ትዕቢት
በንቀት ላይ የተመሠረተ ኩራት፣ የበላይነት ስሜት፣ እብሪት። ትዕቢት የትሕትና ተቃራኒ ነው። “ትዕቢት” እና “ትዕቢተኛ” ተብለው የተተረጎሙት የግሪክኛና የዕብራይስጥ ቃላት “ትልቅ”፣ “ከፍተኛ” እና “የበላይ” መስሎ መታየት የሚል ትርጉም አላቸው። ትዕቢተኛ የሆነ ሰው ከሌሎች ሰዎች ሁሉ የበላይ ወይም ከፍ ያለ እንደሆነ ይሰማዋል። በመሆኑም እንዲህ ያለው ሰው ብዙውን ጊዜ ከተገቢው በላይ ክብርና ትኩረት እንዲሰጠው ይፈልጋል፤ ሌሎችን በንቀት የሚመለከት ከመሆኑም በላይ አክብሮት በጎደለው መንገድ ይይዛቸዋል።
የልብ ሁኔታ። ትዕቢት ከአስተሳሰብ ጋር ብቻ የተያያዘ መጥፎ ባሕርይ አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስ ትዕቢትን ከግድያ፣ ከሌብነት፣ ከስድብና ከሌሎች ክፉ ድርጊቶች ጋር የፈረጀው ሲሆን እንደነዚህ ያሉት ነገሮች “ከውስጥ ይኸውም ከሰው ልብ” እንደሚወጡ ተናግሯል። (ማር 7:21, 22) የኢየሱስ እናት የሆነችው ማርያም “በልባቸው ሐሳብ ትዕቢተኛ የሆኑትንም በትኗቸዋል” በማለት ስለ ይሖዋ ተናግራለች። (ሉቃስ 1:51) ዳዊትም “ልቤ አይኩራራም” በማለት ወደ ይሖዋ ጸልዮአል።—መዝ 131:1፤ ኢሳ 9:9፤ ዳን 5:20
አምላክን በትሕትና ሲያገለግል የቆየ ሰው እንኳ ሀብት ወይም ሥልጣን በማግኘቱ አሊያም በቁንጅናው፣ ባገኘው ስኬት፣ በጥበቡ ወይም ከሌሎች በሚያገኘው ሙገሳ ምክንያት ትዕቢተኛ ሊሆን ይችላል። የይሁዳው ንጉሥ ዖዝያ በዚህ ረገድ ምሳሌ ይሆነናል። ለበርካታ ዓመታት ሕዝቡን በጥሩ ሁኔታ ሲያስተዳድር የይሖዋን በረከት አግኝቶ ነበር። (2ዜና 26:3-5) መጽሐፍ ቅዱስ ከጊዜ በኋላ የሆነውን ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “ይሁን እንጂ ዖዝያ በበረታ ጊዜ ለጥፋት እስኪዳረግ ድረስ ልቡ ታበየ፤ በዕጣን መሠዊያው ላይ ዕጣን ለማጠን ወደ ይሖዋ ቤተ መቅደስ በመግባት በአምላኩ በይሖዋ ላይ ታማኝነት የጎደለው ድርጊት ፈጸመ።” (2ዜና 26:16) ዖዝያ በትዕቢት ተነሳስቶ አምላክ ለእስራኤል ነገሥታት ፈጽሞ የከለከለውን የክህነት ሥራ ለማከናወን ሞክሯል፤ አምላክ ግን የንግሥናና የክህነት ሥራን ለያይቶ አስቀምጧል።
ጥሩ ንጉሥ የነበረው ሕዝቅያስም በአንድ ወቅት ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ልቡ ታብዮ ነበር፤ ይህ ባሕርይ ወደሚገዛው ሕዝብም ተጋብቶ እንደነበር ጥርጥር የለውም። ሕዝቅያስ ስኬታማ መሆን የቻለው ይሖዋ ስለባረከው ነበር፤ ይሁን እንጂ አምላክ ላደረገለት ነገር አድናቆት ማሳየትም ሆነ ለዚያ ሁሉ መመስገን ያለበት ይሖዋ እንደሆነ መቀበል አቃተው። ፀሐፊው ስለ እርሱ ሲጽፍ እንዲህ ብሏል፦ “ይሁንና ሕዝቅያስ ልቡ ታብዮ ስለነበር ለተደረገለት መልካም ነገር አድናቆት ሳያሳይ ቀረ፤ የአምላክም ቁጣ በእሱ፣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ መጣ።” ደስ የሚለው ግን ይህን አደገኛ ዝንባሌ አስወግዷል። ዘገባው በመቀጠል እንዲህ ይላል፦ “ይሁን እንጂ ሕዝቅያስ ስለ ልቡ ትዕቢት ራሱን ዝቅ አደረገ፤ እሱና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ትሕትና አሳዩ፤ የይሖዋም ቁጣ በሕዝቅያስ ዘመን አልመጣባቸውም።”—2ዜና 32:25, 26፤ ከኢሳ 3:16-24 እና ሕዝ 28:2, 5, 17 ጋር አወዳድር።
አምላክ ትዕቢተኞችን ይቃወማል። ትዕቢተኛ ሰዎች በቅን ሰዎች የሚጠሉ ቢሆንም ከዚህ የሚከፋው ይሖዋ አምላክ የሚቃወማቸው መሆኑ ነው። (ያዕ 4:6፤ 1ጴጥ 5:5) ትዕቢት ሞኝነትና ኃጢአት ነው (ምሳሌ 14:3፤ 21:4)፤ ይሖዋም ትዕቢተኞችን ይቃወማል እንዲሁም ዝቅ ያደርጋቸዋል። (2ሳሙ 22:28፤ ኢዮብ 10:16፤ 40:11፤ መዝ 18:27፤ 31:18, 23፤ ኢሳ 2:11, 17) አንድ ሰው የትዕቢት ባሕርይውን ማስወገድ ካልቻለ ጥፋት ያስከትልበታል። በአምላክና በሕዝቦቹ ላይ በትዕቢት የተነሳው የጥንቱ የሞዓብ ብሔር ድምጥማጡ ጠፍቷል። (ኢሳ 16:6፤ 25:10, 11፤ ኤር 48:29) አሥሩን ነገድ ያቀፈው የእስራኤል መንግሥት እንኳ በልቡ በታበየና እብሪተኛ በሆነ ጊዜ ከቅጣት አላመለጠም።—ኢሳ 9:8-12
ራስን ከትዕቢት መጠበቅ። አንድ ሰው በልቡ ውስጥ ትዕቢት እንዳይኖር መጠንቀቅ ይኖርበታል። በተለይ የሚያደርጋቸው ነገሮች ሲሳኩለት ወይም ከፍ ያለ ቦታ ወይም ኃላፊነት ሲሰጠው መጠንቀቅ ይኖርበታል። “ኩራት ጥፋትን፣ የትዕቢት መንፈስም ውድቀትን” እንደሚቀድም መዘንጋት አይኖርበትም። (ምሳሌ 16:18) በውስጡ ትዕቢት እንዲያድግ ከፈቀደ ይህ ባሕርይ ሙሉ በሙሉ ሊቆጣጠረውና አምላክ ተቀባይነት ለሌለው አስተሳሰብ አሳልፎ ከሚሰጣቸው ብሎም ሞት ይገባቸዋል ከሚላቸው ሰዎች ተርታ እንዲመደብ ሊያደርገው ይችላል። (ሮም 1:28, 30, 32) እንዲህ ያለው ማስጠንቀቂያ በተለይ በእነዚህ “በመጨረሻዎቹ ቀናት” መሰጠቱ በጣም አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱ ለመቋቋም አስቸጋሪ በሆነው በዚህ ዘመን ሰዎች ትዕቢተኞች እንደሚሆኑ አስቀድሞ ተነግሯል።—2ጢሞ 3:1, 2
በተጨማሪም የአምላክን ሞገስ ማግኘት የሚፈልግ ሰው ሌሎች የትዕቢት መንፈስ እንዲያድርባቸው ከሚያደርገው ባሕርይ ይኸውም ከሽንገላ መራቅ ይኖርበታል። የምሳሌ መጽሐፍ “ባልንጀራውን የሚሸነግል ሰው፣ ለእግሩ ወጥመድ ይዘረጋበታል” ይላል። (ምሳሌ 29:5) አንድ ሰው ሌሎችን የሚሸነግል ከሆነ በባልንጀራው ላይ ጥፋት ከማስከተሉም በላይ (“የሚሸነግል አንደበትም ጥፋት ያስከትላል”፣ ምሳሌ 26:28) እሱ ራሱ የአምላክን ሞገስ ያጣል። ሐዋርያው ጳውሎስ ከሽንገላ እና ከትዕቢት ለመራቅ ጥረት አድርጓል።—1ተሰ 2:5, 6