መበለት ሆኜ ስኖር እውነተኛ መጽናናት አገኘሁ
በሊሊ አርተር እንደተነገረው
በሕንድ አገር ኦወታካመንድ በሚባል ክልል አንድ ወጣት የይሖዋ ምስክር የሆነ አገልጋይ ከቤት ወደ ቤት ያንኳኳ ነበር። በባሕሉ መሠረት ሴቶች ለአንድ የማይታወቅ እንግዳ ሰው በር አይከፍቱም። ከጥቂት ሰዓቶች በኋላ ደክሞትና ተስፋም እንደመቁረጥ ብሎ ወደ ቤቱ ሊሄድ ፊቱን አቀና። ይሁን እንጂ ቀጥሎ ያለውን በር እንዲያንኳኳ ውስጣዊ ስሜቱ ስለገፋፋው ቆመ። እስቲ ስለሆነው ነገር በሩን የከፈተችለት ሴት የገለጸችውን እንመልከት።
የሁለት ወር ሕፃን ሴት ልጄን በእጆቼ ታቅፌና የ22 ወር ወንድ ልጄን ከጎኔ አድርጌ በሩን ወዲያው ከፈትኩ፤ ከደጃፉም አንድ እንግዳ ሰው ቆሞ አየሁ። ከዚያ ዕለት በፊት በነበረው ምሽት ከመጠን በላይ ተክዤ ነበር። መጽናናት በመፈለግ “ሰማያዊ አባት በቃልህ አማካኝነት አጽናናኝ” ብዬ ጸልዬ ነበረ። እንዲያውም ይግረምሽ ብሎ እንግዳው ሰው “ከአምላክ ቃል የመጽናናትና የተስፋ መልእክት ይዤልሽ መጥቻለሁ” ሲል ገለጸልኝ። በአምላክ የተላከ ነቢይ እንደሆነ ተሰማኝ። ይሁንና ለእርዳታ እንድጸልይ ያነሣሣኝ ሁኔታ ምን ነበር?
የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መማር
በደቡብ ሕንድ ውስጥ በኒልጊሪ ውብ ተራሮች በተከበበች ጉዳለር በምትባል ገጠር ውስጥ በ1922 ተወለድኩ። እናቴ እኔ ገና የሦስት ዓመት ሕፃን ሆኜ ሞተች። በኋላም የፕሮቴስታንት ቄስ የነበረው አባቴ ሌላ ሴት አገባ። መናገር ስንችል አባቴ ወዲያውኑ ወንድሞቼን፣ እኅቶቼንና እኔን መጸለይ አስተማረን። በአራት ዓመቴ አባቴ በወንበሩ ላይ ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስ ሲያነብ እኔም በወለሉ ላይ ተቀምጬ መጽሐፍ ቅዱሴን አነብ ነበር።
ሳድግ መምህር ሆንኩ። ከዚያም ዕድሜዬ 21 ዓመት ሲደርስ አባቴ ዳረኝ። ባሌና እኔ ሳንዶር የሚባል ወንድ ልጅና ራትና የምትባል ሴት ልጅ በማግኘት ተባረክን። ራትና በተወለደችበት ጊዜ ባሌ በጠና ታመመና ወዲያው ሞተ። በ24 ዓመት ዕድሜዬም ሁለት ትናንሽ ልጆች ከማሳደግ ኃላፊነት ጋር በድንገት መበለት ሆንኩ።
ከዚያ በኋላ በቃሉ እንዲያጽናናኝ አምላክን ለመንኩ፤ የይሖዋ ምስክር የሆነው አገልጋይ በሬን ያንኳኳው በማግስቱ ነበር። ወደ ቤቴ አስገባሁትና “እግዚአብሔር እውነተኛ ይሁን” የሚለውን መጽሐፍ ተቀበልኩ። በዚያ ሌሊት መጽሐፉን ሳነብ ለእኔ እንግዳ የሆነ ይሖዋ የሚባለውን ስም እመለከት ጀመር። በኋላም አገልጋዩ ተመልሶ ሲመጣ ይህ ስም የአምላክ ስም መሆኑን ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳየኝ።
ወዲያውም እንደ ሥላሴና የሲኦል እሳት የመሳሰሉት ትምህርቶች መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት እንደሌላቸው ተማርኩ። በአምላክ መንግሥት ስር ምድር ገነት እንደምትሆንና በሞት የተለዩን የምናፈቅራቸው ሁሉ በትንሣኤ እንደሚመለሱ ስማር መጽናናትና ተስፋ አገኘሁ። ከሁሉ በላይ ግን ጸሎቴን የሰማውንና ለርዳታ የደረሰልኝን እውነተኛ አምላክ ይሖዋን ማወቅና መውደድ ጀመርኩ።
አዲስ ያገኘሁትን እውቀት ለሌሎች ማካፈል
እነዚያን የአምላክ ስም ያለባቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች እንዴት ሳላነብ እንዳለፍኳቸው ይገርመኝ ጀመር። እንደዚሁም ግልጽ የሆነውን በገነት ምድር የዘላለም ሕይወት ተስፋ ከግል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቤ ያልተረዳሁት ለምን ነበር? የማስተምረው በፕሮቴስታንት ሚስዮናውያን በሚካሄድ ትምህርት ቤት ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶቹን ለትምህርት ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አሳየኋት። (ዘፀዓት 6:3፤ መዝሙር 37:29፤ 83:18፤ ኢሳይያስ 11:6-9፤ ራእይ 21:3, 4) እነዚህን ጥቅሶች ሳናስተውላቸው የቀረን መሆኑንም ጠቀስኩ። ይሁን እንጂ ደስ አለመሰኘቷ አስገረመኝ።
ከዚያም በሌላ ከተማ ለምትኖረው ዲሬክተር እነዚህን ጥቅሶች ጠቅሼ ጻፍኩላት። ከሷ ጋር ለመነጋገር አጋጣሚ እንዳገኝም ጠየቅኋት። የሰጠችኝ መልስ በእንግሊዝ አገር እውቅ የሆነው ቄስ ማለትም አባቷ ስለ ጉዳዩ ከእኔ ጋር እንደሚወያይ የሚገልጽ ነበር። የዲሬክተሯ ወንድም ታዋቂ የሆነ ጳጳስ ነበር።
ሁሉንም ነጥቦችና ጥቅሶች አዘጋጅቼ “እግዚአብሔር እውነተኛ ይሁን” የሚለውን መጽሐፌንና ልጆቼን ይዤ ወደሚቀጥለው ከተማ ሄድኩ። በከፍተኛ ስሜት ይሖዋ ማን መሆኑን፣ ሥላሴ እንደሌለና ሌሎችም የተማርኳቸውን ነገሮች አስረዳሁ። አዳመጡኝ፤ ግን አንዲትም ቃል አልተነፈሱም። ከዚያም ከእንግሊዝ አገር የመጣው ቄስ “እጸልይልሻለሁ” አለና ከጸለየልኝ በኋላ ተመለስኩ።
ከመንገድ ወደ መንገድ መመስከር
አንድ ቀን የይሖዋ ምስክሮች አገልጋይ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ መጽሔቶችን ይዤ ከመንገድ ወደ መንገድ እንድመሰክር ጋበዘኝ። ያ ፈጽሞ ላደርገው የማልችለው ነገር መሆኑን ነገርኩት ምክንያቱም በሕንድ ውስጥ ሰዎች በመንገድ ላይ ስለምትቆም ወይም ከቤት ወደ ቤት ስለምትሄድ ሴት በጣም መጥፎ ነገር ያስባሉ። በሴቲቱ ስም ላይ እንዲሁም በቤተሰብዋም ስም ላይ ሳይቀር ስድብ ያመጣል። አባቴን በጥልቅ እወደውና አከብረው ስለነበር በስሙ ላይ ስድብ ላመጣበት አልፈለግሁም።
ይሁን እንጂ አገልጋዩ “ልጄ ሆይ፣ ጠቢብ ሁን፤ ልቤንም ደስ አሰኘው፤ ለሚሰድበኝ መልስ መስጠት ይቻለኝ ዘንድ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አሳየኝ። (ምሳሌ 27:11) “አንቺም ለይሖዋና ለመንግሥቱ መሆንሽን በሕዝብ ፊት በማሳየት ልቡን ደስ ታሰኚያለሽ” አለኝ። ከምንም ነገር በላይ የይሖዋን ልብ ደስ ለማሰኘት በመፈለግ መጽሔቶቹን የያዘውን ቦርሳ ይዤ ከሱ ጋር ከመንገድ ወደ መንገድ ለመመስከር ሄድኩ። እስካሁንም እንኳ እንዴት እንዳደረግሁት ሳስበው ይገርመኛል። ያም የሆነው ከአገልጋዩ ጋር መጀመሪያ ከተገናኘን ከአራት ወር በኋላ በ1946 ነበር።
ፍርሃትን ለማሸነፍ መበረታታት
በ1947 በምሥራቃዊ ሕንድ ባሕር ዳርቻ የምትገኝ ማድራስ የምትባል ከተማ አካባቢ አስተማሪ ሆኜ ከልጆቼ ጋር ወደዚያ ተዛወርኩ። ስምንት የሚሆኑ ይሖዋ ምስክሮች ቡድን በከተማዋ አዘውትረው ይሰበሰባሉ። በእነዚያ ስብሰባዎች ለመካፈል 25 ኪሎ ሜትሮች መጓዝ ነበረብን። በዚያ ዘመን በሕንድ ውስጥ ሴቶች አብዛኛውን ጊዜ ብቻቸውን አይጓዙም ነበር። እንዲያደርሷቸው በወንዶች ላይ ይመኩ ነበር። አውቶቡስ ላይ እንዴት እንደምወጣ፣ ቲኬት እንዴት እንደምጠይቅ፣ ከአውቶቡሱ ላይ እንዴት እንደምወርድ ወዘተ አላውቅም ነበር። ይሖዋን ማገልገል እንዳለብኝ ይሰማኛል፤ ግን እንዴት እንደማገለግለው ተቸገርኩ። ስለዚህ እንዲህ ስል ጸለይኩ። “ይሖዋ አምላክ አንተን ሳላገለግል መኖር አልችልም። ይሁን እንጂ እንደ አንዲት ሕንዳዊት ሴት መጠን ከቤት ወደ ቤት መሄድ ለእኔ ፈጽሞ የማይቻል ነው።”
ከዚህ ግጭት ለመገላገል ይሖዋ እንድሞት ያደርገኛል ብዬም ተስፋ አደረግሁ። ይሁን እንጂ ከመጽሐፍ ቅዱስ አንድ ነገር ለማንበብ ወሰንኩ። መጽሐፍ ቅዱሴን ስከፍት እንዳጋጣሚ “ወደምሰድህ ሁሉ ዘንድ ትሄዳለህና፣ የማዝዝህንም ሁሉ ትናገራለህና:- ብላቴና ነኝ አትበል። እኔ አድንህ ዘንድ ከአንተ ጋር ነኝና ከፊታቸው አትፍራ” የሚለውን ከኤርምያስ መጽሐፍ አነበብኩ።—ኤርምያስ 1:7, 8
ይሖዋ ራሱ እየተናገረኝ እንዳለ ተሰማኝ። ስለዚህ ተበረታታሁና ወዲያውኑ ወደ ስፌት መኪናዬ ሄጄ መጽሔቶች የምይዝበት ቦርሳ ሰፋሁ። ልባዊ ጸሎት ካቀረብኩ በኋላ ብቻዬን ከቤት ወደ ቤት ሄድኩና ጽሑፎቼን ሁሉ አበርክቼ እንዲያውም ያንኑ ዕለት የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀምሬ አደርኩ። ለይሖዋ በሕይወቴ የመጀመሪያውን ቦታ ልሰጠው ቆረጥኩ፤ ሙሉ እምነቴንና ትምክህቴን በሱ ላይ ጣልኩ። ስድብ ቢደርስብኝም የሕዝባዊ ስብከቱ ሥራ የዕለታዊ ሕይወቴ ክፍል ሆነ። ተቃውሞ ቢኖርም ሥራዬ በአንዳንዶች ዘንድ ጥልቅ አድናቆትን አተረፈ።
ይህም ግልጽ የሆነው ከብዙ ዓመታት በኋላ በማድራስ ከተማ ከሴት ልጄ ጋር ከቤት ወደ ቤት በሄድንበት ጊዜ ነበር። የከፍተኛው ፍርድ ቤት ዳኛ የሆነ የሒንዱ ታላቅ ሰው ዕድሜዬን አሳንሶ በመገመት “እነዚህን መጽሔቶች ገና አንቺ ከመወለድሽ በፊት ጀምሮ አውቃቸዋለሁ። ከ30 ዓመታት በፊት አንዲት ወይዘሮ በማውንት ጎዳና ላይ አዘውትራ በመቆም ታበረክታቸው ነበር” አለኝ። ኮንትራት መግባት ፈለገ።
በሌላ ቤት አንድ ጡረታ የወጣ ባለ ሥልጣን የሆነ የሒንዱ ብራህማን ወደ ቤቱ እንድንገባ ጋበዘንና እንዲህ አለ፦ “ከብዙ ዓመታት በፊት አንዲት ወይዘሮ በማውንት ጎዳና ላይ ሆና መጠበቂያ ግንብ መጽሔት ታበረክት ነበር። አሁንም እናንተ የምትሰጡኝን ለሷ ያለኝን አክብሮት ለመግለጽ ስል እወስዳለሁ።” ሁለቱም የጠቀሷት ወይዘሮ እኔ መሆኔን ስለማውቅ ሳቅሁ።
ተጠናከርኩ ተባረክሁም
ሕይወቴን ለይሖዋ መወሰኔን በውኃ ጥምቀት የገለጽኩት ጥቅምት 1947 ነበር። በወቅቱ በአገሪቱ በሙሉ የታሚል ቋንቋ ተናጋሪ የሆንኩት የይሖዋ ምስክር እኔ ብቻ ነበርኩ። አሁን ግን በመቶ የሚቆጠሩ ታሚል ተናጋሪ ሴቶች ታማኝና ንቁ የይሖዋ ምስክሮች ናቸው።
ከተጠመቅሁ በኋላ ተቃውሞ ከሁሉም አቅጣጫዎች መጡብኝ። ወንድሜ እንዲህ ሲል ጻፈ፦ “ከማንኛውም ስነ ሥርዓትና መልካም ምግባር ወጥተሻል።” ከምሠራበት ትምህርት ቤትና ከማኅበረሰቡም ተቃውሞ ደረሰብኝ። ይሁን እንጂ በማያቋርጥ ልባዊ ጸሎት ይበልጡን ከይሖዋ ጋር ተጣበቅሁ። ሌሊት ከነቃሁ የፋኖስ መብራቴን አበራና መጽሐፍ ቅዱስ አጠናለሁ።
እየተጠናከርኩ በሄድኩ መጠን ሌሎችን ለማጽናናትና ለመርዳት በምችልበት የተሻለ አቋም ላይ ደረስኩ። እኔ ያስጠናኋት አንዲት በዕድሜ የገፋች የሒንዱ ሴት ለይሖዋ አምልኮ ጽኑ አቋም ወሰደች። እሷ ስትሞት በቤተሰቡ ውስጥ ያለች አንዲት ሌላ ሴት እንዲህ አለች፦ “በጣም ያስደሰተን ልታመልከው ለመረጠችው አምላክ እስከ መጨረሻው ያሳየችው ታማኝነት ነበር።”
ሌላዋ አስጠናት የነበረች ሴት ፈጽሞ ፈገግ ብላ የማታውቅ ነበረች። ዘወትር በፊቷ ላይ የሚታየው ጭንቀትና ኀዘን ነበር። ስለ ይሖዋ ካስተማርኳት በኋላ ግን እሱ ችግራችንን ስለሚያውቅና ስለሚያስብልን ወደሱ እንድትጸልይ አበረታታኋት። በሚቀጥለው ሳምንት ፊቷ ያበራ ነበር። ፈገግ ስትል ያየኋት ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ቀን ነበር። “ወደ ይሖዋ ስጸልይ ነበር፤ ስለዚህ የአእምሮና የልብ ሰላም አገኘሁ” ስትል ገለጸችልኝ። ሕይወቷን ለይሖዋ ወሰነች። ብዙ ችግሮች ቢኖሩባትም ታማኝ ሆና ቀጥላለች።
ኃላፊነቶችን በሚዛናዊነት ማጠናቀቅ
ሁለት ትናንሽ ልጆችን ከማሳደግ ጋር ይሖዋን አቅኚ ሆኜ ሙሉ ጊዜዬን የማገልገል ፍላጎቴን ከግቡ ማድረስ የማይመስል ሆኖ ይሰማኝ ነበር። ይሁን እንጂ ያን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ወደ ታሚል ቋንቋ የሚተረጉም ሰው ባስፈለገ ጊዜ አዲስ የአገልግሎት በር ተከፈተ። በይሖዋ እርዳታ ይህን ሥራ ከመምህርነት ሥጋዊ ሥራዬ፣ ልጆቼን ከመንከባከብ፣ የቤት ውስጥ ሥራዬን ከመሥራት፣ በሁሉም ስብሰባዎች ላይ ከመገኘትና በመስክ አገልግሎት ከመካፈል ጋር ልሠራ ችያለሁ። በመጨረሻም ልጆቼ ትልልቆች ከሆኑ በኋላ ልዩ አቅኚ ሆንኩ። ይህም ባለፉት ሠላሳ ሦስት ዓመታት ስካፈልበት የቆየሁበት ሥራ ነው።
ሳንደርና ራትና ገና ጨቅላ በነበሩበት ጊዜም እንኳ ሳይቀር ለይሖዋ ፍቅርንና በማንኛውም የሕይወታቸው ገጽታ የይሖዋን ፈቃድ የማስቀደምን ፍላጎት ላሳድርባቸው እሞክር ነበር። ጧት ከእንቅልፋቸው ገና ሲነቁ መጀመሪያ የሚያናግሩት እሱን መሆኑንና ማታ ከመተኛታቸው በፊትም ሊያናግሩት የሚገባቸው የመጨረሻው እሱ መሆኑን ያውቁ ነበር። እንዲሁም ለትምህርት ቤት የቤት ሥራ ተብሎ ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎችና ለመስክ አገልግሎት የሚያደርጉት ዝግጅት ችላ ሊባል እንደማይገባው ያውቁ ነበር። በትምህርት ቤት ሥራቸው የተቻላቸውን ያህል እንዲሠሩ ባበረታታቸውም እርሱን በሕይወታቸው ውስጥ ከሁሉ የበለጠው አስፈላጊ ነገር እንደሆነ አድርገው እንዳያዩት በመፍራት ከፍተኛ ውጤት እንዲያመጡ ጎትጉቻቸው አላውቅም።
ከተጠመቁ በኋላ ትምህርት ቤት የሚዘጋበትን ጊዜ በአቅኚነት ለማገልገል ይጠቀሙበት ነበር። ራትና እኔ በፊት እንደነበርኩት ዓይነት ፈሪና ዓይናፋር ሳትሆን ደፋር እንድትሆን አበረታታት ነበር። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷንና የንግድ ሥልጠናዋን ከጨረሰች በኋላ አቅኚነት ጀመረች፤ በኋላም ልዩ አቅኚ ሆነች። ከጊዜ በኋላ ተጓዥ የበላይ ተመልካች የነበረውንና አሁን በሕንድ ላለው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በቅርንጫፍ ኮሚቴ አስተባባሪነት እየሠራ ያለውን ሪቻርድ ገብርኤልን አገባች። እነሱና ሴት ልጃቸው አቢጋኤል በሕንድ ቅርንጫፍ ቢሮ ሙሉ ጊዜ ይሠራሉ። ትንሹ ወንድ ልጃቸው አንድሩ ደግሞ የምሥራቹ አስፋፊ ነው።
ሳንደር በ18 ዓመት ዕድሜው ከይሖዋ ምስክሮች ጋር መተባበሩን ባቆመ ጊዜ ቅስሜን ሰበረው። ተከታዮቹ ዓመታት ለእኔ የሥቃይ ዓመታት ነበሩ። እርሱን ሳሳድግ ምናልባት የሠራሁት ስሕተት ካለ ይቅር እንዲለኝና ልጁንም ወደ ልቡ እንዲመልስልኝ ይሖዋን ያለማቋረጥ ለመንኩት። ከጊዜ በኋላ ግን ተስፋ ቆረጥኩ። ከዚያም ከ13 ዓመታት በኋላ መጣና “እማማ አይዞሽ ደህና እሆናለሁና አትጨነቂ” አለኝ።
ከዚያ በኋላ ወዲያውኑ ሳንደር በመንፈሳዊ የጎለመሰ ሰው ለመሆን የተለየ ጥረት አደረገ። የይሖዋ ምስክሮች ጉባኤ የበላይ ተመልካች እስከ መሆን ድረስ መሻሻል አደረገ። በኋላም አቅኚ ለመሆን ጥሩ ክፍያ የሚያገኝበትን ሥራውን ለቀቀ። ባሁኑ ጊዜ እሱና ሚስቱ አስቴር በደቡባዊው ሕንድ ክፍል በሚገኘው በባንጋሎር ውስጥ በዚህ የአቅኚነት ሥራ አብረው በማገልገል ላይ ናቸው።
የዕድሜ ልክ መጽናኛ
ለብዙ ዓመታት ሥቃይና ችግር እንዲደርስብኝ በመፍቀዱ ይሖዋን ዘወትር አመሰግነዋለሁ። እነዚህ ተሞክሮዎች ባያጋጥሙኝ ኖሮ የይሖዋን ደግነት፣ ምሕረቱንና የርኅራኄ ክብካቤውንና ፍቅሩን በዚህን ያህል መጠን የምፈትንበት ውድ መብት አላገኝም ነበር። (ያዕቆብ 5:11) ይሖዋ “ለድሀ አደጉና (አባት የሌለው ልጅ) ለመበለት (ባል የሞተባት ሴት)” ስለሚያደርገው ክብካቤና አሳቢነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ማንበብ ልብን በደስታ የሚያሞቅ ነው። (ዘዳግም 24:19-21) ቢሆንም የሱ ክብካቤና አሳቢነት በራስ ሕይወት ላይ ሲያጋጥም ከሚሰጠው መጽናናትና ደስታ ጋር ሊወዳደር የሚችል አንድም ነገር የለም።
በራሴ ማስተዋል መመካት ሳይሆን በመንገዴ ሁሉ እሱን በማሰብ በይሖዋ ላይ የማያወላውል እምነትና ትምክህቴን ማድረግን ተምሬአለሁ። (መዝሙር 43:5፤ ምሳሌ 3:5, 6) ገና ወጣት መበለት በነበርኩበት ጊዜ በቃሉ እንዲያጽናናኝ ወደ አምላክ ጸለይኩ። አሁን በ68 ዓመት ዕድሜዬ መጽሐፍ ቅዱስን በመረዳትና ምክሮቹን በሥራ ላይ በማዋል ከልክ ያለፈ መጽናኛ እንዳገኘሁ በእርግጠኝነት ለመናገር እችላለሁ።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሊሊ አርተር ከቤተሰቦቿ ጋር