የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • wt ምዕ. 16 ገጽ 144-150
  • “እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ”

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • “እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ”
  • እውነተኛውን አንድ አምላክ አምልክ
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ችግሮች ሲፈጠሩ
  • ፍቅርህን ለማስፋት ጥረት አድርግ
  • “እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ”
    እውነተኛው አንድ አምላክ ያስገኘው የአምልኮ አንድነት
  • “በፍቅር መመላለሳችሁን ቀጥሉ”
    ወደ ይሖዋ ቅረብ
  • ‘ከሁሉ በላይ ከልብ ተዋደዱ’
    ነቅተህ ጠብቅ!
  • የወንድማማችነት ፍቅራችሁ እያደገ ይሂድ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
ለተጨማሪ መረጃ
እውነተኛውን አንድ አምላክ አምልክ
wt ምዕ. 16 ገጽ 144-150

ምዕራፍ አሥራ ስድስት

“እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ”

1. በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚገኙ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ የሚማርካቸው ነገር ምንድን ነው?

ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ሲመጡ ብዙውን ጊዜ እዚያ በሚያዩት ፍቅር ይማረካሉ። ለእነሱ የሚደረግላቸው ሞቅ ያለ አቀባበልም ሆነ በጉባኤው ውስጥ የሚታየው የወዳጅነት መንፈስ ይህን ፍቅር እንዲያስተውሉ ያደርጋቸዋል። በአውራጃ ስብሰባዎቻችን ላይ የሚገኙ አዳዲስ ሰዎችም ይህን ፍቅር ያስተውላሉ። አንድ የዜና ዘጋቢ አንድን የአውራጃ ስብሰባ በተመለከተ እንዲህ ሲል ጽፏል:- ‘አደንዛዥ ዕፅ የወሰደ ወይም መጠጥ የጠጣ አልነበረም። መጯጯኽ የለም፤ መጋፋት አሊያም ሰውን ገፍትሮ ማለፍ የለም። ስድብ ወይም የእርግማን ቃል አይሰማም። አስቀያሚ ቀልድም ሆነ ጸያፍ ቃል ከአፋቸው አይወጣም። የሚያጨስ የለም። የሚሰርቅ የለም። የምግብም ሆነ የመጠጥ ቆርቆሮዎችን ሜዳ ላይ አይጥሉም። ይህ ፈጽሞ ያልተለመደ ሁኔታ ነው።’ ይህ ሁሉ የይሖዋ ሕዝቦች “ተገቢ ያልሆነ ነገር አያደርግም፤ ራስ ወዳድ አይደለም” የተባለለት ዓይነት ፍቅር እንዳላቸው የሚያሳይ ማስረጃ ነው።—1 ቆሮንቶስ 13:4-8

2. (ሀ) ለሌሎች የምናሳየው ፍቅር ከጊዜ ወደ ጊዜ ምን እየሆነ መሄድ አለበት? (ለ) የክርስቶስን ምሳሌ በመኮረጅ ምን ዓይነት ፍቅር ማዳበር ያስፈልገናል?

2 የወንድማማች ፍቅር የእውነተኛ ክርስቲያኖች መለያ ምልክት ነው። (ዮሐንስ 13:35) በመንፈሳዊ እያደግን ስንሄድ ፍቅርን ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ መግለጽ የምንችልበትን መንገድ እንማራለን። ሐዋርያው ጳውሎስ የክርስቲያን ባልንጀሮቹ ፍቅር “በዝቶ እንዲትረፈረፍ” ጸልዮአል። (ፊልጵስዩስ 1:9) ሐዋርያው ዮሐንስ ፍቅራችን የራሳችንን ጥቅም መሥዋዕት እንድናደርግ የሚገፋፋ መሆን እንዳለበት ተናግሯል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወቱን ስለ እኛ አሳልፎ ስለ ሰጠ፣ ፍቅር ምን እንደ ሆነ በዚህ እናውቃለን፤ እኛም ሕይወታችንን ስለ ወንድሞቻችን አሳልፈን ልንሰጥ ይገባናል።” (1 ዮሐንስ 3:16፤ ዮሐንስ 15:12, 13) በእርግጥ ሕይወታችንን ለወንድሞቻችን እንሠዋለን? ምንም እንኳ አብዛኞቹ ሁኔታዎች እንዲህ እንድናደርግ የሚጠይቁብን ባይሆኑም አመቺ በማይሆንበት ጊዜም እንኳ ወንድሞቻችንን ለመርዳት ምን ያህል ጥረት እናደርጋለን?

3. (ሀ) ፍቅራችንን ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ መግለጽ የምንችለው በምን መንገድ ነው? (ለ) በአሁኑ ጊዜ አንዳችን ለሌላው የጠበቀ ፍቅር ሊኖረን የሚገባው ለምንድን ነው?

3 የራሳችንን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ እንዳለን የሚያሳዩ ድርጊቶችን ከመፈጸም በተጨማሪ ለወንድሞቻችን ከልብ የመነጨ የፍቅር ስሜት ሊኖረን ይገባል። የአምላክ ቃል “እርስ በርሳችሁ በወንድማማች መዋደድ አጥብቃችሁ ተዋደዱ” በማለት አጥብቆ ያሳስበናል። (ሮሜ 12:10) ሁላችንም ለተወሰኑ ሰዎች እንዲህ ዓይነት ስሜት አለን። ይሁንና ለሌሎችም እንዲህ ያለ ስሜት እንዲኖረን ማድረግ እንችላለን? የዚህ አሮጌ ሥርዓት ፍጻሜ እየተቃረበ በሄደ መጠን ወደ ክርስቲያን ባልንጀሮቻችን ይበልጥ መቅረባችን በጣም አስፈላጊ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “የሁሉ ነገር መጨረሻ ተቃርቦአል፤ . . . ፍቅር ብዙ ኀጢአትን ይሸፍናልና ከሁሉ በላይ እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ” ይላል።—1 ጴጥሮስ 4:7, 8

ችግሮች ሲፈጠሩ

4. (ሀ) በጉባኤ ውስጥ ባሉት መካከል ችግሮች ሊፈጠሩ የሚችሉት ለምንድን ነው? (ለ) የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ሥራ ላይ ማዋል ሁልጊዜ የሚቀናን ባይሆንም እንኳ ይህን ማድረጋችን ምን ጥቅም ሊያስገኝ ይችላል?

4 እርግጥ ነው፣ ፍጽምና የጎደለን እንደመሆናችን መጠን ሌሎችን ቅር የምናሰኝባቸው ጊዜያት ይኖራሉ። ወንድሞቻችንም በተለያዩ መንገዶች ሊበድሉን ይችላሉ። (1 ዮሐንስ 1:8) እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥምህ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? ቅዱሳን ጽሑፎች አስፈላጊውን መመሪያ ይሰጣሉ። ሆኖም ቅዱሳን ጽሑፎች የሚሰጡን ምክር እኛ ፍጽምና የጎደለን የሰው ልጆች ለማድረግ ከምናስበው ነገር ጋር ላይስማማ ይችላል። (ሮሜ 7:21-23) ይሁንና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ምክር ሥራ ላይ ለማዋል ከልባችን የምንጥር ከሆነ ይሖዋን ለማስደሰት ልባዊ ፍላጎት እንዳለን እናሳያለን። በተጨማሪም ይህን ማድረጋችን ለሌሎች ንጹሕ ፍቅር እንድናሳይ ይረዳናል።

5. አንድ ሰው ሲበድለን አጸፋ መመለስ የሌለብን ለምንድን ነው?

5 አንዳንድ ጊዜ ሰዎች በደል ሲደርስባቸው የጎዳቸውን ወይም ያስቀየማቸውን ሰው የሚበቀሉበትን መንገድ ይፈልጋሉ። ይሁን እንጂ ይህ ችግሩን ከማባባስ በስተቀር የሚፈይደው ነገር የለም። በቀልን ለአምላክ መተው ይኖርብናል። (ምሳሌ 24:29፤ ሮሜ 12:17-21) ሌሎች ደግሞ የበደላቸውን ሰው ጨርሶ ለመራቅ ይሞክራሉ። ሆኖም አምልኳችን በአምላክ ፊት ተቀባይነት ማግኘቱ በከፊል የተመካው ወንድሞቻችንን በመውደዳችን ላይ በመሆኑ የአምልኮ ባልንጀሮቻችንን መራቅ አይኖርብንም። (1 ዮሐንስ 4:20) ስለሆነም ጳውሎስ “እርስ በርሳችሁ ተቻቻሉ፤ ከእናንተ አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖር ይቅር ተባባሉ፤ ጌታ ይቅር እንዳላችሁ እናንተም ሌላውን ይቅር በሉ” ሲል ጽፏል። (ቈላስይስ 3:13) አንተስ ይህን ማድረግ ትችላለህ?

6. (ሀ) ወንድማችንን ምን ያህል ጊዜ ይቅር ማለት አለብን? (ለ) ሌሎች የሚፈጽሙብንን በደል እንዳንቆጥር የሚረዳን ስለ ራሳችን የትኛውን ሐቅ መገንዘባችን ነው?

6 አንድ ሰው ደጋግሞ ቢበድልህና የፈጸማቸው ድርጊቶች ከጉባኤ ሊያስወግዱት የሚችሉ ባይሆኑስ? ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ያሉትን ቀላል በደሎች “እስከ ሰባት ጊዜ” ይቅር ለማለት ሐሳብ አቅርቦ ነበር። ሆኖም ኢየሱስ “እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ ብቻ አልልህም” ብሎታል። ኢየሱስ አንድ ሰው በእኛ ላይ የሚፈጽመው በደል እኛ በአምላክ ላይ ከምንፈጽመው በደል ጋር ሲነጻጸር ከቁጥር የማይገባ መሆኑን ጎላ አድርጎ ገልጿል። (ማቴዎስ 18:21-35) አምላክን እየበደልነው እንዳለን እንኳ ሳይታወቀን በየዕለቱ በብዙ መንገዶች እናሳዝነዋለን። ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅበት ድርጊት በመፈጸም፣ በንግግራችን፣ በሐሳባችን አሊያም ደግሞ ማድረግ ያለብንን ነገር ሳናደርግ በመቅረት አምላክን እንበድለዋለን። (ሮሜ 3:23) ይሁንና አምላክ ሁልጊዜ ምሕረት ያደርግልናል። (መዝሙር 103:10-14፤ 130:3, 4) እኛም እርስ በርስ ባለን ግንኙነት እንዲሁ እንድናደርግ ይጠብቅብናል። (ማቴዎስ 6:14, 15፤ ኤፌሶን 4:1-3) እንዲህ የምናደርግ ከሆነ “በደልን አይቈጥርም” የተባለውን ዓይነት ፍቅር እያሳየን ነው ማለት ነው።—1 ቆሮንቶስ 13:4, 5፤ 1 ጴጥሮስ 3:8, 9

7. አንድ ወንድም በእኛ ቅር እንደተሰኘ ብናስተውል ምን ማድረግ ይኖርብናል?

7 አንዳንድ ጊዜ እኛ በወንድማችን ቅር የተሰኘንበት ነገር ባይኖርም እንኳ እሱ በእኛ ቅር እንደተሰኘ እናስተውል ይሆናል። በዚህ ጊዜ 1 ጴጥሮስ 4:8 በሚሰጠው ምክር መሠረት ሁኔታውን ‘በፍቅር መሸፈን’ የተሻለ እንደሆነ ሊሰማን ይችላል። አሊያም ደግሞ ራሳችን ቅድሚያውን ወስደን ወንድማችንን በማነጋገር ሰላማዊ ግንኙነታችንን ለማደስ ጥረት ልናደርግ እንችላለን።—ማቴዎስ 5:23, 24

8. አንድ ወንድም ቅር የሚያሰኝ ነገር ሲያደርግ ብንመለከት ምን ልናደርግ እንችላለን?

8 አንድ ወንድም አንተን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ቅር የሚያሰኝ ነገር እያደረገ ሊሆን ይችላል። ታዲያ ይህን ሰው ማነጋገሩ የተሻለ አይሆንም? የተሻለ ሊሆን ይችላል። አሳቢነት በተሞላበት መንገድ ቀርበህ ብታነጋግረው ጥሩ ውጤት ሊገኝ ይችላል። በቅድሚያ ግን ‘በእርግጥ እየሠራ ያለው ነገር ቅዱስ ጽሑፉን የሚጻረር ነው? ወይስ እንዲህ የተሰማኝ አስተዳደጌ ከእሱ የተለየ ስለሆነ ነው?’ ብለህ ራስህን መጠየቅ ይኖርብሃል። የራስህን መሥፈርት በማውጣት በሌሎች ላይ እንዳትፈርድ ተጠንቀቅ። (ያዕቆብ 4:11, 12) ይሖዋ የተለያየ አስተዳደግ ያላቸውን ሰዎች ሁሉ ያለአድልዎ የሚቀበል ሲሆን በመንፈሳዊ እድገት እስኪያደርጉ ድረስም ይታገሳቸዋል።

9. (ሀ) በጉባኤ ውስጥ ለሚፈጸም ከባድ ኃጢአት ተገቢውን ትኩረት መስጠት ያለባቸው እነማን ናቸው? (ለ) በደል የተፈጸመበት ሰው ቀዳሚውን እርምጃ መውሰድ የሚጠበቅበት መቼ ነው? ይህን የሚያደርገውስ በምን ዓላማ ነው?

9 በጉባኤ ውስጥ ያለ አንድ ግለሰብ እንደ ጾታ ብልግና ያለ ከባድ ኃጢአት ቢሠራ ጉዳዩ አፋጣኝ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ይህን ማድረግ ያለባቸው እነማን ናቸው? ሽማግሌዎች ናቸው። (ያዕቆብ 5:14, 15) ይሁን እንጂ ጉዳዩ ከገንዘብ አሊያም በአንደበት ከመጉዳት ጋር የተያያዘ በአንድ ግለሰብ ላይ የተፈጸመ በደል ከሆነ በደሉ የተፈጸመበት ሰው በቅድሚያ ግለሰቡን በግል ቀርቦ ለማነጋገር መጣር ይኖርበታል። (ማቴዎስ 18:15) በዚህ መንገድ ችግሩን መፍታት ካልተቻለ በማቴዎስ 18:16, 17 ላይ በሰፈረው መመሪያ መሠረት ተጨማሪ እርምጃዎች መውሰድ ያስፈልጋል። በደሉን ለፈጸመብን ወንድማችን ያለን ፍቅርና ወንድማችንን ‘የራሳችን ለማድረግ’ ያለን ፍላጎት ልቡን ለመንካት በሚያስችል መንገድ እንድናነጋግረው ይረዳናል።—ምሳሌ 16:23

10. ችግር በሚፈጠርበት ጊዜ ጉዳዩን በትክክለኛው መንገድ ለማየት የሚረዳን ምንድን ነው?

10 ትንሽም ሆነ ትልቅ ችግር በሚፈጠርበት ጊዜ ይሖዋ ጉዳዩን እንዴት እንደሚመለከተው ለማወቅ መጣራችን ጠቃሚ ነው። ማንኛውም ዓይነት ኃጢአት በይሖዋ ፊት ተቀባይነት የሌለው ከመሆኑም በላይ ንስሐ ሳይገቡ ከባድ ኃጢአት መሥራታቸውን የሚቀጥሉ ሰዎችን ራሱ በወሰነው ጊዜ ከድርጅቱ ያስወግዳቸዋል። ይሁን እንጂ ሁላችንም ከባድ ያልሆኑ ኃጢአቶችን እንደምንፈጽምና የይሖዋ ትዕግሥትና ምሕረት እንደሚያስፈልገን መዘንጋት የለብንም። በመሆኑም ይሖዋ ሌሎች ሲበድሉን ልንኮርጀው የሚገባ ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል። ለሌሎች ምሕረት ስናደርግ የእሱን ፍቅር ማንጸባረቃችን ነው።—ኤፌሶን 5:1, 2

ፍቅርህን ለማስፋት ጥረት አድርግ

11. ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን ፍቅራቸውን እንዲያሰፉ ያበረታታቸው ለምንድን ነው?

11 ጳውሎስ በግሪክ የሚገኘውን የቆሮንቶስ ጉባኤ በማነጽ በርከት ያሉ ወራት አሳልፎ ነበር። በዚያ የሚገኙትን ወንድሞች ለመርዳት ብዙ የጣረ ከመሆኑም በላይ በጣም ይወዳቸው ነበር። ሆኖም አንዳንዶቹ ለእሱ ሞቅ ያለ ፍቅር አልነበራቸውም። የመተቸትና የመንቀፍ ባሕርይ ነበራቸው። በዚህም ምክንያት ጳውሎስ ፍቅራቸውን እንዲያሰፉ አጥብቆ አሳሰባቸው። (2 ቆሮንቶስ 6:11-13፤ 12:15) ሁላችንም ለሌሎች ምን ያህል ፍቅር እያሳየን እንዳለን መመርመርና ፍቅራችንን ለማስፋት መጣር ይኖርብናል።—1 ዮሐንስ 3:14

12. በጉባኤ ውስጥ ላሉት ሁሉ ያለንን ፍቅር ልናሳድግ የምንችለው እንዴት ነው?

12 በጉባኤ ውስጥ ብዙም የማንቀርባቸው ሰዎች አሉ? እነሱ እንዲያደርጉልን እንደምንፈልገው ሁሉ እኛም በመካከላችን ያለውን የባሕርይ ልዩነት ወደ ጎን ትተን የምንቀርባቸው ከሆነ በመካከላችን ጥሩ ወዳጅነት ሊመሠረት ይችላል። በተጨማሪም መልካም ባሕሪዎቻቸውን ለመመልከትና በእነዚያ ላይ ለማተኮር የምንጥር ከሆነ ለእነሱ ያለን አመለካከት ሊለወጥ ይችላል። ይህ ለእነሱ ያለንን ፍቅር እንደሚያጠነክረው ጥርጥር የለውም።—ሉቃስ 6:32, 33, 36

13. በጉባኤያችን ላሉት ፍቅራችንን ማስፋት የምንችለው እንዴት ነው?

13 ለሌሎች ልናደርግ የምንችለው ነገር ውስን መሆኑ አይካድም። በእያንዳንዱ ስብሰባ ላይ ሁሉንም ሰው ሰላም ማለት አንችል ይሆናል። ወንድሞችን ቤታችን በምንጋብዝበት ጊዜም ሁሉንም መጥራት አንችል ይሆናል። ሆኖም በጉባኤያችን ካሉት መካከል አንዱን ቀረብ ብለን ለጥቂት ደቂቃዎች በማጫወትና ከዚያ ሰው ጋር ይበልጥ በመተዋወቅ ፍቅራችንን ማስፋት እንችል ይሆን? አልፎ አልፎ በደንብ የማናውቃቸውን ወንድሞች በመስክ አገልግሎት አብረውን እንዲያገለግሉ ልንጋብዛቸው እንችላለን?

14. ቀደም ሲል በማናውቃቸው ክርስቲያኖች መካከል በምንሆንበት ጊዜ ለእነሱ ያለንን ከልብ የመነጨ ፍቅር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

14 ክርስቲያናዊ የሆኑ ትልልቅ ስብሰባዎች ፍቅራችንን ለማስፋት የሚያስችሉ ግሩም አጋጣሚዎች ናቸው። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሊገኙ ይችላሉ። ከሁሉም ጋር ተገናኝተን መጫወት ባንችልም ከእኛ ምቾት ይልቅ የእነሱን ደኅንነት እንደምናስቀድም በተግባር ልናሳይ እንችላለን። በስብሰባው የዕረፍት ጊዜያት በአካባቢያችን ያሉትን ቀረብ ብለን በማጫወት እንደምናስብላቸው ልናሳይ እንችላለን። በምድር ላይ የሚኖሩ ሁሉ እውነተኛ አምላክና የሁሉም አባት በሆነው በይሖዋ አምልኮ የተሳሰሩ ወንድማማቾችና እህትማማቾች የሚሆኑበት ጊዜ ይመጣል። በዚያን ጊዜ ከማናውቃቸው ሁሉ ጋር መተዋወቅ መቻል ምንኛ የሚያስደስት ይሆናል! ለሌሎች ያለን ከልብ የመነጨ ፍቅር ይህን እንድናደርግ ይገፋፋናል። ታዲያ አሁኑኑ ለምን አትጀምርም?

የክለሳ ውይይት

• በክርስቲያኖች መካከል ችግር በሚፈጠርበት ጊዜ ችግሩ እልባት ማግኘት የሚኖርበት እንዴት ነው? ለምንስ?

• በመንፈሳዊ እያደግን ስንሄድ ፍቅራችንም እያደገ መሄድ ያለበት በምን መንገዶች ነው?

• ለቅርብ ጓደኞቻችን ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ከልብ የመነጨ ፍቅር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

[በገጽ 148 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲያናዊ ፍቅር በብዙ መንገዶች ከሚገለጽባቸው ቦታዎች አንዱ የጉባኤ ስብሰባ ነው

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ