ጥናት 38
ማደግህ በግልጥ ይታይ
1, 2. ሁላችንም ዕድገት ስለማድረግ ማሰብ ያለብን ለምንድን ነው?
1 በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ያሉትን ትምህርቶች በሙሉ በጥንቃቄ ካጠናህና በሥራ ላይ ካዋልህ በኋላ ከቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ለመመረቅ ዝግጁ ትሆናለህ ማለት ነውን? አይደለም፤ ምክንያቱም ይህ ቀጣይ የሆነ የአገልግሎት ማሠልጠኛ ፕሮግራም ነው። አምላካዊ እውቀትን በመሰብሰብና የተማርከውን በሥራ ላይ በማዋል በኩል ሥልጠናውን ጨርሰህ ልትመረቅ አትችልም። ከዚህ ይልቅ ትጉ ተማሪ በመሆን ከአንተ ጋር ትውውቅ ላላቸው ሁሉ በግልጥ የሚታይ ዕድገት ማሳየትህን ለመቀጠል ትችላለህ።
2 ሐዋርያው ጳውሎስ አብሮት ይሖዋን የሚያመልከውን ወጣቱን ጢሞቴዎስን ‘ማደጉ ለሰው ሁሉ በግልጥ ይታይ ዘንድ በሕዝብ ፊት ወጥቶ ለማንበብ፣ በጥሞና ለመምከር፣ ለማስተማር፣ የተማራቸውን ነገሮች ለማብላላትና በእነዚህ ነገሮች ለመመሰጥ የሚያሳየውን ትጋት ሊቀጥልበት እንደሚገባ’ አጥብቆ አሳስቦታል። (1 ጢሞ. 4:13, 15 አዓት) አንተም የምታመልከው ያንኑ አምላክ ስለሆነ ማደግህ ለሌሎች በግልጥ እንዲታይ ለማድረግ ትችላለህ። በዕድገት ሂደት ላይ የመጨረሻ ነጥብ ስለሌለ ሁልጊዜ እያሻሻልህ ለመሄድ ትችላለህ። የእውነተኛ እውቀት ሁሉ ምንጭ ይሖዋ ነው። ይህ ምንጭ አርኪ ውኃ እንደሚያፈልቅ ጥልቀቱም ሊደረስበት እንደማይቻል የውኃ ጉድጓድ ነው። ለመቼውም ቢሆን ያንን ጥልቅ ውኃ ቀድተን ልንጨርሰው ባንችልም ከዚያ ጉድጓድ ሁልጊዜ አርኪ ውኃ እየጠጣን ለመኖር እንችላለን። (ሮሜ 11:33, 34፤ ኢሳ. 55:8, 9) እንግዲያው ማደግህ ለተመልካቾች በግልጥ ሊታይ የሚችለው እንዴት ነው?
3, 4. በአገልግሎት ትምህርት ቤትና በሌሎቹ የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ማደጋችንን የምናሳየው እንዴት ነው?
3 ዕድገት በግልጥ የሚታይባቸው መንገዶች። ዕድገትህ በግልጥ መታየት የሚችልበት አንዱ መንገድ በአገልግሎት ትምህርት ቤት በምትሰጠው ንግግር ነው። ትልቅ ዕድገት እንዳላደረግህ ሊሰማህ ይችላል። ይሁን እንጂ ከራስህ ይልቅ ሌሎች ጥሩ ዕድገት እንዳደረግህ ሊመለከቱ ይችላሉ። በዚህ ረገድ ‘ምን ነው ቶሎ ቶሎ ባደግሁ’ ብሎ እንደሚመኘው ልጅ ነን። ዘመዶች ሊጠይቋቸው ሲመጡ “እንዴ! እንዴት በአንድ ጊዜ ተመዘዝክ!” በማለት በአድናቆት ይናገራሉ። ወደኋላ ተመልሰህ በትምህርት ቤቱ ውስጥ የመጀመሪያውን ንግግር የሰጠህበትን ጊዜ አስታውስ። ታስታውሰዋለህን? እስቲ ያንን ንግግር በቅርቡ ከሰጠሃቸው ንግግሮች ጋር አወዳድር። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ብዙ ነገር ተምረሃል። ብዙ ጠቃሚ ልምድ አግኝተሃል። አይደለም እንዴ? እንግዲያው በዚያው ግፋበት!
4 ዕድገት የሚገለጠው በአገልግሎት ትምህርት ቤት በሚሰጡት ንግግሮች ላይ ብቻ አይደለም። በሌሎች የጉባኤው ስብሰባዎችም ላይ ሊታይ ይችላል። በስብሰባ አዘውትረህ ትገኛለህን? የምትገኝ ከሆነ በማደግ ላይ እንዳለህ፤ ይሖዋ ለመንፈሳዊ ደህንነታችን ያደረገልንን ዝግጅቶች እንደምታደንቅ ታሳያለህ። ከዚህም በተጨማሪ በስብሰባዎች ላይ የምትሰጣቸው ጥራት ያላቸው ሐሳቦች ዕድገት በማድረግ ላይ መሆንህን ሊያሳዩ ይችላሉ። መልሱን ከጽሑፉ በማንበብ ፋንታ በራሳቸው አነጋገር የሚያብራሩ ሁሉ ዕድገት ማድረጋቸውን ያሳያሉ። በተመሳሳይም በመጠናት ላይ ያለው ትምህርት ምን ትርጉም እንዳለውና በሕይወታቸው ውስጥ ምን ዋጋ እንደሚሰጥ ሐሳብ የሚሰጡ የማስተዋልን ችሎታ እያዳበሩ ናቸው። እንግዲያው ምን ዕድገት እንደተደረገ በሚገመገምበት ጊዜ በስብሰባ አዘውትሮ መገኘትና በግል የሚደረገው ተሳትፎ ምን ያህል ጥራት እንዳለው ግምት ውስጥ መግባት ያለባቸው ነገሮች ናቸው።
5. በመስክ አገልግሎት በኩል ዕድገት እንዳደረግን የሚያሳየው ምንድን ነው?
5 በመስክ አገልግሎት የምታደርገው ዕድገትስ? በመስክ አገልግሎት ለመጀመሪያ ጊዜ ለመሳተፍ ወጥተህ ወደ መጀመሪያዋ በር ስትደርስ እንዴት እንደተሰማህ ትዝ ይበልህ። በአሁኑ ጊዜ በየበሩ ቆመህ ለመናገር ካለህ ችሎታ ጋር እስቲ አወዳድረው። ዕድገት ተደርጓል። አይደለም እንዴ? ቢሆንም በስብከቱና በማስተማሩ በኩል ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን ተጨማሪ ዕድገት ማድረግ እንደሚቻል ትገነዘባለህ። ከዚህም በተጨማሪ አቅምህ በሚፈቅድልህ ሁሉ በማንኛውም የአገልግሎት ዘርፍ ሙሉ ተሳትፎ ለማድረግ ትችል ይሆን? ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው ሲል በጥሞና መክሮናል:- “እግዚአብሔርን ለማስደሰት እንዴት መኖር እንደሚገባችሁ ከኛ ተምራችኋል፤ አሁንም የምትኖሩት እንዲሁ ነው፤ በጌታ በኢየሱስ ስም የምንለምናችሁና የምንመክራችሁም ከዚህ በፊት ካደረጋችሁት ይበልጥ እንድታደርጉ ነው” ብሏል። (1 ተሰ. 4:1 የ1980 ትርጉም ) በይሖዋ አገልግሎት የተሟላ ተሳትፎ እያደረግህ በየጊዜው ማደግህን ስትቀጥል ስብከትህና ትምህርትህ ይበልጥ ውጤታማ ከመሆናቸውም በተጨማሪ ይሖዋን ለማገልገሉ ልዩ መብት ያለህ አድናቆት ይበልጥ ጥልቅ ይሆናል። በየቤቱ የምናገኛቸው ሰዎች የሚሰጡት ምላሽ ጥሩ ባይሆንም እንኳ የይሖዋን መልእክት ይዘህ ወደ ሰዎች እንድትሄድ ይሖዋ በአንተ መጠቀሙን እንደ መብት ትቆጥረዋለህ።
6. የአንድ ሰው ንግግር መንፈሳዊ ዕድገት ያደረገ መሆኑን ሊያንጸባርቅ የሚችለው እንዴት ነው?
6 የአንድ ሰው ዕድገት ከሌሎች ጋር በሚያደርገው ንግግርም ሊገለጽ ይችላል። ኢየሱስ ‘አንድ ሰው በልብ ሞልቶ የተረፈውን በአፉ ይናገረዋል’ ብሏል። (ሉቃስ 6:45) የአንድ ሰው ንግግር በይሖዋና በዓላማዎቹ ላይ በይበልጥ እያተኮረ ሲሄድ ዕድገት እንደተደረገ በግልጥ ይታያል። ግለሰቡ ለይሖዋ ባለው አድናቆት እያደገና ወደ አምላክም በይበልጥ እየተጠጋ መሆኑን ያሳያል። ወደ ይሖዋ በይበልጥ መጠጋታችን አስተማማኝ ጥበቃ ይሆንልናል።
7. የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ በማድረግ በኩል መሻሻላችንን የት ቦታ ላይ ልናሳይ እንችላለን?
7 የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በዕለታዊ ኑሮአችን በሥራ ላይ ማዋላችንም ዕድገታችንን ያሳያል። አሁን የምታደርጋቸው ነገሮች ከይሖዋ ቃል ጋር ትውውቅ ሳይኖርህ ታደርጋቸው ከነበሩት የተለዩ አይደሉምን? ነገሮችን ይሖዋ በሚፈልገው መንገድ በማድረግ በኩል የምታሳየው ይህ ዕድገት በማንኛውም ቦታ ባሉህ የሥራ እንቅስቃሴዎች ላይ መንፀባረቁ አይቀርም። በቤትህ ውስጥ ከቤተሰብህ አባላት ጋር ባለህ ግንኙነት ይህ ለውጥ ይታያል። የተጣሉብህን ኃላፊነቶች በምትወጣበትም መንገድ ይንጸባረቃል። በሥራ ቦታህ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ለማድረግ ከበፊቱ የበለጠ ጥንቃቄ ታደርጋለህ። ይህ ሁሉ የተወሰነ ዕድገት ያደረግህ መሆኑን የሚያሳይ ነው። እዚህም ላይ ቢሆን ሁላችንም ለማሻሻል እንችላለን። የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ይበልጥ በተሟላ መንገድ ሥራ ላይ ለማዋል ልንጥር እንችላለን።
8, 9. ሌሎች አስፋፊዎችን ለመርዳት ራሳችንን ብናቀርብ ይህ ምን የሚያመለክት ነው? ለዚህስ ምን አጋጣሚዎች ይኖራሉ?
8 ራስህን አቅርብ። ማደጋችንን በግልጥ የምናሳይበት ሌላው መንገድ በይሖዋ አገልግሎት ለበለጠ ኃላፊነት ራሳችንን በማቅረብ ነው። መዝሙር 110:3 “ወታደራዊ ኃይልህን በምታሳይበት ቀን ሕዝብህ በፈቃዳቸው ራሳቸውን ያቀርባሉ” ይላል። (አዓት) የአንተ ሁኔታ ልክ እዚህ ላይ እንደተገለጸው ነውን? ወደፊትስ ከአሁኑ በተሻለ ሁኔታ እንደዚያ ለማድረግ ትችላለህን?
9 በልባዊ አሳቢነት ተገፋፍተህ ሌሎችን ለመርዳት ያለህን ፈቃደኝነት ለማሳየት ትችላለህ። የጉባኤው ሽማግሌዎች ወንድሞችን ወይም እህቶችን በሆነ መንገድ እንድትረዳቸው ሊጠይቁህ ይችላሉ። ወደ ስብሰባ ለመምጣት እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ይኖሩ ይሆናል። ታዲያ እነርሱን ለመርዳት ራስህን ታቀርባለህን? አንድ ሰው ቀርቦ እርዳኝ ብሎ እስኪጠይቅህ ድረስ መጠበቅ አይኖርብህም። እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች እንዳሉ ከተሰማህ እነርሱን ለመርዳት ያለህን ፈቃደኝነት ለምን አትገልጽላቸውም? የታመመ ወይም ሆስፒታል የገባ አለን? ሽማግሌዎች ይህን እስኪነግሩህ ድረስ መጠበቅ አያስፈልግህም። ከዚህ ይልቅ በራስህ አነሣሽነት ሄደህ ልትጠይቃቸው ወይም እርዳታ የሚያስፈልግበት መንገድ ካለ በዚያ መንገድ ልትረዳቸው ትችላለህ። እቤትህ ውስጥ ቋሚ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አለን? ከጉባኤው ጋር መቀራረብ የጀመሩ አዲስ ቤተሰብ ካሉ አለፍ አለፍ እያልክ ወደዚህ ጥናት እንዲመጡና ከቤተሰብህ ጋር እንዲያጠኑ ብትጋብዛቸው ሊረዳቸው ይችል ይሆን? ወይም ወደ መስክ አገልግሎት ለብቻህ የምትሄድ ብትሆን ብትጋብዛቸው አብረውህ ለመሄድ የሚችሉ አስፋፊዎች ይኖራሉን? ሌላ አስፋፊ አብሮህ እንዲሄድ ለመጋበዝ ለምን በቅድሚያ እቅድ አታወጣም? አዎን፤ በእነዚህ ጊዜያት የይሖዋ አገልጋዮች በጣም ሥራ የበዛላቸው ሆነዋል። ይሁን እንጂ ለሌሎች ወንድሞችና እህቶች እርዳታ ለመስጠት ፈቃደኞች መሆናችን አንዱ የዕድገታችን መለኪያ ነው። “አጋጣሚ ጊዜ ካገኘን ለሰዎች ሁሉ ይልቁንም ለሚያምኑ ቤተ ሰዎች መልካም ነገርን እናድርግ።” — ገላ. 6:10 የ1980 ትርጉም
10, 11. ወንድሞች ከ1 ጢሞቴዎስ 3:1 ጋር በሚስማማ መንገድ ራሳቸውን ሊያቀርቡ የሚችሉት እንዴት ነው?
10 ወንድም ከሆንክ የአምላክ ቃል በጉባኤ ውስጥ የአመራሩን ቦታ ለሚይዙት ያወጣቸውን ብቃቶች ለማሟላት በመጣር ራስህን ለበለጠ ሥራ ለማቅረብ ትችላለህ። አንደኛ ጢሞቴዎስ 3:1 ወደ በላይ ተመልካችነት ሥራ ለመድረስ የሚጣጣሩትን ወንድሞች ያመሰግናቸዋል። ይህም ማለት እወቁኝ ባይ መሆን ወይም ከሌሎች ጋር መፎካከር ጥሩ ነው ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ጎልማሳ ክርስቲያን ለመሆን፣ “ሽማግሌ” በሚያስፈልግበት በማንኛውም ቦታ ለማገልገል ፈቃደኛና ብቃት ያለው ለመሆን መጣጣር ማለት ነው። በእያንዳንዱ ጉባኤ ውስጥ በማስተማሩና በስብከቱ ሥራ መሪ የሚሆኑ እንዲሁም የጉባኤ ኃላፊነቶችን የሚሸከሙ ብዙ “ሽማግሌዎች” እና “ዲያቆናት” ያስፈልጋሉ።
11 ፈቃደኛ የሆኑ ሁሉ በጉባኤው ውስጥ ልዩ ልዩ መብቶችን አግኝተው በደስታ ሊሠሩ ይችላሉ። በአገልግሎት ስብሰባ ላይ በትዕይንት ውስጥ ገብተው እንዲሳተፉ ሊጠየቁ ወይም ሽማግሌዎችን ወይም ዲያቆናትን እንዲያግዙ ሊጠየቁ ይችላሉ። ይህ ሊሆን የሚችለው ፈቃደኛ መሆናቸውንና ምንም ዓይነት ሥራ ቢሰጣቸው በኃላፊነት እንደሚወጡት ያረጋገጡ ወንድሞች በመሆናቸው ነው። አስፈላጊነቱ በሚነሣበት ጊዜ ፈቃደኝነታቸውና ዕድገታቸው ለጉባኤ አገልጋይነት እንዲታጩ ሊያበቃቸው ይችላል። በዚህ ቦታ የሚሾሙት ለምንድን ነው? ምክንያቱም ፈቃደኝነታቸውንና ዕድገታቸውን አሳይተዋል። ይሖዋ በቃሉ ውስጥ ያስቀመጣቸውን ብቃቶች አሟልተዋል። አገልጋይ እንዲሆኑ የሚሾሙ ወንድሞች የጉባኤ ጉዳዮችን በማከናወን ረገድ ተጨማሪ ማሠልጠኛ በሚሰጥበት በመንግሥቱ የአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት እንዲሳተፉ በየወቅቱ ይጋበዛሉ።
12, 13. ራሳቸውን ለማቅረብ ፈቃደኛ የሆኑና ሁኔታቸው የሚፈቅድላቸው ሁሉ ምን መብቶች ተከፍተውላቸዋል?
12 ፈቃደኞች ከሆንን፣ ሁኔታችንም የሚፈቅድ ከሆነ፣ ሁላችንም ልናገኛቸው የምንችል አስደሳች ተጨማሪ መብቶች አሉ። በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ አስፋፊዎች እንደሚያደርጉት በየወቅቱ ረዳት አቅኚ ለመሆን ራስህን ልታቀርብ ትችላለህን? ምናልባትም የዘወትር አቅኚ ልትሆንና በየጊዜው እያደገ ላለው ቁጥራቸው አስተዋጽኦ ልታደርግ ትችል ይሆናል። አስፈላጊ ከሆነም ወደ ሌላ ቦታ ተዛውረህ ለማገልገል የሚያስችል ሁኔታ አለህን? ለይሖዋ አገልግሎት ያለህ አመለካከትስ ለዚህ ርምጃ ፈቃደኛ ለመሆን የሚያበቃህ ነውን? ብዙ ወንድሞችና እህቶች ልዩ አቅኚዎች በመሆን ወይም ጊልያድ ትምህርት ቤት ገብተው የሚስዮናዊ አገልግሎትን በመጀመር ወይም ርዳታ ይበልጥ ወደሚያስፈልግበት ቦታ ተዛውረው የሚያገለግሉ አስፋፊዎች በመሆን ልክ እንደዚሁ አድርገዋል። አንዳንዶች በዓለም ዙሪያ በሚገኙት በተለያዩ የቤቴል መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ማገልገል ጀምረዋል። ራሳቸውን በውዴታቸው ለይሖዋ በማቅረባቸውም እጅግ በጣም ተባርከዋል።
13 በዚህ ዘመን ውስጥ መኖራችን የሚያስፈነድቅ ነው! በእነዚህ “መጨረሻ ቀኖች” ውስጥ ይሖዋ አስደናቂ የሆነ የስብከትና የማስተማር ሥራ በመላዋ ምድር እንዲካሄድ በማድረግ ላይ ነው። ይሖዋ በድርጅቱ በኩል በአንዱ የአገልግሎት ዘርፍ እንድትሳተፍ ግብዣ ሲያቀርብልህ “ይህ ግብዣ ከይሖዋ የመጣልኝ ይሆን?” እያልክ ራስህን ጠይቅ። የራስህን ሁኔታዎችና ልብህን መርምር። እስካሁን ድረስ የተወሰነ ዕድገት አድርገሃል። የተወሰነ ፈቃደኝነትም አሳይተሃል። ይህ ጥሩ ነው። ይሁን እንጂ ራስህን በተሟላ ሁኔታ በማቅረብ ዕድገት ማሳየት የምትችልባቸው ሌሎች መንገዶች ይኖሩ ይሆን? ይሖዋ የሚያሳይህን አቅጣጫ ለመከተል ፈጣን በመሆን ረገድ ዕድገት ስታሳይና መመሪያውን ለመፈጸም እሺ ባይ ስትሆን በብዙ ትባረካለህ። በዓለም ዙሪያ ያሉት ፈቃደኛ የሆኑት የይሖዋ አገልጋዮች ለዚህ ሐቅ ምሥክር ሊሆኑ ይችላሉ። እንዲያውም የበረከቶች በረከት የሆነው በአዲሱ የአምላክ ሥርዓት ውስጥ የሚገኘው የዘላለም ሕይወት ዕድገት በማድረጋችን ላይ የተመካ ነው። የአምላክ ቃል እንደሚከተለው ሲል አጥብቆ የሚያሳስበንም በዚህ ምክንያት ነው:- “መሻሻልህን ሰዎች ሁሉ እንዲያዩ፣ በእነዚህ ነገሮች ትጋ፤ እነዚህንም ነገሮች በሥራ ላይ በማዋል ሰውነትህን በሙሉ ለእነርሱ ስጥ። ለራስህና ለማስተማር ሥራህ ተጠንቀቅ፤ በእነዚህም ነገሮች ጽና፤ ምክንያቱም ይህን ስታደርግ ራስህንና የሚሰሙህንም ታድናለህ።” — 1 ጢሞ. 4:15, 16 የ1980 ትርጉም