የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • sg ጥናት 22 ገጽ 113-116
  • ውጤታማ መግቢያዎች

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ውጤታማ መግቢያዎች
  • ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • **********
  • **********
  • በጉጉት ለማዳመጥ የሚጋብዝ መግቢያ
    በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ
sg ጥናት 22 ገጽ 113-116

ጥናት 22

ውጤታማ መግቢያዎች

1–3. በንግግርህ መግቢያ ላይ ለትምህርቱ ስሜት ለመቀስቀስ የምትችለው በምን አማካኝነት ነው?

1 ስሜት የሚቀሰቅስ። የአንድ ንግግር መግቢያ ስለ ርዕሰ ጉዳዩ ለመስማት ስሜት የሚቀሰቅስ መሆን ይገባዋል። የአድማጮችህን ትኩረት ሊስብና ቀጥሎ የምታቀርበውን ትምህርት በጥሩ መንፈስ እንዲከታተሉ ሊያዘጋጃቸው ይገባል። ይህንን ለማከናወን ርዕሰ ጉዳዩ ለአድማጮች ምን ያህል ዋጋ እንዳለው ማሳየት አስፈላጊ ነው።

2 አንድን ንግግር ለመከታተል ስሜት ለመቀስቀስ ከሚያስችሉት በጣም የተሻሉ መንገዶች አንዱ ጉዳዩ አድማጮችን እንደሚመለከት አድርጎ ማቅረቡ ነው። ትምህርቱ ለእነርሱ በጣም አስፈላጊ እንደሆነና ሕይወታቸውን የሚመለከት መሆኑን እንዲገነዘቡ አድርግ። ለዚህም ከአድማጮችህ የግንዛቤ ደረጃ መነሣት ይኖርብሃል። ይህም የምታቀርበው ሐሳብ ከአድማጮችህ አጠቃላይ የእውቀት ክልል መውጣት የለበትም ማለት ነው። ምሳሌ በመስጠት፣ መፍትሔ የሚያስፈልገው ችግር በመጥቀስ ወይም ተከታታይ ጥያቄዎችን በማቅረብ ንግግርህን ልትከፍት ትችላለህ። ያም ሆነ ይህ የተናገርከው ነገር አድማጮችህ እንዲገባቸውና ከራሳቸው ሁኔታ ጋር እንዲያገናኙት ከተፈለገ የሚያውቁት ነገር መሆን ይኖርበታል።

3 አንዳንድ ጊዜ አድማጮችህ በወሬ በሰሙት ብቻ ያደረባቸው አግባብ የሌለው ጥላቻ ወይም ቅሬታ ካለ በመግቢያህ ላይ በመጀመሪያ እርሱን ማስተካከል ሊኖርብህ ይችላል። በተለይ ርዕሰ ጉዳዩ በጣም አወዛጋቢ ከሆነ እንደዚያ ማድረግ ይኖርብሃል። ሁኔታው እንደዚህ በሚሆንበት ጊዜ አሳማኝ ምክንያቶችን አንድ በአንድ ማቅረብ እስክትጀምር ድረስ አድማጮችህ በትዕግሥት እንዲከታተሉህ ለማድረግ መግቢያህ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት አብዛኛው ሰው የሚያቀርበውን የተቃውሞ መልስ ገና ከመጀመሪያው በመጥቀስ አስተሳሰባቸውን በዘዴ ለማስተካከልና ልታቀርብላቸው ያዘጋጀኸውን ትምህርት ለማስከተል ትችል ይሆናል።

4–6. መግቢያዎቻችን ስሜት የሚቀሰቅሱ እንዲሆኑ ምን ሌሎች ነገሮች ይረዳሉ?

4 ምን ጊዜም ቢሆን በአንደኛ ደረጃ አስፈላጊ የሆነው ነገር ለሰዎቹ ምን ሐሳብ ወይም ትምህርት ይቅረብላቸው የሚለው ጥያቄ ነው። ነገር ግን በመግቢያህ አማካኝነት ትምህርቱን ለመከታተል ስሜት ለመቀስቀስ ከፈለግህ ከማንኛውም የንግግርህ ክፍል ይልቅ መግቢያህ ላይ ‘እንዴት ባለ ሁኔታ መናገር አለብኝ’ የሚለውን ጥያቄ ልታስብበት ይገባል። በዚህ ምክንያት በመግቢያህ ላይ ምን እንደምትል ብቻ ሳይሆን እንዴት ባለ አነጋገር እንደምታቀርበው ቀደም ብለህ በጥንቃቄ መዘጋጀት ይኖርብሃል።

5 ብዙውን ጊዜ አጫጭርና ቀላል የሆኑ ዓረፍተ ነገሮች የመግቢያህን ዓላማ ለማሳካት የተሻሉ ናቸው። መግቢያህን ለማቅረብ ባለህ አጭር ጊዜ ውስጥ ግብህን ለመምታት የቃላት ምርጫ በጣም አስፈላጊ በመሆኑ የመጀመሪያዎቹን ሁለት ወይም ሦስት ዓረፍተ ነገሮች በጣም በጥንቃቄ ማዘጋጀቱ ጠቃሚ ሆኖ ልታገኘው ትችላለህ። እነዚያን ዓረፍተ ነገሮች ለማንበብ እንድትችል በማስታወሻህ ላይ ጻፋቸው ወይም የመክፈቻ ቃላትህ በሙሉ ኃይል መቅረብ እንዲችሉ እነዚያን ዓረፍተ ነገሮች በቃል ያዛቸው። ከዚህም በተጨማሪ እንደዚያ በማድረግህ ንግግርህን በልበ ሙሉነት ትጀምራለህ፤ እንዲሁም አዳዲስ ሐሳብ እያፈለቅህ እንድትናገር የሚያስችል እርጋታ ይኖርሃል።

6 ምንም እንኳን ምክር ሰጪው ከዚህኛው የንግግር ባሕርይ ጋር በማያያዝ እነዚህን ነጥቦች ትሠራባቸው እንደሆነ ባይከታተልህም የመግቢያህን አቀራረብ በተመለከተ መጨመር የምንፈልጋቸው ጥቂት ምክሮች አሉን። ድንጋጤ ወይም ፍርሃት ከተሰማህ ረጋ ብለህ ረገብ ባለ ቃና ተናገር። በልበ ሙሉነት ተናገር፤ ሆኖም ጭፍን አቋም ያለህ አክራሪ እንዳትመስል ተጠንቀቅ። እንዲህ ያለ አቋም ገና ከጅምሩ የአድማጮችህን ስሜት ሊዘጋ ይችላል።

7. መግቢያህን ማዘጋጀት ያለብህ መቼ ነው?

7 ምንም እንኳን በመጀመሪያ የሚቀርበው ነገር የንግግሩ መግቢያ ቢሆንም መግቢያው ይበልጥ ውጤታማ ሊሆን የሚችለው የንግግሩ ሐተታ በደንብ ከተቀነባበረ በኋላ የተዘጋጀ እንደሆነ ነው። ይህም ያዘጋጀኸውን ትምህርት በትክክል ለማስተዋወቅ ምን ብለህ መናገር እንዳለብህ ለማወቅ ያስችልሃል።

**********

8–10. መግቢያዎቻችን ከአርዕስቱ ጋር እንዲስማሙ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

8 ለአርዕስቱ የሚስማማ። መግቢያህ አድማጮችህን ወደ ርዕሰ ጉዳዩ በጥሩ ሁኔታ ሊመራ የሚችለው ከንግግሩ አርዕስት ጋር የሚጣጣም ከሆነ ብቻ ነው። በመግቢያህ ላይ ለንግግሩ ዓላማ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ሐሳብ ብቻ ለመጨመር ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። እርግጥ የመንግሥቱን መልዕክት ክብር የሚቀንስና በአድማጮች መካከል ያሉትን እንግዶች ቅር የሚያሰኝ ሆኖ መዘጋጀት የለበትም።

9 መግቢያህ ውይይት ወደሚደረግበት ርዕሰ ጉዳይ የሚመራ መሆኑ ብቻ አይበቃም፤ ርዕሰ ጉዳዩን ከምን አቅጣጫ እንደምትመለከተው ወይም እንደምታስፋፋው በግልጽ ማስቀመጥ ይኖርበታል። ይህም ጉዳዩን ከአንድ የተወሰነ አርዕስት አንፃር ማብራራት፣ ከዚያም ተግባራዊ ሆኖ ካገኘኸው በተቻለ መጠን ያንን አርዕስት በሆነ መንገድ መጠቆም ወይም ማሳወቅ አለብህ ማለት ነው። አርዕስቱን ለይተህ ካልገለጽክ በውስጡ ያሉትን ቁልፍ የሆኑ ቃላት አንዳንድ ጊዜ በመግቢያው ላይ ልትጠቀምባቸው ትችላለህ። ይህን ካደረግህ አድማጮችህ የንግግርህ አርዕስት የሚጠቁማቸውን የርዕሰ ጉዳዩን ሌሎች ገጽታዎች እንድትሸፍን አይጠብቁም።

10 ሁሉም ንግግሮች አንድ ወጥ መሆን አለባቸው። በአንድ ሐሳብ ተጀምረው በሌላ ነገር የሚደመደሙ መሆን አይገባቸውም። ከዚህም ሌላ መግቢያው ትምህርቱን ለመከታተል ስሜት የሚቀሰቅስ መሆን አለበት ቢባልም ከንግግሩ ርዕስ ጋር የሚስማማ የመሆኑ ጉዳይም አብሮ መታሰብ አለበት። በሌላ አነጋገር በጥሩ ታሪክ ለመጀመር ሲባል የንግግሩ አርዕስት መረሳት የለበትም። በመግቢያው ላይ የሚጨመሩትን ነጥቦች ለመምረጥ መሠረት መሆን ያለበት የንግግሩ ዓላማ ነው። ነጥቦቹ ከንግግሩ ሐተታ ጋር ተገጣጥመው አንድ ላይ የሚሄዱ መሆን ይኖርባቸዋል።

**********

11–14. የመግቢያው መጠን ልከኛ መሆኑን ለማወቅ የምንችልበት መንገድ ምንድን ነው?

11 ልከኛ። የመግቢያው ርዝመት ምን ያህል መሆን አለበት? ለሁሉም ሁኔታዎች የሚስማማ የተወሰነ መልስ መስጠት አይቻልም። የመግቢያው ርዝማኔ ለርዕሰ ጉዳዩ በተሰጠው የጊዜ መጠን፣ በንግግሩ ዓላማና በአድማጮቹ እንዲሁም በሌሎች ብዙ ጉዳዮች ላይ የተመካ ነው።

12 እንዲያውም አንድ ንግግር በሚቀርብበት ጊዜ እንደ ሰንሰለት የተያያዘ እንዲሆን አድማጮች መግቢያውን ከንግግሩ ሐተታ ለመለየት እስኪቸገሩ ድረስ አንድ ወጥ መሆን ይገባዋል። በዚህ ምክንያት ምክር ሰጪው በንግግር ምክር መስጫ ቅጽ ላይ ለዚህ የንግግር ባሕርይ እርማት ለመስጠት ይቸገራል። ሁሉም ተማሪ ንግግር ሲሰጥ አንዳንድ የመግቢያ ሐሳቦችን መናገሩ አይቀርም። ምክር ሰጪው ለማወቅ የሚፈልገው መግቢያው በጣም ዝብርቅርቅ ያለና ዝርዝር ጉዳዮች ውስጥ የሚገባ መሆኑን፤ እንዲሁም በጣም ከመንዛዛቱ የተነሣ ወደ ዋናው ሐተታ ከመግባቱ በፊት አድማጮች እንዲሰላቹ የሚያደርግ መሆኑን ነው።

13 መግቢያው ለትምህርቱ ስሜት የሚቀሰቅስ ሆኖ እያለ የተወሰነ አቅጣጫ ይዞ በሥርዓትና በተቀላጠፈ ሁኔታ ወደ ርዕሰ ጉዳዩ መግባት ይኖርበታል። በሐሳቦች መካከል ምንም ክፍተት ሳይኖር በተሟላ መልክ መቅረብ ይኖርበታል። ይህ በጥንቃቄ ማሰብን ይጠይቃል፤ ምክንያቱም ገና ከአነሳስህ ከዋናው ሐተታ በጣም በመራቅህ ምክንያት ወደዚያ ለመድረስ ረዥምና የተንዛዛ ማብራሪያ መስጠት ካስፈለገህ መግቢያውን እንደገና ተመልክተህ ማስተካከል ይኖርብሃል፤ ምናልባትም አዲስ መነሻ ነጥብ ማግኘት ሊያስፈልግህ ይችላል።

14 መግቢያውን ከንግግሩ ሐተታ መለየት የሚያስቸግር ከሆነ ምናልባት የመግቢያህ መጠን ልከኛ ሊሆን ይችላል። አድማጮችህን በጥሩ ሁኔታ እየመራህ ሳይታወቃቸው ወደ ዋናው ትምህርት እንዲገቡና ማስረጃዎቹን መስማት እንዲጀምሩ ማድረግህን ያመለክታል። በሌላው በኩል ግን ወደ ዋናው ሐሳብ የሚመጣው መቼ ነው እያሉ ራሳቸውን መጠየቅ ከጀመሩ መግቢያህ ከመጠን በላይ ረዥም እንደነበረ እርግጠኛ ለመሆን ትችላለህ። ይህ ድክመት የመግቢያን ርዝማኔ በየበሩ መለዋወጥ በሚያስፈልግበት ከበር ወደ በር በሚደረገው ምሥክርነት ወቅት ጎልቶ ይታያል።

15, 16. ንግግራችን የአንድ በተከታታይ ተናጋሪዎች የሚሸፈን ርዕሰ ጉዳይ ክፍል ከሆነ መግቢያችን ምን ያህል ርዝመት ሊኖረው ይገባል?

15 በፕሮግራሙ ላይ ንግግር የምትሰጠው አንተ ብቻ ከሆንክ ወይም የተማሪ ንግግር የምትሰጥ ከሆነ ከሌሎች ጊዜያት ይልቅ እዚህ ላይ መግቢያህ ትንሽ ረዘም ሊል ይችላል። ነገር ግን ንግግርህ በተከታታይ ተናጋሪዎች የሚሸፈን የአንድ ርዕሰ ጉዳይ ክፍል ከሆነ ወይም በአገልግሎት ስብሰባ ላይ የሚቀርብ አንድ ክፍል ከሆነ መግቢያህ እጥር ምጥን ብሎ ነጥቡን የሚያስይዝ ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱም ንግግርህ ቀደም ሲል መግቢያ የተሰጠበት አርዕስት አካል ስለሆነ ነው። ረዥምና የተወሳሰበ መግቢያ መስጠቱ ሳያስፈልግ ጊዜ ማባከን ይሆናል። ያዘጋጀሃቸውን ዋና ሐሳቦች ለአድማጮች የሚያቀርበው የንግግሩ ሐተታ ነው።

16 ለማጠቃለል ያህል የመግቢያህ ዓላማ ባንተና በአድማጮች መካከል ግንኙነት መዘርጋት፣ ትምህርቱን ለመስማት ስሜት መቀስቀስና ወደ ዋናው ቁም ነገር መምራት ነው። ይህንን ዓላማ በተቀላጠፈ ሁኔታ አሳክተህ ወደ ዋናው ርዕሰ ጉዳይ ግባ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ