ጥናት 4
ማንበብና ያነበቡትን ማስታወስ የሚቻልበት መንገድ
1, 2. የምናነበውን ነገር ለማስታወስ መቻላችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
1 ለጊዜ ማሳለፊያ ወይም ለመዝናኛ ያህል ብቻ ለሚያነቡ ሰዎች ያነበቡትን ማስታወስ እምብዛም አስፈላጊ አይሆንም። በአንድ ሙያ ለመሠልጠን ብሎ ለሚያጠና ሰው ግን በመማሪያ መጻሕፍቱ ውስጥ ያነበባቸውን ነገሮች የግድ ማስታወስ ያስፈልገዋል። የሚሰጠውን ፈተና ሊያልፍና በመረጠው ሙያ ሊሰማራ የሚችለው ያጠናውን ካስታወሰ ብቻ ነው። አንድ ክርስቲያን አገልጋይ ግን ተዝናንቶ የሚያነብም ይሁን በትኩረት የሚያጠና፣ ያነበበውን ማስታወሱ ከዚያ የበለጠ አስፈላጊ ነው። የሚያነብበት ዓላማ ይበልጥ ወደ ይሖዋ ለመቅረብና አገልግሎቱን በማሻሻል ለይሖዋ የበለጠ ውዳሴ ለማስገኘት ነው። — ዘዳ. 17:19
2 አንድ ክርስቲያን የሚያነባቸው ዋነኛ መጻሕፍት መጽሐፍ ቅዱስና መጽሐፍ ቅዱስን በትክክል ለመረዳት የሚያግዙ ጽሑፎች ናቸው። ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው እውቀት እንደሆነ ያውቃል። ውጤታማ አገልጋይ እንዲሆን የሚያስታጥቀው ይህ ዓይነቱ ንባብ ነው። በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤትም በአንደኛ ደረጃ የምናተኩረው እነዚህን ጽሑፎች በማንበቡ ላይ ነው።
3, 4. የምናነበውን ነገር መምረጥ የሚገባን ለምንድን ነው?
3 በንባብ አማካኝነት ወደ አእምሮአችን የምናስገባው እውቀት ወደ ሆዳችን ከምናስገባው ምግብ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ሁለቱም ሁኔታዎች መራጭ መሆንን የሚጠይቁ ናቸው። ምግብ የሚበላ ሰው ረሃቡን ለማስታገስ ብቻ የሚበላ እንኳን ቢሆን ሆዱ ገብቶ ሊፈጭ የማይችል ወይም ለሰውነቱ ምንም ዓይነት ጥቅም የማይሰጥ ይባስ ብሎም ሰውነቱን ሊመርዝ የሚችል ነገር ቢበላ ሞኝነት ይሆንበታል። የምንበላው ምግብ ጥሩና ዘላቂ ጥቅም እንዲያስገኝልን ከተፈለገ በቀላሉ የሚፈጭና ከሰውነት ጋር የሚዋሃድ መሆን ይኖርበታል።
4 በንባብም ቢሆን እንዲሁ ነው። ተዝናንተን የምናነብም ሆንን በትኩረት የምናጠና፣ የምናነበው ነገር ወደ አእምሮአችን ገብቶ ሊዋሃድና አእምሮአችንን ለዘለቄታው ሊጠቅም የሚችል መሆን ይገባዋል። አእምሮአችንን ሐሰት የሆነ፣ አምላካዊ ያልሆነና ከትክክለኛ ሥነ ምግባር ውጭ የሆነ ነገር መግበን መንፈሳዊ ብስና እንዲፈጠርብን አንፈልግም። (ፊልጵ. 4:8) ከዚህም ሌላ ምንም ዓይነት ጥቅም የማይሰጥ ነገር በማንበብ ጊዜያችንን ለማባከን አንፈልግም። የምንበላውን ነገር እንደምንመርጥ ሁሉ የምናነበውንም ነገር መምረጥ ይኖርብናል።
5, 6. የግል ንባብ የምናደርግበትን ጊዜ ወስነን ቋሚ ማድረግ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? ይህስ ንባብ የሚደረገው መቼ ሊሆን ይችላል?
5 የግል ንባብ ፕሮግራም። ትክክለኛውን የሚነበብ ጽሑፍ ከመረጥክ በኋላ ሁለተኛውን እርምጃ መውሰድ ያስፈልግሃል። ይኸውም ከአኗኗርህ ጋር የሚመቻች የንባብ ፕሮግራም ማውጣት ነው። የምታነብባቸውን የተወሰኑ ቀናት ወይም ምሽቶች መወሰን ካልቻልክ ጥረትህ ሁሉ መልክ ያለው ስለማይሆን የተሳካ ውጤት አታገኝም። — ሥራ 17:11
6 በጥሞናና በትኩረት ለማንበብ በሚመረመረው ጉዳይ ላይ ለማሰላሰል የሚያመች አካባቢና በቂ ጊዜ ያስፈልጋል። ይሁን እንጂ ንባብህ ረዘም ባለና በተወሰነ የጥናት ጊዜ ብቻ መደረግ ይኖርበታል ማለት አይደለም። በየቀኑ አሥር ወይም አሥራ አምስት ደቂቃ ብቻ እንኳን ለንባብ ብትመድብ ምን ያህል ውጤት ልታገኝ እንደምትችል ትገረማለህ። አንዳንዶች ማለዳ ተነስተው ወይም ማታ ከመተኛታቸው በፊት ያነባሉ። ሌሎች ደግሞ ወደ ዓለማዊ የሥራ ቦታቸው ወይም ወደ ትምህርት ቤታቸው በሚሄዱበት ጊዜ በሕዝብ ማመላለሻዎች ውስጥ እንዳሉ ወይም በምሳ ሰዓታቸው ያነባሉ። በአንዳንድ ቤቶች ውስጥ መላው ቤተሰብ አንድ ላይ ሆኖ በየቀኑ ከምግብ በኋላ ወይም ከመኝታ በፊት ለአምስት ወይም ለአሥር ደቂቃ ያነባል። ሳያቋርጡ በየቀኑ ማንበብ በጣም ጥሩ ውጤት ያስገኛል።
7. መጽሐፍ ቅዱስ በምናነብበት ጊዜ ዓላማችን ምን መሆን ይኖርበታል?
7 የግል ፕሮግራምህ ራሱን መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብን የሚጨምር መሆን ይኖርበታል። መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር ከማንበብ ብዙ ጥቅም ይገኛል። በየቀኑ ወይም በየሳምንቱ የተወሰኑ ምዕራፎችን ወይም ገጾችን በማንበብ መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር ማንበብ ይቻላል። ይሁን እንጂ የምታነብበት ዓላማ አጠቃላይ የሆነ ግንዛቤ ለማግኘትና ያነበብከውን ለማስታወስ መሆን ይኖርበታል እንጂ አንድን ጽሑፍ ለመጨረስ ብቻ መሆን የለበትም። ያነበብከውን ነገር በደንብ ለማብላላት ጊዜ ውሰድ። መጽሐፍ ቅዱስን በምታነብበት ጊዜ ከሁሉ የበለጠውን መንፈሳዊ ምግብ በመመገብ ላይ እንደሆንክ እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ።
8, 9. በንባብ ፕሮግራማችን የትኞቹን ጽሑፎች ብንጨምር ጠቃሚ ይሆናል?
8 በተጨማሪም በመጠበቂያ ግንብ ጥናትና በሌሎች ስብሰባዎች ላይ የሚጠኑትን ጽሑፎች ለመዘጋጀት በቂ ጊዜ መመደብ ያስፈልጋል። በስብሰባው ላይ ስለምትሰጠው ሐሳብ እያሰብክ መዘጋጀት ጥሩ ቢሆንም ዋናው ዓላማህ መልሶቹን ማግኘት መሆን የለበትም። የምታነበውን ለመረዳት ሞክር። የግል ሕይወትህን እንዴት እንደሚነካው መርምር።
9 በጉባኤው ሳምንታዊ ስብሰባዎች ላይ የማይጠኑ የመጠበቂያ ግንብ ርዕሶችም አሉ። በንቁ! መጽሔት ገጾች ላይ ብዙ ትምህርት ሰጪ ቁም ነገሮች ይወጣሉ። በተጨማሪም ቀደም ሲል በራስህ ቋንቋ የወጡትን ጽሑፎች አንብበሃልን? ለንባብ ብዙ ጊዜ በመደብክ መጠን ብዙ በረከት ታገኛለህ። የአንድ ሰው የመንፈሣዊ እድገት ፍጥነት የሚመካው በአብዛኛው በንባብ አዘውታሪነቱና በአነባበቡ ጥራት ላይ ነው።
10–17. የምናነበውን ነገር ለማስታወስ ምን ዓይነት ዘዴዎች ሊረዱን ይችላሉ?
10 ለማስታወስ የሚረዱ ነገሮች። ከምናነበው ነገር ሙሉ ጥቅም ለማግኘት ከፈለግን ያነበብነውን ማስታወስ ይኖርብናል። ብዙ ጊዜ ሰዎች ጥሩ የማስታወስ ችሎታ ስለሌለኝ ያነበብኩትን አላስታውስም ይላሉ። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ ችግሩ ጥሩ የማስታወስ ችሎታ ስለሌላቸው ሳይሆን የማስታወስ ችሎታቸውን ስላላሰለጠኑት ወይም ስላላሠሩት ሊሆን ይችላል። ከምናነበው ነገር የተሟላ ጥቅም ለማግኘት መፈለግ የጥበብ መንገድ ነው። የተነበበው ነገር ፈጥኖ ከተረሳ ዘላቂ ጥቅም ሊያስገኝ አይችልም። ማስታወስ እንደምንችል ሆነን ማንበብን መማር አለብን። ተሞክሮ ያላቸው አንባቢዎች ጠቃሚ ሆነው ያገኙአቸው ዘዴዎች አሉ። እነዚህ ዘዴዎች ሊጠቅሙህ ይችላሉ።
11 በምታነብበት ጊዜ ነጠላ ቃላትን ሳይሆን በርከት ያሉ ቃላትን ወይም ሐረጎችን በአንድ ላይ ለማንበብ ሞክር። ይህን ማድረግህ ንባብህን ከማፋጠኑም በላይ ከቃላት ጋር ከመታገል ይልቅ ሐሳቦቹን እንድትጨብጥ ይረዳሃል። በመደበኛው ንባብህ ጊዜ ድምፅህን አሰምተህ ቃሎቹን አትጥራ ወይም ከንፈርህን አታንቀሳቅስ። ቁልፍ የሆኑ ሐሳቦችን በሚገባ ለመረዳት ካልሆነ በስተቀር ያነበብከውን እንደገና ወደኋላ ተመልሰህ አታንብብ። እርግጥ ነው ከበድ ያለና የተወሳሰበ ነገር የምታነብ ከሆነ ትክክለኛውን ሐሳብ ማግኘትህን ለማረጋገጥ ስትል ፍጥነትህን ዝግ ልታደርግ ትችላለህ። እንዲያውም ጮክ ብለህ ወይም ድምፅህን ውጠህ ከንፈርህን እያንቀሳቀስክ ልታነበው ትፈልግ ይሆናል። (መዝ. 1:2) ለምሳሌ ያህል የመዝሙርና የምሳሌ መጻሕፍት በጥሞና ማሰላሰልን የሚጠይቁ ናቸው እንጂ በፍጥነት የሚነበቡ ጽሑፎች አይደሉም። — መዝ. 77:11, 12
12 በተጨማሪም በእጅህ እርሳስ ይዘህ ቁልፍ ቃላትን ብታሰምር ወይም ሌላ ጊዜ ተመልሰህ ልትመለከት የፈለግከው ሐሳብ ላይ ምልክት ብታደርግ ጥሩ ነው። በብዛት ብታሰምር ግን ተለይቶ እንዲታይ የፈለግከው ሐሳብ ቁልጭ ብሎ እንዳይታይ ስለሚያደርግ ማስመርህ ዓላማውን የሳተ ይሆናል። ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት ብዙ ጊዜ ለሚያጋጥሙን የተቃውሞ አስተያየቶች መልስ ለመስጠት የሚረዳ ሐሳብ ወይም ማስረጃ ካጋጠመህ ሐሳቡ የሚገኝበትን ገጽና አንቀጽ ከመጽሐፉ ጀርባ ላይ ብትጽፍ ጠቃሚ ሊሆንልህ ይችላል። ባስፈለገህ ጊዜ በቀላሉ ልታገኘው ትችላለህ። መጽሐፉ የራስህ ካልሆነ ግን ምንም ዓይነት ምልክት ማድረግ አይገባህም።
13 ዋና ዋናዎቹን ነጥቦች ለማስታወስ ከፈለግህ ቆም ብለህ ሳታሰላስልና የተሰጠውን ሐሳብ ከዚህ በፊት ስለጉዳዩ ከምታውቀው ጋር ሳታነጻጽር አንድን መጽሐፍ ወይም ርዕስ ከዳር እስከ ዳር አንብበህ መጨረስ የለብህም። ለቀረበው መደምደሚያ ድጋፍ ሆነው የተሰጡትን ምክንያቶችና ማስረጃዎች ልብ እያልክ ያነበብከውን ነገር መመርመርን ተለማመድ። በተጨማሪም ሕይወትህን የሚመለከቱትንና ለዕለታዊ ኑሮህ መመሪያ የሚሆኑትን መሠረታዊ ሥርዓቶች ለማስተዋል ንቁ ሁን። እንዴት በሥራ ላይ ልታውላቸው እንደምትችል ለማስተዋል ቆም ብለህ አስብ።
14 ከተጠረዙት የማኅበሩ ጽሑፎች አንዱን በትኩረት በምታነብበት ጊዜ መጀመሪያ የመጽሐፉን ርዕስና በአርዕስት ማውጫው ላይ የቀረበውን የነጥቦች ቅደም ተከተል ብትመረምር ጠቃሚ ነው። እንደዚያ ማድረግህ የመጽሐፉን አጠቃላይ መልእክት እንደትገነዘብ ያስችልሃል። የአንድን መጽሔት ርዕስ ወይም በአንድ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኝ አንድ ምዕራፍ በምታነብበት ጊዜ በመጀመሪያ በውስጡ የሚገኙትን ንዑስ ርዕሶች ተመልከት። ንዑስ ርዕሶቹ የምዕራፉ ወይም የትምህርቱ መልእክት እንዴት ባለ ቅደም ተከተል እንደሚቀርብ ያመለክታሉ። አብዛኛውን ጊዜ በእያንዳንዱ አንቀጽ መጀመሪያ ገደማ ላይ የሚገኙትን ርዕሳነ አረፍተ ነገሮች ወይም የአንቀጹን ፍሬ ሐሳብ የሚገልጹትን አረፍተ ነገሮች ልብ በል። እነዚህ አረፍተ ነገሮች የእያንዳንዱን አንቀጽ ፍሬ ሐሳብ ጠቅለል አድርገው ይገልጹልሃል። የምታነብበውን ርዕሰ ጉዳይ አጠቃላይ ሐሳብ በማግኘት ላይ አተኩር።
15 ሌላው ዘዴ ደግሞ የምታነበውን ነገር በዓይነ ሕሊናህ ለመመልከት መሞከርና ለማስታወስ የሚረዱ የአእምሮ ሥዕሎችን መሳል ነው። በዓይነ ሕሊናህ ተዋናዮቹንና ከድርጊቱ በስተጀርባ ያለውን ሁኔታ ተመልከት። በሁኔታዎቹ ውስጥ የሚገለጹትን ድምፆች ስማ፣ ሽታዎቹን አሽትት፣ ምግቡንና መጠጡን አጣጥም፣ ከሐዘኑም ሆነ ከደስታው ተካፈል። በሚገለጸው ትርዒት ውስጥ ራስህን ለማስቀመጥ ሞክር። ሁሉንም የስሜት ሕዋሳት በግምታዊው ሁኔታ ውስጥ ለማስገባትና የመጽሐፍ ቅዱሱን ታሪክ ሕያው በሆነ ሁኔታ ለመመልከት ይቻላል። በዚህ መንገድ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን ምንባብ እንዳይረሱ ለማድረግ ይቻላል።
16 አንድን ምዕራፍ ከጨረስክ በኋላ አጠር ላለ ጊዜ በአእምሮህ ውስጥ ከልሰው። ከዚያም በኋላ በአእምሮህ ውስጥ የተቀረጸውን አጠቃላይ ሥዕል ከጽሑፉ ጋር በድጋሚ አስተያይ።
17 የሚቻል ከሆነ የተማርካቸው ነገሮች በአእምሮህ ውስጥ ገና ትኩስ እያሉ ከሌላ ሰው ጋር ተወያይባቸው። በድጋሚ መናገርህ ትምህርቱ ወደ አእምሮህ ይበልጥ ጠልቆ እንዲገባ ያደርጋል። ከሌላ ሰው ጋር መወያየትህ ደግሞ በጉዳዩ ላይ ያለህን እውቀት ሊጨምርልህ ይችላል። ለመስክ አገልግሎት የሚጠቅሙ ነጥቦች ካገኘህ በተቻለህ ፍጥነት ተጠቀምባቸው። ይህም ትምህርቱ በአእምሮህ ውስጥ እንዲቀረጽ ያደርጋል።
18–20. በደንብ ለማንበብ መቻል በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
18 ውጤታማ የሆነ ንባብ የሚያስገኘው ጥቅም። ንባብ በሕይወታችን ላይ ቀጥተኛ የሆነ ተጽዕኖ አለው። የምንሠራው የሥራ ዓይነት፣ የምናዳብረው ችሎታ፣ ከሕይወት የምናገኘው ደስታና መንፈሣዊ ዕድገታችን ከንባብ ችሎታችን ጋር ቀጥተኛ የሆነ ግንኙነት አላቸው። አንድ ሰው ጥሩ የሆነ የንባብ ችሎታ ከሌለው ብዙ የመማርና ልምድ የማግኘት አጋጣሚ ያጣል። ወላጆች ሥርዓት ያለው የንባብ ማስተማሪያ ፕሮግራም አዘጋጅተው ልጆቻቸውን በማሰልጠን ሊረዷቸው ይችላሉ። ልጆቻችሁ ጮክ ብለው እንዲያነቡላችሁ በየጊዜው ብትጠይቋቸው ጥሩ ነው። ለምሳሌ ያህል ቅዱሳን ጽሑፎችን በየዕለቱ መመርመር ከተባለው ቡክሌት የዕለት ጥቅሱንና ሐሳቡን እንዲያነቡላችሁ ልትጠይቋቸው ትችላላችሁ። አንተም ራስህ ቀልጣፋ አንባቢ ካልሆንክ በየቀኑ ከአሥራ አምስት እስከ ሠላሳ ደቂቃ ለሚደርስ ጊዜ ንባብ ብትለማመድ በጣም ትጠቀማለህ። በጥቂት ወራት ውስጥ ጥሩ ውጤት ልታገኝ ትችላለህ።
19 ጥሩ የንባብ ልማድ፣ ለማንበብና ለመመርመር የተወሰነ ፕሮግራም ማውጣትና እዚህ ላይ የተገለጹትን ዘዴዎች መጠቀም የአገልግሎት ችሎታህን በጣም ያሻሽልልሃል። በጣም ውድ የሆኑትን የአምላክ ቃላት በይበልጥ ለማስታወስና በሕይወትህና በአገልግሎትህ ለመጠቀም ትችላለህ። ሸምገል ያሉ ሰዎችም እንኳን እዚህ ላይ የተገለጹትን ዘዴዎች ቢለማመዱ የማስታወስ ችሎታቸውን ሊያሻሽሉ ይችላሉ። ማንም ቢሆን እኔ አርጅቻለሁና ከእንግዲህ ወዲያ ልሻሻል አልችልም ብሎ ማሰብ የለበትም።
20 አምላክ ታላላቅ ዓላማዎቹ በመጽሐፍ ላይ እንዲሰፍሩ ያደረገበት ምክንያት የሰው ልጆች አስደናቂ ሥራዎቹን እንዲያውቁና ለረዥም ዘመናት እንዲያስታውሱ ነው። (መዝ. 78:5–7) በዚህ ረገድ ያደረገልንን ልግስና እንደምናደንቅ የምናሳየው ይህን ሕይወት ሰጪ ቃል በትጋት በማንበብና በማስታወስ ነው።