መንፈሳዊ ሰካራሞች እነማን ናቸው?
“ለኤፍሬም ሰካሮች (ሰካራሞች) ወዮላቸው!”—ኢሳይያስ 28:1
1. ብዙ ሰዎች ምን ብሩህ ሁኔታ እየመጣ እንዳለ ተሰምቷቸዋል? ይሁን እንጂ ተስፋ ያደረጉት ነገር ይፈጸም ይሆን?
ስሜትን በሚቀሰቅስ ዘመን ውስጥ እንኖራለን። ብዙ ሰዎች አስገራሚ የፖለቲካ ለውጦች መደረጋቸውና የተባበሩት መንግሥታት ይበልጥ ሲንቀሳቀስ ማየታቸው መገረምንና ደስታን ቀስቅሶባቸዋል። ታህሣስ 1989 ላይ የዲትሮይ ፍሪ ፕሬስ እንዲህ አለ፦“ፕላኔቲቱ ወደ 1990ዎቹ ዓመታት ስትገባ ሰላም በየስፍራው ፈነጠቀ።” የሶቪየት መጽሔትም “ሰይፋችንን ማረሻ አድርገን ለመቀጥቀጥ እየተዘጋጀን ነው” ሲል አስታውቋል። የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ደግሞ “ከእንግዲህ በቀዝቃዛው ጦርነት ውስጥ አይደለንም” በማለት በይፋ አስታወቁ። አዎን፤ ሰዎች ከፍ ያለ ተስፋ አድሮባቸዋል። የዓለም መልክም በመለወጥ ላይ መሆኑ ምንም አያጠራጥርም። በቅርቡ የተነሣው የባሕረ ሰላጤው ውጊያ ለውጦች እንዴት በፍጥነት ሊደርሱ እንደሚችሉ አሳይቷል። ይሁን እንጂ የአሁኑ ዓለም እውነተኛ ሰላምና ዋስትና ያለው ኑሮ እንዲሁም ይህ ሁኔታ የሚያስከትላቸው ጥቅሞች የሚያይበት ጊዜ በእርግጥ ይመጣ ይሆን? መልሱ አይመጣም ነው። እንዲያውም ዓለምን እስከ መሠረቷ የሚያናጋ ከባድ ውድቀት በጥንስስ ላይ ነው። መጪው ከባድ ውድቀት ሃይማኖትን በጥልቅ የሚነካ ይሆናል።
2. የአሁኑ ጊዜ ሁኔታ በጥንቷ እሥራኤልና በይሁዳ ከነበረው ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?
2 ይህ ከባድ ውድቀት በ8ኛውና በ7ኛው መቶ ዘመናት ከዘአበ በጥንቷ እሥራኤልና በይሁዳ የደረሱት ሁኔታዎች ጥላ የሆኑለት ነው። ያኔም ሕዝቦች ሰላምን የጨበጡ መስሏቸው ነበር። አምላክ ግን በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት የሰላም ተስፋቸው በከንቱ ራስን ማሞኘት እንደሆነና ፈጥኖ እንደሚጋለጥ አስጠነቀቃቸው። ዛሬም ይሖዋ በተመሳሳይ መንገድ የሰው ልጆች በሰብዓዊ ጥረቶቻቸው አማካኝነት ዘላቂ ሰላም ለማግኘት ተስፋ የሚያደርጉ ከሆነ እየተታለሉ መሆናቸውን በምሥክሮቹ አማካኝነት እያስጠነቀቃቸው ነው። የይሖዋን ትንቢታዊ ማስጠንቀቂያ እናነበውና ዛሬም እንዴት እንደሚሠራ እንመልከት። ማስጠንቀቂያው የሚገኘው በትንቢተ ኢሳይያስ 28ኛ ምዕራፍ ላይ ሲሆን የተጻፈውም በክፉው የእሥራኤል ንጉሥ በፋቁሄና በጠማማው የአይሁድ ንጉሥ በአካዝ ዘመነ መንግሥት ከ740 ከዘአበ ቀደም ብሎ ነው።
“የኤፍሬም ሰካራሞች”
3. ኢሳይያስ ምን አስደንጋጭ የሆነ የሚያወግዝ መልዕክት አሰማ?
3 በምዕራፍ 28 ቁጥር 1 ኢሳ 28:1 ላይ “የኤፍሬም ሰካራሞች የላቀች አክሊል ለሆነችውና፣ በወይን ጠጅ የተሸነፉ በሚኖሩበት ለምለም ሸለቆ ራስ ላይ ላለች የውበቷ ጌጥ ለሆነችው የጠወለገች አበባ ወዮ!” የሚል ደንገጥ የሚያደርግ አነጋገር ስናነብ ስሜታችን ነቃ ይላል። (አዓት) እሥራኤላውያን ያንን የሚሰቀጥጥ የውግዘት ቃል ሲሰሙ እንዴት ክው ብለው ይሆን! እነዚህ “የኤፍሬም ሰካራሞች” እነማን ነበሩ? “የላቀች አክሊል” የተባለችውስ ምን ነበረች? “የለመለመው ሸለቆ ራስ” ምንድን ነው? እነዚህ ቃላት ዛሬ ለእኛ ምን ትርጉም አላቸው የሚለው ጥያቄም ይበልጥ ያሳስበናል።
4. (ሀ) ኤፍሬምና የለምለሙ ሸለቆ ራስ ምን ነበሩ? (ለ) እሥራኤል ደኅንነቷ ዋስትና እንዳለው ሆኖ የተሰማት ለምን ነበር?
4 ኤፍሬም ከአሥሩ የእሥራኤል ነገዶች ትልቁ ስለነበረ “ኤፍሬም” የሚለው አነጋገር አንዳንድ ጊዜ ሰሜናዊውን መንግሥት በሞላ ያመለክት ነበር። ስለዚህ “የኤፍሬም ሰካራሞች” የተባሉት በእርግጥ የእሥራኤል ሰካራሞች ነበሩ። የእሥራኤል ዋና ከተማ ሰማርያ ነበረች። እርሷም በለመለመ ሸለቆ ራስ ላይ በከፍታ ቦታ ቁብ ብላ ትገኝ ነበር። ስለዚህ “የለመለመች ሸለቆ ራስ” የሚለው አነጋገር ሰማርያን ያመለክታል። እነዚህ ቃላት በተጻፉበት ጊዜ የእሥራኤል መንግሥት በሃይማኖታዊ አቋሙ በጣም ተበላሽቶ ነበር። ከዚህም በላይ ሰማርያ ይሁዳን ለመውጋት ከሶሪያ ጋር ፖለቲካዊ ኅብረት መሥርታ ነበርና ያለ ምንም ስጋት ተዝናንታ ትኖር ነበር። (ኢሳይያስ 7:1-9) ያ ሁኔታ ሊለወጥ ቀርቦ ነበር። ከባድ ውድቀት አፍጥጦ እየመጣ ነበር። ለዚህም ነበር ይሖዋ “የኤፍሬም ሰካራሞች የላቀች አክሊል ለሆነችው ወዮ” ሲል የተናገረው።
5. (ሀ) የእሥራኤል የላቀ አክሊል ምን ነበር? (ለ) የኤፍሬም ሰካራሞች እነማን ነበሩ?
5 “የላቀች አክሊል” የተባለችው ምንድን ነች? አክሊል የንጉሣዊ ሥልጣን ምልክት ነው። እንግዲያውስ “የላቀች አክሊል” እስራኤል ከይሁዳ ጥገኝነት ተላቃ ራሷን የቻለች መንግሥት በመሆን የነበራት አቋም ነው። የእሥራኤልን ነፃ መንግሥትነት የሚያጠፋ ነገር በመምጣት ላይ ነበር። “የኤፍሬም ሰካራሞች” ታዲያ እነማን ነበሩ? ሰማርያ ጸያፍ ምግባር የሚያበረታታ የጣዖት አምልኰ መድረክ ሆኖ ስለ ነበር በውስጧ ቃል በቃል ሰካራሞች እንደነበሩ አያጠራጥርም። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ከዚያ የባሰ ዓይነት ስካር እንዳለ ይናገራል። በኢሳይያስ 29:9 ላይ እንዲህ እናነባለን፦ “በወይን ጠጅ አይሁን እንጂ ስከሩ። በሚያሰክር መጠጥ አይሁን እንጂ ተንገዳገዱ።” ይህ ርኩስ የሆነና ሞት የሚያስከትል መንፈሳዊ ስካር ነበር። የእሥራኤል መሪዎች በተለይም ሃይማኖታዊ መሪዎቿ መንፈሳዊ ስካር በግልጽ አጥቅቷቸው ነበር።
6. የጥንቷን እሥራኤል ያሰከራት ምን ነበር?
6 ለጥንቷ እሥራኤል መንፈሳዊ ሰካራምነት መንስኤው ምን ነበር? በመሠረቱ ይህ ስካር የብሔሩን መሪዎች ከስጋት ያሳረፋቸው በይሁዳ ላይ የተጠነሰሰ ሰማርያ ከሶሪያ ጋር ያደረገችው የትብብር ቃል ኪዳን ነበር። ይህ መንፈሳዊ ስካር እሥራኤልን ከእውነቱ ዓለም በላይ አንሳፈፋት። ልክ ቃል በቃል እንደሰከረ ሰው ሰማርያ ሁኔታው ሁሉ ብሩህ መስሎ ታያት፤ ሆኖም ለዚህ የሚያበቃ ምንም ምክንያት አልነበራትም። ከዚህም በላይ እሥራኤል ከሶሪያ ጋር የነበራትን የትብብር ቃል ኪዳን ልክ ለጌጥ እንደተደረገ የአበባ ጉንጉን በኩራት በራሷ ላይ አድርጋው ነበር። ይሁን እንጂ ኢሳይያስ እንዳለው ብዙ ሊቆይ የማይችል ረጋፊ የአበባ ጉንጉን ነበር።
7, 8. የጥንቷ እሥራኤል ደኅና እንደሆነች ቢሰማትም ምን ይጠብቃት ነበር?
7 ኢሳይያስ ይህንን በምዕራፍ ኢሳ 28 ቁጥር 2 ላይ ጠበቅ አድርጎ ይገልጸዋል። “እነሆ [በይሖዋ (አዓት)] ዘንድ ኃይልና ብርቱ የሆነ አለ። እንደ በረዶ ወጨፎ እንደሚያጠፋም ዐውሎ ነፋስ እንደሚያጥለቀልቅም እንደ ታላቅ ውሃ ፈሳሽ በጠነከረ እጅ ወደ ምድር ይጥላል።” ይህ “ኃያልና ብርቱ የሆነ” ማን ነው? በጥንቷ እሥራኤል ዘመን ኃያሉ የአሦር መንግሥት ነበር። ይህ ጨካኝና ርህራሄ የሌለው የዓለም ኃይል በእሥራኤል ላይ እንደሚያጥለቀልቅ ታላቅ ጐርፍ ሆኖ የሚመጣበት ጊዜ ነበር። ከምንስ ውጤት ጋር?
8 ኢሳይያስ በመቀጠል “የኤፍሬም ሰካራሞች የላቀች አክሊል በእግር ትረገጣለች። በለምለሙ ሸለቆ ራስ ላይ ያለች የጠወለገች የክብሩ የአበባ ጉንጉን ከመከር በፊት አስቀድሞ እንደማትበስል በለስ ትሆናለች። ሰው ባያት ጊዜ በእጁ እንዳለች ይውጣታል” ይላል። (ኢሳይያስ 28:3, 4 አዓት) የእሥራኤል ዋና ከተማ ሰማርያ ለአሦር ቀጥፎ ለመብላት እንደተዘጋጀች እንደበሰለች በለስ ነበረች። የአበባ ጉንጉን የመሰለው እሥራኤል ከሦርያ ጋር የነበራት ኅብረት ሊረገጥ ተቃርቦ ነበር። አምላክ ስለ አድራጎቷ ከእርሷ ጋር ለመተሳሰብ በሚመጣበት ቀን ላይ ያ ኅብረት ምንም ዋጋ አይኖረውም። ከዚህ የባሰ ደግሞ አክሊል መሰል የሆነው የነፃነት ክብሯ በሦሪያዊው ጠላት እግር ሥር ሊደቅ ነበር። እንዴት ያለ መዓት ሊወርድባት ነው!
“ካህናትና ነቢያት ስተዋል”
9. ይሁዳ ለጥንቷ እሥራኤል ይሖዋ ከተላከው የተሻለ መልዕክት የጠበቀችው ለምን ሊሆን ይችላል?
9 አዎን እሥራኤል ስለ ፈጸመችው በደል አስከፊ ፍርድ እየጠበቃት ነበር። ይሖዋ እንዳስጠነቀቃቸውም ያ ፍርድ በአሦር በጠፋችበት ጊዜና ሰሜናዊው መንግሥት እንደ አንድ ነፃ መንግሥት ሆኖ መኖሩ ባበቃበት በ740 ከዘአበ ላይ መጣ። ቆይተን እንደምንመለከተው በጥንቷ እሥራኤል ላይ የደረሰው ነገር በዛሬው ጊዜ ላለው እምነት አጉዳይ የሐሰት ሃይማኖት እንደ አስፈሪ ማስጠንቀቂያ ሆኖ ያገለግላል። ይሁን እንጂ በደቡብ በኩል የምትገኘው የእሥራኤል እህት የሆነችው መንግሥት ይሁዳስ? በኢሳይያስ ዘመን የይሖዋ ቤተመቅደስ የይሁዳ ዋና ከተማ በሆነችው በኢየሩሳሌም ገና በመሥራት ላይ ነበር። ክህነቱም ገና እየሠራ ነበር፤ እንደ ኢሳይያስ፣ ሆሴዕና ሚክያስ የመሳሰሉት ነቢያትም በይሖዋ ስም ይናገሩ ነበር። ታዲያ ይሖዋ ለይሁዳስ ምን መልእክት ነበረው?
10, 11. በይሁዳ ምን አስጸያፊ ሁኔታ ነበረ?
10 ኢሳይያስ ትንቢቱን በመቀጠል እንዲህ ብሎ ይነግረናል፦ “እነዚህም ደግሞ [ማለትም የኢየሩሳሌም ካህናትና ነቢያት] ከወይን ጠጁ የተነሣ ይስታሉ፤ ከሚያሰክርም መጠጥ የተነሣ ይፋንናሉ።” (ኢሳይያስ 28:7) በግልጽ እንደሚታየው የይሁዳ ሃይማኖታዊ መሪዎችም ሰክረው ነበር። በእሥራኤል እንደነበሩት ሰዎች አንዳንዶቹ ቃል በቃልም ሰካራሞች ሳይሆኑ አልቀሩም። ይህ ከሆነ ደግሞ ውርደት ነበር። ካህናት በቤተመቅደስ በሚያገለግሉበት ጊዜ ኃይለኛ መጠጥ እንዳይጠጡ የአምላክ ሕግ ለይቶ ከልክሏቸው ነበር። (ዘሌዋውያን 10:8-11) በአምላክ ቤት ውስጥ ቃል በቃል መስከር ሕጉን በሚዘገንን መንገድ መርገጥ ማለት ነበር።
11 ይበልጥ አሳሳቢው ግን በይሁዳ መንፈሳዊ ስካርም መኖሩ ነው። እሥራኤል ይሁዳን በመቃወም ከሦሪያ ጋር እንደተባበረች ሁሉ ይሁዳም ከአሦር ጋር ኅብረት በመፍጠር ለደኅንነቷ ዋስትና ለማግኘት ፈለገች። (2 ነገሥት 16:5-9) የአምላክ ቤተመቅደስና ነቢያት እያሉ ይሁዳ በይሖዋ መተማመን ሲገባት እምነቷን በሰዎች ላይ አደረገች። ከዚህም በላይ እንዲህ ዓይነቱን አልባሌ ኅብረት በመመሥረታቸው በሰሜን እንደነበሩት መንፈሳዊ ሰካራም ጐረቤቶቻቸው እነሱም ስጋት ቀረልን በማለት አሳባቸውን ጣሉ። የምንቸገረኝነት ዝንባሌያቸው ይሖዋን በጣሙን አስከፋው።
12. የይሁዳ መንፈሳዊ ሰካራምነት ምን ማስከተሉ የማይቀር ነበር?
12 ኢሳይያስ በመቀጠል እንዲህ ይላል፦ “ከወይን ጠጁ የተነሳ ግራ ተጋብተዋል፤ በሚያሰክረው የአልኮል መጠጥ ምክንያት ወዲያና ወዲህ ይዋልላሉ፤ መንገዳቸውን የሚያስት ነገር ይታያቸዋል፤ ውሳኔ ማድረግ እስኪሳናቸው ድረስ ጨርሶ ደንዝዘዋል። ገበታዎቹ ራሳቸው በትፋት ተሞልተዋል—ትፋቱ ያላበላሸው ንጹሕ ስፍራ የለም።” (ኢሳይያስ 28:7, 8 አዓት) አንዳንዶቹ በሚሰክሩበት ጊዜ ቃል በቃል በቤተመቅደሱ ማስታወካቸው የማይቀር ነው። ከዚህ የከፋው ግን ሃይማኖታዊ መመሪያ መስጠት የነበረባቸው ካህናትና ነቢያት መንፈሳዊ ትውከት መትፋታቸው ነበር። ከዚህም በላይ ከጥቂት ታማኞች በስተቀር የነቢያቱ የማመዛዘን ችሎታ ተዛብቶ ስለነበር ለሕዝቡ የሚያዩለት ሐሰተኛ ነገርን ነበር። ለዚህ መንፈሳዊ ርኩሰት ይሖዋ ይሁዳን መቅጣት ነበረበት።
መንፈሳዊ ሰካራሞች በዛሬው ጊዜ
13. በእሥራኤልና በይሁዳ የነበረውን የሚመስል ምን ሁኔታ ነው በ1ኛው መቶ ዘመን እዘአ የነበረው? ዛሬስ ምን ተመሳሳይ ነገር አለ?
13 የኢሳይያስ ትንቢቶች የተፈጸሙት በጥንቶቹ እሥራኤልና ይሁዳ ላይ ብቻ ነበርን? በፍጹም አልነበረም። ኢየሱስና ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ መንፈሳዊ ስካር ኢሳይያስ የተናገራቸውን ቃላት ጠቅሰው በዘመናቸው በነበሩት ሃይማኖታዊ መሪዎች ላይ እንደሚሠሩ ገልጸዋል። (ኢሳይያስ 29:10, 13፤ ማቴዎስ 15:8, 9፤ ሮሜ 11:8) ዛሬም የኢሳይያስን ዘመን የሚመስል ሁኔታ ተከስቷል፤ አምላክን እወክላለሁ ብላ በምትናገር ዓለም አቀፍ ሃይማኖታዊት ድርጅት በሕዝበ ክርስትና ላይ ተመሳሳይ ሁኔታ ይገኛል። ለእውነት ጽኑ አቋም በመውሰድና በይሖዋ በመታመን ፋንታ ሕዝበ ክርስትና ካቶሊክም ሆነች ፕሮቴስታንት እምነቷን በዓለም ላይ ጥላለች። በመሆኑም እንደ እሥራኤልና እንደ ይሁዳ ሰካራሞች እየተንገዳገደች ነው። የእነዚያ የጥንት መንግሥታት መንፈሳዊ ሰካራሞች ለዛሬዎቹ የሕዝበ ክርስትና መንፈሳዊ መሪዎች ጥላ ናቸው። ይህ እንዴት ሊሆን እንደቻለ አበጥረን እንመልከት።
14. የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ መሪዎች እንደ ጥንቶቹ ሰማርያና ኢየሩሳሌም ሰካራሞች የሆኑት እንዴት ነው?
14 እንደ ሰማርያና ኢየሩሳሌም ሁሉ ሕዝበ ክርስትናም ፖለቲካዊ ኅብረት በመፍጠር በጣም ሰክራለች። በ1919 ሕዝበ ክርስትና የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር እንዲመሠረት ከጐተጐቱት ከዋነኞቹ ኃይሎች አንዷ ነበረች። ኢየሱስ ክርስቲያኖች የዓለም ክፍል እንደማይሆኑ ተናግሮ ሳለ የሕዝበ ክርስትና መሪዎች ግን ከፖለቲካዊ መሪዎች ጋር ዝምድና ያዳብራሉ። (ዮሐንስ 17:14-16) የእንዲህ ዓይነቱ አድራጐት ምሳሌያዊ ወይን የቀሳውስቱን ስሜት ሞቅ ያደርጋል። (ከራእይ 17:4 ጋር አወዳድር) ፖለቲካውያን ምክር ሲጠይቋቸውና ከዚህ ዓለም ታላላቆች ጋር ተቀምጠው ሲወያዩ በጣም ደስ ይላቸዋል። ከዚህም የተነሳ ለሰው የሚሰጡት እውነተኛ መንፈሳዊ መመሪያ የላቸውም። የእውነትን ንጹሕ መልእክት ከመናገር ይልቅ ርኩሰትን ይተፋሉ። (ሶፎንያስ 3:9) እይታቸው ብዥ ብዥ ስለሚልና ስለተደናበሩ ለሰው ልጆች የሚያስተማምኑ መሪዎች አልሆኑም።—ማቴዎስ 15:14
“ትዕዛዝ በትዕዛዝ ላይ”
15, 16. በኢሳይያስ ጊዜ የነበሩት ሰዎች ማስጠንቀቂያዎቹን ሲሰሙ ምን አሉ?
15 ከዘመናችን አቆጣጠር በፊት በ8ኛው መቶ ዘመን ኢሳይያስ በተለይ የይሁዳን መንፈሳዊ መሪዎች የስሕተት አካሄድ አጋልጦአል። ያን ሲሰሙ ምን አሉ? ቃሉን ጠሉት! ኢሳይያስ የአምላክን ማስጠንቀቂያዎች ማወጁን አላቆም ባለ ጊዜ የሃይማኖት መሪዎቹ “እውቀትን ለማን ያስተምረዋል? ወይስ ወሬ ማስተዋልን ለማን ይሰጣል? ወተት ለተዉ ወይስ ጡት ለጣሉ ነውን?”በማለት በንዴት መልስ ሰጡት። (ኢሳይያስ 28:9) አዎን፤ ኢሳይያስ ለትናንሽ ልጆች እንደሚናገር አድርጎ አስቦ ነበርን? የኢየሩሳሌም የሃይማኖት መሪዎች ለራሳቸው ውሣኔ ለማድረግ ብቁ እንደሆኑ አዋቂዎች እንደሆኑ አድርገው ራሳቸውን ይቆጥሩ ነበር። የኢሳይያስን ነዝናዛ ማሳሰቢያ ማዳመጥ አላስፈለጋቸውም።
16 እንዲያውም እነዚያ ሃይማኖተኞች በኢሳይያስ የስብከት ሥራ እየቀለዱ ይስቁበት ነበር። “ትዕዛዝ በትዕዛዝ፣ ትዕዛዝ በትዕዛዝ፣ ሥርዓት በሥርዓት፣ ሥርዓት በሥርዓት፣ ጥቂት በዚህ ጥቂት በዚያ ነው” እያሉ በፌዝ ይዘምሩበት ነበር። (ኢሳይያስ 28:10) “ኢሳይያስ ያንኑን ነገር ይደጋግማል” ማለታቸው ነበር። ሁልጊዜ “ይሖዋ ያዘዘው ይህ ነው! ይሖዋ ያዘዘው ይህ ነው፤ የይሖዋ ሥርዓት ይህ ነው! የይሖዋ ሥርዓት ይህ ነው” ይላል እያሉ አፌዙበት። በቀድሞው ዕብራይስጥ ኢሳይያስ 28:10 ተደጋጋሚ የሆነ ቤት የሚመታ ግጥም ነበር፤ ያውም በመዋዕለ ሕፃናት ያሉ ልጆች እንደሚዘምሩት ያለ ግጥም ነበር። ነቢዩ ኢሳይያስም ለእነዚያ የሃይማኖት መሪዎቹ ልክ እንደዚያ መስሎ ነው የታያቸው። ያንኑን ነገር ልክ እንደ ልጅ የሚደጋግም ሆነባቸው።
17. ዛሬስ ብዙ ሰዎች በይሖዋ ምሥክሮች ለሚታወጀው መልዕክት ምላሻቸው እንዴት ነው?
17 በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ የኢየሱስና የደቀመዛሙርቱ ስብከትም እንደዚሁ ፍሬ የሌለው ድግግሞሽ መስሎ ይታይ ነበር። ኢየሱስን የተከተሉት ሰዎች በአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች ዘንድ እንደተረገሙና ምንም የማያውቁ የገጠር ሰዎች፣ ያልተማሩና ተራ እንደሆኑ ሰዎች ተደርገው ይታዩ ነበር። (ዮሐንስ 7:47-49፤ ሥራ 4:13) በዘመናችንም የይሖዋ ምሥክሮች ብዙ ጊዜ እንደዚያ ተደርገው ይታያሉ። በሕዝበ ክርስትና መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶች ገብተው አልተማሩም፤ እንደ ቀሳውስቱ ከፍ ባሉ የማዕረግ ስሞች አይጠሩም ወይም በተራቀቀ መንፈሣዊ አነጋገር አይጠቀሙም። ስለዚህ የሕዝበ ክርስትና ታላላቆች በንቀት ይመለከቷቸዋል። ቦታቸውን ማወቅ እንዳለባቸውና ለእነዚህ ሃይማኖታዊ መሪዎች የበለጠ ክብር መስጠት እንደሚገባቸው አድርገው ያስባሉ።
18. ዛሬ የሃይማኖት መሪዎች የዘነጉት ነገር ምንድን ነው?
18 ይሁን እንጂ እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች የዘነጉት ነገር አለ። የኢሳይያስ ዘመን ታላላቆች መልእክቱን ባይቀበሉትም እሱ የተናገረው እውነት ነበር። ማስጠንቀቂያዎቹም ደርሰውባቸዋል! በተመሳሳይም ዛሬ የይሖዋ ምሥክሮች የሚናገሩት ማስጠንቀቂያ እውነት ነው፤ በአምላክ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጽኑ መሠረት ያለው ነው። (ዮሐንስ 17:17) ስለሆነም ማስጠንቀቂያው ይፈጸማል።
የስሌትና የፍርዱ ሰዓት
19. ይሁዳ የሚንተባተብ ቋንቋ የሚናገሩ ባዕዳንን በጥሞና ለማዳመጥ የተገደደችው እንዴት ነበር?
19 በኢሳይያስ 28:11 ላይ እንዲህ እናነባለን፦ “በከንፈራቸው እየተንተባተቡ በሚናገሩ፣ በልዩም ልሣን በሚናገሩ ሕዝቦች ይህንን ሕዝብ ይናገረዋል።” (አዓት) የኢሳይያስ ትምህርት ለይሁዳ ሕዝብ ልክ እንደ ባዕድ ቋንቋ መንተባተብ ሆኖባቸው ነበር። ይሁዳ እሥራኤልን ከደመሰሰው የአሦር ጥቃት ቢያመልጥም ጊዜው ሲደርስ ይሖዋ በሌላ ባዕድ ይኸውም በናቡከደነፆር ተጠቅሞ የሚገባቸውን ሰጥቷቸዋል። (ኤርምያስ 5:15-17) ለእነዚህ ዕብራውያን የባቢሎናውያን ቋንቋ ሸካራና መንተባተብ ሆኖባቸው ነበር። ይሁን እንጂ በ607 ከዘአበ ኢየሩሳሌምና ቤተመቅደሷ ሲጠፉና ነዋሪዎቿም ምርኰኞች ሆነው ወደ ባቢሎን ሲጋዙ ያንን ቋንቋ ለመስማት ተገደዱ። ዛሬም በተመሳሳይ ሕዝበ ክርስትና እንደ ቀድሞዋ ይሁዳ የይሖዋን ማሳሰቢያዎች ገሸሽ ስላደረገች ዋጋዋን ማግኘት ይኖርባታል።
20, 21. የይሖዋ ምሥክሮች ሳያቋርጡ የሚያውጁት ምንድነው? የሕዝበ ክርስትና መሪዎች ግን ምን ማድረግ አሻፈረን ብለዋል?
20 ስለ እነዚህ ዓይነቶቹ ሰዎች ትንቢቱ እንዲህ ይላል፦ “እርሱም ‘ዕረፍት ይህች ናት፤ የደከመውን አሳርፉ፤ ይህችም ወደኋላ እንዲወድቁ እንዲሰበሩም ተጠምደውም እንዲያዙ የእግዚአብሔር ቃል ትዕዛዝ በትዕዛዝ፣ በትዕዛዝ፣ ሥርዓት በሥርዓት፣ ሥርዓት በሥርዓት፣ ጥቂት በዚህ ጥቂት የዚያ ይሆንባቸዋል።”—ኢሳይያስ 28:12, 13
21 ኢሳይያስ ሳያቋርጥ የአምላክን መልእክት ይናገር እንደነበረ ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮችም ሕዝበ ክርስትና ተስፋዋን በይሖዋ ቃል ላይ መጣል እንዳለባት ባለማቋረጥ ይነግሯታል። እሷ ግን ለመስማት አሻፈረኝ ብላለች። በሷ ዓይን ምሥክሮቹ በባዕድ ቋንቋ የሚንተባተቡ መስለው ይታያሉ። በማይገባት ቋንቋ ነው የሚነጋገሩት። ሕዝበ ክርስትና ለደከመው ስለመጪው የአምላክ መንግሥትና ስለ አዲስ ዓለም በመንገር ዕረፍትን ለመስጠት እምቢ ብላለች። ከዚህ ይልቅ ከዚህ ዓለም ጋር ባላት ዝምድና ሰክራለች። ለሰው ልጅ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሄዎችን ለመደገፍ ትመርጣለች። በኢየሱስ ዘመን እንደነበሩት አይሁድ ሁሉ እርሷም ለራሷ የሚያሳርፈውን መንግሥት አልፈለገችም፤ ለሌሎችም ስለዚሁ መንግሥት አትነግራቸውም።—ማቴዎስ 23:13
22. ይሖዋ የሕዝበ ክርስትናን መሪዎች ስለ ምን ነገር በቅድሚያ አስታውቋቸዋል?
22 ስለዚህ የኢሳይያስ ትንቢታዊ ቃላት ይሖዋ ሁልጊዜ ምንም ጉዳት በሌላቸው ምክሮቹ አማካኝነት ሲናገር እንደማይኖር ቀሳውስቱን ያስጠነቅቃቸዋል። በቅርቡ ይሖዋ የራሱን “ትዕዛዝ በትዕዛዝ ላይ ሥርዓት በሥርዓት ላይ” ተግባራዊ ያደርጋል። ከዚህም የተነሳ ሕዝበ ክርስትና ጉድ ይፈላባታል። ሃይማኖታዊ መሪዎቿና መንጎቻቸው “ይሰበራሉ፣ ተጠምደውም ይያዛሉ።” አዎን፤ እንደ ጥንቷ ኢየሩሳሌም ሁሉ የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ ሥርዓትም እንዳልነበረ ሆኖ ይጠፋል። ያ ሲከሰት እንዴት ያለ አስደንጋጭና ያልተጠበቀ ለውጥ ይሆናል!ካህናቱ ከይሖዋ ማሳሰቢያዎች ይልቅ መንፈሳዊ ሰካራምነትን ስለመረጡ እንዴት ያለ አስፈሪ መዓት ይወርድባቸዋል!
ልታብራራ ትችላለህን?
◻ የኤፍሬም ሰካራሞች እነማን ነበሩ? ያሰከራቸውስ ምን ነበር?
◻ የኤፍሬም ሰካራሞች የላቁ አክሊሎች የተረገጡት እንዴት ነበር?
◻ ኢሳይያስ በይሁዳ የነበረ ምን አሳፋሪ ሁኔታ አጋለጠ?
◻ ዛሬስ መንፈሳዊ ሰካራምነትን የምናየው የት ነው?
◻ ሕዝበ ክርስትና በጥንቱ የይሁዳ ሕዝብ ላይ የደረሰውን ነገር ልብ ብላ ማዳመጥ የሚገባት ለምንድን ነው?