ኃጢአትን የመናዘዝ ልማድ ጉድለት ይኖርበት ይሆን?
“ኃጢአትን መናዘዝ በመንፈሳዊ መንጻት፣ እንደ አዲስ መጀመር፣ ሰሌዳውን መጥረግ ማለት ነው። ኃጢአቴን ለመናዘዝ ወደ ንስሐ አባቴ ስሄድና የሠራኋቸውን ኃጢአቶች ስነግረውና እርሱም ይቅር ሲለኝ በጣም ደስ ይለኛል” በማለት አንድ የካቶሊክ ሃይማኖት ታማኝ ተናግሯል።—አባት ሆይ፣ ኃጢአት ሠርቻለሁና ባርከኝ ከተባለው መጽሐፍ
በአዲሱ ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ መሠረት “ኃጢአትን ይቅር ለማለት ወይም ለመያዝ ክርስቶስ ሥልጣን የሰጠው ለካህኑ (ለቄሱ) ብቻ ነው።” ይኸው ኢንሳይክሎፒድያ አዘውትሮ ኃጢአትን መናዘዝ “በአሳዛኝ በደል ምክንያት የታጣውን የነፍስን ቅድስና መመለስና ሕሊናን ማጥሪያ ነው” ሲል ይናገራል። ይሁን እንጂ በብዙ አገሮች የሚታየው የሥነ ምግባር ይዞታ ይህ አዘውትሮ ኃጢአትን የመናዘዝ ልማድ ሰዎች “ከክፉ እንዲመለሱና መልካምን እንዲያደርጉ” እንዳላነሳሳቸው ያሳያል። (መዝሙር 34:14) ታዲያ የጐደለው ነገር ይኖር ይሆን?
እንዲሁ ሥነ ሥርዓት ብቻ ነውን?
የንስሐ ኑዛዜ እንዲሁ ለሥነ ሥርዓት ያህል ብቻ ሊደረግ ይችላል። በአየርላንድ የመጀመሪያ ንስሐ ኑዛዜ የሚደረገው ከመጀመሪያው ቁርባን በፊት ነው። ታዲያ አንዲት የሰባት ዓመት ልጅ ይበልጥ የምታስበው ‘በአሳዛኝ ኃጢአት የታጣውን የነፍስ ቅድስና ከመመለስ ይልቅ ለመጀመሪያ ጊዜ በቁርባን በምትካፈልበት ዕለት ስለምትለብሰው ቆንጆ የትንሽ ሙሽራ ቀሚስ ቢሆን ያስደንቃልን?
ራሞና ሰባት ዓመት እንደሞላት የመጀመሪያ የንስሐ ኑዛዜዋን ባደረገች ቀን “ከሁሉ በላይ ያጓጓኝ ነገር ከዘመዶቼ ከማገኘው ገንዘብ ሌላ ቀሚሱ ነበር” በማለት አምናለች። በመቀጠልም “በማውቃቸው ልጃገረዶች ሁሉ መካከል ምንም ዓይነት መንፈሳዊ ስሜት አልነበረም። እንዲያውም በወቅቱ ማንኛችንም ስለ አምላክ አላሰብንም” ብላለች።
እንዲያውም ልጆች ኃጢአታቸውን አዘውትረው እንዲናዘዙ ማስገደድ ትርጉም የሌለው ድግግሞሽ ሊያደርገው ይችላል። የንስሐ ኑዛዜ ልማዱን በሰባት ዓመት ዕድሜው ጀምሮ የነበረውን ሚካኤል “በምናዘዝበት ጊዜ ሁልጊዜ የተጻፈውን የኑዛዜ ቃል ብቻ እደጋግም ነበር” ብሏል።
አባት ሆይ፣ ኃጢአት ሠርቻለሁና ባርከኝ በሚለው መጽሐፍ ውስጥ አንዳንድ ካቶሊኮች የሰጡት አስተያየት የሚያሳየው አዋቂዎች ከሆኑ በኋላም እንኳን ሳይቀር የንስሐ ኑዛዜ ለእነሱ ምንም መንፈሳዊ ጥቅም እንደሌለው ነው። አንድ ሰው “የንስሐ ኑዛዜ መዋሸትን ያስተምርሃል ምክንያቱም ለቄሱ መናገር የማትፈልጋቸው አንዳንድ ነገሮች አሉ” ሲል አምኗል። በቀሳውስት መካከል የአቋም አንድነት አለመኖሩ ተናዛዦቹ በተቻለ መጠን አነስተኛ ንስሐ የሚጠይቀውን ቄስ እንዲፈልጉ ሊያደርግ ይችላል። አንዳንዶች ሊሰሙ የሚፈልጉትን ምክር የሚሰጣቸውን “ጥሩ” ንስሐ አባት ይፈልጋሉ። አንዲት ወጣት ሴት “ለሦስት ወራት ቤተክርስቲያን ሳማርጥ ከቆየሁ በኋላ የንስሐ አባቴን አገኘሁ። በየወሩ በማስታረቂያ ክፍሉ በግንባር አማክረዋለሁ። በጣም ጐበዝ ነው” ብላለች። ሌላዋ ካቶሊክ ስትናገር “ቀልጣፋ ብትሆኚ ደንቆሮና ‘ሥሪ ሄይል ሜሪ’ ከሚሉት ቃላት በስተቀር እንግሊዝኛ መናገር የማይችል ቄስ ታገኛለሽ” አለች።
እንግዲያውስ በአንዳንድ ሰዎች በልማድ እንደሚደረገው በንስሐ ኑዛዜ ላይ ጉድለት እንዳለ ግልጥ ነው። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “ኃጢአቱን የሚሰውር አይለማም። የሚናዘዝባትና የሚተዋት ግን ምህረትን ያገኛል” ሲል በደልን የመናዘዝ አስፈላጊነትን ይጠቁማል።—ምሳሌ 28:13
ይህ ማለት አንድ ክርስቲያን ኃጢአቱን ሁሉ መናዘዝ አለበት ማለት ነውን? ከሆነስ ለማን? የሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት እነዚህን ጥያቄዎች ይመረምራል።