የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • be ጥናት 35 ገጽ 206-ገጽ 208 አን. 3
  • ነጥቡን ለማጉላት መደጋገም

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ነጥቡን ለማጉላት መደጋገም
  • በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • መደጋገምና የሰውነት እንቅስቃሴዎች
    ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ
  • ዋና ዋና ነጥቦች ጎላ ብለው እንዲታዩ ማድረግ
    በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • ዋና ዋና ነጥቦች ጎላ ብለው እንዲታዩ ማድረግ
    ለማንበብ እና ለማስተማር የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ
  • አርዕስቱንና ዋና ዋና ነጥቦችን ማጉላት
    ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ
ለተጨማሪ መረጃ
በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
be ጥናት 35 ገጽ 206-ገጽ 208 አን. 3

ጥናት 35

ነጥቡን ለማጉላት መደጋገም

ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

አድማጮች ይበልጥ እንዲያስታውሱት የምትፈልገውን ነጥብ ከአንድ ጊዜ በላይ ጥቀስ።

አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

መደጋገም ነጥቦቹ እንዳይረሱ ከማገዙም በተጨማሪ አንድ ተናጋሪ ዋና ዋናዎቹን ሐሳቦች ጥሩ አድርጎ ለማጉላት ሊጠቀምበት ይችላል። ይህም አድማጮች እነዚህን ነጥቦች በግልጽ እንዲያስተውሉ ይረዳል።

መደጋገም አንዱ ጥሩ የማስተማር ዘዴ ነው። በጣም አስፈላጊ የሆነ ነጥብ ተደጋግሞ ከተጠቀሰ አድማጮች ለማስታወስ እንደሚቀልላቸው የታወቀ ነው። ሐሳቡ ትንሽ ለየት ባለ መንገድ ተደግሞ ቢገለጽ ይበልጥ ግልጽ ሊሆንላቸው ይችላል።

አድማጮች የተናገርከውን ነገር ማስታወስ ካልቻሉ ንግግርህ በእምነታቸውም ሆነ በአኗኗራቸው ላይ ለውጥ ሊያመጣ አይችልም። በደንብ የምታጎላቸው ነጥቦች ከአድማጮችህ አእምሮ ቶሎ አይጠፉም።

ታላቁ አስተማሪያችን ይሖዋ የመደጋገምን ዘዴ በመጠቀም ረገድ ምሳሌ ይሆነናል። ለእስራኤል ብሔር አሥርቱን ትእዛዛት ሲሰጥ በመጀመሪያ በሲና ተራራ ግርጌ በመልአክ አማካኝነት እንዲነገራቸው አድርጓል። ከዚያም በጽላት ጽፎ ለሙሴ ሰጠው። (ዘጸ. 20:​1-17፤ 31:​18፤ ዘዳ. 5:​22) የእስራኤል ብሔር ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመግባቱ በፊት ሙሴ ከይሖዋ በተሰጠው መመሪያ መሠረት እነዚህኑ ትእዛዛት የደገመላቸው ሲሆን በመንፈስ ቅዱስ እርዳታም በ⁠ዘዳግም 5:​6-21 ላይ አስፍሯቸዋል። ለእስራኤላውያን ከተሰጡት ሕግጋት መካከል አንዱ ይሖዋን በፍጹም ልባቸው፣ በፍጹም ነፍሳቸውና በፍጹም ኃይላቸው እንዲወድዱና እንዲያገለግሉ የሚያዝዝ ነበር። ይህ ሕግ ተደጋግሞ ተጠቅሷል። (ዘዳ. 6:​5፤ 10:​12፤ 11:​13፤ 30:​6) ለምን? ምክንያቱም ኢየሱስ እንደተናገረው ከትእዛዛት ሁሉ ‘ታላቅና ፊተኛ’ ስለሆነ ነው። (ማቴ. 22:​34-38) የአምላክን ትእዛዛት መጠበቃቸው በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ይሖዋ በነቢዩ ኤርምያስ አማካኝነት የይሁዳን ሰዎች ከ20 ጊዜ በላይ ደጋግሞ አሳስቧቸዋል። (ኤር. 7:​23፤ 11:​4፤ 12:​17፤ 19:​15) እንዲሁም አምላክ በሕዝቅኤል አማካኝነት አሕዛብ ‘እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ’ በማለት ከ60 ጊዜ በላይ ደጋግሞ ተናግሯል።​—⁠ሕዝ. 6:​10፤ 38:​23

ስለ ኢየሱስ አገልግሎት በሚናገረው ዘገባ ውስጥም የመደጋገም ዘዴ ውጤታማ በሆነ መንገድ ተሠርቶበት እናገኛለን። ለምሳሌ ያህል አራቱን ወንጌሎች እንመልከት። እያንዳንዱ ወንጌል በሌሎች ወንጌሎች ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙትን ጉልህ ክንውኖች ትንሽ ለየት ባለ መንገድ በድጋሚ ይዘግባል። ኢየሱስ ራሱም ቢሆን አቀራረቡን እየለዋወጠ አንድን ዋና ነጥብ በተለያየ ጊዜ ደጋግሞ አስተምሯል። (ማር. 9:​34-37፤ 10:​35-45፤ ዮሐ. 13:​2-17) ከመሞቱ ጥቂት ቀናት በፊት ደግሞ በደብረ ዘይት ተራራ ተቀምጦ ሳለ “ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ” የሚለውን በጣም አስፈላጊ ምክር ለማጉላት በዚሁ ዘዴ ተጠቅሟል።​—⁠ማቴ. 24:​42፤ 25:​13

በአገልግሎት። በአገልግሎት የምታገኛቸው ሰዎች የምትነግራቸውን ነገር እንዲያስታውሱ ትፈልጋለህ። ነጥቡን በሚገባ እየደገምህ ከነገርካቸው ሊያስታውሱት ይችላሉ።

ብዙውን ጊዜ ስለ አንድ ጉዳይ ውይይት ሲደረግ ነጥቡን ደግሞ ደጋግሞ መጥቀስ በሰውዬው አእምሮ ውስጥ እንዲቀረጽ ያደርጋል። ጥቅሱን ካነበብክለት በኋላ ቁልፍ የሆነውን የጥቅሱን ክፍል በመጠቆም እንዲሁም “እዚህ ላይ ምን እንደሚል ልብ ብለሃል?” የሚል ጥያቄ በማንሳት ማጉላት ትችላለህ።

በውይይታችሁ መደምደሚያ ላይ የምትናገራቸውን ዓረፍተ ነገሮች ውጤታማ በሆነ መንገድ ልትጠቀምባቸው ትችላለህ። ለምሳሌ ያህል “ከውይይታችን . . . የሚለውን ነጥብ እንደተገነዘብህ ተስፋ አደርጋለሁ” ልትል ትችል ይሆናል። ከዚያም በአጭሩ ድገምለት። እንደሚከተለው ማለት ትችላለህ:- “አምላክ ምድር ገነት እንድትሆን ዓላማ አለው። ይህ ዓላማው እንደሚፈጸም የተረጋገጠ ነው።” ወይም ደግሞ “መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ሥርዓት የመጨረሻ ቀናት ውስጥ እንደምንኖር በማያሻማ መንገድ ይጠቁማል። በዚህ ሥርዓት ላይ ከሚመጣው ጥፋት ለመትረፍ ከፈለግን አምላክ ከእኛ ምን እንደሚፈልግ መማር ይኖርብናል” ማለት ትችል ይሆናል። አለዚያም “እስካሁን እንዳየነው መጽሐፍ ቅዱስ በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙትን ችግሮች በተመለከተ ጠቃሚ ምክር ይሰጣል” ማለት ትችላለህ። አንዳንድ ጊዜ አድማጮች እንዲያስታውሱት የሚፈለገውን ነጥብ የሚጠቁም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ደግሞ ማንበብ ይቻላል። እርግጥ ይህን ለማድረግ አስቀድመህ በሚገባ መዘጋጀት ይኖርብሃል።

ተመላልሶ መጠየቅ ስታደርግም ሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ስታስጠና ተፈላጊዎቹን ነጥቦች ለመድገም በክለሳ ጥያቄዎች ልትጠቀም ትችላለህ።

አንድ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር መረዳት ወይም ሥራ ላይ ማዋል ከከበደው ጉዳዩን በተደጋጋሚ ጊዜ ልታነሳለት ያስፈልግ ይሆናል። ይህን ስታደርግ ግን ነጥቡን በተለያየ መንገድ ለማስረዳት ሞክር። ውይይታችሁ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪው ስለ ጉዳዩ እንዲያስብ የሚያደርገው ሊሆን ይገባል። ሆኖም የግድ ረጅም መሆን የለበትም። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ የነበራቸውን ከሌሎች የበላይ ሆኖ የመታየት ዝንባሌ እንዲያስተካክሉ ሲል በተለያየ መንገድ እየደጋገመ እንዳስረዳቸው አስታውስ።​—⁠ማቴ. 18:​1-6፤ 20:​20-28፤ ሉቃስ 22:​24-27

ንግግር ስትሰጥ። ንግግር ስትሰጥ ዓላማህ ነጥቡን ተናግረህ መሄድ ብቻ አይደለም። አድማጮች እንዲገባቸው፣ እንዲያስታውሱትና እንዲሠሩበት ትፈልጋለህ። ይህን ለማድረግ ደግሞ በሚገባ መደጋገም ያስፈልግሃል።

ይሁን እንጂ ዋና ዋና ነጥቦቹንም ቢሆን አሁንም አሁንም የምትደግም ከሆነ አድማጮችህ ላይከታተሉህ ይችላሉ። ለየት ባለ መንገድ መጉላት ያለባቸውን ነጥቦች በጥንቃቄ ምረጥ። እነዚህ ብዙውን ጊዜ ንግግርህ የተመሠረተባቸው ዋና ዋና ነጥቦች ናቸው። ይሁን እንጂ ለአድማጮችህ ልዩ ትርጉም ያላቸው ነጥቦችም ከዚሁ ጋር ሊካተቱ ይችላሉ።

በመደጋገም ዘዴ ለመጠቀም በመጀመሪያ መግቢያህ ላይ ዋና ዋና ነጥቦችህን መዘርዘር ትችላለህ። ይህን ስታደርግ የምታብራራውን ነጥብ ጠቅለል አድርገው የሚገልጹ አጫጭር ዓረፍተ ነገሮችን ተጠቀም። ዓረፍተ ነገሮችህ ጥያቄ አዘል ወይም መፍትሔ የሚያስፈልገውን ችግር የሚጠቅሱ ሊሆኑ ይችላሉ። ዋና ዋና ነጥቦችህ ስንት እንደሆኑ ልትጠቅስና በቁጥር ልትዘረዝራቸውም ትችል ይሆናል። ከዚያም እነዚህን ነጥቦች በንግግርህ መሃል አንድ በአንድ ታብራራቸዋለህ። በንግግርህ መሃል አንዱን ዋና ነጥብ ጨርሰህ ወደሚቀጥለው ከመሸጋገርህ በፊት ነጥቡን ደግመህ መጥቀስ ይበልጥ ለማጉላት ያስችልሃል። ወይም ደግሞ ዋናው ነጥብ ለአድማጮች እንዴት እንደሚሠራ የሚያሳይ ምሳሌ በመጥቀስ ማጉላት ይቻላል። በሌላ በኩል ዋና ዋናዎቹን ነጥቦች ይበልጥ ለማጉላት መደምደሚያህ ላይ ስትደርስ ደግመህ መዘርዘር፣ የተለያዩ ሐሳቦችን ማነጻጸር፣ በመግቢያህ ላይ ያነሳሃቸውን ጥያቄዎች መልስ መጥቀስ ወይም የችግሮቹ መፍትሔ ምን እንደሆነ በአጭሩ ደግመህ መግለጽ ትችላለህ።

ከዚህ በተጨማሪ ልምድ ያለው ተናጋሪ አድማጮቹን አንድ በአንድ ስለሚያስተውል ከመካከላቸው ነጥቡን ለመረዳት የተቸገረ ካለ ማየቱ አይቀርም። ነጥቡ አስፈላጊ ከሆነ ደግሞ ይጠቅሰዋል። ይሁን እንጂ ያንኑ ቃል ደግሞ መጥቀሱ ብቻ ነጥቡን ግልጽ ላያደርገው ይችላል። ጥሩ አስተማሪ ከዚህም የበለጠ ነገር ማድረግ ይኖርበታል። እንደ ሁኔታው ተጨማሪ ነጥቦችን በማከል ማብራራት ያስፈልገው ይሆናል። በዚህ መንገድ የአድማጮችን ሁኔታ እያስተዋልክ መናገር ከቻልክ በማስተማር ችሎታህ ምን ያህል እድገት እንዳደረግህ የሚያሳይ ይሆናል።

ይህን ማድረግ ያለብህ መቼ ነው?

  • አንድ ጉልህ ነጥብ ከጠቀስክ ወይም አንድን ዋና ነጥብ ካብራራህ በኋላ።

  • በውይይታችሁ ወይም በንግግርህ መደምደሚያ ላይ።

  • አድማጮችህ አንድን ቁልፍ ነጥብ ለመረዳት እንደተቸገሩ ስታስተውል።

  • ተመላልሶ መጠየቅ ስታደርግና መጽሐፍ ቅዱስ ስታስጠና ከሆነ ደግሞ በቀናት ወይም በሳምንታት ልዩነት መደጋገም ያስፈልግሃል።

መልመጃ፦ (1) አገልግሎት ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ካገኘኸው ሰው ጋር የምታደርገውን ውይይት ስትቋጭ የተወያያችሁበትንና ግለሰቡ እንዲያስታውሰው የምትፈልገውን አንድ ጉልህ ነጥብ ደግመህ ጥቀስ። (2) በተመላልሶ መጠየቅ ወቅት ውይይታችሁን ስትደመድም ሰውዬው እንዲያስታውስ የምትፈልጋቸውን አንድ ወይም ሁለት ቁልፍ ነጥቦች ደግመህ ጥቀስ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ