ጥናት 9
ድምፅን መለዋወጥ
በአስፈላጊው ቦታ እያጠበቅህ መናገርህ አድማጮች የምትናገረውን ነገር በቀላሉ እንዲረዱ ያስችላቸዋል። የድምፅህን መጠን፣ ፍጥነትና ቃና በሚገባ እየለዋወጥህ መናገርህ ደግሞ ንግግሩ የበለጠ ጣዕምና ለዛ ያለው እንዲሆን ይረዳል። ከዚህም በላይ አድማጮች ስለ ትምህርቱ ያለህን ስሜት እንዲረዱ ያስችላል። ከመድረክ ስትናገርም ይሁን በመስክ አገልግሎት ካገኘኸው ሰው ጋር ስትወያይ አንተ ለትምህርቱ ያለህ ዝንባሌ በአድማጭህም ላይ ይንጸባረቃል።
የሰው ድምፅ በብዙ መንገድ ሊለዋወጥ የሚችል ድንቅ የተፈጥሮ ስጦታ ነው። በሚገባ ከተጠቀምንበት አንድን ንግግር ሕያው ሊያደርግ፣ የአድማጮችን ልብ ሊነካና ስሜታቸውን ሊቀሰቅስ እንዲሁም ለተግባር ሊያነሳሳቸው ይችላል። ይሁን እንጂ የት ቦታ ላይ ስትደርስ የድምፅህን መጠን እንደምትጨምር ወይም እንደምትቀንስ፣ ፍጥነትህን እንደምትለውጥ ወይም ቃናህን እንደምትቀይር ማስታወሻህ ላይ ምልክት ስላደረግህ ብቻ ይህን ግብ ማሳካት አትችልም። እንዲህ ባሉት ምልክቶች እየተመሩ ድምፅን ለመለዋወጥ መሞከር ውበት አይኖረውም። ንግግርህ ለዛ ያለውና ሕያው እንዲሆን ከማድረግ ይልቅ አድማጮችህ ዘና ብለው እንዳይከታተሉህ እንቅፋት ሊሆን ይችላል። ድምፅን እየለዋወጡ መናገር በግድ የሚመጣ የንግግር ባሕርይ አይደለም።
አንድ ተናጋሪ በጥሩ ሁኔታ ድምፁን እየለዋወጠ የሚናገር ከሆነ አድማጮቹ ትምህርቱን ተመስጠው ይከታተላሉ እንጂ ትኩረታቸው በእርሱ ላይ አይሆንም።
የድምፅህን መጠን እንደ ሁኔታው አስተካክል። የድምፅህን አወጣጥ ከምትለዋውጥባቸው መንገዶች አንዱ የድምፅህን መጠን እንደ ሁኔታው ማስተካከል ነው። ይህ ሲባል ግን አለፍ አለፍ እያሉ ድምፅን አንዴ ከፍ አንዴ ዝቅ ማድረግ ማለት አይደለም። እንደዚያ ማድረግህ የትምህርቱን መልእክት ያዛባል። አሁንም አሁንም ጮክ እያልክ የምትናገር ከሆነ በአድማጮችህ ላይ የሚያሳድረው ስሜት ጥሩ አይሆንም።
በንግግር ወቅት የምትጠቀምበት የድምፅ መጠን ለትምህርቱ የሚስማማ መሆን ይኖርበታል። በራእይ 14:6, 7 ወይም በራእይ 18:4 ላይ እንደሚገኘው ያለ አጣዳፊ ትእዛዝ ወይም በዘጸአት 14:13, 14 ላይ እንደሰፈረው ያለ ጠንካራ እምነት የተንጸባረቀበት ንግግር እያነበብህ ነው እንበል። እንደነዚህ ባሉት አጋጣሚዎች ድምፅህን በመጠኑ ከፍ አድርገህ መናገርህ ተገቢ ይሆናል። በተመሳሳይም በኤርምያስ 25:27-38 ላይ የሚገኘውን የመሰለ የውግዘት መልእክት በምታነብበት ጊዜ የድምፅህን መጠን መለዋወጥህ በጥቅሱ ውስጥ ያሉት አንዳንድ አገላለጾች ከሌሎቹ ይልቅ ጎልተው እንዲታዩ ያደርጋል።
በተጨማሪም የንግግርህን ዓላማ ግምት ውስጥ አስገባ። ዓላማህ አድማጮችህን ለተግባር ማነሳሳት ነው? ወይስ የትምህርቱ ዋና ነጥብ ጎልቶ እንዲታይ ማድረግ? በጥበብ ከተጠቀምህበት የድምፅህን መጠን ከፍ ማድረግህ ይህን ዓላማህን ለማሳካት ይረዳሃል። ሆኖም እንዲሁ መጮህ ዓላማህን ሊያከሽፍብህ ይችላል። ለምን? የምትናገረው ነገር ወዳጃዊ ስሜት ማንጸባረቅን እንጂ የድምፅ መጠን መጨመርን የሚጠይቅ ላይሆን ይችላል። ይህን በጥናት 11 ላይ እንመለከተዋለን።
በደንብ በታሰበበት መንገድ ድምፅን ዝቅ ማድረግ አድማጮች ቀጥሎ የምትናገረውን ነገር በጉጉት እንዲጠባበቁ ሊያነሳሳቸው ይችላል። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ ወዲያው ድምፅህን ጋል ማድረግ ይኖርብሃል። ዝቅ ባለ ድምፅ ረገጥ አድርጎ መናገር ስጋትን ወይም ፍርሃትን ለመግለጽ ሊያገለግል ይችላል። በተጨማሪም በዙሪያው ካለው ሐሳብ አንጻር ሲታይ ሁለተኛ ደረጃ የሚሰጠውን ነጥብ ለመግለጽ ድምፅን ዝቅ አድርጎ መናገር ይቻላል። ንግግሩ ተጀምሮ እስኪያልቅ ዝቅ ባለ ድምፅ የምትናገር ከሆነ ግን በምትናገረው ነገር እርግጠኛ እንዳልሆንክ ወይም ርዕሰ ጉዳዩ ብዙም ያልማረከህ ሊያስመስል ይችላል። ከዚህ በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ለስለስ ያለ የድምፅ ቃና ስትጠቀም ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ ሊኖርህ ይገባል።
ፍጥነትህን መለዋወጥ። በዕለት ተዕለት ንግግራችን ብዙም ሳንጨነቅ የምንፈልገውን መልእክት ማስተላለፍ እንችላለን። ልዩ ስሜት ስላሳደረብን ነገር ስንናገር ፍጥነት ይኖረናል። የምንናገረውን ነገር ሰዎች በትክክል እንዲያስታውሱ በምንፈልግበት ጊዜ ግን የንግግራችን ፍጥነት ይቀንሳል።
ይሁን እንጂ ለመድረክ አዲስ የሆኑ ብዙ ተናጋሪዎች ፍጥነታቸውን አይለዋውጡም። ለምን? የሚናገሯቸው ቃላት በጥንቃቄ የተጠኑ ስለሆኑ ነው። ምናልባትም አንድ በአንድ ጽፈውት ይመጡ ይሆናል። ምንም እንኳ ንግግራቸውን ቀጥታ በንባብ መልክ ባያቀርቡትም በቃላቸው ሸምድደውት ሊሆን ይችላል። ከዚህ የተነሣ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ የንግግር ፍጥነታቸው አንድ ዓይነት ይሆናል። በአስተዋጽኦ የመጠቀም ልማድ ማዳበር ይህን ችግር ለማረም ይረዳል።
እያዘገመች ትሄድ የነበረች ድመት፣ ውሻ ስታይ ድንገት ተስፈንጥራ እንደምትሮጥ ሁሉ በድንገት የድምፅህን ፍጥነት አትጨምር። በተጨማሪም የምትናገራቸውን ቃላት አጥርቶ ለመስማት እስኪያስቸግር ድረስ መፍጠን አይኖርብህም።
በንግግር መሃል የተለያየ የድምፅ ፍጥነት ለመጠቀም ስትል ብቻ አለፍ አለፍ እያልህ መፍጠንና ዝግ ማለት አይኖርብህም። እንዲህ ዓይነቱ አቀራረብ ትምህርቱን ይበልጥ ማራኪ ከማድረግ ይልቅ አድማጮች በትኩረት እንዳይከታተሉ እንቅፋት ሊሆን ይችላል። የፍጥነትህን ሁኔታ የሚወስነው የምትናገረው ነገር፣ ልታስተላልፍ የፈለግኸው ስሜትና የተነሳህበት ዓላማ ነው። ንግግርህን በተመጠነ ፍጥነት አቅርብ። በዕለት ተዕለት ንግግርህ እንደምታደርገው ልዩ ስሜት ስላሳደረብህ ነገር ስትናገር ፍጥነትህን ጨመር አድርግ። በተጨማሪም በንግግርህ ውስጥ ብዙም ጉልህ ስፍራ የሌላቸውን ነጥቦች ስትጠቅስ ወይም በጣም አስፈላጊ ያልሆኑ ዝርዝር ጉዳዮች ያሉበትን ታሪክ ስትተርክ ተመሳሳይ ዘዴ መጠቀምህ ተገቢ ይሆናል። ይህም ንግግርህ አንድ ዓይነት አቀራረብ ያለውና ድርቅ ያለ እንዳይሆን ይረዳል። በሌላ በኩል ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ አሳማኝ ነጥቦች፣ ዋና ዋና ነጥቦችና የመደምደሚያ ሐሳቦች ላይ ስትደርስ ፍጥነትህን ዝቅ ማድረግህ ተገቢ ይሆናል።
የድምፅህን ቃና መለዋወጥ። የሙዚቃ መሣሪያ የሚጫወት አንድ ሰው አለ እንበል። አንዳንድ ጊዜ ጮክ፣ አንዳንድ ጊዜ ዝቅ፣ አንዳንድ ጊዜ ፈጠን፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ዝግ እያደረገ ለአንድ ሰዓት ወይም ከዚያ ለሚበልጥ ጊዜ አንድ ዓይነት ድምፅ ብቻ ይጫወታል። እንዲህ ዓይነቱ ‘ሙዚቃ’ ስሜት አይማርክም። በተመሳሳይም ስንናገር ድምፃችን ሁልጊዜ አንድ ዓይነት ከሆነ ንግግራችን ለጆሮ ብዙም የሚጥም አይሆንም።
የድምፅ ቃና ለውጥ በሁሉም ቋንቋዎች አንድ ዓይነት ውጤት እንደማይኖረው ልብ ማለት ይገባል። እንደ ቻይና ባሉ አንዳንድ ቋንቋዎች የቃና ለውጥ የትርጉም ለውጥ ሊያስከትል ይችላል።
የቃና ለውጥ የትርጉም ለውጥ በማያስከትልባቸው ቋንቋዎችም የድምፅን ቃና መለዋወጥ የተለያየ መልእክት ሊያስተላልፍ ይችላል። ለምሳሌ ቃሉን ረዘም አድርጎ በመጥራትና ከዚሁ ጋር በሚመጣጠን ሁኔታ የድምፅን መጠን በመጨመር መልእክቱን ማጥበቅ ይቻላል። በሌላ በኩል ደግሞ የቃና ለውጥ መጠንን ወይም ርቀትን ሊያመለክት ይችላል። በአንድ ዓረፍተ ነገር መጨረሻ ላይ የድምፅን ቃና መቀየር ጥያቄን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።
የደስታ ስሜትና ግለት ከፍ ባለ የድምፅ ቃና ሊገለጽ ይችላል። ሐዘንና ፍርሃትን ለመግለጽ ደግሞ ለስለስ ያለ የድምፅ ቃና ሊያስፈልግ ይችላል። እዚህ ላይ የተጠቀሱት ስሜቶች አንድ ተናጋሪ የሰዎችን ልብ መንካት እንዲችል የሚረዱ ናቸው። እነዚህን ስሜቶች ለማንጸባረቅ በምትፈልግበት ጊዜ እንዲሁ ቃሎቹን በመጥራት ብቻ መወሰን የለብህም። አንተ ራስህ ያለህ ስሜት በድምፅህ ሊንጸባረቅ ይገባል።
መሠረት መጣል። ታዲያ ድምፅን ለመለዋወጥ መሠረት የሚጣለው መቼ ነው? የምታቀርባቸውን ነጥቦች ስትመርጥ ነው። ንግግርህ በሙሉ በማሳመኛ ነጥቦች ወይም በምክር ብቻ የተሞላ ከሆነ ድምፅህን ለመለዋወጥ የሚያስችል ብዙ አጋጣሚ አይኖርህም። ስለዚህ አስተዋጽኦህን በመመርመር ንግግርህ ሕያውና ግንዛቤ የሚያሰፋ እንዲሆን የሚያስችሉ ነጥቦች የተካተቱበት መሆኑን አረጋግጥ።
በንግግርህ መሐል አቀራረብህ የሚያሰለች እንደሆነ ተሰምቶህ ለውጥ ማድረግ ፈለግህ እንበል። በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ ትችላለህ? የትምህርትህን አቀራረብ ለውጥ። እንዴት? አንዱ ዘዴ እንዲሁ ከመናገር ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስህን ገልጠህ አድማጮችህም መጽሐፍ ቅዱሳቸውን እንዲያወጡና አብረውህ ጥቅስ እንዲያነቡ መጋበዝ ነው። ወይም ደግሞ አንዳንዱን ዓረፍተ ነገር በጥያቄ መልክ በማቅረብና ቆም በማለት አድማጮች በጉዳዩ ላይ እንዲያስቡ አድርግ። ቀለል ያሉ ምሳሌዎችንም ልትጠቀም ትችላለህ። ይህ ልምድ ያላቸው ተናጋሪዎች የሚጠቀሙበት ዘዴ ነው። ብዙ ልምድ ኖረህም አልኖረህ የንግግርህን ነጥቦች በምታዘጋጅበት ጊዜ በእነዚሁ ዘዴዎች ልትጠቀም ትችላለህ።
ድምፅን መለዋወጥ ለአንድ ንግግር ቅመም ነው ሊባል ይችላል። ትክክለኛው ቅመም በተገቢው መጠን ከተጨመረ አንድ ምግብ ጥሩ ጣዕም እንደሚኖረው ሁሉ ድምፅን በተገቢው መንገድ መለዋወጥም ለትምህርቱ ጣዕም ከመጨመሩም ሌላ አድማጮች ደስ ብሏቸው እንዲያዳምጡ ይረዳል።