የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
ክርስቲያናዊ አገልግሎታችንን የሚያስጌጥ ጠባይ
ሐዋርያው ጴጥሮስ “በአሕዛብ መካከል ኑሮአችሁ መልካም ይሁን” ሲል ክርስቲያኖችን መክሯል። (1 ጴጥሮስ 2:12) ሐዋርያው ጳውሎስም በአኗኗራችን ‘ስለ አምላክ የሚሆነውን ትምህርት በሁሉ ነገር ልናስመሰግን’ እንደምንችል ገልጿል። (ቲቶ 2:10) የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ በጥሩ ጠባያቸው ጥሩ ስም አትርፈዋል። አንዳንድ ምሳሌዎችን ቀጥላችሁ ተመልከቱ፦
በመልካም ጠባይ አንድ አስተማሪ ተሳበ
◻ ኮስታ ሪካ የሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ በዚያ አገር ያሉ ብዙ ወጣቶች ጥሩ ምሳሌ እንደሚያሳዩ ገልጿል። አንድ ወንድም ወደ እውነት ምን እንደሳበው ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “እኔን የሳበኝ ነገር ትንንሾችና ትልልቆች፣ ይልቁንም ትንንሽ ልጆች የሚያሳዩት ጥሩ ጠባይ ነው። አስተማሪ ሆኜ በምሠራበት ጊዜ በትምህርት ቤቴ የነበሩትን ምሥክሮች በቅርብ ለማየት አጋጣሚ አግኝቼ ነበር። ጐረቤቶቼም የይሖዋ ምሥክር የሆነ ቤተሰብ ስለነበረ እዚያም ጭምር የልጆቹን ጠባይ ለማየት ችያለሁ።
“በትምህርት ቤቴ ውስጥ በነበሩት የይሖዋ ምሥክር በሆኑትና ባልሆኑት ልጆች መካከል ጉልህ ልዩነት ተመለከትሁ። ምሥክሮቹ ሁልጊዜ በሰዓቱ ይደርሳሉ፤ ጠባያቸው የታረመ ነበር፤ በፍጹም አይዋሹም፤ የቤት ሥራቸውንም ሁልጊዜ ይሠራሉ። በፈተና ጊዜም ምንም እንኳ ሌሎቹ ልጆች ቢኰራረጁም እነርሱ ግን ታማኞች ነበሩ። ከዚህም በላይ በመምህርነቴ ሁልጊዜ ጥሩ አነጋገርና አክብሮት ያሳዩኝ ነበር። በትምህርት ቤትና በምኖርበት ቤት ወጣት ምሥክሮቹ በሚያሳዩት ጠባይ ተሳብኩና ይህን ሃይማኖት መመርመር ጀመርኩ፤ በመጨረሻም እውነት ተቀበልሁ።”
በወረዳ ስብሰባ የምናሳየው መልካም ጠባይ ጥሩ ውጤት ያመጣል
◻ በኤል ሳልቫዶር ምዕራባዊ ክፍል በሚገኝ አንድ ጉባኤ ያለ አንድ የይሖዋ ምሥክር የመንግሥቱን ምሥራች ለሁለት ሥጋዊ ወንድሞቹ ለማካፈል ፈለገ። አንዱ አዳመጠና ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። ሌላው ወንድሙ የሰላም መስፍን ተብሎ የሚጠራ የኢቫንጀሊካል ቤተክርስቲያን አባል ሲሆን ወንድሙን “አታናግረኝ፤ አንተ የዲያብሎስን ፍላጎት የምታራምድ ነህ” አለው።
የወረዳ ስብሰባ በደረሰ ጊዜ በማጥናት ላይ የነበረው ወንድሙ ሌላው ወንድሙ ወደ ስብሰባው አብሮት እንዲሄድ ጋበዘው። ወንድሙም “እሺ እሄዳለሁ፤ ግን የምሄደው የይሖዋ ምሥክሮችን በምን መንቀፍ እንደሚቻል ለማየት ብዬ ነው” አለው። ሁለቱ ወንድማማቾች በወረዳ ስብሰበው አብረው ተገኙ። የተሰብሳቢዎቹ ብዛትና በወረዳ ስብሰባው ላይ የሚታየው ሥነ ስርዓት የኢቫንጀሊካል ቤተክርስቲያን ተከታይ የሆነውን ወንድም በጣም ማረከው። እስከ ዛሬ ድረስ እንደዚህ ያለ ነገር አይቼ አላውቅም አለ። ወደ ቤት ከተመለሱ በኋላ ለወንድሙ “ጨብጠኝ አለው። እሱም “ይህ ሁሉ ነገር ምንድን ነው?” አለው። ወንድሙም “ጨብጠኝ ብቻ” ብሎ መለሰለት። ተጨባበጡና የኢቫንጀሊካል ቤተክርስቲያን አባል የሆነው ወንድም እንዲህ አለ፦ “ካሁን ጀምሮ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር አጠናለሁ። ብዙ ነገር ቀርቶብኝ እንደነበረ አላውቅም ነበር።” በአሁኑ ጊዜ እርሱም ጭምር የአምላክን መንግሥት ምሥራች በትጋትና በቅንዓት ያውጃል።