የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • be ጥናት 12 ገጽ 121-ገጽ 123 አን. 2
  • አካላዊ መግለጫዎች

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • አካላዊ መግለጫዎች
  • በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • መደጋገምና የሰውነት እንቅስቃሴዎች
    ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ
  • በጋለ ስሜት መናገር
    ለማንበብ እና ለማስተማር የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ
  • በጭውውት መልክ መናገር
    ለማንበብ እና ለማስተማር የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ
  • ወዳጃዊ ስሜትና አሳቢነት ማሳየት
    ለማንበብ እና ለማስተማር የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ
ለተጨማሪ መረጃ
በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
be ጥናት 12 ገጽ 121-ገጽ 123 አን. 2

ጥናት 12

አካላዊ መግለጫዎች

ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

የእጅህን፣ የትከሻህን ወይም የመላ አካልህን እንቅስቃሴ ተጠቅመህ ሐሳብህን፣ ስሜትህን ወይም አመለካከትህን ግለጽ።

ምትናገረው ነገር ይበልጥ ኃይል እንዲኖረውና ስሜትህን መግለጽ እንድትችል የዓይንህን፣ የአፍህን እንዲሁም የጭንቅላትህን እንቅስቃሴ ሳይቀር ተጠቀም።

አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

አካላዊ መግለጫ ንግግርህን ለማጠናከርና ይበልጥ ሕያው ለማድረግ ይረዳል። ይበልጥ በስሜት እንድትናገር ሊያነሳሳህ ስለሚችል ድምፅህ ጭምር ስሜትህን የሚገልጽ ይሆናል።

በአንዳንድ ባሕሎች ሰዎች ሲያወሩ አካላዊ መግለጫዎችን እንደ ልብ ይጠቀማሉ። በሌሎች ባሕሎች ደግሞ ሁኔታው እንደዚያ ላይሆን ይችላል። ይሁንና ሁሉም ሰው ለማለት ይቻላል ከአንድ ግለሰብ ጋር ሲወያይም ይሁን ንግግር ሲሰጥ ፊቱ ላይ ከሚነበበው ስሜት በተጨማሪ አንዳንድ አካላዊ መግለጫዎችን መጠቀሙ አይቀርም።

ኢየሱስም ሆነ ደቀ መዛሙርቱ አካላዊ መግለጫዎችን ይጠቀሙ ነበር። በአንድ ወቅት አንድ ሰው እናትህና ወንድሞችህ ሊያነጋግሩህ ይፈልጋሉ የሚል መልእክት ይዞ ወደ ኢየሱስ መጣ። ኢየሱስም “እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?” ሲል ከጠየቀ በኋላ ‘እጁንም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዘርግቶ:- እነሆ እናቴና ወንድሞቼ’ በማለት እንደተናገረ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (ማቴ. 12:​48, 49) ከሌሎች ቦታዎች በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ በሥራ 12:​17 እና 13:​16 ላይ ሐዋርያው ጴጥሮስም ሆነ ሐዋርያው ጳውሎስ አካላዊ መግለጫ እንደተጠቀሙ ይጠቁማል።

ሐሳብንና ስሜትን መግለጽ የሚቻለው በድምፅ ብቻ ሳይሆን አካላዊ መግለጫዎችን በመጠቀም ጭምር ነው። አንድ ተናጋሪ አካላዊ መግለጫዎችን በሚገባ ሳይጠቀም ከቀረ ለንግግሩ ብዙም ትኩረት እንዳልሰጠ ሊያስመስልበት ይችላል። ይሁን እንጂ አካላዊ መግለጫዎችን ጥሩ አድርጎ መጠቀም ንግግሩ የተዋጣለት እንዲሆን ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። ሌላው ቀርቶ በስልክ እንኳ ስትነጋገር እንደ አስፈላጊነቱ አካላዊ መግለጫዎችን የምትጠቀም ከሆነ መልእክትህ ምን ያህል ክብደት እንዳለውና አንተ ራስህ ስለ ጉዳዩ ምን እንደሚሰማህ ከድምፅህ በቀላሉ መረዳት ይቻላል። እንግዲያው በቃልህ ስትናገርም ይሁን ከጽሑፍ ስታነብብ ወይም አድማጮች ቀና ብለው እያዩህም ይሁን መጽሐፍ ቅዱሳቸውን እያነበቡ በማንኛውም ጊዜ አካላዊ መግለጫዎችን መጠቀምህ በጣም አስፈላጊ ነው።

የምትጠቀምባቸው አካላዊ መግለጫዎች ከመጽሐፍ የተጠኑ መሆን የለባቸውም። ሳቅን ወይም ቁጣን ከሌላ ሰው አልተማርክም። አካላዊ መግለጫዎች በውስጥህ ያለውን ስሜት የሚያንጸባርቁ መሆን አለባቸው። እነዚህ መግለጫዎች ብዙ ሳትጨነቅ በራሳቸው የሚመጡ ከሆነ ይበልጥ የተሻለ ይሆናል።

አካላዊ መግለጫዎች በጥቅሉ በሁለት ይከፈላሉ። እነርሱም ገላጭና ማጠናከሪያ ይባላሉ። ገላጭ የሚባሉት አንድን ድርጊት የሚገልጹ ወይም መጠንና አቅጣጫን የሚጠቁሙ ናቸው። በትምህርት ቤቱ ውስጥ አካላዊ መግለጫዎች በሚለው ነጥብ በምትሠራበት ጊዜ አንድ ወይም ሁለት አካላዊ መግለጫ በማሳየትህ ብቻ መርካት የለብህም። ንግግርህ ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ ብዙም ሳትጨነቅ አካላዊ መግለጫዎችን ለማሳየት ሞክር። ይህንን ማድረግ የሚያስቸግርህ ከሆነ አቅጣጫን፣ ርቀትን፣ መጠንን፣ ቦታን ወይም አቀማመጥን ለሚያመለክቱ ቃላት ትኩረት መስጠቱን ጠቃሚ ሆኖ ታገኘው ይሆናል። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ ሌሎች ስለ አንተ የሚኖራቸውን ግምት እያሰብህ ከመጨነቅ ይልቅ በትምህርቱ መመሰጥና ንግግርህም ሆነ እንቅስቃሴህ እንደወትሮህ እንዲሆን ማድረግህ አስፈላጊ ነው። አንድ ሰው ዘና ብሎ የሚናገር ከሆነ አካላዊ መግለጫዎችን ለማሳየት አይቸገርም።

ማጠናከሪያ የሚባሉት አካላዊ መግለጫዎች የተናጋሪውን ስሜትና ጽኑ እምነት የሚያንጸባርቁ ናቸው። መልእክቱን ለማጉላት፣ ሕያው ለማድረግና ይበልጥ ለማጠናከር ያገለግላሉ። ማጠናከሪያ አካላዊ መግለጫዎች በጣም አስፈላጊ ናቸው። ይሁን እንጂ ካልተጠነቀቅህ አጉል ልማድ ሊሆኑብህም ይችላሉ። አንድ ዓይነት አካላዊ መግለጫ ደግመህ ደጋግመህ የምትጠቀም ከሆነ ንግግርህን የሚያጠናክር መሆኑ ይቀርና የአድማጮችን ትኩረት ወደ አንተ የሚስብ ይሆናል። የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች በዚህ ረገድ ችግር እንዳለብህ ከጠቆመህ ለተወሰነ ጊዜ ገላጭ የሆኑትን አካላዊ መግለጫዎች ብቻ ለመጠቀም ሞክር። ከጊዜ በኋላ ማጠናከሪያ አካላዊ መግለጫዎችን እንደገና መጠቀም ልትጀምር ትችላለህ።

ማጠናከሪያ አካላዊ መግለጫዎችን ምን ያህል መጠቀም እንዳለብህና የትኞቹን ብትጠቀም የተሻለ እንደሚሆን ለመወሰን የሚያዳምጡህን ሰዎች ስሜት ከግምት ውስጥ አስገባ። ጣትህን ብትቀስርባቸው ልታሸማቅቃቸው ትችላለህ። በአንዳንድ ባሕሎች አንድ ወንድ መገረሙን ለማሳየት አፉን በእጁ እንደ መያዝ የመሳሰሉ አካላዊ መግለጫዎችን ቢጠቀም እንደ ሴት እንደተቅለሰለሰ ሊቆጠርበት ይችላል። በአንዳንድ አገሮች ደግሞ አንዲት ሴት እጆቿን እያወራጨች የምትናገር ከሆነ ሥርዓታማ እንዳልሆነች ተደርጎ ይታያል። እንግዲያው እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት ባለባቸው አካባቢዎች እህቶች ከእጆቻቸው ይልቅ ፊት ላይ በሚነበቡ መግለጫዎች ይበልጥ መጠቀም ያስፈልጋቸው ይሆናል። በየትኛውም የዓለም ክፍል ለማለት ይቻላል አንድ ሰው በጥቂት ሰዎች ፊት የተጋነነ አካላዊ መግለጫ የሚጠቀም ከሆነ ሆነ ብሎ ሰዎችን ለማሳቅ እንዳደረገው ሊቆጠር ይችላል።

ተሞክሮ እያዳበርክ ስትሄድና ይበልጥ በነፃነት መናገር ስትጀምር የምትጠቀምባቸው ማጠናከሪያ አካላዊ መግለጫዎች በሙሉ ውስጣዊ ስሜትህን የሚገልጹና በጉዳዩ ከልብ እንደምታምንበት የሚያሳዩ ይሆናሉ። ንግግርህንም ይበልጥ ሕያው ያደርጉልሃል።

ፊትህ ላይ የሚነበበው ስሜት። ከየትኛውም የሰውነት ክፍል ይልቅ ብዙውን ጊዜ ስሜትህ የሚነበበው ፊትህ ላይ ነው። ዓይኖችህ እንዲሁም የአፍህና የጭንቅላትህ እንቅስቃሴ ሁሉ የየራሳቸው መልእክት አላቸው። አንድም ቃል ሳትተነፍስ ፊትህ ላይ ግዴለሽነት፣ መጸየፍ፣ ግራ መጋባት፣ መገረም ወይም ደስታ ሊነበብ ይችላል። ፊት ላይ የሚነበቡት እንዲህ ያሉት ስሜቶች የሚነገረውን ቃል ይበልጥ ሕያው ያደርጉታል። አምላክ በፊታችን አካባቢ በአጠቃላይ ከ30 የሚበልጡ ጡንቻዎችን ፈጥሮልናል። ፈገግ ስትል ከእነዚህ መካከል ግማሽ የሚያህሉትን ጡንቻዎች ትጠቀማለህ።

ከመድረክ ስትናገርም ይሁን በመስክ አገልግሎት ስትሳተፍ ለአድማጮችህ አንድ አስደሳች መልእክት ልታካፍላቸው እየሞከርህ ነው። ሞቅ ያለ ፈገግታ ማሳየትህ ደግሞ ይህንኑ እንዲገነዘቡ የሚረዳቸው ይሆናል። በሌላ በኩል ፊትህ ላይ ምንም ዓይነት ስሜት የማይነበብ ከሆነ አድማጮች ከልብ እየተናገርህ መሆንህን ሊጠራጠሩ ይችላሉ።

ከዚህም በተጨማሪ ፈገግታ ማሳየትህ በደግነት እያነጋገርካቸው እንዳለ እንዲሰማቸው ያደርጋል። በተለይ ዛሬ ብዙ ሰዎች የማያውቁት ሰው ሲያነጋግራቸው ስጋት ስለሚያድርባቸው ፈገግ ማለትህ በጣም አስፈላጊ ነው። ፈገግታህ ሰዎች ዘና እንዲሉና በቀላሉ መልእክትህን እንዲቀበሉ ሊያደርግ ይችላል።

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች

  • አካላዊ መግለጫ ይበልጥ ውጤታማ የሚሆነው ውስጣዊ ስሜትን የሚገልጽ ሲሆን ነው። ሌሎች ተናጋሪዎችን ልብ ብለህ ተመልከት። ይሁን እንጂ ሁሉንም ነገር ከእነርሱ መኮረጅ አለብህ ማለት አይደለም።

  • ትምህርቱ በደንብ እስኪገባህ ድረስ አጥናው። በንግግሩ ተመሰጥ፣ በዓይነ ሕሊናህ ሳለው። ከዚያም ድምፅህን፣ እጆችህንና ፊትህን ተጠቅመህ ለመግለጽ ሞክር።

መልመጃ፦ (1) ዘፍጥረት 6:​13-22⁠ን አንብብ። የመርከቡን ግንባታና የእንስሳት መሰብሰቡን ሥራ በራስህ አባባል ለመግለጽ ሞክር። ስለ ዝርዝር ጉዳዮቹ አትጨነቅ። የምታስታውሰውን ብቻ ተናገር። ይህንን ስታደርግ ገላጭ የሆኑ አካላዊ መግለጫዎችን ተጠቀም። አንድ ሰው እንዲያይህና አስተያየት እንዲሰጥህ ጠይቅ። (2) ስለ አምላክ መንግሥትና ስለሚያመጣቸው በረከቶች እየመሠከርህ እንዳለህ ሆነህ ተናገር። ስለምትናገረው መልእክት ያለህ ውስጣዊ ስሜት ፊትህ ላይ እንዲነበብ አድርግ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ