ክፍል 4
የገንዘብ አያያዝ
“መመካከር ሲኖር የታቀደው ነገር ይሳካል።”—ምሳሌ 20:18
ሁላችንም ብንሆን ለቤተሰባችን የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለማሟላት ገንዘብ ያስፈልገናል። (ምሳሌ 30:8) ደግሞም “ገንዘብ ጥበቃ” ያስገኛል። (መክብብ 7:12) ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ስለ ገንዘብ መነጋገር አስቸጋሪ ሊሆን ቢችልም ገንዘብ በትዳራችሁ ውስጥ ችግር እንዲፈጥር አትፍቀዱ። (ኤፌሶን 4:32) ባልና ሚስት ገንዘባቸውን እንዴት ማውጣት እንዳለባቸው በሚወስኑበት ጊዜ እርስ በርስ መተማመንና መተባበር ይኖርባቸዋል።
1 በጥንቃቄ ዕቅድ አውጡ
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ከእናንተ መካከል፣ ግንብ ለመገንባት ፈልጎ ለመጨረስ የሚያስችል በቂ ገንዘብ እንዳለው ለማወቅ በመጀመሪያ ተቀምጦ ወጪውን የማያሰላ ማን ነው?” (ሉቃስ 14:28) ገንዘባችሁን እንዴት እንደምትጠቀሙበት አንድ ላይ ሆናችሁ ዕቅድ ማውጣታችሁ አስፈላጊ ነው። (አሞጽ 3:3) ምን መግዛት እንደሚያስፈልጋችሁና ማውጣት የምትችሉት ምን ያህል እንደሆነ ወስኑ። (ምሳሌ 31:16) አንድን ነገር ለመግዛት የሚያስችል ገንዘብ ስላላችሁ ብቻ የግድ መግዛት ይኖርባችኋል ማለት አይደለም። ዕዳ ውስጥ ላለመግባት ተጠንቀቁ። በእጃችሁ ካለው ገንዘብ በላይ አታውጡ።—ምሳሌ 21:5፤ 22:7
ምን ማድረግ ትችላላችሁ?
አስፈላጊ የሆኑ ወጪዎችን ሁሉ ከሸፈናችሁ በኋላ በተረፈው ገንዘብ ምን እንደምታደርጉበት አንድ ላይ ሆናችሁ ወስኑ
ወጪያችሁ ከገቢያችሁ ከበለጠ ወጪያችሁን ለመቀነስ ምን እንደምታደርጉ ግልጽ የሆነ ዕቅድ አውጡ። ለምሳሌ ያህል፣ ምግብ ቤት በመብላት ፋንታ ቤት ውስጥ ምግብ ማዘጋጀት ትችላላችሁ
2 ግልጽና ምክንያታዊ ሁኑ
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “በይሖዋ ፊት ብቻ ሳይሆን በሰዎችም ፊት ሁሉንም ነገር በሐቀኝነት [አከናውኑ]።” (2 ቆሮንቶስ 8:21) ገቢና ወጪህን በተመለከተ ለትዳር ጓደኛህ ሐቀኛ ሁን።
ከገንዘብ ጋር የተያያዘ ከበድ ያለ ውሳኔ ስታደርግ ምንጊዜም ከትዳር ጓደኛህ ጋር ተመካከር። (ምሳሌ 13:10) ስለ ገንዘብ መነጋገራችሁ በትዳራችሁ ውስጥ ሰላም እንዲኖር ይረዳል። ገቢህን እንደ ግል ገንዘብህ ሳይሆን እንደ ቤተሰቡ ገንዘብ አድርገህ ተመልከተው።—1 ጢሞቴዎስ 5:8
ምን ማድረግ ትችላላችሁ?
አንዳችሁ ሌላውን ሳታማክሩ ምን ያህል ገንዘብ ማውጣት እንደምትችሉ ተነጋግራችሁ ወስኑ
ስለ ገንዘብ ለመነጋገር ችግር እስኪፈጠር አትጠብቁ