ምዕራፍ ሁለት
የተሳካ ትዳር ለመመሥረት መዘጋጀት
1, 2. (ሀ) ኢየሱስ ዕቅድ የማውጣትን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) ዕቅድ ማውጣት ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው በምን ረገድ ነው?
አንድን ሕንፃ መገንባት ጥንቃቄ የተሞላበት ቅድመ ዝግጅት ይጠይቃል። መሠረቱ ከመጣሉ በፊት ሕንፃው የሚሠራበት ቦታ ማግኘትና ፕላኑን መንደፍ ያስፈልጋል። ይሁን እንጂ ሌላም በጣም የሚያስፈልግ ነገር አለ። ኢየሱስ “ከእናንተ ግንብ ሊሠራ የሚወድ ለመደምደሚያ የሚበቃ ያለው እንደ ሆነ አስቀድሞ ተቀምጦ ኪሳራውን የማይቈጥር ማን ነው?” ሲል ተናግሯል።—ሉቃስ 14:28
2 ሕንፃን ለመገንባት መደረግ ያለበት ነገር የተሳካ ትዳር ለመመሥረት መደረግ ካለበት ነገር ጋር ተመሳሳይ ነው። ብዙዎች “ማግባት እፈልጋለሁ” ይላሉ። ይሁን እንጂ ጋብቻ የሚጠይቀውን መሥዋዕትነት ቆም ብለው የሚያስቡት ስንቶቹ ናቸው? መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ትዳር መልካም ጎን ቢናገርም የሚያስከትላቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሳይጠቅስ አላለፈም። (ምሳሌ 18:22፤ 1 ቆሮንቶስ 7:28) ስለዚህ ጎጆ ለመውጣት የሚያስቡ ሁሉ ጋብቻ የሚያስገኛቸውን በረከቶችም ሆነ የሚጠይቀውን መሥዋዕትነት በተመለከተ ትክክለኛ አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል።
3. መጽሐፍ ቅዱስ የማግባት ዕቅድ ላላቸው ሰዎች ጠቃሚ መምሪያ የሆነው ለምንድን ነው? ለየትኞቹ ሦስት ጥያቄዎችስ መልስ እንድናገኝ ይረዳናል?
3 መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ ሊጠቅም ይችላል። በውስጡ የሚገኘው ምክር የጋብቻ መሥራች በሆነው በይሖዋ አምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ነው። (ኤፌሶን 3:14, 15፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16) ጥንታዊ ቢሆንም እንኳ እጅግ ወቅታዊ በሆነው በዚህ መምሪያ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን መሠረታዊ ሥርዓቶች በመጠቀም (1) አንድ ሰው ትዳር ለመመሥረት ዝግጁ መሆንና አለመሆኑን እንዴት ማወቅ እንደሚችል፣ (2) ለትዳር ጓደኝነት ከሚታጭ ሰው ምን ነገሮችን መጠበቅ እንደሚገባና (3) ክብራማ በሆነ መንገድ ከተቃራኒ ጾታ ጋር መጠናናት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ እንመርምር።
ትዳር ለመመሥረት ዝግጁ ነህን?
4. ስኬታማ ትዳርን ጠብቆ ለማቆየት ትልቅ ሚና የሚጫወተው ነገር ምንድን ነው? ለምንስ?
4 አንድ ሕንፃ ለመሥራት ከፍተኛ ወጪ ሊጠይቅ ይችላል፤ ሆኖም በየጊዜው ሕንፃውን ማሳደስ የሚጠይቀው ወጪም እንዲህ የዋዛ አይደለም። ጋብቻንም በተመለከተ ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ማግባቱ ብቻ እንኳ ራሱን የቻለ ተፈታታኝ ሁኔታ ሊሆን ይችላል፤ ይሁን እንጂ የጋብቻ ዝምድናን ከዓመት ዓመት ጠብቆ ማቆየቱም እንደ ቀላል የሚታይ ነገር አይደለም። እንዲህ ዓይነቱን ዝምድና ዘላቂ ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? በዚህ ረገድ ትልቁን ሚና የሚጫወተው ከልብ ቃል ኪዳን መጋባት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የጋብቻ ዝምድናን እንዲህ ሲል ይገልጸዋል:- “ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፣ በሚስቱም ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።” (ዘፍጥረት 2:24) ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ሰው የትዳር ጓደኛውን ፈትቶ ሌላ ማግባት የሚችልበት ብቸኛው ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያት “ዝሙት” ማለትም ከጋብቻ ውጪ የሚፈጸም ሕገወጥ የጾታ ግንኙነት እንደሆነ ገልጿል። (ማቴዎስ 19:9) ለማግባት እያሰብክ ከሆነ እነዚህን ቅዱስ ጽሑፋዊ መሥፈርቶች አስታውስ። በእንዲህ ዓይነቱ ከባድ ቃል ኪዳን ውስጥ ለመግባት ዝግጁ ካልሆንክ ትዳር ለመመሥረት ዝግጁ አይደለህም ማለት ነው።—ዘዳግም 23:21፤ መክብብ 5:4, 5
5. አንዳንዶች በጋብቻ ቃል ኪዳን መታሰር በጣም የሚያስፈራቸው ቢሆንም የማግባት ዕቅድ ያላቸው ሰዎች ከፍ አድርገው ሊመለከቱት የሚገባቸው ለምንድን ነው?
5 እንዲህ ዓይነቱ ቃል ኪዳን ብዙዎቹን ያስፈራቸዋል። “ሁለታችንም ዕድሜ ልካችንን ተሳስረን የምንኖር መሆናችንን ሳስበው ምንም የማያፈናፍን አጣብቂኝ ውስጥ እንደገባሁ ሆኖ ይሰማኛል” ሲል አንድ ወጣት ሳይሸሽግ ተናግሯል። ይሁን እንጂ ልታገቡት ያሰባችሁትን ሰው ከልብ የምታፈቅሩት ከሆነ ቃል ኪዳኑ ሸክም ሆኖ አይታያችሁም። ከዚህ ይልቅ ጥሩ ጥበቃ ሆኖ ይታያችኋል። በጋብቻ መካከል ያለው ቃል ኪዳን ባልና ሚስቱ በክፉውም ሆነ በደጉ ጊዜ አንድ ላይ ሆነው ለመቀጠልና ምንም ነገር ቢመጣ እርስ በርሳቸው ለመደጋገፍ ፍላጎት እንዲያድርባቸው ያደርጋቸዋል። ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጳውሎስ እውነተኛ ፍቅር “ይታገሣል፣” እንዲሁም “በሁሉ ይጸናል” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 13:4, 7) “የጋብቻ ቃል ኪዳን የበለጠ ጠንካራ እምነት እንዲያድርብኝ ያደርገኛል” ስትል አንዲት ሴት ተናግራለች። “አንድ ላይ ተደጋግፈን ለመኖር መወሰናችንን ለራሳችንም ሆነ ለሌሎች ግልጽ ማድረጋችን ከፍተኛ እርካታ ይሰጠኛል።”—መክብብ 4:9-12
6. በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ለማግባት ከመጣደፍ መቆጠብ የተሻለ የሆነው ለምንድን ነው?
6 እንዲህ ዓይነቱን ቃል ኪዳን ጠብቆ መኖር ብስለት ይጠይቃል። በመሆኑም ክርስቲያኖች ‘ማግባት ወደሚገባቸው ዕድሜ ከደረሱ’ በኋላ ማለትም የጾታ ፍላጎት ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድርበትንና የአንድን ሰው የማመዛዘን ችሎታ ሊያዛባ የሚችልበትን ዕድሜ ካለፉ በኋላ ቢያገቡ የተሻለ እንደሚሆን በመግለጽ ጳውሎስ ምክር ሰጥቷል። (1 ቆሮንቶስ 7:36) ወጣቶች እያደጉ ሲሄዱ ፈጣን የሆነ ለውጥ ያደርጋሉ። በአፍላ የጉርምስና ዕድሜያቸው የሚያገቡ ብዙዎች ከጥቂት ዓመታት በኋላ እነርሱም ሆኑ የትዳር ጓደኛቸው የሚያስፈልጓቸው ነገሮችና የሚመኟቸው ነገሮች እንደተለወጡ ይገነዘባሉ። በአሥራዎቹ ዕድሜያቸው ያገቡ ወጣቶች፣ ቆየት ብለው ካገቡ ወጣቶች ይበልጥ በጋብቻቸው እንደማይደሰቱና ለመፋታት እንደሚፈልጉ የሚወጡት አኃዛዊ መረጃዎች ያሳያሉ። ስለዚህ ለማግባት አትቸኩሉ። በወጣትነታችሁ ነጠላ ሆናችሁ የተወሰኑ ዓመታት ማሳለፋችሁ ይበልጥ እንድትበስሉና ተስማሚ የትዳር ጓደኛ ለመሆን የተሻለ ብቃት እንድታገኙ የሚረዳ በጣም ጠቃሚ የሆነ ተሞክሮ ሊያስገኝላችሁ ይችላል። በተጨማሪም ለማግባት አለመጣደፋችሁ ራሳችሁን ይበልጥ እንድታውቁ ሊረዳችሁ ይችላል፤ ይህ ደግሞ በትዳራችሁ ውስጥ ጥሩ ዝምድና ለመመሥረት እንድትችሉ የግድ አስፈላጊ የሆነ ነገር ነው።
በመጀመሪያ ራሳችሁን እወቁ
7. ለማግባት ዕቅድ ያላቸው ሰዎች በመጀመሪያ ራሳቸውን መመርመር ያለባቸው ለምንድን ነው?
7 ለትዳር ጓደኝነት የምታጩት ሰው ምን ዓይነት ባሕርያት ቢኖሩት እንደምትመርጡ በቀላሉ መዘርዘር ትችላላችሁን? አብዛኞቹ ሰዎች ይህን ማድረጉ አይከብዳቸውም። ይሁን እንጂ የእናንተ የራሳችሁ ባሕርያትስ? የተሳካ ትዳር ለመመሥረት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ምን ምን ባሕርያት አሏችሁ? ምን ዓይነት ባል ወይም ሚስት ትሆናላችሁ? ለምሳሌ ያህል ስህተታችሁን ያለ ምንም ማንገራገር በማመን የሚሰጣችሁን ምክር ትቀበላላችሁ ወይስ እርማት ሲሰጣችሁ ሁልጊዜ ራሳችሁን ንጹሕ ለማድረግ ትጥራላችሁ? በአብዛኛው የደስተኝነት ስሜት የሚነበብባችሁና አዎንታዊ አመለካከት ያላችሁ ናችሁ ወይስ በሆነ ባልሆነው ማጉረምረምና ፊታችሁን እንደ ሐምሌ ዳመና ማጨፍገግ ይቀናችኋል? (ምሳሌ 8:33፤ 15:15) ጋብቻ ባሕርያችሁን እንደማይለውጠው አትዘንጉ። ነጠላ ሳላችሁ ኩሩዎች፣ አትንኩኝ ባዮች ወይም ደግሞ ከልክ በላይ አፍራሽ አመለካከት የተጠናወታችሁ ከሆናችሁ ስታገቡም እንደዚያው ትሆናላችሁ። ሌሎች እኛን በሚያዩበት መንገድ ራሳችንን ማየት አስቸጋሪ ስለሆነ ወላጆቻችሁ ወይም ደግሞ የምታምኑት ጓደኛችሁ ግልጽ የሆነ አስተያየትና ሐሳብ እንዲሰጧችሁ ለምን አትጠይቋቸውም? ልታሻሽሏቸው የሚገቡ ነገሮች እንዳሉ ካወቃችሁ ለማግባት አንዳንድ እርምጃዎችን ከመውሰዳችሁ በፊት እነዚያን ነገሮች ለማሻሻል ጣሩ።
ነጠላ ሳላችሁ፣ በትዳር ውስጥ በጣም የሚጠቅሟችሁን ባሕርያት፣ ልማዶችና ችሎታዎች አዳብሩ
8-10. መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው ለትዳር ዝግጁ እንዲሆን የሚረዳ ምን ምክር ይሰጣል?
8 የአምላክ ቅዱስ መንፈስ በእኛ ላይ እንዲሠራና እንደ “ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የውሃት፣ ራስን መግዛት” ያሉትን ባሕርያት እንዲያፈራ እንድንፈቅድለት መጽሐፍ ቅዱስ ማበረታቻ ይሰጠናል። በተጨማሪም ‘አእምሯችንን በሚያንቀሳቅሰው ኃይል እንድንለወጥና ለእውነት በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው እንድንለብስ’ ይመክረናል። (ገላትያ 5:22, 23፤ ኤፌሶን 4:23, 24) ነጠላ ሳላችሁ ይህን ምክር በሥራ ላይ ማዋላችሁ ወደፊት ስታገቡ ልክ በባንክ እንደሚቀመጥ ገንዘብ እጅግ ጠቃሚ ሆኖ ታገኙታላችሁ።
9 ለምሳሌ ያህል ሴት ከሆንሽ ከውጫዊ ውበትሽ የበለጠ ‘ለተሰወረው የልብ ሰው’ የላቀ ትኩረት መስጠትን ተማሪ። (1 ጴጥሮስ 3:3, 4) አቅምንና ቦታን ማወቅና ጤናማ አስተሳሰብ መያዝ እውነተኛ “የተዋበ ዘውድ” የሆነውን ጥበብ እንድታገኚ ይረዳሻል። (ምሳሌ 4:9፤ 31:10, 30፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10) ወንድ ከሆንክ ደግሞ ሴቶችን በደግነትና በአክብሮት መያዝን ተማር። (1 ጢሞቴዎስ 5:1, 2) ውሳኔ ማድረግንና ኃላፊነት መሸከምን ከመማር በተጨማሪ አቅምንና ቦታን ማወቅንና ትሕትናን መማር ይኖርብሃል። የአምባገነንነት ጠባይ ትዳርን ያናጋል።—ምሳሌ 29:23፤ ሚክያስ 6:8፤ ኤፌሶን 5:28, 29
10 ምንም እንኳ በእነዚህ ነገሮች ረገድ አስተሳሰብን ማስተካከል ቀላል ባይሆንም ሁሉም ክርስቲያኖች ሊሠሩበት የሚገባ ጉዳይ ነው። በተጨማሪም የተሻላችሁ የትዳር ጓደኞች መሆን እንድትችሉ ይረዳችኋል።
ለማግባት የምትፈልጉት ሰው ሊያሟላው የሚገባ ብቃት
11, 12. ሁለት ሰዎች ትዳር ቢመሠርቱ የሚጣጣሙ መሆንና አለመሆናቸውን ማወቅ የሚችሉት እንዴት ነው?
11 እናንተ በምትኖሩበት አካባቢ ሰዎች ለትዳር ጓደኝነት የሚፈልጉትን ሰው የሚመርጡት ራሳቸው ናቸውን? በአካባቢያችሁ ያለው የተለመደ ሁኔታ እንደዚህ ከሆነና ያፈቀራችሁት ሰው ካለ ማድረግ የሚኖርባችሁ ነገር ምንድን ነው? በመጀመሪያ ‘በእርግጥ ትዳር የመመሥረት ዓላማ አለኝን?’ ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ። የማይሆን ተስፋ በመስጠት በሌላው ሰው ስሜት መጫወት ሰብዓዊነት የጎደለው ድርጊት ነው። (ምሳሌ 13:12) ከዚያም ‘ማግባት በምችልበት ሁኔታ ላይ ነኝን?’ ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ። ለሁለቱም ጥያቄዎች አዎንታዊ መልስ መስጠት ከቻላችሁ ከዚያ ቀጥሎ የምትወስዷቸው እርምጃዎች እንደየአካባቢው ባህል የተለያዩ ናቸው። በአንዳንድ አገሮች ግለሰቡን እንዲሁ ስታጠኑት ከቆያችሁ በኋላ ይበልጥ ልትተዋወቁት እንደምትፈልጉ ቀርባችሁ ልትገልጹለት የምትችሉበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል። ግለሰቡ ፈቃደኛ ካልሆነ ለመጫን መሞከር የለባችሁም። እሱም በጉዳዩ ላይ የራሱን ውሳኔ የማድረግ መብት እንዳለው አትዘንጉ። ግለሰቡ ፈቃደኛ ከሆነና ከተስማማ ግን ጤናማ በሆኑ እንቅስቃሴዎች አብራችሁ ጊዜ ለማሳለፍ ሁኔታዎችን ልታመቻቹ ትችላላችሁ። እንዲህ ዓይነቱ ዝግጅት ከዚህ ግለሰብ ጋር ትዳር መመሥረቱ ጥሩ መሆንና አለመሆኑን እንድታውቁ መልካም አጋጣሚ ይሰጣችኋል።a እዚህ ደረጃ ላይ ከደረሳችሁ በኋላ ልትጠብቋቸው የሚገቡ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ምንድን ናቸው?
12 ይህን ጥያቄ ለመመለስ ሁለት የሙዚቃ መሣሪያዎችን፣ ምናልባትም ፒያኖንና ጊታርን ወደ አእምሯችሁ ልታመጡ ትችላላችሁ። በትክክል ከተቃኙ ሁለቱም የየራሳቸውን ጣዕመ ዜማ ሊያሰሙ ይችላሉ። ሆኖም በአንድ ጊዜ በሁለቱም መሣሪያዎች ብትጫወቱስ? በዚህ ጊዜ የሁለቱም ቃና እርስ በርሱ መጣጣም አለበት። በእናንተና ለትዳር ጓደኝነት ባሰባችሁት ሰው መካከል ያለው ሁኔታም እንደዚሁ ነው። ሁለታችሁም በግለሰብ ደረጃ የየራሳችሁን ባሕርያት “ለመቃኘት” ከፍተኛ ጥረት ስታደርጉ ቆይታችሁ ሊሆን ይችላል። አሁን ግን ጥያቄው፣ እርስ በርሳችሁ ትስማማላችሁን? ወይም በሌላ አነጋገር እርስ በርሳችሁ ትጣጣማላችሁን? የሚል ነው።
13. የእናንተ ዓይነት እምነት ከሌለው ሰው ጋር መጠናናት ጥሩ ያልሆነው ለምንድን ነው?
13 ሁለታችሁም የምታምኑባቸው ነገሮችና የምትመሩባቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች አንድ ዓይነት መሆናቸው በጣም አስፈላጊ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ” ሲል ጽፏል። (2 ቆሮንቶስ 6:14፤ 1 ቆሮንቶስ 7:39) የተለየ እምነት ያለውን ሰው ማግባት በአብዛኛው ከባድ አለመግባባት መፍጠሩ አይቀርም። በሌላ በኩል ግን ሁለታችሁም ለይሖዋ አምላክ ያደራችሁ መሆናችሁ በመካከላችሁ ጠንካራ አንድነት ይፈጥራል። ይሖዋ ደስተኞች እንድትሆኑና ከምታገቡት ሰው ጋር በጣም የተቀራረበ ትስስር እንዲኖራችሁ ይፈልጋል። እርስ በርሳችሁ ብቻ ሳይሆን፣ ይሖዋን ጨምሮ ሦስታችሁም በሦስት በተገመደ የፍቅር ማሰሪያ በአንድ እንድትታሰሩ ይፈልጋል።—መክብብ 4:12
14, 15. በትዳር ውስጥ አንድነት ለመፍጠር የሚያስችለው ባለ ትዳሮቹ አንድ ዓይነት እምነት ያላቸው መሆኑ ብቻ ነውን? አብራራ።
14 አምላክን አንድ ላይ ሆናችሁ ማምለካችሁ በመካከላችሁ አንድነት እንዲኖር ከምንም ነገር በላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያደርግ ቢሆንም ሌላም የሚያስፈልግ ነገር አለ። እርስ በርሳችሁ መጣጣም እንድትችሉ የእናንተና ለትዳር ጓደኝነት ያሰባችሁት ሰው ግቦች አንድ ዓይነት መሆን አለባቸው። እናንተ ያሏችሁ ግቦች ምንድን ናቸው? ለምሳሌ ያህል ልጅ ስለ መውለድ ያላችሁ ስሜት ምንድን ነው? በሕይወታችሁ ውስጥ የመጀመሪያውን ቦታ የምትሰጧቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?b (ማቴዎስ 6:33) ትዳር በእርግጥ የተሳካ እንዲሆን ባልና ሚስቱ ጥሩ ጓደኛሞች መሆን ያለባቸው ከመሆኑም በላይ በወዳጅነታቸው የሚደሰቱ መሆን አለባቸው። (ምሳሌ 17:17) ይህ እንዲሆን ደግሞ የጋራ የሆኑ ፍላጎቶች ሊኖሯቸው ይገባል። እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ከሌለ ግን እንኳን የጠበቀ ወዳጅነት እንዲኖር ለማድረግ ቀርቶ ትዳሩንም ጠብቆ ለማቆየት በጣም አስቸጋሪ ይሆናል። ይህ ሲባል ታዲያ ለትዳር ጓደኝነት ያሰባችሁት ሰው ለሽርሽር የእግር ጉዞ ማድረግ ወይም ሌላ ዓይነት እንቅስቃሴ የሚያስደስተው ቢሆንና እናንተ ደግሞ ለዚህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ ፍላጎት ባይኖራችሁ ፈጽሞ መጋባት የለባችሁም ማለት ነውን? እንደዚያ ማለት አይደለም። ምናልባት ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ሌሎች የጋራ ፍላጎቶች ሊኖሯችሁ ይችላሉ። ከዚህም በተጨማሪ ለትዳር ጓደኝነት ያሰባችሁት ሰው በሚወዳቸው ጤናማ እንቅስቃሴዎች በመካፈል እንዲደሰት ልታደርጉት ትችላላችሁ።—ሥራ 20:35
15 እንዲያውም አቻነት የሚለካው ፍጹም አንድ ዓይነት በመሆናችሁ ሳይሆን ሁለታችሁም ራሳችሁን ከአዳዲስ ሁኔታዎች ጋር ማስማማት በመቻላችሁ ነው። “በሁሉም ነገር እንስማማለንን?” ብሎ ከመጠየቅ ይልቅ “በመካከላችን አለመግባባት ሲፈጠር ምን እናደርጋለን? እርስ በርስ በመከባበር ነገሮችን በረጋ መንፈስ ልንወያይባቸው እንችላለን? ወይስ ብዙውን ጊዜ የሚደረጉት ውይይቶች መስመራቸውን ስተው ወደተጋጋለ ጭቅጭቅ ይለወጣሉ?” ብሎ መጠየቁ የተሻለ ይሆናል። (ኤፌሶን 4:29, 31) ትዳር መመሥረት የምትፈልጉ ከሆነ ኩሩና ሐሳበ ግትር እንዲሁም እኔ ያልኩት ካልሆነ ብሎ ድርቅ ከሚል ወይም ደግሞ ሁሉም ነገር እሱ ባሻው መንገድ ብቻ እንዲፈጸም ከሚፈልግና ከሚጥር ሰው ጋር ዝምድና እንዳታበጁ መጠንቀቅ ይኖርባችኋል።
አስቀድማችሁ በሚገባ አጥኑ
16, 17. አንድ ወንድ ወይም አንዲት ሴት ለትዳር ጓደኝነት ያሰቡትን ሰው አስቀድመው በሚያጠኑበት ጊዜ ከዚያ ሰው ሊጠብቋቸው የሚችሏቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?
16 በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት የሚሰጣቸው ወንድሞች ‘አስቀድመው የተፈተኑ’ ናቸው። (1 ጢሞቴዎስ 3:10) እናንተም ይህን መሠረታዊ ሥርዓት ልትጠቀሙበት ትችላላችሁ። ለምሳሌ ያህል አንዲት ሴት እንዲህ እያለች ልትጠይቅ ትችላለች:- “ይህ ሰው ምን ዓይነት ስም ነው ያለው? ጓደኞቹ እነማን ናቸው? ራሱን ይገዛልን? አረጋውያንን የሚይዘው እንዴት ነው? በምን ዓይነት ቤተሰብ ውስጥ ነው ያደገው? ከቤተሰቡ ጋር ያለው ግንኙነት እንዴት ነው? ለገንዘብ ያለው አመለካከት እንዴት ነው? የአልኮል መጠጦችን አለአግባብ ይጠቀማልን? ግልፍተኛ፣ አልፎ ተርፎም ጠበኛ ነውን? ምን የጉባኤ ኃላፊነቶች አሉት? እነዚህን ኃላፊነቶች የሚይዘውስ እንዴት ነው? በጥልቅ ላከብረው እችላለሁን?”—ዘሌዋውያን 19:32፤ ምሳሌ 22:29፤ 31:23፤ ኤፌሶን 5:3-5, 33፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:8፤ 6:10፤ ቲቶ 2:6, 7
17 አንድ ወንድ ደግሞ እንዲህ እያለ ሊጠይቅ ይችላል:- “ይህች ሴት ለአምላክ ፍቅርና አክብሮት አላትን? ቤት በሚገባ መያዝ ትችላለችን? ቤተሰቧ ከእኛ ምን ይጠብቃሉ? ጥበበኛ፣ ታታሪና ቆጣቢ ነችን? ስለ ምን ነገር ነው ማውራት የምትወደው? ስለ ሌሎች ሰዎች ደህንነት ከልቧ ታስባለች ወይስ ራስ ወዳድና በሌሎች ሰዎች ጉዳይ ጣልቃ የምትገባ ናት? እምነት የሚጣልባት ናትን? ለራስነት ሥልጣን ለመገዛት ፈቃደኛ ነች ወይስ ግትር፣ አልፎ ተርፎም ዓመፀኛ ነች?”—ምሳሌ 31:10-31፤ ሉቃስ 6:45፤ ኤፌሶን 5:22, 23፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:13፤ 1 ጴጥሮስ 4:15
18. በምትጠናኑበት ወቅት አንዳንድ አነስተኛ ድክመቶች ብትመለከቱ ምን ነገር ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርባችኋል?
18 ለትዳር ጓደኝነት የምታስቡት ሰው አለፍጽምና ያለበት የአዳም ዘር እንጂ በልብ ወለድ ታሪክ ውስጥ ፍጹም ተደርጎ የተሳለ ገጸ ባሕርይ አለመሆኑን አትዘንጉ። ሁሉም ሰው የራሱ ድክመቶች አሉት፤ የእናንተም ሆነ ለትዳር ጓደኝነት ያሰባችሁት ሰው አንዳንድ ድክመቶች እንዲሁ መታለፍ ያለባቸው ናቸው። (ሮሜ 3:23፤ ያዕቆብ 3:2) በተጨማሪም አንድ ድክመት መታወቁ በመንፈሳዊ እድገት ለማድረግ አጋጣሚ ሊፈጥር ይችላል። ለምሳሌ ያህል በምትጠናኑበት ጊዜ በመካከላችሁ ጭቅጭቅ ተፈጠረ እንበል። በሚዋደዱና በሚከባበሩ ሰዎች መካከልም እንኳ አንዳንድ ጊዜ አለመግባባት እንደሚፈጠር ልብ በሉ። (ከዘፍጥረት 30:2 እና ከሥራ 15:39 ጋር አወዳድሩ።) ሁለታችሁም ትንሽ ‘መንፈሳችሁን መግታትና’ ነገሮችን ይበልጥ ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፍታትን መማር ያስፈልጋችሁ ይሆን? (ምሳሌ 25:28) ለትዳር ጓደኝነት ያሰባችሁት ሰው ለመሻሻል ፍላጎት እንዳለው ያሳያልን? እናንተስ ይህ ፍላጎት እንዳላችሁ ታሳያላችሁን? ወዲያው ከመቆጣትና ከመከፋት ይልቅ ነገሮችን መቻልን ልትማሩ ትችላላችሁን? (መክብብ 7:9) ለችግሮች እልባት ማግኘትን መማራችሁ ምንም ነገር ሳትደባበቁ በግልጽ መነጋገር የምትችሉበት የሐሳብ ግንኙነት መስመር በመካከላችሁ እንዲዘረጋ ሊያደርግ ይችላል። ይህ ደግሞ ወደፊት የምትጋቡ ከሆነ ለትዳራችሁ እጅግ አስፈላጊ የሆነ ነገር ነው።—ቆላስይስ 3:13
19. በምትጠናኑበት ወቅት ከባድ ችግሮች ብቅ ቢሉ ምን ማድረጉ ጥበብ ይሆናል?
19 ይሁን እንጂ ከፍተኛ ችግር የሚፈጥሩባችሁ ነገሮች እንዳሉ ካወቃችሁ ምን ማድረግ ይኖርባችኋል? እንዲህ ዓይነት ጥርጣሬ ካደረባችሁ ነገሩን በጥሞና ልታስቡበት ይገባል። ምንም ያህል ፍቅር ቢይዛችሁ ወይም ደግሞ ምንም ያህል የማግባት ጉጉት ቢያድርባችሁ ከባድ ለሆኑ ጉድለቶች ዓይናችሁን መጨፈን የለባችሁም። (ምሳሌ 22:3፤ መክብብ 2:14) አጥብቃችሁ የምትቃወሟቸውን ነገሮች ከምታዩበት ሰው ጋር ግንኙነት ፈጥራችሁ ከሆነ ግንኙነቱን ማቋረጥና ከዚያ ሰው ጋር ዘላቂ የሆነ ቃል ኪዳን ከመግባት መቆጠባችሁ ብልህነት ነው።
በመጠናናት የምታሳልፉት ጊዜ ንጹሕ ይሁን
20. መጠናናት የጀመሩ ወንድና ሴት ሥነ ምግባራዊ አቋማቸውን ከነቀፋ ነፃ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?
20 በመጠናናት የምታሳልፉት ጊዜ ንጹሕ መሆን የሚችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ሥነ ምግባራችሁ የሚያስነቅፍ እንዳይሆን መጠንቀቅ አለባችሁ። በምትኖሩበት አካባቢ ያልተጋቡ ወንድና ሴት እጅ ለእጅ መያያዛቸው፣ መሳሳማቸው፣ ወይም ደግሞ መተቃቀፋቸው የማያስነቅፍ ነውን? እንዲህ ዓይነቶቹ የፍቅር መግለጫዎች የማያስነቅፉ ቢሆኑ እንኳ ለመጋባት ቁርጥ ውሳኔ እስካላደረጋችሁ ድረስ እነዚህን ድርጊቶች መፈጸም የለባችሁም። የፍቅር መግለጫዎች ንጹሕ ወዳልሆነ ድርጊት አልፎ ተርፎም ዝሙት ወደ መፈጸም እንዳያደርሱ መጠንቀቅ አለባችሁ። (ኤፌሶን 4:18, 19፤ ከመኃልየ መኃልይ 1:2፤ 2:6፤ 8:5, 9, 10 ጋር አወዳድር።) ልብ አታላይ ስለሆነ በቤት፣ በአፓርታማ፣ በቆመ መኪና ወይም ደግሞ መጥፎ ድርጊት ለመፈጸም የሚያስችል አጋጣሚ ሊፈጥር በሚችል በሌላ በማንኛውም ቦታ ሁለታችሁ ብቻችሁን እንዳትሆኑ ጥንቃቄ ማድረጋችሁ ጥበብ ነው። (ኤርምያስ 17:9) በመጠናናት የምታሳልፉት ጊዜ በሥነ ምግባር ንጹሕ እንዲሆን መጣራችሁ ራሳችሁን እንደምትገዙና ከራሳችሁ ፍላጎት ይልቅ ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ ለሌላው ሰው ደህንነት እንደምታስቡ የሚያሳይ ግልጽ ማስረጃ ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ በመጠናናት አብራችሁ የምታሳልፉት ጊዜ ንጹሕ መሆኑ አገልጋዮቹ ከርኩሰትና ከዝሙት እንዲርቁ ያዘዘውን ይሖዋ አምላክን ያስደስተዋል።—ገላትያ 5:19-21
21. በመጠናናት የምታሳልፉት ጊዜ ንጹሕ እንዲሆን ምን ዓይነት ግልፅ የሆነ የሐሳብ ግንኙነት መስመር መዘርጋት ሊያስፈልግ ይችላል?
21 በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ንጹሕ በሆነ መንገድ መጠናናት፣ ምንም ነገር ሳትደባበቁ በግልጽ መነጋገርንም ይጨምራል። የምታደርጉት መጠናናት መጋባት ወደምትችሉበት ደረጃ እያደገ ሲሄድ አንዳንድ ጉዳዮችን ግልጽ በሆነ መንገድ መወያየት ያስፈልጋችኋል። የምትኖሩት የት ነው? ሁለታችሁም ሰብዓዊ ሥራ ይኖራችኋል? ልጅ መውለድ ትፈልጋላችሁ? በተጨማሪም አንዳንድ ነገሮችን ምናልባትም ጋብቻውን ሊነኩ የሚችሉ ቀደም ሲል የተፈጸሙ ነገሮችን ማንሳቱ ተገቢ ነው። እነዚህም ከበድ ያሉ የገንዘብ ዕዳዎችን ወይም ግዴታዎችን አሊያም ደግሞ ያለባችሁን ከባድ ሕመም ወይም እክል የመሰሉ ከጤና ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ሊያጠቃልሉ ይችላሉ። በኤች አይ ቪ (ኤድስ አማጭ በሆነው ቫይረስ) የተለከፉ ብዙ ሰዎች ወዲያውኑ የበሽታው ምልክቶች ስለማይታዩባቸው አንድ ግለሰብ ወይም አሳቢ የሆኑ ወላጆች ቀደም ሲል ልቅ የሆነ የጾታ ብልግና ይፈጽም የነበረን ወይም ደግሞ አደንዛዥ ዕፆችን በደም ሥሩ ይወስድ የነበረን ሰው የኤድስ የደም ምርመራ እንዲያደርግ ቢጠይቁት ምንም ስህተት የለውም። የምርመራው ውጤት ግለሰቡ በበሽታው መያዙን የሚያረጋግጥ ሆኖ ከተገኘና ሌላኛው ወገን ግንኙነታቸው እንዲቋረጥ ከፈለገ በበሽታው የተያዘው ሰው ግንኙነታቸው እንዲቀጥል ተጽዕኖ ማድረግ የለበትም። ለበሽታው እጅግ የሚያጋልጥ ዓይነት አኗኗር ሲከተል የቆየ ሰው መጠናናት ከመጀመሩ በፊት በፈቃደኝነት የኤድስ የደም ምርመራ ቢያደርግ ጥሩ ይሆናል።
ከሠርጉ ቀን ባሻገር መመልከት
22, 23. (ሀ) አንድ ሰው ሠርግ ሲደግስ ሚዛኑን ሊስት የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) ስለ ሠርጋችሁና ስለ ትዳራችሁ በምታስቡበት ጊዜ ምን ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ ይኖርባችኋል?
22 ከጋብቻ በፊት ባሉት የመጨረሻ ወራት ሁለታችሁም ለሠርጉ በሚደረግ ዝግጅት መወጠራችሁ አይቀርም። ድግሱን መጠነኛ በማድረግ አብዛኛውን ውጥረት ልትቀንሱ ትችላላችሁ። የተንዛዛ ሠርግ ዘመድ አዝማድንና የአካባቢውን ሰው ሊያስደስት ቢችልም በአዲሶቹ ተጋቢዎችና በቤተሰቦቻቸው ላይ ከፍተኛ የሆነ አካላዊ ድካም የሚያስከትል ከመሆኑም በላይ ገንዘባቸውን ያሟጥጣል። በተወሰነ ደረጃ የአካባቢውን ባሕል መከተሉ ምክንያታዊ ቢሆንም ባሕሉን ሙሉ በሙሉ ለመከተል የሚደረገው ጥረትና ምናልባትም ደግሞ በፉክክር መንፈስ የሚደገስ ድግስ የሠርጉን ትርጉም ሊያጠፋውና ማግኘት ያለባችሁን ደስታ እንድታጡ ሊያደርጋችሁ ይችላል። የሌሎች ስሜት ግምት ውስጥ መግባት ያለበት ቢሆንም በሠርጉ ድግስ ላይ መከናወን ያለበትን ነገር በይበልጥ የመወሰን ኃላፊነት ያለው ሙሽራው ነው።—ዮሐንስ 2:9
23 ሠርጋችሁ የሚቆየው ለአንድ ቀን ብቻ መሆኑን አስታውሱ፤ ትዳራችሁ ግን ዕድሜ ልካችሁን አብሯችሁ የሚኖር ነው። ስለ ጋብቻው ሥነ ሥርዓት ከልክ በላይ መጨነቅ አይኖርባችሁም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ አምላክ መመሪያ እንዲሰጣችሁ ጠይቁት፤ በተጨማሪም ተጋብታችሁ ስለምታሳልፉት ሕይወት አስቀድማችሁ ዕቅድ አውጡ። ከዚያ በኋላ ስኬታማ ለሆነ ትዳር በሚገባ የተዘጋጃችሁ ትሆናላችሁ።
a ይህ ሁኔታ የሚሠራው ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥሮ መጫወት ለክርስቲያኖች ተቀባይነት ያለው ሆኖ በሚገኝባቸው አገሮች ነው።
b በክርስቲያን ጉባኤ ያሉ አንዳንዶችም እንኳ በምሳሌያዊ አነጋገር በቋፍ ላይ ያሉ ሊሆኑ ይችላሉ። በሙሉ ልባቸው የሚሠሩ የአምላክ አገልጋዮች ከመሆን ይልቅ የዓለም አመለካከትና አኗኗር ተጽዕኖ የሚያደርግባቸው ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ።—ዮሐንስ 17:16፤ ያዕቆብ 4:4