የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w91 2/1 ገጽ 15-19
  • የይሖዋ ዋና ወኪል የሆነውን ልጁን ማክበር

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የይሖዋ ዋና ወኪል የሆነውን ልጁን ማክበር
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ሰዎች ኢየሱስን የሚያዋርዱባቸው ሌሎች መንገዶች
  • ልጁን ለማክበር የምንገፋፋባቸው ምክንያቶች
  • ለእኛ ያደረጋቸው ነገሮች
  • ልጁን ልናከብር የምንችለው እንዴት ነው?
  • ይሖዋን ማክበር—ለምንና እንዴት?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ሁሉንም ዓይነት ሰዎች ማክበር
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ሌሎችን አክብሩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ክብር ለሚገባው ክብር ስጡ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2017
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
w91 2/1 ገጽ 15-19

የይሖዋ ዋና ወኪል የሆነውን ልጁን ማክበር

“ወልድን የማያከብር የላከውን አብን አያከብርም።”​—ዮሐንስ 5:23

1. የሕዝበ ክርስትና የሥላሴ ትምህርት ለኢየሱስ ክብር የማይሰጠው እንዴት ነው?

በዛሬው ዘመን በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ያሉ ብዙ ሰዎች ኢየሱስን እንደሚያከብሩ ቢናገሩም የሚያደርጉት ግን የዚህን ተቃራኒ ነው። እንዴት ቢባል ብዙዎቹ ኢየሱስ ሁሉን የሚችለው አምላክ ነው፣ ወደ ምድር መጥቶ ሰው ሆኖ የኖረውና የሞተው ፈጣሪ ራሱ ነው ይላሉ። ይህ አባባል የሕዝበ ክርስትና ዋነኛ ትምህርት በሆነው በሥላሴ መሠረተ ትምህርት ላይ የተመሰረተ ነው። ይሁን እንጂ የሥላሴ ትምህርት ሐሰት ከሆነና ኢየሱስ ከአባቱ ያነሰና የአባቱ ተገዥ ከሆነ በዚህ መንገድ ከአባቱ ጋር ያለውን ዝምድና በተሳሳተ መንገድ ብንረዳ ኢየሱስን አያሳዝነውምን? በእርግጥ በዚህ መንገድ ያለውን ቦታ ማዛባታችን ራሱንም ሆነ እርሱ ያስተማራቸውን ነገሮች ማቃለል ይሆንብናል።

2. ኢየሱስ ከአባቱ ያነሰና የእርሱም ተገዥ መሆኑን ቅዱሳን ጽሑፎች በግልጽ የሚያሳዩት እንዴት ነው?

2 እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ኢየሱስ ሁሉን የሚችል አምላክ ነኝ ብሎ አያውቅም። እንዲያውም እርሱ የአምላክ ልጅ እንደሆነ ደጋግሞ ተናግሮአል። ጠላቶቹ እንኳን ይህን ተረድተውለት ነበር። (ዮሐንስ 10:36፤ 19:7) ኢየሱስ አባቱን ከፍ ለማድረግና ራሱንም ለአባቱ ለማስገዛት ይጠነቀቅ ነበር። ራሱ እንደተናገረው “አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም። ያ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ያደርጋልና። እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም። . . . የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻምና።” እንደገናም “እኔ ግን ከእርሱ ዘንድ ነኝ፣ እርሱም ልኮኛልና” ብሎአል። በተጨማሪም “እኔ ከእግዚአብሔር ወጥቼ መጥቼአለሁና” ብሎአል። (ዮሐንስ 5:19, 30፤ 7:28, 29፤ 8:42) ኢየሱስ ሁሉን የሚችለው አምላክ እንደሆነ ወይም ከአባቱ ጋር እኩል እንደሆነ ያመለከተበት ጊዜ የለም። ስለዚህ እንደዚህ ያለውን ትምህርት ማስተማር ኢየሱስን ማዋረድ ነው።

ሰዎች ኢየሱስን የሚያዋርዱባቸው ሌሎች መንገዶች

3. (ሀ) በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ያሉ አንዳንድ ሰዎች ምን ነገር በመካድ ለኢየሱስ ክብር ሳይሰጡ ቀርተዋል? (ለ) ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት ስለነበረው ሕላዌ ምን ምስክርነት ሰጥቶአል?

3 በዛሬው ዘመን እንግዳ ነገር ቢመስልም ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት ሰማያዊ ሕላዌ እንደነበረው በመካድ ኢየሱስን የሚያዋርዱ ሰዎች በሕዝበክርስትና ውስጥ አሉ። ይሁን እንጂ ኢየሱስን በተገቢ ሁኔታ ልናከብር የምንችለው ቃል በቃል ከሰማይ ወደ ምድር እንደመጣ ስናምን ብቻ ነው። ኢየሱስ ራሱ ሰው ከመሆኑ በፊት በሰማይ ይኖር እንደነበረ ተናግሮአል። “ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም። እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው።” ብሎአል። በኋላም “ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ . . . እንግዲህ የሰው ልጅ አስቀድሞ ወደ ነበረበት ሲወጣ ብታዩ እንዴት ይሆናል?” ብሎአል። እንደገናም “እናንተ ከታች ናችሁ፣ እኔ ከላይ ነኝ። እናንተ ከዚህ ዓለም ናችሁ፣ እኔ ከዚህ ዓለም አይደለሁም . . . እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ፣ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ” ብሎአል። (ዮሐንስ 3:13፤ 6:51, 62፤ 8:23, 58) በተጨማሪም ኢየሱስ አልፎ በተሰጠባት ምሽት ለሰማያዊ አባቱ ባቀረበው ጸሎት ላይ ሰው ከመሆኑ በፊት ሕላዌ እንደነበረው አመልክቶአል።​—ዮሐንስ 17:5

4. (ሀ) ብዙዎች ለኢየሱስ ክብር ሳይሰጡ የቀሩት በምን ሌላ መንገድ ነው? (ለ) ኢየሱስ በእርግጥ የነበረ ሰው ለመሆኑ የትኛው ማስረጃ በቂ ሊሆን ይገባ ነበር? ለምንስ?

4 ኢየሱስ በታሪክ የተረጋገጠና በትክክል በምድር ላይ ይኖር የነበረ ሰው መሆኑን እስከመጠራጠር የሚደርሱ ሰዎች በሕዝበ ክርስትና ውስጥ አሉ። ኢየሱስ ያልነበረ ሰው ከሆነ እንዴትና ለምን እንደምናከብረው መነጋገር ምንም ትርጉም አይኖረውም። ይሁን እንጂ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ተመዝግቦ የምናገኘው የዐይን ምሥክሮች የምሥክርነት ቃል ኢየሱስ በእርግጥ በምድር ላይ የኖረ ሰው መሆኑን በማያጠራጥር ሁኔታ ሊያረጋግጥልን ይገባል። (ዮሐንስ 21:25) በተለይም የጥንት ክርስቲያኖች ስለ ኢየሱስ ያስተምሩ የነበሩት ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ስለነበረ ምሥክርነታቸው በጣም አስተማማኝ ነው። (ሥራ 19:1-4፤ ራዕይ 1:9) ይሁን እንጂ ኢየሱስ በእርግጥ የነበረ ሰው ለመሆኑ ተከታዮቹ ከጻፉት ሌላ ማስረጃ ሊገኝ ይችላል?

5, 6. ከቅዱሳን ጽሑፎች ሌላ የታሪክ ማስረጃ ኢየሱስ ክርስቶስ በእርግጥ በሕይወት የነበረ ሰው ስለመሆኑ ምን ያመለክታል?

5 ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ (1987) እንዲህ ይላል፦ “በጥንት ዘመንም የክርስትና ተቃዋሚዎች እንኳን ኢየሱስ ታሪካዊ ሰው መሆኑን ተጠራጥረው እንደማያውቁ ነፃ ከሆኑ ታሪኮች ማረጋገጥ ተችሎአል።” ከእነዚህ ነፃ ከሆኑ የታሪክ መዛግብት አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው? አይሁዳዊው ምሑር ጆሴፍ ክላውስነር እንደሚሉት የጥንት ታልሙዳዊ ጽሑፎች አሉ። (የናዝሬቱ ኢየሱስ ገጽ 20) የመጀመሪያው መቶ ዘመን የአይሁድ ታሪክ ፀሐፊ የነበረው የጆሴፈስ ምሥክርነትም አለ። ለምሳሌ ያህል ስለ ያዕቆብ መወገር ሲጽፍ ያዕቆብ “ክርስቶስ የተባለው የኢየሱስ ወንድም” እንደሆነ ገልጾአል።​—ጅውሽ አንትክዊቲስ (የአይሁዳውያን የጥንት ታሪክ) XX, [ix, 1]

6 በተጨማሪም የጥንት ሮማውያን ታሪክ ጸሐፊዎች በተለይም በጣም ከፍ ተደርጎ የሚታየው የታሲተስ ማስረጃ አለ። ታሲተስ በሁለተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ “በሚጸየፉአቸው ነገሮች ምክንያት ስለሚጠሉትና ብዙሃኑ ክርስቲያኖች ብለው ስለሚጠሩአቸው ሰዎች” ሲጽፍ “ክርስቲያን የሚለው ቃል መገኛ የሆነው ክርስቶስ በጢባርዮስ ዘመነ መንግሥት ከገዥዎቻችን በአንዱ እጅ የመጨረሻውን አሰቃቂ ቅጣት ተቀብሎአል” ብሎአል። የአሥራ ስምንተኛው መቶ ዓመት የሥነ ምግባር ፈላስፋ የነበረው ፈረንሣዊው ዣንዣክ ሩሶ ኢየሱስ ታሪካዊ ሰው እንደነበረ የሚያረጋግጡ ብዙ ማስረጃዎች መኖራቸውን ተገንዝቦ “ማንም ሊጠራጠር የማይደፍረው የሶቅራጥስ ታሪክ የኢየሱስ ክርስቶስን ያህል የተረጋገጠ አይደለም” ብሎአል።

ልጁን ለማክበር የምንገፋፋባቸው ምክንያቶች

7.(ሀ) ኢየሱስ ክርስቶስን እንድናከብር የሚያስገድደን የትኛው የቅዱሳን ጽሑፎች ማስረጃ ነው? (ለ) ይሖዋ ልጁን በሌላ ተጨማሪ መንገድ እንዴት ክብር ሰጥቶታል?

7 አሁን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ማክበር ጉዳይ እንመለሳለን። የኢየሱስ ተከታዮች እርሱን የማክበር ግዴታ ያለባቸው መሆኑን ራሱ በዮሐንስ 5:22, 23 ላይ ከተናገረው ቃል መረዳት ይቻላል። “ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩት ወልድን ያከብሩት ዘንድ ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ አብ በአንድ ሰው ስንኳ አይፈርድም። ወልድን የማያከብር የላከውን አብን አያከብርም።” ክርስቶስ ከሙታን ከተነሣ ወዲህም ይሖዋ ልጁን ‘እስከሞት ድረስ የታመነ ስለሆነ ክብርና ግርማ አቀዳጅቶ’ የበለጠ ክብር ሰጥቶታል። (ዕብራውያን 2:9፤ 1 ጴጥሮስ 3:22) በመሠረቱ ኢየሱስ ምን ዓይነት ሰው እንደነበረና ምን እንዳደረገ ስናስበው እርሱን ለማክበር የሚያስገድዱ ምክንያቶች እናገኛለን።

8. ኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ሊቀበል የሚገባው በምን ልዩ በሆኑ ምክንያቶች የተነሳ ነው?

8 ኢየሱስ ክርስቶስ ሎጎስ ወይም ቃል እንደመሆኑ መጠን ተተካካይ የሌለው የይሐዋ ቃል አቀባይ ስለሆነ ሊከበር ይገባዋል። “ቃል” የሚለው የኢየሱስ ስያሜ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊትም ሆነ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ የሚጠራበት መሆኑን ከቅዱሳን ጽሑፎች መረዳት ይቻላል። (ዮሐንስ 1 : 1፤ ራዕይ 19:13) በራዕይ 3:14 ላይ ስለራሱ ሲናገር “በእግዚአብሔርም ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው” ብሎአል። እርሱ የፍጥረት ሁሉ መጀመሪያ ከመሆኑም በላይ “አንድያ ልጁ” ስለሆነ ይሖዋ አምላክ በቀጥታ የፈጠረው ኢየሱስን ብቻ ነው። (ቆላስይስ 1:15፤ ዮሐንስ 3:16) በተጨማሪም “ሁሉ በእርሱ ሆነ፣ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም።” (ዮሐንስ 1:3) ስለዚህ በዘፍጥረት 1:26 ላይ አምላክ “ሰውን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር” ሲል ሎጎስን ወይም ቃልን ጨምሮ መናገሩ ነበር። በእርግጥም ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት ከይሖዋ ጋር በፍጥረት ሥራ የመካፈል መብት ማግኘቱ ታላቅ ክብር ሊቀበል የሚገባው ያደርገዋል።

9. ኢየሱስ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ነው ብለን የምንደመድመው ለምንድን ነው? ሚካኤል በሙሴ ሥጋ ረገድ ይሖዋን ያከበረው እንዴት ነው?

9 በተጨማሪም ኢየሱስ የይሖዋ ሊቀመላእክት ወይም የመላእክት አለቃ ስለሆነ ታላቅ ክብር ሊቀበል ይገባዋል። ይህን ለማለት የሚያስችለን ምንድን ነው? “አለቃ” የሚለው ቃል “ዋነኛ” የሚል ትርጉም ስላለው አንድ የመላእክት አለቃ ብቻ መኖሩን ያመለክታል። የአምላክ ቃል ከሙታን የተነሳው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የመላእክት አለቃ እንደሆነ ይናገራል። እንዲህም እናነባለን፣ “ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምጽ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፣ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሳሉ።” (1 ተሰሎንቄ 4:16) ይህ የመላእክት አለቃ በይሁዳ 9 ላይ እንደምናነበው ስም አለው። “የመላእክት አለቃ ሚካኤል ግን ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ስለ ሙሴ ሥጋ ሲነጋገር [ይሖዋ(አዓት)] ይገሥጽህ አለው እንጂ የስድብን ፍርድ ሊናገረው አልደፈረም።” ኢየሱስ በዲያብሎስ ላይ የቅጣት ፍርድ በማምጣት ከይሖዋ ቀድሞ እርምጃ ባለመውሰድ ሰማያዊ አባቱን አክብሮአል።

10. (ሀ) ሚካኤል ለአምላክ መንግሥት በግንባር ቀደምነት የተዋጋው እንዴት ነው? (ለ) ሚካኤል ለእስራኤል ሕዝብ ምን የሥራ ድርሻ አበርክቶአል?

10 የመላእክት አለቃ ሚካኤል ሰማያትን ከሠይጣንና ከአጋንንታዊ ጭፍሮቹ በማጽዳት ለአምላክ መንግሥት ግንባር ቀደም ሆኖ ተዋግቷል። (ራዕይ 12:7-10) ነቢዩ ዳንኤልም ‘ለአምላክ ሕዝብ እንደሚቆም’ ተናግሮአል። (ዳንኤል 12:1) ስለዚህ “በእስራኤል ሠራዊት ፊት ይሄድ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ”፣ አምላክ ሕዝቦቹ ወደ ተስፋይቱ ምድር ለማምጣት የተጠቀመበት መልአክ ሚካኤል ሳይሆን አይቀርም። አምላክ “በፊቱ ተጠንቀቁ፣ ቃሉንም አድምጡ፣ ስሜም በእርሱ ስለሆነ” በማለት አዝዞ ነበር። (ዘፀአት 14:19፤ 23:20, 21) የይሖዋ ሊቀመላእክት በይሖዋ ስም ስለተጠሩት የጥንት ሕዝቦቹ አጥብቆ ያስብ እንደነበረ አያጠራጥርም። ነቢዩ ዳንኤልን ለማጽናናት ሲሄድ በኃይለኛ ጋኔን ታግዶ የቆየውን መልአክ መርዳቱ ተገቢ ነበር። (ዳንኤል 10:13) ስለዚህ የሰናክሬብን 185,000 ጦረኞች የገደለው ከመላእክት አለቃ ሚካኤል ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ሊሆን ይችላል።​—ኢሳይያስ 37:36

11. ኢየሱስ ክብር ሊሰጠው የሚገባው በምድር ሳለ እንዴት ያለ አኗኗር ስለኖረ ነው?

11 ኢየሱስ ክርስቶስ መከበር የሚገባው ስለማንነቱ ብቻ ሳይሆን ስላደረጋቸውም ነገሮች ጭምር ነው። ለምሳሌ ፍጹም ሕይወት የኖረ ሰው ከኢየሱስ በቀር ማንም የለም። አዳምና ሔዋን ፍጹም ሆነው ቢፈጠሩም እንኳን ፍጽምናቸው በአጭሩ ተቀጭቶ ቀርቶአል። ኢየሱስ ግን ከዲያብሎስ ብዙ ፈተናና ስደት ቢደርስበትም ‘ታማኝ፣ ነውር የሌለበትና ከኃጢአተኞች የተለየ’ ሆኖ እስከ መጨረሻው ጸንቷል። በደረሰበት ነገር ሁሉ “ኃጢአት አልሰራም፤ ከአፉም ነውር አልተገኘበትም።” ሃይማኖታዊ ተቃዋሚዎቹን “ከእናንተ ስለ ኃጢአት የሚከሰኝ ማነው?” ለማለት ችሎአል። አንዳቸውም ሊከሱት አልቻሉም። (ዕብራውያን 7:26፤ 1 ጴጥሮስ 2:22፤ ዮሐንስ 8:46) ኢየሱስ ከኃጢአት ርቆ ንጹሕ አቋሙን በመጠበቁ ሰማያዊ አባቱ ትክክለኛ የጽንፈ ዓለሙ የበላይ ገዥና ሰይጣንም ወራዳ ቀጣፊ ውሸታም መሆኑን አረጋግጦአል።​—ምሳሌ 27:11

12. ኢየሱስ እንዴት ያለ ሰው ነበር? ለሌሎች ሲል ምን አድርጎአል? ምንስ ደርሶበታል? (ለ) ኢየሱስ ስላደረጋቸውና ስለተቀበላቸው መከራዎች ሊከበር ይገባዋል የምትለው ለምንድን ነው?

12 ኢየሱስ ክርስቶስን ማክበር የሚገባን ፍጹምና ኃጢአት የሌለበት ሕይወት ስለኖረ ብቻ ሳይሆን ራስወዳድነት የሌለበት ጥሩ ሰው፣ ራሱን መሥዋዕት የሚያደርግ ሰው ስለነበረ ጭምር ነው። (ከሮሜ 5:7 ጋር አወዳድር) ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ለሰዎች መንፈሣዊና ሥጋዊ ፍላጎት አገልግሎአል። ለአባቱ ቤት ከፍተኛ ቅንዓት እንዳለው አሳይቶአል። ደቀመዛሙርቱንም በጣም ታግሶአል። የአባቱን ፈቃድ ለማድረግ ሲል ከፍተኛ መከራ ለመቀበል ፈቃደኛ ሆኖአል። መጽሐፍ ቅዱስ በጌቴሰማኒ ስለደረሰበት ሥቃይ ሲናገር “ሲጣጣር አጽንቶ ይጸልይ ነበር። ወዙም በምድር ላይ እንደሚወርድ እንደ ደም ነጠብጣብ ነበረ” ይላል። አዎን፣ “ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎት ገና ምልጃን አቀረበ።” (ሉቃስ 22:44፤ ዕብራውያን 5:7) ነቢዩ ኢሳይያስ በኢሳይያስ 53:3-7 ላይ የደረሰበትን መከራ ሁሉ በጣም ትክክል በሆነ ሁኔታ ተንብዮ ነበር።

13. ኢየሱስ ሰማያዊ አባቱን በማክበር ረገድ ምን ምሳሌ ትቶልናል?

13 በተጨማሪም ኢየሱስ ሰማያዊ አባቱን በማክበር ረገድ ጥሩ ምሳሌ ስለተወልን ልናከብረው ይገባናል። “አባቴን አከብራለሁ” ለማለት ችሎ ነበር። (ዮሐንስ 8:49) በማንኛውም ጊዜ በንግግሩም ሆነ በድርጊቶቹ ይሖዋ አምላክን አስከብሮአል። በዚህም ምክንያት አንድ ሰው በፈወሰ ጊዜ ሰዎቹ ኢየሱስን ሳይሆን ‘እግዚአብሔርን እንዳከበሩ’ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። (ማርቆስ 2:12) ስለዚህም ምድራዊ አገልግሎቱን በጨረሰበት ጊዜ ለሰማያዊ አባቱ ሲጸልይ “ላደርገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር አከበርሁህ” ለማለት ችሎ ነበር። ​—ዮሐንስ 17:4

ለእኛ ያደረጋቸው ነገሮች

14. ኢየሱስ ሊከበር የሚገባው ሞቱ ምን ውጤት ስላስገኘልን ነው?

14 ኢየሱስ ክርስቶስ ላደረገልን ታላላቅ ነገሮች ሁሉ ሊከበር ይገባዋል። ከይሖዋ አምላክ ጋር እንድንታረቅ ለማስቻል ለኃጢአታችን ሞቶአል። ኢየሱስ ስለራሱ ሲናገር፣ “የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም” ብሎአል። (ማቴዎስ 20:28) ስለዚህ መንግሥቲቱ ለሰው ልጆች የምታደርግላቸው ነገሮች በሙሉ ሊገኙ የቻሉት፣ የሙሽራው ክፍል አባላት የሚሆኑት 144, 000 ቅቡዓን በሰማይ ሞት የማይደፍረው ሕይወት የሚሰጣቸው፣ እምነታቸውንና ታዛዥነታቸውን በፈተና ያረጋገጡ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች በገነቲቱ ምድር የዘላለም ሕይወት የሚያገኙት ኢየሱስ ስለሞተ ነው።​—መዝሙር 37:29፤ ራዕይ 14:1-3፤ 21:3, 4

15. ኢየሱስ የአባቱን ባሕርይ ከገለጸባቸው መንገዶች አንዱ የትኛው ነው?

15 በተጨማሪም ኢየሱስ ክርስቶስ ታላቅ አስተማሪ እንደመሆኑ መጠን የአባቱን ፈቃድና ባሕርይ ፍጹም በሆነ ሁኔታ ስለገለጸልን ሊከበር ይገባዋል። ለምሳሌ ያህል በተራራ ስብከቱ ላይ አባቱ ለጻድቃንም ለኃጢአተኞችም ፀሐይና ዝናብ እኩል በመስጠቱ ልበ ሰፊ መሆኑን ከገለጸ በኋላ “እንግዲህ የሰማዩ አባታችሁ ፍጹም እንደሆነ እናንተም ፍጹማን ሁኑ” ብሎአል።​—ማቴዎስ 5:44-48

16. ጳውሎስ ክብር ሊሰጠው የሚገባውን የኢየሱስ አኗኗር አጠቃልሎ የገለጸው እንዴት ነው?

16 ሐዋርያው ጳውሎስ የሚከተለውን በመጻፍ ክብር ሊሰጠው የሚገባውን የኢየሱስ አኗኗር አጠቃልሎ ገልጾአል፦ “በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን። እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቆጠረውም። ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ። በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፣ ለሞትም ይኸውም [የመከራ እንጨት(አዓት)] እንኳን የታዘዘ ሆነ።”​—ፊልጵስዮስ 2:5-8

ልጁን ልናከብር የምንችለው እንዴት ነው?

17, 18. ኢየሱስን ለማክበር የምንችለው በምን የተለያዩ መንገዶች ነው?

17 ኢየሱስ ክርስቶስ ሊከበር የሚገባው መሆኑ የማያጠራጥር ስለሆነ ልጁን ልናከብር የምንችለው እንዴት ነው ወደሚለው ጥያቄ እንመጣለን። ልጁን የምናከብረው በቤዛዊ መሥዋዕቱ በማመን ነው። ይህንንም እምነታችንን የምናረጋግጠው አስፈላጊ የሆኑትን የንሥሐ፣ የመለወጥ፣ ራስን የመወሰንና የመጠመቅ እርምጃ በመውሰድ ነው። በኢየሱስ ስም ወደ ይሖዋ በጸሎት በመቅረብ ኢየሱስን እናከብረዋለን። ከዚህም በላይ “እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ [የመከራውንም እንጨት (አዓት)] ተሸክሞ ይከተለኝ” የሚለውን ቃሉን በመከተል እናከብረዋለን። (ማቴዎስ 16:24) የአምላክን መንግሥትና ጽድቁን አስቀድመን እንድንፈልግ የሰጠውን መመሪያ ስንከተል፣ ደቀመዛሙርት በማድረግ ሥራ እንድንካፈል የሰጠውን ትዕዛዝ ስንፈጽም ኢየሱስ ክርስቶስን እናከብራለን። እንደገናም ኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮቹን ለይቶ የሚያሳውቅ ምልክት እንደሆነ የተናገረለትን የወንድማማች ፍቅር ስናሳይ ኢየሱስን እናከብራለን።​—ማቴዎስ 6:33፤ 28:19, 20፤ ዮሐንስ 13:34, 35

18 ከዚህም በላይ ስሙን በመሸከም፣ ራሳችንን ክርስቲያን ብለን በመጥራትና ከዚህም ስም ጋር በሚስማማ አኗኗር በመኖር ለልጁ ክብር እናመጣለን። (ሥራ 11:26፤ 1 ጴጥሮስ 2:11, 12) ሐዋርያው ጴጥሮስ የኢየሱስን ፈለግ እንድንከተል መክሮናል። (1 ጴጥሮስ 2:21) ስለዚህ በጠባያችንና በአኗኗራችን ሁሉ እርሱን ስንመስል እናከብረዋለን። ከዚህም በላይ የክርስቶስን ሞት መታሰቢያ በየዓመቱ ስናከብር የተለየ ክብር እንሰጠዋለን።​—1 ቆሮንቶስ 11:23-26

19, 20. (ሀ) ኢየሱስ ተከታዮቹ ስላከበሩት አሁንና ወደፊት ምን ሽልማት ይሰጣቸዋል? (ለ) በልጁ ረገድ ምን ትምክህት ሊኖረን ይችላል?

19 ኢየሱስ ደቀመዛሙርቱ እርሱን በሚያስከብር አኗኗር በመኖራቸው ምን ሽልማት ይሰጣቸዋል? እንዲህ ብሎአል፣ “እውነት እላችኋለሁ፣ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እህቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን ወንድሞችን እህቶችን እናቶችንም ልጆችንም እርሻንም መቶ እጥፍ፣ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም።”​—ማርቆስ 10:29, 30

20 ለኢየሱስ ብለን ምንም ዓይነት መሥዋዕትነት ብንከፍል ተገቢውን ሽልማት እንድናገኝ ያደርጋል ማለት ነው። ኢየሱስ የሚከተለውን ዋስትና ይሰጠናል፦ “ስለዚህ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ።” (ማቴዎስ 10:32) ስለዚህ ሰማያዊው አባት የሚያከብሩትን እንደሚያከብር ሁሉ የይሖዋ አንድያ ልጅም በሌሎች ነገሮች አባቱ የሚያደርገውን እንደሚያደርግ በዚህ ረገድም አባቱን በመምሰል የሚያከብሩትን ያከብራል።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

◻ በሕዝበክርስትና ውስጥ ያሉ ብዙ ሰዎች ኢየሱስን የሚያዋርዱት እንዴት ነው?

◻ ኢየሱስ ስለ ቅድመ ሰብዓዊ ሕልውናው ምን ምስክርነት ሰጥቶአል?

◻ ኢየሱስን እንድናከብር የሚያደርጉን አንዳንድ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

◻ ኢየሱስን ማክበራችንን ከምናሳይባቸው መንገዶች አንዳንዶቹ ምንድ ናቸው?

◻ ኢየሱስን ማክበር ምን ጥቅሞችን ያስገኛል?

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ