በእምነት ጤናሞች ሁናችሁ ሁኑ
ከቲቶ የተገኙ ዋና ዋና ነጥቦች
በሜዲትራንያን ባሕር ውስጥ በሚገኘው የቀርጤስ ደሴት የሚገኙት ጉባኤዎች መንፈሣዊ እርዳታ ያስፈልጋቸው ነበር። ይህን እርዳታ ማን ሊሰጣቸው ይችላል? የሐዋርያው ጳውሎስ የሥራ ባልደረባ የነበረው ቲቶ አለ። ቲቶ ደፋር፣ ለማስተማር የሚበቃ፣ ለመልካም ሥራ የሚቀና፣ በእምነት ጤናማ ነበር።
ጳውሎስ በመጀመሪያውና በሁለተኛው የሮማ እሥራቱ መካከል ቀርጤስን ጎብኝቶ ነበር። ቲቶ አንዳንድ ነገሮችን እንዲያስተካክልና የጉባኤ ሽማግሌዎችን እንዲሾም በቀርጤስ ደሴት እንዲቆይ ጳውሎስ ትቶት ነበር። በተጨማሪም ቲቶ የሐሰት አስተማሪዎችን እንዲገስጽና ጥሩ ምሳሌ እንዲሆን ይፈለግበት ነበር። ይህ ሁሉ ነገር ጳውሎስ ከ61 እስከ 64 እዘአ በሜቄዶንያ ሆኖ ለቲቶ በጻፈው ደብዳቤ ተገልጾአል። የሐዋርያውን ምክር መከተል የዘመናችን የበላይ ተመልካቾችና የእምነት ባልደረቦቻቸው ደፋሮች፣ ቀናተኞችና በመንፈሳዊ ጤናሞች እንዲሆኑ ሊረዳቸው ይችላል።
ከበላይ ተመልካቾች ምን ይፈለጋል?
የበላይ ተመልካቾችን መሾምና አንዳንድ ከበድ ያሉ ችግሮችን መፍታት ያስፈልግ ነበር። (1:1-16) አንድ ሰው የበላይ ተመልካች ሆኖ እንዲሾም ከተፈለገ የማይከሰስ፣ በግልም ሆነ በቤተሰብ አኗኗሩ ጥሩ ምሳሌ የሚሆን፣ እንግዳ ተቀባይ፣ ሚዛኑን የጠበቀ፣ ራሱን የሚገዛ መሆን ይገባዋል። እውነት የሆነውን ማስተማር፣ ተቃዋሚ ትምህርት የሚያስተምሩትን በብርቱ መምከርና መገሰጽ ይኖርበታል። በጉባኤው ውስጥ አለአግባብ የሚመላለሱ ሰዎች ጸጥ መደረግ ስለሚኖርባቸው ድፍረት ያስፈልገዋል። በተለይ ከግዝረት ያልተላቀቁ ሰዎች ሙሉ ቤተሰቦችን ስለሚገለብጡ ዝም እንዲሉ መደረግ ይኖርባቸዋል። ጉባኤዎች በመንፈሳዊ ጤናሞች ሆነው እንዲቆዩ ከተፈለገ ጠንከር ያለ ተግሳጽ ሊሰጥ ይገባል። ዛሬም ቢሆን ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ጉባኤውን ለማነጽ ሲሉ ምክርና ተግሳጽ ለመስጠት እንዲችሉ ድፍረት ሊኖራቸው ይገባል።
ጤናማ ትምህርቶችን በሥራ ማዋል
ቲቶ በመንፈሳዊ ጤናማ የሆነ ትምህርት ማስተላለፍ ነበረበት። (2:1-15) የሸመገሉ ወንዶች በልከኝነት፣ በጭምትነት፣ በአእምሮ ጤናማነት፣ በእምነት፣ በፍቅርና በጽናት ምሳሌ መሆን ይገባቸዋል። አሮጊቶችም በጠባያቸው ቅዱስ መሆን ይኖርባቸዋል። ‘የበጎ ነገር አስተማሪዎች’ መሆን ስለሚኖርባቸው ወጣት ሴቶች ለሚስትነትና ለእናትነት ግዴታቸው ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖራቸው ሊረዱአቸው ይችላሉ። ወጣት ወንዶችም ጤናማ አእምሮ ያላቸው፣ ባሮች የሆኑ የአምላክን ትምህርት በሚያስከብር ሁኔታ ለጌቶቻቸው የሚገዙ መሆን ይኖርባቸዋል። ክርስቲያኖች ሁሉ በዚህ ሥርዓት ሲኖሩ የአምላክንና የኢየሱስ ክርስቶስን ክብራማ መገለጥ እየጠበቁ ለአምላክ አክብሮት የማያሳይን ኑሮ መካድና በአእምሮ ጤናሞች መሆን አለባቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ “ከዐመጽ ሁሉ እንዲቤዠን መልካሙንም ለማድረግ የሚቀናውን ገንዘቡም የሚሆነውን ሕዝብ ለራሱ እንዲያነጻ ስለ እኛ ነፍሱን ሰጥቶአል።” እኛም እንደዚህ ያለ ጤናማ ትምህርት በሥራ ላይ በማዋል ‘የአምላክን ትምህርት እናስጊጠው።’
የጳውሎስ የመደምደሚያ ምክር ለመንፈሳዊ ጤንነት የሚረዳ ነበር። (3:1-15) ለገዥዎች በተገቢ ሁኔታ መገዛትና ምክንያታዊነትን መኮትኮት ያስፈልግ ነበር። ክርስቲያኖች የዘላለም ሕይወት ተስፋ አላቸው። የጳውሎስም ቃላት አእምሮአቸውን በመልካም ሥራ ላይ እንዲያኖሩ የሚያበረታቷቸው እንዲሆኑ ጠበቅ ብለው መገለጽ ነበረባቸው። በሕጉ ላይ የሚደረግ የሞኝነት ክርክርና ጥል መወገድ ነበረበት። ኑፋቄ የሚያስፋፋ ሰው ሁለት ጊዜ ከተመከረ በኋላ ከእርሱ መራቅ ያስፈልግ ነበር። ዛሬም ሽማግሌዎች እንዲህ ያለውን ምክር በሥራ ሲያውሉ እነርሱም ሆኑ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን በእምነት ጤናማ ሆነው ለመኖር ይችላሉ።
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ለወይን ጠጅ የማይገዙ፦ ሴቶች ወንዶችን በጉባኤ ውስጥ ማስተማር ባይችሉም በዕድሜ ከፍ ያሉ እህቶች ወጣት ሴቶችን በግላቸው ሊያስተምሩአቸው ይችላሉ። ይሁን እንጂ በዕድሜ ከፍ ያሉ እህቶች በዚህ ረገድ የተሳካላቸው እንዲሆኑ ቀጥሎ ያሉትን የጳውሎስ ቃላት ልብ ማለት ይኖርባቸዋል፦ “አሮጊቶች ሴቶች አካሄዳቸው ለቅዱስ አገልግሎት የሚገባ፣ የማያሙ፣ ለብዙ ወይን ጠጅ የማይገዙ፣ በጎ የሆነውን ነገር የሚያስተምሩ ይሁኑ።” (ቲቶ 2:1-5፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:11-14) መጠጥ በራሳቸው ላይ ሊያመጣው በሚችለው ውጤት ምክንያት የበላይ ተመልካቾች፣ ዲያቆናትና በዕድሜ ከፍ ያሉ ሴቶች ልከኞች መሆንና ለብዙ የወይን ጠጅ የማይገዙ መሆን ነበረባቸው። (1 ጢሞቴዎስ 3:2, 3, 8, 11) ክርስቲያኖች ሁሉ ከስካር መራቅ አለባቸው። ‘ቅዱስ የሆነውን የወንጌል ሰባኪነት ሥራ’ በሚፈጽሙበት ጊዜ ደግሞ የአልኮል መጠጥ ከመጠጣት መጠበቅ ይኖርባቸዋል።—ሮሜ 15:16፤ ምሳሌ 23:20, 21