ትምህርት 13
እውነተኛውን ሃይማኖት ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው?
አምላክን የሚያስደስተው አንድ ሃይማኖት ብቻ ነው ወይስ ሁሉም ሃይማኖቶች? (1)
ክርስቲያን ነን የሚሉ ብዙ ሃይማኖቶች የኖሩት ለምንድን ነው? (2)
እውነተኛ ክርስቲያኖችን ለይተህ ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው? (3-7)
1. ኢየሱስ ያቋቋመው አንድ እውነተኛ የክርስትና ሃይማኖት ብቻ ነበር። ስለዚህ በአሁኑ ጊዜም መኖር ያለበት የይሖዋ አምላክ እውነተኛ አምላኪዎችን ያቀፈ አንድ ቡድን ብቻ ነው። (ዮሐንስ 4:23, 24፤ ኤፌሶን 4:4, 5) መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ሕይወት በሚወስደው ጠባብ መንገድ ላይ የሚገኙት ጥቂት ሰዎች ብቻ እንደሆኑ ያስተምራል።—ማቴዎስ 7:13, 14
2. መጽሐፍ ቅዱስ ሐዋርያት ሞተው ካለቁ በኋላ የሐሰት ትምህርቶችና ክርስቲያናዊ ያልሆኑ ልማዶች ወደ ክርስቲያን ጉባኤ ቀስ በቀስ ሰርገው እንደሚገቡ ተንብዮ ነበር። አንዳንድ ሰዎች የክርስቶስ ሳይሆን የራሳቸው ተከታዮች እንዲሆኑ አማኞችን አባብለው ይወስዳሉ። (ማቴዎስ 7:15, 21-23፤ ሥራ 20:29, 30) ክርስቲያን ነን የሚሉ እጅግ ብዙ የተለያዩ ሃይማኖቶች የኖሩት በዚህ ምክንያት ነው። ታዲያ እውነተኞቹን ክርስቲያኖች እንዴት ለይተን ለማወቅ እንችላለን?
3. ዋነኛው የእውነተኛ ክርስቲያኖች መለያ ምልክት እውነተኛ ፍቅር በመካከላቸው መኖሩ ነው። (ዮሐንስ 13:34, 35) ሌላ ዘር ወይም የቆዳ ቀለም ካላቸው ሰዎች የተሻሉ እንደሆኑ እንዲሰማቸው የሚያደርግ ትምህርት አይሰጣቸውም። የሌላ አገር ሰዎችንም እንዲጠሉ የሚያደርግ ትምህርት አይማሩም። (ሥራ 10:34, 35) በዚህ ምክንያት በጦርነት አይካፈሉም። እውነተኛ ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው እንደ ወንድምና እህት ይተያያሉ።—1 ዮሐንስ 4:20, 21
4. ሌላው የእውነተኛ ሃይማኖት መለያ ምልክት አባሎቹ ለመጽሐፍ ቅዱስ የጠለቀ አክብሮት ያላቸው መሆኑ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን ይቀበላሉ፣ የሚናገረውንም ያምናሉ። (ዮሐንስ 17:17፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) የአምላክን ቃል ከሰዎች አስተሳሰብ ወይም ባሕል የላቀ ቦታ ይሰጡታል። (ማቴዎስ 15:1-3, 7-9) የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል በዕለታዊ ኑሯቸው ሥራ ላይ ለማዋል ይጥራሉ። ስለዚህ የሚሰብኩት ነገርና የሚያደርጉት ነገር አይጋጭም።—ቲቶ 1:15, 16
5. በተጨማሪም እውነተኛው ሃይማኖት የአምላክን ስም ማክበር ይኖርበታል። (ማቴዎስ 6:9) ኢየሱስ ይሖዋ የተባለውን የአምላክ ስም አሳውቆ ነበር። እውነተኛ ክርስቲያኖችም እንዲሁ ማድረግ ይኖርባቸዋል። (ዮሐንስ 17:6, 26፤ ሮሜ 10:13, 14) በምትኖርበት አካባቢ ለሰዎች ስለ አምላክ ስም የሚናገሩት እነማን ናቸው?
6. እውነተኛ ክርስቲያኖች ስለ አምላክ መንግሥት መስበክ አለባቸው። ኢየሱስ ይህን አድርጓል። አዘውትሮ ስለ መንግሥቱ ይናገር ነበር። (ሉቃስ 8:1) ደቀ መዛሙርቱም ይህንኑ መልእክት በመላው ምድር እንዲሰብኩ አዟል። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) እውነተኛ ክርስቲያኖች ለዚህች ምድር እውነተኛ ሰላምና ደህንነት የሚያመጣው የአምላክ መንግሥት ብቻ እንደሆነ ያምናሉ።—መዝሙር 146:3-5
7. የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የዚህ ክፉ ዓለም ክፍል መሆን የለባቸውም። (ዮሐንስ 17:16) በዓለም የፖለቲካ ጉዳዮችና ማኅበራዊ ውዝግቦች አይካፈሉም። በዓለም ውስጥ ተስፋፍተው ከሚገኙ ጎጂ ባሕርያት፣ ድርጊቶችና ዝንባሌዎች ይርቃሉ። (ያዕቆብ 1:27፤ 4:4) በምትኖርበት አካባቢ እነዚህ የእውነተኛ ክርስትና መለያ ምልክቶች የሚታዩበት ሃይማኖታዊ ቡድን አለን?
[በገጽ 26 እና 27 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
እውነተኛ ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው ይዋደዳሉ፣ ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት አላቸው፣ ስለ አምላክ መንግሥትም ይሰብካሉ