አርዓያ የሚሆኑ ሰዎች—አሳፍ
አሳፍ ግራ የሚያጋባ ሁኔታ አጋጥሞታል። በዙሪያው የሚያያቸው ሰዎች የአምላክን ሕግጋት ቢጥሱም መጥፎ ነገር የሚደርስባቸው አይመስልም! በዚህም የተነሳ አሳፍ፣ አምላክን ለማስደሰት መጣሩ ምንም ዋጋ እንደሌለው ይሰማው ጀመር። “ለካ ልቤን ንጹሕ ያደረግሁት በከንቱ ነው፤ እጄንም በየዋህነት የታጠብሁት በከንቱ ኖሮአል!” አለ። ይሁንና አሳፍ በጉዳዩ ላይ በደንብ ሲያስብበት አመለካከቱን አስተካከለ። ክፉዎች የሚያገኙት ማንኛውም ደስታ ጊዜያዊ እንደሆነ ተገነዘበ። ታዲያ ምን መደምደሚያ ላይ ደረሰ? “በምድርም ከአንተ ሌላ የምሻው [“ደስ የሚያሰኘኝ፣” NW] የለኝም” በማለት ለይሖዋ በመዝሙር ነግሮታል።—መዝሙር 73:3, 13, 16, 25, 27
አንተም የአምላክን መመሪያዎች መከተል ጠቃሚ መሆኑን የተጠራጠርክባቸው ጊዜያት ይኖሩ ይሆናል። ላይ ላዩን የምታየው ነገር አያታልህ፤ ከዚህ ይልቅ እንደ አሳፍ ነገሩን በጥልቅ አስብበት። የይሖዋን ሕግጋት ችላ ያሉ ሰዎች ሕይወታቸው ምን እንደሚመስል አስተውል። እውነት ሰላም አላቸው? እነዚህ ሰዎች፣ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች የማያውቁት ለደስታ ቁልፍ የሆነ ነገር አግኝተዋል? ነገሩን በጥሞና ካሰብክበት አንተም እንደ አሳፍ ‘ለእኔ ግን ወደ አምላክ መቅረብ ይሻለኛል’ እንደምትል ምንም ጥርጥር የለውም።—መዝሙር 73:28