የአምላክ ትዕግሥት የሚቆየው ለምን ያህል ጊዜ ነው?
ወደ ሦስት ሺህ ከሚጠጉ ዓመታት በፊት አንድ ጥበበኛ ሰው “ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው” በማለት ጽፎ ነበር። (መክብብ 8:9) ይህን አስተያየት ከሰጠበት ጊዜ ወዲህም እንኳ ቢሆን የተሻሻሉ ነገሮች የሉም። በታሪክ ዘመናት በሙሉ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ሥልጣን ጨብጠው ሌሎች ሰዎችን እየተፈራረቁ በጭቆና ገዝተዋል። ይሖዋ አምላክ ይህን ሁኔታ ታግሦ ቆይቷል።
መንግሥታት በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ወደ ጦርነት ለሞት ሲልኩና እንዲሁም ከባድ የሆኑ ኢኮኖሚያዊ የፍትሕ መጓደሎች እንዲኖሩ ሲያደርጉ ይሖዋ ታግሦ ቆይቷል። ዛሬም ቢሆን ሰዎች የኦዞንን ንብርብር ሲያጠፉና ከባቢውን አየርና ባሕሩን ሲያበላሹ አምላክ ታግሦአቸዋል። ለም መሬቶች ሲበላሹና ደኖችና የዱር አራዊት አለገደብ ሲጨፈጨፉ ሲያይ ምንኛ ያሳዝነዋል!
አምላክ ይህን ያህል የታገሠው ለምንድን ነው?
ይህን ጥያቄ ለመመለስ አንድ ቀላል ምሳሌ ሊረዳን ይችላል። አንድ ተቀጣሪ ሠራተኛ ሁልጊዜ አርፍዶ የሚመጣ ከሆነ በመሥሪያ ቤቱ ሥራ ላይ የሚያስከትለውን ችግር አስብ። የድርጅቱ ባለቤት ምን ማድረግ ይኖርበታል? ወዲያው ሠራተኛውን ቢያባርረው ፍትሕ አጎደለ ሊባል አይችልም። ይሁን እንጂ “ለትዕግሥተኛ ሰው ብዙ ማስተዋል አለው፤ ቁጡ ግን ስንፍናውን ከፍ ከፍ ያደርጋል” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ሊያስታውስ ይችላል። (ምሳሌ 14:29) እርምጃ ከመውሰድ መዘግየት አስተዋይነት እንደሆነ ሊሰማው ይችላል። ሥራው የበለጠ እንዳይበደል በሰውየው ቦታ የሚተካ ሰው እስኪሰለጥን ድረስ ጥቂት ጊዜ ለመቆየት ሊወስን ይችል ይሆናል።
የሰብዓዊነት ስሜትም እንዲቆይ ሊያደርገው ይችላል። ቸልተኛ የሆነው ተቀጣሪ ልማዱን እንዲያስተካክል ማስጠንቀቂያ ቢሰጠውስ? ዘወትር የሚዘገየው መፍትሔ ሊያገኝ በሚችል ችግር ምክንያት ወይም ሊሻሻል በማይችል መጥፎ ዝንባሌ ምክንያት መሆኑን ለማወቅ ቢያነጋግረውስ? የድርጅቱ ባለቤት ትዕግሥት ለማሳየት ቢወስንም ትዕግሥቱ ወሰን የሌለው አይሆንም። ሠራተኛው ልማዱን ማሻሻል ወይም ከሥራው መባረር ይኖርበታል። ለሥራውና ሕግ አክባሪ ለሆኑት ሠራተኞች ሲባል እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ይሆናል።
ከዚህ ጋር በሚመሳሰል መንገድ ይሖዋ አምላክ ለአንዳንድ ችግሮች መፍትሔ ለማምጣት የሚያስችል ጊዜ ለመፍቀድ ሲል ስህተቶች እየተሠሩ እያየ ታግሦአል። ከዚህም በላይ ትዕግሥቱ በደለኛ ሰዎች መንገዳቸውን እንዲለውጡና የዘላለም ጥቅሞችን እንዲያገኙ ዕድል ይሰጣቸዋል። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ በመታገሡ እንዳንበሳጭ ያበረታታናል። ከዚህ ይልቅ “የጌታችንም ትዕግሥት መዳናችሁ እንደሆነ ቁጠሩ” ይላል።—2 ጴጥሮስ 3:15
የአምላክ ትዕግሥት ምሳሌ
ይሖዋ አምላክ በኖኅ ዘመን ከደረሰው የጥፋት ውሃ በፊት የሰው ልጆችን ታግሦ ነበር። በዚያን ጊዜ የነበረው ዓለም በአመጽ የተሞላና በጣም ክፉ ነበር። እንዲህ እናነባለን፦ “[ይሖዋ (አዓት)] የሰው ክፋት በምድር ላይ እንደ በዛ . . . አየ። . . . [ይሖዋም (አዓት)]፦ የፈጠርሁትን ሰው ከምድር ላይ አጠፋለሁ” አለ። (ዘፍጥረት 6:5, 7) አዎን ይሖዋ በዚያን ጊዜ ለነበረው ክፋት፣ ክፉ ሰዎችን በማጥፋት የማያዳግም መፍትሔ ሊሰጠው አስቦ ነበር። ይሁን እንጂ ይህንን እርምጃ ወዲያውኑ አልወሰደም። ለምን?
ምክንያቱም ሁሉም ሰው ክፉ ስላልነበረ ነው። ኖኅና ቤተሰቡ በአምላክ ፊት ጻድቆች ነበሩ። ስለዚህ ስለ እነርሱ ሲል ይሖዋ ጥቂት ጻድቅ ግለሰቦች የሚድኑበትን ዝግጅት እንዲያደርጉ ጊዜ ሰጠ። በተጨማሪም ይህ ለረጅም ጊዜ የተደረገ ቆይታ ኖኅ “የጽድቅ ሰባኪ” በመሆን ክፉ የነበሩት ሰዎች መንገዳቸውን ለመለወጥ የሚያስችል አጋጣሚ እንዲያገኙ አስችሏል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍስ በውኃ የዳኑበት መርከብ ሲዘጋጅ፣ የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኖኅ ዘመን በቆየ ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም።”—2 ጴጥሮስ 2:5፤ 1 ጴጥሮስ 3:20
አምላክ አሁን ታጋሽ የሆነበት ምክንያት
ዛሬም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ምድር አሁንም እንደገና በአመጽ ተሞልታለች። በኖኅ ዘመን እንዳደረገው አምላክ በዚህ ምድር ላይ ቀደም ሲል ፍርዱን ሰጥቷል፤ ስለዚህ ጉዳይ መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔርን የማያመልኩት ሰዎች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ተጠብቀው” እንዳሉ ይናገራል። (2 ጴጥሮስ 3:7) ይህ በሚሆንበት ጊዜ አካባቢን ማቆሸሽ፣ ደካሞችን መጨቆን፣ ወይም በስስት ሥልጣንን አላግባብ መጠቀም አይኖርም።
ታዲያ አምላክ እስካሁን አምላክ የለሽ ሰዎችን ለምን አላጠፋቸውም? ምክንያቱም መፍትሔ ማግኘትና መስተካከል የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች በመኖራቸው ነው። በእርግጥም ይሖዋ ብዙ ነገሮችን ለሚጨምረው የክፋት ችግር ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ከበሽታና ከሞት ባርነት ለማዳኑ ችግር ጭምር ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ወደፊት በመግፋት ላይ ነው።
ይህን በመጨረሻ የተገለጸውን ነገር በአእምሮው በመያዝ ይሖዋ ለኃጢአታችን ቤዛ ሊሰጥ የሚችል አንድ አዳኝ ለማዘጋጀት አሰበ። ስለ እርሱም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።” (ዮሐንስ 3:16) ኢየሱስ መጥቶ ለሰው ዘር ሲል ሕይወቱን መስዋዕት የሚያደርግበትን መንገድ ለማዘጋጀት በሺዎች የሚቆጠሩ ዓመታት ወስዷል። በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ውስጥ አምላክ በፍቅር ታግሦአል። ይሁን እንጂ ይህ ዝግጅት ቢጠበቅ የሚገባው ጉዳይ አይደለምን?
ኢየሱስ ወደ ሁለት ሺህ ከሚጠጉ ዓመታት በፊት ለሰው ዘር መስዋዕትን አቅርቧል። ታዲያ አምላክ እስከ አሁን ድረስ ትዕግሥት ማሳየቱን የቀጠለው ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት የኢየሱስ መሞት የአንድ የትምህርት ዘመቻ መጀመር ምልክት በመሆኑ ነው። የሰው ዘሮች ይህንን ፍቅራዊ ዝግጅት መማርና ሊቀበሉት ወይም ሊተዉት ዕድል ማግኘት ይኖርባቸዋል። ይህ ጊዜ የሚወስድ ሊሆን ይችላል፤ ቢሆንም በጥሩ ነገር ያለፈ ጊዜ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው [ይሖዋም (አዓት)] ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፣ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል።”—2 ጴጥሮስ 3:9
የመንግሥት ጥያቄ
ሌላ ጊዜን የሚወስድ አስፈላጊ የሆነ ጉዳይም አለ። የሰውን መንግሥት ችግር ማስተካከሉም አስፈላጊ የሆነ ጉዳይ ነው። በመጀመሪያ ሰው በመለኮታዊ መንግሥት ሥር ይኖር ነበር። ሆኖም በኤደን ገነት ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን በዚህ አገዛዝ ላይ ጀርባቸውን አዞሩ። ከአምላክ ነፃ ለመሆንና ራሳቸውን በራሳቸው ለመግዛት ፈለጉ። (ዘፍጥረት 3:1-5) እንደ እውነቱ ከሆነ ሰው ራሱን እንዲገዛ አልተፈጠረም። ነቢዩ ኤርምያስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ይሖዋ ሆይ፣ ለምድራዊ ሰው መንገዱ ከራሱ እንዳልሆነ በሚገባ አውቃለሁ። ለሚራመደው ሰው እርምጃውን እንኳ ለማቅናት አልተሰጠውም።”—ኤርምያስ 10:23፤ ምሳሌ 20:24
የሆነው ሆኖ የመንግሥት ጥያቄ ከተነሣበት ጊዜ ጀምሮ ይሖዋ ለጉዳዩ መፍትሔ ለመስጠት በትዕግሥት ጊዜ ፈቅዷል። በእርግጥም በቸርነቱ ሰው የሚቻለውን ያህል ሁሉንም ዓይነት አገዛዝ እንዲሞክር በሺዎች የሚቆጠሩ ዓመታትን ፈቅዷል። ይህ ያስገኘው ውጤት ምን ነበር? ማንኛውም ዓይነት የሰው አገዛዝ ጭቆናን፣ አድልዎን፣ ወይም ለሐዘን ምክንያት የሚሆኑ ሌሎች ነገሮችን ለማስወገድ እንደማይችል ግልጽ ሆኗል።
ከሰው ዘር ታሪክ አንጻር ሲታይ አምላክ ሁሉንም መንግሥታት ለማስወገድና በራሱ መንግሥት ለመተካት ያለውን ዕቅዱን ሲገልጽ ፍትሕ የጎደለው ነው ብሎ ለመናገር የሚችል ሰው ይኖራልን? ማንም እንደማይኖር ምንም አያጠራጥርም። የሚከተለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት አፈጻጸም በአዎንታ እንቀበለዋለን፦ “በእነዚያም ነገሥታት ዘመን የሰማይ አምላክ ለዘላለም የማይፈርስ መንግሥት ያስነሣል፤ ለሌላ ሕዝብም የማይሰጥ መንግሥት ይሆናል፤ እነዚያንም መንግሥታት ሁሉ ትፈጫቸዋለች ታጠፋቸውማለች፣ ለዘላለምም ትቆማለች።”—ዳንኤል 2:44
የዚያች መንግሥት ሰማያዊ ንጉሥ ከሞት የተነሣው ኢየሱስ ነው። እርሱን ለዚያ ሥልጣን ማዘጋጀቱ እንዲሁም ከእርሱ ጋር አብረው የሚገዙትን መምረጡ ጊዜ ወስዷል። በዚህን ጊዜ ሁሉ አምላክ ትዕግሥት አሳይቷል።
በአሁኑ ጊዜ ከአምላክ ትዕግሥት ተጠቀሙ
ዛሬ በ212 አገሮች ውስጥ የሚገኙ በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ግለሰቦች ከአምላክ ትዕግሥት ተጠቅመዋል። አምላክን ለመታዘዝና ሰማያዊው መንግሥቱን ለማገልገል ባላቸው ምኞት አንድ ሆነዋል። በመንግሥት አዳራሾቻቸው ውስጥ በአንድነት በሚሰበሰቡበት ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በሥራ ላይ ማዋሉ ምን ያህል የተሻለ እንደሆነ ይማራሉ። እነዚህ መንግሥታት ሥራቸውን እንዲቀጥሉ አምላክ ታግሦ እስከፈቀደላቸው ድረስ ራሳቸውን ለሰብአዊ መንግሥታት የሚያስገዙ ቢሆንም እንኳ በዚህ ዓለም ከፋፋይ ፖለቲካ አይሳተፉም።—ማቴዎስ 22:21፤ ሮሜ 13:1-5
እንደዚህ ያለው በብዙ ሰዎች መካከል የሚገኝ ኅብረት ይሖዋን በነፃ ፈቃደኝነት እርሱን እንዲያፈቅሩ በተማሩትና እርሱን ለማገልገል በሚፈልጉት ሰዎች መካከል ስምምነትን ለመፍጠር የሚችል እንደሆነ አድርጎ ያሳውቀዋል። እነዚህ ሰዎች ኢየሱስ ራሱ ጀምሮት የነበረውን ሥራ ይኸውም የአምላክን መንግሥት የምሥራች የማስፋፋቱን ሥራ በመሥራት ላይ እያሉ ሳያጋጥሙህ እንደማይቀር አያጠራጥርም። ኢየሱስ እንደሚከተለው ብሎ በመናገር ይህ ሥራ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚደርስበትን ሁኔታ ተንብዮአል፦ “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።”—ማቴዎስ 24:14
ከአሁን በኋላ ብዙ አይቆይም!
የአምላክ የጽድቅ መንግሥት የምድርን የዕለት ተዕለት አገዛዝ እንድትረከብ የተደረጉት ዝግጅቶች ወደ መጠናቀቅ መድረሳቸውን በዓይን የሚታየው ማስረጃ ያረጋግጣል። ኢየሱስ በዚህ መቶ ዘመን ውስጥ የተመለከትናቸውን በሰው አገዛዝ ድክመት ምክንያት የመጡትን አሳዛኝ ውጤቶች ከገለጸ በኋላ እንዲህ አለ፦ “እንዲሁ ደግሞ እናንተ ይህ ሁሉ መሆኑን ስታዩ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደቀረበች እወቁ።”—ሉቃስ 21:10, 11, 31
አምላክ በቅርቡ ክፋትን ከምድር ገጽ ያስወግዳል። የመዝሙራዊው ቃላትም ቃል በቃል ተፈጻሚ ይሆናሉ፦ “ክፉ አድራጊዎች ይጠፋሉና . . . ገና ጥቂት፣ ኃጢአተኛም አይኖርም፤ ትፈልገዋለህ ቦታውንም አታገኝም።” (መዝሙር 37:9, 10) ክፋት የሌለበት ዓለም በዓይነ ሕሊናህ ይታይሃልን? በዚያን ጊዜ ነገሮችን የሚመራው ማን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “እነሆ፣ ንጉሥ [በሰማያት የነገሠው ክርስቶስ ኢየሱስ] በጽድቅ ይነግሣል፣ መሳፍንትም [በምድር ላይ የሚገኙት ታማኝ ተሿሚዎቹ] በፍርድ ይገዛሉ። የጽድቅም ሥራ ሰላም፣ የጽድቅም ፍሬ ለዘላለም ጸጥታና መታመን ይሆናል። ሕዝቤም በሰላም ማደሪያ በታመነም ቤት በጸጥተኛ ማረፊያ ይቀመጣል።”—ኢሳይያስ 32:1, 17, 18
ስለዚህ የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት የሰው ስህተት ያስከተላቸውን መጥፎ ውጤቶች ታስወግዳለች፤ በአንድ ስምም በሆነ ሰብአዊ ኅብረተሰብ ውስጥ በመሆን በእርሱ ተስፋ የሚያደርጉትን ታደራጃለች። ይህንን ስምምነት ሲገልጽ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡- “ተኩላ ከበግ ጠቦት ጋር ይቀመጣል፣ ነብርም ከፍየል ጠቦት ጋር ይተኛል፤ ጥጃና የአንበሳ ደቦል ፍሪዳም በአንድነት ያርፋሉ፤ ታናሽም ልጅ ይመራቸዋል። . . . በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ አይጎዱም አያጠፉምም፤ ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር [ይሖዋን (አዓት)] በማወቅ ትሞላለችና።”—ኢሳይያስ 11:6-9
ይህ አምላክ ትዕግሥት በማሳየቱ የተገኘ እንዴት ያለ አስደናቂ ውጤት ነው! ስለዚህ አምላክ ለረጅም ጊዜ ቆየ ብለህ ከማጉረምረም ይልቅ ለምን በትዕግሥቱ ተጠቅመህ ራስህን የመንግሥቱ ተገዢ አታደርግም? የእርሱ የአቋም ደረጃዎች ምን እንደሆኑ ከመጽሐፍ ቅዱስ ተምረህ ከእነርሱ ጋር ተስማማ። በስምምነት ለእርሱ ተገዢ ከሆኑት ከሌሎች ጋር ተባበር። እንደዚህ ካደረግህ የአምላክ ትዕግሥት የዘላለም በረከት ያመጣልሃል።