የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • be ጥናት 5 ገጽ 97-ገጽ 100 አን. 3
  • በተገቢው ቦታ ቆም ማለት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በተገቢው ቦታ ቆም ማለት
  • በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የድምፅ መጠንና ቆም እያሉ መናገር
    ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ
  • ጥርት ያለ ንባብ
    በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • ‘ለሕዝብ ለማንበብ መትጋት’
    ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ
  • ምክር ይገነባል
    ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ
ለተጨማሪ መረጃ
በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
be ጥናት 5 ገጽ 97-ገጽ 100 አን. 3

ጥናት 5

በተገቢው ቦታ ቆም ማለት

ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

በንግግርህ መሃል በተገቢ ቦታዎች ላይ ቆም በል። አንዳንዴ ለአጭር ጊዜ ቆም ትል ወይም ድምፅህን ለጊዜው ብቻ በጣም ዝቅ ታደርግ ይሆናል። በተገቢው ቦታ ላይ ቆም ብለሃል ሊባል የሚችለው በዓላማ ካደረግኸው ብቻ ነው።

አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

በተገቢው ቦታ ላይ ቆም ማለት አድማጮች ንግግሩን በቀላሉ እንዲረዱት በማድረግ ረገድ ትልቅ ድርሻ አለው። ከዚህም በተጨማሪ ዋና ዋናዎቹ ነጥቦች እንዲጎሉ ያደርጋል።

በንግግር መካከል በትክክለኛው ቦታ ላይ ቆም ማለት በጣም አስፈላጊ ነው። ንግግር ስታቀርብም ይሁን በተናጠል ከሰዎች ጋር ስትወያይ በተገቢው ቦታ ቆም እያልክ መናገርህ ጠቃሚ ነው። በዚህ መልኩ ቆም የማትል ከሆነ የምትናገረው ነገር አንድ ግልጽ የሆነ መልእክት የሚያስተላልፍ መሆኑ ይቀርና እንዲሁ ቃላትን የምታነበንብ ሊመስል ይችላል። በአንጻሩ ግን ይህንን ማድረግህ ንግግርህ ግልጽ እንዲሆን ይረዳል። ከዚህም በላይ ዋና ዋና ነጥቦችህ በአድማጮች አእምሮ ውስጥ እንዲቀረጹ ሊያደርግ ይችላል።

መቼ ቆም ማለት እንዳለብህ እንዴት ማወቅ ትችላለህ? ደግሞስ ርዝማኔው ምን ያህል መሆን አለበት?

ሐሳቡን በትክክል ለማስተላለፍ ቆም ማለት። ሥርዓተ ነጥብ የጽሑፍ ቋንቋ አቢይ ክፍል ነው። የአንድን ሐሳብ ወይም ጥያቄ መጨረሻ ሊጠቁም ይችላል። በአንዳንድ ቋንቋዎች ደግሞ ከሌላ ምንጭ የተጠቀሱ ሐሳቦችን ለመለየት ያገለግላል። አንዳንድ ሥርዓተ ነጥቦች አንዱ የዓረፍተ ነገር ክፍል ከሌላው ጋር ያለውን ዝምድና ያመለክታሉ። ሰውዬው ለራሱ እያነበበ ከሆነ ሥርዓተ ነጥቦቹን ያያቸዋል። ይሁን እንጂ ለሌሎች በሚያነብበት ጊዜ በጽሑፉ ላይ ያሉትን ሥርዓተ ነጥቦች ትርጉም በድምፁ ቃና ማንጸባረቅ ይኖርበታል። (ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት “ጥርት ያለ ንባብ” የሚለውን ጥናት ቁጥር 1 ተመልከት።) ሥርዓተ ነጥቡ ቆም ማለትን የሚጠይቅ ሆኖ እያለ ቆም ሳትል ከቀረህ ሌሎች ሰዎች ያነበብኸውን ነገር መረዳት ሊቸግራቸው አልፎ ተርፎም የጽሑፉ መልእክት ሊዛባ ይችላል።

ከሥርዓተ ነጥብ በተጨማሪ በአንድ ዓረፍተ ነገር ውስጥ ሐሳቦቹ የገቡበት መንገድም የት ቦታ ቆም ማለት ተገቢ እንደሚሆን በመጠቆም ረገድ የራሱ ድርሻ አለው። በአንድ ወቅት አንድ ታዋቂ ሙዚቀኛ እንዲህ ብሏል:- “እኔ ኖታውን ከሌሎች ፒያኖ ተጫዋቾች የተለየ አድርጌ ተጫውቼው አይደለም። ምሥጢሩ ያለው በኖታዎቹ መካከል እንዴትና መቼ ቆም ማለት እንዳለብህ ማወቁ ላይ ነው።” በንግግርም ቢሆን ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። በተገቢው ቦታ ቆም ማለት ጥሩ አድርገህ ለተዘጋጀኸው ትምህርት ውበትና ለዛ ይጨምርለታል።

ለሌሎች ለማንበብ ስትዘጋጅ በጽሑፉ ላይ ምልክት ማድረጉን ጠቃሚ ሆኖ ታገኘው ይሆናል። ትንሽ ቆም የምትልበት ቦታ ላይ አንድ የቁም ሰረዝ አድርግ። ረዘም ላለ ጊዜ ቆም የምትልበት ቦታ ላይ ደግሞ ሁለት የተጠጋጉ የቁም ሰረዞችን ተጠቀም። በትክክል ለማንበብ የምትቸገርበት ቦታ ካለና በተደጋጋሚ ጊዜ ያለ ቦታው ቆም የምትል ከሆነ ያስቸገረህ ሐረግ ውስጥ ያሉትን አብረው የሚነበቡ ቃላት ለማያያዝ በእርሳስ ምልክት አድርግባቸው። ከዚያም ሐረጉን ሙሉ በሙሉ አንብበው። ብዙ ልምድ ያላቸው ተናጋሪዎችም የሚጠቀሙበት ዘዴ ይኸው ነው።

በዕለት ተዕለት ውይይቶች ወቅት ምን ማለት እንደምትፈልግ ስለምታውቅ ብዙውን ጊዜ ቆም በማለት ረገድ ችግር አይኖርብህም። ይሁን እንጂ ሐሳቡ የት ቦታ ላይ ቆም ማለት እንደሚጠይቅ ግምት ውስጥ ሳታስገባ እንዲሁ በልማድ በየቦታው ቆም የምትል ከሆነ የንግግርህ ኃይል ይዳከማል እንዲሁም መልእክቱ ይሸፈናል። “ቅልጥፍና” በሚለው ጥናት 4 ውስጥ በዚህ ረገድ ማሻሻያ ለማድረግ የሚረዱ ሐሳቦች ተሰጥተዋል።

የሐሳብ ለውጥ ለማድረግ ቆም ማለት። ከአንዱ ዋና ነጥብ ወደ ሌላው በምትሸጋገርበት ጊዜ ቆም ማለትህ አድማጮችህ መለስ ብለው የሚያስቡበት፣ ራሳቸውን ከነጥቡ ጋር የሚያስተያዩበት፣ ውይይቱ ወደ የት አቅጣጫ እያመራ እንዳለ የሚያብላሉበት እንዲሁም ቀጣዩን ነጥብ በግልጽ መጨበጥ የሚችሉበት ፋታ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። መኪና በምታሽከረክርበት ጊዜ አንድ መንገድ ይዘህ ስትጓዝ ቆይተህ ወደ ሌላ መንገድ ስትታጠፍ ፍጥነትህን መቀነስ እንደሚያስፈልግህ ሁሉ ከአንዱ ሐሳብ ወደ ሌላው ስትሻገርም ቆም ማለት አስፈላጊ ነው።

አንዳንድ ተናጋሪዎች ያለ ፋታ ከአንዱ ሐሳብ ወደ ሌላው የሚሸጋገሩበት አንዱ ምክንያት በንግግራቸው ብዙ ነጥቦችን ለማካተት ስለሚሞክሩ ነው። አንዳንዶቹ ደግሞ የዕለት ተዕለት ውይይታቸውም ከዚህ የተለየ ስላልሆነ ነው። ምናልባት በቅርብ የሚያገኟቸው ሰዎችም አነጋገር ተመሳሳይ ሊሆን ይችላል። ይህ ግን ውጤታማ አስተማሪ ለመሆን አይበጅም። አድማጮች ሊሰሙት ደግሞም ሊያስታውሱ ይገባል የምትለውን ነጥብ ስትናገር መልእክቱ ግልጽ እንዲሆንላቸው ጊዜ መስጠት ያስፈልግሃል። ንግግሩ ግልጽ እንዲሆን ቆም ማለት የግድ አስፈላጊ መሆኑን አትዘንጋ።

ንግግርህን የምታቀርበው አስተዋጽኦ ይዘህ ከሆነ በዋና ዋና ነጥቦች መካከል የት ቦታ ላይ ቆም ማለት እንደምትችል በግልጽ በሚያሳይ መንገድ የተዋቀረ መሆን አለበት። በንባብ የሚቀርብ ጽሑፍ ከሆነ ከአንዱ ዋና ነጥብ ወደሌላው በሚሸጋገርበት ቦታ ላይ ምልክት አድርግ።

የሐሳብ ለውጥ ለማድረግ ሲባል ቆም የምትልበት የጊዜ መጠን ሥርዓተ ነጥብ ላይ ቆም ከምትልበት ጊዜ ይበልጥ ረዘም ይላል። ይሁን እንጂ ንግግርህ እስኪንዛዛ ድረስ መሆን የለበትም። ረዘም ላለ ጊዜ ቆም የምትል ከሆነ ጥሩ ዝግጅት እንዳላደረግህና ቀጥሎ ምን ማለት እንዳለብህ የምታስብ ሊያስመስልብህ ይችላል።

ለማጥበቅ ሲባል ቆም ማለት። ብዙውን ጊዜ ማጥበቅ የፈለግኸውን ሐሳብ ወይም ጥያቄ ረገጥ አድርገህ ከተናገርህ ወይም ካነበብህ በኋላ ቆም ማለት የአድማጮችን አእምሮ ያነቃል። እንዲህ ማድረግ አድማጮች በተነገረው ነገር ላይ እንዲያሰላስሉ አጋጣሚ ይሰጣቸዋል ወይም ከዚያ ቀጥሎ የሚነገረውን ነገር በጉጉት እንዲጠብቁ ያነሳሳቸዋል። ሁለቱ ተመሳሳይ ነገሮች አይደሉም። ስለዚህ የትኛውን ዘዴ ብትጠቀም የተሻለ እንደሚሆን ወስን። ይሁንና ለማጉላት ብሎ ቆም የማለት ዘዴ ሊሠራበት የሚገባው አስፈላጊ ለሆኑ ነጥቦች ብቻ እንደሆነ ማስታወስ ይኖርብሃል። አለበለዚያ እነዚህ ነጥቦች ይደበቃሉ።

ኢየሱስ ናዝሬት በሚገኘው ምኩራብ ድምፁን ከፍ አድርጎ ቅዱሳን ጽሑፎችን ባነበበበት ወቅት ቆም የማለትን ዘዴ ጥሩ አድርጎ ተጠቅሞበታል። በመጀመሪያ ከነቢዩ ኢሳይያስ ጥቅልል ስለ እርሱ የተጻፈውን አነበበ። ይሁን እንጂ የጥቅሱን ተግባራዊ ገጽታ ከማብራራቱ በፊት ጥቅልሉን እንደነበረ መልሶ ለአገልጋዩ ሰጠና ተቀመጠ። ከዚያም በምኩራብ ያሉት ሰዎች ሁሉ ዓይን በእርሱ ላይ ባረፈ ጊዜ “ዛሬ ይህ መጽሐፍ በጆሮአችሁ ተፈጸመ” አላቸው።​—⁠ሉቃስ 4:​16-21

በሁኔታዎች አስገዳጅነት ቆም ማለት። አልፎ አልፎ ንግግርህን የሚረብሹ ነገሮች ቆም እንድትል ያደርጉህ ይሆናል። በአካባቢው የሚያልፍ ተሽከርካሪ ድምፅ ወይም የሚያለቅስ ሕፃን አገልግሎት ላይ ካገኘኸው ሰው ጋር የምታደርገውን ውይይት ለትንሽ ጊዜ እንድታቋርጥ ያስገድድህ ይሆናል። በስብሰባ ቦታ የሚረብሽ ድምፅ ቢፈጠር ለመደማመጥ የሚያስቸግር እስካልሆነ ድረስ ድምፅህን ከፍ አድርገህ መቀጠል ትችል ይሆናል። ይሁን እንጂ የሚረብሸው ድምፅ ከፍተኛና ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆይ ከሆነ ቆም ማለት ይኖርብሃል። በመሠረቱ መናገርህን ብትቀጥልም አድማጮች ሊያዳምጡህ አይችሉም። እንግዲያው አድማጮችህ ከምትነግራቸው መልካም ነገር ሙሉ ጥቅም እንዲያገኙ ስትል ቆም እያሉ የመናገርን ዘዴ ጥሩ አድርገህ ተጠቀምበት።

የሌሎችን ሐሳብ ለመስማት ቆም ማለት። የምታቀርበው ንግግር መደበኛ በሆነ መንገድ ተሳትፎ ማድረግን የሚጠይቅ ባይሆንም አድማጮች ለራሳቸው መልስ እንዲሰጡ ማድረግ አስፈላጊ ነው። አድማጮችህ እንዲያስቡ የሚያደርግ ጥያቄ ካነሳህ በኋላ በደንብ ቆም ብለህ ጊዜ ካልሰጠሃቸው ጥያቄዎችህ እምብዛም ዋጋ አይኖራቸውም።

እርግጥ ከመድረክ ንግግር ስትሰጥ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ሰዎች ስትመሠክርም ቆም ማለት ያስፈልግሃል። አንዳንድ ሰዎች ሲናገሩ ፋታ አይሰጡም። አንተም ተመሳሳይ ችግር ካለብህ ይህንን የንግግር ባሕርይ ለማዳበር ልባዊ ጥረት አድርግ። ይህ የንግግር ባሕርይ ከሌሎች ጋር ያለህን የሐሳብ ግንኙነት የሚያሻሽልልህ ከመሆኑም ሌላ በመስክ አገልግሎት ያለህን ውጤታማነት ለማሳደግ ይረዳሃል። በንግግር መሃል ቆም ማለት የዓረፍተ ነገሩን መልእክት በትክክል ለማስተላለፍ፣ ነጥቡን ለማጉላት፣ የአድማጮችን ትኩረት ለማግኘትና ነቃ ብለው እንዲያዳምጡ ለማድረግ ይረዳል መባሉ ተገቢ ነው።

ዕለት ተዕለት ከሰዎች ጋር በምናደርገው ውይይት ሐሳባችንን እንገልጻለን፤ የእነርሱንም ሐሳብ እናዳምጣለን። እነርሱ ሲናገሩ የምታዳምጥና የሚሉትን ነገር በትኩረት የምትከታተል ከሆነ እነርሱም አንተን ለማዳመጥ ይገፋፋሉ። ይህም ሐሳባቸውን እንዲገልጹ ፋታ መስጠትን ይጠይቅብሃል።

ብዙውን ጊዜ አገልግሎታችን ይበልጥ ውጤታማ የሚሆነው እኛ ብቻ ከመናገር ይልቅ እነርሱም ሐሳብ እንዲሰጡ ስናደርግ ነው። ብዙ ምሥክሮች ከሰላምታ ልውውጡ በኋላ ርዕሰ ጉዳያቸውን አስተዋውቀው አንድ ጥያቄ ማንሳቱን ውጤታማ ሆኖ አግኝተውታል። የሚያነጋግሩት ሰው ሐሳቡን እንዲገልጽ ፋታ ለመስጠት ቆም ካሉ በኋላ ምን ማለት እንደፈለገ መረዳታቸውን ይገልጻሉ። በውይይቱ ወቅት በየመሃሉ ሐሳቡን የሚገልጽበት አጋጣሚ ይሰጡታል። ግለሰቡ እየተወያዩበት ስላለው ርዕሰ ጉዳይ ምን ዓይነት አመለካከት እንዳለው ከገባቸው በተሻለ መንገድ መርዳት እንደሚችሉ ያውቃሉ።​—⁠ምሳሌ 20:​5

እርግጥ ሁሉም ሰው ለምታነሳው ጥያቄ አዎንታዊ መልስ ይሰጣል ማለት አይደለም። ይሁንና ሰዎች አዎንታዊ መልስ ላይሰጡ ይችላሉ የሚለው ሐሳብ በኢየሱስ ላይ ተጽእኖ አልነበረውም። ኢየሱስ ተቃዋሚዎቹ እንኳ ሳይቀሩ ሐሳባቸውን እንዲገልጹ አጋጣሚ ሰጥቷቸዋል። (ማር. 3:​1-5) ግለሰቡ እንዲናገር አጋጣሚ መስጠት በጉዳዩ ላይ እንዲያስብበት ስለሚያደርገው በልቡ ያለውን አውጥቶ ሊነግረን ይችላል። እንዲያውም የአገልግሎታችን አንዱ ዓላማ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትንና ሰዎች በግለሰብ ደረጃ ውሳኔ ሊያደርጉባቸው የሚገቡትን ክብደት ያላቸው ጉዳዮች በማንሳት የታሰበበት ምላሽ እንዲሰጡ ማነሳሳት ነው።​—⁠ዕብ. 4:​12

በእርግጥም በአገልግሎት ከሰዎች ጋር ስንወያይ በተገቢው ቦታ ላይ ቆም እያልን መናገር ራሱን የቻለ ጥበብ ነው። ይህን የንግግር ባሕርይ በሚገባ ከሠራንበት የምናስተላልፈው ሐሳብ ግልጽ ከመሆኑም በተጨማሪ በአድማጫችን አእምሮ ውስጥ ይቀረጻል።

ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

  • ለሌሎች በምታነብበት ጊዜ ለሥርዓተ ነጥቦች ለየት ያለ ትኩረት ስጥ።

  • ጥሩ ችሎታ ያላቸውን ተናጋሪዎች በጥሞና በማዳመጥ የት ቦታ ላይና ለምን ያህል ጊዜ ቆም እንደሚሉ አስተውል።

  • አድማጮችህ እንዲያስታውሱት የምትፈልገውን ነገር ከተናገርህ በኋላ ነጥቡ በአእምሮአቸው እንዲቀረጽ ትንሽ ቆም በል።

  • ከሰዎች ጋር ስትወያይ ሐሳባቸውን እንዲገልጹ በመጋበዝ የሚሰጡትን መልስ አዳምጥ። አስጨርሳቸው። በመሃል አቋርጠህ አትግባ።

መልመጃ:- ማርቆስ 9:​1-13ን ድምፅህን ከፍ አድርገህ አንብብ። እያንዳንዱ ሥርዓተ ነጥብ ላይ ስትደርስ ለሥርዓተ ነጥቡ እንደሚስማማ ቆም እያልክ አንብብ። ንባብህ መንዛዛት የለበትም። ጥሩ አድርገህ ከተለማመድህ በኋላ አንድ ሰው ንባብህን እያዳመጠ ቆም በማለት ረገድ ማሻሻል የምትችልባቸውን ቦታዎች እንዲጠቁምህ አድርግ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ