የአምላክን መንጋ የሚመሩና አንድነቱን የሚጠብቁ እረኞች
አንዳንዶች ‘ዓለም አቀፍ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ የሚተዳደረው እንዴት ነው?’ ብለው ይጠይቃሉ። እኛም ‘የአስተዳደሩ ሥርዓት የመጀመሪያውን መቶ ዘመን የክርስቲያን ጉባኤ ምሳሌ የተከተለ ነው’ ብለን እንመልሳለን።
በ1870ዎቹ ዓመታት ቻርልስ ቴዝ ራስልና ጓደኞቹ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታቸው ያገኙትን እውቀት በንግግርም ሆነ በጽሑፎች አማካኝነት ማስፋፋት ጀመሩ። በአገሩ በሙሉ የሚኖሩ በዚህ ሥራ ለመተባበር የፈለጉ ሰዎች ሁሉ ራስልንና የቅርብ ተባባሪዎቹን የጌታን ሥራ በመሥራት ረገድ ከሁሉ የበለጠ ልምድ ያላቸውና ለሥራቸው የሚያስፈልጋቸውን ምክር ሊሰጧቸው የሚችሉ ሰዎች እንደሆኑ አድርገው ይመለከቷቸው ነበር።
በ1884 የጽዮን መጠበቂያ ግንብ ትራክት ማኅበር በፔንሲልቫኒያ የጋራ ብልጽግና ግዛት ሕግ መሠረት ተቋቋመ። ራስልና ኃላፊነት የነበራቸው ተባባሪዎቹ ይህን ማኅበርና የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹን ሥራ ይመሩ ነበር። በ1909 ዋና መሥሪያ ቤታቸውን ወደ ብሩክሊን ኒው ዮርክ አዛወሩ። ባለፉት ዓመታት በሙሉ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ዲሬክተሮችና የቅርብ ረዳቶቻቸው የሆኑና መንፈሳዊ ብቃት ያላቸው ሌሎች ቅቡዓን ክርስቲያን ወንዶች የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባሎች በመሆን ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
የአስተዳደር አካሉ ከቅቡዓን ክርስቲያን ወንዶች የተውጣጣ ቡድን ሲሆን ከመካከላቸው 7ቱ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የዲሬክተሮች ቦርድ አባላት ሆነው የሚያገለግሉ ናቸው። (በ1991 ቁጥራቸው 12 ነበር) የአስተዳደር አካሉ ዓለም አቀፉን የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ በበላይነት ይቆጣጠራል። ማንኛውም ነገር በአምላክ መንፈስ የሚገለጥላቸው ሰዎች ስላልሆኑ ፈጽሞ የማይሳሳቱ አይደሉም። ቢሆንም ሊሳሳት የማይችለውን የአምላክ ቃል በምድር ላይ የመጨረሻው ከፍተኛ ባለ ሥልጣን አድርገው በመመልከት ይመሩበታል። ለአምላክ ፈቃድ በመገዛት ረገድም የዕድሜ ልክ ልምድ አላቸው። እያንዳንዳቸው በይሖዋ ምሥክሮች የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለ50 ወይም ከዚያ በላይ ለሆኑ ዓመታት የቆዩ ናቸው።
የአስተዳደር አካሉ ማኅበሩ የሚያትመውን ጽሑፍ ይቆጣጠራል። በጽሑፍ የሚወጣው ትምህርት ለመንጋው በሚያስፈልጉት መንፈሳዊ ነገሮች ላይ የተመሠረተ ሲሆን ጸሎት የታከለበት ጥልቅ የአምላክ ቃል ጥናትና ምርምር ተደርጐበት የሚዘጋጅ ነው። እነዚህ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ሲያጠኑና የአምላክን ዓላማ አፈጻጸም ማለትም ትንቢቶች በዓለም ሁኔታ ላይ ያላቸውን ተፈጻሚነት፣ የአምላክ ሕዝቦች በዓለም ውስጥ ያሉበትን ሁኔታ ሲያስተውሉ በአንዳንድ ትምህርቶች ላይ የነበራቸውን መረዳት ይበልጥ ማብራራት ወይም ማስተካከያ ማድረግ የሚያስፈልጋቸው ጊዜ ሊኖር ይችላል። በዚህም መንገድ የእውነት እውቀት ከመቼውም የበለጠ እየበዛ ይሄዳል።—መዝሙር 97:11፤ ምሳሌ 4:18፤ ዳንኤል 12:4
የአስተዳደር አካሉ ከ200 በላይ በሆኑ አገሮችና ደሴቶች የሚከናወነውን ሥራ እንዲቆጣጠሩ በምድር ዙሪያ ባሉ ወደ 100 በሚጠጉ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ሦስት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ መንፈሳዊ ብቃት ያላቸው ወንዶች የሚገኙበትን የቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ ሾሟል። ቅርንጫፍ ቢሮዎቹ በክልላቸው ከሚገኙት ጉባኤዎች ጋር ግንኙነት ያደርጋሉ። በአስተዳደር አካሉና በቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴዎች መካከል የዘወትር ግንኙነት አለ። የአስተዳደር አካሉ አባሎች ሁኔታዎችን በቅርብ ለማየት እንዲችሉ በየዓመቱ ብዙ ቅርንጫፍ ቢሮዎችን ይጐበኛሉ።
እነዚህ ወንዶች በሌሎች ሰዎች እምነት ላይ አለቆች ሆነው የሚገዙ አይደሉም። ብዙ ተጨማሪ ሰዎች ስለ አምላክ ቃል ይማሩ ዘንድ ተግተው የሚሠሩ አገልጋዮች ናቸው። የሚያገለግሉት የገንዘብ ጥቅም ለማግኘት አይደለም። የሚያስፈልጋቸውን ቁሳዊ ነገር የሚያገኙት ሌሎቹ የቤቴል ቤተሰቦች በሚያገኙበት በዚያው መንገድ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ የሚያሳዩት ቅንዓት፣ አንድነት፣ ከፍተኛ የሥነ ምግባር ደረጃና ለመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ያላቸው ታማኝነት እነዚህ ሰዎች በታማኝነት በማገልገል ላይ ለመሆናቸው ጥሩ ማስረጃ ይሆናል።—1 ቆሮንቶስ 3:5–9፤ 4:1, 2፤ 2 ቆሮንቶስ 1:24፤ 3:1–3፤ 1 ጴጥሮስ 5:2, 3
● እንዴት ያለ የአስተዳደር ዝግጅት ተደርጓል?
● በአሁኑ ጊዜ የአስተዳደር አካል አባላት ሆነው የሚያገለግሉት እነማን ናቸው? ኃላፊነታቸውስ ምንድን ነው?
● በሌሎች አገሮች የሚከናወነው ሥራ አመራር የሚያገኘው እንዴት ነው?
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ካርታ]
● የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክን ፈቃድ የሚያደርጉባቸው አካባቢዎች
[በገጽ 26 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዘዳንቶች
ሲ ቲ ራስል 1884–1916
ጄ ኤፍ ራዘርፎርድ 1917–1942
ኤን ኤች ኖር 1942–1977
ኤፍ ደብልዩ ፍራንዝ 1977–1992
[በገጽ 27 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የይሖዋ ምሥክሮችን ዓለም አቀፍ ሥራ ከሚቆጣጠሩት ወደ 100 ከሚጠጉት ቅርንጫፍ ቢሮዎች ጥቂቶቹ
ካናዳ
ዛምቢያ
ጀርመን
ጃፓን
አውስትራሊያ
ብራዚል