ጤንነትና ደስታ—ሊገኙ የሚችሉ ነገሮች ናቸውን?
የጤንነትና የደስታ ፍላጎት ፍጽምና የጎደላቸው ወንዶችና ሴቶች በምድር ላይ መኖር ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ የቆየ ነው። በእርግጥም እነዚህ ሁለት ነገሮች በጣም አስፈላጊ የሆኑ የሰው ምኞቶች ቢሆኑም እውን ሊሆኑ ያልቻሉ ምኞቶች ሆነዋል።
ሰዎች ለዚህ ጉዳይ ብዙ ትኩረት ሰጥተዋል፣ ብዙ ምክርም ሰጥተውበታል። ዶክተር ዴኒስ ጄፍ፦ “በዛሬው ጊዜ ዘላቂ ጤንነትና ፈውስ የማግኘቱ ቁልፍ በአብዛኛው በራስህ ባሕርይ ላይ የተመካ ነው” በማለት ገልጸዋል። አብርሃም ሊንከን አንድ ጊዜ እንዲህ ሲሉ አስተያየት ሰጥተው ነበር፦ “የሰዎች ደስተኛነት በራሳቸው አእምሮ ላይ የተመካ ነው።” በዚህ ትስማማለህን? ደስታን ምን ያህል ተግተህ ትፈልገዋለህ? ደስታንስ ማግኘት በጥሩ ጤንነት ላይ የተመካው ምን ያህል ነው?
ሰዎች ደስታን ለማግኘት በተለያዩ መንገዶች ጥረት አድርገዋል። ፍልስፍናን፣ ስነ ልቦናንና ረቂቅ ጥበባትን መርምረዋል። አንዳንዶች ደስታ የሚገኝበትን መንገድ ለመፈለግ ሲሉ ሳይንስን፣ ኪነ ጥበብንና ሙዚቃንም መርምረዋል። ሆኖም የእውነተኛ ደስታ ዋነኛ ክፍል ጥሩ ጤንነት ከማግኘት ጋር የተዛመደ መሆኑ አጠራጣሪ አልሆነም። አንድ ተወዳጅ የሆነ የቴሌቪዥን ማስታወቂያ “ጤንነት ካላችሁ ሁሉም ነገር አላችሁ” ብሏል።
ብዙ ሰዎች ይህንኑ ጎዳና በመከተል ብዙ የተለመዱና ያልተለመዱ የጤና ንድፈ አሳቦችን መርምረዋል። አብዛኛዎቹ ወይም ሁሉም ቤተ መጻሕፍት ስለ አመጋገብ ሥርዓቶችና ስለ ተለያዩ የሕክምና ዘዴዎች የሚገልጹ መጻሕፍት አሉአቸው። ዝነኛ የልብ ሕክምና ባለሞያ የሆኑት ዶክተር ፖል ደድሊ ዃይት “ከጥንት ዘመን ጀምሮ ስለ ጤና ብዙ መጻሕፍት ተጽፈዋል” ሲሉ ተናግረዋል። “ከእነዚህም የሚበልጠው ከአንድ ሺህ ዓመታት በፊት የተጻፈው ሬጂመንት ኦፍ ሄልዝ (የጤና ሕግ) ነው።”
ይህ ሁሉ ጥረት ቢደረግም ጤንነትንና ደስታን ለማግኘት የተደረገው ፍለጋ ለአብዛኞቹ ሰዎች ተስፋ የሚያስቆርጥ ሆኗል። ሥልጣኔያችን የደረሰበትን ከፍተኛ ደረጃ ስታስብ ይህ ያስገርምሃልን? በግልጽ እንደሚታየው ሳይንስ በሽታን፣ እርጅናንና ሞትን አላስወገደም።
ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ለደስታ ትክክለኛ ፍቺ ለመስጠትም ሆነ የደስታን መጠን የምንለካበት መለኪያ ለማግኘት አለመቻላችን አያስገርምህምን? ፔር ቴልሃርድ ቻርዲን “በደስታ ላይ የተደረጉ ጥናቶች” በሚል ርዕስ በሰጡት ንግግር ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “ይህ ጉዳይ ለብዙ ምዕተ ዓመታት የብዙ መጻሕፍት፣ የምርምሮች፣ በግለሰብ ደረጃም ሆነ በኅብረት የተደረጉ የብዙ ሙከራዎች ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል። ሆኖም በአንድ አሳብ ላይ ለመስማማት አለመቻሉ በጣም ያሳዝናል። ብዙዎቻችን ከብዙ ውይይት በኋላ የደረስንበት መደምደሚያ ተጨማሪ ምርምር ማድረግ ምንም ጥቅም የሌለው መሆኑን ነው።”
አንተስ ስለ ደስታ የሚሰማህ እንደዚህ ነውን? እስቲ ራስህን በሐቀኛነት አንዳንድ የግል ጥያቄዎችን ጠይቅ። በእርግጥ አሁን ደስተኛ ነህን? እውነተኛ ደስታ የሚገኘው በሰማይ ላይ ብቻ ነውን? ጤንነትና ደስታ በዚሁ ምድር ላይ እንደምናገኝ የተረጋገጠ ተስፋ አለንን?