የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • fy ምዕ. 11 ገጽ 128-141
  • በቤተሰባችሁ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን አድርጉ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በቤተሰባችሁ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን አድርጉ
  • ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ባልሽ የተለየ እምነት ያለው ከሆነ
  • ሚስት የተለየ እምነት በሚኖራት ጊዜ
  • ልጆችን ማሠልጠን
  • ሃይማኖትህ ከወላጆችህ እምነት የተለየ ከሆነ
  • የእንጀራ ወላጅ መሆን የሚያስከትለው ፈታኝ ሁኔታ
  • ቁሳዊ ነገሮች ለማግኘት የምታደርጉት ጥረት ቤተሰባችሁን ይከፋፍለዋልን?
  • ቤተሰብህ ደስተኛ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
    መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምረናል?
  • የቤተሰብን ኑሮ የተሳካ ማድረግ
    በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ
  • ትዳርን ዘላቂ ለማድረግ የሚረዱ ሁለት ቁልፍ ነገሮች
    ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?
  • አምላክን የሚያስደስት የቤተሰብ ሕይወት
    አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው?
ለተጨማሪ መረጃ
ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?
fy ምዕ. 11 ገጽ 128-141

ምዕራፍ አሥራ አንድ

በቤተሰባችሁ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን አድርጉ

1. ቤተሰብን ሊከፋፍሉ የሚችሉ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?

ፍቅር፣ ስምምነትና ሰላም በሰፈነበት ቤተሰብ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ደስተኞች ናቸው። የእናንተም ቤተሰብ እንዲህ እንደሆነ እናምናለን። የሚያሳዝነው ግን ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ቤተሰቦች እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ የማይታይባቸውና በተለያየ ምክንያት የተከፋፈሉ ናቸው። ቤተሰቦችን የሚከፋፍሉ ነገሮች ምንድን ናቸው? በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ቤተሰብን የሚከፋፍሉ ሦስት ነገሮችን እንመለከታለን። በአንዳንድ ቤተሰቦች ውስጥ የቤተሰቡ አባላት የተለያየ ሃይማኖት ያላቸው ይሆናሉ። በሌሎቹ ቤተሰቦች ውስጥ የሚገኙት ልጆች ከተለያዩ ወላጆች የተወለዱ ሊሆኑ ይችላሉ። በአንዳንዶቹ ቤተሰቦች ውስጥ ደግሞ መተዳደሪያ ለማግኘት የሚደረገው ትግል ወይም ተጨማሪ ቁሳዊ ነገሮችን ለማግኘት ያላቸው ፍላጎት የቤተሰቡን አባላት ሊከፋፍላቸው ይችላል። ሆኖም አንዱን ቤተሰብ የሚከፋፍሉት ሁኔታዎች በሌላው ቤተሰብ ላይ ምንም ተጽዕኖ ላያሳድሩ ይችላሉ። ይህ የሚሆነው ለምንድን ነው?

2. አንዳንዶች ስለ ቤተሰብ ሕይወት መመሪያ ለማግኘት የሚጥሩት ከማን ነው? ይሁን እንጂ በዚህ ረገድ ከሁሉ የተሻለ መመሪያ የሚገኘው ከየት ነው?

2 በዚህ ረገድ አንዱ ትልቅ ሚና የሚጫወተው ነገር አመለካከት ነው። የሌላውን ሰው አመለካከት ለመረዳት ከልባችሁ የምትጥሩ ከሆነ የቤተሰባችሁ አንድነት ተጠብቆ መቀጠል እንዲችል ምን ማድረግ እንደምትችሉ ማስተዋል አያዳግታችሁም። ሌላው ትልቅ ሚና የሚጫወተው መመሪያ አድርጋችሁ የምትጠቀሙበት ነገር ነው። ብዙ ሰዎች የሥራ ጓደኞቻቸው፣ ጎረቤቶቻቸው፣ የጋዜጣ አምድ አዘጋጆች ወይም ሌሎች ሰብዓዊ አማካሪዎች የሚሰጧቸውን ምክር ይከተላሉ። ይሁን እንጂ አንዳንዶች የአምላክ ቃል እነርሱ ስላሉበት ሁኔታ ምን እንደሚናገር በመመርመር ያገኙትን ትምህርት ሥራ ላይ አውለዋል። አንድ ቤተሰብ እንዲህ ማድረጉ ዘወትር በቤቱ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ ሊረዳው የሚችለው እንዴት ነው?​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:​16, 17

ባልሽ የተለየ እምነት ያለው ከሆነ

በገጽ 130 ላይ የሚገኝ ሥዕል

የሌላውን ሰው አመለካከት ለመረዳት ጣሩ

3. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ የተለየ እምነት ያለውን ሰው ማግባትን በተመለከተ ምን ምክር ይሰጣል? (ለ) አማኝ ያልሆነ የትዳር ጓደኛ ያለውን ሰው የሚመለከቱ አንዳንድ ዋና ዋና መሠረታዊ ሥርዓቶች የትኞቹ ናቸው?

3 መጽሐፍ ቅዱስ የተለየ ሃይማኖታዊ እምነት ያለውን ሰው እንዳናገባ አጥብቆ ይመክረናል። (ዘዳግም 7:​3, 4፤ 1 ቆሮንቶስ 7:​39) ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የሰማሽው ካገባሽ በኋላ ሊሆን ይችላል፤ ባልሽ ደግሞ እውነትን አልተቀበለ ይሆናል። በዚህ ጊዜ ምን ታደርጊያለሽ? የጋብቻችሁ መሐላ በዚህ ጊዜም እንደጸና ይቀጥላል። (1 ቆሮንቶስ 7:​10) መጽሐፍ ቅዱስ የትዳር ማሰሪያን ዘላቂነት ጠበቅ አድርጎ የሚገልጽ ከመሆኑም በላይ የትዳር ጓደኛሞች በመካከላቸው አለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜ ለችግሩ እልባት ለማግኘት መጣር እንጂ ከችግሩ መሸሽ እንደሌለባቸው ያሳስባል። (ኤፌሶን 5:​28-31፤ ቲቶ 2:​4, 5) ይሁን እንጂ ባልሽ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን እምነት በመከተልሽ አጥብቆ ቢቃወምሽስ? ወደ ጉባኤ ስብሰባዎች እንዳትሄጂ ሊከለክልሽ ይሞክር ይሆናል፤ ወይም ደግሞ ከቤት ወደ ቤት እየሄድሽ ስለ ሃይማኖት እንድትሰብኪ አልፈልግም ይልሽ ይሆናል። በዚህ ጊዜ ምን ታደርጊያለሽ?

4. አንዲት ሚስት ባሏ ከእሷ የተለየ እምነት ያለው ከሆነ ስሜቱን ልትጋራው የምትችለው በምን መንገድ ነው?

4 ‘ባሌ እንዲህ ዓይነት ስሜት ሊያድርበት የቻለው ለምንድን ነው?’ ብለሽ ራስሽን ጠይቂ። (ምሳሌ 16:​20, 23) እያደረግሽ ያለውን ነገር በትክክል አልተረዳ ከሆነ ለአንቺ ደህንነት እያሰበ ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ ዘመዶቹ ከፍ አድርገው በሚመለከቷቸው አንዳንድ ባሕላዊ ልማዶች ላይ ባለመካፈልሽ ተጽዕኖ እያደረጉበት ይሆናል። “ቤት ውስጥ ብቻዬን ስቀር እንደተተውኩ ሆኖ ይሰማኛል” ሲል አንድ ባል ተናግሯል። ይህ ሰው ሃይማኖት ሚስቱን እንደነጠቀው ሆኖ ተሰምቶት ነበር። ሆኖም የነበረው ኩራት የተሰማውን የብቸኝነት ስሜት አውጥቶ እንዳይናገር አግዶት ነበር። ለይሖዋ ያለሽ ፍቅር ቀደም ሲል ለባልሽ የነበረሽን ፍቅር እንደማይቀንሰው ባልሽ እንዲገነዘብ ማድረግ ሊያስፈልግሽ ይችላል። ከባልሽ ጋር ጊዜ ማሳለፍ ይኖርብሻል።

5. የተለየ እምነት የሚከተል ባል ያላት ሚስት ምን ዓይነት ሚዛን መጠበቅ አለባት?

5 ይሁን እንጂ ሁኔታውን ጥበብ በተሞላበት መንገድ መቋቋም እንድትችይ ከዚህም ይበልጥ ልታስቢበት የሚገባ ነገር አለ። የአምላክ ቃል “በጌታ እንደሚገባ ለባሎቻችሁ ተገዙ” ሲል ሚስቶችን አጥብቆ ያሳስባል። (ቆላስይስ 3:​18) በዚህ መንገድ ሚስቶች በራስ ከመመራት መንፈስ እንዲጠበቁ ያሳስባል። በተጨማሪም “በጌታ እንደሚገባ” የሚለው የዚህ ጥቅስ አነጋገር ሚስቶች ለባሎቻቸው በሚገዙበት ጊዜ ለጌታም መገዛት እንዳለባቸው መዘንጋት እንደማይኖርባቸው ያመለክታል። ሚዛናዊ መሆን ያስፈልጋል።

6. አንዲት ክርስቲያን ሚስት የትኞቹን መሠረታዊ ሥርዓቶች ማስታወስ ይኖርባታል?

6 አንድ ክርስቲያን በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የመገኘትና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን እምነቱን ለሌሎች የመመሥከር ኃላፊነት አለበት፤ እነዚህ ነገሮች ችላ ሊላቸው የማይገቡ የእውነተኛው አምልኮ ዘርፎች ናቸው። (ሮሜ 10:​9, 10, 14፤ ዕብራውያን 10:​24, 25) እንግዲያው አንድ ሰው አምላክ ያዘዘውን ነገር እንዳታደርጊ በቀጥታ ቢያዝሽ ምን ታደርጊያለሽ? የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል” ሲሉ ገልጸዋል። (ሥራ 5:​29) እነዚህ ሐዋርያት የተዉት ምሳሌ በዛሬው ጊዜ በብዙ ሁኔታዎች ሊሠራ የሚችል ነው። ለይሖዋ ያለሽ ፍቅር ለእሱ የሚገባውን አምልኮ እንድታቀርቢ ይገፋፋሻልን? ከዚሁ ጋር ጎን ለጎን ደግሞ፣ ለባልሽ ያለሽ ፍቅርና አክብሮት ይህን አምልኮ ባልሽን በማያስቆጣ መንገድ ለማቅረብ እንድትሞክሪ ያነሳሳሻልን?​—⁠ማቴዎስ 4:​10፤ 1 ዮሐንስ 5:​3

7. አንዲት ክርስቲያን ሚስት ምን ዓይነት ቁርጥ ውሳኔ ሊኖራት ይገባል?

7 ኢየሱስ እንዲህ ማድረግ የማይቻልባቸው ሁኔታዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ አመልክቷል። በእውነተኛው አምልኮ ላይ በሚሰነዘር ተቃውሞ ምክንያት አማኝ የሆኑ የአንዳንድ ቤተሰብ አባላት ከተቀሩት የቤተሰባቸው አባላት ጋር በሰይፍ የተለያዩ ያህል ሆነው እንደሚከፋፈሉ አስጠንቅቋል። (ማቴዎስ 10:​34-36) በጃፓን የምትኖር አንዲት ሴት ይህ ሁኔታ ደርሶባታል። ባሏ ለ11 ዓመታት ያህል ይቃወማት ነበር። በጣም ያሰቃያት የነበረ ከመሆኑም በላይ ብዙ ጊዜ ከቤት አስወጥቶ ይቆልፍባት ነበር። ሆኖም በአቋሟ ጸናች። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ ጓደኞቿ አስፈላጊውን እርዳታ አደረጉላት። ያለማቋረጥ ወደ ይሖዋ ትጸለይ የነበረ ከመሆኑም በላይ 1 ጴጥሮስ 2:​20 ጥሩ ማበረታቻ ሆኖላታል። ይህች ክርስቲያን በአቋሟ ከጸናች፣ አንድ ቀን ባሏ ተለውጦ ከእሷ ጋር ይሖዋን ማገልገል እንደሚጀምር ጽኑ እምነት ነበራት። ያሰበችው አልቀረም፤ ከጊዜ በኋላ ይህ እምነቷ እውን ሆነ።

8, 9. አንዲት ሚስት በባልዋ ፊት አላስፈላጊ እንቅፋቶች እንዳትፈጥር ምን ማድረግ ይኖርባታል?

8 የትዳር ጓደኛሽን አመለካከት ለመለወጥ ውጤታማ የሆኑ ብዙ ነገሮች ማድረግ ትችያለሽ። ለምሳሌ ያህል ባልሽ ሃይማኖትሽን የሚቃወም ከሆነ በሌሎች መስኮች ስሞታ ለማቅረብ የሚያስችል ነገር እንዳያገኝ ጥረት አድርጊ። ቤቱን በንጽሕና ያዢ። ራስሽን ጠብቂ። ዘወትር ፍቅርሽንና አድናቆትሽን ግለጪለት። ከመተቸት ይልቅ ድጋፍ ስጭው። የእሱን የራስነት አመራር እንደምትፈልጊ አሳዪው። እንደበደለሽ ሆኖ ከተሰማሽ አጸፋውን ለመመለስ ማሰብ የለብሽም። (1 ጴጥሮስ 2:​21, 23) ያለበትን ሰብዓዊ አለፍጽምና ግምት ውስጥ አስገቢ፤ ጭቅጭቅ ከተፈጠረ ደግሞ በትሕትና ይቅርታ ለመጠየቅ ቀዳሚ ሁኚ።​—⁠ኤፌሶን 4:​26

9 በስብሰባዎች ላይ መገኘትሽ የእራቱ ሰዓት እንዲዘገይበት ምክንያት መሆን የለበትም። በተጨማሪም አንዳንዴ ክርስቲያናዊ አገልግሎትሽን ባልሽ እቤት በማይኖርበት ጊዜ ማከናወን የተሻለ ሆኖ ልታገኚው ትችያለሽ። አንዲት ክርስቲያን ሴት ባሏ እንድትሰብክለት የማይፈልግ ከሆነ እንዲህ ከማድረግ መታቀብ ይኖርባታል። ከዚህ ይልቅ የሚከተለውን የሐዋርያው ጴጥሮስ ምክር ትከተላለች:- “እንዲሁም፣ እናንተ ሚስቶች ሆይ፣ ከባሎቻችሁ አንዳንዱ ለትምህርት የማይታዘዙ ቢኖሩ፣ በፍርሃት ያለውን ንጹሑን ኑሮአችሁን እየተመለከቱ ያለ ትምህርት በሚስቶቻቸው ኑሮ እንዲገኙ ተገዙላቸው።” (1 ጴጥሮስ 3:​1, 2) ክርስቲያን ሚስቶች የአምላክን መንፈስ ፍሬዎች በማፍራት ይበልጥ በተሟላ መንገድ ይሠራሉ።​—⁠ገላትያ 5:​22, 23

ሚስት የተለየ እምነት በሚኖራት ጊዜ

10. አንድ አማኝ የሆነ ባል ሚስቱ ከእሱ የተለየ እምነት ያላት ከሆነች እንዴት ሊይዛት ይገባል?

10 ባል ክርስቲያን ሆኖ ሚስት የተለየ እምነት ያላት በምትሆንበት ጊዜስ? መጽሐፍ ቅዱስ ለእንዲህ ዓይነቶቹ ሁኔታዎች መመሪያ ይሰጣል። “ከወንድሞች ወገን ያላመነች ሚስት ያለችው ቢኖር እርስዋም ከእርሱ ጋር ልትቀመጥ ብትስማማ፣ አይተዋት” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 7:​12) በተጨማሪም “ሚስቶቻችሁን ውደዱ” ሲል ባሎችን አጥብቆ ይመክራል።​—⁠ቆላስይስ 3:​19

11. አንድ ባል ሚስቱ ክርስቲያን ካልሆነች አስተዋይ መሆንና የራስነት ሥልጣኑን በዘዴ መጠቀም የሚችለው እንዴት ነው?

11 ሚስትህ ከአንተ የተለየ እምነት ያላት ከሆነች ለሚስትህ አክብሮት ለማሳየትና ለስሜቷ ትኩረት ለመስጠት ይበልጥ መጠንቀቅ ይኖርብሃል። ዐዋቂ እንደ መሆኗ መጠን አንተ የማትስማማባቸው ቢሆኑም እንኳ ሃይማኖታዊ እምነቶቿን መፈጸም የምትችልበት የተወሰነ ነፃነት ሊኖራት ይገባል። ስለ እምነትህ ለመጀመሪያ ጊዜ ስትነግራት ለብዙ ዓመታት አብረዋት የኖሩትን እምነቶች በአንድ ጊዜ እርግፍ አድርጋ በመተው አዲሱን እምነት ትቀበላለች ብለህ መጠበቅ የለብህም። እሷም ሆነች ቤተሰቧ ለረጅም ጊዜ ከፍ አድርገው ሲመለከቷቸው የቆዩት ልማዶች ሐሰት መሆናቸውን በቀጥታ ከመናገር ይልቅ ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀስክ አሳማኝ በሆነ መንገድ በትዕግሥት ልታወያያት ሞክር። ለጉባኤ ሥራዎች ብዙ ጊዜ የምታውል ከሆነ ሚስትህ እንደተተወች ሆኖ ሊሰማት ይችላል። ይሖዋን ለማገልገል የምታደርገውን ጥረት ትቃወም ይሆናል፤ ከበስተጀርባ ያለው መልእክት ግን “ከእኔ ጋር የበለጠ ጊዜ እንድታሳልፍ እፈልጋለሁ!” የሚል ብቻ ሊሆን ይችላል። ታጋሽ ሁን። ለሚስትህ ፍቅራዊ አሳቢነት ማሳየትህ ከጊዜ በኋላ እውነተኛውን አምልኮ እንድትቀበል ሊረዳት ይችላል።​—⁠ቆላስይስ 3:​12-14፤ 1 ጴጥሮስ 3:​8, 9

ልጆችን ማሠልጠን

12. አንድ ባልና ሚስት እምነታቸው የተለያየ በሚሆንበት ጊዜም እንኳ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙት መሠረታዊ ሥርዓቶች ልጆችን በማሠልጠን ረገድ እንዴት ሊሠራባቸው ይገባል?

12 በአምልኮ በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ አንዳንድ ጊዜ ለልጆቹ የሚሰጠውን ሃይማኖታዊ ትምህርት በተመለከተ አከራካሪ ጉዳይ ሊፈጠር ይችላል። በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙት መሠረታዊ ሥርዓቶች ሥራ ላይ መዋል ያለባቸው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ልጆችን የማስተማሩን ዋነኛ ኃላፊነት የሚሰጠው ለአባት ነው፤ ሆኖም እናትም በዚህ ረገድ ከፍተኛ ሚና ትጫወታለች። (ምሳሌ 1:​8፤ ከዘፍጥረት 18:​19 እና ከ⁠ዘዳግም 11:​18, 19 ጋር አወዳድሩ።) አባትየው የክርስቶስን የራስነት ሥልጣን ባይቀበልም እንኳ የቤተሰቡ ራስ እሱ ነው።

13, 14. አንዲት ሚስት ልጆቿን ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ይዛ እንዳትሄድ ወይም ደግሞ እንዳታስጠናቸው ባሏ ቢከለክላት ምን ማድረግ ትችላለች?

13 አንዳንድ የማያምኑ አባቶች እናትየው ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን ለልጆቿ ብታስተምር አይቃወሟትም። ሌሎቹ ግን ይቃወማሉ። ባልሽ ልጆቹን ወደ ጉባኤ ስብሰባዎች ይዘሻቸው እንዳትሄጂ አልፎ ተርፎም ቤት ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳታስጠኛቸው ቢከለክልሽስ? በዚህ ጊዜ የተለያዩ ግዴታዎችሽን ማለትም ለይሖዋ አምላክ፣ ለባልሽና ለውድ ልጆችሽ ያሉብሽን ግዴታዎች ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መወጣት ይኖርብሻል። እነዚህን ነገሮች ማስታረቅ የምትችዪው እንዴት ነው?

14 ስለ ጉዳዩ እንደምትጸልዪ የታወቀ ነው። (ፊልጵስዩስ 4:​6, 7፤ 1 ዮሐንስ 5:​14) ይሁን እንጂ በመጨረሻ የምትወስጂውን እርምጃ መወሰን ያለብሽ ራስሽ ነሽ። የባልሽን የራስነት ሥልጣን እየተቀናቀንሽ እንዳልሆነ ግልጽ በማድረግ በዘዴ ግዴታዎችሽን ለመወጣት ጥረት የምታደርጊ ከሆነ ከጊዜ በኋላ የባልሽ ተቃውሞ ሊረግብ ይችላል። ባልሽ ልጆችሽን ወደ ስብሰባዎች እንዳትወስጂያቸው ወይም ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳታስጠኚያቸው ቢከለክልሽ እንኳ እነሱን ማስተማር የምትቺይበት መንገድ አለ። በየዕለቱ ከልጆችሽ ጋር የምታደርጊውን የሐሳብ ልውውጥ መሣሪያ አድርገሽ በመጠቀምና ጥሩ ምሳሌ በመሆን በተወሰነ ደረጃ ለይሖዋ ፍቅር እንዲያድርባቸው፣ በቃሉ እንዲያምኑ፣ አባታቸውን ጨምሮ ወላጆቻቸውን እንዲያከብሩ፣ ለሌሎች ሰዎች ፍቅራዊ አሳቢነት እንዲኖራቸውና የሥራ ፍቅር እንዲያድርባቸው ለማድረግ ጣሪ። ከጊዜ በኋላ አባታቸው የተገኙትን ጥሩ ውጤቶች ሊመለከትና ያደረግሽው ጥረት ያስገኘውን ጥቅም ሊያደንቅ ይችላል።​—⁠ምሳሌ 23:​24

15. ልጆችን በማስተማር ረገድ አማኝ የሆነ ባል ምን ኃላፊነት አለበት?

15 አማኝ ያልሆነች ሚስት ያለህ ባል ከሆንክ ደግሞ ልጆችህን “በጌታ ምክርና በተግሣጽ” የማሳደጉን ኃላፊነት መሸከም አለብህ። (ኤፌሶን 6:​4) እርግጥ ይህን በምታደርግበት ጊዜ ከሚስትህ ጋር ባለህ ግንኙነት ደግ፣ አፍቃሪና ምክንያታዊ መሆን ይኖርብሃል።

ሃይማኖትህ ከወላጆችህ እምነት የተለየ ከሆነ

16, 17. ልጆች ከወላጆቻቸው የተለየ እምነት ከያዙ የትኞቹን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ማስታወስ አለባቸው?

16 ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆች እንኳ ከወላጆቻቸው የተለዩ ሃይማኖታዊ አመለካከቶችን መቀበላቸው እንግዳ ነገር አይደለም። አንተም እንደዚህ አድርገሃልን? እንደዚህ አድርገህ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ለአንተም የሚሆን ምክር ይዟል።

17 የአምላክ ቃል “ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ፣ ይህ የሚገባ ነውና። . . . አባትህንና እናትህን አክብር” ይላል። (ኤፌሶን 6:​1, 2) ይህ ለወላጆች ጤናማ አክብሮት ማሳየት ይጠይቃል። ይሁን እንጂ ወላጆችን መታዘዝ አስፈላጊ ቢሆንም እንኳ ይህ ታዛዥነት ለእውነተኛው አምላክ መሰጠት ያለበትን ቦታ የሚጋፋ መሆን የለበትም። አንድ ልጅ አድጎ የራሱን ውሳኔዎች ማድረግ ሲጀምር ለሚያደርጋቸው ነገሮች ያለበት ኃላፊነት ይጨምራል። ይህ በሰብዓዊ ሕግ ረገድ ብቻ ሳይሆን በመለኮታዊውም ሕግ ረገድ የበለጠ ይሠራል። መጽሐፍ ቅዱስ “እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን” ሲል ይገልጻል።​—⁠ሮሜ 14:​12

18, 19. ልጆች ሃይማኖታቸው ከወላጆቻቸው የተለየ ከሆነ ወላጆቻቸው እምነታቸውን ይበልጥ እንዲያውቁት ሊረዷቸው የሚችሉት እንዴት ነው?

18 እምነትህ በሕይወትህ ላይ ለውጥ ካመጣ የወላጆችህን አመለካከት ለመረዳት መጣር ይኖርብሃል። የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች በመማርህና በሥራ ላይ በማዋልህ ምክንያት ከበፊቱ ይበልጥ ወላጆችህን የምታከብር፣ የምትታዘዝና ያዘዙህን ነገር በትጋት የምታከናውን ከሆንክ ሊደሰቱ እንደሚችሉ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ከዚህ በተጨማሪ አዲሱ እምነትህ ወላጆችህ በግላቸው ከፍ አድርገው የሚመለከቷቸውን እምነቶችና ልማዶች እንድትተው የሚያደርግህ ከሆነ እነርሱ ሊያወርሱህ የሚፈልጉትን ቅርስ እንዳቃለልክ ሆኖ ሊሰማቸው ይችላል። በተጨማሪም እያደረግክ ያለኸው ነገር በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ከሆነ ወይም ደግሞ ቁሳዊ ብልጽግና እንድታገኝ ሊረዱህ ይችላሉ ብለው በሚያስቧቸው ነገሮች ላይ እንዳታተኩር የሚያደርግህ ከሆነ ለደህንነትህ ሊሰጉ ይችላሉ። ኩራትም እንቅፋት ሊሆንባቸው ይችላል። በተዘዋዋሪ መንገድ እኔ ትክክል ነኝ፤ እናንተ ተሳስታችኋል እንዳልካቸው ሆኖ ይሰማቸው ይሆናል።

19 ስለዚህ በተቻለ መጠን ወላጆችህ በጉባኤህ ውስጥ ከሚገኙ አንዳንድ ሽማግሌዎች ወይም ሌሎች የጎለመሱ ክርስቲያኖች ጋር ቶሎ እንዲገናኙ ለማድረግ ሞክር። ወላጆችህ ወደ መንግሥት አዳራሹ መጥተው እዚያ የሚሰጠውን ትምህርት ራሳቸው እንዲሰሙና የይሖዋ ምሥክሮች ምን ዓይነት ሰዎች እንደሆኑ እንዲመለከቱ አበረታታቸው። ውሎ አድሮ የወላጆችህ አቋም ሊለዝብ ይችላል። ወላጆች በተቃውሟቸው ሲገፉ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ሲቀዳድዱና ልጆቻቸው ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች እንዳይሄዱ ሲከለክሉ እንኳ ብዙውን ጊዜ በሌላ ቦታ ማንበብ፣ ከመሰል ክርስቲያኖች ጋር መነጋገር እንዲሁም መደበኛ ባልሆነ መንገድ መመስከርና ሌሎችን መርዳት የሚቻልባቸው አጋጣሚዎች ይኖራሉ። በተጨማሪም ወደ ይሖዋ መጸለይ ትችላለህ። አንዳንድ ወጣቶች የበለጠ መሥራት የሚችሉት ለአካለ መጠን ደርሰው ከቤተሰባቸው ውጪ ራሳቸውን ችለው መኖር ሲጀምሩ ነው። ይሁን እንጂ ቤት ውስጥ ያለው ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ‘አባትህንና እናትህን ማክበር’ እንዳለብህ አትዘንጋ። በቤታችሁ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን የበኩልህን አስተዋጽኦ አድርግ። (ሮሜ 12:​17, 18) ከሁሉ በላይ ደግሞ ምንጊዜም ከአምላክ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ይኑርህ።

የእንጀራ ወላጅ መሆን የሚያስከትለው ፈታኝ ሁኔታ

20. ልጆች አባታቸው ወይም እናታቸው እንጀራ ወላጅ ከሆኑ ምን ስሜት ሊያድርባቸው ይችላል?

20 በብዙዎቹ ቤተሰቦች ውስጥ ከሁሉ ይበልጥ ፈታኝ ሁኔታ የሚፈጥረው ሃይማኖት ሳይሆን በቤተሰቡ ውስጥ የእንጀራ ወላጅ መኖሩ ነው። በአሁኑ ጊዜ በብዙዎቹ ቤተሰቦች ውስጥ አንደኛው ወይም ሁለቱም ወላጆች ከቀድሞ የትዳር ጓደኛቸው የወለዷቸው ልጆች ይኖራሉ። በእንዲህ ዓይነቱ ቤተሰብ ውስጥ የሚገኙ ልጆች የቅናት ስሜት ሊያድርባቸው፣ ቂም ሊይዙ ምናልባትም ደግሞ ለእንጀራ ወላጃቸው ታማኝ ሆኖ መገኘት ሊቸግራቸው ይችላል። በዚህም የተነሳ የእንጀራ ወላጆች ጥሩ አባት ወይም እናት ሆነው ለመገኘት ከልባቸው የሚያደርጉትን ጥረት ላይቀበሉት ይችላሉ። የእንጀራ ወላጅ ያለባቸው ቤተሰቦች የተሳካ ሕይወት መምራት እንዲችሉ ሊረዳቸው የሚችለው ነገር ምንድን ነው?

በገጽ 138 ላይ የሚገኝ ሥዕል

ሥጋዊ ወላጅም ሆናችሁ የእንጀራ ወላጅ መጽሐፍ ቅዱስን መመሪያ አድርጋችሁ ተጠቀሙበት

21. የእንጀራ ወላጆች ምንም እንኳ ያሉበት ሁኔታ የተለየ ቢሆንም እርዳታ ለማግኘት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን መሠረታዊ ሥርዓቶች መመልከት ያለባቸው ለምንድን ነው?

21 ምንም እንኳ በእንዲህ ዓይነቶቹ ቤተሰቦች ውስጥ ያሉት ሁኔታዎች የተለዩ ቢሆኑም ሌሎቹን ቤተሰቦች የተሳካ ሕይወት መምራት እንዲችሉ የረዷቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች እነዚህንም ቤተሰቦች ሊረዷቸው ይችላሉ። እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች ችላ ማለቱ ለጊዜው ችግሩን የሚያቃልል መስሎ ሊታይ ቢችልም የኋላ ኋላ ግን የከፋ ሐዘን ማስከተሉ አይቀርም። (መዝሙር 127:​1፤ ምሳሌ 29:​15) ዘላቂ ጥቅም የሚያስገኙትን አምላካዊ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶች ሥራ ላይ ለማዋል የሚያስችል ጥበብና የቤተሰባችሁ አባላት አንዳንድ ነገሮችን የሚናገሩትና የሚያደርጉት ለምን እንደሆነ ለማወቅ የሚያስችል ጥሩ የማስተዋል ችሎታ አዳብሩ። የሌላውን ሰው ስሜት መጋራትም በጣም አስፈላጊ ነው።​—⁠ምሳሌ 16:​21፤ 24:​3፤ 1 ጴጥሮስ 3:​8

22. ልጆች የእንጀራ ወላጅን መቀበል ሊከብዳቸው የሚችለው ለምንድን ነው?

22 የእንጀራ ወላጅ ከመሆናችሁ በፊት የቤተሰቡ ወዳጅ በነበራችሁበት ጊዜ ልጆቹ በጥሩ ሁኔታ ይቀበሏችሁ እንደነበረ ታስታውሱ ይሆናል። ሆኖም የእንጀራ ወላጃቸው ስትሆኑ አመለካከታቸው ሊለወጥ ይችላል። አብሯቸው የሌለውን ወላጅ በማስታወስና ምናልባትም ደግሞ ለእሱ ያላቸውን ፍቅር ለመንጠቅ እንደምትፈልጉ አድርገው በማሰብ ለእናንተ ታማኝነት ለማሳየት ሊቸገሩ ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ አንተ አባቴ አይደለህም ወይም አንቺ እናቴ አይደለሽም ብለው ፊት ለፊት ሊናገሯችሁ ይችላሉ። እንዲህ ዓይነቱ አነጋገር በጣም ይጎዳል። ሆኖም “በነፍስህ ለቁጣ ችኩል አትሁን።” (መክብብ 7:​9) የልጆቹን ስሜት ላለመጉዳት አስተዋይ መሆንና ስሜታቸውን መጋራት በጣም አስፈላጊ ነው።

23. የእንጀራ ልጆች ባሉበት ቤተሰብ ውስጥ ተግሣጽ እንዴት ሊሰጥ ይችላል?

23 አንድ ወላጅ ተግሣጽ በሚሰጥበት ጊዜ እነዚህን ባሕርያት ማሳየቱ በጣም ወሳኝ ነው። የምትሰጡት ተግሣጽ ተለዋዋጭ መሆን የለበትም። (ምሳሌ 6:​20፤ 13:​1) በተጨማሪም ሁሉም ልጆች አንድ ዓይነት ስላልሆኑ የሚሰጣቸው ተግሣጽ የተለያየ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ የእንጀራ ወላጆች ቢያንስ ቢያንስ መጀመሪያ ላይ ይህን ኃላፊነት ወላጅ እናት ወይም አባት ቢወጣው ይመርጣሉ። ሆኖም ተግሣጹን ሁለቱም ወላጆች ሊስማሙበትና ሊደግፉት ይገባል፤ ከአብራካቸው ለወጣ ልጃቸው ማድላት የለባቸውም። (ምሳሌ 24:​23) ልጆቻችሁ ታዛዥ መሆናቸው በጣም አስፈላጊ ነው፤ ሆኖም ያለባቸውን አለፍጽምና ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርባችኋል። ከሚገባው በላይ ቁጡዎችና ኃይለኞች አትሁኑባቸው። በፍቅር ገሥጿቸው።​—⁠ቆላስይስ 3:​21

24. የእንጀራ ወላጅ ባለበት ቤተሰብ ውስጥ በሚገኙ ተቃራኒ ጾታዎች መካከል የሥነ ምግባር ችግር እንዳይፈጠር ለመከላከል ሊረዳ የሚችለው ነገር ምንድን ነው?

24 በቤተሰብ ደረጃ መወያየት ችግሮችን ለማስወገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል። ቤተሰቡ በሕይወት ውስጥ ይበልጥ አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩር ሊረዳው ይችላል። (ከፊልጵስዩስ 1:​9-11 ጋር አወዳድሩ።) በተጨማሪም እንዲህ ዓይነቱ ውይይት ቤተሰቡ ያወጣቸው ግቦች ላይ እንዲደርስ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል እንዴት የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚችል እንዲገነዘብ ይረዳዋል። ከዚህም በተጨማሪ ግልጽ የቤተሰብ ውይይት ማድረግ ሥነ ምግባራዊ ችግሮችን ሊያስወግድ ይችላል። ልጃገረዶች በእንጀራ አባታቸውና ከእንጀራ ወላጃቸው በተወለዱት ወንድሞቻቸው ፊት ምን ዓይነት አለባበስና ምግባር ሊኖራቸው እንደሚገባ ማወቅ አለባቸው፤ ወንዶች ልጆችም ለእንጀራ እናታቸውና ከእንጀራ ወላጃቸው ለተወለዱት እህቶቻቸው ትክክለኛ ሥነ ምግባር እንዲያሳዩ ምክር ሊሰጣቸው ይገባል።​—⁠1 ተሰሎንቄ 4:​3-8

25. የእንጀራ ወላጅ ባለበት ቤተሰብ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ሊረዱ የሚችሉት ባሕርያት የትኞቹ ናቸው?

25 የእንጀራ ወላጅ መሆን የሚያስከትለውን ለየት ያለ ፈታኝ ሁኔታ ለመቋቋም በምታደርጉት ጥረት ታጋሾች መሆን ይኖርባችኋል። አዲስ ዝምድና ለማዳበር ጊዜ ይጠይቃል። ከአብራካችሁ ያልወጡ ልጆችን ፍቅርና አክብሮት ለማትረፍ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ሊጠይቅባችሁ ይችላል። ሆኖም የማይቻል ነገር አይደለም። ይሖዋን ለማስደሰት ጠንካራ ፍላጎት ያለው ጥበበኛና አስተዋይ ልብ የእንጀራ ወላጅ ባለበት ቤተሰብ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ቁልፍ ሚና ይጫወታል። (ምሳሌ 16:​20) እንዲህ ዓይነቶቹ ባሕርያት ሌሎች ሁኔታዎችንም እንድትቋቋሙ ሊረዷችሁ ይችላሉ።

ቁሳዊ ነገሮች ለማግኘት የምታደርጉት ጥረት ቤተሰባችሁን ይከፋፍለዋልን?

26. ከቁሳዊ ነገሮች ጋር የተያያዙ ችግሮችና አመለካከቶች አንድን ቤተሰብ ሊከፋፍሉ የሚችሉት በምን መንገዶች ነው?

26 ከቁሳዊ ነገሮች ጋር የተያያዙ ችግሮችና አመለካከቶች ቤተሰቦችን በብዙ መንገዶች ሊከፋፍሏቸው ይችላሉ። የሚያሳዝነው፣ አንዳንድ ቤተሰቦች በገንዘብና ባለጸጋ ለመሆን ወይም ደግሞ ቢያንስ ቢያንስ ተጨማሪ ቁሳዊ ነገሮች ለማግኘት በመፈለግ የተነሳ በሚፈጠሩ ጭቅጭቆች ታምሰዋል። ሁለቱም የትዳር ጓደኛሞች ሰብዓዊ ሥራ ሲይዙና “በገዛ ገንዘቤ” መባባል ሲጀምሩ መከፋፈል ሊፈጠር ይችላል። ሁለቱም የትዳር ጓደኛሞች ሥራ በሚይዙበት ጊዜ ጭቅጭቅ ባይኖር እንኳን አብረው የሚያሳልፉት ጊዜ ሊያጡ ይችላሉ። በአሁኑ ጊዜ አባቶች እቤት ሆነው ሊያገኙ ከሚችሉት የበለጠ ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ለረጅም ጊዜ፣ ለወራት አልፎ ተርፎም ለዓመታት ከቤተሰባቸው ርቀው የሚሠሩበት ሁኔታ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተስፋፋ መጥቷል። ይህ በጣም የከፉ ችግሮች ሊያስከትል ይችላል።

27. የገንዘብ ችግር ያለበትን ቤተሰብ ሊረዱ የሚችሉ አንዳንድ መሠረታዊ ሥርዓቶች ምንድን ናቸው?

27 የተለያዩ ቤተሰቦች ያሉባቸው ተጽዕኖዎችና የሚያስፈልጓቸው ነገሮች የተለያዩ ስለሚሆኑ እነዚህን ሁኔታዎች መቋቋም የሚቻልበትን መንገድ በተመለከተ ራሱን የቻለ ሕግ ማውጣት አይቻልም። ያም ሆኖ ግን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ሊጠቅም ይችላል። ለምሳሌ ያህል ‘አንድ ላይ ሆኖ በመማከር’ አላስፈላጊ የሆነን ትግል ማስቀረት እንደሚቻል ምሳሌ 13:​10 ይናገራል። ይህ የራስን አመለካከት መግለጽ ማለት ብቻ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ምክር መጠየቅና ሌላው ሰው ስለ ጉዳዩ ያለውን አመለካከት ማወቅ ይጠይቃል። በተጨማሪም ትክክለኛ የሆነ በጀት ማውጣት ቤተሰቡ የሚያደርገውን ጥረት ለማስተባበር ሊረዳ ይችላል። አንዳንድ ጊዜ፣ በተለይ ደግሞ ልጆች ወይም በቤተሰቡ ሥር የሚተዳደሩ ሌሎች ሰዎች ካሉ ተጨማሪ ወጪዎችን ለመሸፈን፣ ለተወሰነ ጊዜ ሊሆን ይችላል፣ ሁለቱም የትዳር ጓደኛሞች ሥራ መያዛቸው አስፈላጊ ነው። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ ባልየው በእንዲህ ዓይነቱ ወቅትም ቢሆን ከእሷ ጋር የሚያሳልፈው ጊዜ እንዳለው በመግለጽ ሚስቱን ሊያጽናናት ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ ብቻዋን የምታከናውናቸውን አንዳንድ ሥራዎች ከልጆቹ ጋር ሆኖ በመሥራት ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ሊረዳት ይችላል።​—⁠ፊልጵስዩስ 2:​1-4

28. አንድ ቤተሰብ የትኞቹን ማሳሰቢያዎች ሥራ ላይ ማዋሉ አንድነት እንዲያገኝ ሊረዳው ይችላል?

28 ይሁን እንጂ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ገንዘብ አስፈላጊ ነገር ቢሆንም እንኳ ደስታ እንደማያመጣ መዘንጋት የለባችሁም። ሕይወት ሊያስገኝ አይችልም። (መክብብ 7:​12) እንዲያውም ቁሳዊ ነገሮችን ከሚገባው በላይ ከፍ አድርጎ መመልከት መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ ውድቀት ሊያስከትል ይችላል። (1 ጢሞቴዎስ 6:​9-12) ይሖዋ ለሕይወት የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለማግኘት የምናደርገውን ጥረት የሚባርክልን በመሆኑ አስቀድመን የአምላክን መንግሥትና ጽድቁን መፈለጋችን ምንኛ የተሻለ ነው! (ማቴዎስ 6:​25-33፤ ዕብራውያን 13:​5) መንፈሳዊ ነገሮችን የምታስቀድሙና ከሁሉ በፊት ከአምላክ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖራችሁ የምትጥሩ ከሆነ ቤተሰባችሁ በአንዳንድ ሁኔታዎች የተከፋፈለ ቢሆን እንኳ ይበልጥ አስፈላጊ በሆኑት መንገዶች አንድነት ያለው ይሆናል።

የሚከተሉት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች . . . የቤተሰብ አባላት በቤታቸው ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ እንዲችሉ ሊረዷቸው የሚችሉት እንዴት ነው?

ክርስቲያኖች ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ ያዳብራሉ።​—⁠ምሳሌ 16:​21፤ 24:​3

አንድ ባልና ሚስት አንዳቸው ለሌላው ፍቅርና አክብሮት ማሳየት ያለባቸው አንድ ዓይነት ሃይማኖት ሲኖራቸው ብቻ አይደለም።​—⁠ኤፌሶን 5:​23, 25

አንድ ክርስቲያን የአምላክን ሕግ ሆን ብሎ አይጥስም።​—⁠ሥራ 5:​29

ክርስቲያኖች ሰላም ፈጣሪዎች ናቸው።​—⁠ሮሜ 12:​18

ለመቆጣት አትቸኩሉ።​—⁠መክብብ 7:​9

ትክክለኛ ጋብቻዎች ክብርና ሰላም ያስገኛሉ

በዘመናችን ብዙ ወንዶችና ሴቶች በሕግ ሳይጋቡ እንደ ባልና ሚስት ሆነው አንድ ላይ ይኖራሉ። አንድ አዲስ አማኝ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ያለ ሊሆን ይችላል። በአንዳንድ ሁኔታዎች ጥምረቱ በማኅበረሰቡ ወይም ደግሞ በጎሳው ልማድ ተቀባይነት ያገኘ ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም ሕጋዊ አይደለም። ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርት መሠረት አንድ ጋብቻ በትክክል ሕጋዊ እውቅና አግኝቶ የተመዘገበ መሆን አለበት። (ቲቶ 3:​1፤ ዕብራውያን 13:​4) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በጋብቻ መጣመር የሚችሉት አንድ ባልና አንዲት ሚስት ብቻ መሆናቸውን ይደነግጋል። (1 ቆሮንቶስ 7:​2፤ 1 ጢሞቴዎስ 3:​2, 12) በቤታችሁ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን በመጀመሪያ ከዚህ መሥፈርት ጋር መስማማት ይኖርባችኋል። (መዝሙር 119:​165) ይሖዋ ያወጣቸው ብቃቶች ተግባራዊ ሊሆኑ የማይችሉ ወይም ደግሞ ሸክም አይደሉም። ይሖዋ የሚያስተምረን የሚበጀንን ነገር ነው።​—⁠ኢሳይያስ 48:​17, 18

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ