የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
“የምታነበው ጥቅስ ሁሉ ልቤን ነካው”
ሐዋርያው ጳውሎስ “የአምላክ ቃል ሕያው ነው፤ የሚገፋፋ ኃይልም አለው” ብሏል። (ዕብራውያን 4:12 አዓት) ይህም ቃል ከቪየትናም በመጣችና የቡድሃ እምነት ተከታይ ሆና ባደገች አንዲት ሴት ላይ እውነት ሆኗል። ታሪክዋን ቀጥለን እንመልከት።
“አሁንም በቪየትናም የሚኖሩት ወላጆቼ የስም ቡድሂስቶች ነበሩ። ስለዚህ በ22 ዓመቴ እስካገባሁበት ጊዜ ድረስ ቡድሂስት ሆኜ ኖርሁ። የባሌ ቤተሰቦች በካቶሊክ ቤተክርስቲያን እንድጠመቅ ሊያስገድዱኝ ሞከሩ። የሞተችው አማቴ እኔ ቡድሂስት በመሆኔ ምክንያት ወደ ሰማያዊ ገነት ከመግባት እንደተከለከለች ይናገሩ ነበር! በመጀመሪያ ለመጠመቅ ፈቃደኛ አልነበርኩም። በኋላ ግን እነርሱን ለማስደሰት ስል ተጠመቅሁ። ይሁን እንጂ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውስጥ የነበረውን ግብዝነት በመጥላቴ ምክንያት በልቤ ቀልድ ሆኖ ይሰማኝ ነበር። ከቡድሃ ሃይማኖት ምንም የተለየ አልነበረም። በጦርነትና በፖለቲካ ውስጥ በመግባት በኩል አንድ ናቸው። ሁለቱም ሃይማኖቶች ለሞቱ ዘመዶች የሚደረገውን አምልኮ ይደግፋሉ።
“ቪየትናም ውስጥ ብሆን ኖሮ እውነትን ለመማር አጋጣሚ አይኖረኝም ነበር። ያደግኩት የፖለቲካ ማዕበል ደቡብ ቪየትናምን ባናወጠበት ጊዜ ላይ ነበር። ከሳይጎን በጣም በሚርቅ አንድ ከተማ ውስጥ እኖር ነበር። ስለዚህ ወደ አውስትራሊያ ሸሽቼ ለማምለጥ መቻሌ በረከት ነበር።
“በጀልባ ማምለጥ ከቻሉት ዕድለኛ ሰዎች አንዷ እኔ ነበርኩ። የሁለት ወር ልጄን ታቅፌ ከፖሊስ ለማምለጥና ወደ ዓሣ ማጥመጃ ጀልባዋ ለመድረስ በጨለማ ውስጥ መሮጥ ነበረብኝ። በባሕር ላይ ለሰባት ቀናት ከቆየን በኋላ ወደ ማሌዥያ ደረስን። እዚያም ወደ አውስትራሊያ ከመምጣታችን በፊት ለጥቂት ወራት በስደተኞች ካምፕ ቆየን።
“አውስትራሊያ ውስጥ ለሁለት ዓመት ተኩል ከቆየሁ በኋላ የይሖዋ ምስክሮች ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ሲያገለግሉ አገኙኝ። መጀመሪያ ባነጋገሩኝ ቀን አጋጣሚው እንግሊዝኛ ለመማር ጥሩ እንደሆነ አድርጌ ስላሰብኩ ዘወትር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግልኝ ፈቃደኛ ሆንኩ። ይሁን እንጂ ያገኘችኝ ምስክር የነበራት ጠባይና ያስተማረችኝ እውነት ስሜቴን በጣም ነካው። የምታነበው ጥቅስ ሁሉ ልቤን ይነካው ነበር፤ በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ምንም ግብዝነት አላየሁም። መጽሐፍ ቅዱስን ለአንድ ዓመት ተኩል ካጠናሁ በኋላ ሕይወቴን ለይሖዋ ወስኜ ተጠመቅሁ።
“እውነት ለሕይወት የነበረኝን አጠቃላይ አመለካከት ለውጦታል ለማለት እችላለሁ። ባሌ አያምንም፤ ቢሆንም ይሖዋ ከትንሹ ቤተሰቤ ጋር ረድቶኛል፣ ለሕይወት የሚያስፈልገውንም ሰጥቶኛል። ታላቅ አስተማሪዬም ስለሆነ የተሻልኩ ሚስትና እናት እንድሆን አስተምሮኛል። ይሖዋ ከመንፈሳዊ ጨለማ እንድወጣና የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ብርሃን እንዳገኝ ስለረዳኝ አመሰግነዋለሁ።”
በእርግጥም በዚህ ተሞክሮ እንደታየው የአምላክ ቃል ለጥሩ ዓላማ የሚገፋፋ ኃይል አለው። መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናትና የተማሩትን በሥራ ላይ ማዋል ለሕይወት ትርጉምና ዓላማ ይሰጠዋል፤ በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ወደሚኖረው የዘላለም ሕይወትም ይመራል። ሙሴ “ይህ ነገር ሕይወታችሁ ነው እንጂ ለእናንተ ከንቱ አይደለምና” ብሎ እንዲናገር አምላክ በመንፈሱ እንዳነሳሳው ነው።—ዘዳግም 32:47