መበቀል ስሕተት ነውን?
በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በአንድ መኪናዎች በፍጥነት በሚተላለፉበት ሰፊ መንገድ ላይ አንድ ባለመኪና ወደ ዳር ወጣ ብሎ ሊያቆምና ከኋላው የሚመጣውን መኪና ሊያሳልፍ ፈልጎ ቀስ እያለ ይነዳ ነበር። የሁለተኛው መኪና ነጂ ባናደደው መኪና ላይ ተኮሰበትና ከምኑም የሌለበትን ንጹሕ ተሳፋሪ ገደለ።
አንዲት በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል የምትገኝ ልጃገረድ በትምህርት ቤት ጨዋታ በሌላ ልጃገረድ ተሸነፈች። ላሸነፈቻት ልጃገረድ የወንድ ጓደኛ ልጂቱ አንድ የሌላ ትምህርት ቤት ልጅ ጓደኛ እንደያዘች በሐሰት በመናገር ተበቀለቻት። በመሆኑም ከወንድ ጓደኛዋ ጋር ያላትን ዝምድና አበላሸችባት።
ብዙ ሰዎች የተበደሉ በሚመስላቸው ጊዜ በቀል መመለስ ትክክል ሆኖ ይሰማቸዋል። በአንዱም ይሁን በሌላው መንገድ “ተበቀል እንጂ አትናደድ” የሚለውን መርሕ ይከተላሉ። በዛሬው ጊዜ የጎረቤት ፍቅር እጅግ የተመናመነ ሲሆን የበቀል መንፈስ ግን እየጨመረ ነው።—ማቴዎስ 24:12
የሆነ ሆኖ አንተ በቀልን እንዴት ትመለከተዋለህ? በመጽሐፍ ቅዱስ የምታምን ከሆነ በቀል በመሠረቱ ስሕተት መሆኑ ይሰማህ ይሆናል። ነገር ግን የምንኖረው አምላካዊ ባልሆነ ዓለም ውስጥ በመሆኑ የበቀል ተቃራኒ የሆነው ይቅር ባይነት ብዙውን ጊዜ የማያዋጣ እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል። ተታልለህ ወይም ተቀምተህ ከሆነ ምን ይሰማሃል? አንድ ሰው ችላ ቢልህ ወይም አንተን በማንቋሸሽ ለሌሎች ቢናገር ቂም ትይዝበታለህን? ተበቃይ ነህ ወይስ ይቅር ባይ?
የቂመኛነት ዝንባሌ ይጎዳል
በእርግጥ የተለያዩ የማስቀየም ደረጃዎች አሉ። ሰውን ለመበቀል የሚፈልጉ አብዛኞቹ ሰዎች ግን ቅሚያ ወይም የድብደባ ወንጀል የተፈጸመባቸው አይደሉም። በዚህ አንቀጽ መጀመሪያ ላይ የተጠቀሱት “ጥፋቶች” ለመበቀል ለወሰኑት ሰዎች አስተሳሳብ ትልቅ ሆነው ቢታዩም ከቁም ነገር የማይገቡ ነበሩ።
መጽሐፍ ቅዱስ የበቀል ዝንባሌ መኮትኮት እንደሌለብን ይናገራል። ምሳሌ 24:29 እንዲህ በማለት ይናገራል፦ “እንዳደረገብኝ እንዲሁ አደርግበታለሁ፤ እንደ ሥራውም እመልስበታለሁ አትበል።” ለምን? መጀመሪያ ነገር እንዲህ ዓይነቱ ዝንባሌ በስሜትና በአካል ላይ ጉዳት የሚያስከትል ነው። የበቀል አስተሳሰቦች የአእምሮ ሰላም በማሳጣት ጤናማ አስተሳሰብን ያቃውሳሉ። ይህን የዜና ዘገባ ተመልከት፦ “ሁለት ገበሬዎች ከልጅነታቸው ጀምሮ ለ40 ዓመት የቆየ ቂም ስለነበራቸው ከኋላ ክፍት በሆኑ የጭነት መኪናዎቻቸው ላይ ሆነው በመታኮስ ተገዳደሉ።” ተመልከት፣ የእነዚህ ሁለት ሰዎች አስተሳሰብ ዕድሜአቸውን በሙሉ በሚያመረቅዝ የበቀል ስሜት ተመርዞ ነበር ማለት ነው!—ምሳሌ 14:29, 30
የበቀል መንፈስ መኮትኮት የሌለብን ሌላው ምክንያት ከባድ ጥፋት የፈጸሙብንም ሰዎች ቢሆኑ ሊለወጡ የሚችሉ መሆናቸው ነው። ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ጳውሎስ በአንድ ወቅት በደቀመዝሙሩ እስጢፋኖስ መገደል ተስማምቶና “ የጌታን ደቀመዛሙርት ለመግደል ዝቶ” ነበር። ነገር ግን ተለወጠ። ዓመታት ካለፉ በኋላ ቀደም ሲል ሕይወቱ በጳውሎስ ምክንያት አደጋ ሊደርስበት የነበረው ሐዋርያው ጴጥሮስ “የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ” በማለት ጠርቶታል። (ሥራ 8:1፤ 9:1፤ 2 ጴጥሮስ 3:15) ጳውሎስ ታውሮ ሐናንያን ሲጠብቅ ሳለ ክርስቲያኖች ደማስቆ አግኝተውት ለመበቀል ሊሞክሩ ይችሉ ነበር። (ሥራ 9:3-15) ይህም በጣም ትልቅና አሳዛኝ ስሕተት በሆነ ነበር!
ስለዚህ ጳውሎስ በሮሜ 12:20 ላይ “ጠላትህ ቢራብ አብላው፤ ቢጠማም አጠጣው” ሊል ችሏል። ለምን? ምክንያቱም ጠላታችንን ራሳችን ከተበቀልን የሱን ልብና በመሃላችን ያለውን ጠላትነት እናጠነክረዋለን። ነገር ግን ላስቀየመን ሰው መልካም ካደረግን ሁኔታውን ልናለሰልሰውና ወዳጃችን ወደመሆን ልንለውጠው እንችላለን።
የራሳችንን ድክመቶች መገንዘብም ወደመበቀል ምኞት የሚመራውን መራራነት ለማሸነፍ ይረዳናል። መዝሙራዊው “አቤቱ ያህ ሆይ ኃጢአትንስ ብትጠባበቅ ይሖዋ ሆይ ማን ይቆማል?” በማለት ጠይቋል። (መዝሙር 130:3 (አዓት)) ሁላችንም ሌሎችን አስቀይመናል። ለመበቀል ሳይሞክሩ በመቅረታቸው አልተደሰትንምን? እኛስ በተመሳሳይ ራሳችንን ከመበቀል ልንገታ አይገባንም? ኢየሱስ “ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉላቸው” በማለት መክሯል።—ማቴዎስ 7:12
እውነት ነው መጽሐፍ ቅዱስ “ክፋትን ጥሉ” ይላል። (መዝሙር 97:10፤ አሞጽ 5:15) ነገር ግን ክፋት ያደረገውን ሰው እንድንጠላ አይነግረንም። እንዲያውም ኢየሱስ “ጠላቶቻችሁን መውደዳችሁንና ለሚያሳድዷችሁ መጸለያችሁን ቀጥሉ” በማለት አዝዟል። (ማቴዎስ 5:44 (አዓት)) ክፋትን በክፋት ከመለስን የክፉ አድራጊውን መንፈስ ቀዳን ማለት ነው። የጥንቱ ምሳሌ “ክፉ እመልሳለሁ አትበል። ይሖዋን ተማመን፤ እሱም ያድንሃል” ይላል። (ምሳሌ 20:22) ምንኛ የጥበብ ዝንባሌ ነው! ክፋት አድራጊዎችን የመምሰልና ግፊት በመቋቋም አሸናፊዎች መሆናችንን ማሳየት እንዴት የተሻለ ነው!—ዮሐንስ 16:33፤ ሮሜ 12:17, 21
ቅጣት መስጠት የሚገባው ማን ነው?
እርግጥ አንዳንድ ድርጊቶች ከግል ጉዳት ወይም ውርደት የበለጠ ክብደት ይኖራቸዋል። የአንድ ዓይነት ወንጀል ተጠቂዎች ሆነን ከነበረስ? ለፍትሕ ሲባል አንድ ነገር መደረግ እንዳለበት ይሰማናል። ግን ምን መደረግ አለበት? በአንዳንድ ሕብረተሰቦች ውስጥ ጉዳዩን በግል መበቀል ያልተለመደ ነገር አይደለም። ነገር ግን እንዲህ ዓይነት ኅብረተሰቦች ብዙውን ጊዜ በደም በቀል ተለያይተው ይቀራሉ። ዛሬ የአምላክ ሕግም ሆነ አብዛኛው የሰው ሕግ ግለሰቦች ወንጀለኞችን ራሳቸው እንዲበቀሉ አይፈቅዱም። ይህም የሆነው በጥሩ ምክንያት ነው። እንዲህ ዓይነቶቹ በግል የሚመለሱ በቀሎች ተጨማሪ ዓመፅን ይወልዳሉ።
ታዲያ አንድ በዓመፅ የተጠቃ ሰው ጉዳቱን ተሸክሞ አርፎ ቁጭ ይበል ማለት ነውን? ስብዕናችን ወይም ንብረታችን ሲደፈር አቤት የምንልባቸው ባለሥልጣኖች አሉ። ፖሊስ መጥራት ትፈልግ ይሆናል። በሥራ ቦታ ከሆነ ወደ ሥራ አስኪያጁ ልትሄድ ትችላለህ። በትምህርት ቤት ለርዕሰ መምህሩ አቤቱታ ልታቀርብ ትችላለህ። እዚያ ሥልጣን ላይ ከተቀመጡበት ምክንያቶች አንዱ ፍትሕን ማስከበር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ መንግሥታዊ ባለሥልጣኖች “ቁጣውን ለማሳየት ክፉውን የሚበቀል የእግዚአብሔር አገልጋይ” መሆናቸውን ይናገራል። (ሮሜ 13:4) መንግሥታት ሥልጣናቸውን በሥራ እንዲገልጹ ክፉ አድራጎትን እንዲያስቆሙና ክፉ አድራጊዎችን እንዲቀጡ የፍትሕ ሥርዓት ይጠይቅባቸዋል።
እውነት ነው አንዳንድ ጊዜ ፍትህ በቶሎ አይፈጸምም። አንድ ዓለም የሰለቸው ጸሐፊ “ፍትሕ ሁልጊዜ ዘግይቶ እንደሚደርስ ባቡር ነው” ብሏል። እውነትም አንዳንድ ጊዜ ባቡሩ ጭራሹንም ሳይደርስ ይቀራል። ሕገ ወጥ ሰዎች ባለሥልጣኖች ሊቆጣጠሯቸው እስከማይችሉ ድረስ ኃይለኞች ሊሆኑ ይችላሉ። ያም ቢሆን የጥበብ መንገድ የሚሆነው ራስን መቆጣጠር ነው። “ሰነፍ ሰው ቁጣውን ሁሉ ያወጣል፣ ጠቢብ ግን በውስጡ ያስቀረዋል” ይላል መጽሐፍ ቅዱስ። —ምሳሌ 29:11
መበቀል የሚገባው ማነው?
ራሳችንን ከበቀል መግታታችን ጥቅም አለው። ፍትሕ መሟላት ያለበት ከሆነ አምላክ በተገቢው ጊዜ እንደሚያደርገው በማወቅ ረጋ ብለን ልንጠብቅ እንችላለን። ይሖዋ ቁጥጥር ያልተደረገበት ክፉ አድራጎት ወደ ክፋትና ሕገወጥነት እንደሚመራ ያውቃሉ። (መክብብ 8:11) ልማደኛ ዓመፅ አድራጊዎች የሰው ልጆችን ለዘላለም እንዲጨቁኑ አይፈቅድላቸውም። ለዚህ ነው ሐዋርያው ጳውሎስ “ወዳጆች ሆይ ራሳችሁ አትበቀሉ፣ ለቁጣው ፈንታ ስጡት እንጂ ‘በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ’ ይላል ይሖዋ ተብሎ ተጽፎአልና” በማለት የመከረን። (ሮሜ 12:19) በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ ፈጣሪአችን የሚበቀልበት ቀን እንዳለ ይናገራል። ይህ የበቀል ቀን የትኛው ነው? የአምላክ የበቀሉ ዒላማዎች የሚሆኑትስ እነማን ናቸው? ይህንን በሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት ላይ እንወያይበታለን።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የመበቀልን ስሜት ለመቆጣጠር የሚከተሉትን አስታውስ
□ አምላክ ስለ ፍትሕ አጥብቆ ያስባል
□ ቂም መያዝና ለመበቀል መፈልግ ጎጂ ነው
□ ደግ መሆን ከሌሎች ጋር የሚፈጠረውን ግጭት ያለዝባል
□ እኛ የፈጸምናቸው ብዙ በደሎች በይቅርታ ታልፈዋል
□ በደል የፈጸሙ ሰዎች ሊለወጡ ይችላሉ
□ ዓለምን ድል የምናደርገው መንገዶቹን በመቃወም ነው