የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • uw ምዕ. 6 ገጽ 46-54
  • በፍጥረታት ሁሉ ፊት የተደቀነ የአቋም ጥያቄ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በፍጥረታት ሁሉ ፊት የተደቀነ የአቋም ጥያቄ
  • እውነተኛው አንድ አምላክ ያስገኘው የአምልኮ አንድነት
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ለጥያቄው የሰጡት ምላሽ
  • የግል መልሳችን ምንድን ነው?
  • በሁላችንም ፊት የተደቀነ የአቋም ጥያቄ
    እውነተኛውን አንድ አምላክ አምልክ
  • መንግሥቲቱ ‘ለመምጣት’ ይህን ያህል ጊዜ የወሰደባት ለምንድን ነው?
    “መንግሥትህ ትምጣ”
  • አምላክ የሰው ልጆች እንዲሠቃዩ የፈቀደው ለምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • አምላክ ሥቃይና መከራ እንዲኖር ለምን ፈቀደ?
    ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት
ለተጨማሪ መረጃ
እውነተኛው አንድ አምላክ ያስገኘው የአምልኮ አንድነት
uw ምዕ. 6 ገጽ 46-54

ምዕራፍ 6

በፍጥረታት ሁሉ ፊት የተደቀነ የአቋም ጥያቄ

1. (ሀ) በዔደን ውስጥ ሰይጣን ምን ጥያቄ አስነሳ? (ለ) አነጋገሩ ይህንን ጥያቄ እንዳስነሳ የሚያሳየው እንዴት ነው?

በዔደን ውስጥ ዓመጽ ሲቀሰቀስ ፍጥረታትን ሁሉ የሚነካ አንድ ትልቅ የአቋም ጥያቄ ተነስቷል። ሰይጣን ወደ ሔዋን ቀርቦ እርሷና ባሏ በጣም እንደተበደሉ የሚጠቁም ቃል ተናገራቸው። “በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዟልን?” ብሎ ጠየቃት። ሔዋንም ስለ አንዱ ዛፍ ብቻ አምላክ “እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ፣ አትንኩትም” ብሎናል ስትል መለሰች። ሰይጣንም ቀበል አደረገና የሔዋንም ሆነ የአዳም ሕይወት አምላክን በመታዘዝ ላይ እንዳልቆመ በመናገር ይሖዋን ሐሰተኛ ነው ብሎ በቀጥታ ክስ ሰነዘረበት። አምላክ ፍጡሮቹን አንድ ትልቅ ነገር እንዳስቀረባቸው፤ ይኸውም በሕይወታቸው ውስጥ ነገሮችን የሚመዝኑበት የአቋም ደረጃ ራሳቸው ማውጣት እንዳይችሉ አፍኗቸዋል ብሎ ተናገረ። “ሞትን አትሞቱም፣ ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ” ብሎ ሰይጣን አጥብቆ ተከራከረ። (ዘፍጥረት 3:1-5) ሰይጣን ሔዋንን አግባብቶ የራሷን ጉዳይ ራሷ ብትወስን የተሻለ እንደሚሆን አሳመናት። በተዘዋዋሪ አምላክ ስላለው የመግዛት መብት፤ አገዛዙም ጥሩ ስለመሆኑ ተገዳደረ። ጥያቄው ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነትን የሚመለከት ነበር።

2. የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት ከስሕተት ምን ሊጠብቃቸው ይችል ነበር?

2 ሔዋን ለአምላክ ማሳየት የሚገባት ፍቅር ከስሕተት ሊጠብቃት ይችል ነበር። የባልዋንም የራስነት ሥልጣን ብታከብር ኃጢአት ከመስራት ልትገታ ትችል ነበር። እርስዋ ግን ወዲያው የሚገኝ የመሰላት ጥቅም ብቻ ታያት። የተከለከለው ነገር አምሮ ታያት። ሰይጣን ባቀረበላት የሚያባብል ሐሳብ ፈጽማ ተታለለችና የአምላክን ሕግ አፈረሰች። ከዚያም አዳምን ወደ ድርጊቱ አስገባችው። እርሱም ቢሆን በሰይጣን ውሸት ባይታለልም አምላክ ላሳየው ፍቅር በከፍተኛ ሁኔታ የአድናቆት ጉድለት አሳየ። የይሖዋን የራስነት ሥልጣን ቸል በማለት የዓመጸኛዋ ሚስቱ ዕጣ ተካፋይ ለመሆን መረጠ። — ዘፍጥረት 3:6፣ 1 ጢሞቴዎስ 2:13, 14

3. (ሀ) ሰይጣን በይሖዋ ሉዓላዊነት ላይ ካስነሳው ተቃውሞ ጋር የተያያዘው ሌላው ጥያቄ ምንድን ነው? (ለ) ጥያቄውስ እነማንን ይነካል?

3 ሰይጣን በይሖዋ ሉዓላዊነት ላይ የጀመረው ጥቃት በዔደን ብቻ አልቆመም። የተሳካ ከሚመስለው ከዚህ ጅምር በመቀጠል ሌሎች ፍጡሮች ለይሖዋ በታማኝነት የመቆማቸው ጉዳይ አጠያያቂ ነው አለ። ስለዚህ ይኸኛው ጉዳይ ከመጀመሪያው ጋር የተሳሰረ በሁለተኛ ደረጃ የሚታይ ጥያቄ ሆነ። የሰይጣን ክርክር ይዘቱ ሰፋና የአዳምን ዘሮችና የአምላክን መንፈሳዊ ልጆች በሙሉ፤ በጣም ተወዳጅ የሆነውን የይሖዋ የበኩር ልጅ ሳይቀር የሚመለከት ሆነ። ፍጡሮች ይሖዋን የሚያገለግሉት አምላክንና አገዛዙን ስለሚወዱ ሳይሆን ራስ ወዳድ ስለሆኑ ለጥቅማቸው ብለው ነው ሲል ሰይጣን በኢዮብ ዘመን ክርክር አስነሳ። መከራ ቢደርስባቸው ሁሉም ወደ ግል ጥቅማቸው ዘወር ይላሉ ብሎ ተከራከረ። ታዲያ ትክክል ነበርን? — ኢዮብ 1:6-12፤ 2:1–6፤ ራእይ 12:10

ለጥያቄው የሰጡት ምላሽ

4. ብዙ ሰዎች የይሖዋን ሉዓላዊነት ያልደገፉት ለምንድን ነው?

4 ይሖዋ ሰይጣንን በዓመጹ የሚተባበሩት ሌሎች ፍጡሮች ሊገኙ አይችሉም ብሎ አላሰበም። እንዲያውም በዔደን ውስጥ ፍርድ በሚሰጥበት ጊዜ ወደፊት ‘የእባቡ ዘር’ የሚሆኑትን ጠቅሷቸዋል። (ዘፍጥረት 3:15) ከእነርሱም መካከል ኢየሱስን ለማስገደል የዶለቱት ፈሪሳውያንና አሳልፎ የሰጠው የአስቆሩቱ ይሁዳ ይገኙበታል። እነዚህ ሰዎች ባለማወቅ ስሕተት ላይ የወደቁ አልነበሩም። ትክክለኛውን ነገር እያወቁ ሆነ ብለው ይሖዋንና አገልጋዮቹን የሚጻረር አቋም ወስደዋል። ይሁንና የይሖዋን ብቃቶች የማያሟሉት ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሌሎች ሰዎች መጥፎ የሠሩት ባለማወቅ ነው። — ሥራ 17:29, 30

5. (ሀ) ለይሖዋ ታማኝ ሆነው የቆሙት ሰዎች ቃሉን እንደ ሔዋን ሳይሆን እንዴት አድርገው ተመልክተዋል? (ለ) ኖኅ ታማኝነቱን ያረጋገጠው እንዴት ነው? የእርሱስ ምሳሌ እንዴት ሊጠቅመን ይችላል?

5 በሌላው አንጻር ግን ስለ ፈጣሪያቸው ዕውቀት ቀስመው እርሱን እንደ ሉዓላዊ ገዥ አድርገው በመመልከት በታማኝነት የቆሙለት የእምነት ወንዶችና ሴቶች ነበሩ። እነዚህ ሰዎች አምላክን አመኑ። ሕይወታቸው የቆመው እርሱን በመስማትና በመታዘዝ ላይ መሆኑን አወቁ። ከእነርሱ አንዱ ኖኅ ነበር። አምላክ “የሥጋ ሁሉ ፍጻሜ በፊቴ ደርሷል . . . መርከብን ለአንተ ሥራ” ብሎ በነገረው ጊዜ ኖኅ የይሖዋን መመሪያ እሺ ብሎ ታዟል። በዘመኑ የነበሩ ሌሎች ሰዎች ግን ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም አዲስ ነገር አይመጣም ብለው በማሰብ እንደ ወትሯቸው መኖር ቀጠሉ። ኖኅ ግን በጣም ግዙፍ መርከብ ሠራ፤ ለሌሎችም ስለ ይሖዋ የጽድቅ መንገዶች መስበኩን ቀጠለ። የታሪክ መዝገቡ እንደሚለው ኖኅ “እግዚአብሔር እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ አደረገ።” — ዘፍጥረት 6:13-22፤ በተጨማሪም ዕብራውያን 11:7​ና 2 ጴጥሮስ 2:5 ተመልከት።

6. (ሀ) በንጹሕ አቋማቸው የጸኑት ሁሉ ያሳዩአቸው ሌሎች ጠባዮች ምንድን ናቸው? (ለ) ሣራ እነዚህን ጠባዮች እንዴት አሳየች? ከእርሷስ ምሳሌ በምን መንገድ ልንጠቀም እንችላለን?

6 አቋማቸውን ሳያጐድፉ የጸኑ ሁሉ ለራስነት ሥርዓት ከፍተኛ አክብሮት የማሳየትና ከይሖዋ ጋር በፍቅርና በታማኝነት የመጣበቅ ጠባዮች ጐልተው ታይተውባቸዋል። ባልዋን ቀድማ እርምጃ እንደወሰደችው እንደ ሔዋን አልሆኑም። የይሖዋን ሕግ ችላ እንዳለው እንደ አዳምም አልሆኑም። የአብርሃም ሚስት ሣራ እነዚህን በጎ ጠባዮች በተግባር አሳይታለች። በአፍዋ ብቻ ሳይሆን በልብዋም ጭምር አብርሃም ‘ጌታዋ’ ነበር። ከዚህም ሌላ በግሏ ይሖዋን አጥብቃ የምትወድ የእምነት ሴት ነበረች። ከአብርሃም ጋር ሆና “መሠረት ያላትን እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ” ማለትም የአምላክን መንግሥት ትጠባበቅ ነበር። — 1 ጴጥሮስ 3:5, 6፤ ዕብራውያን 11:10-16

7. (ሀ) ሙሴ የይሖዋን ሉዓላዊነት ደግፎ የቆመው እንዴት ባሉ ሁኔታዎች ውስጥ ነው? (ለ) የእርሱ ምሳሌ እንዴት ሊጠቅመን ይችላል?

7 አብርሃም የትውልድ አገሩን ለቆ ከወጣ ከ430 ዓመታት በኋላ ከግብጹ ፈርዖን ጋር ፊት ለፊት በተካሄደ ፍጥጫ ሙሴ የይሖዋን ሉዓላዊነት ደግፎ ቆሞአል። ይህ የሆነው ሙሴ ዕብሪተኛ ስለነበረ አይደለም። እንዲያውም በደንብ ለመናገር ስለ መቻሉ ተጠራጥሯል። ቢሆንም ይሖዋን ታዘዘ። በይሖዋ እየተደገፈና ወንድሙ አሮን አጋዥ ሆኖለት በፈርዖን ፊት የይሖዋን ቃል በተደጋጋሚ አቅርቧል። ፈርዖን ልበ ደንዳና ነበር። ከዚህም ሌላ አንዳንድ የእስራኤል ልጆች ሙሴ የሚያደርገውን ነገር ክፉኛ ነቅፈዋል። እርሱ ግን በታማኝነት በመቆም ይሖዋ ያዘዘውን ሁሉ ፈጸመ። እስራኤላውያንም በእርሱ አማካይነት ከግብጽ ባርነት ነፃ ወጡ። — ዘጸአት 7:6፤ 12:50, 51

8. (ሀ) ለይሖዋ ታማኝ ሆኖ መቆም እርሱ በጽሑፍ ያሰፈረውን ብቻ መጠበቅ እንዳልሆነ የሚያሳየው ምንድን ነው? (ለ) እንደዚህ ላለው ታማኝነት ያለን አድናቆት 1 ዮሐንስ 2:15ን እንድንሠራበት ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?

8 ለይሖዋ በታማኝነት የቆሙ ሁሉ ‘የሚፈለግብን የሕጉን ፊደል ማለትም ይሖዋ በጽሑፍ ያሰፈረውን መፈጸም ብቻ ነው’ ብለው አላመካኙም። ለምሳሌ የጶጢፋር ሚስት ዮሴፍ ከእርሷ ጋር እንዲያመነዝር ልታስተው በሞከረች ጊዜ ምንዝርን ለይቶ የሚከለክል ከአምላክ የመጣ የጽሑፍ ትእዛዝ አልነበረም። ቢሆንም ዮሴፍ ይሖዋ በዔደን ስላቋቋመው የጋብቻ ሥርዓት በነበረው ዕውቀት መሠረት ከሌላ ሰው ሚስት ጋር ሩካቤ ሥጋ መፈጸም አምላክን እንደማያስደስት ያውቅ ነበር። እስከምን ድረስ እንደ ግብጻውያን ለመሆን አምላክ እንደሚፈቅድለት ለመሞከር አልፈለገም። ዮሴፍ ከዚያ በፊት አምላክ ለሰው ልጆች በተናገራቸውና ባደረጋቸው ነገሮች ላይ በማሰላሰል የይሖዋን መንገዶች ጠበቀ፤ የአምላክ ፈቃድ ነው ብሎ የተረዳውንም ነገር በጥንቃቄ ፈጸመ። — ዘፍጥረት 39:7-12፤ ከመዝሙር 77:11, 12 ጋር አወዳድር።

9. ሰይጣን በኢዮብ ጊዜ ባስነሳው ክርክር በተደጋጋሚ ጊዜያት ውሸታምነቱ የተረጋገጠው እንዴት ነው?

9 ይሖዋን በእውነት ያወቁት ሰዎች ከባድ ፈተና ቢደርስባቸውም እርሱን ከድተው አልሄዱም። ይሖዋ ከፍተኛ የአድናቆት ቃል የተናገረለት ኢዮብም እንኳ ንብረቱን ሁሉ ቢያጣና በአካሉ ላይ ስቃይ ቢደርስበት አምላክን ይተዋል ብሎ ሰይጣን ተከራክሮ ነበር። ኢዮብ ግን ዲያብሎስን ሐሰተኛ አደረገው። በዚያ ሁሉ የመዓት ጐርፍ ለምን እንደተዋጠ ባያውቅም በአቋሙ ጸና። (ኢዮብ 2:3, 9, 10) ሰይጣን ላለመረታት ሙከራውን ቀጠለና አንድን በቁጣ የነደደ የባቢሎን ንጉሥ አነሳስቶ ሦስት ወጣት ዕብራውያን ንጉሡ ላቆመው ምስል ባይሰግዱ ወደሚነደው እሳት እንደሚጣሉ እንዲያስፈራራቸው አድርጓል። ወጣቶቹ ከንጉሡ ትእዛዝና ጣዖት ማምለክን ከሚያወግዘው የይሖዋ ሕግ አንዱን ለመምረጥ ሲገደዱ እነርሱ ይሖዋን እንደሚያገለግሉና የመጨረሻው ሉዓላዊ ገዥአቸው እርሱ እንደሆነ ቁርጥ ባለ አነጋገር አስታወቁ። ለአምላክ ታማኝ መሆንን ከሕይወታቸው ይበልጥ ክቡር እንደሆነ አድርገው ተመለከቱ። — ዳንኤል 3:14-18

10. ፍጽምና የሌለን ሰዎች ለይሖዋ በእርግጥ በታማኝነት እንደምንቆም እንዴት ልናሳይ እንችላለን?

10 ታዲያ አንድ ሰው ለይሖዋ በታማኝነት እንዲቆም ከተፈለገ ፍጹም መሆን ይኖርበታል፤ ስሕተት ከሠራም ፈተናውን ጨርሶ ወድቋል ብለን በዚህ እንደመድማለንን? በፍጹም እንደዚያ ብለን አንደመድምም። ሙሴ የተሳሳተባቸውን ጊዜያት መጽሐፍ ቅዱስ ለይቶ ጠቅሷል። በዚህ ይሖዋ አዘነ፤ ቢሆንም ከአገልጋይነቱ አልሰረዘውም። ሐዋርያት በብዙ መንገዶች ጥሩ ምሳሌ ቢሆኑም የራሳቸው ድክመቶች ነበሯቸው። በታማኝነት መቆም የማይለዋወጥ ልባዊ ታዛዥነት ማሳየትን ይጠይቃል። ይሖዋ ግን አለፍጽምናን እንደወረስን ግምት ውስጥ በማስገባት በማንኛውም ሁኔታ ፈቃዱን ሆነ ብለን ቸል እስካላልን ድረስ በእኛ ደስ ይለዋል። በድክመት ኃጢአት ብንሠራ ግን ከልብ ንስሐ መግባትና ያንን ኃጢአት እንደ ልማድ አድርገን እንዳንቀጥልበት መጠንቀቅ ይኖርብናል። በዚህ መንገድ ይሖዋ ጥሩ ነው የሚለውን ነገር ከልብ እንደምንወድ፣ መጥፎ ነው ብሎ የነገረንን ግን እንደምንጠላ በተግባር እናሳያለን። ኃጢአትን ማስተሰረይ በሚችለው የኢየሱስ መስዋዕት ላይ ባለን እምነት መሠረት በአምላክ ፊት ንጹሕ አቋም ይዘን በደስታ ለመኖር እንችላለን። — አሞጽ 5:15፣ ሥራ 3:19፤ ዕብራውያን 9:14

11. (ሀ) ከሰዎች መካከል ፍጹም ለአምላክ ያደረ መሆኑን ያሳየው ማን ነበር? ይህስ ምን አረጋገጠ? (ለ) እርሱ ያደረገው ነገር እንዴት ይረዳናል?

11 ሆኖም ሰብዓዊ ፍጡሮች ፍጹም ለአምላክ ያደሩ ሆነው መኖራቸው የማይቻል ነገር ይሆን? የዚህ ጥያቄ መልስ ለ4,000 ዓመታት ያህል “ቅዱስ ምስጢር” ሆኖ ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 3:16 አዓት) አዳም ፍጹም ሆኖ ቢፈጠርም ለአምላክ ያደረ በመሆን በኩል ፍጹም ምሳሌ አልተወም። ታዲያ ማን ይችል ይሆን? ከኃጢአተኛ ዘሮቹ መካከል አንዱም እንደማይችል የተረጋገጠ ነው። ይህንን ለማድረግ የቻለው ሰው ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። ኢየሱስ ከነበረበት በተሻለ ሁኔታዎች ውስጥ የነበረው አዳም ቢፈልግ ኖሮ በፍጽምና ደረጃ ንጹሕ አቋሙን ሳያጐድፍ መኖር ይችል እንደነበር ኢየሱስ ያከናወነው ሁኔታ አረጋግጧል። ችግሩ አምላክ ሰውን ጐደሎ አድርጎ ስለፈጠረው አይደለም። እንግዲያው ለመለኮታዊ ሕግ ታዛዥ በመሆን ብቻ ሳይሆን ለጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ ለይሖዋ ያደርን ሆነን በመኖር በኩል የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ ለመከተል እንፈልጋለን።

የግል መልሳችን ምንድን ነው?

12. ለይሖዋ ሉዓላዊነት ያለንን አቋም በተመለከተ ዘወትር ነቅተን መጠበቅ ያለብን ለምንድን ነው?

12 ዛሬ እያንዳንዳችን በጽንፈ ዓለም ፊት ለቀረበው የአቋም ጥያቄ መልስ መስጠት ይኖርብናል። ከዚህ ለመሸሽ አንችልም። በይሖዋ ጐን እንደተሰለፍን በግልጽ ካሳወቅን ሰይጣን የጥቃቱ ዒላማ ያደርገናል። ከየአቅጣጫው ተጽዕኖዎችን ያመጣል። ክፉው ሥርዓቱ እስከሚወድምበት ጊዜ ድረስ እንደዚያ ማድረጉን ይቀጥላል። ጥበቃችንን ማላላት የለብንም። (1 ጴጥሮስ 5:8) ምግባራችን በዚህ ከፍተኛ የአቋም ጥያቄ በኩል የት ላይ እንደቆምን ያሳያል።

13. (ሀ) ከውሸትና ከስርቆት መራቅ ያለብን ምንጫቸው ምን ስለሆነ ነው? (ለ) ሰዎችን ወደ መጥፎ ድርጊቶች ስለሚመሩ ሁኔታዎች የቀረቡትን ከአንቀጾቹ ቀጥሎ ያሉትን ጥያቄዎች አንድ በአንድ መልስ።

13 ታማኝነት የጐደለው ምግባር በዓለም ዘንድ የተለመደ ስለሆነ ብቻ እንደ ቀላል ነገር ልናልፈው አንችልም። ንጹሕ አቋምን ሳያጐድፉ መጠበቅ በማንኛውም የኑሮ ዘርፍ የይሖዋን የጽድቅ መንገዶች መከተልን ይጠይቃል። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል ቀጥሎ ያሉትን ተመልከት:-

(1 ) ሰይጣን የመጀመሪያዎቹን ወላጆቻችን ወደ ኃጢአት ለማስገባት በውሸት ተጠቅሟል። “የሐሰት አባትም ” ሆነ። (ዮሐንስ 8:44)

አልፎ አልፎ ልጆች ለወላጆቻቸው እውነቱን የማይናገሩት በምን ጊዜ ነው? ክርስቲያን ወጣቶች ከዚህ መራቃቸው በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ምሳሌ 6:16-19)

አንድ ሰው ከእውነት አምላክ ጋር ሳይሆን ከሐሰት አባት ጋር ዝምድና እንዳለው የሚያሳዩት አንዳንድ የንግድ ሥራ ድርጊቶች ምንድን ናቸው? (ሚክያስ 6:11, 12)

በሰው ፊት ከእውነቱ ትንሽ ሻል ያለ ግምት እንዲሰጠን ብለን አንዳንድ ነገር ብንናገርና ይህ ማንንም የማይጐዳ ቢሆን አድራጎቱ ስሕተት ነውን? (መዝሙር 119:163፤ ከሥራ 5:1-11 ጋር አወዳድር።)

አንድ ሰው ከባድ ኃጢአት ቢሠራ ውሸት ተናግሮ ነገሩን ለመሸፋፈን መሞከር የማይገባው ለምንድን ነው? (ምሳሌ 28:13)

(2 ) በመጀመሪያ ሔዋን በኋላም አዳም መልካምንና ክፉውን በሚመለከት የራሳቸውን ውሳኔ ራሳቸው እንዲያደርጉ ሰይጣን ያቀረበላቸውን ሐሳብ ሰምተው እርምጃ በወሰዱ ጊዜ በመጀመሪያ ያደረጉት ነገር የራሳቸው ያልሆነውን መውሰዳቸው ነው። ስለዚህ ሌቦች ሆኑ።

አንድ ሰው ቸግሮት ቢሰርቅ ወይም ንብረቱ የተወሰደበት ሰው ኃብታም ቢሆን አድራጐቱን ትክክል ያደርገዋልን? (ምሳሌ 6:30, 31፤ 1 ጴጥሮስ 4:15)

በምንኖርበት አካባቢ መስረቅ የተለመደ ቢሆን ወይም የተሰረቀው ነገር ትንሽ ቢሆን የድርጊቱ ክብደት ይቀንሳልን? (ሮሜ 12:2፤ ኤፌሶን 4:28፤ ሉቃስ 16:10)

14, 15. (ሀ) በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ፍጻሜ ላይ የሰው ልጆች ሁሉ ምን ፈተና ይመጣባቸዋል? (ለ) አሁን የምናደርጋቸው ነገሮች በመጨረሻው የሚኖረንን ሁኔታ የሚነኩት እንዴት ነው?

14 በሺው ዓመት የክርስቶስ ግዛት ውስጥ ሰይጣንና አጋንንቱ የሰውን ልጆች ማሳት በማይችሉበት ጥልቅ ውስጥ ይጣላሉ። ያኔ እንዴት ግልግል ይሆንልናል! ሆኖም ከሺው ዓመት በኋላ ለትንሽ ጊዜ ይለቀቃሉ። ሰይጣንና ተከታዮቹ “በቅዱሳን” ላይ ይኸውም ወደ ፍጽምና በደረሱትና ንጹሕ አቋማቸውን ሳያጐድፉ በሚጠብቁት የሰው ልጆች ላይ ተጽዕኖ ያመጣሉ። ሰይጣን “የተወደደች ከተማ” በተባለችው ሰማያዊቱ አዲስ ኢየሩሳሌም ላይ ውጊያ በመክፈት በምድር ላይ ያስፋፋችውን ጽድቅ ለማጥፋት ይሞክራል። — ራእይ 20:7-10

15 እንደ አሁኑ ጊዜ ሁሉ በዚያን ጊዜም ሰይጣን ሰዎችን አስቶ ከይሖዋ ለማስከዳት በልዩ ልዩ የተንኮል ዘዴዎች መጠቀሙና ለግል ጥቅምና ለኩራት ማራኪ የሆኑ ነገሮችን ማቅረቡ የማይቀር ነው። በዚያን ጊዜ በሕይወት ለመኖር ብንታደል ምን እናደርግ ይሆን? የጽንፈ ዓለሙን ጥያቄ በሚመለከት የልባችን ውሳኔ ምን ይሆን? በዚያን ጊዜ የሚኖር ሰው ሁሉ ፍጹም ስለሚሆን ለአምላክ ታማኝ ሆኖ አለመቆምን የሚያሳይ ማንኛውንም ነገር ማድረግ ሆን ተብሎ የተደረገ ነገር ይሆናል። ስለሆነም የዘላለም ጥፋት ያስከትላል። እንግዲያው በዚያን ጊዜ ታማኝ እንድንሆን ዛሬ ይሖዋ በቃሉም ይሁን በድርጅቱ በኩል የሚሰጠንን መመሪያ ፈጥኖ የመከተልን ልማድ መኮትኮት እንዴት በጣም አስፈላጊ ነው! እንደዚህ ብናደረግ ይሖዋን የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ አድርገን በመመልከት ለእርሱ ያደርንና ከእርሱ ጋር በፍቅራዊ ታማኝነት የተጣበቅን መሆናችንን እናሳያለን።

የክለሳ ጥያቄዎች

● ፍጥረታት ሁሉ የግድ መልስ የሚሰጡበት ትልቁ የአቋም ጥያቄ ምንድን ነው? ነገሩ እኛን የጨመረው እንዴት ነው?

● በገጽ 49 ላይ የተጠቀሱት ሰዎች እያንዳንዳቸው ለይሖዋ ያላቸውን የጸና አቋም ያሳዩበት ልዩ መንገድ ምንድን ነው?

● በምናደርገው ሁሉ ይሖዋን ለማስከበር በየቀኑ መጠንቀቅ ያለብን ለምንድን ነው?

[በገጽ 49 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የይሖዋን ሉዓላዊነት ደግፈዋል

ኖህ

ሣራ

ሙሴ

ዮሴፍ

ኢዮብ

ከምሳሌያቸው ልንጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ