ሕይወትህ ወዴት አቅጣጫ እያመራ ነው?
• ብዙ ሰዎች በዕለት ተዕለት የኑሮ ጉዳዮች በጣም ስለተጠመዱ ሕይወታቸው ወዴት አቅጣጫ እያመራ እንዳለ ቆም ብለው አያስቡም።
• መጽሐፍ ቅዱስ ወደፊት አስደሳች ክስተቶች እንደሚኖሩ ይገልጽልናል። በተጨማሪም በዓለም ዙሪያ ባሉ ሰብዓዊ ተቋማት ላይ ሥር ነቀል ለውጥ እንደሚካሄድ ይናገራል። መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን በመስማት ራሳችንን ከጥፋት ለማዳን የግድ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ አለብን።
• መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን የሚያውቁና ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ የሚጥሩ አንዳንድ ሰዎች በኑሮ ጭንቀቶች ተውጠው ትክክለኛውን የሕይወት አቅጣጫ ስተዋል።
• እየተከተልከው ባለኸው የሕይወት አቅጣጫ ሙሉ በሙሉ ደስተኛ ነህ? አንዳንድ ነገሮችን ለማከናወን ዕቅድ ስታወጣ እነዚህ ነገሮች የረጅም ጊዜ የሕይወት ግብህን እንዴት ሊነኩ እንደሚችሉ ቆም ብለህ ታስባለህ?
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
በሕይወትህ ውስጥ ትልቅ ቦታ የምትሰጠው ነገር ምንድን ነው?
ከታች ለተዘረዘሩት ነገሮች የምትሰጠው ደረጃ ምንድን ነው? በደረጃቸው መሠረት ቁጥር ስጣቸው።
በሕይወትህ ውስጥ ሁሉም የራሳቸው ድርሻና ቦታ እንዳላቸው የታወቀ ነው። ሆኖም ምረጥ ብትባል አንደኛ፣ ሁለተኛ፣ ሦስተኛ ወዘተ ደረጃ የምትሰጠው ለየትኛው ነው?
― መዝናኛ
― ሥራዬ
― ጤናዬ
― ደስታዬ
― የትዳር ጓደኛዬ
― ወላጆቼ
― ልጆቼ
― ቆንጆ ቤት፣ ምርጥ ልብስ
― ከሌሎች የተሻልኩ ሆኜ መገኘት
― አምልኮ
[በገጽ 10, 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የምታደርጋቸው ምርጫዎች ሕይወትህን ወደምትፈልገው አቅጣጫ እየመሩት ነው?
የሚከተሉትን ጥያቄዎች አስብባቸው
መዝናኛ:- የምዝናናበት ነገር መንፈሴን የሚያድስ ነው? ሕይወቴን ለአደጋ የሚያጋልጥ ብሎም ለአካል ጉዳተኝነት ሊዳርገኝ የሚችል ነው? ለጊዜው የሚያስደስትና የሚያዝናና ቢሆንም የኋላ ኋላ ለጸጸት የሚዳርግ ነው? የምዝናናበት ነገር ምንም ጉዳት የማያስከትል ቢሆንም እንኳ ጊዜን የሚያባክንና ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች የማውለውን ጊዜ የሚሻማ ነው?
ሥራዬ:- የምሠራው ለኑሮ መሠረታዊ የሆኑ ነገሮችን ለማግኘት ያክል ነው ወይስ ለሥራዬ ሙሉ በሙሉ ባሪያ ሆኛለሁ? ጤንነቴ እስኪቃወስ ድረስ ጉልበቴን እያሟጠጠው ነው? በሥራ ቦታ ተጨማሪ ሰዓት መሥራት እመርጣለሁ ወይስ ከትዳር ጓደኛዬ ወይም ከልጆቼ ጋር ጊዜ ማሳለፍ? አሠሪዬ ሕሊናዬን የሚረብሽ ሥራ እንድሠራ ቢያዘኝ ወይም ለመንፈሳዊ ነገሮች ጊዜ እስካጣ ድረስ ሥራ ቢያበዛብኝ ሥራዬን ላለማጣት ስል የተባልኩትን ሁሉ አደርጋለሁ?
ጤናዬ:- ጤንነቴን በተመለከተ ቸልተኛ ነኝ ወይስ ጤንነቴን ለመጠበቅ የተቻለኝን ጥንቃቄ አደርጋለሁ? ሁልጊዜ የማወራው ስለ ጤንነቴ ብቻ ነው? ለጤንነቴ የማደርገው ጥንቃቄ ለቤተሰቤ እንደማስብ ያሳያል?
ደስታዬ:- ከሁሉ ይበልጥ የሚያሳስበኝ የራሴ ደስታ ብቻ ነው? ከትዳር ጓደኛዬ ወይም ከቤተሰቤ ደስታ ይልቅ የራሴን ደስታ አስቀድማለሁ? ደስታ ለማግኘት የምጥረው አንድን የእውነተኛው አምላክ አገልጋይ በማያስነቅፍ መንገድ ነው?
የትዳር ጓደኛዬ:- የትዳር ጓደኛዬን ምንጊዜም እንደ አጋሬ አድርጌ እመለከታታለሁ? ለትዳር ጓደኛዬ ከፍ ያለ አክብሮት እንዳለኝ አሳያለሁ? በአምላክ ላይ ያለኝ እምነት ለትዳር ጓደኛዬ ተገቢ አመለካከት እንዲኖረኝ አድርጓል?
ወላጆቼ:- ገና በወላጆቼ ሥር ያለሁ ከሆንኩ በአክብሮት በማናገር፣ በቤት ውስጥ የሚሰጡኝን ሥራዎች በመሥራት፣ ባሉኝ ሰዓት ቤት በመግባት እንዲሁም ከክፉ ባልንጀርነትና ከመጥፎ ነገሮች እንድርቅ የሚሰጡኝን ምክር በመስማት ወላጆቼን እታዘዛለሁ? ራሴን የቻልኩ ከሆንኩ ደግሞ ወላጆቼ የሚሰጡኝን ምክር እሰማለሁ? በተጨማሪም አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ተገቢውን ድጋፍና እርዳታ አደርግላቸዋለሁ? ከወላጆቼ ጋር ባለኝ ግንኙነት የአምላክ ቃል የሚሰጠውን ምክር ተግባራዊ አደርጋለሁ ወይስ የራሴን ጥቅምና ምቾት አስቀድማለሁ?
ልጆቼ:- ልጆቼን በጥሩ ሥነ ምግባር ኮትኩቶ የማሳደግ ኃላፊነት እንዳለብኝ ይሰማኛል ወይስ ይህን ሥልጠና በትምህርት ቤት እንደሚያገኙ በማሰብ ኃላፊነቴን ቸል እላለሁ? ከልጆቼ ጋር በቂ ጊዜ አሳልፋለሁ ወይስ በአሻንጉሊት እንዲጫወቱ፣ ቴሌቪዥን እንዲመለከቱ ወይም የኮምፒውተር ጨዋታ እንዲጫወቱ በማድረግ ከእነሱ ለመገላገል እሞክራለሁ? ልጆቼ የአምላክን ትእዛዛት በጣሱ ቁጥር ተግቼ እገስጻቸዋለሁ ወይስ ተግሳጽ የምሰጣቸው ሲያበሳጩኝ ብቻ ነው?
ቆንጆ ቤት፣ ምርጥ ልብስ:- ለአለባበሴና ለንብረቶቼ ያለኝን አመለካከት የሚወስነው ኑሮዬ ይታይልኝ የሚል መንፈስ ነው? የቤተሰቦቼ ደኅንነት ነው ወይስ ከአምላክ ጋር ያለኝ ግንኙነት?
ከሌሎች የተሻልኩ ሆኜ መገኘት:- ማንኛውንም ነገር በተሻለ መንገድ ማከናወን እንዳለብኝ ይሰማኛል? ከሌሎች ልቄ ለመገኘት እጥራለሁ? አንድ ሰው አንድን ነገር ከእኔ በተሻለ መንገድ ቢያከናውን ቅር እሰኛለሁ?
አምልኮ:- ይበልጥ የሚያሳስበኝ በማን ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት ነው? በትዳር ጓደኛዬ፣ በልጆቼ፣ በወላጆቼ፣ በአሠሪዬ ወይስ በአምላክ ዘንድ? የተደላደለ ኑሮ ለመኖር የማደርገው ሩጫ ለአምላክ የማቀርበውን አገልግሎት ወደ ጎን ገሸሽ እንዳደርግ እያስገደደኝ ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ምክር ልብ በል
ለአምላክ የምታቀርበው አምልኮ በሕይወትህ ውስጥ ምን ቦታ አለው?
መክብብ 12:13:- “እግዚአብሔርን ፍራ፤ ትእዛዛቱንም ጠብቅ፤ ይህ የሰው ሁለንተናዊ ተግባሩ ነውና።”
ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ:- አኗኗሬ እንዲህ ዓይነት አመለካከት እንዳለኝ የሚያሳይ ነው? በቤት፣ በሥራ ቦታ ወይም በትምህርት ቤት ያሉብኝን ኃላፊነቶች የምወጣው የአምላክን ትእዛዛት እንደማከብር በሚያሳይ መንገድ ነው? ወይስ ሌሎች ጉዳዮች ወይም የኑሮ ውጥረቶች ለአምላክ አገልግሎት በማውለው ጊዜ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ?
ከአምላክ ጋር ያለህ ዝምድና ምን ይመስላል?
ምሳሌ 3:5, 6:- “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ፤ እርሱም ጐዳናህን ቀና ያደርገዋል።”
ማቴዎስ 4:10:- “ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ስገድ፤ እርሱንም ብቻ አምልክ።”
ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ:- ከአምላክ ጋር ባለኝ ግንኙነት ረገድ እንዲህ ይሰማኛል? የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዬም ሆነ በየጊዜው የሚያጋጥሙኝን ችግሮች ለመወጣት ጥረት የማደርግበት መንገድ ለአምላክ ያደርኩ መሆኔንና ሙሉ በሙሉ በእሱ እንደምታመን የሚያሳይ ነው?
መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብንና የማጥናትን አስፈላጊነት ምን ያህል ከፍ አድርገህ ትመለከተዋለህ?
ዮሐንስ 17:3:- “እውነተኛ አምላክ የሆንኸውን አንተንና የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።”
ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ:- የአምላክን ቃል ለማንበብና በቃሉ ላይ ለማሰላሰል የማደርገው ጥረት ይህን እንደማምን ያሳያል?
በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የመገኘትን አስፈላጊነት ምን ያህል አክብደህ ትመለከተዋለህ?
ዕብራውያን 10:24, 25:- “እርስ በርሳችንም ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንዴት እንደምንነቃቃ እናስብ። አንዳንዶች ማድረጉን እንደተዉት መሰብሰባችንን አንተው፤ ይልቁንም ቀኑ እየተቃረበ መምጣቱን ስታዩ እርስ በርሳችን እንበረታታ።”
መዝሙር 122:1:- “‘ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ’ ባሉኝ ጊዜ፣ ደስ አለኝ።”
ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ:- አኗኗሬ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ይህን መመሪያ በአድናቆትና በቁም ነገር እንደምመለከተው የሚያሳይ ነው? ባለፈው ወር ውስጥ ለሌሎች ነገሮች ቅድሚያ በመስጠት ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎች የቀረሁባቸው ቀናት አሉ?
ሌሎችን ስለ አምላክና ስለ ዓላማዎቹ በማስተማሩ ሥራ በቅንዓት ትካፈላለህ?
ማቴዎስ 24:14:- “ምስክር እንዲሆን፣ ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል።”
ማቴዎስ 28:19, 20:- “ስለዚህ ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው።”
መዝሙር 96:2:- “ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ ስሙንም ባርኩ፤ ማዳኑንም ነጋ ጠባ አውሩ።”
ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ:- ለዚህ ሥራ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቻለሁ? በዚህ ሥራ የማደርገው ተሳትፎ ያለንበት ጊዜ ወሳኝ ወቅት መሆኑን እንደማምን ያሳያል?