምትፈልጋቸውን ነጥቦች ለማስተዋል ሞክር፤ ወይም የራስህን ሐሳቦች ጻፍ።
ኢንተርኔት ሲጠቀም ማሳየት ስላለበት ምግባር ከልጄ ጋር መወያየት
ልጄ ሌሎች እንዳገለሉት ሲሰማው ይህን ስሜት መቋቋም የሚችለው እንዴት እንደሆነ ማሠልጠን
ልጄ በኢንተርኔት አማካኝነት ለመጥፎ ነገሮች እንዳይጋለጥ በተቻለኝ መጠን ጥንቃቄ ማድረግ
በየተወሰነ ጊዜው ልጄ ስልኩ ላይ የሚጠቀማቸውን ነገሮች ማየት
የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን በቀን ለምን ያህል ጊዜ መጠቀም እንደሚችል ገደብ ማበጀት
ልጄ ሌላ ሰው በሌለበት፣ በተለይም ምሽት ላይ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን እንዳይጠቀም መከልከል
ምግብ እየተበላ የሞባይል ስልኩን እንዳይጠቀም መከልከል