የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w91 12/1 ገጽ 6-8
  • ማንኛውም ሃይማኖት ጥሩ ነውን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ማንኛውም ሃይማኖት ጥሩ ነውን?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • አስፈላጊ የሆነ ልዩነት
  • የመምረጥ አስፈላጊነት
  • እውነተኛውን ሃይማኖት እንዴት መምረጥ ይቻላል?
  • እውነትና ፍሬ
  • በአሁኑ ጊዜ እውነተኛው ሃይማኖት ያላቸው ሰዎች አሉ
  • የሐሰት ሃይማኖቶች የአምላክን ስም ያሰደቡት እንዴት ነው?
    ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ
  • የሐሰት ሃይማኖት የሚጠፋበት ጊዜ ቀርቧል!
    የሐሰት ሃይማኖት የሚጠፋበት ጊዜ ቀርቧል!
  • የሃይማኖት ምርጫህ ልዩነት ያመጣል
    በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ
  • ከሐሰት ሃይማኖት መላቀቅ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
w91 12/1 ገጽ 6-8

ማንኛውም ሃይማኖት ጥሩ ነውን?

“የዘመናችን ዕጣ አሳዛኝ ነው። ሃይማኖት ያስፈልገናል። ነገር ግን ካሉት ሃይማኖቶች ጋር የሚስማማ አምላክ አላገኘንም።”​—ሉሲያን ቡላጎ፣ ሩማኒያዊው ገጣሚና ፈላስፋ።

“ሃይማኖትና ቀሳውስት ለብዙ ዘመናት ዋነኞቹ የዕድገትና የነፃነት ጠላቶች ሆነው ቆይተዋል። ወደፊትም በዚሁ ጠላትነታቸው የሚቆዩ ይመስላል።”​—ክሪስት ቦሌቭ፣ የቡልጋሪያ ገጣሚ

በስተቀኝ የሰፈሩት ጥቅሶች ብዙ ቅን ሰዎች የሚገኙበትን ግራ የተጋባ ሁኔታ የሚያስተጋቡ ናቸው። እነዚህ ሰዎች በውስጣቸው የሃይማኖት አስፈላጊነት በጥልቅ ይሰማቸዋል። ነገር ግን ቀሳውስቱ የሚያስተምሯቸው ምስጢራዊ አምላክ ሊገነዘቡት፣ ሊረዱትና ሊወዱት የሚችሉት ዓይነት አምላክ አይደለም። ከዚህም በላይ ቀሳውስቱና ሃይማኖቶቻቸው የሰውን ዕድገትና ነፃነት ለመግታት ብዙ የጣሩ መሆናቸውን ይገነዘባሉ። አዎን ቅን የሆኑ ሰዎች የሃይማኖት አስፈላጊነት ይበልጥ እየተሰማቸው ቢሄድም ማንኛውንም ሃይማኖት በመያዝ ረክተው አይኖሩም።

አስፈላጊ የሆነ ልዩነት

ሃይማኖት በሰው ልጅ አደረጃጀትና ታሪክ ላይ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒድያ ብሪታኒካ ስለ ሃይማኖት “በሰው ገጠመኝ፣ ባሕልና ታሪክ ያለ ሐቅ” እንደሆነ ይናገርና “ሃይማኖታዊ ዝንባሌዎችና እምነቶች የመኖራቸው ማስረጃ በማንኛውም የሕብረተሰብ ክፍል ይገኛል” በማለት ይጨምራል። ነገር ግን ከዓለም ታላላቅ ሃይማኖቶች አንዱም ቢሆን ለሰው ልጅ በረከት እንዳልሆነ ታሪክ ይገልጻል።

አንድ ጊዜ የሕንድ መሪ የነበሩት ጃዋሃርላል ኔህሩ እንዲህ በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተው ነበር፦ “ሃይማኖት የሚባለው ነገር፣ ሌላው ቢቀር የተደራጀው ሃይማኖት በሕንድና በሌላም አገሮች የሚዘገንኑ ነገሮችን አምጥቶብናል።” በሃይማኖት ስም የተካሄዱትን ጦርነቶችና የተፈጸሙትን ወንጀሎች በቅንነት ከተመለከትክ ከዚህ የፖለቲካ ሰው ጋር አትስማማምን?

በ18ኛው መቶ ዘመን ፈረንሳዊው ፈላስፋ ቮልቴር ይህን አስደናቂ ልዩነት ገልጿል፦ “ሃይማኖት ቁጥር ስፍር የሌላቸው ስመጥፉ ድርጊቶችን አፍርቷል ትላላችሁ። ሃይማኖት ከማለት ይልቅ አጉል እምነት ማለትም በአሳዛኟ ምድራችን ላይ እየገዛ ያለው አጉል እምነት ማለት ይኖርባችኋል። አጉል እምነት ለልዑሉ አምላክ ማቅረብ የሚገባን የእውነተኛና የንጹሕ አምልኮ ጨካኝ ጠላት ነው።” ቮልቴር በዘመኑ የነበረውን አለመቻቻል ተዋግቷል። ቢሆንም በአጽናፈ ዓለሙ ፈጣሪ አምላክ ያለውን እምነቱን ጠብቆ ኖሯል። በእውነተኛና በሐሰተኛ ሃይማኖት መካከል ያለውን ልዩነት ተገንዝቦ ነበር።

የመምረጥ አስፈላጊነት

ሁሉም ሰዎች ከቮልቴር ጋር የሚስማሙ አይደሉም። አንዳንዶች በሁሉም ሃይማኖቶች የየራሳቸው ጥሩነት አላቸው ይላሉ። ስለዚህ እውነተኛውን ሃይማኖት የመፈለግ አስፈላጊነት አይሰማቸውም። እንዲህ ዓይነቶቹ ግለሰቦች እንደሚከተለው ብሎ በጻፈው በነቢዩ ኢሳይያስ የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ ልብ ሊሉ ይገባል፦ “ክፉውን መልካም መልካሙን ክፉ ለሚሉ ጨለማውን ብርሃን ብርሃኑን ጨለማ ለሚያደርጉ ጣፋጩን መራራ መራራውንም ጣፋጭ ለሚያደርጉ ወዮላቸው!” (ኢሳይያስ 5:20) የሃሰት ሃይማኖት ለሰው ልጅ ያፈራለት መጥፎ ፍሬ ብቻ ነው። መንፈሳዊ ጨለማን ከማስከተሉም በላይ ቅን ልብ ባላቸው ሰዎች አፍ ውስጥ መራራ ጣዕም ትቷል።

ስለዚህ ምርጫው አምላክ የለሽ በመሆንና ማንኛውንም ሃይማኖት በማመን መሃል አይደለም። ጉዳዩ እንዲህ ቀላል አይደለም። አንድ ሰው የአምላክን አስፈላጊነት ከተገነዘበ በኋላ እውነተኛውን ሃይማኖት መፈለግ አለበት። ተመራማሪ ኤሚሊ ፖላት ትልቁ የሃይማኖት አትላስ በሚል መጽሐፍ ውስጥ ግሩም በሆነ መንገድ እንደገለጻቸው ነው፦ “[ሃይማኖቶች] የሚያስተምሩትና ከአማኞቻቸው የሚጠይቁት ግዳጅ በጣም የተለያየ ከመሆኑ የተነሣ በሁሉም ማመን ፈጽሞ የማይቻል ነገር ነው” ከዚህ ጋር በመስማማት የፈረንሳይ ኢንሳይክሎፒዲያ ዩኒቨርሳሊስ እንዲህ ይላል፦ “21 ኛው መቶ ዓመት ወደ ሃይማኖት የሚመለስ ከሆነ . . . ለሰው ልጅ የሚቀርቡት ቅዱስ የተባሉ ነገሮች እውነት ወይም ሐሰት መሆናቸውን መወሰን ይኖርበታል።”

እውነተኛውን ሃይማኖት እንዴት መምረጥ ይቻላል?

እውነተኛውን ሃይማኖት በምንመርጥበት ጊዜ የሚመራን ነገር ምንድን ነው? ኢንሳይክሎፒዲያ ዩኒቨርሳሊስ የእውነትን አስፈላጊነት አበክሮ መግለጹ ትክክል ነው። ሐሰትን የሚያስተምር ሃይማኖት እውነተኛ ሊሆን አይችልም። በምድር ላይ ከኖሩት ነቢያት ሁሉ የበለጠው ነቢይ “እግዚአብሔር መንፈስ ነው የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል” ብሎአል።​—ዮሐንስ 4:24

ይህ ነቢይ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እሱም እንዲህ ብሏል፦ “የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውስጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኩላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ። ከፍሬአቸው ታውቋቸዋላችሁ. . . . መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያደርጋል። የተበላሸ ዛፍ ክፉ ፍሬ ያደርጋል።” (ማቴዎስ 7:15-17 እንደ ፊሊፕስ ትርጉም) ብዙ ቅን ሰዎች የዓለም “ታላላቅ” ሃይማኖቶች፣ በተለያዩ ጊዜያት የተነሡት ኑፋቄዎችና ሃይማኖታዊ ክፍሎች እንኳ ሳይቀሩ ያፈሩትን መጥፎ ፍሬ በማየት ሁሉንም ምንም ዓይነት ጥሩነት የሌላቸው “የተበላሹ ዛፎች” እንደሆኑ አድርገው ይመለከቷቸዋል። ነገር ግን እውነተኛውን ሃይማኖት ሊያገኙ የሚችሉት እንዴት ነው?

በግልጽ እንደሚታየው ምርጫ ከማድረግ በፊት በሕዝበ ክርስትና ውስጥም ሆነ ከሕዝበ ክርስትና ውጭ ያሉትን በሺህ የሚቆጠሩ ሃይማኖቶች በሙሉ ማጥናት የማይቻል ነገር ነው። ይሁን እንጂ ኢየሱስ እንዳለው እውነትንና ፍሬን እንደ መመዘኛ መስፈርት ተጠቅመን እውነተኛውን ሃይማኖት መለየት እንችላለን።

እውነትና ፍሬ

ኢየሱስ እውነትን ጠቅሷል። በዚህ ረገድ ዛሬ ወደአብዛኞቹ ሃይማኖቶች ሰርገው የገቡትን ከጥንት አፈታሪኮችን ከግሪክ ፍልስፍና የተወሰዱ ሃይማኖታዊ ውሸቶችን የማይቀበል የአማኞች ቡድን የቱ ነው? ከእንዲህ ዓይነቶቹ ሐሰቶች አንዱ ነፍስ በባሕሪዋ የማትሞት ናት የሚለው ትምህርት ነው።a ይህም ትምህርት አምላክን የሚያዋርደውን የሲኦል እሳት ትምህርት አስከትሏል።

ኢየሱስ ፍሬንም ጠቅሷል። በዚህ ረገድ የዘር፣ የቋንቋና ብሔረሰባዊ ልዩነቶች በፍቅርና እርስ በርስ በመግባባት የተወገዱበትን እውነተኛ ዓለም አቀፍ አንድነት ያፈራ ሃይማኖት ታውቃለህን? በብሔራዊ ስሜትም ይሁን በሃይማኖት ስም ፖለቲከኞችም ሆኑ የሃይማኖት መሪዎች ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን እንዲጠሉና እንዲገድሏቸው ሲያነሣሡአቸው እሺ ብሎ ከመቀበል ይልቅ መሰደድን የሚመርጡ አባሎች ያሉት ዓለም አቀፍ ሃይማኖታዊ ማህበረሰብ ታውቃለህን? እንዲህ ዓይነት ሃይማኖታዊ ውሸቶችን የማይቀበልና እንዲህ ዓይነት ፍሬዎች የሚያፈራ ሃይማኖት እውነተኛ ለመሆኑ ኃይለኛ ማስረጃ ያለው አይመስልህምን?

በአሁኑ ጊዜ እውነተኛው ሃይማኖት ያላቸው ሰዎች አሉ

ታዲያ እንዲህ ዓይነት ሃይማኖት ይገኛልን? አዎ አለ። ነገር ግን ይህ ሃይማኖት ከዓለም ታላላቅ ሃይማኖቶች አንዱ እንዳልሆነ አምነህ መቀበል አለብህ። ከዓለም ታላላቅ ሃይማኖቶች አንዱ ያለመሆኑ ሊያስደንቀን ይገባልን? አይገባም። ኢየሱስ በዝነኛው የተራራ ስብከቱ ላይ፦ “በጠበበው ደጅ ግቡ። ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሠፊ መንገዱም ትልቅ ነውና ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው። ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ መንገዱም የቀጠነ ነውና የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው” ብሏል።​—ማቴዎስ 7:13, 14

ታዲያ እውነተኛ ሃይማኖት የሚገኘው የት ነው? በፍጹም ትሕትናና ሐቀኛነት በዚህ ‘ጠባብ ደጅ’ የሚሄደው የይሖዋ ምሥክሮች ያቋቋሙት ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ነው ብለን ለመናገር እንገደዳለን። እውነት ነው ዋነኞቹ ሃይማኖቶች የይሖዋ ምሥክሮችን በንቀት ኑፋቄ ብለው ይጠሩአቸዋል። ነገር ግን ይህን አጠራር በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ከሀዲ የሃይማኖት መሪዎች የቀድሞ ክርስቲያኖችን ይጠሩበት የነበረ ስም ነው።​—ሥራ 24:1-14

የይሖዋ ምሥክሮች እውነተኛው ሃይማኖት እንድላቸው እርግጠኞች የሆኑት ለምንድን ነው? ከ200 በላይ በሆኑ አገሮች ዓለም አቀፍ ወንድማማችነት መሥርተዋል። ይህም ወንድማማችነት በብሔር፣ በዘር፣ በቋንቋና በማህበራዊ ደረጃ መከፋፈልን እያስወገደ ነው። እንደዚሁም የቱንም ያህል ጥንታዊ ይሁን መጽሐፍ ቅዱስ ከሚናገረው ጋር በግልጽ የሚጋጩ መሠረተ ትምህርቶችን አያምኑም። ነገር ግን ወደዚህ የሚያስቀና ሁኔታ የመጡት እንዴት ነው? የእውነተኛ ሃይማኖት ተግባርስ ምን ምን ነገሮችን ያጠቃልላል? ይህና ሌሎችም ጥያቄዎች በሚቀጥሉት ሁለት አንቀጾች ላይ ውይይት ይደረግባቸዋል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ስለዚህ እምነት አፈ ታሪካዊ አመጣጥ የሚያስረዳ በማስረጃ የተደገፈ ማብራሪያ ለማግኘት ሰው አምላክን ለማግኘት ያደረገው ፍለጋ የተሰኘውን በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትናንሽ ጽሑፎች ማህበር የታተመ መጽሐፍ ተመልከቱ።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመስቀል ጦርነቶች ከሐሰት ሃይማኖት የተበላሸ ፍሬ የሚመደቡ ነበሩ

[ምንጭ]

Bibliothèque Nationale, Paris

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እውነተኛ ሃይማኖት መልካም ፍሬ ያፈራል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ