በመንግሥቱ ተስፋ ደስ ይበላችሁ!
“በተስፋ ደስ ይበላችሁ። በመከራ ታገሡ።”—ሮሜ 12:12
1. ከይሖዋ ጋር በመወዳጀት ደስታ ልናገኝ የምንችለው ለምንድን ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖችን ምን እንዲያደርጉ አበረታትቷቸዋል?
“ደስተኛው አምላክ።” (1 ጢሞቴዎስ 1:11 (አዓት)) ይህ ሐረግ ይሖዋን ግሩም በሆነ መንገድ ይገልጸዋል! ለምን ቢባል ሥራዎቹ በሙሉ ታላቅ ደስታ ስለሚያመጡለት ነው። ይሖዋ የጥሩና አስደሳች የሆኑ ነገሮች ሁሉ ምንጭ ስለሆነ አስተዋይ ፍጥረቶቹ በሙሉ ከሱ ጋር በመወዳጀት ደስታ ሊያገኙ ይችላሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖችን ይሖዋ አምላክን የማወቅ አስደሳች መብታቸውን እንዲያደንቁ፣ ለአስደናቂ የፍጥረት ስጦታዎቹ አመስጋኞች እንዲሆኑና በሚያሳያቸው ፍቅራዊ ቸርነት ሁልጊዜ እንዲደሰቱ አጥብቆ አሳስቧቸዋል። ጳውሎስ “ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ። ደግሜ እላለሁ ደስ ይበላችሁ” በማለት ጽፏል።—ፊልጵስዩስ 4:4፤ መዝሙር 104:31
2. ትልቅ ደስታ የሚያመጣው የትኛው ተስፋ ነው? ክርስቲያኖችስ ስለዚህ ተስፋ ምን እንዲያደርጉ ያበረታታቸዋል?
2 ክርስቲያኖች ይህን ጳውሎስ የሰጣቸውን ማሳሰቢያ ልብ ብለውታልን? በእርግጥ ልብ ብለውታል? የኢየሱስ ክርስቶስ መንፈሳዊ ወንድሞች አምላክ በከፈተላቸው ክብራማ ተስፋ እየተደሰቱ ነው። (ሮሜ 8:19-21፤ ፊልጵስዩስ 3:20, 21) አዎን፣ ከክርስቶስ ጋር በሰማያዊው መንግሥት አስተዳደር በማገልገል ለሕያዋንም ሆነ ለሙታን መጪውን የሰው ልጆች ታላቅ ተስፋ በመፈጸም ሥራ እንደሚካፈሉ ያውቃሉ። ነገሥታትና ካህናት ሆነው በሚያገለግሉበት ጊዜ ተባባሪ ወራሾች የመሆን መብት በማግኘታቸው ምን ያህል እንደሚደሰቱ ገምቱ! (ራእይ 20:6) ታማኝ የሰው ልጆችን ወደ ፍጽምና የማድረሱንና ምድራችንን ወደ ገነትነት የመመለሱን ሥራ በመምራት ሲረዱ እንዴት ዓይነት ደስታ ያገኛሉ! እውነትም ሁሉም የአምላክ አገልጋዮች “ሊዋሽ የማይችለው አምላክ ከዘላለም ዘመናት በፊት ተስፋ የሰጠው የዘላለም ሕይወት ተስፋ መሠረት” አላቸው። (ቲቶ 1:2) በዚህ ታላቅ ተስፋ ምክንያት ሐዋርያው ጳውሎስ ሁሉንም ክርስቲያኖች “በተስፋ ደስ ይበላችሁ” በማለት አበረታቷቸዋል።—ሮሜ 12:12a
እውነተኛ ደስታ ከልብ የሚመነጭ ባሕርይ ነው
3, 4. (ሀ) “መደሰት” የሚለው ቃል ትርጉሙ ምንድን ነው? ክርስቲያኖችስ መደሰት ያለባቸው ለምን ያህል ጊዜ ነው? (ለ) እውነተኛ ደስታ ምንድን ነው? በምንስ ላይ የተመካ ነው?
3 “መደሰት” ማለት የተድላ ስሜት መሰማት ወይም መግለጽ ማለት ነው። ደስታ ያለማቋረጥ መፈንጠዝ ወይም መፈንደቅ ማለት አይደለም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ደስታ”፣ “ሐሴት” እና “መደሰት” ከሚሉት ቃላት ጋር የሚመሳሰሉ የዕብራይስጥና የግሪክኛ ግሦች ውስጣዊውን ስሜትና ውጫዊ መግለጫውን ያመለክታል። ክርስቲያኖች “በመደሰት እንዲቀጥሉ”፣ “ሁልጊዜ ደስ እንዲላቸው” ተበረታትተዋል።—2 ቆሮንቶስ 13:11፤ 1 ተሰሎንቄ 5:16
4 ታዲያ አንድ ሰው ሁልጊዜ የሚደሰተው እንዴት ነው? ይህ የሚቻለው እውነተኛ ደስታ ከልብ የሚመነጭ፣ ጥልቅ፣ ከውስጥ የሚመነጭና መንፈሳዊ ባሕርይ ስለሆነ ነው። (ዘዳግም 28:47፤ ምሳሌ 15:13፤ 17:22) ጳውሎስ ከፍቅር ቀጥሎ የመዘገበው የአምላክ መንፈስ ፍሬ ደስታ ነው። (ገላትያ 5:22) ውስጣዊ ባሕርይ እንደመሆኑ መጠን በውጫዊ ነገሮች፣ በወንድሞቻችን ላይም እንኳ ሳይቀር የተመካ ነገር አይደለም። በአምላክ መንፈስ ቅዱስ ላይ የተመካ ነው። እውነትን እንደያዛችሁ፣ የመንግሥቱ ተስፋ እንዳላችሁና ይሖዋን የሚያስደስተውን እያደረጋችሁ እንዳላችሁ ከማወቅ የሚመጣ ጥልቅ የሆነ ውስጣዊ እርካታ ነው። ስለዚህ ደስታ አብሮን የሚወለድ የባሕሪያችን ክፍል አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስን ልዩ አድርገው ያሳወቁት ባሕርያት ስብስብ የሆነው የ“አዲሱ ሰውነት” ክፍል ነው።—ኤፌሶን 4:24፤ ቆላስይስ 3:10
5. ደስታ ከውጭ በሚታይ ሁኔታ የሚገለጠው መቼና እንዴት ነው?
5 ደስታ ከልብ የሚመነጭ ባሕርይ ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ ከውጭ ሊታይ ይችላል። እነዚህ ደስታ ከውጭ የሚገለጥባቸው መንገዶች ምንድን ናቸው? በፊት ላይ ከሚታይ የእርጋታ መልክ በእልልታ እስከ መዝለል ሊደርሱ ይችላሉ። (1 ነገሥት 1:40፤ ሉቃስ 1:44፤ ሥራ 3:8፤ 6:15) ታዲያ ይህ ማለት ብዙ የማይናገሩ ሰዎች ወይም ሁልጊዜ ፈገግታ የማይታይባቸው ሰዎች ደስታ የላቸውም ማለት ነው? አይደለም። እውነተኛ ደስታ የሚገለጸው በማያቋርጥ ልፍለፋ፣ በሳቅ፣ በፈገግታ ወይም በመንከትከት አይደለም። ደስታ የሚገለጽባቸውን መንገዶች የሚወስኑት የተለያዩ ሁኔታዎች ናቸው። በመንግሥት አዳራሽ ተወዳጆች የሚያደርገን ደስታ ብቻ ሳይሆን የወንድማማች መዋደድና ፍቅር ጭምር ነው።
6. ክርስቲያኖች የማያስደስቱ ሁኔታዎች ሲያጋጥሟቸውም እንኳን ሳይቀር ሁልጊዜ ሊደሰቱ የሚችሉት ለምንድን ነው?
6 ዘወትር ፀንቶ የሚኖርና በቀላሉ የማይጠፋ የሆነው ከልብ የሚመነጭ የክርስቲያን አዲስ ስብዕና ክፍል ነው። ሁል ጊዜ ለመደሰት የሚቻለውም በዚህ ምክንያት ነው። በእርግጥ አንዳንድ ጊዜ በአንድ ነገር እንረበሽ ይሆናል፤ ወይም የማያስደስቱ ሁኔታዎች ያጋጥሙን ይሆናል። ያም ሆኖ በልባችን ውስጥ ደስታ ሊኖረን ይችላል። አንዳንድ የቀድሞ ክርስቲያኖች በቀላሉ የማይደሰቱ ጌቶች የነበሩአቸው ባሮች ነበሩ። እንዲህ ዓይነቶቹ ክርስቲያኖች ሁልጊዜ ሊደሰቱ ይችሉ ነበርን? አዎን፣ በመንግሥቱ ተስፋቸውና በልባቸው ባለው ደስታ ምክንያት ሁልጊዜ ሊደሰቱ ይችሉ ነበር።—ዮሐንስ 15:11፤ 16:24፤ 17:13
7. (ሀ) በመከራ ጊዜ ስለመደሰት ኢየሱስ ምን አለ? (ለ) በመከራ ጊዜ እንድንጸና የሚረዳን ምንድን ነው? በዚህ ረገድስ በጣም ጥሩ ምሳሌ የተወልንን ማን ነው?
7 ሐዋርያው ጳውሎስ “በተስፋ ደስ ይበላችሁ” ካለ በኋላ ቀጠል አድርጎ “በመከራ ታገሡ” ብሏል። (ሮሜ 12:12) ኢየሱስም በማቴዎስ 5:11, 12 ላይ “ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ . . . ደስተኞች ናችሁ። ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና እልል በሉ፤ ተደሰቱ” በማለት ሲናገር በመከራ ጊዜ ስለሚኖር ደስታ ተናግሯል። እዚህ ላይ የተጠቀሰው መደሰትና እልል ማለት ቃል በቃል ከውጭ ለሚመለከቱ ሰዎች የሚታይ መሆን አይኖርበትም። በመሠረቱ በፈተና ጸንቶ በመቆም ይሖዋንና ኢየሱስ ክርስቶስን በማስደሰት የሚገኘው ጥልቅ የሆነ ውስጣዊ እርካታ ነው። (ሥራ 5:41) እንደ እውነቱ ከሆነ በመከራ እንድንጸና የሚረዳን ደስታ ነው። (1 ተሰሎንቄ 1:6) በዚህ ረገድ ኢየሱስ በጣም ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። ቅዱስ ጽሑፉ “በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታገሠ” በማለት ይነግረናል።—ዕብራውያን 12:2
ችግር ቢኖርም በተስፋ መደሰት
8. ክርስቲያኖች ምን ዓይነት ችግሮች ሊያጋጥሟቸው ይችላሉ? ይሁን እንጂ ችግሮች የአንድን ክርስቲያን ደስታ የማይወስዱበት ለምንድን ነው?
8 አንድ ሰው የይሖዋ አገልጋይ መሆኑ ከችግር ነፃ አያደርገውም። የቤተሰብ ችግር፣ የኢኮኖሚ ችግር፣ የጤና እክል ሊያጋጥመው ወይም የሚወደው ሰው ሊሞትበት ይችላል። እንዲህ ዓይነት ነገሮች ኀዘን ሊያስከትሉ የሚችሉ ሲሆን በመንግሥቱ ተስፋ ለመደሰት ያለንን ምክንያት፣ በልባችን ውስጥ ያለውን ጥልቅ ደስታ አይወስዱብንም።—1 ተሰሎንቄ 4:13
9. አብርሃም ምን ችግሮች አጋጥመውት ነበር? ሆኖም በልቡ ደስታ እንደነበረው የምናውቀው እንዴት ነው?
9 ለምሳሌ ያህል አብርሃምን እንውሰድ። ለሱ ሕይወት ሁልጊዜ ቀናና ደስ የሚያሰኝ አልሆነለትም ነበር። የቤተሰብ ችግሮች ነበሩበት። ቁባቱ አጋርና ሚስቱ ሣራ አልተስማሙም ነበር። እርስ በርሳቸው ይጨቃጨቁ ነበር። (ዘፍጥረት 16:4, 5) እስማኤል በይስሐቅ ላይ በማላገጥ አሳዶት ነበር። (ዘፍጥረት 21:8, 9፤ ገላትያ 4:29) በመጨረሻም የአብርሃም ተወዳጅ ሚስት ሣራ ሞተች። (ዘፍጥረት 23:2) እነዚህ ችግሮች ሁሉ ቢኖሩበትም የምድር ነገዶች ሁሉ ራሳቸውን በሚባርኩበት በመንግሥቱ ዘር ማለትም በአብርሃም ዘር ተስፋ ተደስቷል። (ዘፍጥረት 22:15-18) በልቡ ውስጥ ደስታ ስለነበረው የተወለደበትን የዑርን ከተማ ለቆ ከወጣ በኋላ ለመቶ ዓመት በይሖዋ አገልግሎት ጸንቷል። በዚህም ምክንያት “መሠረት ያላትን እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ ይጠብቅ ነበር” ተብሎ ተጽፎለታል። አብርሃም በመጪው መሲሐዊ መንግሥት እምነት ስለነበረው ጌታ ኢየሱስ ንጉሥ እንዲሆን በተቀባ ጊዜ “አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሐሴት አደረገ አየም ደስም አለው” ሊል ችሏል።—ዕብራውያን 11:10፤ ዮሐንስ 8:56
10, 11. (ሀ) እኛም ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ምን ትግል አለብን? ከዚህ ትግል የምንድነውስ እንዴት ነው? (ለ) ከኃጢአተኛው ሥጋችን ጋር ለመዋጋት ያለብንን የችሎታ ጉድለት የሚሸፍንልን ምንድን ነው?
10 እኛም ፍጹማን ያልሆን ሰዎች በመሆናችን የሚወጋንና የምንዋጋው ኃጢአተኛ ሥጋ አለን፣ ትክክል የሆነውን ለማድረግ የምናደርገው ይህ ትግል በጣም አስጨናቂ ሊሆንብን ይችላል። ከድካሞቻችን ጋር የምንዋጋ መሆናችን ግን ተስፋ የለንም ማለት አይደለም። ጳውሎስ በዚህ ትግል ምክንያት ጐስቋላ መሆኑ ተሰምቶታል። “ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል? በኢየሱስ ክርስቶስ በጌታችን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን” ብሏል። (ሮሜ 7:24, 25) በኢየሱስ ክርስቶስና እርሱ ባቀረበው ቤዛ አማካኝነት ድነናል።—ሮሜ 5:19-21
11 ውጊያውን ፍጹም በሆነ መንገድ ለመዋጋት ያለብንን የችሎታ ጉድለት የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ይሸፍንልናል። ቤዛው ንጹሕ ሕሊናና ከኃጢአታችንም ይቅርታ ስለሚያስገኝልን ልንደሰት እንችላለን። ጳውሎስ በዕብራውያን 9:14 ላይ “ከሞተ ሥራ ሕሊናን ስለሚያነጻው የክርስቶስ ደም” ይናገራል። በመሆኑም የክርስቲያኖች ሕሊና በኩነኔና በጥፋተኝነት ስሜት አይቸገርም። ይህም ካለን ተስፋ ጋር ተጨምሮ ለደስተኛነት ጠንካራ ምክንያት ይሆነናል። (መዝሙር 103:8-14፤ ሮሜ 8:1, 2, 32) ሁላችንም ተስፋችንን በማሰላሰል ትግሉን በተሳካ ሁኔታ ለመታገል እንበረታታለን።
ተስፋችንን በሐሳባችን አቅርበን ማየት
12. ቅቡዓን ክርስቲያኖች የትኛውን ተስፋ ሊያሰላስሉ ይችላሉ?
12 በመንፈስ ለተቀቡት ቀሪዎችም ሆነ ለሌሎች በጎች “የመዳንን ተስፋ” እንደ ተከላካይ ቁር በመድፋት ተስፋቸውን አቅርበው ማየታቸው አስፈላጊ ነው። (1 ተሰሎንቄ 5:8) ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሰማይ ያለመሞትን ባሕርይ የማግኘትን፣ ይሖዋ አምላክን ለማየት የመቻልንና ከተከበረው ከኢየሱስ ክርስቶስና ባለፉት መቶ ዓመታት በሙሉ ፍጹም አቋማቸውን ከጠበቁት የ144,000 ክፍሎች የሆኑ ሐዋርያትና ሌሎች ሰዎች አንድ ላይ የመሆንን አስደናቂ መብት ሊያሰላስሉ ይችላሉ። ከእነዚህ ጋር ለመገናኘት መቻል ሊገለጽ የማይችል ታላቅ ሀብት ነው!
13. አሁንም ቢሆን በምድር ላይ ያሉት ቅቡዓን ስለተስፋቸው ምን ይሰማቸዋል?
13 በምድር ላይ ያሉት ጥቂት ቅቡዓን ስለ መንግሥቱ ተስፋቸው እንዴት ይሰማቸዋል? የሚሰማቸው በ1913 የተጠመቀ አንድ ቅቡዕ በተናገራቸው ቃላት ሊጠቃለል ይችላል፦ “ተስፋችን እርግጠኛ ነገር ነው። 144,000 አባሎች ያሉት የትንሹ መንጋ ለሆነ ሁሉ ከምንገምተው በላይ በሆነ መጠን ሙሉ በሙሉ ይፈጸማል። በ1914 የነበርነው የቅቡዓን ክፍሎች ሁላችንም ወደ ሰማይ እንሄዳለን ብለን እንጠባበቅ በነበርንበት ጊዜ ለዚህ ተስፋ ዋጋማነት ያለንን ከፍተኛ ግምት አላጣንም ነበር። አሁንም ቢሆን ለዚህ ተስፋ ያለን ግምት ከፍተኛ ነው። ተስፋችንን እየጠበቅን የምንቆይበት ጊዜ በረዘመ መጠን ለተስፋው ያለን አድናቆት ጨምሮአል። ለሚልዮን ዓመታት የሚያስጠብቅ ቢሆንም እንኳ ሊጠባበቁት የሚገባ ተስፋ ነው። ተስፋችንን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ከፍ አድርጌ እመለከተዋለሁ፤ ለሱ ያለኝን አድናቆትም ማጣት አልፈልግም። የሌሎች በጎች ክፍል የሆኑት እጅግ ብዙ ሰዎች ያላቸው ተስፋም የታናሹ መንጋ ተስፋ ከግምታችን በላይ በሆነ መንገድ የሚፈጸም ለመሆኑ ዋስትና ይሰጠናል። ይህን ተስፋ እስከዚህች ሰዓት ድረስ አጥብቀን የያዝነው በዚህ ምክንያት ነው። አምላክ ‘የተከበረና እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋውን’ እንደፈጸመልን እስኪያረጋግጥ ድረስ እንጸናለን።”—2 ጴጥሮስ 1:4፤ ዘኁልቁ 23:19፤ ሮሜ 5:5
በአሁኑ ጊዜ በገነት ተስፋ መደሰት
14. እጅግ ብዙ ሰዎች ሊያስታውሱ የሚያስፈልጋቸው የትኛውን ተስፋ ነው?
14 እንዲህ ዓይነቱ የሚያስፈነድቅ እምነት መግለጫ የሌሎች በጎች ክፍል የሆኑት እጅግ ብዙ ሰዎች የሚደሰቱባቸውን ታላላቅ ምክንያቶች ይሰጣቸዋል። (ራእይ 7:15, 16) እነዚህ ሕዝቦች ከአርማጌዶን ለመዳን ተስፋ ሊያደርጉ ይችላሉ። አዎን የአምላክ መንግሥት ዲያብሎስ አምላካቸው የሆነላቸውን ክፉዎችን ከምድር ለማጽዳት ታላቁን መከራ አምጥታ የይሖዋ አምላክን ጽንፈ ዓለማዊ የበላይ ገዥነት ስታረጋግጥ ክብራማ ስሙን ስታስቀድስ ለማየት በጉጉት ይጠባበቃሉ። ከዚያ ታላቅ መከራ በሕይወት ተርፎ ማለፍ ምንኛ የሚያስደስት ነገር ይሆናል!—ዳንኤል 2:44፤ ራእይ 7:14
15. (ሀ) ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ምን የመፈወስ ሥራ ፈጽሞ ነበር? ለምንስ? (ለ) የአርማጌዶን ተራፊዎች የጤና ችግር ምን ይሆናል? እነሱስ ትንሣኤ ከሚያገኙት የሚለዩት ለምንድን ነው?
15 ራእይ 7:17ም እጅግ ብዙ ሰዎች “በጉ እረኛቸው ይሆናልና፣ ወደ ሕይወትም ውኃ ምንጭ ይመራቸዋልና እግዚአብሔርም እንባዎችን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል” ይላል። ይህ ትንቢት በአሁኑ ጊዜ መንፈሳዊ ፍጻሜ ያለው ቢሆንም ከአርማጌዶን የሚተርፉት ሰዎች ግን ቃል በቃል ሲፈጸም ያዩታል። እንዴት? ኢየሱስ በምድር በነበረበት ጊዜ ያደረገው ምንድን ነው? አካለ ጐደሎዎችን ፈውሷል። አንካሶችን እንዲሄዱ፣ የደንቆሮዎች ጆሮዎችና የዕውሮች ዓይኖች እንዲከፈቱ አድርጓል፤ ለምጽን፣ ሽባነትን፣ “በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ” ፈውሷል። (ማቴዎስ 9:35፤ 15:30, 31) ታዲያ ክርስቲያኖችስ የሚያስፈልጋቸው ይህ ዓይነቱ ፈውስ አይደለምን? እጅግ ብዙ ሰዎች ወደ አዲሲቱ ዓለም የሚገቡት የአሮጌውን ዓለም አካለ ስንኩልነትና ሕመም ሁሉ ይዘው ነው። ታዲያ በጉ ስለዚህ ጉዳይ ምን እንደሚያደርግ ተስፋ ልናደርግ እንችላለን? ለአርማጌዶን ተራፊዎች የሚያስፈልጋቸው በትንሣኤ የሚነሡት ሰዎች ከሚያስፈልጋቸው በጣም የተለየ ይሆናል። ትንሣኤ የሚያገኙት ሰዎች ሰብአዊ ፍጽምና ባይኖራቸውም ሙሉና ጤናማ የሆነ አካል ይዘው እንደገና ይፈጠራሉ። በትንሣኤ ተአምር ምክንያት ከመሞታቸው በፊት ከነበራቸው አካለ ስንኩልነት በተአምራዊ ፈውስ አማካኝነት መታደስ አያስፈልጋቸውም። በሌላ በኩል ደግሞ አብዛኞቹ የእጅግ ብዙ ሰዎች አባሎች ከአርማጌዶን በመትረፍ ባገኙት ተወዳዳሪ የሌለው ተሞክሮ ምክንያት ከአካለ ስንኩልነታቸው በተአምራዊ ፈውስ መታደስ ያስፈልጋቸዋል፤ ይታደሳሉም። በግልጽ እንደሚታየው ኢየሱስ በተአምር ይፈውስ የነበረበት ዋነኛ ዓላማ እጅግ ብዙ ሰዎች ከጥፋት ከመትረፋቸው በተጨማሪ ፈውስም እንደሚያገኙ ለማሳየት ነበር።
16. (ሀ) ለአርማጌዶን ተራፊዎች ተአምራዊ ፈውስ የሚደረገው መቼ ነው? ከምንስ ውጤት ጋር? (ለ) በሺው ዓመት ጊዜ በምን ተስፋ በመደሰት እንቀጥላለን?
16 እንዲህ ዓይነቱ ፈውስ ለአርማጌዶን ተራፊዎች የሚፈጸምላቸው ከአርማጌዶን ወዲያው ቀጠል ብሎ ትንሣኤ ከመጀመሩ በፊት እንደሚሆን ማሰብ ምክንያታዊ ነው። (ኢሳይያስ 33:24፤ 35:5, 6፤ ራእይ 21:4፤ ከማርቆስ 5:25-29 ጋር አወዳድር) በዚያን ጊዜ ሰዎች መነጽራቸውን፣ ከዘራቸውን፣ ምርኩዛቸውን፣ ተሽከርካሪ ወንበራቸውን፣ አርቲፊሻል ጥርሶቻቸውን፣ ለማዳመጥ የሚረዱ መሣሪያዎቻቸውንና የመሳሰሉትን ይወረውሯቸዋል። ለመደሰት የሚያስችል ከፍተኛ ምክንያት ነው! ለእነዚህ የአዲሲቱ ዓለም መሠረት ለሚሆኑ የአርማጌዶን ተራፊዎች በኢየሱስ የሚደረግላቸው እድሳት ምንኛ አስፈላጊ ነው! በአሮጌው ዓለም ውስጥ በተጠቁባቸው በሽታዎች ወደኋላ ሳይጐተቱ በፊታቸው በሚዘረጋው የሺህ ዓመት ውስጥ የሚከናወኑትን አስደናቂ እንቅስቃሴዎች በጉጉት በመጠባበቅ በደስታ መንፈስ ወደፊት መግፋት ይችሉ ዘንድ አካለ ስንኩል የሚያደርጉ በሽታዎች ከመንገዳቸው ላይ ይወገዳሉ። አዎን እጅግ ብዙ ሰዎች ከአርማጌዶን በኋላም እንኳ በሺህ ዓመቱ መጨረሻ ላይ የሚደርሱበትን ፍጹም የሆነ ሰብአዊ ሕይወት ተስፋ በማድረግ እየተደሰቱ ይኖራሉ። በሺው ዓመት ዘመን በሙሉ ወደዚያ ግብ የመድረስ ተስፋቸውን እያሰቡ ይደሰታሉ።
17. ገነትን የመመለሱ ሥራ ሲካሄድ ምን ደስታዎች ይኖራሉ?
17 ያንተም ተስፋ ይህ ከሆነ ገነትን ወደ ምድር በመመለሱ ሥራ መካፈል የሚያስገኘውን ደስታ አሰላስል። (ሉቃስ 23:42, 43) የአርማጌዶን ተራፊዎች ምድርን ለማጽዳትና ሙታን የሚነሡበትን አስደሳች ቦታ ለማዘጋጀት እንደሚረዱ አያጠራጥርም። የቀብር ስነ ሥርዓቶች በሞት የተለዩንን የምንወዳቸውን ሰዎች ጨምሮ ከሙታን ለሚነሡ ሰዎች አቀባበል በሚደረግላቸው ስብሰባዎች ይተካሉ። ባለፉት በመቶ የሚቆጠሩ ዓመታት ከኖሩና ከነበሩ ትንሣኤ ካገኙ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች ጋር መገናኘት የሚያስገኘውን ደስታ አስቡ። በተለይ ልታነጋግሩ የምትፈልጉት ማንን ወይም እነማንን ነው? አቤልን፣ ሄኖክን፣ ኖኅን፣ ኢዮብን፣ አብርሃምን፣ ሣራን፣ ይስሐቅን፣ ያዕቆብን፣ ዮሴፍን፣ ሙሴን፣ ኢያሱን፣ ረዓብን፣ ዲቦራን፣ ሳምሶንን፣ ዳዊትን፣ ኤልያስን፣ ኤልሳዕን፣ ኤርምያስን፣ ሕዝቅኤልን፣ ዳንኤልን፣ ወይም ዮሐንስ መጥምቁን ነውን? ይህ አስደሳች ተስፋም የተስፋህ ክፍል ነው። ከነሱ ጋር ለመነጋገር፣ እነሱ ለመማርና መላዋን ምድር ገነት ለማድረግ ከነሱ ጋር አብረህ መሥራት ትችላለህ።
18. ምን ተጨማሪ ደስታዎችንስ ልናሰላስል እንችላለን?
18 እንደዚሁም ምድር ይሖዋ በመጀመሪያ ሲፈጥራት እንደነበረችው ፍጹም የሆነ የአካባቢ ሚዛን ሲኖራት የሚገኘውን ለሰውነት ተስማሚ የሆነ ምግብ፣ ንጹሕ ውኃና ንጹሕ አየር ገምቱ። በዚያን ጊዜ ሕይወት ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ የማይደረግበት አይሆንም። ከዚህ ይልቅ አስደሳች ሥራዎች የሚሠሩበት ንቁና ትርጉም ያለው ተሳትፎ የሚደረግበት ጊዜ ይሆናል። ሕዝቦች ከወንጀል፣ ራስን ብቻ ከመውደድ፣ ከቅንዓትና ከጠብ ነፃ ስለሚሆኑበት፣ ሁሉም የመንፈስ ፍሬ ስለሚኮተኩቱበትና ስለሚያፈሩበት ወንድማማችነት የሰፈነበት ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ አሰላስል። እንዴት የሚያስፈነድቅ ነው!—ገላትያ 5:22, 23
ሕይወትን አስደሳች የሚያደርግ ተስፋ
19. (ሀ) በሮሜ 12:12 ላይ የተጠቀሰው ደስታ የሚገኘው መቼ ነው? (ለ) የኑሮ ሸክሞች ተስፋችንን እንዲገፈትሩብን ላለመፍቀድ መቁረጥ ያለብን ለምንድን ነው?
19 ተስፋ ከተፈጸመ በኋላ ተስፋ መሆኑ ይቀራል። ስለዚህ በሮሜ 12:12 ላይ ጳውሎስ የተናገረለት ደስታ የሚገኘው አሁን ነው። (ሮሜ 8:24) የአምላክ መንግሥት ስለምታመጣቸው በረከቶች ማሰቡ ራሱ በአሁኑ ጊዜ በዚህ ተስፋ ለመደሰት ምክንያት ይሆናል። ስለዚህ የተበላሸው ዓለም የኑሮ ሸክሞች ክብራማውን ተስፋህን ወደ ጐን እንዲገፈትሩት አትፍቀድ። ተስፋህን አሻግረህ ለማየት ባለመቻል አትሸነፍ፤ አትዛል። (ዕብራውያን 12:3) ክርስቲያናዊ አካሄድህን መተውህ ችግሮችህን አያቃልላቸውም። ዛሬ አንድ ሰው በኑሮ ሸክሞች ምክንያት አምላክን ማገልገሉን ከተወ ከችግሩ ካለመገላገሉም ሌላ ተስፋው ይጠፋበታል። ስለዚህ በመጪዎቹ አስደናቂ ተስፋዎች የመደሰትን አጋጣሚ ያጣል።
20. የመንግሥቱ ተስፋ ተስፋውን በሚቀበሉት ሰዎች ላይ ምን ውጤት አለው? ለምንስ?
20 የይሖዋ ሕዝቦች በኑሮአቸው ደስተኞች የሚሆኑበት ብዙ ምክንያት አላቸው። ብሩኅና የሚያነቃቃ ተስፋቸው ሕይወትን አስደሳች ያደርግላቸዋል። ይህን አስደሳች ተስፋ ለራሳቸው ብቻ ይዘው አያስቀሩም። ከሌሎችም ጋር ሊካፈሉት ዝግጁዎች ናቸው። (2 ቆሮንቶስ 3:12) ስለዚህ የመንግሥቱን ተስፋ የያዙ ሰዎች እርግጠኛ ተስፋ ያላቸው ሕዝቦች ናቸው። ሌሎችንም ከአምላክ የሆነውን የምሥራች በመንገር ለማበረታታት ይፈልጋሉ። ይህም ለሰው ዘሮች ከተሰጡት ተስፋዎች ሁሉ የላቀውና ገነትን ለምድር የሚመልሰው የመንግሥት ተስፋ መልእክቱን የተቀበሉት ሰዎች ሁሉ ሕይወታቸውን ግሩም በሆነ ተስፋ እንዲሞሉ ያስችላቸዋል። ሰዎች መልእክቱን ባይቀበሉትም እኛ ተስፋው ስላለን በመደሰት እንቀጥላለን። ዞሮ ዞሮ የሚጐዱት ጆሮአቸውን ለመልእክቱ የሚያደነቁሩት ናቸው እንጂ እኛ አይደለንም።—2 ቆሮንቶስ 4:3, 4
21. ምን ነገር ቀርቧል? ተስፋችንንስ መመልከት ያለብን እንዴት ነው?
21 የአምላክ ተስፋ “እነሆ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ” ይላል። (ራእይ 21:5) አዲሲቱ ዓለም ከአስደሳችና ፍጻሜ ከሌለው በረከቶቿ ሁሉ ጋር ቀርባለች። ተስፋችን በሰማይ መኖርም ይሁን በምድራዊ ገነት፣ የላቀና ክቡር ተስፋ ነው። አጥብቀን እንያዘው። ከምንጊዜውም የበለጠ አስጨናቂ በሆኑት በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ይህን “ተስፋ እርግጥና ጽኑ እንደሆነ የነፍስ መልህቅ” ተመልከቱት። የተስፋችን መልህቅ “የዘላለም አምባ” በሆነው በይሖዋ ላይ የተጣለ በመሆኑ አሁንም እንኳ በፊታችን ባለው ተስፋ ለመደሰት የሚያስችል ጠንካራና ደስ የሚያሰኝ ተስፋ አለን።—ዕብራውያን 6:19፤ ኢሳይያስ 26:4
[የግርጌ ማስታወሻ]
የክለሳ ጥያቄዎች
◻ የሰው ልጆች ታላቅ ተስፋ ምንድን ነው?
◻ እውነተኛ ደስታ ምንድን ነው?
◻ የአርማጌዶን ተራፊዎች ተአምራዊ ፈውስ የሚያገኙት መቼ ሳይሆን አይቀርም?
◻ የኑሮ ጭነቶች ተስፋችንን እንዲገፈትሩብን መፍቀድ የሌለብን ለምንድን ነው?
◻ በአዲሲቱ ዓለም ምን ዓይነት ደስታ እንጠብቃለን?
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ የፈጸማቸው ዓይነት ፈውሶች ሲፈጸሙ ብታይ ልብህን በደስታ አይሞላውምን?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በመንግሥቱ ተስፋ ደስ የሚላቸው ተስፋቸውን በማካፈል ሌሎችን ያበረታቱአቸዋል