ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ሙሴ ያለ ነቢይ የነበረው እንዴት ነው?
ይሖዋ አምላክ አይዋሽም። (ቲቶ 1:2፤ ዕብራውያን 6:18) በዚህም ምክንያት የቃሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች አስተማማኝና እውነተኛ ናቸው።
ከእነዚህ በመለኮታዊ መሪነት ከተጻፉት ትንቢቶች መሃል ዕብራዊው ነቢይ ሙሴ መሲሑን በሚመለከት የመዘገበው ቃል ይገኝበታል። ሙሴ ይሖዋ የተናገረውን በመጥቀስ “(ከእስራኤላውያን) ከወንድሞቻችሁ መካከል እንደ አንተ ያለ ነቢይ አስነሣለሁ። ቃሌንም በአፉ አደርጋለሁ፣ ያዘዝሁትንም ቃል ይነግራችኋል” ብሎ ነበር።—ዘዳግም 18:17, 18
ሐዋርያው ጴጥሮስ “ሙሴም ለአባቶች [ይሖዋ (አዓት)] አምላክ እኔን እንዳስነሣኝ ነቢይን ከወንድሞቻችሁ መካከል ያስነሣላችኋል፤ በሚነግራችሁ ሁሉ እርሱን ስሙት አለ” ብሎ በተናገረ ጊዜ ይህ ትንቢት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚናገር እንደሆነ ገልጿል። (ሥራ 3:22) እንዲያውም ኢየሱስ ራሱ “ሙሴን ብታምኑት ኖሮ እኔን ባመናችሁ ነበር። እርሱ ስለእኔ ጽፏልና” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 5:46) ኢየሱስና ሙሴ የሚመሳሰሉት በምን መንገዶች ነበር?
በሕይወታቸው መጀመሪያ ላይ ተመሳሳይ ሁኔታዎች ገጥመዋቸው ነበር
ሙሴና ኢየሱስ ሁለቱም ሕፃናት በሙሉ ሲገደሉ ያመለጡ ናቸው። ሕፃኑ ሙሴ እሥራኤላውያን ወንዶች ልጆች በሙሉ እንዲገደሉ ከግብጽ ፈርዖን በታዘዘው መሠረት ከግድያው ሊያመልጥ የቻለው በአባይ ወንዝ ዳር በቄጤማ ውስጥ ተሸሽጎ ነበር። ኢየሱስም በሕፃንነቱ በቤተልሔምና በአውራጃዎቿ በሙሉ የነበሩ እስከ ሁለት ዓመት የሆናቸው ሕፃናት ሲገደሉ አምልጧል። ይህ ግድያ የታዘዘው እንደ ፈርዖን የአምላክና የአምላክ ሕዝቦች ጠላት በነበረው በታላቁ ሄሮድስ ነበር።—ዘጸአት 1:22–2:10፤ ማቴዎስ 2:13-18
ሙሴና ኢየሱስ ሁለቱም የየዋህነት ወይም የትሕትና መንፈስ አሳይተዋል። ሙሴ ያደገው በኃያሉ የግብጽ ንጉሥ ቤተሰብ ውስጥ እንደ ልጅ ተቆጥሮ ቢሆንም “በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ሰው” ሆኗል። (ዘኁልቁ 12:3) ከዚህ ጋር በሚመሳሰል መንገድ ኢየሱስም በሰማይ ሳለ ኃያሉ መሥፍን ሚካኤል ሆኖ ያገለገለ ቢሆንም በትህትና ወደ ምድር መጥቷል። (ዳንኤል 10:13፤ ፊልጵስዩስ 2:5-8) ከዚህም በላይ ኢየሱስ ለሰዎች ርኅራኄ ስለነበረው “ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ። እኔ የዋህ በልቤም ትሁት ነኝና ለነፍሳችሁም እረፍት ታገኛላችሁ” ብሎ ሊናገር ችሏል።—ማቴዎስ 11:29፤ 14:14
ሙሴና ኢየሱስ ሁለቱም ለይሖዋ አገልግሎት ሲሉ ስም የሚያስጠራ ሥልጣንና ከፍተኛ ሀብትን የማግኘት አጋጣሚያቸውን ትተዋል። ሙሴ ይሖዋንና ሕዝቡን ለማገልገል ሲል በግብጽ የነበረውን ሀብትና የተከበረ ደረጃውን ትቷል። (ዕብራውያን 11:24-26) በተመሳሳይም ኢየሱስ አምላክንና ሕዝቡን ለማገልገል ሲል ወደ ምድር የመጣው በሰማይ የነበረውን ከሁሉ የበለጠ ውድ ሥልጣንና ብልጽግና ጥሎ ነው።—2 ቆሮንቶስ 8:9
ሙሴና ኢየሱስ ሁለቱም የአምላክ ቅቡዓን ሆነዋል። ነቢዩ ሙሴ ለእሥራኤል ሕዝብ የይሖዋ ቅቡዕ በመሆን አገልግሏል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደተናገረው ሙሴ “ከግብጽ ብዙ ገንዘብ ይልቅ እንደ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለጠግነት እንዲሆን አስቦአል።” (ዕብራውያን 11:26፤ ዘጸአት 3:1–4:17) ኢየሱስ ቅቡዕ ወይም ክርስቶስ የሆነው መቼ ነበር? ይህ የሆነው በተጠመቀና በአምላክ ቅዱስ መንፈስ ወይም ፈጣን ኃይል በተቀባ ጊዜ ነበር። ኢየሱስ በሲካር በያዕቆብ ጉድጓድ አጠገብ ሳለ ለሳምራዊቱ ሴትና ተከሶ በእስራኤል ሊቀ ካህናት ፊት በቀረበ ጊዜ እሱ መሲሕ ወይም ክርስቶስ መሆኑን መስክሯል።—ማርቆስ 14:61, 62፤ ዮሐንስ 4:25, 26
ሙሴና ኢየሱስ ሁለቱም ለ40 ቀናት ጾመዋል። ሙሴ የአምላክ ቃል አቀባይ የመሆን ሥራውን ሲጀምር በሲና ተራራ ላይ ለ40 ቀኖች ጾሟል። (ዘጸአት 34:28) ኢየሱስም በምድረበዳ ተስፋ የተገባው መሲሕ የመሆን ሥራውን ሲጀምር ሰይጣናዊ ፈተናዎችን የተቋቋመው ለ40 ቀናት ከጾመ በኋላ ነበር።—ማቴዎስ 4:1-11
ሁለቱም ሰዎች ይሖዋን አክብረዋል
ይሖዋ ሙሴንም ሆነ ኢየሱስን ቅዱስ ስሙን ከፍ ከፍ ለማድረግ ተጠቅሞባቸዋል። አምላክ ሙሴን “በአባቶቻቸው አምላክ በይሖዋ ስም” ወደ እሥራኤላውያን እንዲሄድ ነገረው። (ዘፀአት 3:13-16) ሙሴ የአምላክ ኃይል ይገለጥበት ዘንድና ስሙ በምድር ሁሉ ላይ ይነገር ዘንድ እንዲኖር በተፈቀደለት በፈርዖን ፊት የአምላክ እንደራሴ ሆኗል። (ዘፀአት 9:16) ኢየሱስም በተመሳሳይ የመጣው በይሖዋ ስም ነው። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ “እኔ በአባቴ ስም መጥቻለሁ፤ አልተቀበላችሁኝምም” ብሏል። (ዮሐንስ 5:43) ኢየሱስ አባቱን አክብሮአል፤ አምላክ ለሰጠው ሰዎችም የይሖዋን ስም ገልጦላቸዋል፤ ስሙ በምድር ላይ በደንብ እንዲታወቅ አድርጓል።—ዮሐንስ 17:4, 6, 26
ሙሴና ኢየሱስ ሁለቱም በመለኰታዊ ኃይል አምላክን ያስከበሩ ተአምራቶች አድርገዋል። ሙሴ በይሖዋ አምላክ የተላከ መሆኑን ለማረጋገጥ ተአምራቶች አድርጓል። (ዘፀአት 4:1-31) ቀይ ባሕርን እንዲከፍል አምላክ የተጠቀመበት ሙሴ ዘመን ይሖዋን ያስከበሩ ተአምራትን ፈጽሟል። (ዘጸአት 5:1 እስከ 12:36፤ 14:21-31፤ 16:11-18፤ 17:5-7፤ መዝሙር 78:12-54) ኢየሱስም በተመሳሳይ ብዙ ተአምራትን በመፈጸም ለአምላክ ክብር አምጥቷል። እሱ የፈጸማቸው ተአምራት ስለ አምላክ የሚመሰክሩ ወይም የአምላክን ክብር የሚገልጹ ከመሆናቸው የተነሣ “እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑኝ። ባይሆንስ ስለ ራሱ ስለ ሥራው እመኑኝ” ሊል ችሏል። (ዮሐንስ 14:11) ከፈጸማቸው ተአምራት መሃል የገሊላ ባሕር ጸጥ ይል ዘንድ የባሕሩን ማዕበል ጸጥ ማሰኘቱ ይገኝበታል።—ማርቆስ 4:35-41፤ ሉቃስ 7:18-23
የሚመሳሰሉባቸው ሌሎች አስፈላጊ ሁኔታዎች
ሙሴና ኢየሱስ ሁለቱም ከተአምራዊ የምግብ ዝግጅቶች ጋር በተዛመደ ሁኔታ ተገልጸዋል። ለእሥራኤላውያን ምግብ በተአምራዊ መንገድ ይሰጥ በነበረበት ጊዜ ሙሴ የይሖዋ ነቢይ ነበር። (ዘፀአት 16:11-36) በተመሳሳይም ኢየሱስ በሁለት ወቅቶች ብዙ ሕዝብን በተአምራዊ መንገድ ሥጋዊ ምግብ እንደመገበ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሠፍሯል።—ማቴዎስ 14:14-21፤ 15:32-38
የሰማይ መና ከሙሴና ከኢየሱስ ከሁለቱም አገልግሎት ጋር ግንኙነት አለው። እስራኤላውያን ቃል በቃል መና ከሰማይ በሚቀርብላቸው ጊዜ ይመራቸው የነበረው ሙሴ ነበር። (ዘጸአት 16:11-27፤ ዘኁልቁ 11:4-9፤ መዝሙር 78:25) ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ሆኖ ግን በጣም አስፈላጊ በሆነ መንገድ ኢየሱስ የራሱን ሥጋ እንደ ሰማይ መና አድርጎ ለታዛዥ የሰው ልጆች ሕይወት ሰጥቷል።—ዮሐንስ 6:48-51
ሙሴና ኢየሱስ ሁለቱም ሕዝቦችን ከባርነት ወደ ነፃነት መርተዋል። ሙሴ እሥራኤላውያንን ከግብጻውያን ባርነት የአምላክ ሕዝብ ወደመሆን ነፃነት እንዲመራ አምላክ ተጠቅሞበታል። (ዘፀአት 12:37-42) በተመሳሳይም ኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮቹን ወደ ነፃነት መርቷቸዋል። ክርስቶስ ገና ወደፊትም ታዛዥ የሰው ዘሮችን ከሰይጣን ዲያብሎስ ድርጅትና ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ወደ ነፃነት ይመራቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 15:24-26፤ ቆላስይስ 1:13፤ 1 ዮሐንስ 5:19
ሙሴና ኢየሱስ ሁለቱም የቃል ኪዳን መካከለኞች ሆነዋል። ሙሴ በይሖዋና በእሥራኤላውያን መካከል የሕጉ ቃል ኪዳን መካከለኛ ነበር። (ዘፀአት 19:3-9) ኢየሱስ በአምላክና በመንፈሳዊ እሥራኤላውያን መካከል ላለው አዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው።—ኤርምያስ 31:31-34፤ ሉቃስ 22:20፤ ዕብራውያን 8:6-13
የመፍረድ ሥልጣን ለሙሴና ለኢየሱስ ክርስቶስ ለሁለቱም ተሰጥቷል። ሙሴ ለሥጋዊ እሥራኤላውያን እንደ ፈራጅና ሕግ ሰጪ በመሆን አገልግሏል። (ዘጸአት 18:13፤ ሚልክያስ 4:4) ኢየሱስም ዳኛ በመሆን ያገለግላል። ለመንፈሳዊ “የአምላክ እሥራኤልም” ሕጎቹንና ትዕዛዛቱን ሰጥቷቸዋል። (ገላትያ 6:16፤ ዮሐንስ 15:10) ክርስቶስ ራሱ “ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩት ወልድን ያከብሩት ዘንድ ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ አብ በአንድ ሰው እንኳ አይፈርድም። ወልድን የማያከብር የላከውን አብን አያከብርም” ብሏል።—ዮሐንስ 5:22, 23
ሙሴና ኢየሱስ ሁለቱም በአምላክ ቤት ላይ የራስነት ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል። ሙሴ በጥንቷ እሥራኤል በአምላክ ቤት ላይ ራስ በመሆን በታማኝነት አገልግሏል። (ዘኁልቁ 12:7) ከዚህ ጋር በሚመሳሰል መንገድ በይሖዋ ልጆች መንፈሳዊ ቤት ላይ ራስ ተደርጓል። በዚህ ራስነቱም ታማኝ ሆኗል። በእርግጥ “ሙሴ ደግሞ በቤቱ ሁሉ የታመነ እንደሆነ እርሱ (ኢየሱስ) ለሾመው የታመነ ነበር። ቤትን የሚያዘጋጀው ከቤቱ ይልቅ የሚበልጥ ክብር እንዳለው መጠን እንዲሁ እርሱ ከሙሴ ይልቅ የሚበልጥ ክብር የተገባው ሆኖ ተቆጥሯልና።. . . ሙሴ በኋላ ስለሚነገረው ነገር ምሥክር ሊሆን በቤቱ ሁሉ ላይ እንደ ሎሌ የታመነ ነበር። ክርስቶስ ግን እንደ ልጅ በቤቱ ሁሉ ላይ የታመነ ነው። እኛም የምንደፍርበትን የምንመካበትንም ተስፋ እስከ መጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ ቤቱ ነን።”—ዕብራውያን 3:2-6
በአሟሟታቸውም እንኳ ሙሴና ኢየሱስ ተመሳሳዮች ነበሩ። እንዴት? ይሖዋ የሙሴን ሥጋ አስወግዶታል። በዚህም ሰዎች እንዳያረክሱት ወይም ጣኦት አድርገው እንዳያመልኩት አግዷቸዋል። (ዘዳግም 34:5, 6፤ ይሁዳ 9) በተመሳሳይም አምላክ የኢየሱስን ሥጋ በማስወገድ መበስበስን እንዳያይና ለእምነት እንቅፋት እንዳይሆን አድርጎታል።—መዝሙር 16:10፤ ሥራ 2:29-31፤ 1 ቆሮንቶስ 15:50
ትንቢቶችን ልብ በሉ
ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ሙሴ ያለ ነቢይ መሆኑ ከተረጋገጠባቸው መንገዶች መሃል እነዚህ ከላይ የተወያየንባቸው ሁኔታዎች ይገኙባቸዋል። አምላክ ለሙሴ እንዳንተ ያለ ነቢይ አስነሳላቸዋለሁ ያለው ቃሉ አስደናቂ በሆነ መንገድ ፍጻሜውን አግኝቷል።
ይሖዋ እንደ ሙሴ ያለ ነቢይ እንደሚያስነሣ የሰጠውን ትንቢታዊ ተስፋውን እንደፈጸመው ምንም አያጠያይቅም። የዘዳግም 18:18 ቃላት በኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወትና ባጋጠሙት ሁኔታዎች ላይ ተፈጽመዋል። እንዲህ ዓይነቶቹ የትንቢት ፍጻሜዎች በሌሎችም የአምላክ ቃል ትንቢታዊ ገጽታዎች ላይ እምነት እንዲኖረን ምክንያት ይሰጡናል። ስለዚህ ሁልጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢት ልብ እንበለው።