የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w91 10/15 ገጽ 29-30
  • “ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ”

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • “ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ”
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ገነት
    ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር
  • “ገነት ውስጥ እንገናኝ!”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2018
  • “ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2022
  • ከአንድ ወንጀለኛ የምናገኘው ትምህርት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2013
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
w91 10/15 ገጽ 29-30

“ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ”

ወንጀለኛው በሚሞትበት እንጨት ላይ ተሰቅሎ በስቃይ ሲሞት ሳለ በጎኑ ለተሰቀለው ለኢየሱስ “ጌታ ሆይ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ” ብሎ ልመና አቀረበ። ኢየሱስም ራሱ በሥቃይ እየሞተ የነበረ ቢሆንም “እውነት እልሃለሁ ዛሬ፤ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” በማለት መልስ ሰጠ። (ሉቃስ 23:42, 43) ይህ ቃል በመሞት ላይ ላለ ሰው በጣም የሚያጽናና ተስፋ ነበር።

ከላይ የተጠቀሰው የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም እነዚህን የኢየሱስን ቃላት ሲተረጉም ነጠላ ሰረዙን ያስቀመጠው “ዛሬ” ከሚለው ቃል በኋላ መሆኑን አስተውላችኋልን? ይህም ሐሳብ የሚያስተላልፈው ኢየሱስ በሞቱ ቀንም ሳይቀር ለዚያ ወንጀለኛ የገነትን ሕይወት ተስፋ መስጠት ችሎ እንደነበረ ነው። በሌላ በኩል ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል የኢየሱስን ቃላት እንደሚከተለው ያለ ነጥብ አድርጎለታል፦ “ይህን እነግርሃለሁ፦ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ።” ሌሎች ብዙ ትርጉሞችም ኢየሱስና ያን ዕለት የሞተው ወንጀለኛ በዚያኑ ዕለት ወደ ገነት መሄዳቸው ነበር የሚለውን ሐሳብ በማስተላለፍ ከዚህ ትርጉም (ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል) ጋር ይስማማሉ። ከአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ጋር ለምን ተለያዩ? ትክክለኛው የየትኛው የነጥብ አቀማመጥ ነው?

እንደ እውነቱ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በእጅ በተጻፈበት የጥንቱ የግሪክኛ ስነ ጽሑፍ ሥርዓተ ነጥብ የሚባል ነገር አልነበረም። ስለዚህ ሥርዓት ነጥብን መጠቀም ለመጀመሪያ ጊዜ ሲጀመር የመጽሐፍ ቅዱስ ገልባጮች (ቅጂ አዘጋጆችና ተርጓሚዎች) የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በተረዱበት መሠረት ሥርዓት ነጥቡን ማስገባት ነበረባቸው። ታዲያ የተለመደው ትርጉም አቀራረብ ትክክል ነው? ኢየሱስና ክፉ አድራጊው በሞቱበት ዕለት ወደ ገነት ሄደዋልን?

አልሄዱም። በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት የሄዱት በግሪክኛው ሐዴስ በዕብራይስጥ ደግሞ ሺኦል ወደተባለው ቦታ ሲሆን ሁለቱም ቃላት (ሐዴስና ሺኦል) የሚያመለክቱት የሰውን ልጅ የጋራ መቃብር ነው። (ሉቃስ 18:31-33፤ 24:46፤ ሥራ 2:31) በዚህ ቦታ (በሺኦል ወይም በሐዴስ) ስላሉት ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ፦ “ሙታን ግን አንዳች አያውቁም. . . አንተ በምትሄድበት በሺኦል (ግሪክኛው ሐዴስ) ሥራና አሳብ፣ ዕውቀትና ጥበበ አይገኙምና” ይላል።​—መክብብ 9:5, 10

ኢየሱስ እስከ ሦስተኛው ቀን ድረስ ከሐዴስ አልተነሣም ነበር። ከዚያም በኋላ ለስድስት ሳምንታት ያህል በፓለስቲና ምድር ለነበሩት ተከታዮቹ ብዙ ጊዜ ተገልጦላቸዋል። ከእነዚያ ወቅቶች በአንዱ ለማርያም “ገና ወደ አባቴ አላረግሁም” ብሎ ነግሮአታል። (ዮሐንስ 20:17) ስለዚህ ከሞት ከተነሣም እንኳን ገነት ሊባል ወደሚችል ማንኛውም ቦታ አልሄደም።​—ራእይ 2:7

የክርስትና ትምህርትና የግሪክ ፍልስፍና ውሕደት እየተጧጧፈ በነበረበት በሦስተኛው መቶ ዘመን እዘአ ኦሪገን ኢየሱስ “ዛሬ ከእኔ ጋር በእግዚአብሔር ገነት ትሆናለህ” እንዳለ አድርጎ ተናግሮአል። በአራተኛው መቶ ዘመን እዘአ የቤተ ክርስቲያን ጸሐፊዎች ሥርዓተ ነጥብ “ዛሬ” ከሚለው ቃል በኋላ ለምን ተደረገ ብለው ተከራከሩ። ይህም የተለመደው የኢየሱስ ቃላት አነባበብ የቆየ ታሪክ እንዳለው ያሳያል። ነገር ግን በአራተኛው መቶ ዘመን እዘአ እንኳ ሳይቀር የኢየሱስን ቃላት አንዳንዶች በአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ውስጥ በተተረጎሙበት መንገድ ያነብቡት እንደነበረ ያመለክታል።

በዛሬው ጊዜም ብዙ ተርጓሚዎች የሉቃስ 23:43ን ሥርዓተ ነጥብ በቤተ ክርስቲያን ልማድ መሠረት ቢያደርጉም አንዳንዶች የአዲሲቱ ዓለም ትርጉምን ሥርዓተ ነጥብ ተጠቅመዋል። ለምሳሌ ያህል በፕሮፌሰር ቪልሄልም ሚክኤሊስ የጀርመንኛ ትርጉም መሠረት የኢየሱስ ቃላት “በእውነት ይህን ማረጋገጫ ዛሬውኑ እሰጥሃለሁ (አንድ ቀን) ከእኔ ጋር በአንድነት በገነት ትሆናለህ” በማለት ይነበባሉ።

ታዲያ የኢየሱስ ቃላት ለዚያ ክፉ አድራጊ ምን ትርጉም ነበራቸው? ክፉ አድራጊው ኢየሱስ ተስፋ የተደረገው ንጉሥ ነው ሲባል ሰምቶ ይሆናል። ሌላው ቢቀር ጲላጦስ ጽፎ ከኢየሱስ ራስ በላይ ስለሰቀለው “የአይሁድ ንጉሥ” የሚል ማዕረግ ያውቅ እንደነበር ጥርጥር የለውም። (ሉቃስ 23:35-38) የሃይማኖት መሪዎች ኢየሱስን አጥብቀው ቢቃወሙም ይህ ንስሐ የገባ ወንጀለኛ “ኢየሱስ ሆይ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ” በማለት እምነት አሳይቷል። ከኢየሱስ ጋር ለመግዛት ተስፋ አላደረገም። ነገር ግን ከኢየሱስ አገዛዝ ለመጠቀም ፈልጎ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ በከባድ መከራ ላይ ሳለ ክፉ አድራጊው በገነት ከሱ ጋር እንደሚሆን ቃል ገባለት።

በየትኛው ገነት? በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት የመጀመሪያዋ ገነት የመጀመሪያ ወላጆቻችን ያጠፉአት በኤደን ምሥራቅ የነበረችው መናፈሻ መሰል የአትክልት ስፍራ ነበረች። መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ንጉሡ በሆነለት የአምላክ መንግሥት አማካኝነት ምድራዊ ገነት እንደሚመለስ ተስፋ ሰጥቷል። (መዝሙር 37:9-11፤ ሚክያስ 4:3, 4) ስለዚህ ኢየሱስ ያንን ክፉ አድራጊና ሌሎች ቁጥር ስፍር የሌላቸውን ሙታን የአምላክን ፈቃድ ማድረግን እንዲማሩና ለዘላለም የመኖርን አጋጣሚ እንዲያገኙ ከመቃብር አስነሥቶ በምድራዊ ገነት ላይ በሚያኖራቸው ጊዜ ከእነሱ ጋር ይሆናል።​—ዮሐንስ 5:28, 29፤ ራእይ 20:11-13፤ 21:3, 4

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ